Site icon የሕይወት እንጀራ

“መጽሐፍ ቅዱስ ሊታመን አይችልም – ቀደምት ቅጂዎች ጠፍተዋልና፡፡”

አንዳንድ ሙስሊሞች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቀደምት ቅጂዎች ስለጠፉ አሁን ያለውን መጽሐፍ ቅዱስን ማመን አንችልም ይላሉ፡፡ በተጨማሪም የዛሬዉን መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ከቀደሙት ዋነኛ ቅጂዎች ጋር አመሳክሮ ለማወቅ የሚያስችል ሁኔታም የለም ይላሉ፡፡

እርግጥ ነው፣ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች አልተገኙም፣ ምናልባትም ጠፍተው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይኸው እውነት ለቁርአኑም እንደሚሰራ መታወቅ አለበት፡፡ በቅዱስ ቁርአን፡- ትርጉምና ማብራሪያ፣ (2ኛ እትም፣ 1977 እ.ኤ.አ.) በመግቢያዉ ገጽ 32 ጸሐፊው ዩሱፍ አሊ እንዲህ ያስነብበናል፡-

የቁርአን ክፍሎች እንደወረዱ፣ በቅዱሱ ነቢይ አጻፊነትና መሪነት በቴምር ዛፍ ቅጠሎች ላይ፣ በዛፍ ግንዶች ላይ፣ አጥንቶች፣ ወዘተ ላይ ከተጻፉ በኋላ ጽሑፎቹ በአንድ ኮሮጆ ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡

የቁርአን ጥቅሶች በቅጠሎች፣ በዛፍ ቅርፊቶች፣ በአጥንቶች፣ ወዘተ ላይ ተጽፈው እንደነበረ ልብ ይበሉ፡፡ በአል ቡካሪ የተዘጋጀው ሳሂህ አል-ቡካሪ በሐዲት (የሙስሊም ሐይማኖት ትራዲሽን ስብስብ/መጽሐፍ) መሰረት፣ የቁርአን ጥቅሶች በነጭ ድንጋዮች እና በወንዶች ደረት ላይ ጭምር ተጽፈው እንደ ነበረ በተጨማሪ ምርምሮች ለማወቅ ተችሏል፡፡

“በወንዶች ደረት” ላይ የሚለው ሃረግ፣ በቀጥታ ተወስዶ ቢነበብም ሆነ ዘይቢያዊ አነጋገር እንደሆነ ቢታሰብ (ማለትም ጥቅሶቹን በቃላቸው የሸመደዱ ሰዎችን ቢወክል) ሁለቱም ፍቺዎች በ “ኮሮጆ ውስጥ ተቀመጠ” ከሚለው አሳብ ጋር ሊጣጣም አይችልም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ እነዚህ ቀደምት ቅጂዎች ማለትም የዘንባባ ቅጠሎች፣ የዛፍ ቅርንጫፎች፣ ነጭ ድንጋዮች ወይም አጥንቶች በማንም ሰው እጅም ሆነ ቤተ መዘክር መገኘታቸውን የሚጠቁም ምንም መረጃ የለም፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን በአሁኑ ሰአት ያለው ቁርአን ከሙሐመድ ሞት 20 አመት በኃላ በሙስሊሙ መሪ ኡትማን ከተረጋገጠው የመጨረሻ ቅጂ ጋር የሚስማማ ቢሆንም ከነቢዩ አንደበት በቀጥታ የተነገሩ ስለመሆናቸው ማንኛዉም ሙስሊም ምንም አይነት ማረጋገጫ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ የቀደሙት ቅጂዎች ጠፍተዋልና፡፡ 

አንድ ሙስሊም፣ የቀደምት ቅጂዎች ማመሳከሪያ በሌለበት ሁኔታ የቁርአኑን ተአማኒነት ለመቀበል ካልተቸገረ፣ ክርስቲያኑም የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት ለመቀበል የሚያሳየዉን እምነት ለመቀበል ሊከብደዉ አይገባም፡፡
አንድ ሙስሊም መጽሐፍ ቅዱስን ለመቀበል መቸገር የለበትም፤ ምክንያቱም ቁርአኑ ራሱ የመጣዉ ከእርሱ በፊት ያሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ለማረጋገጥ ነውና፡፡ ይህ እዉነት ከሆነ ሙስሊሙ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ቀደምት ቅጂዎች መጨነቅ አይገባዉም ማለት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጉልህ ስህተቶች ኖረው ቢሆን ኖሮ ቁርአኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለማረጋገጥ ሳይሆን ለመሻርለመተካት አልያም ለማስተካከል ይመጣ ነበርና፡፡ ነገር ግን ቁርአን ለዚህ ጉዳይ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ የለም፡፡ ስለዚህ ሙስሊሙ፣ በራሱ ቁርአን መሰረት፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ተአማኒነት ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡

_________________________________________________

 ሱኒ ሙስሊሞች፣ ሳሂህ አል-ቡካሪ ከስድስቱ የሐዲት ትክክለኛ እና እውነተኛ ስብስቦች መካከል አንዱ ነው በማለት ይቀበላሉ፡፡ እነዚህ በሐዲት ውስጥ ያሉ እስላማዊ ልማዶች (ባሕል/ወግ) ለዘመናት በቃል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ ከቆዩ በኋላ የፋርስ ሰው በሆነው ሙስሊም ምሁር ሙሐመድ ኢብን ኢስማኤል አል-ቡካሪ በአንድ ላይ የተጠናቀሩ ናቸው፡፡ የሱኒ ሙስሊሞች እነዚህን ስድስት የሐዲት ጥንቅሮች ከቁርአን ቀጥሎ እውነተኛዎቹ ወይም ትክክለኛዎቹና ስልጣን ያላቸው የሐዲት ጥንቅሮች እንደሆኑ አድርገው ይቀበላሉ፡፡ ሳሂህ (Sahih) የሚለው አረብኛ ቃል ትርጉም እውነተኛ ወይም ትክክኛ ማለት ነው፡፡ ሳሂህ አል-ቡካሪ የነቢዩ ሙሐመድን አባባሎችና ገድሎች የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ቡካሪ ነብዩ ከሞተ ከጥቂት ክፍለ ዘመን በኋላ የኖረና ሐዲትን የሰበከ ሰው ነበር:: 

http://en.wikipedia.org/wiki/Sahih_al-Bukhari

ሐዲት የሚሚለው ቃል ትርጉም ስለ አንድ ነገር ዘገባ ወይንም ዜና ማቅረብን ያሳያል፡፡ ሐዲቶች ስለ ሙስሊሙ ነቢይ ሙሐመድ ቃሎችና ምግባሮች የሚያወሱ ትረካዎች ናቸው፡፡ ሐዲቶች ቁርአንን እና እስላማዊ ሕግጋቶችን በአግባቡ ለመረዳት ጠቃሚ መሣሪያዎች እንደሆኑ ይታመናል፡፡ እነዚህ ሐዲቶች ግምገማ ከተደረገባቸው በኋላ በ8ኛው እና በ9ኛው ክፍለ ዘመናት ውስጥ በአንድነት ተጠናቅረዋል፡፡ እነዚህ ጥንቅሮች አሁን ባለንበት ዘመን የእስልምና ሕግጋቶችና ታሪኮች መገለጫዎች በመሆን እያገለገሉ ይገኛል፡፡ የእስልምና ሁለቱ የተለያዩ ክፍሎች (ሴክቶች) – ሺአቶችና ሱኒዎች በሐዲት ጥንቅሮች ላይ አይስማሙም፡፡ ሁለቱም የተለያዩ የሐዲት ጥንክሮች አሏቸው፡፡

http://en.wikipedia.org/wiki/Hadith

Exit mobile version