አንድ ቀን ዮሐንስና ተስፋዬ በከተማ ውስጥ ይንሸራሸሩ ነበር። ዮሐንስ ሰዎች ክርስቲያን ከመሆን ባሻገር፥ ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት እንዲያድጉ አጥብቆ የሚፈልግ መጋቢ ነበር። ተስፋዬ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሲመጡ ለማየት የሚናፍቅ ወንጌላዊ ነበር። በከተማይቱ ውስጥ እየተጓዙ ሳለ፥ ዮሐንስ የተለያዩ ክርስቲያኖችን በማግኘቱ ስለ መንፈሳዊ ሕይወታቸው፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለ መሄዳቸውና በጸሎት ስለ መትጋታቸው ይጠይቃቸው ጀመር። የተስፋዬ ዐይኖች ወንጌሉን አምነው እንዳልተቀበሉ በሚያውቃቸው ሰዎች ላይ ዐረፉ። ሙስሊሞችን፥ ጫት ቃሚዎችን፥ ወዘተ… በሚመለከትበት ጊዜ ሰላምታ በመስጠት፥ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ሞከረ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐንስና ተስፋዬ ያላቸው የተለያየ አመለካከት በሚመለከቷቸውና በሚያተኩሩባቸው ነገሮች ላይ ያስከተለው ለውጥ ምንድን ነው? ለ) ሽማግሌ፥ የኳየር አባል፥ ወይም ተራ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሆናችን ወደ ቤተ ክርስቲያን በምንሄድበት ጊዜ ነገሮችን በምንመለከትበት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?
ለሕይወት አስፈላጊ ናቸው በምንላቸው ነገሮች ላይ አመለካከታችንን የሚቀርጹ የተለያዩ ነገሮች አሉ። አስተዳደጋችን፡ ባህላችን፥ የትንሽ ወይም የትልቅ ከተማ ነዋሪዎች መሆናችን፥ ከኦርቶዶክስ ወይም ከፕሮቴስታንት ቤተሰብ መምጣታችን፥ የተወሰኑ ነገሮችን የምንመለከትበትን ሁኔታ ይለውጣሉ። አገልግሎታችንም ነገሮችን በምንመለከትበት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ፥ ዮሐንስ መጋቢ በመሆኑ፥ ሁልጊዜ ክርስቲያኖችን እየተከታተለ እንዲያድጉ ለማበረታታት የሚችልበትን መንገድ ይፈልጋል። ተስፋዬ ደግሞ ወንጌላዊ በመሆኑ፥ ክርስቲያኖችን ችላ ባይልም ክርስቲያን ያልሆኑትን ሰዎች እየፈለገ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክርበትን መንገድ ይተልማል። ዮሐንስና ተስፋዬ የቤተ ክርስቲያን የሽማግሌዎች ቦርድ አባላት ቢሆኑ፥ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና፥ አማኞች በእምነታቸው እንዲያድጉ በሚረዱቸው የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ እንድታተኩር መገፋፋቱ የማይቀር ነው። ተስፋዬ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ለጠፉት እንድትመሰክር ያበረታታል። እነዚህ ሁለት ሰዎች ስለ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ፍጹም የተለያዩ አሳቦችን ሊይዙ ይችላሉ።
ስለ አራቱ ወንጌላት ጸሐፊዎችም ተመሳሳይ አሳብ መናገር ይቻላል። እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ ያደገው በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ነው። ማቴዎስ አይሁዳዊ ስለሆነ ክርስቶስ የአይሁዶችን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዴት እንዳሟላ ለመግለጽ ፈለገ። በተጨማሪም ያደገው ከአሕዛብ ጋር ነው። ቀረጥ ሰብሳቢ እንደ መሆኑ፥ ገንዘብ በማግበስበስ የሰዎችን ጥላቻ ለማትረፍ በቅቷል። ማርቆስ ያደገው በኢየሩሳሌም ሲሆን፥ አብዛኛውን አገልግሎቱን ያሳለፈው ጳውሎስንና ጴጥሮስን በመርዳት ነበር። ሉቃስ ለድሆችና ሕይወት ላልተሳካላቸው ሰዎች ትኩረት የሚሰጥ አሕዛብ ሐኪምና የታሪክ ምሁር ነበር። ዮሐንስ መጋቢና የሥነ መለኮት ምሑር ሲሆን፥ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ማወቅ በሚገባቸው አሳብና እርስ በርሳቸው በሚዛመዱበት ሁኔታ ላይ አተኩሯል። እያንዳንዱን ወንጌል በምናነብበት ጊዜ እነዚህ ልዩነቶች ሲንጸባረቁ እንመለከታለን። ከእነዚህ የተለያዩ ሥራዎች የተነሣ እያንዳንዱ የወንጌል ጸሐፊ ስለ ክርስቶስ የተለየ አመለካከት ይሰጠናል። ስለ ደራሲው ይበልጥ ባወቅን ቁጥር፥ ለምን በዚያ መንገድ እንደ ጻፈ መገንዘብ እንችላለን።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የመጀመሪያው ወንጌል ርእስ ምንድን ነው? ለ) ማቴ. 9፡9፣ 10፡3፣ ሉቃለ 5፡27-32፤ የሐዋ. 1፡13 ኣንብብ። ስለ ማቴዎስ ምን ልንማር እንችላለን? ሐ) ስለ ማቴዎስ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ላይ ተመልከት። የመጀመሪያው ወንጌል ጸሐፊ ማን ነው? ስለ ጸሐፊው የምታውቀውን ሁሉ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። መ) ወንጌሉ የተጻፈው መቼ ነው? ሠ) የማቴዎስ ወንጌል አንዳንድ ልዩ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)
ትምህርታችሁን በጣም ዉድጄወለሁኝ ፡በዝሁ መቃጠል እንጅ ሌለ ምንም፡ ልል ፡አልችልም ፡፡አስቴት ፡ከሌኝ ፡ሌለ ጊዜ ።
ትምህርታችሁ በቀላሉ ወንጌልን እንድንረዳ ጥልቅ የሆነ አመሰራረት ያለው ነው። እግዚአብሔር አምላክ ይርዳችሁ