Site icon

ለመሆኑ በመጨረሻው ሰዎች ሁሉ ይድናሉ ወይ? 

ሰዎች በክርስቶስ ሥራ ብቻ እንደሚድኑ ተመልክተናል (ትምህርት 13 እና 14)። እንደዚሁም እግዚአብሔር ወደ ራሱ የጠራቸው የሚያምኑና ንስሐ የሚገቡ፥ ኋላም ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱ፥ በመጨረሻ የደኅንነትን በረከቶች እንደሚያገኙ ተገንዝበናል (ትምህርት 5 እና 16)። ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተረጋገጠው፥ በክርስቶስ ውስጥ እምነታቸው የተረጋገጠላቸው ብቻ ይድናሉ። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር ክርስቶስን ንቀው ሳይቀበሉት የሚቀሩትን ለዘላለም እንደሚቀጣቸው የሚያስተምሩን ብዙ ጥቅሶች አሉ። 

ጥያቄ- ማቴ. 25፡41፥ 46 አንብብ። ሀ) ክርስቶስ አድቃን ባለመሆናቸው የሚፈርድባቸው ወዴት ይሄዳሉ? ለ) 2ኛ ተሰ. 1፡8-9 አንብብ። እግዚአብሔር የማያውቁትን እንዴት አድርጎ ይቀጣቸዋል? ሐ) ራእይ 20፡10፥ 14-15፤ 21፡8 አንብብ። በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ያልተገኙ ምን ይሆናሉ? መ) ለምን ያህል ጊዜ በዚያ ይሆናሉ? 

መጽሐፍ ቅዱስ ደኅንነት በክርስቶስ አማካይነት ይመጣል፥ ደግሞም በክርስቶስ የሚያምኑ ይድናሉ ብቻ ብሎ እያስተምረንም። እንደዚሁም ክርስቶስን የሚንቁ ለዘላለም ይጠፋሉ ሲልም ያስተምራል። በማቴዎስ 25፡31-46 ውስጥ ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች ፍርድ ይነግረናል። በዚህም እርሱን የሚቀበሉትንና እርሱን የሚንቁና የሚተዉትን ለማመልከት ነው። ላይቀበሉት ንቀው የተዉት በዘላለማዊ ኩነኔና በእሳት ይቀጣሉ (ቁጥር 41፥46)። በ2ኛ ተሰ. 1፡8-9 ውስጥ ጳውሎስ ሲናገር፥ እግዚአብሔርን የሚያውቁት ከኃይል ክብሩ ተለይተው በዘላለማዊ ጥፋት ይቀጣሉ ይላል። እንደዚሁም ራእይ ምዕራፍ 20፥ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ቀንና ሌት ስለሚሠቃዩበት የእሳት ባሕር ይገልጻል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ጊዜ ሰዎች ሁሉ እንደሚድኑ የማይናገር መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም አንዳንዶች ክርስቶስን ባለመቀበላቸው ይጠፋሉ። 

ሆኖም ቀን፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በመጨረሻው ጊዜ ሰዎች ሁሉ እንደሚድኑ የሚያስተምሩ የሚመስሉ ጥቂት ክፍለ-ምንባቦች አሉ። እንግዲህ ክርስቶስን ያልተቀበሉ እንደሚጠፉ በግልጽ የተመለከትን ከሆነ፥ የተባሉት ክፍለ ምንባቦች ታዲያ ምን ያስተምራሉ? 

ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐ 1፡29ን አንብብ። የእግዚአብሔር በግ የማንን ኃጢአት ነው የሚያስወግደው? ለ) 1ኛ ጢሞ. 2፡6ን አንብብ። ክርስቶስ ራሱን እንደ ቤዛ አድርጎ የሰጠው ለማን ነው? ሐ) 1ኛ ጢሞ. 4፡10ን አንብብ። ክርስቶስ የሚያድነው ማንን ነው? መ) ዕብ 2፡9 አንብብ። ክርስቶስ ሞትን የቀመሰው ለማን ሲል ነው? ሠ) 1ኛ ዮሐ 2፡2ን አንብብ። ክርስቶስ የኃጢአት ማስተሰሪያ የሆነው ለማን ነው? ረ) 1ኛ ዮሐ 4፡14ን አንብቡ። የልጁ መድኃኒትነት ለማን ነው? 

ጥያቄ፡– 2ኛ ጴጥ. 3፡9 አንብብ። እግዚአብሔር ወደ ንስሐ እንዲመጣ ማንን ይፈልጋል? 

የተወሰኑ የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች በአንድ በኩል ክርስቶስ ለመላው ዓለም ኃጢአት መሞቱን ያስተምራሉ። ዮሐ 2፡9 ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር በግ የዓለምን ኃጢአት መውሰዱን ይናገራል። 1ኛ ጢሞ. 2፡6 ደግሞ ክርስቶስ ራሱን አሳልፎ ቤዛ አድርጎ ለጠ ይላል። 1ኛ ጢሞ. 4፡10 ከርስቶስ የሰዎች ሁሉ አዳኝ ነው ይላል። እንዲሁም ዕብ. 2፡9 ክርስቶስ ለሁሉም ሲል ሞትን ቀመሰ ይላል። 1ኛ ዮሐ 2፡2 ክርስቶስ የዓለም ሁሉ ኃጢአት ማስተሰሪያ ነው ይላል። ቀጥሎም በ1ኛ ዮሐ 4፡14 ውስጥ ወልድ የዓለም አዳኝ ነው ይላል። ለማንኛውም ዘርና ጎሣ በዓለም ክፍሎች ሁሉ ላሉ የሰው ልጆች ክርስቶስ ሞቶአል ብለው እነዚህ ጥቅሶች እንደሚያስተምሩ አድርገው ይገምታሉ። ነገር ግን እነዚህ ጥቅሶች ከዚህ የበለጠ የሚናገሩ ይመስላሉ። በዚሁ መሠረት የክርስቶስ የመሥዋዕትነት ሞት በዓለም ላይ ላሉ ለኃጢአታቸው ቤዛ ሊሆን ይችላል የሚል ግንዛቤ ያላቸው ይመስላሉ። 2ኛ ጴጥ. 3፡9 ሰው ሁሉ ንስሐ እንዲገባና የዘላለምን ሕይወት እንዲያገኝ ይላል። ሐዋርያው በ2ኛ ጴጥ. 2፡1-3 ባለው ክፍል ሲያስጠነቅቅ፥ «የዋጃቸውን ጌታ የሚክዱ» ሐሰተኞች መምህራንና ነቢያት ይነሣሉ ብሏል። የክርስቶስ ሞት የኃጢአታቸውን ዋጋ ሊከፍላላቸው ሲችል ነገር ግን ክርስቶስን ንቀውና ችላ ብለው እነርሱ በፈቀዱት መንገድ ሄዱ። እግዚአብሔር ሰው ሁሉ እንዲድን ፈቃዱ ነው፥ የክርስቶስ ሞት ቤዛ ሆኖ የሁሉንም የኃጢአት ዋጋ እንዲከፍል አደረገ (ዮሐ 1፡29)። እነሆ፥ ክርስቶስ ለሁሉም አስፈላጊውን ቤዛ ከፍሏል (1ኛ ጢሞ. 2፡6)። ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ የኃጢአታችን ማስተሰሪያ ሆኖአል (1ኛ ዮሐ 2፡2)። ክርስቶስ ለሰው ሁሉ ሞትን ቀምሶአል (ዕብ. 2፡9)። ክርስቶስ ሁሉን የሚቤዥ መድኅን ነው (1ኛ ጢሞ. 4፡10፤ 1ኛ ዮሐ 4፡14)። የደኅንነት ተግባር ሁሉ ለሰዎች ሁሉ ተፈጽሞአል። ነገር ግን እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቶስ ያደረገለትን ይህን ተግባር ሊቀበል ወይም ላይቀበል ይችላል። ነገር ግን ይህን ክርስቶስ ያከናወነላቸውን ተግባር ሁሉ በእምነት የሚቀበሉ የደኅንነት በረከቶችን ተቋዳሽ ይሆናሉ። በአንጻሩም ክርስቶስ ያደረገላቸውን ሥራ ንቀው የተዉትን ደግሞ ለዘላለም ይቀጣቸዋል። ልብ አድርጉ እነዚህ ጥቅሶች የሚሉት ሰዎች ሁሉ ይድናሉ ሳይሆን፥ የሚድኑት ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የፈጸመውን ተግባር በእምነት የሚቀበሉት እንደሚሆኑ ነው። በ16ኛው ትምህርት ውስጥ ሌሎች ጥቅሶች እንደሚናገሩት፥ ጌታ ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተግባራት የሚቀበሉና መቀበላቸውንም የሚገልጹ የዘላለምን ደኅንነት ያገኛሉ። 

ጥያቄ፡- ፊልጵ. 2፡10-11 አንብብ። በክርስቶስ ፊት ተንበርክከው ንስሐ የሚገቡት እነማን ናቸው? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 5፡18 አንብብ። ሀ) የአንዱ ጽድቅ ሕይወትን የሰጠው ለማን ነው? ለ) ሮሜ 5፡17 አንብብ። በሕይወት ሳሉ በክርስቶስ አማካይነት የሚገዙ እነማን ናቸው? ሐ) 1ኛ ቆሮ. 6፡22 አንብብ። ሕያዋን የሚሆኑት እነማን ናቸው? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 11፡32 አንብብ። እግዚአብሔር ምሕረቱን ለእነማን አሳየ? 

በመጨረሻው ጊዜ ሰዎች ሁሉ እንደሚድኑ በማስመላል፥ አንዳንዶች የሚጠቀሙባቸው ጥቂት ጥቅሶች አሉ። ነገር ግን እነዚህ የሚጠቅሱዋቸው ክፍሎች የሚያስተምሩት በጣም የተለየ አሳብ ነው። ፊልጵ. 2፡10-11 ላይ ስንመለከት፥ ጉልበት ሁሉ ይንበረከካል፣ ምላስም ሁሉ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክራል፣ ሰዎች ሁሉ የኢየሱስን ደኅንነት ይቀበላሉ ማለቱ ነው ይላሉ። ነገር ግን ይህ ጥቅስ በመጨረሻ ሰዎች ሁሉ ይድናሉ አይልም። 

ይልቅስ ፊልጵ. 2፡10-11 የሚለው፥ የተፈጠሩት ሁሉ ማለትም፥ የሰው ልጆች፥ መላእክት ሆኑ ሰይጣናትም ሳይቀሩ፥ በመጨረሻው ኢየሱስ ጌታ መሆኑን ይመሰክራሉ ነው የሚለው። ስለዚህ ክርስቶስን በፈቃዳቸው የተቀበሉት ሁሉ ጌታ መሆኑን ይመሰክራሉ። በአንጻሩ ደግሞ ፈቅደው ያልተቀበሉት በግድ ጌታ መሆኑን ይመሰክራሉ። ስለሆነም፥ ሁሉም ኢየሱስ ጌታ መሆኑን ይመሰክራሉ፣ ይሁን እንጂ፣ ሁሉም ደግሞ አይድኑም። 

ሮሜ 5፡18 የአንዱ የአዳም ኃጢአት የቅጣትን ፍርድ በሰው ሁሉ ላይ እንዳመጣ፥ እንዲሁም የአንድ የክርስቶስ የጽድቅ ሥራ ብዙዎችን ከቅጣት ነፃ አድርጎ ሕይወትን ይሰጣል ይላል። ይህ ጥቅስ ይህን ማለቱ፥ ሁሉም ሰው ይጸድቃል ማለቱ አይደለም። ጳውሎስ ለመናገር የፈለገው፥ የአዳም ዘር የሆነ ሁሉ እንደ ተኮነነ፥ እንደዚያው ደግሞ በክርስቶስ የጸደቀ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ ነው። በቁጥር 17 ግልጽ እንደሆነው፥ ጳውሎስ በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው ይድናል አላለም፥ እርሱ ያለው የእግዚአብሔርን ጸጋና ጽድቅ የተቀበሉ ብቻ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት የዘላለምን ሕይወት ይወርሳሉ ነው። ሮሜ ምዕራፍ 5ም እንደሚያስተምረው፥ አንድ ሰው ለመዳን የእግዚአብሔርን ጸጋ መቀበል አለበት ይላል። ይህን ሲል ሰው ሁሉ ይድናል ማለት አይደለም። በተመሳሳይ መንገድ 1ኛ ቆሮ. 5፡22 ውስጥ ያለው ቃል፥ ሰው ሁሉ ሕያው ይሆናል አይልም። ሕያዋን የሚሆኑት፥ በክርስቶስ የሆኑ ብቻ ናቸው። እንደ መጨረሻው ጥቅስ ሆኖ ሰዎች ሁሉ በጊዜው ፍጻሜ ላይ እንደሚድኑ ይናገራል ተብሎ የሚጠቀሰው ሮሜ 11፡32 ነው። ቃሉም፥ እግዚአብሔር ምሕረቱን ለሰው ሁሉ ያሳያል የሚለው ነው። ነገር ግን ይህ ጥቅስ ሐዋርያው እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ሳይቀበሉ ስለ ቀሩ፥ እግዚአብሔር በመጨረሻ ደኅንነትን ለአሕዛብ አሳልፎ እንደ ሰጠ፥ በሦስት ምዕራፎች ላይ የተናገረው ትምህርት ማጠቃላያ ነው። እዚህ ላይ የሐዋርያው ጳውሎስ ማጠቃለያ፥ እግዚአብሔር ደኅንነትን ለመስጠት የሰዎችን ታዛዥነትና ወደ እርሱ መመለስን እንደሚፈልቀ ለማስረዳት ነው። ስለዚህ ደኅንነት ለአይሁዶች ብቻ የተሰጠ ነገር አይደለም። ደኅንነት በዓለም ላሉ ሰዎች ሁሉ ሊሰጥ የሚችል ነው። ሮሜ 11፡32 እግዚአብሔር ሁልጊዜ ምሕረቱን ለሌሎች ለመስጠት በአንዳንድ ሰዎች እምቢተኝነት እንደሚጠቀም ለማስተማር ነው። 

ጥያቄ፡- ክርስቶስ ለሰዎች ሁሉ ደኅንነትን ስለ መስጠቱ ያላችሁ አስተያየት ምንድን ነው? 

ክርስቶስ ሰዎች ሁሉ ደኅንነትን እንዲያገኙ የፈቀደ በመሆኑ ተስፋ ቆርጠን ግንኙነታችንን ማቆም የለብንም። እነዚህ ሰዎች ከሃይማኖታቸውና ከእድሜያቸው ሁኔታ ወይም አስቀድመው ክርስቶስን ባለመቀበላቸው ወደ እርሱ ሊመጡ አልቻሉ ይሆናል። ሆኖም ክርስቶስ ለእነርሱ ሲል ሞቶአል። ደግሞም እግዚአብሔር ደኅንነት ሊሰጣቸው ተዘጋጅቷል። ስለዚህ የወንጌልን ቃል በታማኝነት ልንነግራቸውና በድፍረት ልንቀርባቸው ይገባል።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version