በትምህርት 16 ውስጥ፥ ክርስቶስ በመስቀል ላይና በትንሣኤው የሰጠንን ደኅንነት እንዴት ሰዎች በየግላቸው ሊያገኙ እንደሚችሉ ተምረን ነበር። በዚህም ለደኅንነት መሠረታዊ የሆነ አንድ ዋና ነገር፥ በሦስት የተለያዩ መንገዶች መገለጣቸውን ተመልክተናል። እነዚህም ሦስቱ ንስሐ፥ እምነትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ ናቸው። ሰዎች ኃጢአታቸው ከእግዚአብሔር ለይቶአቸው እንደ ነበረ መገንዘብና ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ በራሳቸው ሥራና በሌላም ነገር መታመን እንደሌለባቸው አውቀው፥ በአኳያው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱና በትንሣኤ ብቻ ማመን አለባቸው። ስለዚህ በዚህ አኳኋን ሰዎች ከኃጢአታቸው በሚመለሱበትና ወደ ኢየሱስ ለደኅንነት በሚመጡበት ጊዜ፥ እግዚአብሔርም የደኅንነትን በረከቶች ይሰጣቸዋል። ይህንን አዳኝ የሆነ እውነተኛ እምነትን ያገኙ ሁሉ፥ ኢየሱስን የመከተልና የመታዘዝ የሕይወት ፈለግ ይኖራቸዋል። መልካም ሥራቸው የደኅንነታቸው ውጤትና ፍሬ ይሆናል።
ነገር ግን ሰዎች ደኅንነት እንዴት ሊገኝ እንደሚችል ብዙ ጥያቄዎችን ይሰነዝራሉ። በዚህ ሳምንት ትምህርታችን ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶችን ለመመለስ እንሞክራለን።
መጀመሪያ ቀን-
እምነትና ጥምቀት
ክርስቲያኖች በክርስቶስ ያላቸውን እምነት በሰዎች መካከል ለመግለጥ ቢሹ፥ ሊያደርጉት የሚገባ አንዱና ዋናው ነገር፥ ቅዱስ ጥምቀትን መቀበል ነው። ምክንያቱም በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ጥምቀትን እንዲቀበሉ ታዝዘዋል። በአዲስ ኪዳንም ውስጥ ቅዱስ ጥምቀት ከደኅንነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑን በመገንዘብ ደኅንነትን ለማግኘት መጠመቅ ነበረባቸው። በ16ኛው ትምህርት ውስጥ ለደኅንነት አስፈላጊ የሆነው አንዱ ዐቢይ ነገር በሦስት መንገዶች ተገልጧል። እነዚህም ሦስቱ መንገዶች፡- ንስሐ፥ እምነትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ ናቸው። እንግዲህ የጥምቀት ሚና ምንድን ነው? ጥምቀት ለደኅንነት ማግኛ በሁለተኛው ደረጃ ተፈላጊ ነገር መሆኑ ነው? ሰዎች እንደ መጀመሪያ የደኅንነት ክፍል አድርገው በማሰብ በክርስቶስ ይመኑና ከዚያ በኋላ እንደ ሁለተኛው የደኅንነት ክፍል ቅዱስ ጥምቀትን ይቀበሉ? በዛሬ ትምህርታችን ላይ ስለ ጥምቀት ስላሉዋችሁ ጥያቄዎች አንሥተን ሁሉንም በዝርዝር ልንወያይባቸው አንችልም። ሆኖም ቅዱስ ጥምቀት ደኅንነትን ለእኛ ለማስገኘት፥ ከንስሐና ከእምነት ጋር እንዴት ያለ ተዛምዶ እንዳለው፥ በሚነሡ ጥያቄዎች ላይ መልስ ለመስጠት እንጥራለን።
1. በአዲስ ኪዳን ውስጥ አማኞች በክርስቶስ እንዳመኑ ወዲያውኑ ያጠመቁ ነበር። ይህም ጥምቀት ውጫዊ ምልክትና የውስጣዊ እምነታቸው ማኅተም ነበር።
ጥያቄ፦ ማቴ. 28፡19-20 አንብብ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በምንሆንበት ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 2፡41 አንብብ። ጴጥሮስ በጴንጠቆስጤ ቀን በለማው የምስክርነት ቃል ያመኑ ሰዎች ቃሉን መቀበላቸውን ለማሳየት ምን አደረገ?
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 8፡36-38 አንብብ። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በክርስቶስ ያመነ መሆኑን ለማረጋገጥ ምን ለማድረግ ፈለገ?
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 10፡47-48 አንብብ። ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ መች ተጠመቁ?
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 16፡14-15 አንብብ። ሊድያ መች ተጠመቀች?
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 16፡31-33 አንብቡ። ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ወኅኒ ቤት ዘበኛ ደኅንነትን እንዲያገኝ ምን ማድረግ እንዳለበት ነገረው? ለ) የፊልጵስዩስ ወኅኒ ቤት ዘብ መች ተጠመቀ?
በጥንታዊትዋ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ፥ በኢየሱስ ያመኑ ሰዎች ሁሉ፥ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን ለማሳየት ወዲያውኑ ይጠመቁ ነበር። በማቴዎስ 28፡19-20 ላይ ኢየሱስ አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ወደ ዓለም ሁሉ ሄደው ብዙ ደቀ መዛሙርትን እንዲያፈሩ እዝዞአቸው ነበር። ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስን ለመከተል በሚወስኑበት ጊዜ የእርሱ ተከታዮች መሆናቸውን ለማስመስከር በመጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቅዱስ ጥምቀትን መቀበል ነው። በጰንጠቆስጤ ቀን ሐዋርያው ጴጥሮስ ስብከቱን ለኢየሩሳሌም አይሁዶች ካሰማ በኋላ፥ በሐዋርያት ሥራ 2፡41 ላይ እንደተጻፈው፥ የሐዋርያውን መልእክት የተቀበሉ ሁሉ ተጠመቁ ይላል። በመሆኑም ኢየሱስን እንደ መሢሐቸውና ከኃጢአት እንደሚያድን መድኅን ከተቀበሉ በኋላ ሁሉም በአንድ ቀን ተጠመቁ። በሐዋርያት ሥራ 8፡26-38 ውስጥ ፊልጶስ በትንቢተ ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ውስጥ ስለ ክርስቶስ የተጻፈውን ቃል ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጋር ተወያየ። ወደ ውኃ በቀረቡ ጊዜም፥ ጃንደረባው በራሱ ፍላጎት ለመጠመቅ ጠየቀ። ጥምቀትን በመቀበል፥ በኢየሱስ የማመንና እርሱንም አዳኙ አድርጎ መቀበሉን ሕይወት አለመሰከረ። እግዚአብሔር የልድያንና የቤተሰቦችዋን ልብ እንደ ከፈተ፥ የኢየሱስ ተከታይ መሆንዋን ለመግለጥ ተጠመቀች (የሐዋ. ሥራ 16፡14-15)። ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ቤት በሰበከ ጊዜና በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኙ (የሐዋ. ሥራ 10፡43) ባብራራበት ወቅት ያዳምጡ በነበሩ ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ፥ (የሐዋ. ሥራ 10፡44)። ጴጥሮስም እነዚህ ሰዎች በልባቸው ክርስቶስን አምነው እንደ አዳኛቸው መቀበላቸውን ይህ ድርጊት ሊያረጋግጥለት ቻለ። እርሱም እነዚህ ሰዎች ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ወዲያው እንዲጠመቁ አዘዘ።
ምናልባት አዲስ አማኞች በክርስቶስ እንዳመኑ ወዲያውኑ ይጠመቁ እንደ ነበረ ግልጽ ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀሰው የሐዋርያት ሥራ 16፡31-33 ውስጥ ያለው ክፍል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ ከተማ በነበሩ ጊዜ ከአንዲት አገልጋይ ክነበረች ልጃገረድ ውስጥ ርኩስ መንፈስን ስላስወጡ ታስረው ነበር። በሌሊትም እግዚአብሔር የምድር መንቀጥቀጥ እንዲሆን አደረገ፥ የታሰሩበት ሰንሰለትም ተፈታ፥ የእስር ቤቱ በርም ተከፈተ፡፡ የወኅኒ ቤቱ ዘብ በሩ መከፈቱን ባወቀ ጊዜ ራሱን ሊገድል ነበር። ይህን ያደረገበት ምክንያት እስረኞቹ ሁሉ ያመለጡ ስለ መሰለውና እርሱም በእነርሱ ገመድ እንደሚገባ ስለ ተሰማው ነው። ጳውሎስ ግን ድምፁን ከፍ አድርጎ እስረኞቹ ሁሉ በእስር ቤቱ ውስጥ መሆናቸውን ነገረው። የእስር ቤቱ ዘብ ይህን ጊዜ በደስታ ተውጦ ወደ ጳውሎስ በመምጣት፥ «ለመዳን ምን ማድረግ ይገባኛል?» ሲል ጠየቃቸው? ሐዋርያው ጳውሎስ ሰውዩው ለሚድንበት ሁኔታ ብዙ ነገር ለመዘርዘር አልፈለገም። አንድ ነገር ብቻ እንዲያደርጎ መከረው፥ ይህም፥ «በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እመን፡፡» በዚያን ምሽት የወኅኒ ቤት ዘበኛው ጳውሎስንንና ሲላስን ሊያስተናግድ ወደ ቤቱ ይዟቸው በሄደ ጊዜ ሐዋርያው ጳውሎስ እርሱንና ያመኑትን ቤተሰቦቹን አጠመቃቸው።
ይህ ታሪክ በሦስት ምክንያቶች ጠቃሚ ሆኖ ይገኛል። መጀመሪያ፥ ጳውሎስ ለደኅንነት ይበጃል ብሎ የተናገረው አንድ አስፈላጊ ነገር ነበር። እርሱም እምነት ነው። ሐዋርያው፥ የወኅኒው ጠባቂ ለመዳን መጠመቅ አለበት አላለም። ይህ እንግዲህ በትምህርት 16 ውስጥ የተማርነውን ያላስበናል። ይህም ለደኅንነት አስፈላጊ የሆኑት ንስሐና እምነት ናቸው የሚለው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፥ ምንም እንኳን በእምነታቸው ብቻ ድነው ቢሆኑም፥ ጳውሎስ የወኅኒ ቤቱን ዘበኛና ቤተሰቡን ወዲያው አጠመቃቸው። የአዲሱ እምነታቸው ውጪአዊ መግለፃ ጥምቀታቸው ነበር። ሦስተኛ፥ ዘበኛውና ቤተሰቡ ስለ አዲሱ እምነታቸው የሚያውቁት ጥቂት ቢሆንም ተጠመቁ። መሬት እስከ ተንቀጠቀጠበት ጊዜ ድረስ፥ የጥንታዊ ግሪክና የሮማ ጣዖታት ተከታዮች ነበሩ። ስለ ኢየሱስ የሚያውቁት ጥቂት ነበር። ስለ ብሉይ ኪዳን የአይሁድ እምነትም ግንዛቤአቸው አናሳ ነበር። የገባቸውና ያወቁት ኢየሱስ የደኅንነት መንገድ መሆኑን ስለነበረ፥ በእርሱ አመኑ። እምነታቸውንም ስለ ገለጡ ጳውሎስ ሊያጠምቃቸው ቻለ።
እነዚህ ቁጥሮች በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥምቀት የነበረውን ሚና እንድንረዳ ይረዱናል፥ ጥምቀት የውስጣዊው እምነት ውጫዊ መገለጫ (አዋጅ ነው፡፡ ሰዎች ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው ሲያምኑት፥ አሁን ክርስቶስን እንደሚያምኑና እንደሚከተሉ ለሰው ሁሉ ለማወጅ ይጠመቁ ነበር፡ ጥምቀት ወደ ደኅንነት የሚወስዳቸው መንገድ አልነበረም፡፡ ይልቁንም የደኅንነት መንገዶቻቸው ንስሐና እምነት ነበሩ፡፡ ነገር ግን ጥምቀት ሊሆን የተገባውና አፋጣኝ የሆነ የውስጣዊው እምነት ውጫዊ መገለጫ ነበር። ጥምቀት ውስጣዊውን እምነት ለሌሎች ለማሳየት የሚጠቅም ውጫዊ ሥርዓት ነበር። አንድ ሰው ባይጠመቅ እንዳላመነ ይቆጠር ነበር። አንድ ሰው ንስሐ ሲገባና ቢያምን ውስጣዊ እምነቱን ሊመሰክር እንደ ውጫዊ ምልክት አድርጎ በፍጥነት ይጠመቅ ነበር።
አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጥምቀትን፥ የውስጣዊ እምነት ምልክትና ማኅተም ነው ይላሉ። አንድ ሰው እምነት ያለው ለመሆኑ፥ ጥምቀት ለሌሎች ምልክቱ ነው። እንደዚሁም ጥምቀት ይህንኑ እምነት የሚያረጋግጥ ማኅተም ነው። ጥምቀት ለጥንት ቤተ ክርስቲያን ምን እንደ ነበረ አንድ ምሳሌ እነሆ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚደረጉ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች ውስጥ አንዱ የቀለበት ሥነ ሥርዓት ነው። ሙሽራውና ሙሽራዋ የቃል ኪዳናቸው ምልክትና ማኅተም አድርገው ቀለበት ይለዋወጣሉ። በሕይወት ዘመናቸውም ቀለበቶቻቸውን እንደ ጋብቻ ቃል ኪዳን ምልክትና ማኅተም አድርገው፥ አንዳቸው የሌላው መሆናቸውን ለማሳየት በጣቶቻቸው ላይ እንዳጠለቋቸው ይኖራሉ።
ሰዎች ያለ ቀለበት ሥነ ሥርዓት ሊጋቡ ይችላሉ? አዎን፥ ሊጋቡ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ የቀለበት ሥነ ሥርዓት፥ የጋብቻ ዋና የውጪአዊ ምልክትና እንዲሁም ሙሽሮቹ እርስ በርስ ለሚያደርጉት የቃል ኪዳን ማኅተም ነው። ሙሽሪትና ሙሽራው እርሱም የእርሷ እርሷም የእርሱ ለመሆናቸው የሚያሳዩበት ምልክት የቀለበት ማድረግ ሥነ ሥርዓት ስለሆነና ይህ ድርጊት ተለምዶ በመካሄድ ላይ በመሆኑ ሙሽራው ወይም ሙሽራይቱ አንዳቸው ቀለበት አናደርግም ቢሉ ምን ያህል አስከፊ ድርጊት እንደሚሆን ልትገምቱ ትችላላችሁ። እንደዚሁም፥ ሙሽራው ወይም ሙሽሪት አንዳቸው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ቀለበት አናደርግም ቢሉ ጋብቻቸው ከልብ ስለ መሆኑ የታደሙት ሰዎች ይጠራጠራሉ። በዚሁ አኳኋን በአዲስ ኪዳን ጊዜ የነበሩ አማኞች አንድ ሰው ካልተጠመቀ በስተቀር ራሱን ለክርስቶስ በእውነት አሳልፎ ሰጥቷል ብለው አይቀበሉም ነበር። ካለ ጥምቀት በስተቀር አንድ ሰው በክርስቶስ አምኖ የእርሱ ተከታይ መሆኑ ማረጋገጫ አልነበረም። ለአዲስ ኪዳን አማኞች ጥምቀት የእምነት ክፍል ነበር። የውጪአዊ ምልክትና የውስጣዊ እምነት ማኅተም ነበር። ከዚህ የተነሣ ነው፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ክፍለ ምንባቦች ጥምቀት ከእምነት ጋር በቅርብ የተሣሠረው። የአዲስ ኪዳን አማኞች ጥምቀት የደኅንነታቸው መንገድ እንደ ነበረ አድርገው አልተገነዘቡም። እንደ እነርሱ ግንዛቤ እምነት ብቻ የደኅንነታቸው መንገድ ነበር (ማለትም በ16ኛው ትምህርት ውስጥ እንደ ተመለከትነው)። ነገር ግን ሰዎች በውጪአዊው ሁኔታ እምነታቸውን በጥምቀት ሳያሳውቁና ሳያሳዩ፥ በልባቸው ውስጥ በክርስቶላ ሊያምኑ እንደሚችሉ ምንም ግንዛቤ አልነበራቸውም።
2. ጥምቀት – ለደኅንነት አስፈላጊ መሆኑን የሚያስተምሩ የሚመስሉ የጥቅስ ክፍሎች፥ ጥምቀት መከናወኑ ለውጪአዊ ምልክት ለውስጣዊው ደግሞ ማኅተም መሆኑን ያመለክታል።
ጥያቄ፡- ማር. 16፡15-16 አንብብ። ሀ) የሚድነው ማን ነው? ለ) የሚኮነንስ ማን ነው?
ጥያቄ፡- 1ኛ ጴጥ. 3፡21 አንብብ። ጥርስ ምን ያድናል አለ? ) ጴጥሮስ ይህ አይደለም ያለው ምንድን ነው? ሐ) ጴጥሮስ ይህ ነው ያለው ምን ነው?
ጥያቄ፡- የሐዋ. ሥራ 2፡28 አንብብ። ጴጥሮስ ኢየሱስን የሰቀሉ አይሁዶች የኃጢአት ይቅርታን ለማግኘት ምን ያደርጉ አለ?
ጥምቀት የደኅንነትን ማግኛ መንገድ እንደሆነ የሚመስሉ ብዙ ክፍሎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ። ሆኖም እነዚህን ክፍለ ምንባቦች በጥንቃቄ በዚህ እምነት ከተመለከትናቸው ትምህርቶች አኳያ በጥንቃቄ በምናጠናቸው ጊዜ፥ ሰዎች በመጠመቃቸው ብቻ ይድናሉ አለማለታቸውን እንገነዘባለን። በዚህ ፈንታ እነዚህ የጥቅስ ክፍሎች የሚያሳዩት የጥንት አማኞች ጥምቀትን ከንስሐና ከእምነት ጋር ያያይዙት እንደ ነበረ ነው። እነዚህ የጥቅስ ክፍሎች የሚያመለክቱት የጥንት አማኞች በውስጡ በልቡ በክርስቶስ ያመነ ሰው ወዲያውኑ በመጠመቅ እምነቱን ለሌሎች እንዲገልጥ ይፈልጉ ነበር።
በማርቆስ 16፡15-16 ውስጥ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ወንጌልን እንዲሰብኩ አዝዟቸዋል። በዚህ ትእዛዝም ላይ ያመኑ የተጠመቁ ይድናሉ ብሏል። ስለዚህ የእርሱ ፈቃድ ያመኑ ሁሉ ወዲያውኑ እንዲጠመቁ ነው። በአንጻሩ ደግሞ የማያምኑ እንደሚኮነኑ ተናግሮአል። ማስተዋል ያለባችሁ ያልተጠመቁ ይኮነናሉ አለማለቱን ነው። ሰውን የሚያስኮንነው አለማመኑ ነው። ኢየሱስ በምን ምክንያት ነው፥ ሰው ለመዳን «አምኖ መጠመቅ አለበት» ያለው? መጠመቅ የውስጣዊ እምነት ምልክትና ማኅተም ነው። ያመኑ ሁሉ እንደ እምነታቸው ክፍል መጠመቅ እንዳለባቸው ይጠበቅ ነበር። ይህን ጥቅስ እንድንነዘበው አንድ ማብራሪያ እነሆ፡- እኔ እናንተ ካላችሁበት ከተማ ተነሥቼ ወደ አዋሳ እንደምሄድ አድርጋችሁ ገምቱ። ወደ አውቶቡስ ጣቢያ ወስዳችሁ እንዲህ ትሉኛላችሁ፥ «አውቶቡስን ተሳፈርና ቁጭ በል፥ ዛሬውኑ አዋሳ ትገባለህ። በዚህ አውቶቡስ ላይ ባትሳፈር ግን ዛሬ አዋላ ልትገባ አትችልም።» ታዲያ ይህን አውቶቡሱን ሳልሳፈር ምን እሆናለሁ? አዋላ አልደርስም፡፡ ወደ አውቶቡሱ ውስጥ ገብቼ ብቀመጥስ ምን ይሆናል? በዚያኑ ቀን አዋሳ እደርሳለሁ? ወደ አውቶቡስ ገብቼ ባልቀመጥ ምን እሆናለሁ? ይህን ባደርግ ከሞኝነት ይቆጠርብኛል። አይደለም? ወደ አዋሳ የሚሄድ አውቶቡስ ተሳፍሮ ላይቀመጡ በዚያ ሁሉ ጉዞ ላይ ቆሞ አዋሳ መድረስ ከሞኝነትም ሞኝነት ነው። አውቶቡስ ተሳፍሮ ቁጭ ማለት የተለመደ ድርጊት ነው። በማርቆስ 16፡16 ውስጥ የተጠቀሰው ቃል ይህ አሁን የጠቀሰነውን ምሳሌ ይመስላል። አውቶቡስ ተሳፍሮ መቀመጥ፥ በማመንና አምኖ በመጠመቅ ይመሰላል። በዚሁ ረገድ አውቶቡስን ተሳፍሮ መጓዝ የመቀመጥ ድርጊት ክፍል ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ጥምቀት ኢየሱስን የማመን ክፍል ወይም ድርጊት ነው። ቀጥሎም አውቶቡሱን አለመሳፈሬ ወደ አዋሳ ሊያደርሰኝ እንደማይችል ሁሉ፥ እንዲሁም አንድ ሰው በኢየሱስ አላመነም ማለት ይህ ሰው ይኮነናል ማለት ነው። ማርቆስ 16፡16 እንደሚናገረው፣ ጥምቀት ከኢየሱስ ተከታዮች የሚጠበቅ የውጪአዊ ምልክትና የውስጣዊ እምነት ማኅተም ነው።
1ኛ ጴጥሮስ 3፡21 ተመሳሳይ ጥቅስ ነው። ጴጥሮስ ለአንባቢያን ሊናገር፥ «ጥምቀት አሁን ያድነናል» ይላል። ስለዚህ እነዚህን ቃላት በየራሳቸው ብናነባቸው፥ በቀላሉ መጠመቅ በራሱ ብቻ ያድነናል ብለን እናስብ ይሆናል። እዚህ ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቂት ቃላትን አውጥቶ ብቻ ከሌሎች የጥቅስ አሳብ ጋር ሳያስተያዩና ሳያብላሉ ማንበብ ሁልጊዜም ቢሆን ስሕተት ነው። ጴጥሮስ «ጥምቀት አሁን ድነናል» ሲል የተናገረውን ወዲያውኑ ሲያብራራ፥ «ሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም» ብሏል። ሰዎች በውኃ ውስጥ ጠልቀው በመጠመቅ፥ ወይም በራሳቸው ላይ ውኃ በማፍሰስ ብቻ ይድናሉ አላለም። ጨምሮ ሊያስገነዝብ፥ «ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው» ይላል። እንግዲህ የልሳችንና የአእምሮአችን (ማለትም የሕሊናችን) ውስጣዊው ለውጥ ነው የሚያድነን። ሆኖም ለጴጥሮስና ለሌሎችም አማኞች በአዲስ ኪዳን ጊዜ ለነበሩት ሁሉ፥ «እግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና» የመጣው በዚያኑ በሚጠመቁበት ጊዜ ነበር። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደተመለከትነው፥ ሰዎች ክርስቶስ አዳኛቸው መሆኑን እንዳመኑ ወዲያውኑ ይጠመቁ ነበር። በውኃ የሆነ ሥነ ሥርዓት ሊያድን እንደማይችል ጴጥሮስ በግልጽ ተናግሮአል። ነገር ግን መታወስ ያለበት ሐዋርያው ይህን ሲናገር፥ አያያዞም የበጎ ሕሊና ልመና ያለው ሁሉ ከዚሁ ጋር ሥነ ሥርዓቱን ጠብቆ መጠመቅ እንዳለበት ማሳሰቡ አልቀረም።
ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ውስጥ ያለውን ስብከቱን ባሰማ ጊዜ፥ ለአዳመጡት ሰዎች ይህንኑ የመሰለ ቃል ተናግሮአል። የሰሙትም ሰዎች ኢየሱስን የመስቀላቸው ኃጢአት በተሰማቸው ጊዜ ጮኸው፥ «ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ?» (ሐዋ. ሥራ 2፡37) ሲሉ ጠየቁ። ጴጥሮስም መልሶ፥ «ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ» አላቸው። ይህ የሐዋርያው አነጋገር፥ ሰዎች የኃጢአታቸውን ይቅርታ ለማግኘት መጠመቅ ያለባቸው የሚመስል ትምህርት ሊሆን ይችላል። በጥንቱ ግሪክ ትርጉም ስለዚህ ጥቅስ፥ «ሁላችሁም ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፥ መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፥ እያንዳንዳችሁም ተጠመቁ» የሚል ነው። በጥንቱ ግሪክ ላይ ንስሐ ከኃጢአት ስርየትና መንፈስ ቅዱስን ከመቀበል ጋር በቅርብ የተያያዘ ሲሆን፥ ጥምቀት ግን ለየት ያለ አሳብ ሆኖ ተገልጾአል። ጴጥሮስ የኃጢአት ይቅርታን እንዲቀበሉ ይጠመቁ አይልም። ነገር ግን እንዲጠመቁ ያዝዛቸዋል። እንግዲህ እነዚሁ ሰዎች ነበሩ ከሰባት ሳምንታት በፊት ስጰንጤናዊ ጲላጦስ ፊት ኢየሱስን «ስቀለው» እያሉ ይጮኹ የነበሩት። ስለ ሠሩት ኃጢአት አሳባቸውንም ሆነ ልባቸውን እንዲለውጡ ብቻ ሳይሆን፥ ንስሐ መግባታቸውን በኢየሱስ ስም በመጠመቅ ኢየሱስን እንደ መሢሕና እንደ አዳኛቸው አድርገው መቀበላቸውን በዚህ ውጪአዊ ድርጊት ማሳየት ነበረባቸው።
ጥምቀት የውስጣዊ እምነት ውሣዊ ምልክትና ማኅተም ነው። ክርስቲያን የሆን ሁለተኛው ደረጃ አይደለም። እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲህ በማለት ሊገልጸውና ሊያሳውቅ የሚገባው፣ ለደኅንነቴ ኢየሱስን ብቻ አምናለሁ። እንደ ሕይወቴ ጌታ፥ እርሱን ብቻ እከተላለሁ» የሚለውን ነው።
3. ውጪአዊው የንስሐ ሁኔታ ሁልጊዜ በውስጣዊው እምነት ሊታጀብ ይገባል።
ጥያቄ፡- ሮሜ 10፡9-10 እንብብ። ለመዳን ምን እናድርግ?
ሮሜ 10፡9-10 ያለው ክፍል በግልጽ ስለ ጥምቀት አይናገርም። ነገር ግን ስለ ውስጣዊ እምነትና ስለ ውጫዊ ምስክርነት የሚናገር አስደናቂ ክፍል ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን እንዳስነሣው ብናምን፥ እንደዚሁም፥ እርሱ ጌታ እንደሆነ በአፋችን ብንመሰክር እንድናለን ይላል። በልባችን ማመን ሲባል እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት እንዳነሣውና በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ እንደምንድን ማመን ነው። ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በአፋችን መመስከር ማለት ኢየሱስ ሁሉን ቻይ የሆነ የዓለም ሁሉ ጌታ ስለሆነ በሕይወታችን ውስጥ ልናመልከውና ልንታዘዘው እንደሚገባ ለሁሉ በይፋ ማሳወቅ ማለት ነው። ጳውሎስ ውስጣዊውን እምነት በአፍ ከመመስከር ሁኔታ አልለየውም። ሁለቱም እንደሚፈጸም ያምናል። በእውነት ንስሐ ገብተው በልባቸውና በአሳባቸው ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው የሚቀበሉ ሁሉ በይፋ በአፋቸው መመስከር ይገባቸዋል። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደተመለከትነው፥ እግዚአብሔር እያንዳንዱ አማኝ ይህን ምስክርነት በጥምቀት እንዲያረጋግጠው ይፈልጋል።
ጥያቄ፡- ሀ) በዛሬው ትምህርታችን ላይ አዲስ ኪዳን በጥምቀትና በእምነት መካከል ስላለው ግንኙነት የለጠው ማብራሪያ፥ በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ካሉ አብዛኛዎቹ ምእመናን ግንዛቤ ጋር ምን ያህል ይስማማል? ደግሞስ ይቃረናል? ለ) ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የእምነትና የጥምቀት አስተሳሰብ እንዴት ታብራሩታላችሁ?
ዛሬ ብዙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ስለ ጥምቀት የተመዛዘነ አስተሳሰብ የላቸውም። አንዳንዶች እንደሚያምኑት፥ በመጠመቃቸው ብቻ የኃጢአት ይቅርታን የሚያገኙ ይመስላቸዋል። ነገር ግን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ማንንም ክርስቲያን አያደርግም። እንዲሁም የጥምቀት ሥነ ሥርዓት የማንንም ኃጢአት ሊያስተሰርይ አይችልም። ደኅንነትና የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው ንስሐ በመግባትና በእምነት ብቻ እንጂ በመልካም ሥራ አይደለም። ሌሎች ክርስቲያኖች ደግሞ ለጥምቀት ጨርሶ ክብደት አይሰጡትም። ጥምቀት ክርስቲያኖች ከዳኑ በኋላ በገዛ ፈቃዳቸው የሚፈጽሙት ሥነ ሥርዓት ነው እስከ ማለት ይደርሳሉ። ይህን በማድረግም፥ ሰዎች በውስጣቸው ስለ ክርስቶስ እምነት ካላቸው፥ ስለ ጥምቀት ይህን ያህል ሊጨነቁበት አይገባም የሚል ትምህርት የሚያስፋፉ ይመስላሉ። ነገር ግን ዛሬ እንደተመለከትነው፥ የአዲስ ኪዳን ትምህርት እንደዚህ ወሰን የዘለለ አስተሳሰብ አይደለም። በመሆኑም ወደ ደኅንነት የመድረሻው መንገድ ንስሐና እምነት ብቻ ነው። ሆኖም አዲስ ኪዳን ጥምቀትን፥ የውስጣዊ እምነት ውጫዊ ምልክትና ማኅተም እንደሆነ አድርጎ ይመለከተዋል። አማኞች የሆኑ ሁሉ፥ ለመላው ዓለም እምነታቸውን የሚያሳውቁት በጥምቀት አማካይነት ነው።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
