በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተደጋግሞ የተገለጠው የጌታ መልአክ፥ ወይ የያህዌ መልአክ ራሱ አምላክ መሆኑን የሚያስረዱ ሦስት ክፍሎችን ተምረናል። እንደዚሁም የያህዌ መልአክ፥ የእግዚአብሔር ልጅ በአካል ከመገለጡ በፊት ማለትም ከተሠገዎ ምሥጢር አስቀድም በአካል የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ነበረ ተከታትለናል። እንደዚሁም፥ ሰዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ የያህዌ መልክ ፈጥሮ ደርሶ እንደ ታደጋቸው ተመልክተናል። ዛሬ ደግሞ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የያህዌ መልአክ መገለጡን የሚያስተምሩ ሌሎች ክፍሎችን እናጠናለን። ይህ የእግዚአብሔር በሰብአዊና መልአካዊ አምሳል መታየት፥ ቅድመ- ተሠገዎ የክርስቶስ መገለጥ ሆኖ ሊታሰብ ይችላል።
የያህዌ መልአክ የእግዚአብሔርን ሕዝብ መራ
ጥያቄ፡– ዘፀ. 3፡1-10 እንብብ። ሀ) የያህዌ መልአከ ላሙሴ የተገለጠው እንዴት ነበር? ለ) የያህዌ መልአከ ራሱ እግዚአብሔር ስለ መሆኑ ጥቅሱ ምን ይላል? ሐ) በዚህን ጊዜ የያህዌ መልአክ በምን ምክንያት ለሙሴ ተገለጠለት?
በዘፀ. 3፡1-10 ውስጥ የያህዌ መልአክ በሚቃጠል ቁጥቋጦ ውስጥ ለሙሴ ተገልጦለታል። በቁጥቋጦው ውስጥ ሆኖ ለሙሴ የተናገረው እግዚአብሔር ራሱ እንደሆነ ክፍሉ ያስረዳናል። ስለዚህ ትናንት እንደ ተመለከትናቸው ጥቅሶች ሁሉ፥ እነዚህም ጥቅሶች የያህዌ መልአከ እግዚአብሔር ራሱ
መሆኑን ያስረዳሉ። በዘፀአት 3 ውስጥ የያህዌ መልእክ፥ በሰብአዊ መልክ ወይም በመልአክ ቅርጽ አልታየም። ነገር ግን በዚህ ክፍል፥ ራሱ ያህዌ የሆነው የያህዌ መልእክ በእሳት መልክ ተገለጠ። ትናንትና እንደተመለከትናቸው ክፍሎች የያህዌ መልአክ የተገለጠው ሕዝቡ በትልቅ ችግር ውስጥ በነበረበትና ርዳታውን በፈለጉበት ጊዜ ነበር። ሕዝቡ በግብፃውያን የጭቆና ቀንበር ሥር ሆነው የሚማቅቁበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም የያህዌ መልአክ ከነበሩበት የባርነት ቀንበር ሙሴ ነፃ
እንዲያወጣቸው ሊጠራው ተገለጠ።
ጥያቄ፡- ዘፀ. 13፡21፤ 14፡19፣ 23፡20-23፤ 23፡34፤ 33፡2 አንብብ። ሀ) እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይመራቸው የነበረው የደመናና የእሳት ዓምድ የእግዚአብሔር የራሱ መገለጥ እንደ ነበረ የሚያመለክቱ ምን ምን ነጥቦችን በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ታገኛላችሁ? ለ) እግዚአብሔር በደመናና በእሳት ዓምድ ውስጥ ለእስራኤላውያን በሚገለጥላቸው ጊዜ ምን ያደርግላቸው ነበር?
በዘፀ. 13፡21 ውስጥ እግዚአብሔር ራሱ፥ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ በደመናውና በእሳቱ ዓምድ ውስጥ ሲመራቸው እንደ ነበረ ይናገራል። እሳቱና ደመናው ለየት ያለ የእግዚአብሔር መገለጥ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ ለሕዝቡ የተገለጠው በአካል ላይን ሊያዩት በሚችሉት ሁኔታ ነበር። ዘፀ. 14፡19 እንደሚነግረን ደግሞ ይህ የደመናና የእሳት ዓምድ እርግጠኛ «የእግዚአብሔር መልአክ» መገለጥ እንደ ነበረ ነው። ይህም የያህዌ መልአክ ሳይሆን አይቀርም። ይኸው መልአክ እስራኤላውያንን ወደ ከነዓን እየመራ የሚወስዳቸውና ከፊታቸው ከነበረው ምድር ከነዓናውያንን የሚያባርርላቸው እንደሚሆን እግዚአብሔር ይናገራል። በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ክፍሎች እግዚአብሔር በያህዌ መልአክ አምሳል ቢገለጥም በደመናና በእሳት ዓምድ የተገለጠው የያህዌ መልአክ ዋና ተግባሩ፥ ሕዝቡን መምራትና ጠላቶቻቸውንም ድል ማድረግ ነበር። እግዚአብሔር ራሱ በደመናና በእሳት ዓምድ ውስጥ ስለተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክም በደመናና በእሳት ዓምድ ውስጥ ስለታየ፥ ይህ የእግዚአብሔር ልጅ በተሠገዎ ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ በፊት በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጠበት ሌላው ምሳሌ ነው።
ጥያቄ፡- በሕይወታችሁ ውስጥ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ሆኖ ሲመራችሁና ሲከላከልላችሁ አስተውላችሁ ታውቃላችሁን? ለዚህ ግንዛቤአችሁ ከ2-3 የሚሆኑ ምሳሌዎችን ጻፉ።
እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች በምድረ በዳ በእሳትና በደመና ዓምድ እየመራ ከጠላቶቻቸውም ይከላከልላቸው ነበር። በቀጥታም ከሚቃጠል ቁጥቋጦ ውስጥ ሆኖ እየተናገረ ሙሴን ይመራው ነበር። ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ይህንኑ በመሰለ ታምራዊ አቅጣጫ የሚመራበት ጊዜ አለ። ነገር ግን የዛሬ ክርስቲያኖች በብሉይ ኪዳን ውስጥ የነበሩ አማኞች ያልነበራቸው ነገር አለን። የተሟላ የእግዚአብሔር ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለን። ዛሬ እግዚአብሔር በአብዛኛው መንፈሱ በተጻፈው ቃል፥ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካይነት አዘውትሮ ለሕዝቡ ይናገራል። ቃሉንም በሚያጠኑበት ጊዜ ይመራቸዋል፥ አቅጣጫውንም ያሳያቸዋል። እንደዚሁም እግዚአብሔር እርሱን በሚፈሩት በሳል ክርስቲያን አማኞችና በጥሞናና በጸሎት ውስጥ በሚመጣ የመንፈስ ቅዱስ ፀጥተኛ ድምፅ በመጠቀም፥ ሕዝቡን ይመራል።
የያህዌ መልአክ የእግዚአብሔርን ጠላቶች ቀጣ
ጥያቄ፡– ዘኍ. 22፡22-35 አንብብ። ሀ) የያህዌ መልአክ ለማን ተገለጠ? ለ) አህያይቱ መንገዱን ባትለቅለት ኖሮ፥ የያህዌ መልአክ ምን ያደርግ ነበር? ሐ) ታዲያ መልአኩ ምን አደረገ?
በዘኁልቁ 22 ውስጥ የተከሰተው የያህዌ መገለጥ ከሌሎቹ ለየት ያለ መገለጥ መሆኑን በዚህ ክፍል እንመለከታለን። ይህ ታሪክ የተፈጸመው እስራኤላውያን በሞዓብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ወደ ከነዓን ለመግባት ይዘጋጁ በነበሩበት ጊዜ ነበር። የሞዓባውያን ንጉሥ ባላቅ እስራኤላውያንን ስለ ፈራ፥ በለዓም መጥቶ እንዲረግምለት ጠራው። ምንም እንኳን በለዓም ስለ አንዱና እውነተኛው አምላክ የሚያውቅ ቢሆንም፥ ስለ ኀጢአቱ ሁኔታ በዘኁ. 31፡8፤ በኢያሱ 13፡22፤ በ2ኛ ጴጥ. 2፡15 እና በራእይ 2፡14 ላይ ተጽፎ የሚገኘው እንደሚያረጋግጠው በለዓም እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ ሳይሆን ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። ምንም እንኳን ከጅምሩ እግዚአብሔርን የሚታዘዝ ሲመስልም፥ እንኳን ሄዶ እስራኤላውያንን እንዲረግም እግዚአብሔር በግልጽ አልፈለገም። እንዲሄድ የፈቀደለትም፥ እንዳይሄድ ከከለከለው በኋላ ነበር። በለዓም የኃጢአት ዝንባሌ እንዳለው እግዚአብሔር በግልጽ ያውቅ ነበር። ስለዚህ በመንገድ ላይ ሊቀጣው ስለፈለገ እንዲሄድ ፈቀደለት፤ ከዚያም እስራኤላውያንን ሊረግም እየገሰገሰ ሲመጣ የያህዌ መልአክ ሊገድለው በመንገዱ ላይ ቆሞ ተገናኘው። ነገር ግን እግዚአብሔር የበለዓምን አህያ ዓይን ከፈተ። አህያይቱም የያህዌን መልአክ በፊቷ ባየች ጊዜ ሦስት ጊዘ መንገዱን በመቀየር የበለዓምን ሕይወት – አተረፈች። በመጨረሻውም እግዚአብሔር በለዓም እስራኤላውያንን በመርገም ሊፈጽው ስለተነሣሣበት ኃጢአቱ ሊገድለው በፊት ለፊቱ ቆሞ የነበረውን የያህዌን መልአክ እንዲያይ ዓይኑን ከፈተለት። እግዚአብሔር እንደ ገና እርሱ የነገረውን ብቻ እንዲናገር በለዓምን አስጠነቀቀው። በለዓምም የያህዌ መልአክ ሊገድለው መዘጋጀቱን እንዳየ፥ ለእግዚአብሔር በመታዘዝ እስራኤላውያንን ሳይረግም ቀረ። በመርገም ፈንታም ባረካቸው። በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ የያህዌ መልአክ፥ ለእግዚአብሔር መታዘዝን አሻፈረን የሚሉትን የሚቀጣ ዳኛ ነው፡ 13ኛ ጥያቄ፡- 2ኛ ነገ 19፡35 አንብብ። የጌታ መልአክ በአዎ ራውያን ሠራዊት ላይ ምን ፈጸመ?
በ2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 18-19 ያለው ታሪክ የአምር ሠራዊት እግዚአብሔርን ይፈራ በነበረው በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ እንደ ተነሣበት የሚያወሳ ነው። የአሦር ንጉሥ እግዚአብሔር አንተን ከእኔ እጅ ሊያድንህ ኀይል የለውም በሚል ማስፈራሪያ የጻፈለትን ደብዳቤ ሕዝቅያስ ወደ ቤተ መቅደስ ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት አኖረው። ከዚያም እግዚአብሔር ከዚህ አደጋ እንዲያወጣው ጸለየ። እግዚአብሔርም ከዚህ ወራሪ እንደሚጠብቀው አረጋገጠለት። በዚያኑ ሌሊት የያህዌ መልአክ የአሦራውያንን ሠራዊት በምሽጋቸው እንዳሉ ደመሰሳቸው። የያህዌ መልአክ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማስፈራራት የተነሣሣውን በለዓምን ለመቅጣት እንደ ተንቀሳቀሰ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር ጥበቃ ይታመን የነበረውን ሕዝቡን ለመደምሰስ በማስፈራራት ላይ የነበረውን የአሦርንም ሠራዊት አጠፋው።
ጥያቄ፡- እግዚአብሔር የማይታዘዙትን ወይም የእርሱ በሆኑት ላይ አደጋ የሚጥሉትን ሲቀጣቸው አይታችሁ ከሆነ ከምታስታውሷቸው ሁኔታዎች ውስጥ ምሳሌ የሚሆኑትን ጻፉ።
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን የጎዱትን እንዴት እንደ ቀጣ የሚያመለክቱ ብዙ ሁኔታዎች አሉ። ባለፉት ኀምሳ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያውያን አማኞች ብዙ ጊዜ በስደት ምክንያት ተሠቃይተዋል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ለማጠንከር ሲል እነዚህ አማኞች በመከራቸው እንዲጸኑ አድርጓቸዋል። በሌላ ጊዜ አማኞች ሊሠቃዩ ራሱ በተአምር ጣልቃ ገብቶ ሕዝቡን በመከላከል፥ የሚያሳድዷቸውን የቀጣበት ጊዜያትም ነበሩ። በብሉይ ኪዳን ዘመን ሲያደርገው እንደነበረው፥ እግዚአብሔር ዛሬም ቢሆን የሕዝቡን ጠላቶች ይቀጣቸዋል።
የያህዌ መልአክ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ኃጢአት ቀጣ።
የያህዌ መልአክ የእግዚአብሔር ጠላቶች፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስላስፈራሩ እንደ ቀጣቸው ሁሉ የራሱንም ሕዝብ በኃጢአታቸው ምክንያት ቀጥቶአቸዋል።
ጥያቄ፡– 1ኛ ዜና መዋዕል 2፡1-4፥ 8-19፥ 27 እንብቡ። ሀ) ዳዊት ምን ኃጢአት ሠራ? ለ) ይህ ኃጢአት የሆነበት ምክንያት ለምን ይመስላችኋል? ዳዊት በሠራው ኃጢአት በእስራኤል ላይ ምን ቅጣት ደረሰ? መ) እንደ ቁጥር 12 እና 18 አገላለጽ ይህን ቅጣት የፈጸመው ማን ነው? ሀ) ቅጣቱ በቀረ ጊዜ ዳዊት ምን አደረገ?
1ኛ ዜና መዋዕል 21 ዳዊት ሕዝቡ እንዲቆጠር በማድረግ ኃጢአት እንደ ፈጸመ የሚነግረን ታሪክ ነው። ይህ የዳዊት ድርጊት ኃጢአት ሊሆን የቻለበት ምክንያት ምን ያህል ብዛት ያለው ሠራዊት እንዳለው ለማወቅ የፈጸመው ተግባር ስለነበረ ነው። በዚህ ረገድ ድልን በሚሰጠው በአምላኩ በመታመን ፈንታ በሠራዊቱ ብዛት በጠላቶቹ ላይ ድልን የሚቀዳጅ መስሎት በመታበዩ ኃጢአትን ሠርቷል። ስለዚህ ዳዊት በዚህ አኳኋን ኃጢአት በመሥራቱ እግዚአብሔር ቀጥቶታል። እግዚአብሔርም ሊቀጣው ባሰበ ጊዜ፥ ሦስት ምርጫዎችን አቅርቦለት ነበር። ዳዊትም ከሦስቱ ቅጣቶች መካከል እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ለሦስት ቀናት በቸነፈር እንዲቀጣ ለመነው። ከዚህ የቸነፈር ቅጣት የተነሣ ሰባ ሺህ ሰዎች አለቁ። ይህን ቅጣት የፈጸመው የያህዌ መልአክ ነበር። መልአኩም በያዘው ሰይፍ አማካይነት እነዚህ ሰዎች በቸነፈር እንዲመቱ አደረገ። ከዚህም ቀጥሎ የያህዌ መልአክ በቸነፈር ኢየሩሳሌምንም ለመደምሰስ እንደ ተዘጋጀ ዳዊት ወዲያውኑ ኃጢአቱን ተናዝዞ ሲጸልይ፥ እግዚአብሔር ጸሎቱን አድምጦ ቸነፈሩ እንዲቆም አደረገ፡፡ ከዚያም የያህዌ መልአክ ጋድ በተባለው ነቢይ አማካይነት፥ ዳዊት ወደ እግዚአብሔር በንስሐ መመለሱን ለማሳየት ምን ማድረግ እንዳለበት ነገረው። ስለዚህ የያህዌ መልአክ የቸነፈሩ ቅጣት በሕዝቡ ላይ እንዳይደርስ ባቆመበት ስፍራ፥ ዳዊት መሠዊያ ሠርቶ መሥዋዕት እንዲያቀርብ ነገረው። መሠዊያውም ኦርና በተባለ ሰው አውድማ ላይ እንዲሠራ ታቀደ። በዚሁ መሠረት ዳዊት አውድማውን ከኦርና ገዝቶ መሠዊያውን ከሠራበት በኋላ መሥዋዕትን አቀረበበት።
የያህዌ መልአክ ሕዝቡን ከጥፋት ከመጠበቁና መመሪያም ከመስጠቱ በተጨማሪ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ይቀጣቸው እንደ ነበረ በዚህ ታሪክ ውስጥ እንገነዘባለን። እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚቀጣቸው ስለ ጠላቸው አይደለም። እርሱ ስለሚወዳቸውና ቅዱሳንም እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ይቀጣቸዋል።
ጥያቄ፡- ዕብራውያን 125-6፥10-11 እንቡ። እግዚአብሔር ልጆቹን በምን ምክንያት ይቀጣቸዋል ወይም ይገሥጻቸዋል?
በዕብራውያን 12 ውስጥ እንደምንመለከተው፥ እግዚአብሔር ልጆቹ ቅዱሳን ሆነው እንዲያድጉ ስለሚፈልግና ስለሚያፈቅራቸው ይቀጣቸዋል። ስለዚህ የያህዌ መልአክ በዳዊት ኀጢአት ምክንያት የእስራኤልን ሕዝብ ቀጣ። ሆኖም ሊጎዳቸው አልነበረም። እግዚአብሔር ይህን ቅጣት በሕዝቡ ላይ ያደረገበት ዓላማና ግብ ጻዊትና እስራኤል ዳግም በኃይላቸው እንዳይመኩና በእርሱ ብቻ እንዲታመኑ ለማድረግ ነበር።
ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ቅጣት ደርሶባችሁ ያውቃል? ይህ የደረሰባችሁ መች ነበር? ለ) እግዚአብሔር በዚህ ቅጣት አማካይነት ምን ሊያስተምራችሁ ያሰበ ይመስላችኋል?
ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ልጆቹን ስለሚያፈቅራቸው ይቀጣቸዋል። በዚሁ ረገድ እግዚአብሔር ቅዱሳን ሆነን እንድናድግ ስለሚሻ ኀጢአት በምንሠራበት ጊዜ ይቀጣናል። ምንም እንኳን ኢየሱስ የሚያፈቅረን መድኃኒታችን ቢሆንም፥ በሳል የሆነ የክርስትና ሕይወት እንዲኖረን ለማድረግ ይቀጣናል። ስለሆነም በእግዚአብሔር ቅጣት ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ከሁኔታው ትምህርት በመውሰድ ኃጢአት መሥራትን ማቆምና በቅድስና ማደግ ይገባናል። የያህዌ መልአከ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የተገለጠባቸው ሌሎች ሁኔታዎች፡፡
የያህዌ መልአክ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በግልጽ የተገለጠባቸው ሌሎች ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው፡-
መሳፍንት 6፡11-24 – ክሶምሶንና ከሙሴ ታሪክ ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የያህዌ መልአክ ጌዴዎንን ጠርቶ የጣዖታትን ምስል ሰባብረህ ጣልና የእግዚአብሔር ሕዝብ በጠላቱ ላይ ድልን ይቀዳጅ ዘንድ ምራው አለው።
1ኛ ነገ 19፡5-7- ኤልያስ እግዚአብሔርን ሲያገለግል ቆይቶ፥ ሕይወቱን ለማዳን በሸሸ ጊዜ የያህዌ መልአክ ምግብና ውኃ ሰጠው።
2ኛ ነገ. 1፡15 – የያህዌ መልአክ፥ ኤልያስ ወደ ንጉሥ አክአብ ዘንድ ሄዶ እንዲጋፈጥ አዘዘው።
መዝሙር 34፡7 – የያህዌ መልአክ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ጠበቀ።
መዝሙር 9፡1-6 – የያህዌ መልአክ አገልጋዮቹን የሚጎዱትን አባረረ።
ዘካርያስ 1፡9-21 – የያህዌ መልአክ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ ቀድሞው ስፍራው እንደሚመለስ የማጽናኛ ቃላትን ተናገረ።
በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችና ቀደም ሲል በሌሎች ክፍሎች እንደተመለከትነው ሁሉ፥ የያህዌ መልአክ በተመሳሳይ ሁኔታዎች ተገልጦአል። በቀጥተኛ የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ሕዝቡን ሲጠራ፥ ሲመራና ሲያጽናና ይታያል።
የያህዌ መልአክ የተገለጠበት አንድ ሌላ የብሉይ ኪዳን ክፍል ደግሞ አለ፣ ይህ ክፍል ለየት ያለ ስለሆነ፥ ለብቻው እናጠናዋለን።
የያህዌ መልአክ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚያስገባ መንገድ ሲከፍት
ጥያቄ፡- ዘካርያስ 3፡1-10 አንብቡ። ሀ) የእስራኤል ሊቀ ካህን ከሆነው ከኢያሱ ጋር ቆሞ የነበረው ማን ነበር? ለ) እያንዳንዳቸው ምን ተናገሩ? ሐ) የያህዌ መልአክ ለኢያሱ ምን አደረገላት? መ) የያህዌ መልእክ ለኢያሱ ምን ተስፋ ሰጠው?
ዘካርያስ 3 እስራኤልን ስለ እግዚአብሔር ይቅርታ የሚያስተምር ራእይ ነው። በዚህ ራእይ አንድ መልአክ (ዘካ. 1፡9፥14፤ 28) ኢያሱ የተባለውን የእስራኤልን ሊቀ ካህን፥ በያህዌ መልአክ ፊት ቆሞ ሳለ ለዘካርያስ አሳየው። ነገር ግን በኢያሱ ሌላ ጎን ሰይጣን ቆሞ ነበር። ሰይጣንም እዚያ ቆሞ ኢያሱን ይከስ ነበር። ኢያሱም በወቅቱ ያደፈ ልብስ ለብሶ ነበር። ይህ እንግዲህ ኢያሱና የተቀሩትም የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን በኃጢአታቸው በድለውት እንደ ነበረ ያሳያል። ኃጢአታቸውም በእግዚአብሔር ፊት ቀርበው ማምለክ እንዳይችሉ አድርጓቸው ነበር። በእርግጥም ስለዚህ በኃጢአት ረክሰው ስለ ነበሩ፥ የሰይጣን ክስ ልክ ነበር። ነገር ግን የያህዌ መልአክ የራሱን የያህዌን ቃል በመናገር፥ ሰይጣንን ገሠጸው። ከዚህ በኋላ የያህዌ
መልአክ፥ በእግዚአብሔር ፊት በሚገባ ለመቆም እንዲችል ኢያሱ ንጹሕ ልብስ እንዲለብስ አዘዘ። ኢያሱም ንጹሑን ልብስ ከለበሰ በኋላ፥ የያህዌ መልአክ፥ የያህዌን ቃል መናገሩን ቀጠለ። ኢያሱም ሆነ የተቀረው የእስራኤል ሕዝብ እንዲታዘዘው ካሳሰስ በኋላ፥ ስለሚያገኙት ይቅርታና ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚኖራቸው ኅብረት ተስፋ ሰጣቸው።
ይህ ክፍል ጠቃሚ ክፍል ነው፤ ምክንያቱም የያህዌ መልአክ፥ እርሱም ወደፊት ሥጋ ለብሶ የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሚሰጠው አገልግሎት ስለሚያመለክት ነው። በዚህም መሠረት ለሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ይናገራል። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከልም ያማልዳል። በኃጢአት ለተበከሉ ሰዎችም ይቅርታን ይሰጣል። በዚህም የሰይጣንን ክስ ሳይፈሩ በእግዚአብሔር ፊት እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል።
ጥያቄ፡- ዕብራውያን 10፡19-22 አንብቡ። በጌታ ኢየሱስ ደምና በእርሱ ታላቅ ክህነት ምክንያት አማኞች ምን እንዲያደርጉ ተጠርተዋል?
የያህዌ መልአክ ለኢያሱና ለብሉይ ኪዳን አማኞች እንዳደረገላቸው ሁሉ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዲስ ኪዳን አማኞች ይቅርታን በመስጠት ወደ እግዚአብሔር ፊት እንዲቀርቡ ያደርጋቸዋል። እንደዚሁም የኢየሱስ ደም ይቅርታን ይሰጣል። በሊቀ ክህነቱም በእርሱ የሚያምኑት በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርበው ጸጋን እንዲያገኙ መንገዱን ይከፍትላቸዋል።
በእግዚአብሔር ፊት ብቁዎች ሆናችሁ እንዳትቆሙ የሚያደርጋችሁን ኃጢአት ተናዛችሁ ንስሐ እንድትገቡ ለተወሰነ ጊዜ ጸልዩ። እንደዚሁም የእኛ አቋም ይህ ሆኖ ሳለ፥ በእግዚአብሔር ፊት ብቁዎች ሆነን ለመቅረብ እንድንችል ለሚያደርገን ለጌታ ኢየሱስ በዚህ ወቅት ምስጋና እናቅርብ።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
