ኦሪት ዘፍጥረት

የኦሪት ዘፍጥረት መግቢያ

ጥያቄ፥ «ዘፍጥረት» የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ተመልከት። ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ተጻፈበት ዓላማና ስለ መጽሐፉ አስተዋጽኦ ያገኘኸው ነገር ምንድን ነው?

ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ልናጠናቸውና ልንረዳቸው ከሚገቡን እጅግ ጠቃሚ መጻሕፍት አንዱ ዘፍጥረት ነው። ብዙ ክርስቲያኖች በዘፍጥረት ውስጥ የሚገኙትን ታሪኮች ቢያውቁም እንኳ አብዛኛዎቹን ጥልቅ ትምህርቶች ግን አያጠኗቸውም። የዚህ መጽሐፍ ዓላማ ዘፍጥረትን በጥልቀት ማጥናት ባይሆንም፥ በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸውንና የተተኮረባቸውን ዋና ዋና የሥነ- መለኮት ትምህርቶች ለመመልከት እንሞክራለን።

የኦሪት ዘፍጥረት ስያሜ

ለኦሪት ዘፍጥረት የተሰጠው ስም የመጣው ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ዘፍጥረት የሚለው ቃል በመጽሐፉ የመጀመሪያ ሁለት ምዕራፎች ላይ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ስለ መፍጠሩ በሚናገረው መሠረተ አሳብ ላይ ያተኩራል። እንደግሪኩ ስያሜ መጽሐፉ የሚያተኩረው በተለያዩ ነገሮች «አጀማመር» ላይ ነው።

ጥያቄ፥ ከዚህ ቀደም ኦሪት ዘፍጥረትን በግል ካነበብከው በመነሣት አጀማመራቸው በመጽሐፉ የሆነ የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር።

በዘፍጥረት ውስጥ የቀረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍላችንን ለመረዳት በጣም ጠቃሚ የሆኑ የብዙ ነገሮችን አጀማመር እንመለከታለን። ለምሳሌ፡- የፍጥረታትን አጀማመር እንመለከታለን። እግዚአብሔር ፈጣሪ ስለሆነ እርሱ የፍጥረታት ሁሉ ባለቤትና ተቆጣጣሪ ነው። በዘፍጥረት ውስጥ የወንድና የሴትን፥ የጋብቻን፥ የኃጢአትን፥ ስለ ኃጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ የተለያዩ ከተሞችን፥ የነፍስ ግድያን፥ የሥልጣኔ፥ የነገድና የጎሣዎችን፥ የተለያዩ ቋንቋዎችን አጀማመር፥ ወዘተ እናያለን። አብዛኛዎቹም በኦሪት ዘፍጥረት በመጀመሪያዎቹ 11 ምዕራፎች ውስጥ ይገኛሉ።

ከብሉይ ኪዳን ታሪክ አንጻር ስናየው ግን በጣም አስፈላጊ ክስተት የሆነው የእስራኤል ሕዝብ አጀማመር ነው። የኦሪት ዘፍጥረት አብዛኛው ክፍል (ምዕራፍ 12-50) ስለ እስራኤል ሕዝብ አጀማመር የሚናገር ነው። ይህም ሕዝብ እግዚአብሔር የመረጠው ነው።

የኦሪት ዘፍጥረት ጸሓፊ

ጥያቄ፡ሀ) የኦሪት ዘፍጥረት ጸሐፊ እንደሆነ በይበልጥ የሚገመተው ማን ነው? ለ) እንደ አንዳንድ ምሁራን አስተሳሰብ ዘፍጥረት የተጻፈው እንዴት ነው? ። ሐ) ሙሴ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ተመልክተህ ስለ ሕይወቱ በአጭሩ ጻፍ። መ) ኦሪት ዘፍጥረትን ለመጻፍ ሙሴ የተለየ ብቃት ያገኘው እንዴት ነው?

በዘመናት ሁሉ ሙሴ ዘፍጥረትን ጨምሮ የፔንታቱክ ጸሐፊ መሆኑ ይገመት እንደነበር ቀደም ሲል ተመልክተናል። ጸሐፊው ሙሴ እንደሆነ በዘፍጥረት ባይጠቀስም እንኳ የቀሩቱ የፔንታቱክ መጻሕፍት ግን ሙሴ እንደጻፈው ያሳያሉ። አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት በሙሉ እንደ አንድ ክፍል ስለሚቆጠሩ፥ ዘፍጥረትንም የጻፈው ሙሴ መሆን አለበት። ሙሴ ዘፍጥረትን አልጻፈውም ብለን የምናምንበት አንዳችም ምክንያት የለም። ይልቁንም ሙሴ በዘፍጥረት ውስጥ የምናገኘውን ነገር ለመጻፍ በተለየ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ነበር።

ለአይሁድ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩ እጅግ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ሙሴ ነበር። ከግብፅ ባርነት አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የመራቸው ሙሴ ነበር። ለእስራኤል ሕዝብ ሕግን ለመስጠት እግዚአብሔር የተጠቀመበት ሰው ሙሴ ነበር። አይሁድ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዘወትር «የሙሴ ሕግ» ብለው የሚጠሩት ስለዚህ ነበር። ሙሴ ነቢይ፥ ካህን፥ ሕግ ሰጭ፥ ፈራጅ፥ አማላጅ፡ እረኛ፥ ተአምራት አድራጊና የአይሁድ ሕዝብ የፖለቲካ መሥራች ነበር።

ሙሴ የተወለደው ሌዊ ከተባለው የእስራኤል ነገድ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ወላጆች ነበር። ነገር ግን የተወለደው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ነበር። የእስራኤል ሕዝብ በግብፃውያን ባርነት ሥር ወድቆ፥ ግብፃውያንም እስራኤላውያን የሆኑ ወንዶች ልጆች ሁሉ በሚወለዱበት ጊዜ እንዲገደሉ ሕግ ያወጡበት ጊዜ ነበር። ግብፃውያን ይህንን ያደረጉበት ምክንያት እስራኤላውያን በቁጥር እጅግ ብዙ ይሆኑና ከዚህ ቀደም ሐይክሶሳውያን እንዳደረጉት ሊገለብጡን ይሆናል ብለው ፈርተው ስለ ነበር ነው። በእምነታቸው ጽናት የሙሴ ወላጆች ሊደብቁት እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ አሳደጉት። ሊደብቁት ከማይችሉበት ጊዜ ላይ ሲደርሱ ግን እግዚአብሔር እንደሚታደገው በመተማመን በዓባይ ወንዝ ዳር አስቀመጡት። የግብፅ መሪ የነበረው የፈርዖን ሴት ልጅ ባገኘችው ጊዜ ወደ ቤቷ ወስዳ እንደ ግብፃዊ አሳደገችው።

የሙሴ ሕይወት እያንዳንዳቸው 40 ዓመታት በሆኑ ሦስት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

 1. 40 ዓመታት በግብፅ – በፈርዖን ቤት ውስጥ፡- በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ ሙሴ በሁለት የተለያዩ ባሕሎች ትምህርት አደገ። በመጀመሪያ፥ በአይሁድ ሃይማኖትና ከአባቶች በተወረሰ ትምህርት አደገ። ይህ የሆነው ለጊዜውም ቢሆን ያሳድጉት ዘንድ ኃላፊነቱ በተሰጣቸው በእኅቱ ማርያምና በእናቱ ነበር (ዘጸ. 2፡7-10)። ሁለተኛ፥ ሙሴ እንደፈርዖን ልጅ ሆኖ የማደግ ዕድል በማግኘቱ በዚያ ዘመን ሊኖር የሚችለውን ትምህርት ሁሉ ቀስሞ ነበር (የሐዋ. 7:22 ተመልከት)። ግብፅ በዚያን ዘመን እጅግ የሠለጠነች አገር ስለነበረች፥ ሙሴ እጅግ የተማረ ሰው ነበር ማለት ነው። እስጢፋኖስ ሙሴ «በቃልና በሥራው ሁሉ የበረታ ሆነ» ይላል።

ሙሴ ይህንን ሁሉ ትምህርት በመቅሰሙ፥እግዚአብሔር በኋላ ዘፍጥረትን ጨምሮ የመጀመሪያዎቹን አምስት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲጽፍ ተጠቀመበት። አይሁዳውያን ከነበሩት ወላጆች ስለ ወገኖቹ እንደሰማ ጥርጥር የለውም። ወደ ኋላ ተመልሶ እስከ አዳምና ሔዋን፥ ኖኅ፥ በተለይም አብርሃም፥ ይስሐቅ፥ ያዕቆብና ዮሴፍ ያለውን የሕዝቡን አፈ ታሪኮችን ያውቅ ነበር። በግብፅ ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት ስለአለፈው ጊዜ የሚናገሩ ታሪኮችን የማየት ዕድልም ገጥሞት ነበር። ይህ ታሪክ የዓለምን አፈጣጠር፥ በኖኅ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውኃ፥ የዓለምን መከፋፈል ወዘተ የሚጨምር ነው። ሙሴ ዘፍጥረትን ለመጻፍ በጣም ብቁ ሰው ነበር።

በእነዚህ 40 ዓመታት ሙሴ እስራኤላዊ እንጂ ግብፃዊ እንዳልሆነ አልዘነጋም ነበር። ካደገ በኋላ ኣንድ ውሳኔ ለማድረግ ተገደደ። ውሳኔውስ ዓለማዊ የሆነ ዕድል ባለበት በፈርዖን ቤት ለመቆየት? ወይስ እግዚአብሔር የተለዩ የቃል ኪዳን ሕዝቡ አድርጎ ከመረጣቸውና አሁን ባሮች ከሆኑት ሕዝብ ጋር ማበር ይሆን?

ጥያቄ፥ ዕብ. 11፡24-26 አንብብ። ሀ) ሙሴ ያደረገው ምርጫ ምን ነበር? ለ) ዛሬ ይህንን ምርጫ ማድረግ ያለብን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

ሙሴ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣት የተመረጠ መሪ እንደነበር ተረድቶ ነበር (የሐዋ. 7፡25)። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጊዜ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ ኃይል ነፃ ሊያወጣቸው ሞከረ። ስለዚህ አንድን ሰው ከገደለ በኋላ የፈርዖንን ቤት ትቶ ከግብፅ መሸሽ ግድ ሆነበት።

 1. 40 ዓመታት በምድያም ምድረ በዳ፡- በሰው አመለካከት የሚቀጥሉት 40 ዓመታት የባከኑ ይመስላሉ። ሙሴ በጣም የተማረ ሰው ቢሆንም በግ ማገድ ጀመረ። በእግዚአብሔር አመለካከት ግን በሙሴ ሕይወት ይህ በጣም አስፈላጊ ጊዜ ነበር። ምድረ በዳውና በግ ማገዱ እግዚኣብሔር ሙሴን የእስራኤል ሕዝብ መሪ ወይም እረኛ ለማድረግ የሚያስተምርበት ቦታና ሥራ ነበር። በምድረ በዳው እግዚአብሔር በትምህርቱና በችሎታው የነበረውን ትምክሕት በማስወገድ ሙሴን ትሑት አደረገው። ሙሴ ትሑት ከሆነና እግዚአብሔር በሕይወቱ እንዲሠራ በእርሱ ብቻ ከታመነ፥ ታላቅ ሥራን ይሠራ ዘንድ የእግዚአብሔር መገልገያ ለመሆን ተዘጋጅቷል ማለት ነው።

ጥያቄ፥ ሀ) እግዚአብሔር ሙሴን በኃይል ይገለገልበት ዘንድ ትሑት ሊያደርገው ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? ለ) የእግዚአብሔርን ሕዝብ በምንመራበት ጊዜ በችሎታችንና በእውቀታችን ስለ መመካት ይህ ምን ያስተምረናል? ሐ) ከሙሴ ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ መኖር ስለ ቤተ ክርስቲያን አመራር ምን ለመማር ትችላለህ?

 1. 40 ዓመታት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከግብፅ ወደ ከነዓን መምራት፡ አንድ ቀን እግዚአብሔር ሙሴን በሚቃጠል ቁጥቋጦ ውስጥ ተገናኘውና ወደ ግብፅ ተመልሶ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ በማውጣት እንዲመራቸው ጠራው። ሙሴ ወደ ግብፅ ለመመለስ ቢፈራም፥ በመጨረሻ ከእግዚአብሔር ጋር ተስማማ። እግዚአብሔር ሙሴን በፈርዖን ፊት ስለ እርሱ ሆኖ ይናገር ዘንድ ተገለገለበት። ሙሴ ያደረገው በፈርዖን ቤተ መንግሥት በመሆኑ በፈርዖን ዘንድ እውቅናን ማትረፉ አያጠራጥርም። አሥር ታላላቅ ተአምራዊ መቅሠፍቶችን በግብፅ ላይ በማምጣት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ነፃ አውጥቶ በሙሴ አማካይነት 40 ዓመታት በምድረ በዳ መራቸው። በእነዚህ 40 ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር ሙሴን ፊት ለፊት ተገናኘው። እግዚአብሔር ለሙሴ ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ድረስ የተጻፈውን ሕግ ሰጠው። ሙሴን ኦሪት ዘፍጥረትን፥ ዘጸአትን፥ ዘሌዋውያንን፥ ዘኁልቁንና ዘዳግምን እንዲጽፍ እግዚአብሔር ተጠቅሞበታል። ይህ ሁሉ ቢሆንም እንኳ ሙሴ ለእግዚአብሔር ስላልታዘዘ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ታገደ (ዘኍ. 20፡1-13)። ሕዝቡን እስከ ከነዓን ድንበር ድረስ አደረሳቸው። የተስፋይቱን ምድር በተራራ ጫፍ ላይ ሆኖ ከተመለከታት በኋላ ሞተ።

ጥያቄ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሕይወት ውስጥ እግዚአብሔር እንዴት ኃጢአትን አክብዶ እንደሚያየው ይህ ምን ያስተምረናል?

የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ቅደም ተከተልና አስተዋጽኦ

ጥያቄ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት ዘፍ. 2፡4፤ 5፡1፤ 6፡9፣ 10፡1፤ 11፡10፤ 11፡27፤ 25፡12፤ 25፡19፤ 36፡1፥ 19፤ 37፡2። ሙሴ፡- «የ…..ታሪክ ይህ ነው» የሚላቸውን የተለያዩ ነገሮችን ዘርዝር።

ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን በሚጽፍበት ጊዜ ግልጽ የሆነ አስተዋጽኦ ነበረው። መጽሐፉን ያቀናበረው «የ…ይህ ነው» በሚሉት ቃላት ዙሪያ ነበር። ብዙ ምሁራን ይህንን አከፋፈል የኦሪት ዘፍጥረትን አስተዋጽኦ ለመንደፍ ይጠቀሙበታል።

 1. መግቢያ፡- የነገሮች ሁሉ አፈጣጠር (ዘፍጥ. 1፡1-2፡3)
 2. ከአይሁድ አባቶች በፊት የነበረው ዘመን (ዘፍ. 2፡4-11፡26)

ሀ) የሰማይና የምድር መፈጠር ታሪክ (ዘፍ. 2፡4-4፡26)

ለ) የአዳም ትውልድ እና የልጆቹ ታሪክ (ዘፍ. 5፡1-6፡8)

ሐ) የኖኅ ታሪክ (ዘፍ. 6፡9-9፡29)

መ) የሴም፥ የካምና የያፌት ታሪክ (ዘፍ. 10፡1-11፡9)

ሠ) የሴም ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 11፡10-26)

 1. የአይሁድ አባቶች ዘመን (ዘፍ. 11፡27-50)

ሀ) የታራ ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 11፡27-25፡1)

ለ) የእስማኤል ትውልድ (ዘፍ. 25፡12-18)

ሐ) የይስሐቅ ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 25፡19-35፡29)

መ) የዔሳው ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 36፡1-37፡0

ሠ) የያዕቆብ ትውልድ ታሪክ (ዘፍ. 37፡2-50፡26)

ሙሴ ኦሪት ዘፍጥረትን በዚህ ዓይነት ቢያቀናብረውም ለማስታወስ ቀላል የሆነ ሌላ የቅንብር መንገድ አለ። የሚከተለውን አስተዋጽኦ እየደጋገምህ አጥና ወይም በቃልህ ያዝ፡

 1. ከአይሁድ አባቶች በፊት የነበረው ዘመን (ዘፍ. 1-11)

ሀ. ፍጥረት (ዘፍ. 1-2)

ለ. የሰው ልጅ በኃጢአት መውደቅ (ዘፍ. 3-5)

ሐ. የጥፋት ውኃ በዓለም ላይ (ኖኅ) (ዘፍ. 6-9)

መ. የባቢሎን ግንብና የሰው ዘር መለያየት (ዘፍ. 10-1)

 1. የአይሁድ የእምነት አባቶች ዘመን (ዘፍ. 12-50)

ሀ. አብርሃም (ዘፍ. 12-25) ለ. ይስሐቅ (ዘፍ. 24-26)

ሐ. ያዕቆብ (ዘፍ. 27-36)

መ. ዮሴፍ (ዘፍ. 37-50)

ከዚህ በላይ ባለው አስተዋጽኦ ውስጥ ሁለት ነገሮችን ልብ በል፡- – በመጀመሪያ፥ ዘፍጥረት በሁለት ዓበይት ክፍሎች፥ ማለትም በዘፍጥረት 1-11 እንዲሁም በዘፍጥረት 12-50 እንደተከፈለ ልብ በል። የመጀመሪያው ክፍል የሚናገረው ስለ ጥንት ዘመን ሲሆን፥ ፍጥረታትን የመፍጠር ተግባር የተፈጸመው መቼ እንደሆነና ይህ ክፍለ ዘመን ምን ያህል ዓመታት እንደፈጀ ለማወቅ አንችልም። ዘፍ. 12-50 ደግሞ የሚናገረው ስለ አይሁድ ሕዝብ መመሥረትና ያንን ሕዝብ ስለ ጀመሩት አራቱ የእስራኤል አባቶች ታሪክ ነው።

ሁለተኛ፥ እያንዳንዱ ክፍል በአራት ንዑሳን ክፍሎች መከፈሉን ልብ በል። ከዘፍ. 1-11 ያለው የመጀመሪያው ክፍል ፍጥረትን፥ ውድቀትን፥ የጥፋት ውኃንና የባቢሎንን ግንብ የሚያጠቃልሉ ኣራት ክፍሎች አሉት። ከዘፍ. 12-50 ባለው ክፍል ደግሞ ትኩረት የተሰጣቸው አራት ዋና ዋና ሰዎች አሉ። ይህንን የዘፍጥረትን አስተዋጽኦ ብትከተል በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘውን ታሪክ ለማስታወስ ይረዳሃል።

የኦሪት ዘፍጥረት ልዩ ባሕርያት

በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ መጽሐፉን የበለጠ ለመረዳት ማዕከላዊ የሆኑና ሙሴ ያካተታቸው አንዳንድ ልዩ ነገሮች አሉ።

 1. ዘፍጥረት፥ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ዓላማውን ወደ ፍጻሜ ብዙ ጊዜ ለማድረስ ከተለመደው ባሕላዊ ሁኔታና ተግባር ተቃራኒ በሆነ አቅጣጫ እንደሚጓዝ ያሳያል። ይህ በተለይ የታየው እግዚአብሔር ከበኩሩ (ከመጀመሪያው ልጅ) ይልቅ ሁለተኛውን በመምረጡ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉት በርካታ ባሕሉች አይሁድ የመጀመሪያ ልጅ ልዩ እንደሆነ በማመን፥ ከአባቱ ንብረት የሚበዛውን ክፍል መውረስ እንዳለበት ይስማሙ ነበር። እግዚአብሔር ግን በዚህ ሰው ሠራሽ ባሕል ራሱን አልወሰነም። ለምሳሌ፡- በዘፍጥረት ውስጥ እግዚአብሔር ከቃየን ይልቅ ሴትን፥ ከያፌት ይልቅ ሴምን፥ ከእስማኤል ይልቅ ይስሐቅን፥ ከዔሳው ይልቅ ያዕቆብን፥ ከቀሩት ወንድሞቻቸው ይልቅ ይሁዳንና ዮሴፍን፥ ከምናሴ ይልቅ ኤፍሬምን ሲመርጥ እንመለከታለን። ይህ ሁሉ የሚያስተምረን እግዚአብሔር በእኛ ባሕላዊ ግንዛቤ መሠረት ብቻ ለመሥራት የሚወሰን አለመሆኑን ነው። ይልቁንም ከእኛ ጋር ባለው ግንኙነት ሉዓላዊ ነው። የተለያዩ ግለሰቦችን የሚመርጠውና በአንዳንዶቹ በኃይል የሚሠራው በሌሉቹ ደግሞ ያንኑ ያህል በኃይል የማይሠራው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይህም እግዚአብሔር በሕይወታችን ላይ ባለው ኃይልና የበላይ ተቆጣጣሪነት ከፍተኛ አድናቆትን እንድንሰጠው የሚያደርግ እንጂ በአእምሮአችን ውስጥ ቅንዓትን የሚፈጥር መሆን የለበትም።

ጥያቄ፥ ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ሌሉች ክርስቲያኖች ባለጸጎች መሆናቸውን ወይም እግዚአብሔር ከእነርሱ ይልቅ በኃይል እየተጠቀመባቸው መሆኑን ሲገነዘቡ የሚቀኑት ለምንድን ነው? ለ) ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር ዕቅድ አሳልፎ ስለመስጠት የሚያስተምረን ነገር ምንድን ነው? ሐ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም አስፈላጊው ነገር፥እግዚአብሔር ለሰጠን ስጦታዎችና ችሉታዎች ወይም ሥራዎች ታማኝ መሆን ነው፥ ወይስ በሰዎች ላይ ታላቅ መሪ መሆን? መልስህን አብራራ።

 1. በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ ተምሳሌታዊ ትርጉም ያላቸው አንዳንድ ቁጥሮች ይገኛሉ። የሚከተሉትን ቁጥሮች ተመልከት፡- .

ሀ) አሥር – በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ አሥር ዋና ዋና ክፍሎች አሉ፤ (አሥር ጊዜ «የ … ይህ ነው» ታሪኮች) እንዲሁም በዘፍጥረት 5 ና 11 «አሥር» ትውልዶችን የሚጠቅሱ ትንተናዎች እናገኛለን»። ለአይሁድ ኣሥር የምሉዕነት ተምሳሌት ነው።

ለ) ሰባት – ሰባት የፍጥረታት ሥራ የተከናወኑባቸው ቀናት ከመኖራቸውም፥ በምዕራፍ 4 ውስጥ በሚገኘው የትውልዶች ታሪክ ውስጥ የሚገኙ ሰባት ስሞች፥ በጥፋት ውኃ ታሪክ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሰባት ቁጥሮች፣ ለአብርሃም የተገቡ ሰባት ቃል ኪዳኖች፥ በግብፅ ውስጥ የደረሱ ሰባት የጥጋብና ሰባት የራብ ዓመታት እናገኛለን እንዲሁም 70 (7 ጊዜ 10) የኖኅና የያዕቆብ ዝርያዎች ናቸው። ሰባት ብዙ ጊዜ የፍጹምነት ምሳሌ ነው።

ሐ) አሥራ ሁለት – የያዕቆብና የእስማኤል ነገዶች እያንዳንዳቸው አሥራ ሁለት ነገዶች ነበሩ (ዘፍ. 25፡16፤ 49፡28)።

መ) አርባ፡- በጥፋት ውኃ ታሪክ ውስጥ የተለያዩ የ40 ቁጥር ክፍፍሎች እናያለን (ዘፍ. 6-9)። በኋላም እስራኤላውያን 40 ዓመታት በምድረ በዳ እንደተንከራተቱ እናነባለን።

አንድ ሰው ብሉይ ኪዳንን በሚያጠናበት ጊዜ እነዚህ ቁጥሮች ለአይሁድ የተለዩ እንደሆኑ ግልጽ እየሆነለት ይመጣል። ለምሳሌ 40 ቁጥር የፍርድና የፈተና ጊዜ ይመስላል (ለምሳሌ፡- ኢየሱስ በምድረ በዳ ለ40 ቀናት ተፈትኖአል)። ሰባት ማለት ደግሞ የተሟላ ወይም ፍጹም ማለት ነው፤ (ለምሳሌ፡- በዮሐንስ ራእይ መንፈስ ቅዱስ ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ተብሎ ተጠርቷል)።

 1. በዮሐንስ ራእይ የመጨረሻ ምዕራፎች የሚገኙት በተለይም መንግሥተ ሰማያትን የሚገልጡት ሥዕላዊ መግለጫዎች ከኦሪት ዘፍጥረት የመጀመሪያ ሦስት ምዕራፎች ስለ ዔደን ገነት ከተነገሩ መግለጫዎች የተወሰዱ መሆናቸው ትኩረትን የሚስብ ነው። እነዚህ መጻሕፍት የተጻፉት በ1500 ዓመታት ልዩነት መካከል ቢሆንም ይህን የመሰለ ግንኙነት በመካከላቸው መታየቱ፥ እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ጸሐፊ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

የኦሪት ዘፍጥረት ዋና ዓላማ

የመጽሐፍ ቅዱስን አጠቃላይ ዓላማ ብንመለከት፥ ኢየሱስ ክርስቶስን መግለጥ ነው ለማለት እንችላለን። እርሱ «የእግዚአብሔር ቃል» ነው ( ዮሐ. 1፡1-4፤ ዕብ. 1፡1-3)። «ኢየሱስ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ተሰውሮአል፤ በአዲስ ኪዳን ግን ተገልጦአል» የሚል አንድ አባባል አለ። በሌላ አባባል የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በትንቢቶች አማካይነት የኢየሱስን መምጣት አሻግረው ተመለከቱ። እንዲሁም በሰዎች፥ በድርጊቶችና በነገሮች ሁሉ ውስጥ የመሢሑ መምጣት ሥዕላዊ መግለጫ ነበር። ስለሆነም ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ አጀማመር እናያለን። በዘፍጥረት ስለ ኢየሱስ የተነገሩ ትንቢቶችን አጀማመር እንመለከታለን። በአንዳንድ ታሪኮች ውስጥም የተደበቁ የኢየሱስ ተምሳሌቶች ወይም ሥዕላዊ መግለጫዎች አሉ። ብሉይ ኪዳንን ስናጠና እነዚህም ትንቢቶችና አምሳያዎች መፈለግ አለብን። ይህ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ራእይ የሚቀጥል «የደኅንነት መስመር» በመባል ይታወቃል።

ነገር ግን ሙሴ ፔንታቱክን የጻፈበት ዋና ዓላማ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገውን «ቃል ኪዳን» ለመግለጥ ነበር። ፔንታቱክና መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት መሠረታዊ የሆነው አሳብ ይህ ቃል ኪዳን ነው፤ ስለዚህ የኦሪት ዘፍጥረት ማዕከላዊ እውነቶች የሚያተኩሩት ቃል ኪዳንን በሚመለከት አሳብ ላይ ነው። ዘፍጥረት 1-11 ከተለዩ ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን ያስፈለገበትን ምክንያት ይናገራል። የሰው ልጅ በአጠቃላይ ፈጣሪውን ክዶ ኃጢአትን እንዴት እንደመረጠ ይናገራል። ዘፍ. 12-50 ደግሞ እግዚአብሔር ከአንድ ሰውና ከቤተሰቡ ጀምሮ አይሁድ ተብሎ የተጠራ አንድን የተለየ ሕዝብ እንዴት እንደመረጠ ይገልጻል። እግዚአብሔር ዓለምን ወደ ራሱ ለመመለስ የፈለገው በእነርሱ በኩል ነበር።

ጥያቄ፥ ሀ) በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው የቃል ኪዳን አሳብ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ወይም በአዲስ ኪዳን የሚታየው እንዴት ነው? ለ) የእስራኤል ሕዝብና የቤተ ክርስቲያን ዓላማ የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ሐ) እግዚአብሔር አብርሃምን በመረጠው ጊዜ የነበረውን ዓላማ ዛሬ ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እየፈጸመችው ነው?

(ማብራሪያዎቹ ሁሉ የተወሰዱት በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡) ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡

ኦሪት ዘፍጥረት

መግቢያ

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 1፡1-31

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 2፡1-25

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 3፡1-24

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 4፡1-26

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 5፡1-32

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 6፡1-22

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 7፡1-24

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 8፡1-22

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 9፡1-29

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 10፡1-32

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 11፡1-32

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 12፡1-20

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 13፡1-18

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 14፡1-24

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 15፡1-21

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 16፡1-16

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 17፡1-27

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 18፡1-33

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 19፡1-38

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 20፡1-18

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 15፡1-21

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 21፡1-34

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 22፡1-24

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 23፡1-20

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 24፡1-67

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 25፡1-34

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 26፡1-35

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 27፡1-46

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 28፡1-22

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 29፡1-35

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 30፡1-43

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 31፡1-55

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 32፡1-32

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 33፡1-20

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 34፡1-31

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 35፡1-29

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 36፡1-43

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 37፡1-36

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 38፡1-30

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 39፡1-23

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 40፡1-23

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 41፡1-57

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 42፡1-38

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 43፡1-34

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 44፡1-34

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 45፡1-28

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 46፡1-34

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 47፡1-31

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 48፡1-22

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 49፡1-33

ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 50፡1-26

Leave a Reply

%d bloggers like this: