ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል?

በስነ-መለኮቱ አለም ከሚነሱ ዋነኛ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? የሚለው ነው። እግዚአብሔር መጀመሪያ እና መጨረሻ የለውም፣ ሁሉን ቻይ፣ በሁሉ ስፍራ በአንዴ የሚገኝ እንዲሁም ሁሉን አዋቂ ነው። በተቃራኒው ሰው ደግሞ ፍጡር፣ ውሱን እና በስባሽ ነው። ይህ ፍጡር ትልቁን ፈጣሪ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ሲሞክር ነው እንግዲህ እነኚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች መነሳት የሚጀምሩት። ሰው፣ ፈጣሪውን ሙሉ በሙሉ ሊረዳው እንደሚችል ሊያስብ አይገባውም የሚለውን አጠቃላይ እውቀት ከግንዛቤ ከተን ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እንመለስ።

ለምን እግዚአብሔር ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ እንዲደርስ ይፈቅዳል? ስለዚህ ጉዳይ የኢዮብ መጽሐፍ መጠነኛ ግንዛቤ ይሰጠናል። ሰይጣን ኢዮብን እና የኢዮብ የሆነውን ሁሉ (ከነፍሱ በስተቀር) እንዲያጠፋ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አገኘ። ለዚህ የእግዚአብሔር ውሳኔ የኢዮብ ውሳኔ ምን ነበር? ‘‘እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ’’ (ኢዮብ 13፡15)። ‘‘ራቁቴን ከእናቴ ማኅፀን ወጥቻለሁ፥ ራቁቴንም ወደዚያ እመለሳለሁ እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን’’ (ኢዮብ 1፡21)። በሕይወቱ ላይ ይህ ክፉ ነገር እንዲደርስ እግዚአብሔር ለምን እንደፈቀደ ኢዮብ ምንም ግንዛቤ አልነበረውም። ነገር ግን እግዚአብሔር መልካም እንደሆነ ስለሚያውቅ እምነቱን በእግዚአብሔር ላይ ጣለ። የነገሩም ዋነኛ ጉዳይ ይኸው ነው – በእንደዚህ አይነት ወቅቶች የእኛም ምላሽ እንዲሁ ሊሆን ይገባል።

ለምን ክፉ ነገር በመልካም ሰዎች ላይ ይደርሳል? ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምላሹ – በዚህ ምድር ላይ ምንም አይነት ‘መልካም’ ሰው የለም የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችን ከሃጢአት በታች እንደወደቅን፣ በሃጢአት እንደተበከልን በተደጋጋሚ ይነግረናል (መክብብ 7፡20፤ 1ዮሐንስ 1፡8)። በምድር ላይ መልካም ነገር ገንዘቡ የሆነች፣ ኃጢአትንም የማያደርግ ሰው አለመኖሩን ሮሜ 3፡10-18 በግልጽ ያሳየናል፣ ‘‘ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ በአንድነትም የማይጠቅሙ ሆነዋል፤ ቸርነት የሚያደርግ የለም፥ አንድ ስንኳ የለም። ጕሮሮአቸው እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፥ በመላሳቸውም ሸንግለዋል፤ የእባብ መርዝ ከከንፈሮቻቸው በታች አለ፤ አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል፤ እግሮቻቸው ደምን ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው፤ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው ይገኛል፥ የሰላምንም መንገድ አያውቁም። በዓይኖቻቸው ፊት እግዚአብሔርን መፍራት የለም።’’ በዚህ ምክንያት በዚህ ምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው በአሁኑ ሰአት ሊያገኝ የሚገባው አንድ እና ትክክለኛ ነገር ቢኖር ወደ እቶን እሳት መጣል ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒው በሆነ መንገድ በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፋት እያንዳንዷ መልካም ሰከንድ የእግዚአብሔር ምህረት እና ፀጋ ውጤት ናት እንጂ የተገባን ሆና አይደለም። በዚህች ምድር ላይ የምንቀበለው ትልቁ ክፉ ነገር በሲኦል ልንቀበለው ከነበረው ታላቅ መከራ ጋር ሲተያይ የአግዚአብሔርን ምህረት አሳንሰን እንድናይ ሊያደርገን አይገባም።

እናም፣ ጥያቄው ሊሆን ይገባ የነበረው – ‘‘ለክፉዎች ለምን እግዚአብሔር መልካም ነገር እንዲሆንላቸው ፈቀደ?’’ የሚል ነበር። ሮሜ 5፡8 እንዲህ ይላል፣ ‘‘ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል’’። እርሱ የእኛ  ክፋት፣ ሃጢአትና ጠማማነት ሳያግደው ልጁን ስለእኛ ሲል ለሞት አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ ይወደናል (ሮሜ 6፡23)። ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኝ የምንቀበለው (ዮሐንስ 3፡16፤ ሮሜ 10፡9) ከሆነ፣  ሃጢአታችን ይቅር ይባልልናል፣ በመንግስተ ሰማይም የዘላለም ቤት ይኖረናል (ሮሜ 8፡1)። ይህ የሚገባን ስጦታ አልነበረም። ይገባን የነበረው ገሃነመ እሳት ነበር። ነገር ግን እኛን ስለመውደዱ ምክንያት እምነታቸውን በኢየሱስ ላይ ባደረጉ ሁሉ ላይ ዘላለማዊ ሕይወትን አዟል።

የም ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ክፉ ነገሮች ሊያገኛው አይገባቸውም በምንላቸው ሰዎች ላይ ሲደርሱ ይታያል። እነዚህ ነገሮች ባንረዳቸውም እንኳ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ ውስጥ ፋይዳ እንዳላቸው  ልናምን ይገባል። በሕይወታችን ላይ የመጣው ነገር ምንም ሆነ ምን፣ እግዚአብሔር መልካም፣ ፍቅር እና መሃሪ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም። ልንገነዘባቸው የማንችላቸው ጉዳዮች ሲገጥሙን የእግዚአብሔርን መልካምነት ከመጠራጠር ይልቅ ልንታመንበት ይገባል። ‘‘በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል’’ (ምሳሌ 3፡5-6)።

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading