በትናንትናው ዕለት ከክርስቶስ ጋር መተባበር ምን ማለት እንደሆነ ማጥናት ጀምረን ነበር። በጥናታችን ወቅትም ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት ከክርስቶስ ጋር ሞተን የተነሣን፥ እግዚአብሔር ክርስቶስን በሚመለከትበት ዓይኑ እንደሚያየን፥ ክርስቶስ በውስጣችን እንደሚኖርና እኛም በምድር ላይ የሚታየው የክርስቶስ አካል መሆናችንን አስተውለናል። ይህ ከክርስቶስ ጋር የምንተባበርበት እያንዳንዱ ሁኔታ አስደናቂ በረከት ነው። ሆኖም አማኞች ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ኅብረት የተነሣ የሚመጡ ብዙ የተትረፈረፉ በረከቶችም አሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ እያንዳንዱ የደኅንነት በረከት ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት ጋር የሚዛመድበት ሁኔታ አለ። ዛሬ የምናጠናው ክፍል ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት ስለምናገኛቸው በረከቶች ይሆናል።
1. ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት ምክንያት እግዚአብሔር ማንኛውንም መንፈሳዊ በረከት ይሰጠናል።
ጥያቄ፡– ኤፌ 1፡3 አንብብ። በክርስቶስ ኢየሱስ የተባረክነው በምንድን ነው?
ኤፌ. 1፡3-14 ያለው ክፍል እግዚአብሔር ወደ እርሱ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚመጡት ሁሉ ስለሚያደርገው ተግባር በሚገባ ገልኦ የሚያስረዳ ነው። ስለዚህ ኤፌ. 1፡3 የመላው አንቀጽ ማጠቃለያ አሳብ ነው፦ ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት የተነሣ እግዚአብሔር ስለ ሰጠን በረከት ሁሉ ሐዋርያው ጳውሎስ አምላኩን ያወድሳል። ስለሆነም እኛ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት የሌለን ቢሆን ኖሮ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ በረከቶችን ማግኘት አንችልም ነበር። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለን ስለሆንን ልናስበው የምንችለውን በረከት ሁሉ የማግኘት ዕድል አለን። ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን እግዚአብሔር መረጠን (ቁ 4)። ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን እግዚአብሔር ልጆቹ አድርጎ ተቀበለን (ቁጥር 5)። እንደዚሁም ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት እግዚአብሔር ተቤዥን (ቁ 7)። ደግሞም ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ሰጠን (ቁ 13)። ያገኘናቸውን በረከቶች ሁሉ ልናገኝ የቻልነው ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት የተነሣ ነው።
ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት ምክንያት ያገኘናቸውና አዲስ ኪዳን የሚጠቅላቸው ሌሎች አንዳንድ በረከቶች ምንድን ናቸው?
1.1 ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላላን እግዚአብሔር ይቅር ይለናል፥ ደግሞም በበደላችን እንደማንቀጣም ተስፋ ይሰጠናል።
ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡1 አንብብ። በክርስቶስ ኢየሱስ ስላሉት እውነተኛው ነገር ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- ኤፌ 4፡32 አንብብ። እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ በመሆናችን እግዚአብሔር ምን አደረገልን?
ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለን በመሆናችን እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ከማለቱም በላይ በኃጢአታችን ምክንያት በደለኞች እንደማንባል አስታውቋል። ኤፌ. 4፡32 እኛ በክርስቶስ በመሆናችን እግዚአብሔር ይቅር ብሎናል ይላል። በሮሜ 8፡1 ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው ኩነኔ የለባቸውም ይላል። ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለን በመሆናችንና ከእርሱ ጋር አንድ ስለሆንን፥ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን አይቆጥርብንም። ደግሞም ከኃጢአታችን የተነሣ በደለኞች ሆነን እንደማንታይ እግዚአብሔር ራሱ ተስፋ ሰጥቷል። እኛ በደለኞች ሆነን ስላለመታየታችንና በዚህም ምክንያት ቅጣት እንደማይደርስብን የሚያውጀውን ክፍል በሚመጣው ሳምንት የጽድቅ በረክት የሚለውን በምናጠናበት ጊዜ እንማረዋለን፡፡
1.2 ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው ሁሉ የእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ አካል ከመሆናቸውም በላይ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠበት የሰማይ ክብር ወራሾች ይሆናሉ።
ጥያቄ- ኤፌ 2፡13፥ 19 አንብብ። አሕዛብ ከክርስቶስ ጋር በመተባበራቸው ምን አገኙ?
ጥያቄ፡– ኤፌ 3፡6 አንብብ። አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ» በመሆናቸው ከእስራኤላውያን ጋር ምንን ይካፈላሉ?
ጥያቄ፦ ገላ. 3፡28-29 አንብብ። የክርስቶስ የራሱ ከሆኑ፣ እነዚህ የእግዚአብሔር ተስፋ መራሽ የሆኑ ሕዝብ ሁሉ እንዴት ያሉ ናቸው?
ጥያቄ፦ ሮሜ 8፡17 አንብብ። ከክርስቶስ ጋር ወራሾች በመሆናችን ምን የተረጋገጠልን ነገር አለ?
ጥያቄ፦ ቆላ 1፡27 አንብብ። ክርስቶስ በውስጣቸው ያለ ምን አላቸው?
ጥያቄ፦ 1ኛ ጴጥ. 5፡10 አንብብ። በክርስቶስ ወደ ምን ተጠርተናል?
በብሉይ ኪዳን ዘመን፥ የእግዚአብሔር ምርጥ ሕዝብ እስራኤላውያን ነበሩ፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎችን የሰጣቸው ሲሆን፥ ብዙ የተለዩ ተስፋም ገብቶላቸው ነበር። ነገር ግን አሁን፣ በክርስቶስ አማካይነት ወደ እግዚአብሔር የሚመጡ ሁሉ የእግዚአብሔር የራሱ ሕዝብ አካል የመሆን መብት አላቸው። አሕዛብ በኢየሩሳሌም ባለው መቅደላ ወደ ቅድስቱ መግባት አይፈቀድላቸውም ነበር። ለዚህ ምክንያቱ አይሁዳውያን አሕዛብን ርኩሶችና ከእግዚአብሔር የተለዩ ሰዎች አድርገው ይጥሯቸው ስለነበረ ነው። ነገር ግን በኤፌ 2፡13 እና 19 ውስጥ እነዚሁ አሕዛብ ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ኅብረት ምክንያት አሁን የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል መሆናቸውን ራሱ እግዚአብሔር ይናገራል። በክርስቶስ ደም አማካይነት ወደ እግዚአብሔር ቀርበዋል፤ ከዚህም የተነሣ በእዚአብሐር ሕዝብ መካከል ከእስራኤላውያን ጋር አቻ ዜጎችም ሆነዋል። ኤፌ 3፡6 ከእስራኤላውያን ጋር እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሰጣቸው ተስፋዎች ሁሉ ወራሽ ሆነዋል ይላል። ገላ. 3፡28-29 ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ አንድ ሆነዋል፤ ስለዚህ በአይሁዳዊና በአሕዛብ፥ በአገልጋይና በጌታ፥ በወንድና በሴት ልዩነት የለም ይላል። ሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝብ አካል ናቸው። ሁሉም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ውርስ ተካፋዮች ናቸው።
ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው የሚካፈሉት እጅግ በጣም የላቀው ተስፋ የሰማይ ክብር ተስፋ ነው። ቆላ. 1:27 ላይ የተጻፈው ቃል ባለፉት ዘመናት ተሰውሮ የነበረውን ምሥጢር እግዚአብሔር ገለጠው ይላል። ይህም ክርስቶስ አሁን ከአሕዛብ ጋር ኅብረት ስላለውና በእነርሱም ውስጥ ስለሚያድር እነርሱም ሳይቀሩ የሰማያዊ ክብር የተስፋ ቃል ተጠቃሚዎች ናቸው። በሮማ 8፡17 ከክርስቶስ ጋር ወራሾች የሆኑ ሁሉ የክብሩ ተካፋዮች ለመሆናቸው እርግጠኞች ናቸው ይላል። በ1ኛ ጴጥ. 5፡10 እግዚአብሔር የክርስቶስ የሆኑትን ወደ ዘላለማዊ ክብሩ ጠርቷቸዋል ይላል። ከክርስቶስ ጋር የሚኖር ኅብረት ከእግዚአብሔር ከራሱ ሕዝብ ተገልለው የነበሩትን የራሱ የሰማያዊ ልዩ ሕዝብና የክብሩ ተስፋ ወራሾች ያደርጋቸዋል።
1.3 ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸውን እግዚአብሔር ከሕግ ነፃ ያደርጋቸዋል።
ጥያቄ፡- ገላ. 2፡4 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚጠቅሰው ስለ የትኛው ዓይነት ነጻነት ነው?
ጥያቄ፡- ገላ 5፡6 አንብብ። «በክርስቶስ ዘንድ» ዋጋ ቢስ የሆነ ነገር ምንድን ነው?
ሦስተኛውና ከክርስቶስ ጋር በመተባበር የሚገኘው በረከት፥ ከብሉይ ኪዳን የሕገ ሥነ ሥርዓት ነፃ መውጣት ነው። በገላትያ መልእክት ውስጥ እንደምናነበው ሐሰተኞች መምህራን ወደ ክርስቲያኖች ዘንድ መጥተው ስለ ደኅንነታቸው በክርስቶስ ብቻ ማመን በቂ እንዳልሆነ ይነግሩአቸው ነበር። ክርስቲያናዊ እምነታቸው የተሟላ ይሆን ዘንድ፥ መገረዝና በሙሴ ሕግ ውስጥ የተጠቀሱትን ሥነ ሥርዓቶች መፈጸም እንዳለባቸው ነገሩዋቸው። ጳውሎስ ግን ይህን የሐሰት ትምህርት አጥብቆ ተቃወመ። በዚህ ምክንያት ሙሉውን የገላትያ መልእክት የጻፈው በዳኑ ጊዜ ከክርስቶስ ጋር የመተባበራቸው እንደኛው ውጤት ከሕግ ሥርዓት ነፃ እንዳደረጋቸው ለማሳሰብ ነበር፡ በገላ. 2፡4 ውስጥ ጳውሎስ ሲያስነዝባቸው አንዳንድ ሐሰተኛ ወንድሞች ከክርስቶስ ጋር ካላቸው ኅብረት የተነሣ የተቀዳጁትን ነጻነት ስላዩ መልሰው የሙሴ ሕግ ተገዢዎች ሊያደርጉአቸው እንደ ፈለጉ ነገራቸው። ጳውሎስ በገላ. 5፡6 ውስጥ ሲናገር፣ የግርዛት ሥነ ሥርዓት ተካፋዮችም ይሆኑ ወይም ሳይገረዙ ይቅሩ ይህ ምንም እንደማያጎድልባቸውና የሚጠቅመው በውጪአዊ የፍቅር ድርጊት አማካይነት ራሱን የሚገልጽ እምነት መያዝ መሆኑን ያስገነዝባቸዋል። በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር የተባበሩ ስለሆኑ ደኅንነታቸውን ለማሟላት ወይም ራሳቸውን የበለጠ ቅዱላን ለማድረግ እንደ እርዛት ያለ ተግባር መፈጸም አይኖርባቸውም። በዚህ ፈንታ በእግዚአብሔር በማመንና ሌሎችን በመውደድ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው በየጊዜው ማደግ ይጠበቅባቸዋል። በአንጻሩ፣ ክርስቲያኖች ለአይሁድ ሕግ ከመታዘዝ ነፃ ናቸው ሊባል እንደ ፈለጉት ይኖራሉ ማለትም አይደለም። ነጻነታችንን በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ኃይል መሠረት በመጠቀምና እርስ በርሳችን አንዱ ሌላውን በማገልገል በተግባር ልንገልጠው ይገባል (ገላ. 5፡13 እና 16)።
1.4 ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ላላቸው፥ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ግንዛቤን ይለግሳቸዋል።
ጥያቄ፡- 2ኛ ቆሮ. 3፡14 አንብብ። በክርስቶስ የተወገደው ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡4-5 አንብብ። የቆሮንቶስ ሰዎች በክርስቶስ በመሆናቸው ምን አገኙ?
አማኞች ከክርስቶስ ጋር በሚተባበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር ቀድሞ ያልነበራቸውን መንፈሳዊ ግንዛቤና የቃሉን እውቀት ይሰጣቸዋል። በ2ኛ ቆሮ. 3፡12-18 ውስጥ የአይሁድ ሕዝብ በምን ምክንያት ስለ ክርስቶስ እውነተኛውን ነገር እንዳልተገነዘቡ ጳውሎስ ሲገልጽ ሙሴን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል። እንደዚሁም ጳውሎስ በመቅጠል ሙሌ ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ ክብሩን ካየ በኋላ የእግዚአብሔር ክብር መንጸባረቅ ከፊቱ በሚወጣበት ጊዜ እስራኤላውያን እንዳያዩ ፊቱን ሸፍኖ እንደ ነበረ ለአንባቢዎቹ ያስታውሳቸዋል። ከዚያ ወዲህም ቢሆን የብሉይ ኪዳንን በሚያነቡበት ጊዜ የፊታቸው መሸፈኛ አይለያቸውም ነበር ይላል። አይሁዶች ብሉይ ኪዳን ሲነበብ በሚያዳምጡበት ጊዜ፥ ክብሩ ከፊል፣ ያልተሟላና እየደበዘዘ መሆኑ አይገባቸውም ነበር። አርጌው ኪዳን በክርስቶስ መፈጸም እንደሚኖርበት አይገባቸውም ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ አንድ ሰው ከክርስቶስ ጋር በመተባበርበት ጊዜ መሸፈኛው ይወገዳል ይላል። መሸፈኛውም በሚወገድለት ጊዜ የተወገደለቱ ሰው ወዲያውኑ የአሮጌው ኪዳንን እውነት ሊነዘብ ይችላል። ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ፍጻሜ መሆኑን ያስተውላል። ከክርስቶስ ጋር የሚኖረው ኅብረት የእግዚአብሔርን ቃል ጥልቀት የመገንዘብን ውስጣዊ እውቀት ይሰጣል። ጳውሎስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ቃል በ1ኛ ቆሮ. 1፡4-5 ውስጥ ይናገራል። እግዚአብሔር በጸጋው የቆርንቶስን ሰዎች ከክርስቶስ ጋር አስተባበራቸውና እበለፀጋቸው። እርሱ እንዴት አበለፀጋቸው? ጳውሎስ እንደሚናገረው እነርሱ የተቀበሉት ልዩ ሀብት «ንግግርና ዕውቀት» ነበር። እግዚአብሔር የቃሉን እውነት እንዲገነዘቡ ልዩ መንፈሳዊ ዕውቀትን የሰጣቸው ሲሆን፥ እንደዚሁም ይህን እውቀት ከሌሎች ጋር የመካፈል ልዩ ችሎታም ለግሶአቸዋል። እግዚአብሔር እነዚህን የበለፀጉ ስጦታዎችን የቸራቸው ከክርስቶስ ጋር በነበራቸው ኅብረት ምከንያት ነበር።
1.5 እግዚአብሔር ይቀድሳል፥ ደግሞም ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸውን መውደዱን አያቋርጥም።
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡2 አንብብ። በክርስቶስ የሆኑት ምንን አገኙ?
ጥያቄ፡- ሮሜ 8፡39 አንብብ። በክርስቶስ ካለን ፍቅር ሊለየን የሚችል ምን አለ?
ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ላላቸው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብዙ ሌሎች በረከታች የተዘረዘሩ ቢኖሩም፥ እዚህ ላይ ሁለቱን ብቻ ተጨማሪ አድርገን እናቀርባለን። የመጀመሪያው፥ በ1ኛ ቆሮ. 1፡2 ውስጥ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያላቸው «የተቀደሱ» ናቸው ይላል። ከከር ስቶስ ጋር በምንተባበርበት ጊዜ፣ የእርሱ የግሉ ሆነን እንለያለን፣ ተለይተንም የእርሱን ቅድስና እንላበሳለን። በሚመጣው ሳምንት ትምህርታችን የደኅንነት በረከት ስለሆነው ቅድስና በይበልጥ እንወያያለን። በሁለተኛ ደረጃ ፥ እኛ በክርስቶስ የሆንን ሁላችንን ምንም ፍጥረት እርሱ ከሰጠን ፍቅር ሊለየን እንደማይችል እግዚአብሔር በተስፋው ቃል ያረጋግጥልናል። አባት ልጁን ንጹሕ፥ ጥልቅና ፍጹም በሆነ የሰው ልጅ ጨርሶ በማይገነዘበው ፍቅር ይወዳል። እኛም ከክርስቶስ ጋር በምንተባበርበት ጊዜ፣ አባት ልጁን በወደደበት አኳኋን እኛንም ይወደናል። ይህ ፍቅሩም ታላቅ ከመሆኑ የተነሣ ማንም ከዚህ ፍቅሩ ከቶ ሊለየን አይችልም። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር መተባበር ማለት እግዚአብሔር እኛን መውደዱን አያቋርጥም ማለት ነው።
2. ከክርስቶስ ጋር በሚኖረን ኅብረት ሳቢያ ስለምናገኛቸው በረክቶች ስሜታችንና አስተሳሰባችን እንዴት መሆን ይኖርበታል?
ከክርስቶስ ጋር ኅብረት በማድረጋችን ያገኘነውን የብልጽግና ስጦታ በትናንትናውና በዛሬው ትምህርታችን ላይ ለመመልከት ችለናል። በዚህ ላይ ያለን አስተሳሰብም ሆነ ስሜት ምንድን ነው? አዲስ ኪዳን ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን ማድረግ የሚገቡንን አንዳንድ ልዩ ነገሮች ይነግረናል።
2.1 ከክርስቶስ ጋር የተባበርን በመሆናችን፣ አእምሮአችን በእርሱ መሞላት አለበት፥ ደግሞም ከእርሱ ዘንድ ብርታትንና ኃይል ማግኘት ይኖርብናል።
ጥያቄ፡- ዮሐ 15፡4-5 አንብብ። ሀ) የወይኑ ቀንድ ማን ነው? ደግሞስ ቅርንጣፎቹ እነማን ናቸው? ለ) ቅርንጫፎቹ ፍሬ እንዲያፈሩ ምን ማድረ ይኖርባቸዋል? ሐ) ኢየሱስ በዚህ ክፍል ውስጥ የሚያስተምረንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ እኛ ክርስቲያኖች ምን ማድረ ይኖርብናል?
ጥያቄ፡- ሮሜ 13፡14 እንብብ። ሀ) ልንለብላቸው የሚገቡን ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) ጳውሎስ ይህን የተናገረው ምን ለማለት ፈልጎ ነው?
ጥያቄ፡– ኤፌ 6፡10 አንብብ። ክርስቲያኖች የሰይጣንን ውጊያ መቋቋም እንዲችሉ ኃይልና ብርታትን ከየት ያገኛሉ?
ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን ልናደርገው የሚገባን የመጀመሪያው ተግባር ከክርስቶስ በምናገኘው ብርታትና ኃይል ታግዘን አዲስ ሕይወትን መኖር ነው። በዮሐ 15 ውስጥ ኢየሱስ እኛ ከእርሱ ጋር ባለን ኅብረት እንዴት መኖር እንደሚገባን ለማመልከት የወይንን ግንድና የቅርንጫፎቹን ምሳሌ ተጠቅሞአል። ቅርንጫፎች በወይን ግንድ ላይ እንደሚኖሩ ሁሉ፥ እኛም ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዳለን ይናገራል። ነገር ግን ፍሬ ለማፍራት ብንሻ፣ በእውነት ከክርስቶስ ጋር እንደ ተባበሩ ሰዎች እንድንኖር ካስፈለገ፣ ከእርሱ ጋር ጸንተን መገኘት አለብን። ለዚህም ኃይልና ብርታትን ከእርሱ ዘንድ ማግኘት ይገባናል። አእምሮአችንንም በቃሉ መሙላት ይገባናል። በእርሱ ፊት በጸሎትና የእግዚአብሔርን ቃል በማሰላሰል ቆይታ ማድረግ ይገባናል። ጳውሎስም በሮሜ 13፡14 ውስጥ በጣም ተመሳሳይ ሁኔታን ይነግረናል። በሮሜ 13፡12-13 ውስጥ ሲናገር የጨለማን ሥራ አውልቀን ጥለን እንደ ብርሃን ሰዎች መኖር እንዳለብን ያሳስበናል። ወደ ክርስቶስ ከመምጣታችን በፊት በሕይወታችን ውስጥ አብርን የቆየውን የጨለማ ሥራ እንዴት አውልቀን በመባል ከለማ ሥራ እንላቀቃለን? በቁጥር 14 ውስጥ ሐዋርያው እንዲህ ይላል፣ «ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት።» በገላ 3፡26-27 እንደተመለከትነው፥ ማንኛውም በክርስቶስ ያመነ ሰው ጌታ ኢየሱስን ለብሶታል። እግዚአብሔር በሚመለከተን ጊዜ ወደ እርሱ ከመምጣታችን በፊት እንደ ነበርንበት ሁኔታ አያየንም። እግዚአብሔር በእኛ ምትክ ክርስቶስን ያያል። በዚሁ በሮሜ 13፡14 ውስጥ ጳውሎስ ሲናገረን፥ ራሳችንን ጌታ ኢየሱስን መልበስ እንዳለብን ያሳስበናል። እንዲህ ማለት ምን ማለት ነው? ጳውሎስ ይህን ሲያብራራ፥ ራሳችንን በጌታ ኢየሱስ ማልበስ ማለት ስለ ሥጋ ምኞትና ደስታ አለማሰብ መሆኑን ይናገራል። አእምሮአችንን በኃጢአት አሳብና ምኞት በመሙላት ፈንታ፣ እግዚአብሔር ለእኛ ሕይወት ባለው መልካም አስተሳሰብና ዕቅድ ልንሞላው ያስፈልገናል። ይህ ሲሆን በየዕለቱ የኢየሱስን መልካም አስተሳሰብ ልንላበስ እንችላለን። በኤፈ. 6፡10 ውስጥ ጳውሎስ፣ ሰይጣንን ማሸነፍ እንድንችል በጌታና በኃይሉ ችሎት መበርታት እንዳለብን ያሳስበናል። ከሰይጣን ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ፣ በራሳችን ኃይል በመመካት ፈንታ፥ የጌታን ኃይል መሻት ይኖርብናል። ምክንያቱም ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት የእርሱን ስም ስንጠራና እርሱ በሚሰጠን መንፈሳዊ ኃይል ስንጠቀም፣ ያን ጊዜ የሰይጣንን ፈተና ለማሸነፍ መንፈሳዊ ኃይል ማግኘት እንችላለን።
2.2 ከክርስቶስ ጋር የተባበርን ስለሆንን፥ ለወንጌል እውነትና አስቀድሞ ለተቀበልነው ኃይል ታማኞች ሆነን መኖር አለብን።
ጥያቄ፡- ቆላ. 2፡6-7 አንብብ፡ ሀ) በክርስቶስ* ምን ማድረጎ ይጠበቅብናል (ቁ 6)? ለ) ይህ ማለት ምን ማለት ነው (ቁጥር (ቁ 7)?
በቆላስይስ ለነበሩ አማኞች ሐሰተኞች የሆኑ መምህራን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እውነትና ጥበብ ይልቅ የበለጠ ጥልቅነት ያለው እውነትና ጥበብ እንዳለ ይነግሩዋቸው ነበር። እንደዚሁም እነዚህ ሐሰተኛ መምህራን ለምእመናኑ ከክርስተስ በላይ የሆኑ ኃይሎች አሉ በማለትም ይነግሩዋቸው ነበር። ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በመላው ለእነዚህ ሐሰተኛ መምህራን መልስ ሰጥቷል። በመልሱም ላይ የክርስቶስንና የወንጌሉን ከሁሉ በላይነት ከፍ አድርጎ በማወጅ አቅርቧል። በቆላ. 2፡6-7 ውስጥ አማኞቹ በጌታ ኢየሱስ እንዴት ጸንተው መኖር እንዳለባቸው ጽፎላቸዋል። የቆላስይስ ምእመናን በመጀመሪያ ክርስቶስን በተቀበሉበት ሁኔታ አካሄዳቸውን በማድረግ መቀጠል እንደሚኖርባቸው ተነግሮአቸዋል። ልክ ቀድሞ በተቀበሉት የወንጌል እውነትና ኃይል መሠረት መኖር ይጠበቅባቸው ነበር። በምንም ዓይነት ለክርስቶስ ያደረጉትን መሰጠት በሌላ መተካት አይኖርባቸውም።
ጥያቄ በሕይወታችሁ ውስጥ የተለየ የምን ኃይል ወይም ጥበብ ለመከተል ተረትናችኋል? እግዚአብሔር “ክርስቶስ ጋር ባላችሁ ኅብረት” በመቀጠል እንዴት እንድትኖሩ ይፈልጋል?
አማኞች ዛሬ ዓለም የምታቀርበውን ኃይልና ጥበብ ለመካተል ይፈተናሉ። አንዳንድ ጊዜም ወደ እውነት መዳረሻው ትምህርት ነው ተብሉ ይነገረናል። በሌላ ጊዜም ወደ እውነት የመድረሻው መንገድ እንደ ማርክሲዝም ያሉ የፖለቲካ ፍልስፍናን መከተል ነው የሚል ሁኔታ እንሰማለን። እንደዚሁም በአንዳንድ ወቅት ወደ ሥልጣን የሚደረሰው በፖለቲካ ኃይል ነው ይሉናል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ወደ ኃይል መድረሻው መንገድ መጸለይ ወይም ለሌሎች አማላጆች ወይም መንፈሳዊ ኃይላት ምጽዋት መስጠት ነው ሲሉ እንሰማለን። አንዳንድ ጊዜም ወደ ኃይልና እውነት የመድረሻው መንገድ በሌሎች ሃይማኖቶች መሆኑን ይነግሩናል። በሌላ ጊዜም ወደ እውነት የሚደረሰው ምንም ምክንያታዊና ሳይንሳዊ መሠረት ሳይኖረው ስለ ሃይማኖት የሚነገረውን መተውና ምንም ዓይነት ሃይማኖት አለመከተል ነው ይላሉ። ሌሎች ደግም ወደ ኃይል የሚደረሰውና ተሰሚነት የሚገኘው በሀብት ነው በማለት ይነግሩናል። ከክርስቶስ ጋር ኅብረትን የመሠረቱ አማኞች በመጀመሪያ በተቀበሉት የወንጌል እውነትና ኃይል ላይ ያላቸውን እምነት በማጠንከር ከጌታ ጋር ተቀራርበው መኖር አለባቸው።
2.3 ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ስላለን ደስተኞችና አመስጋኞች ልንሆንና ክርስቶስ ያደረገልንን ሁሉ በይፋ ልናሳውቅ ይገባናል።
ጥያቄ፡- ፊልጵ. 3፡1፤ 4፡4 አንብብ። በጌታ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
ጥያቄ፡- 1ኛ ተሰ. 5፡16-18 አንብብ። በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት የእግዚአብሔር ፈቃድ ምንድን ነው?
ጥያቄ፡- 1ኛ ቆሮ. 1፡30-31 አንብብ። እኛ በምን እንመካለን?
በሕይወት ውስጥ ትካዜና ተስፋ መቁረጥ ያለ ነገር ነው። ነገር ግን እኛ ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ያለን ብዙ ደስ የምንሰኝባቸውና ምስጋናም የምናቀርብባቸው ምክንያቶች አሉን። ቆላ. 2፡7 ከክርስቶስ ጋር ካለን ኅብረት የተነሣ ላገኘናቸው በረከቶች «በብዙ አመስኑ» በማለት ያሳስበናል። 1ኛ ተሰ. 5፡16-18 ያለው ክፍልም፥ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ከሆኑት የሚፈልገው በሁሉ ነገር እርሱን ማመስገንና ደስ መሰኘት መሆኑን ይናገራል። ፊልጵ. 3፡1፤ 4፡4 «በጌታ ደስ ይበላችሁ» ሲል ያዝዛል፤ ደስታችን ሁሉ የሚመጣው በክርስቶስ ከመሆናችን የተነሣ ነው። ከክርስቶስ ጋር ባለን ኅብረት ባገኘናቸው በረከቶች ውስጣዊ ደስታ መደሰት ብቻ አይበቃም። በ1ኛ ቆሮ. 180-31 ሐዋርያው ጳውሎስ ሲናገር፥ በእርሱ ከመሆናችን የተነሣ ክርስቶስ ስለ ሰጠንና ስላደረገልን ሁሉ «በጌታ መመካት አለብን። ይላል። ስለዚህ ለሌሎች ስለ ክርስቶስ ማስተጋባት አለብን። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሚደረግ ኅብረት ስለሚገኘው የበረከት ብልጽግና ለሰዎች ሁሉ ማስተጋባት ይጠበቅብናል። ”
ጥያቄ፦ በክርስቶስ በደመሆናችሁ ካገኛችኋቸው በረከተች ውስጥ የትኞቹ በጣም ምስጋና እንድታቀርቡና ደስም እንድትሰኙ አደረጓችሁ? ለ) ለወደፊቱ የሚያሳዝናችሁና ተስፋ የሚያስቆርጣችሁ ሁኔታ በሚያጋጥማችሁ ጊዜ ስለ እነዚህ በረከተች ማሰብ እንዴት ሊረዳችሁ ይችላል? ሐህ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለለ ኢየሱስና እርሱም ስለ ሰጣችሁ በረከት በይፋ ለመናገር ለመቼ ዕቅዳችኋል?
ባሳለፍናቸው ሁለት ቀናት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር በተባበር ስለሚገኙ ብዙ በረከቶች ሰምተናል። አዲስ ሕይወትም አግኝተናል። እግዚአብሔር በሚመለከተንም ጊዜ የክርስቶስን ጽድቅ ለብሰን ያየናል። ክርስቶስም በእርቅጥ በእኛ ውስጥ ለመኖር መጥቷል። የኃጢአት ይቅርታም አግኝተናል። ስለዚህ ተስፋ የተሰጠበት የሰማይ ክብርም ወራሾች ነን። ከሕ• ሥነ ሥርዓት ነፃ አውጥተ የበለጸገ መንፈሳዊ የውስጥ ግንዛቤን ሰጥቶናል። እርሱ ቅዱሳን ያደርገናል፤ እኛንም ከመውደድ አይቆጠብም። በመንፈሳችን ስናዝንና ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያ ሊሰማን፣ ከእርሱ ጋር ባለን ኅብረት ምክንያት ላላገኘናቸው የበለጸጉ በረከቶች ማሰብ አለን። እግዚአብሔር ስላደረገልን ሁሉ ደስ ልንሰኝና ልናመሰግነው ይገባናል። ነገር ግን የውስጣዊ ደስታ ለማመድ ብቻ ሳይሆን፣ በጎረቤታችን ካሉ ወዳጆቻችን፥ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችንና ከሥራ ባልደረቦቻችን፥ እንዲሁም ከእድርና ከእቁብ አባሎቻችን፥ ከቅርብ ቤተሰቦቻችንና ወላጆቻችን ጋር ስለ እነዚህ በረከቶች መወያየት ይገባናል። ጌታ ከእርሱ ጋር እንድንተባበር በማድረግ ስለ ፈጸመልን ተግባር ሁሉ ለሌሎች በይፋ በምናስታውቅበት ጊዜ ለጌታ ያለንን ምስጋናና ደስታ አብረን እንግለጽ።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
