“በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም::” ሮሜ 8:1

መኮነን ማለት በፍርድ ወይም በቅጣት ስር መውደቅ ማለት ሲሆን ከኩነኔ ነጻ መሆን ማለት ደግሞ ከቅጣት/ፍዳ ነጻ መሆን ማለት ነው። ኩነኔ የሌለበት ሰው ለፍርድ የሚያበቃ ጥፋት ያለተገኘበት እና ከተከሰሰበት ወንጀልም ነጻ ሆኖ የተገኘ ማለት ነው። ኮናኙ (ፈራጁ) እግዚአብሔር ተኮናኙ (የሚፈረድበት) ደግሞ የሰው ልጅ በሆነበት በዚህ ትዕይንት ውስጥ ጻድቅ በሆነው አምላክ ፊት ማን ሊጸድቅ ይችላል የሚለው ጥያቄ የሁላችንም ሊሆን ይገባል። ለዚህ ጥያቄ የራሴን መላ ምት ወደጎን ላድርግና መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚሰጠውን ምላሽ አብረን እናንብ፦

ኢዮብ 25፡4 “ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፥ ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ እንዴት ይችላል?”
መክ. 7፡20 “በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና።”
ሮሜ 3:23 “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤”

ኢዮብ፣ ጠቢቡ ሰለሞን እና ቅዱስ ጳውሎስ የጻፉትን ካነበብን በኋላ፣ በራሴ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሆኜ በመገኘት ከኩነኔ ልድን እችላልሁ ብሎ ማሰብ የማይቻል ብቻ ሳይሆን ድፍረትም ይመስለኛል። የእናነተን ምላሽ ለራሳችሁ ልተውና በብዙ መንገድ በእግዚአብሔር ላይ ያመጽኩትን እኔን ግን “ነጻ” የሚለው ቃል እንደማይመለከተኝ አስረግጬ መናገር እችላለሁ። በእግዚአብሔር መመዘኛዎች ሁሉ የኩነኔ ፍርድ የሚገባኝ ሃጢአተኛ/በደለኛ እንደሆንኩ ያለጥርጥር አውቃለሁ። ለእኔ የሚገባው ትክክለኛ ፍርድ “ወንጀለኛ!” የሚለው ብቻ ነው። ኩነኔ ለማንነቴ የሚመጥን ትክክለኛ የፍርድ አለንጋ ነው። ከጻድቁ ፈራጁ እግዚአብሔር አፍ የወጣውና የሰውን ልጅ ሁሉ ከሃጢአት በታች የሚኩንነው ይህ ፍርድ እኔን ብቻ ሳይሆን የአዳምን ዘር ሁሉ እንደሚመለከትም ጥርጥር የለኝም። ከዚህ ኩነኔ በራሱ የሚያመልጥ ጻድቅ/ንጹህ ሰው በምድር የለምና።

ጻድቅ በሆነው አምላክ የፍርድ ወንበር ፊት ያለ ሃጢአት ጻድቅ ሆኖ በድፍረት ሊቀርብ የሚችል አንድ ሰው ብቻ አለ። ይህ ሰው ሃጢአት አላደረገም (ዕብ. 4:15)። የእግዚአብሔርን መመዘኛዎች (ሮሜ 10:4) ሁሉ ሊያልፍ የቻለ ንጹሕ ሰው ነው (ዮሐ. 17:4)። ማንም ሰለ ሃጢአት ሊወቅሰው አይችልም (ዮሐ. 8:46)። ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ይባላል። ኢየሱስ በአብ ፊት ጻድቅ ሆኖ መታየቱ ብቻ አይደለም የታሪኩ ሙሉ ሃሳብ። በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የፍርድ ወንበር የሚቀርቡ ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ ነጻ መሆናቸውም እንጂ (ሮሜ 8:1)። እርሱ ጻድቅና ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም ጻድቃንና ቅዱሳን ተብለው መቆጠራቸውም እንጂ (1ቆሮ. 6:11፣ ሮሜ. 4:11)።

ይህ ነው እንግዲህ፣ “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” ማለት። እዚህ ላይ፣ ኩነኔ የሌለባቸው በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉቱ ብቻ እነደሆኑ አንባቢ ያስተውል!!! በክርስቶስ ኢየሱስ የሌሉ ሁሉ በኩነኔ ውስጥ ይኖራሉ። በክርስቶስ መሆን ማለት በእኔና በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር መካከል ኢየሱስ ጣልቅ እንዲገባ መፍቀድ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ በእግዚአብሔር እና በእኔ መካከል ኢየሱስ መካከለኛ እንዲሆን መፍቀድ ማለት ነው (1ጢሞ. 2:5)። ማለትም፣ እኔ በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት አፌን ዘግቼ (ሮሜ 3:19) ኢየሱስ ስለ እኔ እንዲናገር (ዕብ. 12:24)፣ ስለ እኔ እንዲታይ (ዕብ. 9:28)፣ ስለ እኔ ጥብቅና እንዲቆም (1ዮሐ. 2:1)፣ ስለ እኔ እንዲማልድ (ሮሜ8:33-34) መፍቀድ ማለት ነው።

“በእርሱ (በኢየሱስ) በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።” ዮሐ. 3:18

ልዑል አምላክ እግዚአብሔር የልቦናችንን አይን ያብራ፣ አሜን!

4 thoughts on ““በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም::” ሮሜ 8:1”

  1. Rahel Yeshitila

    ተባረክ : ትልቅ መልእክት ነው:: የኩነኔን ትርጉም ስላብራራህልኝ:: ኩነኔ ግን እስከዛሬ ይመስለኝ የነበረው : አኔ አራሴን በቂ አይደለሁም ህጥያተኛ ነኝ : በእግዚእእብሄር ፊት መቅረብ አልችልኝ ብዬ እራሴን ስኮንን ነበር የሚመስለኝ :: በክርስቶስ ስሆን ግን ያን ሀሳብ እንዳነሳሁት ይገባኝ ነበር:: ለማንኛውም ፀጋውን ይጨምርልህ ::

  2. ራሄል፣

    ጊዜ ወስደሽ እኔን ለማበረታታት ስለጻፍሽልኝ በጣም አመሰግናለሁ። ጽሁፉ ስለጠቀመሽና ቀድሞ የነበረሽን መረዳት ይበልጥ ስላሰፋውም ደስተኛ ነኝ። ይህን ካንቺ መስማቴም ይበልጥ እንድተጋ ይረዳኛል። የጌታ ኢየሱስ ጸጋ ይብዛልሽ። በወንጌል በድረ-ገጽ ላይ የተጫኑ በርካታ ጠቃሚ ጽሁፎችን ለማንበብም ሆነ አዳዲስ ጽሁፎችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጥያቄዎች ሲጫኑ እንዳያመልጥሽ ወይም ዘግይቶ እንዳይደርስሽ ይረዳሽ ዘንድ የሚከተለው ድረ-ገጽ (website) (https://ethiopiansite.com/) ላይ በመሄድ እና የኢ-ሜይል አድራሻሽን ከድረ-ገጹ የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በስተቀኝ በኩል በሚገኘው ሳጥን ውስጥ በማስገባትና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ሰማያዊ ቁልፍ በመጫን የድረ-ገጹ ተከታታይ (follower) እንድትሆኚ በአክብሮት እጋብዛለሁ። ይህን ስታደርጊ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የውድድር ጥያቄዎችና ሌሎች አዳዲስ ጽሁፎች በድረ-ገጹ ላይ በሚለቀቁበት ጊዜ ሁሉ በኢ-ሜል አድራሻሽ መልዕክት የሚደርስሽ ይሆናል።

    የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንቺ ጋር ይሁን።

  3. የተወደድክ የእግዚአብሔር ሰው በእውነት ፀጋ በዝቶልሃል በትምህርቶችህ ተማርክያለሁ ተምርያለሁ የተግባርና ሰምቶ የምያደርግ ያድርገኝ ከድህረ ገጹ ብዙ እማራለሁ ብዬ እጠብቃለሁ ዘመኖችህ ይባረኩ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading