ስለ ሮሜ መልዕክት ማወቅ ያለብዎ

መግቢያ
ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ የሮሜን መልዕክት ጨምሮ ቢያንስ 13 የአዲስ ኪዳን መልእክቶችን ጽፏል። በርካታ ተስነ-መለኮት ምሁራን እንደሚስማሙበት፣ የሮሜ መልዕክት ጥልቅ በሆኑ ስነ መለኮታዊ ሃስቦች የታጨቀ መጽሐፍ ነው። መልዕክቱ፣ የድነትን (የመዳንን) መንገድ እና ውጤቶች በጥልቀትና በስፋት ይዳስሳል፤ እስራኤል ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነትና ስለሌሎች በርካት ሃሳቦች ያወሳል።

ስለ ጸሃፊው ጥቂት እውነታዎች
1. ማን ጻፈው? ጸሃፊው ጳውሎስ ነው። የጠርሴሱ ሳውል በመባልም ይጠራል (ሐዋ. 9፡11)። ይህ ሳይታክት የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን በባዶ ሃይማኖታዊ ቅናት በመነሳሳት ያሳድድ የነበረ ሰው (ሐዋ. 8፡3፣ 22፡5፣ 19፣ 26:11፣ ገላ. 1፡13) ጌታ ኢየሱስን በደማስቆ መንገድ ላይ በብርሃን ከተገናኘና ሕይወቱ ከተለወጠ በኋላ (ሐዋ. 9፡3-9)፣ ታላቅ ሚስዮናዊ፣ የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተካይ፣ የእልፍ ነፍሳት አስተማሪና መካሪ፣ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ታላቅ የሃይማኖት ምሁር እና የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ግማሽ ያህል ሊሆኑ የተቃረቡ መልዕክቶችን ለመጻፍ የበቃ ሰው ሊሆን ቻለ።

2. ቅዱስ ጳውሎስ የትኞቹን ቅዱሳት መጻሕፍት ጻፈ? የሮሜ መጽሐፍ፣ 1ኛ እና 2ኛ ቆሮንቶስ፣ ገላትያ፣ ኤፌሶን፣ ፊልጵስዩስ፣ ቆላስይስ፣ 1ኛ እና 2ኛ ተሰሎንቄ፣ 1ኛ እና 2ኛ ጢሞቴዎስ፣ ቲቶ፣ ፊልሞና

3. የሮሜ መልዕክት መቼ እና የት ተጻፈ?
ከቆሮንቶስ፣ ለሮሜ ሰዎች፣ በ 57 ዓ.ም

4. ለምን እና ለማን?
የመልዕክቱ ቀዳሚ ተደራሲያን (ተቀባዮች) በሮሜ የነበሩ ክርስቲያኖች ሲሆኑ የመልዕክቱ ዋነኛ አላማም ታላቁን የድነት ርዕሰ ጉዳይ አብራርቶ ማሳየት ነው።

በመልዕክቱ የተካተቱ ሌሎች ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች
1. እግዚአብሔር በሰው ዘር ሁሉ ላይ (በአይሁድም ሆነ በአሕዛብ) ላይ ስለቀጠረው ፍርድ፣
2. መላውን ዓለም በፊቱ በደለኛ አድርጎ አፍ የሚያዘጋ የእግዚአብሔር መለኮታዊ ጽደቅ፣
3. ጽድቅ በእምነት፤ ከአብርሃም እና ከዳዊት ሕይወት አንጻር፣
4. የጽድቅ ውጤቶች፤ በአዳምና በክርስቶስ ሕይወት ንጽጽር ሲታይ፣
5. ወደ ቅድስና የሚያመሩ ሦስት ትእዛዞች-(ሀ) ማወቅ፣ (ለ) መቁጠር፣ እና (ሐ) ማቅረብ፣
6. የእግዚአብሔር ሕግ፣ ከአማኞች እና አማኝ ካልሆኑ ሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት፣
7. የአማኝ አዲስ አቋም እና በክርስቶስ ውስጥ ስላለው የወደፊት ዕጣ፣
8. የእስራኤል ቅድመ ምርጫ፣
9. የእስራኤል በአሁን ጊዜ በእግዚአብሔር ተጥላ መገኘት፣
10. የእስራኤል የወደፊት ዳግም ተሃድሶ፣
11. አማኝ – (ሀ) ከራሱ አካል (ለ) ከስጦታዎቹ (ሐ) ከአማኞች እና (መ) ካልዳኑ ሰዎች ጋር በተያያዘ ስላለበት ሃላፊነት፣
12. አማኝ – (ሀ) ስለ መንግሥት (ለ) ስለ ህብረተሰብ እና (ሐ) ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር በተያያዘ ስላለበት ሃላፊነ፣ት
13. ደካሞ አማኞችን በተመለከት የብርቱ አማኝ ሃላፊነት፣
14. አማኝ ሌላውን እንጂ ራሱን ደስ ሊያሰኝ እንደማይገባ እና የጳውሎስ የወደፊት የጉዞ ዕቅድ፣
15. ጳውሎስ ሰላምታ በሮም ለሚኖሩ ወዳጆቹ እና የጳውሎስ ምክር ለሮም ቤተ ክርስቲያን ችግር ፈጣሪዎች።

የሮሜ መልዕክት ዋነኛ ሰዎች
1. ጳውሎስ፣ የሮሜና እና ቢያንስ 12 ሌሎች የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ጸሃፊ፤ የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ተካይ፣
ወንጌላዊ፣ ሚስዮናዊ እና ምናልባትም ከሁሉም ሐዋርያት ሁሉ ታላቅ ሊሆን የቻለ አገልጋይ፣
2. አብርሃም፣ በብሉይ ኪዳን ጽድቅ ያለግርዘት ማግኘት ስለመቻሉ ጳውሎስ በምሳሌነት የጠቀሰው ታላቅ የእምነት ሰው፣
3. ዳዊት፣ በብሉይ ኪዳን ጽድቅ ከሙሴ ሕግ ውጭ ማግኘት ስለመቻሉ ጳውሎስ በምሳሌነት የጠቀሰው ታላቅ የእምነት ሰው፣
4. ይስሐቅ፣ ያዕቆብ፣ ሙሴ እና የግብጽ ፈርዖኖች፣ የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት ለማስረዳት ጳውሎስ የጠቀሳቸው ሰዎች
5. ፌቤን፣ የሮሜን ደብዳቤ በሮም ለነበረች ቤተክርስትያን እንድታደርስ በአደራ የተሰጣት ፈሪሃ እግዚአብሔር የነበራት ሴት

የሮሜ መልዕክት ልዩ ባህሪያት
1. የሮሜ መልዕክት የክርስትና እምነት ስነመለኮት የተሟል ማጠቃለያ ነው ማለት ይቻላል። ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ ውስጥ ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍ የጠቀሳቸው ጥቅሶች በድምሩ በተቀሩት 12 መልዕክቶቹ ውስጥ ከጠቀሳቸው የብሉይ ኪዳን ጥቅሶች በቁጥር ይበልጣሉ። ይህም፣ ብሉይ ኪዳን ወንጌልን ለመረዳት ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ያሳያል። ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ ከ 57 ያላነሱ የብሉይ ኪዳን ክፍሎችን ጠቅሷል።
2. የሮሜ መልዕክት፣ በአጭሩ ምን ማመን እንዳለብን (ምዕራፍ 1-11) እና እንዴት መኖር እንዳለብን (ምዕራፍ 12-16) ያስረዳናል።
3. የሮሜ መልዕክት ከ 1ኛ የቆሮንቶስ መልዕክት ቀጥሎ የጳውሎስ ረጅሙ ደብዳቤ ነው።
4. የሮሜ መልዕክት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ምዕራፎች በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ እጅግ አስገራሚ ስለሆነው ችሎት ያስነብቡናል።
5. የሮሜ መልዕክት ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት መጻሕፍ ይልቅ በርካታ ታላላቅ ሥነ-መለኮታዊ ቃላቶችን እና ጽንሰ-ሃቦችን ያብራራል። ለአብነት የሚከተሉትን ይመልከቱ፦
• ጽድቅ (5፡1)
• ቅድስና (6፡1-13)
• እርካታ (3፡23-25)
• ክብር (8፡16-23)
• መጠበቅ (8:35-39)
• ምልጃ (8፡26-27)
• መለወጥ (12፡1-2)
6. የሮሜ መልዕክት በአማኙ ሕይወት ውስጥ የሚያድረው መንፈስ ቅዱስ ስለ አማኙ እንደሚጸልይ (8:26-27) የሚናገር ብቸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክት ነው።
7. ይህ መጽሐፍ ስለ ጽድቅ የሚያወራ መጽሐፍ ነው። እግዚአብሔር ጻድቅ እንደሆነ ከሰውም ጽድቅን እንደሚሻ፣ ከሰው የሚሻውን ጽድቅ ደግሞ መልሶ ራሱ እንደሚሰጥ፣ ጽድቅ ምን ማለት እንደሆነ፣ ጽድቅ ምን ማለት እንዳልሆነ፣ ለማን እንደሚያስፈልገው፣ ለምን እንደሚያስፈልግ፣ የት እንደሚገኝ እና የት እንደማይገኝ በሮሜ መልዕክት ውስጥ ተብራርተው እናገኛለን።
8. የሮሜ መጽሐፍ በክርስቶስ እና በአዳም መካከል ያለውን ታላቅ ንጽጽር ያቀርባል (5፡12-21)።
9. የሮሜ መጽሐፍ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ስለነበረው፣ ስላለውና ስለሚኖረው የቀደሞ የአሁን እና የወደፊት ግንኙነት በተመለከተ በጣም ሰፊ ማብራሪያን ይሰጠናል (ምዕራፍ 9-11)።
10. በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች እጅግ በጣም የሚያፅናኑ ጥቅሶችን የያዘ መጽሐፍም ነው (8፡28)።
11. የሮሜ መልዕክት የጾታ ብልግናን እጅግ በጣም ከባድ የሆነ እንደሆነ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው (1:24፣ 32)።
12. የሮሜ መልዕክት የጽድቅን ውጤቶች በተመለከተ ዝርዝር ዘገባ ያቀርባል (5፡1-11)።
13. የሮሜ መልዕክት የእግዚአብሔርን እጅግ የላቀ ጥበብ ሃሳብ ያስተላልፋል (11፡33-36)።
14. የሮሜ መልዕክት መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ አለም መንግስት ጋር በተያያዘ የአማኝ ሀላፊነት እና ግንኙነት ምን መምሰል እንዳለበት በዝርዝር ካስቀመጣቸው ሁለት መልዕክቶች መካከል አንዱን ይዟል (13፡1-7፣ 1ኛ ጴጥ. 2፡13-17)።
15. አማኝ በክርስቶስ ባገኘው ነጻነት ውስጥ አብሮ የተካተተውን ሃላፊነት ከሚያስረዱት ሁለት የጳውሎስ ትምህርቶች መካከል አንዱ በዚሁ የሮሜ መልክት ውስጥ ይገኛል (14:1-6፣ 13-21፣ 1ቆሮ. 8-10)።
16. ስለክርስቶስ የፍርድ ወንበር ከሚናገሩት የፓውሎስ ትምህርቶች መካክለ አንዱ በሮሜ መልዕክት ውስጥ ተካቶ ይገኛል (14:10-12፣ 1ቆሮ. 3:11-17፣ 2ቆሮ. 5:1-10)።
17. ጳውሎስ በመልዕክቶቹ ውስጥ ካሰፈራቸው ሶስት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዝርዝር ውስጥ አንዱ በዚሁ በሮሜ መልክት ውስጥ ይገኛል (12:3-8፣ 1ቆሮ. 12:4-11፣ ኤፌ. 4:11-16)።
18. ጳውሎስ እና ጴጥሮስ በሰማዕትነት የተገደሉት በዚህች ከተማ ውስጥ ነው (2ጴጥ. 1፡14፣ 2ጢሞ. 4፡6-8)።
19. የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ምናልባት በጴንጤ ቆስጤ እለት (በበዓለ ኀምሳ እለት) ጌታን በተቀበሉ አማኞች የተመሰረተች ሳትሆን አትቀርም (ሐዋ 2፡10)።
20. የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ከአይሁድ እና አሕዛብ የተውጣጡ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን አሕዛብ ነበሩ (1:13፣ 11:13፣ 15:16)።
21. ጳውሎስ ይህችን ቤተክርስቲያን ለመጎብኘት ይጓጓ እንደነበር ተገልጿል (1:8-11)።
22. እግዚአብሔርም ጳውሎስ ወደ ሮም እንደሚሄድ አረጋገጠለት (ሐዋ. 23:11)።
23. በዚህ መልዕክት ውስጥ ጳውሎስ ያቃቸው የነበሩትን 26 ሰዎች በስም በመጥራት ሰላምታ ልኳል (ሮሜ 16)።
24. የሮሜ መልዕክት ምናልባትም በሴት እጅ (ፌቤን) ለቤተ ክርስቲያን የተላከ ብቸኛ መጽሐፍ ሳይሆን አይቀርም (16፡1)።

የሮሜ መልዕክት ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትጋር ሲነጻጸር
1. ዘፍጥረት
በዘፍጥረት አብርሃም የእሥራኤል አባት ሲሆን በሮሜ መልዕክት ውስጥ ግን በክርስቶስ ላመኑ ሁሉ አባት ተብሏል (4፡16)።
2. ገላትያ
የገላትያ መልዕክት ከሚያስተላልፈው “መዳን በእምነት” ትምህርት የተነሳ የሮሜ መልዕክት እጥርጥር ተረድጎ በብዞዎች ይወሰዳል።
3. ያዕቆብ
የሮሜ መልዕክት (ለመዳን እምነት ብቻ) የሚለውን የድነትን መሰረት ሲያመለክት የያቆብ መልዕክት ደግሞ የድነትን ፍሬዎች (መልካም ስነምግባራትን) ያሳያል።

የኢየሱስ ስሞች በሮሜ መልዕክት ውስጥ
1. ኢየሱስ ክርስቶስ (1፡1)
2. የዳዊት ዘር (1፡3)
3. የእግዚአብሔር ልጅ (1፡4)
4. ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ (1፡7)
5. ክርስቶስ ኢየሱስ (3፡24)
6. የማስተስረያ መሥዋዕት (3፡25)
7. ኢየሱስ (3፡26)
8. ጌታችን ኢየሱስ (4፡24)
9. የሰራዊት ጌታ (ጌታ ፀባዖት) (9:29)
10. የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ ዓለት (9:33)
11. የሕግ ፍጻሜ (10 4)
12. ነፃ አውጪው (11:26)
13. የሙታንና የሕያዋን ጌታ (14፡9)
14. የእሴይ ሥር (15 12)

ምንጭ፡ ሊበርቲ ዩኒቨርስቲ

በጥያቄና መልሶች በመታገዝ የሮሜ መልዕክትን አብረውን እንዲያጠኑ ተጋብዘዋል! የሚከተለውን ሊንክ ሲጫኑ፣ ወደ ጥያቄና መልሶቹ ፔጅ ይወስዶታል። የሮሜ መልዕክት ጥናት ጥያቄና መልስ – ክፍል 1 (ሮሜ 1:1-17)

2 thoughts on “ስለ ሮሜ መልዕክት ማወቅ ያለብዎ”

  1. Peace be with you This is a wonderful introduction it will lead and incurrage to know the details from book of rome.God bless.

Leave a Reply

%d bloggers like this: