ወንጌላትን እንዴት መረዳትና መተርጎም ይቻላል?

የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዐይነቶች በተለያዩ መንገዶች ይተረጎማሉ። ለምሳሌ፥ ተምሳሌታዊ ቋንቋን የሚከተል ግጥም በተራ ቃላት ከሚጻፍ ደብዳቤ ጋር ተመሳሳይ አይደለም። ከአንድ ጓደኛችን ደብዳቤ ቢደርሰን «ሰምና ወርቁን» መለየት ሳያስፈልገን ከጓደኛችን ጋር አፍ ለአፍ እንደምንነጋገር ሁሉ በቀላሉ ልናነበው እንችላለን። ቅኔን እንደ ደብዳቤ ካነበብን ጥልቅ ምሥጢሩን እናጣዋለን። ስለሆነም የመጽሐፉን መልእክት በቅጡ ለመረዳት፥ የጽሑፉን ዐይነት ለይቶ ማወቅና የዚያን ዐይነት ሥነ ጽሑፍ ለመረዳት የሚቻልበትን መንገድ መገንዘብ ይኖርብናል።

የመጽሐፍ ቅዱስም ሁኔታ እንደዚሁ ነው። ምንም እንኳ መንፈስ ቅዱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሕተቶች እንዳይከሰቱ ቢቆጣጠርም፥ ጸሐፊዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ለመግለጽ የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ስልቶችን እንዲጠቀሙ ፈቅዶላቸዋል። ጳውሎስ የጻፋቸው መልእክቶች ደብዳቤዎች ናቸው። ምሑራን የሐዋርያው ዮሐንስን ራእይ «አቡቀለምሲሳዊ ሥነ ጽሑፍ» ብለው ይጠሩታል። በኋላ ስለዚህ ዐይነቱ ሥነ ጽሑፍ በሰፊው እናጠናለን።

ለመሆኑ አራቱ ወንጌላት ምን ዐይነት ሥነ ጽሑፍ ናቸው። ምናልባት ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆነው አራቱ ወንጌላት ትምህርተ ታሪክ ናቸው የሚለው ይሆናል። ወንጌላትን በምናጠናበት ጊዜ ልናጤናቸው የሚገቡ ሁለት ነገሮች አሉ።

በመጀመሪያ፥ ወንጌላት ታሪክ መሆናቸውን ማስታወስ ኣለብን። ማቴዎስ፥ ማርቆስ፥ ሉቃስና ዮሐንስ ታሪክን አልጀመሩም፤ እውነተኛ ታሪካዊ ሁኔታዎችን ነው የዘገቡት። ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ ያለ ሥራ አልኖረም። ተአምራትን ሠራ። በወንጌላቱ ውስጥ የተጠቀሱትን ነገሮች አስተማረ። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በተአምራት የማያምኑ ምሁራን፥ ኣራቱ ወንጌላት ልብ ወለድ ፈጠራዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነና በውስጡም የሚገኘው አሳብ ሁሉ እውነት መሆኑን የማይቀበል ኣሳብ ማስተናገድ የለብንም።

1ኛ የውይይት ጥያቄ፡- አራቱ ወንጌላት እውነተኛ ታሪኮች መሆናቸውን አጥብቆ ማመን ለምን ያስፈልጋል?

ሁለተኛው፥ ጸሐፊዎቹ ሰዎችን በታሪኮች አማካይነት ለማስተማር እየሞከሩ ነበር። በሌላ አነጋገር፥ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከምናጠናቸው የታሪክ መጻሕፍት በተቃራኒ፥ የተመረጡት ታሪኮችና የቀረቡበት ሁኔታ ያዘጋጀው ሰዎች እንዴት ከክርስቶስ ጋር እንደሚቀራረቡ ለማስተማር ነበር። በአጠቃላይ የወንጌል ጸሐፊዎች ሁለት ነገሮችን ለማከናወኑ ይፈልጉ ነበር።

ሀ) ወንጌላት የክርስቶስን ማንነት ለማብራራት ሞክረዋል። ክርስቶስ ተራ የታሪክ ተዋናይ ሳይሆን፥ ለዓለም ኃጢአት የሞተ አምላክ ነው። እርሱ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የተለየ ነበር። እርሱ ለሰው ኃጢኣት በመሠዋቱ፥ የወንጌሉ ጸሐፊዎች የሆኑ ሰዎች ክርስቶስን ማወቅና ማመን እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር።

ለ) የመጀመሪያዎቹ አራት የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፥ ለክርስቲያኖች የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን እንደሆነ ያስተምራሉ። ክርስቶስ ሞቶ ተነሥቷል። ስለሆነም አሁን ሕያው ነው። በአምላክነቱ ተሰግዶለታል። ክርስቶስ እንደተናገረው፥ እርሱ ለዘላለም ከእኛ ጋር ነው። ስለሆነም የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ማለት እርሱ በሥጋ የተገለጠና ለኃጢአታችን የሞተ አምላክ መሆኑን መቀበል ነው። በተጨማሪም ከእርሱ ጋር ግንኙነት መመሥረት ማለት ነው። ለማቴዎስና ለሌሎች ደቀ መዛሙርት እንደታየው ለእኛ አሁን በአካል ላይታየን ይችላል። ይሁንና እርሱ አሁንም አዳኛችንና ወዳጃችን ሆኖ አብሮን ይኖራል። የክርስቶስ ተከታይ ማለት ያስተማረንን በሥራ ላይ ለማዋል መወሰን ማለት ነው። የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሰው የእርሱን ዐይነት ባሕርይና ተግባር ሊያሳይና ስለ ክርስቶስ ለሌሎች ሊመሰክር ይገባዋል።

2ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ በ«ሀ» እና በ«ለ» ሥር የቀረቡት እሳቦች ለክርስቲያኖች ጠቃሚ የሚሆኑት ለምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን እውነቶች ለምእመኖቿ፥ በተለይም ለአዳዲስ ክርስቲያኖች የምታስተምረው እንዴት ነው?

3ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 1-2 ኣንብብ። ሀ) ማቴዎስ የክርስቶስ የዘር ሐረግ በመዘርዘር ለማስተላለፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? ለ) በክርስቶስ ሕይወት ውስጥ ለማቴዎስ አስፈላጊ ዓመታት የትኞቹ ነበሩ? ሐ) በማቴ. 1፡1-17 የተጠቀሰውን የክርስቶስ የትውልድ ሐረግ በሉቃስ 3፡23-38 ከቀረበው ገለጻ ጋር በማነጻጸር ልዩነቱን አስረዳ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

%d