Site icon

እምነት ከታዛዥነት ጋር እንዴት ይዛመዳል? 

1. መርሆ፡- ታዛዥነትና መልካም ሥራ የሚያድን እምነት ማረጋገጫዎች ናቸው። 

ባለፉት ሦስት ቀናት ወደ ደኅንነት ስለሚያደርሱ መንገዶች ስናጠና ነበር። አዲስ ኪዳን ግልጽ እንደሚያደርገው ሰዎች የክርስቶስን ደኅንነት ለመቀበል እንዲችሉ አንድ ነገር ማድረግ አለባቸው፡- በራሳቸው መታመንን ትተው ወደ ክርስቶስ መመለስ አለባቸው። ይህም ስለ ደኅንነታቸው በበጎ ሥራቸው ላይ ማተኮርን በመተው በኢየሱስና እርሱ በሞቱና በትንሣኤው ባከናወናቸው ድርጊቶች ላይ መመርኮዝ ይጠበቅባቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ይህ የደኅንነት አንድ የሆነ ነገር «ንስሐ» ተብሎ ይጠራል። ይህም ራስን ትቶ ወደ ክርስቶስ መመለስ ማለት ነው። አንዳንዴ ይህ አንድ ለደኅንነት አስፈላጊ የሆነ ነገር «እምነት» ተብሎም ይታወቃል። ይህም በራሳችን ላይ በመደገፍ ፈንታ በኢየሱስ ላይ መመርኮዝ ማለት ነው። በሌላ ጊዜ ደግሞ ይኸው ሁኔታ «ወደ እግዚአብሔር መመለስ» ይባላል። ይህም በኢየሱስ በኩል ወደ እግዚአብሔር መመለስ ሲሆን፥ በአንጻሩ ለደኅንነት ያበቃናል የምንለውን ማንኛውንም ሌላ መመኪያ ትተን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ማለት ነው። ንስሐ፥ እምነትና ወደ እግዚአብሔር መመለስ እነዚህ ሦስቱ ሰዎች የክርስቶስን ደኅንነት ለመቀበል በአጠቃላይ ሊገልጽዋቸው የሚገባ የአንዱ የመመለስ አሳቦች ናቸው። እነዚህ ሦስቱም አሳቦች ደኅንነት በበጎ ሥራችን ሳቢያ የሚመጣ ሳይሆን፥ በበጎ ሥራችን መታመናችንን አቁመን በክርስቶስ ብቻ መታመን ስንጀምር መሆኑን በግልጽ ያስረዳሉ። 

ሆኖም፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለእግዚአብሔር ስለ መታዘዝና ስለ መልካም ሥራ የሚገልጹ ብዙ ጥቅሶች ይገኛሉ። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ጥቅሶች መልካም ሥራም ለደኅንነት አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው የማቅረብ ዝንባሌ ያላቸው መስለው ሊታዩ ይችላሉ። ዛሬ ከእነዚህ ጥቅሶች ስለ ጥቂቶቹ እንማራለን። መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ስለ መልካም ሥራ ጠቃሚነት በሚናገርበት ወቅት፥ መልካም ሥራና ታዛዥነት የሚያድን እምነት መገለጫና ክርስቶስን የሚከተል ደቀ መዝሙር ፍሬ ናቸው ማለቱ መሆኑን እናያለን፡፡ ስለሆነም መልካም ሥራና ታዛዥነት ወደ ደኅንነት መድረሻው መንገድ ሳይሆን፥ የደኅንነት ውጤት ናቸው። 

2. መርሖውን የሚያረጋግጡ ክፍለ ምንባቦች 

2.1 ያዕቆብ 2፡14-26፡- አዳኝ የሆነ እምነት መልካም ሥራን ያፈራል። 

ጥያቄ፡- ያዕቆብ 2፡14-26 አንብቡ። ሐዋርያው ያዕቆብ በዚህ ክፍል ስለ እምነትና መልካም ሥራ የተናገረውን እናንተ ደግሞ በአንድ ዓረፍተ ነገር አጠቃልላችሁ አቅርቡ። 

ጥያቄ፡- አሁን ደግሞ መለስ ብላችሁ የዚህን ክፍል ጥቅሶች አንድ ባንድ አንብቡ። ሀ) ያዕቆብ 2፡14-16 አንብቡ። ሐዋርያው ያዕቆብ እምነት አለኝ እያለ ግን መልካም ሥራ ስለሌለው ሰው ምን አለ? ለ) ያዕቆብ 2፡17 አንብቡ። አንድ ሰው መልካም ሥራ ባይኖረው፥ ሕይወት ያለው እምነት ሊኖረው ይችላል? ሐ) ያዕቆብ 2፡18 አንብቡ። ሐዋርያው እምነት እንዴት ይገለጣል አለ? መ) ያዕቆብ 2፡19 አንብቡ። አጋንንት ማንን ያምናሉ? ሠ) ያዕቆብ 2፡20-26 አንብቡ። የአብርሃምና የረዓብ ታሪክ ምን ያስተምራል? ይህን መልስ ለማግኘት በተለይም ቁጥር 22ን ፣ አጥኑ። 

አንዳንድ ጊዜ የያዕቆብ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ መልእክቶች ሁሉ እጅግ በጣም አደናጋሪ የሆነ ክፍል ሆኖ ይታያል። ኤፌሶን 2፡8-9 እና ሮሜ 45ን በምናነብበት ጊዜ፥ ደኅንነት የሚገኘው በሥራ ሳይሆን በጸጋ መሆኑን እንገነዘባለን። ነገር ግን ወደ ያዕቆብ ምዕራፍ 2 መጥተን ስናነብ ደግሞ፣ ያዕቆብ መልካም ሥራ የሌለው እምነት ምውት ነው ይለናል። ታዲያ ሐዋርያው ያዕቆብ የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ካጻፈው ቃል ጋር ይቃረናል? በፍጹም፣ ሁለቱም ሐዋርያት የጻፉዋቸው መልእክቶች እርስ በርስ አይቃረኑም። የጳውሎስ ትኩረትና አጽንኦት ሰዎች የሚድኑበትን ሁኔታ ለማስረዳት ነው። ሰዎች ሁሉ ስለ ደኅንነታቸውና ደኅንነታቸውን ለማግኘት በክርስቶስ ላይ መደገፍ ይኖርባቸዋል። ያዕቆብ ሊያመላክት የፈለገው የተለያዩ የእምነት ዓይነቶች ስላሉ አዳኝ የሆነ እምነት ውጤት ምን እንደሆነ ለማሳየት ነው። ስለዚህ ሐዋርያው ያዕቆብ እውነተኛና አዳኝ የሆነ እምነት ሁልጊዜ መልካም ሥራን ሊያፈራ መቻሉን ነው የሚያስተምረን። 

በያዕቆብ 2፡14-16 ውስጥ መልካም ፍሬ የማያፈራ እምነት ሰውን ሊያድን አይችልም ይላል። ማንኛውም ሰው በኢየሱስ አምናለሁ እያለ መልካም ሥራ ሳይሠራ፣ ይህ ሰው የሚያድነውን ዓይነት እምነት አላገኘም ማለት ነው። ይህ ሰው ሕያውና አዳኝ በሆነ እምነት ፈንታ የሞተ እምነት ይኖረዋል ማለት ነው (ያዕቆብ 2፡17)። እውነተኛና አዳኝ የሆነ እምነት ራሱን የሚገልጠው በመልካም ሥራ ብቻ ነው (ያዕቆብ 2፡18)። 

አንድ ሰው በመልካም ሥራ አማካይነት የማይገለጥ ምን ዓይነት እምነት ሊኖረው ይችላል? ያዕቆብ በቁጥር 19 ውስጥ አንድ ምሳሌ ያቀርባል። ይህም አጋንንት ካላቸው እምነት ጋር ይመሳሰላል። አጋንንት የእግዚአብሔርን መኖር ያምናሉ። አንድነቱንም ያምናሉ። ስለ እግዚአብሔር አንዳንድ ነገሮች እውነት መሆናቸውንም ያምናሉ። ነገር ገን በእግዚአብሔር ላይ ማመፃቸውን ትተው ለመዳን በእርሱ አያምኑም። አንዳንድ ሰዎችም ይህንኑ አጋንንት ያላቸውን እምነት የመሰለ እምነት አላቸው። በእግዚአብሔር ሕልውና ያምናሉ። አንዳንድ ነገሮች ስለ እግዚአብሔር እውነት እንደሆኑ ይቀበላሉ፤ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፥ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ እንደሆነና ፍጥረታቱን ሁሉ በሉዓላዊነት ሥልጣን እንደሚመራና እንደሚያስተዳድር ያምኑ ይሆናል። እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ መሆኑን የሚያምኑ ይመስላል። እግዚአብሔር አፍቃሪና መሐሪ አምላክ መሆኑንም ያምኑ ይሆናል። ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር እውነት የሆኑትን እነዚህን ነገሮች ቢያምኑም፥ በአንጻሩ ደኅንነትን ለማግኘት በኢየሱስ ብቻ አያምኑም። እነዚህን የመሰሉ ሰዎች እምነት አላቸው፣ ግን እምነታቸው የሚያድን እምነት አይደለም። አጋንንት ካላቸው እምነት ያልተለየ እምነት አላቸው። 

ያዕቆብ አዳኝ የሆነ እምነት ሁልጊዜ መልካም ፍሬ ያፈራል ይላል። ማንም እምነት አለኝ እያለ መልካም ሥራ የማይሠራ ሰው እምነት ከንቱ ነው ይላል (ያዕቆብ 2፡20)። የሚያድነው እምነት አይደለም። አዳኝ ስለሆነ እምነት ያዕቆብ ሁለት ምሳሌዎችን ይሰጣል። የመጀመሪያው ምሳሌ አብርሃም ነው። አብርሃም እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ የሚወርስ ልጅ እንደሚሰጠው የሰጠውን ተስፋ አመነ። ከዚያም እግዚአብሔር ለአብርሃም ይስሐቅን ሰጠው። ላም አብርሃም ይስሐቅን እንዲሠዋለት አዘዘው። አብርሃም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀብሉ ይስሐቅን ሊሠዋለት ተዘጋጀ። ይህ እንግዲህ አብርሃም እግዚአብሔር የሰጠውን ተስፋ ወራሽ የሆነ ልጅ እንደሚሰጠው በእርሱ ለማመኑና በእርሱም ላይ ፍጹም የሆነ አለኝታ እንደነበረው ያረጋግጥልናል። ያዕቆብ በቁጥር 22 ውስጥ እንደሚለው በእምነቱ ሥራው ተፈጸመ። የእርሱ እውነተኛ እምነት በመልካም ሥራው ተረጋግጦ ታወቀ። በተመሳሳይ መንገድ ረዓብም ሁለቱን ዕብራውያን ሰላዮች ተቀብላ በረዳቻቸው ጊዜ ስእግዚአብሔር ላይ እምነት እንደ ነበራት አረጋግጣለች። ረዓብ አስቀድማም በእስራኤል አምላክ እንደምታምን አስታውቃለች። ቀጥላም በእስራኤል አምላክ በእውነት የምታምን መሆንዋን ሰላዮቹን ተቀብላ በረዳቻቸው ጊዜ የእምነትዋን እርግጠኝነት አሳይታለች። እውነተኛ የሆነ እምነቷም በመልካም ሥራዋ ታይቷል፥ ተረጋግጧል፡፡ 

የያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ 2 ለአማኞች ሁሉ በጣም ጠቃሚ የሆነ መልእክት ነው። ትናንትና ከተማርናቸው ክፍሎች ጋር አይቃረንም። ሰዎች በበጎ ሥራቸው ይጸድቃሉም ብሎ እያስተምርም። በምትኩ የሚለው እውነተኛና አዳኝ የሆነ እምነት ወደ መልካም ሥራ ፍሬ ይመራል ነው። ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት የኖረው የጀርመን ተሐድሶ አራማጅ ማርቲን ሉተር፥ የጳውሎስንና ያዕቆብን ትምህርት እንዲህ በማለት ያጠቃልለዋል፡ እምነት ብቻውን ያድናል፥ ግን የሚያድን እምነት ደግሞ ፈጽሞ ብቻውን አይደለም። ሉተር ይህን ሲል የሚያድን እምነት ያላቸው ሰዎች ሁልጊዜ መልካም ሥራ ይሠራሉ ማለቱ ነው። 

2.2 ከጳውሎስ መልእክቶች አንዳንዶቹ፡- የሚያድን እምነት የታዛዥነትንና የመልካም ሥራ ፍሬዎችን ያፈራል ይላሉ። 

ጥያቄ፡– ኤፌሶን 2፡8-10 አንብቡ። ሀ) እኛን በማዳን ረገድ የመልካም ሥራ ድርሻ ምንድን ነው? (ቁጥር 8-9) ለ) የደኅንነታችን ዓላማ ምንድን ነው? (ቁጥር 10) 

ጥያቄ፡- 1ኛ ተሰሎንቄ 1፡2-3 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ በሚጸልይበት ጊዜ ሁሉ ስለ ተሰሎንቄ ሰዎች ምንን እንደሚያስታውስ ተናገረ? 

ጥያቄ፡- ሮሜ 1፡5 አንብቡ። ሐዋርያው ጳውሎስ ጸጋንና ሐዋርያነትን ለምን ዓላማ ተቀበለ? 

እስከዚህ ድረስ በያዕቆብ ምዕራፍ 2 ውስጥ የተማርነውን ትምህርት የሚያብራሩ በዛ ያሉ ክፍሎች በአዲስ ኪዳን ውስጥ ይገኛሉ። በኤፌሶን 2፡8-9 ውስጥ ጳውሎስ እኛ የዳነው በጸጋው በማመን እንጂ በመልካም ሥራችን አለመሆኑን በግልጽ ይናገራል። ነገር ግን ወዲያውኑ እግዚአብሔር እኛን ያዳነበት ዓላማ እና መልካም ሥራ እንድንሠራ ነው ይላል። በእውነት የዳነ ሰው ይህን የእግዚአብሔርን ዓላማ ለመፈጸም መልካም ሥራ ይሠራል። 

መልካም ሥራ የእምነታችን ውጤት ሲሆን ለእምነታችን ምስክር ነው። በ1ኛ ተሰሎንቄ ። ውስጥ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በሚጸልይበት ጊዜ ሁሉ «የእምነታቸውን ሥራ» እንደሚያስታውስ ነግሮአቸው ነበር። «የእምነት ሥራ» የተባለው ሐረግ «ከእምነታችሁ የተነሣ የተገኘ የሥራ ፍሬ» ማለት ነው። ጳውሎስ ስለ ተሰሎንቄ ሰዎች መልካም ሥራ ያስታወሰበት ምክንያት መልካም ሥራው የተገኘው በክርስቶስ የሚያድን ተስፋ ስለነበረው ነው። መልካሙ ሥራቸው አላዳናቸውም፤ በአንጻሩ የሚያድነው እምነታቸው የዚህ እምነታቸው ምስክር የሆነ መልካም ሥራ ሊያፈራ ቻለ። በሮሜ 1፡5 ውስጥ ጳውሎስ ለሐዋርያነት የሚያበቃውን ጸጋ ስለ ተቀበላ፥ አሕዛብ ሁሉ እንዲያምኑና እንዲታዘት ማድረጉን ይናገራል። አማኝ ያልነበሩ ሰዎች የሚያድን እምነትን ሲያገኙ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይጀምራሉ። አዳኝ የሆነ እምነት ደግሞ የመታዘዝን ፍሬ ያፈራል። 

2.3 ወንጌሎች፡- እውነተኛ ደቀ መዛሙርት እምነታቸውን በመልካም ሥራቸው ይገልጹታል ይላሉ። 

ጥያቄ፡- ዮሐንስ 15፡8 አንብቡ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እንዴት እንገልጻለን? 

ጥያቄ፡- ማቴዎስ 7፡16-23 አንብቡ። እነማን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆኑ እንዴት ለይተን ማወቅ እንችላለን? 

ኢየሱስ የእርሱ ደቀ መዝሙር የሚሆነው የእርሱ ደቀ መዝሙር ነኝ የሚለው ሳይሆን፣ የእርሱ ደቀ መዝሙር የሚሆነው እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚሠራ መሆኑን አስተምሯል። በዮሐንስ 15፡8 ውስጥ ኢየሱስ ሲናገር፥ እኛ የእርሱ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን ለመግለጽ የምንችለው በሕይወታችን ፍሬ መሆኑን ያረጋግጣል። መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን እንዲገዛ ብንፈቅድለት፥ ለኢየሱስ እንታዘዛለን፥ ከሌሎች የተለየ ሕይወትን በመኖር የኢየሱስ ተከታዮች መሆናችንንም ለሁሉ እናስመሰክራለን። በማቴዎስ 7፡16-23 ውስጥ ኢየሱስ እንዳለው ነቢያትና ሰባኪዎች ሳይቀሩ ወደ እርሱ ዘንድ መጥተው ተከታዮቹ መሆናቸውን ይገልጻሉ። እንዲያውም ትንቢት ይናገራሉ፥ ተአምራትንም ይሠራሉ፣ ደግሞም አጋንንትን በኢየሱስ ስም ያወጣሉ። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ቢናገሩም፣ በመንፈስም መሞላታቸውን ቢገልጹም፥ እንዲሁም በኢየሱስ ስም ታላቅ ኃይል ያለበት ተግባር ቢፈጽሙም፥ እውነተኛና አዳኝ የሆነ እምነት ሊኖራቸው አይችልም። እንዲያውም በኢየሱስ የሚያምኑ እውነተኛ ሰዎች ሊባሉም አይችሉም። ኢየሱስ ፍርዱን የሚሰጥበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜም እርሱ አላውቃችሁም ይላቸዋል። እነዚህ ሰዎች በኢየሱስ ስም ታላቅ ኃይል ያለበት ሥራ ቢፈጽሙም፣ በኢየሱስ የሚያድን እምነትን ስለመቀበላቸው የሚያረጋግጥ መልካም ሥራ በሕይወታቸው ውስጥ ሊሠሩ አይችሉም። የሚያድን እምነት መልካም ሥራን ያፈራል። ስለሆነም የታላቅ ‘ መንፈሳዊ ኃይል ሥራ የአዳኝ እምነት መገለጫ ሊሆን አይችልም። 

2.4 ወንጌሎች፡- እውነተኞች ደቀ መዛሙርት እምነታቸውን ታማኞች ሆነው በመጽናት ይገልጻሉ።

ጥያቄ፦ ዮሐንስ 6፡60-70 አንብቡ። ሀ) አንዳንዶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ምን አደረጉ? ለ) ይህንንስ ለምን አደረጉ? ሐ) አሥራ ሁለቱስ ምን አደረጉ? መ) በምን ምክንያት ይህንን አደረጉ? 

በዮሐንስ 6፡60–70 ያለው መልእክት ስናጠናቸው ለቆየናቸው ሁለት ዓይነት እምነቶች ተጨማሪ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ላይ ላዩን የሆነ እምነት ስለ እግዚአብሔር ያሉትን ነገሮች እንጂ መልካም ፍሬ በሚያፈራው የሚያድን እምነት አይታመንም። ኢየሱስ ሥጋውን ስለ መብላትና ደሙን ስለ መጠጣት ለአይሁዶች ብዙ ከባድ የሆኑ ትምህርቶችን አስተምሮአቸዋል። (እነዚህን ቁጥሮች በሚቀጥለው ትምህርት ውስጥ እናጠናለን)፡፡ ብዙ አይሁዶችም የጌታ ትምህርት አስቸጋሪ እንደ ነበረ አንሥተው ያጉረመርሙ ነበር። ምንም እንኳን እነዚህ አይሁዶች ኢየሱስን ቢከተሉና ደቀ መዛሙርቱ ተብለው ቢጠሩም፥ ብዙዎቹ በእውነት በእርሱ እንደማያምኑ ነግሮአቸው ነበር (ቁጥር 64)። በውጭአዊው ሁኔታቸው በእርሱ የሚያምኑ ቢመስሉም፣ በውስጣቸው ግን ከልባቸው አያምኑበትም ነበር። ስለዚህ፣ ብዙዎቹ ከእርሱ ተለዩና ወደ ኋላ ተመለሱ። እነዚህ ሰዎች በእውነት የሚያድን እምነት አልነበራቸውም። ነገር ግን አሥራ ሁለቱ ከኢየሱስ ጋር ቆዩ። ኋላም ኢየሱስ እነርሱም ትተውት ሊሄዱ ይፈልጉ እንደሆነ በጠየቃቸው ጊዜ ጴጥሮስ መለሰና፥ «ወደ ማን እንሄዳለን፥ አንተ የዘላለም ቃል አለህ» አለው። ጴጥሮስና ሌሎቹ (ከይሁዳ በስተቀር) ስለ ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮችን ብቻ አላመኑም ነበር። ለዘላለም ደኅንነታቸው ራሳቸውን ለእርሱ አሳልፈው ሰጥተው ነበር። እርሱ ብቻ ሊያድናቸው የሚችል የእግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ አምነው በእርሱ ላይ ተደግፈው ነበር። ይህ እንግዲህ ከኢየሱስ ጋር ጸንተው ለመቆየታቸው ማረጋገጥ የሆነ እውነተኛ አዳኝ እምነት ነበር። ይሁዳ በዚህ ጊዜ እንኳን አብሮት ቆይቶ ነበር። በኋላ ላይ ኢየሱስን ትቶ እስክ ሄደ ድረስ እውነተኛውን ልቡን አላሳየም ነበር (ሉቃስ 22፡1-6 ተመልከቱ)። ዮሐንስ ምዕራፍ 6 ዛሬ በሌሎቹ ክፍሎች ውስጥ የተመለከትናቸውን አብራርቶ ያቀርባል። ይህም በኢየሱስ ላይ የሆነ እውነተኛው የሚያድን እምነት ማለት ለደኅንነት በኢየሱስ መታመን ማለት ሲሆን፥ ይህ ደግሞ በሕይወታችን ኢየሱስን በመከተላችን የሚረጋገጥ ነው። 

2.5 የሐዋርያው ጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች፡- መልካም ሥራ የደኅንነታችን ውጤት እንጂ የደኅንነታችን ፍጻሜ አይደለም። 

ጥያቄ፡- ገላትያ 3፡1-14 አንብቡ። ሀ) የገላትያ ሰዎች መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዴት ጀመሩ? (ቁጥር 2-4) ለ) አብርሃም ጽድቅን እንዴት ሊያገኝ ቻለ? (ቁጥር 6) ሐ) ከአብርሃም ጋር የተባረከው ማን ነበር? (ቁጥር 9) መ) ለመዳን ሕግን መፈጸም ያለባቸው መሆኑን ስለሚያምኑ ሰዎች እውነተኛው ነገር ምንድን ነው? (ቁጥር 10) ሠ) ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅን የሚያገኙት እንዴት ነው? (ቁጥር 11) 

ጥያቄ፦ ገላትያ 5፡13-14፥ 16፥ 19-24 አንብቡ። ሀ) የአማኞች ደኅንነት ውጤት መሆን የሌለበት ምንድን ነው? ታዲያ ውጤቱ ምን መሆን አለበት? (ቁጥር 3) ለ) የኃጢአትን ባሕርይ በሚከተሉት ላይ ምን ይደርስባቸዋል? (ቁጥር 19-21) ሐ) ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሕይወትን እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? (ቁጥር 16፥22-24) 

ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ መልእክት ውስጥ የእምነትንና የሥራችን ሚናዎች በጥንቃቄ ያብራራል። ሐሰተኛ መምህራን ለገላትያ ሰዎች ደኅንነታቸው በእምነት ቢጀመርም ገና የሚቀረው እንዳለና ሙሉ እንዳልሆነ ይነግሩዋቸው ነበር። ስለዚህ ደኅንነታቸው እውነተኛና የተሟላ ይሆን ዘንድ መገረዝና ለቀሪው የሙሴ ሕግ መታዘዝ ነበረባቸው። ለሕጉ በመታዘዝና በሕጉም ውስጥ የተጠቀሱትን ተግባራት በመፈጸም ሙሉ በሙሉ እንደሚድኑ ሐሰተኞቹ መምህራን ይነግሯቸው ነበር። ይህንን ጳውሎስ በሁለት መንገድ መልሶታል። አንደኛ፥ የተሟላ ደኅንነት ሊገኝ የሚችለው በክርስቶስ ባለ እምነት መሆኑን አጥብቆ ያረጋግጣል። ሁለተኛ፥ እውነተኛና የሚያድን እምነት ያላቸው ሰዎች፥ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንደሚሄዱና በመልካም ሥራ ሕይወት ውስጥ እንደሚኖሩ ይገልጻል። በገላትያ 3፡2-4 ውስጥ በክርስቶስ በነበራቸው እምነት በዛኑ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን መቀበላቸውንና የዳኑትም ለሕግ በመገዛት እንዳልነበረ አሳስቧቸዋል። «እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! ለመሆኑ ማን መተት አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊት ለፊታችሁ በግልጥ ተሥሎ ነበር፡፡» ሲል ጳውሎስ ይነግራቸዋል፡፡ (ቁጥር 1)? በርሜ 4 ውስጥ እንዳደረገው፣ ጳውሎስ እንደገና አብርሃምን ስእምነት የዳነ ሰው ምሳሌ አድርጎ ያቀርበዋል? አብርሃምን ሊያጸድቀው የቻለው እምነቱ ነበር። ስለዚህ ለአብርሃም የተሰጠውን የደኅንነት ተስፋ ሊቀበሉ የሚችሉት እምነት ያላቸው ብቻ ናቸው (ገላትያ 3፡6፥9)። ሰዎች መልካም ሥራችን ያድነናል ብለው ቢያምኑ፣ በእግዚአብሔር የተረገሙ ናቸው፥ ምክንያቱም በመልካም ሥራው ማንም በእግዚአብሔር ፊት ሊጸድቅ አይችልም ይላል ጳውሎስ (ገላትያ 3፡10-10። ታዲያ የመልካም ሥራ ሚና ምንድን ነው? ይህን በምዕራፍ 5 ውስጥ በግልጽ አስቀምጦታል። እንዲህ ይላል፥ በኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አማኞች የሆኑ ሁሉ አዲስ ሕይወትን ይኖራሉ ይላል። እንዲሁም እውነተኛ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ውስጥ እየኖሩ ሌሎችን በመውደድ እንዲሄዱ እንጂ በኃጢአት ባሕርይ ውስጥ መኖር እንደሌለባቸው ያስጠነቅቃል (ገላትያ 5፡19-21)። እንደዚሁም እውነተኛና አዳኝ የሆነ እምነትም ሊኖራቸው አይችልም። በእውነት የክርስቶስ የሆኑ ሕይወታቸውን በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንዲመራ በማድረግ በሕይወታቸው ውስጥ የመንፈስን ፍሬ ያሳያሉ። 

በገላትያ ምዕራፍ 3 እና 5 ውስጥ ጳውሎስ ደኅንነት በጸጋ ብቻ በእምነት አማካይነት እንደሚገኝ በግልጽ ጽፎአል። ስለሆነም እውነተኛና አዳኝ የሆነ እምነት ያላቸው በውስጣቸው የሚኖረውን የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ በማፍራት በአዲስ ሕይወት ይኖራሉ። 

3. በሥራ ላይ ማዋል 

ጥያቄ፡– በአካባቢአችሁ ስለሚኖሩ አማኝ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ወይም በቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ ስላሉ እንዲህ ያሉ ሰዎች እስቲ አስቡ። እነዚህ ሰዎች ስለ ደኅንነታቸው ካላቸው እምነት በተጨማሪ ምን ዓይነት ተጨማሪ መልካም ተግባራትን ለመፈጸም ይጥራሉ? ለ) ለእነዚህ ሰዎች መልካም ሥራ የደኅንነት መገለጥ ወይም መታወቂያ እንጂ ደኅንነትን የማግኛ መሣሪያ አለመሆኑን ለማስረዳትና ለመርዳት ዛሬ የተማራችሁትን ትምህርት እንዴት ልታካፍሉዋቸው ትችላላችሁ? 

ብዙ ሰዎች ለደኅንነታቸው መገኘት እምነት በቂ እንዳልሆነ አድርገው ያስባሉ። በክርስቶስ የሚያምኑ ቢሆኑም፥ ለደኅንነታቸው መልካም ሥራ ሠርተው ሊያክሉበት ይጥራሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ለእግዚአብሔር ባይታዘዙና ቅድስና ያለበት ሕይወት ባይኖሩ የማይድኑ መሆናቸውን ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ኦም ባይጾሙ፥ ቤተ ክርስቲያን ባይሄዱ፣ ወይም ለእግዚአብሔር ገንዘብ ባይሰጡ የሚድኑ ሆኖ አይሰማቸውም። አንዳንዶቹ ደግሞ እንደሚያስቡት የግዝረት ሥርዓትን ሳይፈጽሙ ቢቀሩ ደኅንነትን እንደሚያጡ ያምናሉ። በአንጻሩ ደግሞ አንዳንዶች በአንድ ዓይነት ቤተ ክርስቲያን አባላት ካልሆኑ ወይም የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ካላገኙ ደኅንነትን የሚያገኙ አይመስላቸውም። እነዚህ የዘረዘርናቸው ነገሮች አብዛኛዎቹ በጣም ግሩም ነገሮች ናቸው። ነገር ግን አዲስ ኪዳን በግልጽ እንደሚናገረው እነዚህ መልካም ነገሮች የደኅንነት መገለጫዎች ናቸው እንጂ የደኅንነት መቀበያ መሣሪያዎች አይደሉም። ስለሆነም ሰዎች እነዚህ ነገሮች ያድኑናል ብለው የሚያምኑ ከሆኑ፣ በእግዚአብሔር ቁጣ ሥር ናቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መልካም ሥራ እንዲፈጽሙና ዓለምም በዚህ መልካም ሥራቸው እርሱ እንዴት ሕይወታቸውን እንደ ለወጠ እንዲያሳዩ ይፈልጋል። ነገር ግን ደኅንነት ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ነፃ ስጦታ መሆኑን አምኖ በመቀበል የሚገኝ በረከት ነው።

ምንጭ፡- “አስተምህሮ ክርስቶስና ደኅንነት”፤ ጽሑፍ፣ በዶ/ር ስቲቭ ስራውስ፤ ትርጉም በኃይሉ ልመንህ

Exit mobile version