መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው? ተግባሩስ?

1. መንፈስ ቅዱስን አካል/ማንነት የሌለው፣ አንዳች ‹‹አነሳሽ›› ወይም ‹‹ተፅዕኖ ፈጣሪ›› ሃይል አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ማንነት/አካል ያለው እንደሆነ አውቄ ከእርሱ ጋር አብሬ መስራት ይኖርብኛል፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ሐዋ. 5፡3-4 ጴጥሮስም፡- ሐናንያ ሆይ መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለም ሞላ? ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ይህ ነገር ስለምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
1ቆሮ. 2፡10-11
2ቆሮ. 13፡14
ኤፌ. 4፡30
ኢዮብ 33፡4

መንፈስ ቅዱስ አካል/ማንነት አለው፡፡ ተፅዕኖ አድራጊ፣ ወይም ኃይል፣ ወይም አነሳሽ ሳይሆን እግዚአብሔር ነው፡፡ እንደ የልብ ወዳጅ ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህም በላይ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ያለኝ ግንኙነት በብዙ መልኩ በመልካም ትዳር ውስጥ ያለን ቁርኝት ይመስላል፡፡ የትዳር ግንኙነት መገለጫዎች ምንድን ናቸው? መከባበር? መግባባት? አንዱ ሌላውን መንከባከብ?

2. እኔ የእርሱ መቅደስ ነኝ፤ እርሱ በእኔ ውስጥ ይኖራል፡፡

1ቆሮ. 3፡16 የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን?

1ቆሮ. 6፡19-20 ወይስ ስጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በስጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፡፡

እግዚአብሔር የክርስቲያኖች ባለቤት የመሆኑ ጉዳይ፣ በአማኙ እውቅና መስጠት ላይ ያልተመሰረተ እውነታ ነው፡፡ ገሀድ የሆነውን ይህን እውነት ከመቀበል ውጪ የባለቤትነት ድርሻውን ልከለክለውም ሆነ ልሰጠው አልችልም፡፡ አዲስ አማኞች ከዚህ ቀደም ስለ እግዚአብሔር የሳሉት ስዕል ስለማይኖር ብዙውን ጊዜ ይህን እውነት ለመቀበል አይቸገሩም፡፡ በተቃራኒው፣ የሰነበቱ ክርስቲያኖች ግን በእውቀት ደረጃ እውነታውን ቢቀበሉም፣ በሕይወታቸው ተግባራዊ ለማድረግ ሲቸግራቸው ይሰተዋላል፡፡ የባለቤትነት መገለጫዎች ምንድን ናቸው? በባለቤትነት ውስጥ ተቀባይነት የሚያገኙት መብቶች እና ስልጣኖች ምን አይነት ናቸው?

3. የእግዚአብሔር ልጅ ስለ መሆኔ፣ መንፈስ ቅዱስ ማህተሜ (መያዣዬ፣ ዋስትናዬ፣ ማስረጃዬ) ነው፡፡

ሮሜ. 8፡9፣… እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፣ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም፡፡ የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም፡፡

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ሮሜ. 8፡14-16
2ቆሮ. 1፡21-22
2ቆሮ. 5፡5
ገላ. 4፡6
ኤፌ. 1፡13-14
1ዮሐ. 4፡13

መንፈስ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እኔን ስለማዳኑ ማረጋገጫ/ማስረጃ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስን መጠማትና ከእርሱም ምሪትና መመሪያዎች ጋር መተባበር ይገባናል፡፡

4. መንፈስ ቅዱስ በዕለት ተእለት ሕይወቴ ውስጥ ዕቅድ አለው፡፡ ከእርሱ እንድማርና እርሱን አንድታዘዘው ይሻል፡፡ በራሴ ዕቅድ እንድነዳ አይሻም፡፡

መዝ. 139፡16 (አ.መ.ት.) ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍህ ተመዘገቡ።

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ኤር. 10፡23
ኤር. 29፡11
ዮሐ. 14፡16-17
ዮሐ. 14፡26
ዮሐ. 16፡13-15
1ቆሮ. 2፡9-14

የክርስቶስ ደቀ መዝሙር፣ በእግዚአብሔር ዕቅድ ላይ መደገፍ ይኖርበታል፡፡ እግዚአብሔር እንድከተለው እንጂ የእኔ ፍላጎቶች አገልጋይ እንደሆነ አንዳስበው አይሻም። እርሱን ሳላማክር ባወጣኋቸው እቅዶቼ ላይ የይለፍ ማህተም ለማስመታት ብቻ የምፈልገው አድርጌ እንድቆጥረውም አይሻም። የእርሱ እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ ባሰብኩ ቁጥር ሊረዳኝ እንደሚገባው (ግዴታው እንደሆነ) አድርጌ እንድቆጥረውም አይፈልግም፡፡ እርግጥ ነው፣ የቀናትና የወደፊት ጊዜ ጊዜያዊ ዕቅዶች ለማውጣት መከልከል የለብኝም፡፡ ይህን ሳደርግ ግን እግዚአብሔር በማንኛውም ወቅት የእኔን ዕቅዶች ሊቀይራቸው እንደሚችል መዘንጋት የለብኝም፡፡

5. ወደ እግዚአብሔር አብ ይማልድልኛል፣ ፀሎትም ያስተምረኛል፡፡

ሮሜ. 8፡26፣27 እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና።

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ኤፌ. 2፡18
ኤፌ. 6፡17-18
ይሁዳ 20

የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በፀሎት፣ ቃሉን በማንበብ፣ ትምህርቶችን በማዳመጥ፣ ከቅዱሳን ጋር ሕብረት በማድረግ፣ ወዘተ… ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን ንቁና የማይቋረጥ ግንኙነት መጠበቅ አለበት፡፡

6. መንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ አለማቀፋዊ አካል (UNIVERSAL BODY OF CHRIST) ጋር አንድ እሆን ዘንድ አጥምቆኛል፡፡ (ይህ የሚያውራው፣ ስለ ውሀ ጥምቀት ሳይሆን ስለ መንፈስ ጥምቀት ነው)፡፡

ማቴ. 3፡11 እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤

1ቆሮ. 12፡12-13 አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፣ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።

የክርስቶስ ደቀ መዝሙር፣ አንድና ብቸኛ ከሆነችው ቤተክርስቲያን ጋር በመንፈስ ቅዱስ በመተሳሰር አለማቀፋዊ ከሆነው የክርስቶስ አካል ማሕበርተኞች ጋር ያለውን አንድነት ሊረዳ ይገባል፡፡

7. ለማያምኑ ሁሉ፣ ስለ ኢየሱስ እንድመሰክር ሊጠቀምብኝ ይወዳል፡፡

ማር. 13፡11 ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፣ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ዮሐ. 15፡26
ዮሐ. 16፡8-11
ሐዋ. 1፡8

መንፈስ ቅዱስ እኛን በመጠቀም፣ የማያምኑ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶን ወደ ማመን እንዲደርሱ ይረዳቸው ዘንድ ይሻል፡፡ ይህንን ለማድረግ ሁለት ነገሮችን እንድናደርግ ይረዳናል፡፡ አንደኛ ቃሉን በስልጣን እንድንናገር፤ ሁለተኛ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆነውን የኢየሱስን ሕይወት እንድንኖር፡፡

8. ሌሎችን አገለግልበት ዘንድ የሰጠኝን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ(ዎች) ሊጠቀም ይፈልጋል፡፡

ሮሜ. 12፡4-8 በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፣ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፣ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፣ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር።

በተጨማሪ ተከታዮቹን ጥቅሶች ይመልከቱ፡-
ማር. 9፡35
1ቆሮ. 12፡4
1ቆሮ. 12፡7-11
ፊል. 2፡3-4
1ጴጥ. 4፤10-11

በእግዚአብሔር ዕቅድና አላማ ውስጥ እያንዳንዱ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ልዩ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች መካከል የትብብር ሥራ እና ተሳትፎን መፍጠር ይፈልጋል፡፡ (ኢየሱስ በዮሐ. 13፡35 ላይ «እርስ በእርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀመዛሙርቴ እንደሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚያ ያውቃሉ›› ብሏል፡፡) ሌሎች አማኞች የእኔን ፍላጎት ብቻ ሲያሟሉ እንዳይ አይሻም፡፡ መንፈስ ቅዱስ አማኞችን በእኔ ውስጥ ሆኖ ሊያገለግላቸውም ይፈልጋል፡፡

9. እርሱ ብቻውን፣ እኔ ውስጥ እና በእኔ ውስጥ፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ይሠራል፡፡

ዮሐ. 6፡63 ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።

2ቆሮ. 3፡6 እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።

መክ. 3፡14 እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ።

ዘላለማዊ የሆነ ዋጋ ያለው ማንኛውም ነገር የሚመነጨው ከመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡

1 thought on “መንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው? ተግባሩስ?”

  1. Prophet amaru fetala

    አመሰግናለሁ በጣም አስተማረ የሆነው የህይወት ቃል ባጭሩ ትሚርት መሰጠት መልካም thanks to much !!!

Leave a Reply

%d bloggers like this: