Site icon

የዕብራውያን መልእክት ለማን፣ መቼ እና የት ተጻፈ

መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?

የመልእክቱ ተቀባዮች አይሁዶች መሆናቸው ግልጽ ነው። ይህ የጥንት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለመጽሐፉ ከሰጡት «ዕብራውያን» ከሚለው የመጽሐፉ ስያሜ በግልጽ የሚንጸባረቅ ነው። (የዕብራውያን የጥንት የአይሁዶች ስም ነው።) መጽሐፉ አንባቢዎቹ የብሉይ ኪዳንን የመገናኛ ድንኳንና የአምልኮ ሥርዓት እንደሚያውቁም ያመለክታል። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉትን የአይሁዳውያን ጽሑፎችም ያውቁ ነበር።

ይሁንና፥ መጽሐፉ የተጻፈው በሮም ግዛት ውስጥ በሁሉም ስፍራ ለሚገኙ አይሁዶች አይመስልም። ነገር ግን ጸሐፊውን ለሚያውቁና እርሱም በቅርቡ ለመጎብኘት ለሚፈልጋቸው የተወሰኑ የአይሁድ ክርስቲያኖች የተጻፈ ይመስላል። እነዚህ አንባቢዎች ስለነበሩበት ስፍራ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች ቀርበዋል። አንዳንዶች በመሥዋዕት ላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ አንባቢዎቹ ቤተ መቅደሱ በነበረበትና መሥዋዕቶች በሚቀርቡበት በፓለስታይን ምድር የነበሩ መሆናቸውን ያሳያል። ሌሎች ደግሞ እነዚህ አንባቢዎች ከፓለስታይን ውጪ የነበሩ አይሁዶች መሆናቸውን ይናገራሉ። ይሁንና፥ ሁሉም አይሁዳውያን ወንዶች በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ ስላለባቸውና ሁሉም አይሁዳውያን የእንስሳት መሥዋዕቶችን ስለሚያቀርቡ፥ እነዚህ የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ በየትኛውም ስፍራ ሊኖሩ ይችላሉ። በተጨማሪም፥ የዕብራውያን መልእክት ፓለስታይን የሚኖሩ አይሁዶች ቋንቋ በሆነው በአረማይክ ሳይሆን በግሪክ መጻፉ አይሁዶቹ ከፓለስታይን ውጭ የነበሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ይመስላል።

ብዙ ምሁራን እንደሚስማሙበት መጽሐፉ የተጻፈው በሮም ለነበሩ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነው። ምክንያቱም ጸሐፊው በመጽሐፉ መጨረሻ አካባቢ ከኢጣሊያ ሰላምታ ያስተላለፉትን ሰዎች ጠቅሷል። በቀደምት ክርስቲያናዊ ጽሑፎች ውስጥ ከሁሉም በፊት የዕብራይስጥን ቋንቋ የተጠቀመው በሮም ውስጥ የነበረው ክሌመንት መሆኑ ይህን አሳብ ያጠናክረዋል። ሌሎች ደግሞ ብዙ አይሁዶች የነበሩባትን አሌክሳንደሪያን አጭተዋታል።

ከሐዋርያት ሥራና ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው፥ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ዓመታት ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች በጣም አስቸጋሪዎች ነበሩ። ከ10-20 ዓመታት ለነበሩት የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ዓመታት፥ ክርስትና በዋናነት የአይሁዶች ሃይማኖት ነበር። እነዚህ አይሁዶች የወትሮው የአምልኮ ሥርዐታቸውን ብዙም ሳይለውጡ ክርስቶስ ለኃጢአታቸው የሞተ መሢሐቸው መሆኑን አምነዋል። ነገር ግን አሁንም በቤተ መቅደስ ውስጥ ያመልኩ (የሐዋ. 2፡46፥ 3፡1)፥ የእንስሳት መሥዋዕቶች ያቀርቡና የአይሁዶችን ባህላዊ ልምምዶች ሁሉ ይከተሉ ነበር። ከአብዛኞቹ አይሁዶች የሚለዩበት ዋናው ነገር አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በክርስቶስ መሢሕነት ማመናቸው ነበር።

ቆርኔሌዎስ ከተለወጠና የአንፆኪያ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተች በኋላ፥ ቀስ በቀስ ክርስትና እየተለወጠ ሄደ፥ ለመጀመሪያ ግዜ አሕዛብ ክርስቲያኖች ይሆኑ ጀመር። እነዚህ አሕዛብ በቤተ መቅደስ ውስጥ የማምለክ ፍላጎት አልነበራቸውም። የእንስሳት መሥዋዕቶችን ካለማቅረባቸውም በላይ፥ የአይሁዶችን ባህል አይከተሉም ነበር። የአሕዛብ አማኞች ቁጥር በጣም ጥቂት ስለነበር፥ በመጀመሪያ አይሁዳውያን አማኞች እነዚህ ወደ ክርስትና ከመጡት ጥቂት አሕዛብ ጋር ግብግብ መግጠም አላስፈለጋቸውም ነበር።

ይህ ሁሉ የተለወጠው በመጀመሪያው የጳውሎስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ወቅት ነበር። ጳውሎስና በርናባስ በትንሹ እስያ ውስጥ ወንጌልን እየሰበኩ ሲዞሩ፥ ጥቂት አይሁዶችና ብዙ አሕዛብ በወንጌል ማመን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የአሕዛብ አማኞች ቁጥር ቀስ በቀስ የአይሁዶችን አማኞች ቁጥር እያጠፈ ይሄድ ጀመር። የአሕዛብ አማኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በአይሁዳውያን ክርስቲያኖች አእምሮ ውስጥ አንድ አስፈላጊ ጥያቄ ያቃጭል ጀመር። ይኸውም አሕዛብ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን የሚያገኙት እንዴት ነው? የሚለው ነበር። አብዛኞቹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሕዛብ በክርስቶስ ከማመናቸው በተጨማሪ ወደ አይሁድነት መቀየር አለባቸው ብለው ያምኑ ነበር። ስለሆነም አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አሕዛብ አማኞች መገረዝና የብሉይ ኪዳን ሕጎችን መጠበቅ እንዳለባቸው ያስተምሩ ጀመር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይጠቀስም፥ የቤተ መቅደስ፥ የምኩራብና የሌሎችም የአይሁዳውያን ባሕላዊ ልምምዶች ሁኔታ ከግርዘት ጋር አብሮ ሊነሣ የሚችል ጥያቄ ነበር። አሕዛብ ክርስቲያኖች ከተገረዙ፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ ማምለክን ጨምሮ ሌሎች የአይሁዶች ባህሎችን ሁሉ መከተል ይኖርባቸው ነበር። ጴጥሮስና የቀድሞዎቹ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ለመወያየት በተሰበሰቡ ጊዜ፥ አሕዛብ በክርስቶስ በማመናቸው ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንደሚያገኙ ከስምምነት ላይ ተደረሰ። ወደ አይሁዳዊነት መለወጥና የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ልማዶች መቀጠል አያስፈልጋቸውም ነበር (የሐዋ. 15)። ይህም አሕዛብ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው ከሚያስተምረው የብሉይ ኪዳን አመለካከት የተለየ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ ክፍፍል ተፈጠረ። እስካአሁን ድረስ፥ ሌሎች አይሁዶች ክርስትና ሌላው የይሁዲነት የሃይማኖት ክፍል እንደሆነ ያስቡ ነበር። ምንም እንኳን የአይሁድ መሪዎች ክርስቲያኖችን ቢያሳድዱም (የሐዋ. 9)፥ ተራ አይሁዳውያን የናዝሬቱ ኢየሱስን የሚከተሉትን አይሁዶች ወደ መቀበሉ ያዘነብሉ ነበር (የሐዋ. 2፡47። ነገር ግን ከዚሁ የሐዋርያት ሥራ 15ቱ ውሳኔ በኋላ ክርስትና ከይሁዲነት የተለየ መሆኑ ጥርት ብሎ ታየ። ከዚህም የተነሣ፥ ለአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ውጥረት እየጨመረ ይሄድ ጀመር። የማያምኑ አይሁዶች በሚያምኑት አይሁዶችና ክርስትና ላይ ይነሡ ጀመር። የማያምኑ አይሁዶች ክርስትና ከይሁዲነት የተለየ ሃይማኖት መሆኑን በመገንዘባቸው፥ ክርስቲያኖችን በግልጽ ይቃወሙ ጀመር። ይህ ተቃውሞ በተለይ አይሁዶችና አሕዛብ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያመልኩበት በትንሹ እስያ አይሎ ነበር። በኢየሩሳሌም፥ ሁሉም አማኞች በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያመልኩ በመሆናቸው፥ በመጀመሪያ አካባቢ ክርስቶስን በሚከተሉና በማይከተሉ ተራ አይሁዶች መካከል ግልጽ የሆነ ግጭት አልተከሰተም።

በኋላ በ60ዎቹ ዓ.ም አካባቢ ግን በፓለስታይን ሁኔታው ተለወጠ። ይሁዳ ከሮም ቅኝ ግዛት እንድትወጣ የዜጎቿ ፍላጎት እየጨመረ መጣ። የተለያዩ የዐማፅያን ቡድኖች ተመሠረቱ። በአሕዛብ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ በይፋ ይሰነዘር ጀመር። ይህ ጥላቻ በሌሎችም አውራጃ ዎች ተሰራጨ።

ከፍተኛ የሀገር ወዳድነት ስሜት የሚሰማቸው አይሁዶች የመጡት ከፍልስጥኤም ነበር። በዚህ ጊዜ ክርስቲያን አይሁዶች አጣብቂኝ ውስጥ ገቡ። ክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እኅቶቻቸውን ትተው አይሁዳዊነታቸውን ያጠብቃሉ? አይሁዶች ለብቻቸው አሕዛብ ደግሞ ለብቻቸው የሚያመልኩባቸው ሁለት የተለያዩ ባዕዳዊ እምነቶች በመመሠረት አይሁዶችን ከአሕዛብ መለየት የቱ ይሻል ይሆን? በሮም ላይ የሚካሄደውን ዐመፅ ካልደገፉ፥ አገራቸውን እንደ ካዱ ከሃዲዎች ተደርገው ይቆጠሩ ጀመር። የማያምኑ አይሁዶች ክርስቲያን አይሁዶች ከአሕዛብ ተለይተው ወደ ጥንታዊ አምልኮአቸው እንዲመለሱ በመጠየቃቸው ምክንያት በይሁዳና በሮም ግዛቶች ሁሉ ትልቅ ውጥረት ተፈጠረ። ይህን አሳብ ለመቀበል ያልፈለጉ አይሁዶች አይሁዳዊነታቸውን እንደ ካዱ ተቆጠሩ። ከዚህም የተነሣ ከአይሁድ ወንድሞቻቸው ስደት ይሰነዘርባቸው ጀመር። በተለይ በ66 ዓ.ም በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች በሮም ላይ በማመፃቸው ይኸው ውጥረት ከላቀ ደረጃ ላይ ደረሰ። በዚህ ጊዜ በየትኛውም ስፍራ የሚገኙ አይሁዶች ዐመፁን የመደገፍ ወይም ከሮም ጋር የመተባበር ግዴታ ነበረባቸው። በ70 ዓ.ም ሮማውያን ከተማይቱን ቤተ መቅደሱን በመደምሰስ ዐመፁን እስከ ደመሰሱበት ጊዜ ድረስ ይኸው አመጽ አይሁዶችን ከፋፍሎአቸው ቆይቷል። የቤተ መቅደሱ መደምሰስ የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓት ከፍጻሜ አደረሰው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በፖለቲካው (ጎሰኝነት፥ ብሔርተኝነት፥ ወዘተ…) ዓለም ውስጥ እየተከናወነ ያለው ነገር በቤተ ክርስቲያን ላይ እንዴት ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ግለጽ። ለ) ከመንፈሳዊ ቤተሰብህ ይልቅ ከጎሳህ ጋር መወገን ፈታኝ የሚሆነው እንዴት ነው? ሐ) በቤተ ክርስቲያን ወይም በሽማግሌዎች መካከል የሚፈጠረው ክፍፍል አንዳንድ ጊዜ ከጎሳዊ ውርስ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ግለጽ። መ) ጎሰኝነት፥ ዘር ወይም ቤተሰባዊ ውርስ እንዲካሄዱ መፍቀድ ክርስቶስ ከጸለየበት ( ዮሐ 17 አንብብ) እና ጳውሎስ ካስተማረው (ገላ. 3፡28-29) እውነት ጋር የሚጻረረው እንዴት ነው?

ከኢየሩሳሌም መደምሰስ ቀደም ብሎ አማኝ አይሁዶች ወደ ይሁዲነት ሊመለሱ ውጥረት በበዛባቸው ወቅት፥ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ለክርስቲያን አይሁዶች ይህንን ጠቃሚ መልእክት ጽፎላቸዋል። ብዙ አይሁዶች ወደ ጥንታዊቷ እምነታቸው ለመመለስ እያሰቡ ነበር። «ጥንታዊ ልምምዶቻችን ለሙሴ፥ ለዳዊት፥ ለኢሳይያስና ለሌሎችም ጥሩዎች ከነበሩ፤ በክርስቶስ ማመናችንን ትተን ወደ እንስሳት መሥዋዕቶች ብንመለስ ምን አለበት?» ብለው ያስቡ ነበር። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ይህንን መልእክት ያስተላለፈው ወደ ጥንታዊ የአምልኮ መንገዳቸው ለመመለስ ያስቡ ለነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነበር። ጀርባቸውን ለክርስቶስ ሰጥተው ወደ እንስሳት መሥዋዕቶች ቢመለሱ ምን ዓይነት አደጋዎች እንደሚጠብቃቸው ይነግራቸዋል፡፡ ክርስቶስ ለኃጢአታችው ስለ ሞተ፥ የእንስሳት መሥዋዕቶች ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሆነ እርሱን ለማምለክ ከእንግዲህ አማራጭ መንገዶች ሊሆኑ አይችሉም ነበር። ዛሬ እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያድን ብቸኛው መንገድ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ኃጢአት ባቀረበው መሥዋዕት አማካኝነት ብቻ ነው። ጸሐፊው በቅርቡ ቤተ መቅደሱ እንደሚደመሰስና የእንስሳት መሥዋዕቶች የሚቀርቡበት ሥርዓት እንደሚወገድ የሚያሳይ ትንቢታዊ መልእክት አስተላልፎአል (ዕብ. 8፡13)።

የዕብራውያን መልእክት የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

የውይይት ጥያቄ፡– ዕብ 13፡24 አንብብ። ጸሐፊው ሰላምታውን የሚልከው ከየት ሆኖ ነው?

የዕብራውያን መጽሐፍ፥ «ከኢጣልያ የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል» በማለት መልእክቱን ይደመድማል። ይህ ዐረፍተ ነገር ሁለት ትርጉሞች ሊሰጥ ይችላል። በመጀመሪያ፥ ጸሐፊው በኢጣልያ አገር እንደሚኖርና እዚያው ከነበሩት ክርስቲያኖች በሌላ ስፍራ ላሉት አንባቢዎች ሰላምታ እንደሚያቀርብ ሊያመለክት ይችላል። ሁለተኛ፥ ጸሐፊው በየትም ስፍራ ቢሆን፥ አንዳንድ የኢጣልያ አማኞች (እንደ ጵርስቅላና አቂላ) ከእርሱ ጋር እንደነበሩ ሊያሳይ ይችላል። እነዚህ የኢጣልያ አማኞች በሮም ለሚኖሩ አንባቢዎች ሰላምታ ልከውላቸው ይሆናል። ምንም እንኳን የተለያዩ ምሁራን ይህን መልእክት ከሮም፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከአሌክሳንደሪያ፥ ወይም ከሌሎች ከተሞች እንደ ተጻፈ የሚያመለክቱ የተለያዩ ንድፈ ሃሳቦችን ቢያቀርቡም፥ ጸሐፊው የዕብራውያንን መልእክት በጻፈበት ወቅት የት እንደነበረ በትክክል መናገር አይቻልም።

በጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ጽሑፎች ውስጥ የዕብራውያን መልእክት በቀዳሚነት የተጠቀሰው በ95 ዓ.ም ሲሆን፥ ይህንንም ያደረገው የሮም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። ይህም መጽሐፉ በዚያን ጊዜ እንደ ተጻፈ ያመለክታል። ጢሞቴዎስ ገና አልሞተም ነበር (ዕብ. 13፡23)። ለአይሁዶች ወንጌልን የመሰከሩና ክርስቶስን በዓይነ ሥጋቸው የተመለከቱ አንዳንድ አገልጋዮች እንዲሁ በሕይወት ነበሩ (ዕብ. 2፡3)። ጸሐፊው የቤተ መቅደሱን መደምሰስ አለመግለጹ፥ አይሁዶች የእንስሳት መሥዋዕቶች ያቀረቡ መሆናቸው (ዕብ. 10፡2)። እንዲሁም ካህናት ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገለገሉ መሆናቸው (ዕብ. 5፡1-3፥ 7፡23፥ 27፤ 8፡3-5፤ 9፡6-9)፥ ይህ መልእክት ቤተ መቅደሱ ከተደመሰሰበት እና የእንስሳት መሥዋዕት ከቆመበት ከ70 ዓ.ም በፊት እንደ ተጻፈ ያመለክታል። የዕብራውያን መልእክት የተጻፈበት ትክክለኛው ጊዜ ከ60-68 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Exit mobile version