በመጨረሻው ዘመን እስራኤል በሙሉ ይድናሉ ወይ? ሮሜ 11

“በመጨረሻው ዘመን እስራኤል በሙሉ ይድናሉ ወይ?” ለሚለው ጥያቄ፣ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ፣ “…እስራኤል ሁሉ ይድናሉ፤” ሲል ምላሽ ተጥቷል (ሮሜ 11:26 ላይ)፡፡ ከዚህ የጳውሎስ ቀጥተኛ መልስ ካር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ፣ “እስራኤል የሚለው ስያሜ ማንን ነው የሚያመለክተው?” የሚል ነው፡፡ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች “እስራኤል” የሚለው የቃል አጠቃቀም ቀጥተኛ ትርጉም ሊሰጠው አይገባም፤ ምክንያቱም ቃሉ በስጋ እስራኤላውያን የሆኑትን ሰዎች የሚያመለክት ሳይሆን እስራኤልን የተካችውን ቤተ ክርስቲያንን ነውና ይላሉ፡፡ በተቃራኒው፣ በብሉይ ኪዳኑ ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጡት የተስፋ ቃሎች፣ ቃል በቃል (literally) በስጋ እስራኤላውያን የሆኑ አይሁድን የሚመለከቱ እንደሆነ የሚከራከሩቱ ደግሞ፣ እስራኤላውያን በመጨረሻው ዘመን ላይ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን የድነት መንገድ በመቀበል ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ እንደሚፈጽሙና በብሉይ ኪዳን እነሱን አስመልክቶ የተሰጠው መንፈሳዊም ሆነ መልከዓ ምድራዊ ተስፋዎች ተፈጻሚነት እንደሚያገኙ ያምናሉ፡፡ ቀደም ብለን ያየናቸውና በመተካት ስነ መለኮት (replacement theology) የሚያምኑ ሰዎች፣ በዚህ ዘመን፣ ቤተክርስቲያን እስራኤልን ሙሉ በሙሉ በመተካቷ እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጠውን ተስፋ የምትወርሰው ቤተ ክርስቲያን ናት ይላሉ፡፡ ቃል ኪዳኖቹም በመልከዓ ምድራዊ ሳይሆን በመንፈሳዊ ይዘታቸው አንጻር ተፈጻሚነት ያገኛሉ ብለው ያስተምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የመተካት ስነ መለኮት የሚያስተምረው፣ እስራኤል በቤተ ክርስቲያን ተተክታለች፤ በአሁኑ ሰዓተ ቤተክርስቲያን፣ “አዲሲቱ እስራኤል” ነች በማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ በስጋ እስራኤል የሆኑ አይሁዳውያን ከዚህ የኪዳን ተስፋ ተቆርጠዋል፡፡ እናም በስጋ እስራኤላውያን የሆኑ አይሁድ በብሉይ ኪዳን ተስፋ የተገባላቸውን የተስፋዪቱን ምድር አይወርሱም፣ የሚል አስተምህሮ አላቸው፡፡

እስራኤል ለሚለው ስያሜ ቀጥተኛ ትርጉምን የሚከተለው አስተሳሰብ፣ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ሚዛንን የሚደፋ ስለሆነ ከላይ የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የተሻለ አቀራረብ መሆኑን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ ምክንያቶቹም እንደሚከተለው ይነበባሉ፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በስፋት የሚዘግበው የሮሜ መልዕክት ምዕራፍ 11 ከቁጥር 16 እስከ 24፣ እስራኤልን እና ቤተ ክርስቲያንን ለይቶ በግልጽ ያቀርባል፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ፣ “የተፈጥሮ ቅርንጫፎች” የተባሉት አይሁድ ሲሆኑ “የበረሀ ወይራ” የተባሉት ደግሞ በክርስቶስ ያመኑ አህዛብ ናቸው፡፡ “የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹ” አይሁድ፣ ከአለማመናቸው የተነሣ ተሰበሩ፤ “የበረሀ ወይራዎቹ” አማኝ አሕዛብ ደግሞ ከእምነት የተነሣ ቆሞ (ተጣበቁ) ይላል፡፡ ይህ ሂደት፣ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑትን አይሁድ በማስቀናት ወደ ራሳቸው ወይራ ዛፍ እንዲገቡ ማለትም በክርስቶስ እንዲያምኑ በማድረግ ተስፋ የተገባላቸውን ምድር እንዲወርሱ እንደሚያደርጋቸው ከዚህ በታች የምንመለከተው የሮሜ መልዕክት ያመለክታል (ሮሜ 11፡26-29)፡፡ እዚህ ላይ፣ “የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹ” አይሁድ “ከበረሀ ወይራዎቹ” አሕዛብ ተለይተው የቀረቡ መሆናቸውን ልብ ይሉዋል፡፡

ጳውሎስ፣ የ ኢሳይያስ 59:20-21፣ ኢሳይያስ 27፡9 እና ኤርምያስ 31፡33-34 ትንቢቶችን በመጥቀስ እንዲህ ይላል፦ “እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኛነትን ያስወግዳል። ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው። በወንጌልስ በኩል ስለ እናንተ ጠላቶች ናቸው፥ በምርጫ በኩል ግን ስለ አባቶች ተወዳጆች ናቸው፤ እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና፡፡” ሮሜ 11፡26-29፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ፣ ጳውሎስ የእስራኤልን ጥሪ “የማይቀለበስ” ባሕሪይ ያስገነዝበናል (ሮሜ 11፡12)፡፡ ኢሳይያስ በመጽሐፉ፣ አንድ ቀን “የእስራኤል ቅሬታ” “እግዚአብሔር የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ” ተብለው እንደሚጠሩ ተንብዩአል (ኢሳ 62፡12)፡፡ እስራኤል አሁን ያለችበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ወደፊት የሚመጡት የእስራኤል ቅሬታዎች ንስሃ በመግባትና በእምነት የሆነውን የእግዚአብሔርን ስጦታ (ክርስቶስን) በመቀበል የተገባላቸውን ተስፋ ይወርሳሉ (ሮሜ 10፡1-8፣ 11፡5)፡፡ ይህም ሁኔታ፣ ሙሴ የእስራኤል ምድር ለዘለቄታው ተመልሶ የአይሁድ ሕዝብ እንደሚሆን ከተናገረው ትንቢት ጋር ይገጣጠማል (ዘዳግም 30፡1-10)፡፡

ጳውሎስ በሮሜ 11፡26 ላይ እስራኤላውያን “ይድናሉ” ሲል፣ የእስራኤል ቅሬታ በመጨረሻው ዘመን አዳኙን እና መሲሁን በመቀበል “ከኃጢአታቸው ነፃ እንደሚወጡ” (ቁ .27) ሲያመለክት ነው፡፡ ሙሴ በዘዳግም 30፡6 ላይ እንዲህ አለ፦ “በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል”፡፡ ለአብርሃም ተስፋ የተገባለት ምድራዊ ርስት እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን በመጨረሻው ዘመን የሚፈጽመው የተስፋ ቃል ይሆናል (ዘዳግም 30፡3-5)፡፡

እስራኤል የሚድንበትን የድነት ዝርዝር ሃሳቦች በዘካርያስ ምዕራፍ 8 እስከ 14 እና ራዕይ ምዕራፍ 7 እስከ 19 ምንባቦች ውስጥ በስፋት ተካትተው እናነባለን፡፡ እነዚህ ምዕራፎች፣ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወቅት ስለምትኖረው መጻኢዋ እስራኤል ወደ እምነት መመለስ ይናገራሉ፡፡ የመጽኢቱ እስራኤል ቅሬታዎችን ወደ እምነት መመለስ የሚገልጸው ቁልፍ ጥቅስ ዘካርያስ 12፡10 ነው፦ “በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፤ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፤ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኀዘን ያዝኑለታል”፡፡ ይህም የሚሆነው ዳንኤል በተነበየው የመከራ ዘምን መጨረሻ ላይ ይሆናል (ዳንኤል 9፡24-27)፡፡ ሐዋርያው ​​ዮሐንስ ይሄንን ክስተት በዮሐንስ ራዕይ 1፡7 ላይ ጠቅሷል፡፡ የእስራኤል ቅሬታዎች በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 7 ከቁጥር 1 እስከ 8 ላይ ተጠቅሰውም እናነባለን፡፡ እነዚህን ታማኝ የእስራኤል ቅሬታዎች፣ ጌታ በመጨረሻው ዘመን “በእውነትና በጽድቅ” ያድናቸዋል፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ይመልሳቸዋል (ዘካርያስ 8፡7-8)፡፡

የእስራኤል መንፈሳዊ ችግር ከተፈታ በኋላ፣ ክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥቱን በምድር ላይ ይመሰርታል፡፡ እስራኤላውያንም ከምድር ዳርቻዎች ሁሉ ይሰበሰባሉ (ኢሳይያስ 11፡12፣ ኢሳይያስ 62:10)፡፡ በሕዝቅኤል ላይ ተገልጾ የምናነበው የ “ደረቅ አጥንቶች” “ሥጋ መልበስ” እና “እጅግ ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው የመቆም” ትንቢታዊ ቃልም ፍጻሜ ያገኛል (ሕዝቅኤል 37፡1-14).፡፡ እግዚአብሔር ለእስራኤል የገባው የተስፋ ቃል፣ የእስራኤል መንፈሳዊ ተሃድሶ እና መልክዓ ምድራዊ መኖሪያ ያካተተ መሆኑን ሕዝቅኤል በትንቢቱ እንዲህ በማለት አመልክቷል፦ “መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፥ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፥ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ” (ሕዝቅኤል 37፡14)፡፡

በጌታ ቀን፣ እግዚአብሔር “የሕዝቡን ቅሬታ” ይሰበስባል (ኢሳይያስ 11፡11)፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ በእርሱ ላይ ያመጹትን ሰራዊቶች ሁሉ ያጠፋል (ራዕይ 19)፤ ኃጢአተኞች ይፈረድባቸዋል፤ የታመኑት የእስራኤል ቀሪታዎች ለዘላለሙ የእግዚአብሔር ቅዱስ ህዝብ እንዲሆኑ ይለያዩ (ዘካርያስ 13፡8 እስከ 14፡21)፡፡ ከዛም፣ ኢሳይያስ 12 የድነት መዝሙራቸው ይሆናል፡፡

የመልዕክቱ ሃሳብ የተወሰደው ከ https://www.gotquestions.org/ ድረ ገጽ ላይ ነው፡፡

1 thought on “በመጨረሻው ዘመን እስራኤል በሙሉ ይድናሉ ወይ? ሮሜ 11”

  1. Rahel Yeshitila

    ተባረክ ትልቅ ትምህርት ነው የወሰድኩት :: ፀጋውን አብዝቶ ይጨምርልህ

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading