ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ምላሽ አለው። በመጀመሪያ ደረጃ ይህንንም ሆነ ሌሎችን መነፈሳዊ ጥያቄዎችን ስንመልስ በዘፈቀደ በራሳችን ግምትና አመክኗዊ ሃሳብ ላይ ተደግፍን መሆን የለበትም። ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ገለልተኛ አድርጎ በራሱ ልምምድ እና አመክኗዊ እውቀት ላይ በመደገፍ የሚደርስበት ማንኛውም መደምደሚያ ከንቱ ነውና። ማን የእግዚአብሔር ልጅ መሆን እንዳለበት መወሰን የሰው ድርሻ አይደለም። ይህ የፈጣሪ ውሳኔ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደሆኑ በግልጽ ይናገራል “የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና… ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል” (ቆላስይስ 1:16)። እግዚአብሔር መላውን ዓለም እንደሚወድም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” (ዮሐ 3:16)። እናም በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ልጅነት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ መብት ወይም ስልጣን ነው ብለን ስንደመድም እግዚአብሔር በፍጥረቱ ላይ ያለውን መብት ወይም ለፍጥረቱ ያልውን ፍቅር ፈጽሞ የሚጻረር አለመሆኑን በማስመር ነው።
የእግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ አባትነት
እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ባለቤት ከመሆኑ አኳያ ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ የፍጥረት ሁሉ አባት ተብሎ ተጠቅሷል። ይህ እንግዲህ፣ ሄንሪ ፎርድ “የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ አባት” ወይም ጆርጅ ዋሽንግተን እና ጆን አዳምስ “የዩናይትድ ስቴትስ መስራች አባቶች” ብለን እንደምንጠራቸው ማለት ነው። ይህ ግን ፍጥረቱ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የወዳጅነት አንድነት ወይም ቤተሰባዊ ሕብረት እንዳላቸው አያረጋግጥም። እግዚአብሔር የፍጥረት ሁሉ ባለቤት መሆኑን ያረጋግጣል እንጂ። የእግዚአብሔር አባትነት ከሰው ልጅ ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን ክግኡዙ ፍጥረት ጋር በተያያዘም ተገልጿል፣ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ (ያዕቆብ 1:17)። በነዚህ አውዶች የተጠቀሰው የእግዚአብሔር አባትነት የፍጥረት ሁሉ ባለቤት መሆኑን የሚያሳይ እንጂ ፍጥረቱ ከእርሱ ጋር ያለውን ሕብረት ወይም ወዳጅነት አያመለክትም።
የእግዚአብሔር የእስራኤል ሕዝብ የቃል ኪዳን አባትነት
በብሉይ ኪዳን ውስጥ፣ እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያለው የቃል ኪዳን ግንኙነት በአባት/ልጅ ቋንቋ ተገልጿል። እግዚአብሔር እስራኤልን “የበኵር ልጄ ነው” (ዘጸአት 4:23) በማለትና ራሱን ደግሞ “የእስራኤል አባት” ( ኤርምያስ 31:9) በማለት ለነቢያቱ ገልጿል። የእስራኤል ሕዝብ በግብፅ ባሪያዎች ነበሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር ልዩ የሆነ አባታዊ ፍቅር በማሳየት ከባርነት ቀንበር ዋጅቶ የራሱ አደረጋቸው።
ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ አወጣችሁ፥ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። (ዘዳ. 7:6-8)
የእስራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር መንገድ በሳቱ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል እንዲህ ብሎታል፦
እርሱም እንዲህ አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ። እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው። (ሕዝ. 2:3-4)
እግዚአብሔር ሌሎችን አማልክት የሚያመልኩትን አሕዛብ ሲያጠፋ እስራኤላውያንን ግን የኪዳን ፍቅሩን በማስብ እንዴት እንደታደጋቸው በነቢዩ ሚልክያስ አማካኝነት እንዲህ በማለት ያስታውሳቸዋል፦
“እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር…” ሚል 1:6
ሚልክያስ 1:10 ላይ፣ “ለሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለምን? አንድ አምላክስ የፈጠረን አይደለምን?” የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል በመጥቀስ አንዳንድ ሰዎች፣ እግዚአብሔር ለፈጠረው ለእያንዳንዱ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ አባት ነው ሲሉ ይሰማሉ። ነገር ግን ይህ ያቃሉን አውዳዊ አገባብ ካለመገንዘብ የተነሳ እንጂ በክፍሉ ላይ ሚልክያስ የእግዚአብሔር አባትነት ለእስራኤላውያን መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፤ ቀጣይ ቁጥሮችም ያንኑ ያብራራሉ (ሚል 1:11-12)
የልጅነት መብት ለክርስቲያኖች (ለአማኞች)
ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቶቹ መግቢያ ላይ፣ “እግዚአብሔር አባታችን” እያለ ሲጀምር ይህ የእግዚአብሔር አባትነት የሚመለከተው አማኞችን እንደሆነ ግልጽ ነው፦
“በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ በሮሜ ላላችሁት ሁሉ፥ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” ሮሜ. 1:7
“ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።” 1ቆሮ. 1:3
ይህም ልጅነት የተገኘው በክርስቶስ ባገኘነው ቤዛነት በኩል እንደሆን በገልጽ ይናገራል፦
“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ።” ገላ. 4:4-5
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው የሚጠሩት ዳግም ከመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ አማኞች ብቻ እንደሆኑ የሚከተሉት ጥቅሶች ያብራራሉ፦
ዮሐ. 1:12-13 “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።”
ዮሐ. 11:52 “ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ።”
ሮሜ. 8:15-16 “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።”
1ዮሐ 3:1-10 “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። …ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም።….ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ አይችልም። …”
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የጠፉት ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው አይጠሩም ኤፌሶን 2:3 እንደሚናገረው ከመዳናችን በፊት የእግዚአብሔር ልጆች ሳንሆን “ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች” ነበርን። ሮሜ 9:8 “የሥጋ ልጆች የሆኑ የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም” ይላል። ቅዱሱን የወንጌል መልእክት የሚቃወሙ አባታቸው እግዚአብሔር እንዳልሆነ ኢየሱስ ከፈሪሳውያን ጋር ባደረገው ውይይት ውስጥ በግልጽ እናያለን፦ “ኢየሱስም አላቸው፦ እግዚአብሔርስ አባታችሁ ከሆነ በወደዳችሁኝ ነበር፤ እኔ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁና፤ እርሱ ላከኝ እንጂ ከራሴ አልመጣሁምና” (ዮሐ. 8:42)። በአንጻሩ መልእክቱን ስለተቃወሙ የማን ልጆች እንደሆኑ ሲነግራቸው በዚሁ ከፍለ ውስጥ እናነባለን፦ “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ” (ዮሐ. 8:44)። በክርስቶስ አምነው ያልዳኑ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው እንደማይጠሩ የሚከተለው ጥቅስ ይነግረናል፣ “የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች በዚህ የተገለጡ ናቸው፤ ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም” (1ዮሐ. 3:10)።
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ለመጠራት መብት ወይም ስልጣን ያገኘነው በክርስቶስ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካገኘነው ሕብረት የተነሳ ነው፣
“እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ። ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ” ገላ. 4፡5-7።
“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን” ኤፌ. 1:5።
ይህ ሃሳብ በሮሜ መልእክት ውስጥም በግልጽ ቀርቧል፣
“በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ. 8:14-17)።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የሚከተሉት ጥቅሶች በምን በኩልና በማን ምክንያት የእግዚአብሔርን ልጆች መሆን አንደምንችል ይነግሩናል፣
“በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና” (ገላ. 3:6)።
“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን” ኤፌ. 1:5።