እያንዳንዱ አዲስ አማኝ ሊያውቃቸው የሚገቡት አራት ጠቃሚ አሳቦች

1. ኢየሱስን እንደ አዳኝ ማወቅ፡ – ኢየሱስ፣ ኃጢአትህን ሁሉ አስተሰርዮልሃል፡፡ በኢየሱስ የቤዛነት አገልግሎት ማለትም በአንተ ምትክ መሞት ምክንያት አሁን የዘላለም ሕይወት አለህ፡፡

ዮሐ. 5፡24 እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም፡፡

ሮሜ. 4፡7-8 ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው፡፡

ሮሜ. 8፡1 እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፡፡

ሮሜ. 8፡16 የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡

ሮሜ. 8፡31 እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?

ሮሜ. 10፡13 የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና፡፡

1ዮሐ. 5፡11-13 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው፡፡ ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም፡፡ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡

2. ኢየሱስን እንደ ጌታ ማወቅ፡- በክቡር የኢየሱስ ደም በታላቅ ዋጋ ተገዝተሃል፡፡ ከእንግዲህ የራስህ አይደለህም፡፡ አፍቃሪ ልብ ባለውና ያንተን ስኬት በሚሻ ፈጣሪ ስር እንደምትገዛ ማወቅህ ኢየሱስን እንደ ጌታ የመቀበል ውሳኔህ አስጊ ሳይሆን መድህን እንደሆነ እንድትገነዘብ ይረዳሃል፡፡

1ቆሮ. 6፡19-20 ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፡፡

1ቆሮ. 7፡22-23 ባሪያ ሆኖ በጌታ የተጠራ የጌታ ነጻ ነውና፤ እንዲሁም ነጻ ሆኖ የተጠራ የክርስቶስ ባሪያ ነው፡፡ በዋጋ ተገዝታችኋል፤ የሰው ባሪያዎች አትሁኑ፡፡

ሮሜ. 14፡7-8 ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፣ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፡፡ እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን፡፡

3. እግዚአብሔር አንተን በዚህ ምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ ልዩ አድርጎ እንደፈጠረህ እንድታውቅ ይሻል፡፡ እግዚአብሔር ኮፒ ልጆች የሉትም፡፡ ሁሉም ልዩ ናቸው፡፡ አንተም ልዩ ነህ፡፡ ልዩ ስለሆንክ እግዚአብሔር በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚዘልቅ ለአንተ የተለየ እቅድ አለው፡፡ ሕይወትህን በማስተዳደር ይህን እቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋል፡፡

መዝ. 139፡16 ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ፡፡

ኤር. 29፡11 ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም፡፡

ምሳሌ 3፡5-6 በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል፡፡

4. መንፈስ ቅዱስ፣ እርሱ ብቻውን ይህን ልዩ የሆነ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ሚገልጽልህና በዚያ መንገድ ላይ ሊመራህ የሚችለውም እርሱ ብቻ እንደሆነ እንድታውቅ ይሻል፡፡

ኤር. 10፡23 አቤቱ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም፡፡

ኢሳ. 55፡8-9 አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር፡፡ ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው፡፡

1ቆሮ. 2፡9-14 ነገር ግን፡፡ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው ተብሎ እንድተጻፈ እንዲህ እንናገራለን፡፡ መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ስንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው፡፡ በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን ማንም አያውቅም፡፡ እኛ ግን ከእግዚአብሔር እንዲያው የተሰጠንን እናውቅ ዘንድ ከእግዚአብሔር የሆነውን መንፈስ እንጂ የዓለምን መንፈስ አልተቀበልንም፡፡ ….

መዝ. 32፡8 አስተምርሃለሁ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ ዓይኖቼን በአንተ ላይ አጠናለሁ፡፡

ዮሐ. 14፡26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል፡፡

ዮሐ. 16፡13-15 ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል፡፡ እርሱ ያከብረኛል ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና፡፡ ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፡፡ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: