Site icon

ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ገልጾአል ፤ ኢየሱስ ይቅርታን መስጠት ይችላል 

ስለ ኢየሱስ መለኮታዊነት ከሚጠቀሱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መተማመኛ ነጥቦች አንዱና ዋንኛው ኢየሱስ ስለ ራሱ ሲያስብና ሲናገር የነበረውን መመልከት ነው። ኢየሱስ የኖረበት የአይሁዳውያን ሳሕል በአንዱ አምላክ ብቻ አጠንክር የሚያምን ነበር። ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ግርማ ሞገስ ያለው ኃይለኛና ከሰዎችም ሁሉ በላይ መሆኑን አስተምሯል። ይህ እንግዲህ ሰው አምላክ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት የሚሳነው ባህል ነበር። የሆነ ሆኖ ኢየሱስ በዚህ ባሕል ውስጥ ያደገ ቢሆንም እርሱ እግዚአብሔር መሆኑን አስታውቋል። በአንድ አምላክ በሚያምን ባሕል ውስጥ ስለኖረም፥ ኢየሱስ በግልጽ «እኔ አምላክ ነኝ» አላለም። በዚህ ፈንታ እርሱ አምላክ መሆኑን በንግግሩና በሥራው አማካይነት በተዘዋዋሪ መንገድ ይገልጽ ነበር። ስለ አምላክነቱ በአካባቢው ለነበሩ ሰዎች ብዙ ማስረጃዎችን ሰጥቷል። ስለሆነም ኢየሱስ አምላክነቱን በባሕርይውና በተግባሩ ያረጋግጥ ነበር። 

አንዳንድ መናፍቃንና የሃይማኖት ክፍሎች የኢየሱስን አምላክነት ሲክዱም፥ በአንጻሩ ታላቅ ሰው መሆኑን፥ ነቢይነቱንና እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ በላይና በኩር መሆኑን ይናገራሉ። በዛሬው ጥናታችን፥ ኢየሱስ ራሱ አምላክ መሆኑን ሲገልጽ እንመለከታለን። እንግዲህ ኢየሱስን ለማክበር የሚፈልግ ሰው፥ እርሱ ስለ ራሱ ያሳወቀውንና የገለጸውን ሐቅ መቀበል አለበት። ስለዚህ ማንም ሰው በአንድ በኩል ኢየሱስን እያከበረ፥ በሌላ በኩል አምላክነቱን ሊክድ አይችልም።

ኢየሱስ ይቅርታን ሰጠ 

ጥያቄ፡ በማርቆስ ወንጌል 2፡1-22 ያለውን ታሪክ አንብቡ። ሀ) በዚህ ክፍለ ምንባብ ውስጥ ኢየሱስ አምላክነቱን ያረጋገጠባቸው ብዙ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ቢያንስ ሦስት መንገዶችን ፈልጉ፡ ላ) በቁጥር 5 ላይ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን ያውቅ እንደነበር የሚገልጽ ምን ተናገረ? ሐ) በቁጥር 7 ላይ የሕግ መምህራን ጥያቄ | አንሥተዋል። ለዚህ ጥያቄ መልሱ ምን ይመስላችኋል? 

ማርቆስ 2፡1-12 ኢየሱስ በብዙ ምክንያቶች እግዚአብሔር መሆኑን የሚያስገነዝብ ማረጋገጥ ነው። በመጀመሪያ፥ ኢየሱስ ሽባውን ሰው ሲፈውስ በታምራዊ ኃይሉ አምላክነቱን አሳይቷል። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ የሕግ መምህራኑ ያሰቡት የነበረውን ያውቅ እንደ ነበር በአነጋገሩ አስገንዝቦአቸዋል። ኢየሱስ የሰዎችን አሳብና ሌሎችንም ነገሮች ሁሉ ያውቅ ስለ ነበረ እግዚአብሔር መሆኑን አሳይቷቸዋል። ሦስተኛው፡ ኢየሱስ አምላክነቱን የገለጸው ኃጢአትን ይቅር በማለት ነበር። ኢየሱስ ሽባውን ሰው ከመፈወሱ በፊት ገና እንዳየው «ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» አለው። ይህ አነጋገር እዚያ የነበሩትን የሕግ መምህራን አስከፋ። ምክንያቱም ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ያስቡ ስለነበር ነው። አዎን፥ ትክክል ነበሩ፥ ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ይህንንም ኢየሱስ ደህና አድርጎ ያውቅ ነበር። ስለዚህ፥ ለሽባው ሰው «ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» ሲለው፥ በተዘዋዋሪ መንገድ «እኔ የእግዚአብሔር ሥልጣን አለኝ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ» ማለቱ ነበር። ከዚያም ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው ሽባውን ሰው በመፈወስ አረጋገጠ። ስለዚህ ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን እንዳለው በመግለጽ፥ እርሱ እግዚአብሔር መሆኑንም አረጋግጧል። 

ጥያቄ፡- ሉቃስ 7፡36-50 አንብቡ። ይህ ታሪክ በማርቆስ 2፡1-12 ካለው ጋር በምን መንገድ ይመሳሰላል? 

በሉቃስ 7፡36-50 ተመሳሳይ ታሪክ ተፈጽሟል። ኢየሱስ ስምዖን ወደ ተባለ ፈሪሳዊ ቤት እራት ተጋብዞ ነበር። እዚያም በማዕድ ላይ ሳሉ አንዲት ኃጢአተኛ ሴት ወደ ቤቱ ገብታ በኃጢአቷ እየተጸጸተች የኢየሱስን እግር በሽቶ ቀባችው። ኢየሱስም ንስሐ መግባቷንና እምነትዋን ካየ በኋላ «ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» አላት። ልክ በማርቆስ 2 ላይ እንደተናገሩት ኢየሱስ ኃጢአትን ይቅር በማለቱ የሃይማኖት መሪዎች ተበሳጩ። ልክ በማርቆስ 2 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ እግዚአብሔር ብቻ ኃጢአትን ይቅር እንደሚል ያውቅ ነበር። ነገር ግን ለሴትዮዋ ኃጢአትሽ ተሰረየልሽ በማለቱ በተዘዋዋሪ መንገድ አምላክ መሆኑን ገለጸ።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version