በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች (FAQs)
አንዳንድ ክርስቲያኖች ኃጢአትን የምር መጥፎ የሆኑና እምብዛም መጥፎ ያይደሉ በማለት ይከፋፍሏቸዋል። በዚሁ ሁኔታ አንዳንዶቹ ኃጢአቶች የእግዚአብሔር ካባድ ቅጣት እንደሚያስፈልጋቸው ሌች ደግሞ ይህን ያህል የማያስቀጡ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም፥ አንዳንደ ኃጢአቶች ደኅንነትን የሚያሳጡዋቸው ሆነው ሲታዩዋቸው፥ ሌሎች የኃጢአት ዓይነቶች ደግሞ ደኅንነትን የማያሳጡዋቸው መስለዉ ይታዩዋቸዋል። ይሁንና አንዳንድ ኃጢአቶች ከሌሎቹ ይልቅ የባሱ ናቸው?
2.1 ኃጢአቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል በደለኞች ያደርጉናል።
ጥያቄ፡– ገላ 3፡10 እና ያዕ. 2፡10 እንብብ። ከትእዛዛቱ መካከል አንዱን እንኳን በማይታዘዙት ላይ ምን ደረሰባቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እኩል በደለኞች እንደሚያደርጉን ያስተምረናል። አንድ ኃጢአት ምንም ያህል ትንሽ ቢሆንም የኃጢአትን ቅጣት ያመጣብናል። ገላ. 3፡10 ከሕጎች አንዱን ያፈረሰ ሰው የተረገመ ነው ይላል። ያዕ. 2፡10 ደግሞ ከሕግ ትእዛዛት አንዲቱን ያጎደለ መላውን ያፈረሰ በደለኛ ሆኖ ይቆጠራል ይላል። በዚህ አኳኋን ኃጢአት ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ያደርገናል።
2.2 አንዳንድ ኃጢአቶች ከሌሎቹ ይልቅ ከእግዚአብሔርና ከሌሎችም ሰዎች ጋር ያሉንን ግንኙነቶች በበለጠ ይጎዱዋቸዋል።
ጥያቄ፡- ሕዝ 8፡6 አንብብ። እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ምን ታያለህ አለው?
ጥያቄ፡- ዮሐ 19፡11 አንብብ። ኢየሱስ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ አሳልፈው ስለ ሰጡት ምን አለ?
ጥያቄ፡- ማቴ. 23፡23 አንብብ። ኢየሱስ ፍርድን፥ ምሕረትን እና ታማኝነትን ምን ብሎ ጠራ?
ጥያቄ፡- ሉቃስ 10፡10 አንብብ። የትኞቹ ከተሞች የከፋ ቅጣትን ይቀበላሉ? ለምን?
ጥያቄ፡- ሉቃስ 12፡42-48 አንብብ። ሀ) የጌታውን ፈቃድ እያወቀ በማይፈጽም አገልጋይ ላይ ምን ይደርስበታል? ለ) የጌታውን ፈቃድ በሚያውቀውና በሚያደርገው እገልጋይ ላይላ ምን ይደርስበታል?
ጥያቄ፡- ያዕ. 3፡1 አንብብ። የእግዚአብሔርን ቃል በሚያስተምሩት ላይ ምን ይደርሳል?
ኃጢአቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በደለኛች የሚያደርጉን ሲሆን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስንመለከት አንዳንድ ኃጢአቶች ከሌሎቹ ብሰው የሚታዩበት ሁኔታ ያለ ይመስላል። እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል፥ ካየው የበለጠ እጅግ አስነዋሪ የሆነ ነገር ገና እንደሚያይ ነግሮታል (ሕዝ. 8፡6)። ኢየሱስም ለጴንጤናዊው ጲላጦስ አሳልፈው ስለ ሰጡት ሲናገር፥ አሳልፈው የሰጡት ከጲላጦስ የባለ ኃጢአት እንደሚያደርጉ አስጠንቅቆአቸዋል (ዮሐ 19፡1)። እንዲሁም፥ ከሕግ ውስጥ ፍርድ፥ ምሕረትና ታማኝነት ዋና ቁም ነገሮች ናቸው ብሏል (ማቴ. 23፡23)። በዚህም ኢየሱስ፥ አንዳንድ ኃጢአቶችን ከሌሎች የበለጠ የሚከብዱ መሆናቸውን ሊያስገነዝበን አንዳንዶቹ የሕግ ትእዛዛትም ከሌሎቹ የተለዩ ናቸው። በሉቃስ 10፡10-5 ውስጥ እንደተጻፈው የቅፍርናሆምንና የቤተ ሳይዳን ከተሞች ከሰዶም፥ ከጢሮስና ከሊዶን ከተሞች የበለጠ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ኢየሱስ ፈርዶባቸዋል። የበለጠ ቅጣትን የሚቀበሉበትም ምክንያት ከሌሎቹ ከተሞች ይልቅ እነዚህኞቹ በኢየሱስና በሠራቸው ተአምራት ውስጥ እግዚአብሔርን በላቀ መገለጥ ስላዩት ነው። ከእግዚአብሔር ታላቅ መገለጥ ሲመጣ እያዩ ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች በአነስተኛ መገለጥ ውስጥ ሆነው ኃጢአት ከሚሠሩት የበለጠ በደል ይፈጽማሉ። በሉቃስ 12፡42-48 ውስጥ ኢየሱስ በምሳሌ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያወቁ የማያደርጉት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካለማወቃቸው የተነሣ ከማያደርጉት የበለጠ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ገልጾአል። እያወቁ በድፍረት ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎች ምንም እንኳን ኃጢአት እንደ ፈጸሙ ቢገነዘቡም የባሰ ኃጢአት ያደርጋሉ።
እንደዚሁም አንዳንድ ኃጢአቶች የእግዚአብሔርን ስም የሚያጎድፉ ወይም ራሳችንና ሌሎች አማኞችን ጭምር የሚጎዱ ከሆኑ ከሌሎች ይልቅ ክብደት የሚሰጣቸው ወይም የባሱ ሆነው የሚቆጠሩ ይመስላሉ።
ጥያቄ፡- አንዳንድ ኃጢአቶች በእግዚአብሔር፥ በራሳችንና በሌሎች ሰዎች ላይ ትልቅ ጉዳትን እንዴት እንደሚያመጡ ምሳሌ ጠቅሳችሁ ጻፉ።
አንዳንድ የኃጢአት ዓይነቶች ከሌሎች በበለጠ እግዚአብሔርንና ስሙን፥ እኛንና ሌሎችን ይጎዳሉ። ለምሳሌ ያህል፥ አንድ ሰው የጎረቤቱን መኪና ቢመኝ የእርሱ ያልሆነውን ተመኝቷል እና በደለኛ ይሆናል። ነገር ግን ያንን መኪና ቢሰርቅ የባሰ ኃጢአት ይሠራል። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ስም ላይ ትልቁ ሐፍረትን በጎረቤቱም ላይ ጉዳትን ያደርሳልና ነው። እንዲሁም አንድ ሰው ሚስቱ ያልሆነችውን ሴት ለግብረ ሥጋ ቢመኛት፥ ኃጢአት ስለሚሆንበት በእግዚአብሔር ዘንድ በደለኛ ይሆናል። ነገር ግን ከሴትዮዋ ጋር የተረጋገጠ ግብረ ሥጋ ግንኙነት ቢያደርግ፥ የባሰ ኃጢአት ያደርጋል። ምክንያቱም እርስዋን አሳስቶ ኃጢአት እንድትሠራ ከማድረጉም በላይ፥ የእግዚአብሔርንም ስም የሚያረክስ ተግባር ፈጽሟልና ነው። አግብቶ ከሆነ ደግሞ ሚስቱን፥ ልጆቹንና ትዳሩን ይጎዳል። ሴትዮዋም ያገባች ከሆነች ደግሞ ባለቤትዋን፣ ልጆቿንና ጋብቻዋን ትጎዳለች። እርሱም ሆነ ሴትዮዋ ሁለቱም ያላገቡ ከሆኑ ይህ ተግባር የወደፊት የጋብቻ ዕድላቸውን ያበላሻል። ጳውሎስ የግብረ ሥጋ ኃጢአት የሰውን አካል የሚያረክስ ከመሆኑም በላይ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን አንድነት የሚያበላሽ መሆኑን ሰፋ አድርጎ አስተምሯል (1ኛ ቆሮ. 6፡15-18)። ስለዚህ አንዳንዶቹ ኃጢአቶች የእግዚአብሔርን ስም፥ ኃጢአት የሚሠራውን ሰውና ሌሎች ሰዎችንም ስለሚጎዱ ከሌሎች ኃጢአቶች የባሱ ናቸው።
በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር በተለይ ክርስቲያን መሪዎችን በኃጢአታቸው ይጠይቃቸዋል። ያዕቆብ 3፡1 የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስተምሩ መምህራን የባሰ ፍርድ እንደሚቀበሉ ያስገነዝባል። አንድ ክርስቲያን የሆነ መሪ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ በተለይ የእግዚአብሔር ስም ይሰደባል። ስለዚህ የክርስቲያን መሪ ኃጢአት ከሌላው ክርስቲያን ኃጢአት የበለጠ ነው። ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ያደርገናል። ሁሉም ኃጢአት ደግሞ ይቅር ሊባል ይችላል። አንዳንድ ኃጢአቶችን ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚያስጠይቁ እያወቁ ይፈጽሟቸዋል። ስለሆነም አንዳንዶቹ ኃጢአቶች በእግዚአብሔር፥ በራሳችንና በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳትን ያደርሳሉ። በተለይም በክርስቲያን መሪዎች የሚፈጸሙ ኃጢአቶች በእግዚአብሔር ስም ላይ ኀፍረትን ያመጣሉ። እግዚአብሔር እነዚህን ኃጢአቶች ከሌሎች የባሱ ሆነው ስለሚያያቸው በዚያኑ መጠን የባሰ ቅጣት ይሰጣል።
ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ
