ከሉቃስና ከዮሐንስ በተቃራኒ፥ ማቴዎስ ወንጌሉን ለምን እንደ ጻፈው ምክንያቱን አይገልጽም (ሉቃስ 1፡1-4፤ ዮሐ 20፡30-3)። ስለሆነም የማቴዎስን ዓላማ የምንረዳው ወንጌሉን በመገንዘብ ነው። ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈባቸው ብዙ ምክንያቶች እንደሚኖሩ ባይጠራጠርም፤ ጥቂቶቹን እንደሚከተለው ዘርዝረናል።
1 ማቴዎስ ክርስቶስ ለዓለም በተለይም ለአይሁዶች የእግዚአብሔር ዐላማ ፍጻሜ እንደሆነ ያሳያል።
1ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 1፡2-232፡5፥ 17-18 4፡14-16፤ 27፡9-10 አንብብ። ሀ) እነዚህ ሁሉ ክርስቶስ የፈጸማቸው የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ምን ያሳያሉ፤ ለ) ለአይሁዶች እነዚህን ሁሉ እውነቶች ማመን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ሐ) ማቴ. 1፡1 9፡27 22፡41-45 አንብብ። እነዚህ ምንባቦች በየትኛው የክርስቶስ የሕይወት ገጽታ ላይ ያተኩራሉ?
ማቴዎስ ሕዝቡ ለሆኑት አይሁዶች በጣም ያስብ ነበር። አይሁዶች የብሉይን ኪዳን ሕዝብና የእግዚአብሔር ምርጦች ነበሩ። ነገር ግን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቢኖሯቸውም እንኳ፥ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ለአይሁዶች የሰጣቸው ትንቢቶች ፍጻሜ መሆኑን ለመረዳት ተቸግረው ነበር። ስለሆነም ሲጠብቁት የነበረው መሢሕ መሆኑን አይሁዶችን ለማሳመን ሲል ወንጌሉን ጻፈ። ማቴዎስ ይህንን ያደረገው እንዴት ነበር?
ሀ. ከየትኛውም ወንጌል በላይ ማቴዎስ ክርስቶስ እንዴት ብሉይ ኪዳን ስለ መሢሑ የተነበየውን ቃል እንደ ፈጸመ ያሳያል። ማቴዎስ ከብሉይ ኪዳን ቢያንስ 60 ጥቅሶችን ወስዷል። እያንዳንዱ የክርስቶስ ሕይወት የጥንቱን ትንቢት እንዴት እንደ ፈጸመ ያሳያል። ክርስቶስ በቤተልሔም መወለዱ፥ ወደ ግብፅ መሸሹ፥ በገሊላና በናዝሬት ማደጉ፥ በምሳሌ ማስተማሩ ሁሉ በብሉይ ኪዳን ተተንብዮ ነበር። ማቴዎስ እያንዳንዱ የክርስቶስ ሕይወት ክፍል እግዚአብሔር ትንቢትን ለማሟላት በተጠቀመበት መንገድ እንደ ተጓዘ አብራርቷል።
ለ. ኢየሱስ «የዳዊት ልጅ» በመሆኑ፥ መሢሕ ለመሆን ይችላል። ማቴዎስ የክርስቶስ የዘር ሐረግ ከዳዊት መምጣቱን አሳይቷል። ማቴዎስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ብቻ ሳይሆን በሕጋዊ የንግሥና የዘር ሐረግ የዳዊት ልጅ መሆኑን ለማመልከት፥ የዮሴፍ ሕጋዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ የአይሁዶች ንጉሥ ማለትም መሢሕ ለመሆን የሚያበቁትን መመዘኛዎች ሁሉ እንዴት እንዳሟላ አሳይቷል።
ሐ. ማቴዎስ ክርስቶስ ምን ዐይነት መንግሥትን እንደ ሰበከ በወንጌሉ ገልጾአል። አይሁዶች ምድራዊና ፖለቲካዊ መንግሥት ይፈልጉ ነበር። እንዲያውም ማቴዎስ ወንጌሉን በሚጽፍበት ጊዜ አይሁዶች በሮም መንግሥት ላይ ትግል ማካሄድ ጀምረው ነበር። እንደ መቃብያን፥ ዳዊትና ሰለሞን ዘመን የራሳቸውን አገር የሚቆጣጠሩበትን ፖለቲካዊ ነጻነት ይሹ ነበር። አይሁዶች በክርስቶስ ለማመን ከተቸገሩበት ምክንያት አንዱ፥ ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶች የተረዱትን የፖለቲካዊ ነፃ አውጪነትን ተግባር አለማከናወኑ ነበር። ሮማውያን በቀላሉ ይዘው የሰቀሉት ሰው እንዴት መሢሕ እንደሚሆን ሊከሰትላቸው አልቻለም።
2ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡3፥ 10፥ 19፥ 20፣ 1፡11-12፤ 13፡1-52፣ 18፡1-4፤ 19፡14-30፣ 25፡1-46 እንብብ። ማቴዎስ ያተኮረባቸው የመንግሥተ ሰማይ ባሕርያት ምንድን ናቸው?
ማቴዎስ ክርስቶስ ፖለቲካዊ ሳይሆን መንፈሳዊ መንግሥት ማምጣቱን ለማመልከት ሲል፥ ለክርስቶስ መንግሥት «የሰማይ መንግሥት» የሚል ስያሜ ሰጥቷል። ማቴዎስ «የሰማይ መንግሥት» በማለቱ፥ ክርስቶስ በአይሁዶች ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን አገዛዝ የሚያሳይ መንግሥት እንደሚመሠርት እያመለከተ ነበር። የእርሱ መንግሥት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተሉ ላይ ያተኩር ነበር። ይህም በኣንድ ሰው ልብ ውስጥ የሚቀመጥና ባሕርዩን የሚለውጥ መንግሥት ነበር (ማቴ. 5-7። በዚህ ታሪካዊ ወቅት እግዚአብሔር ክርስቶስ ይህንን መንፈሳዊ መንግሥት እንዲጀምር ልኮታል። ነገር ግን ክርስቶስ በሙሉ ክብሩ ተመልሶ የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎች ሁሉ የሚፈጸሙበትን ምድራዊ መንግሥት ይመሠርታል። ወደዚያ መንግሥት የሚገቡት ግን፥ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ መንግሥት ሕይወታቸውን የሚያስገዙ አይሁዶች ወይም ኣሕዛብ ብቻ ይሆናሉ።
3ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቶስ በግል ሕይወታችንና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ባለው መንፈሳዊ አገዛዝ እንድናተኩር የሚፈልገው እንዴት ነው? ለ) ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ እንዲገዛ ከፈቀዱ፥ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ለውጦችን ገልጾአል። ማቴዎስ 5፡1-16 አንብብ። ከእነዚህ ለውጦች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? በሕይወትህ ውስጥ እነዚህን ለውጦች በመፈጸም ንጉሡ ክርስቶስን እንዴት ልታከብር እንደምትሻ ግለጽ።
- የማቴዎስ ወንጌል የሚጀምረው «የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ» በማለት ነው (ማቴ. 1፡1)። ይህም ማቴዎስ ወንጌሉ የዳዊት ልጅና ትክክለኛ የእስራኤል ንጉሥ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደሚያተኩር ያሳያል። ክርስቶስ ስለ መሢሑ የተነገሩት ትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜ ነው። እነዚህም የዳዊት ልጅ በእስራኤልና በዓለም ሁሉ እንደሚነግሥ የሚያመለክቱ ትንቢቶች ነበሩ (ለምሳሌ፥ ኢሳ 11፡1-16)። በተጨማሪም ማቴዎስ ክርስቶስ የአብርሃም ልጅ መሆኑን ገልጾአል። ይህም ክርስቶስ አይሁዳዊ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፥ የአብርሃም ቃል ኪዳን ፍጻሜ መሆኑንም ያስረዳል።
4ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ዘፍጥ. 12፡1-3 አንብብ። ሀ) እግዚእብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው ቃል ኪዳን ምንድን ነው? ለ) ክርስቶስ የአብርሃምን ቃል ኪዳን የፈጸመው እንዴት ነው?
በዚህ ቃል ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ለአብርሃም ብዙ የተስፋ ቃሎችን ሰጥቶታል። አብዛኞቹ የተስፋ ቃሎች ከእስራኤል ሕዝብ ጋር የተያያዙ ናቸው። ስለሆነም ማቴዎስ ክርስቶስ ፍጹም እስራኤላዊና እግዚአብሔር ለአይሁዶች የሰጣቸውን ተስፋዎች ሁሉ የሚፈጽም መሆኑን ያሳያል (ገላ. 3፡16 አንብብ።) በተጨማሪም እግዚአብሔር ለአብርሃም በእርሱ አማካይነት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ እንደሚባረኩ ተናግሯል። ይህ የተስፋ ቃል የተፈጸመበት ዋንኛው መንገድ የአብርሃም ልጅ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነበር። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞቱ ለሰዎች ሁሉ ይቅርታን አስገኝቶላቸዋል። በክርስቶስ በማመን ሰዎች ሁሉ የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ይሆናሉ (ገላ. 3፡7-9)። ጳውሎስ እንዳለው፥ እነዚህ ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ ተቀላቅለዋል (ሮሜ 11፡11-24)።
- ማቴዎስ አዳዲስ ክርስቲያኖችን ለማስተማር በማሰብ ወንጌሉን እንደ ጻፈ የሚያስቡ ምሑራን አሉ። ብዙዎች በክርስቶስ ቢያምኑም (ሮሜ 10፡9-10)፥ ስለ ክርስቶስ የሚያውቁት ብዙ ነገር አልነበራቸውም። ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በአካል እየተገኙ በሚያስተምሩበት ስፍራ ብቻ ሳይሆን፥ በሌሎችም አካባቢዎች ተስፋፍታ ነበር፤ እነርሱም ስለ ክርስቶስ መሢሕነት ለእያንዳንዱ አማኝ ያስተምሩ ነበር። ይሁን እንጂ ሐዋርያትና ክርስቶስን በአካል የሚያውቁት የነበሩ ሰዎች እያረጁ በመሄድ ላይ ይገኙ ነበር። ሌሎቹም ተሠውተው ነበር። ስለዚህም ማቴዎስ የክርስቶስን ታሪክ ለመጻፍ ፈለገ። ማቴዎስ አዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ማንነትና በመስቀል ላይ በመሞት ስላከናወነው ተግባር ግልጽ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ፈለገ። ማቴዎስ «በክርስቶስ አምናለሁ» የሚለው አጠቃላይ አሳብ ብቻ ለክርስቲያኖች በቂ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ስለ ክርስቶስ ማንነት፥ ምን እንዳደረገ፥ ስለ ሞቱና ትንሣኤው፥ እንዲሁም እከተልሃለሁ ከሚሉት ሰዎች ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር። ማቴዎስ ክርስቶስ ተከታዮች ስለመሆን ያስተማረውን ዘግቧል። አጠቃላይ የሕይወት ለውጥ ያስፈልግ ነበር። ከእንግዲህ በውጫዊ ደንቦችና ሕጎች ላይ ሳይሆን፥ በውስጣዊ ባሕርይና አመለካከት ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል (ማቴ. 5-7)። አይሁዶች ከሌሎች ጎላዎች እንደሚበልጡ በማሰብ በብሔራዊ ውርሳቸው መኩራራት እንደሌለባቸውና የአሕዛብና የአይሁዶች ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን መከተል እንዳለባቸው ገልጾአል። እውነትም ወንጌሉና የእግዚአብሔር በረከት ለሰዎች ሁሉ የተሰጠ እንጂ ለአንድ ጎሳ ብቻ አልነበረም።
5ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለኣዳዲስ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ባሕርይ ግልጽ ግንዛቤ መጨበጡ ለምን የሚያስፈልግ ይመስልሃል? ለ) ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ከተከታዮቹ ሕይወት ለማየት ስለሚፈልጋቸው ነገሮች ግልጽ ግንዛቤ ማግኘቱ ለምን ያስፈልጋል? ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ የምታደርግባቸውን መንገዶች አብራራ። መ) ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ክርስቶስን የበለጠ እንዲያውቁ ለማገዝ ልታደርጋቸው የሚገባቸው ተጨማሪ ነገሮች ምንድን ናቸው?
- የማቴዎስ ወንጌል እግዚአብሔር ለአሕዛብ ልዩ ዕቅድ እንዳለው ያሳያል። በማቴዎስ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ አይሁዶች አሕዛብን ስለሚጠሉ፥ እግዚአብሔርም አሕዛብን እንደሚጠላ ያስቡ ነበር። አንዳንድ አይሁዶች እግዚአብሔር አሕዛብን የፈጠረው መልሶ ሊያጠፋቸው እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ማቴዎስ ግን በመጽሐፉ ውስጥ ለአሕዛብ ልዩ ትኩረት ይሰጣል። ክርስቶስ የኣይሁድ ንጉሥ መሆኑን መጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡት ከኣሕዛብ ወገን የሆኑት ሰብዓ ሰገል ነበሩ (ማቴ. 2)። ንጉሥ ሄሮድስ ኢየሱስን ሊገድለው በፈለገ ጊዜ በቤቷ የተቀበለችው አሕዛባዊቷ ምድር ግብፅ ነበረች (ማቴ. 2፡13-15)። ከአሕዛብ ወገን የነበረው የመቶ አለቃ በብዙ አይሁዶች መካከል ያልነበረውን የእምነት ምሳሌነት አሳይቷል (ማቴ. 8፡10)። ክርስቶስ አሕዛብ ከእግዚአብሔር ቤተሰብ ጋር ስለሚቀላቀሉበት ጊዜ ተንብዮአል (ማቴ. 8፡11-12)። በመጨረሻም፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ወንጌሉን ለተለያዩ የኣሕዛብ አገሮች እንዲያደርሱ እዝዟቸዋል (ማቴ. 28፡1920)።
- የመጀመሪያው ወንጌል ክርስቶስ ሰው ብቻ ሳይሆን፥ በነገሮች ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክም እንደሆነ ያሳያል። ማቴዎስ ክርስቶስ በበሽታ (ማቴ. 9፡22፤ 14፡35-36)፥ በተፈጥሮ (ማቴ. 8፡23-27)፤ በኃጢአት (ማቴ. 9፡2)፥ በክፉ መናፍስት (ማቴ. 8፡31-32)፥ በሰዎች ዘላለማዊ ሕይወት ዕጣ ፈንታ (ማቴ. 7፡21-23፤ 24፡29-31)፥ እንዲሁም በራሱ ሕይወት ላይ (ማቴ. 16፡21፣ 20፡7-19) ሥልጣን እንዳለው አሳይቷል። ክርስቶስ ኃያል በመሆኑ፥ ሰዎች አምልከውታል (ማቴ. 8፡2፤ 14፡33)። ኢየሱስ አምላክ በመሆኑ ለሰዎች የራቀና ስለ ሰዎችም ግድ የሌለው ኣምላክ አልነበረም። ሁልጊዜ ለሰዎች ይራራ ነበር (ማቴ. 9፡36፤ 14፡14)። ሰዎች የሚፈልጉትን ዘላለማዊና መንፈሳዊ ዕረፍት የሚያገኙት በእርሱ ነው (ማቴ. 11፡28-30)።
- ማቴዎስ፥ አይሁዶች በክርስቶስ መሢሕነት ላይ ለሚያነሡዋቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደፈለገ የሚገልጹ ምሑራን አሉ። ለምሳሌ፥ ኣይሁዶች ክርስቶስ የዮሴፍ (የሥጋ ተፈጥሯዊ) ልጅ እንዳልሆነ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ ዲቃላ ነው ብለው ያስቡ ስለነበር (ዮሐ 8፡4)፤ ማቴዎስ ስለ ልደቱ በጥንቃቄ ያብራራል። ሌሎች ኢየሱስ በቤተልሔም እንዳልተወለደና ብሉይ ኪዳን ስለ መሢሑ የተነበየውን አሳብ እንደማያሟላ ይናገሩ ነበር። ማቴዎስ፥ ኢየሱስ በቤተልሔም እንደ ተወለደና የብሉይ ኪዳን የተስፋ ቃሎችን እንደ ፈጸመ ኣሳይቷል። ክርስቶስ ከወቅቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነሣ ወደ ግብፅና ናዝሬት ተጉዟል። ይህም በበኩሉ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች እንደ ተፈጸሙ የሚያሳይ ነበር። ሌላው ምሳሌ፥ ማቴዎስ ከክርስቶስ ትንሣኤ ጋር የተገናኘውን የጠባቂዎቹን ታሪክ ለማፍረስ መፈለጉ ነው (ማቴ. 28፡1115)። ማቴዎስ ጠባቂዎቹ ለምን እንደ ዋሹ ለማሳየት ወደደ።
ሌላም በሮም ግዛት የነበሩ ሰዎች ሁሉ፥ በተለይም አይሁዶች የሚያነሡት ጥያቄ ነበር። «ክርስቶስ መሢሕ ከነበረ እንዴት ይሰቀላል? የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በእርሱ ከተፈጸሙ በኋላ የሃይማኖት መሪዎች ለምን አልተቀበሉትም?» ስለሆነም ማቴዎስ፥ አይሁዶች፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች ለምን ክርስቶስን እንዳልተቀበሉ ያብራራል። ይህ የሆነው ክርስቶስ መሢሕ ስላልሆነ፥ ተኣምራትን ስላላደረገ፥ ወዘተ. . አይደለም። ክርስቶስን ያልተቀበሉት በተወዳጅነቱ ስለ ቀኑበትና ለሰው ሥርዓቶች ባለመገዛቱ ስለ ተበሳጩበት ነበር።
ልዩ ገጽታዎች
1 ስለ ቤተ ክርስቲያን በቀጥታ የተናገረው የማቴዎስ ወንጌል ብቻ ነው (ማቴ. 16፡18-19፤ 18፡17)። ማቴዎስ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሰው ሳይሆን የክርስቶስ ሥራ እንደሆነ ያሳያል። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን ስለሚገነባ፥ የትኛውም መንግሥት ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የሚያደርገው ጥረት ሊሳካና የቤተ ክርስቲያንም ዕድገት ሊገታ አይችልም። ክርስቲያኖች ለቤተ ክርስቲያን ንጽሕናና ኣንድነት ተግተው ሊሠሩ ይገባል። በተጨማሪም፥ ዐመፀኝነትንና ኃጢአትን ለማስወገድ መትጋት አለብን። ስለሆነም ሰዎች ሕይወታቸውን ለክርስቶስ ሥልጣን እንዲያስገዙ ካደረግን በኋላ፥ ንጉሥ ለሆነው ክርስቶስ ለመገዛት የማይፈልጉትን እንድናስወግድ ታዝዘናል (ማቴ. 18፡5-17)።
- ኢየሱስ በሠራው ሥራ ላይ ካተኮሩት ከሌሎች ተመሳሳይ ወንጌላት ይልቅ፥ ማቴዎስ ለክርስቶስ ትምህርት አጽንኦት ሰጥቷል። እንዲያውም ክርስቶስ ካስተማራቸው ነገሮች ውስጥ ረጅሙ ክፍል በማቴዎስ 5-7 ውስጥ ይገኛል። ይህም ክርስቶስ ያስተማራቸው የተለያዩ ትምህርቶች ማጠቃለያ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ምንባብ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ የሚፈልጋቸውን ውስጣዊ ባሕርያት ያሳያል። ክርስቶስ ስለ ወንጌል ስርጭት የሰጠው ትምህርት (ማቴ. 10)፥ ምሳሌዎቹ (ማቴ. 13)፥ የይቅርታ ትምህርቱ (ማቴ. 18)፥ እንዲሁም የመጨረሻ ዘመን ትምህርቱ (ማቴ. 24-25) በተለያዩ ክፍሎች ቀርቧል።
- ማቴዎስ የክርስቶስን ታሪክ ሲዘግብ፥ የደቀ መዛሙርቱ መጠራት በቤተ ክርስቲያ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ መሆኑን አመልክቷል። ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረ፥ እንዳስተማረና ተአምራትን እንዳደረገ፥ ክርስቶስ ለዓለም ኃጢአት በመሞት በትንሣኤው አምላክነቱን እንዳረጋገጠ፥ እንዲሁም በተቀረው ታሪክ ሁሉ ከተከታዮቹ ጋር ለመኖር ቃል መግባቱን ከማቴዎስ ዘገባ እንረዳለን (ማቴ. 28፡20)። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ፥ ማዕበሉን ፀጥ ያሰኘው ጌታ፥ ዛሬም ኃይል እንዳለውና የሕይወታችንን ማዕበል እንደሚቆጣጠር መገንዘብ አለብን።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በማንኛውም ዘመን ለሚኖሩ የክርስቶስ ተከታዮች ምሳሌ ናቸው። ዋጋው ምንም ያህል ታላቅ ቢሆንም፥ ክርስቶስን ከመከተል ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ተጠርተዋል። ወንጌሉን ወደ ዓለም ሁሉ ማድረስ ነበረባቸው። የክርስቶስን ቃል በመናገር የሚያምኑ ሰዎች የኃጢአትን ይቅርታ እንደሚያገኙና የማያምኑት ግን ዘላለማዊ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል (ማቴ. 16፡18-19)። የክርስቶስን ትእዛዛት ለመፈጸም እስከሚያዳግታቸው ድረስ በቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ አያስፈልጋቸውም ነበር (ማቴ. 10፡9-10)። ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ ክርስቶስ ሸክማቸውን እንደሚያግዝ ማወቅ ያስፈልጋቸው ነበር (ማቴ. 1፡28-30)።
- ማቴዎስ በሕግ ላይ ትኩረት ሰጥቷል። የአይሁዶች የሃይማኖት ግንዛቤ የመነጨው ከሙሴ ሕግ ነበር። ለሕጉ መታዘዝ መልካም አይሁዶች መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር ሊያደርጉት የሚገባቸውን ግዴታ እየተወጡ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ያስቡ ነበር። አንድ ሰው የሚከተላቸው ሕግጋት እየበዙ ሲሄዱ፥ መንፈሳዊነት እየጠነከረ እንደሚሄድ ይታሰብ ነበር። ማቴዎስ ስለ እግዚአብሔር ሕግ ጠቃሚ ነገሮችን አስተምሯል።
ሀ. ማቴዎስ የእግዚአብሔር ሕግ ዘላለማዊ እንደሆነ ገልጾአል። ከሕግ አንዲት ነጥብ እንኳ ከእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አትወድቅም (ማቴ. 5፡18)። ይህም ክርስትና የብሉይ ኪዳንን ሕግ እንዳላስወገደ፥ ዳሩ ግን እንደፈጸመው ያሳያል።
ለ ላይ ላዩን ለሕግ ከመታዘዝ ይልቅ፥ እግዚአብሔር ሕጉን የሰጠበትን ምክንያት ማወቅና የሕጉን መንፈስ መታዘዝ እንደሚልቅ ከማቴዎስ ወንጌል መረዳት ይቻላል። ስለሆነም ምንም እንኳ ዝሙትን አለመፈጸሙ አስፈላጊ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ለመከላከል የፈለገው የዝሙትን ተግባርን ብቻ ሳይሆን፥ ወደ ዝሙት የሚመራውን የልብ ምኞት ጭምር ነበር።
ሔ ማቴዎስ አይሁዶች የሃይማኖት ማዕከል አድርገው የሚመለከቱትን ሕግን መጠበቅ አስመልክቶ፥ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የክርስቶስ ቀንደኛ ጠላቶች የነበሩት በብሉይ ኪዳን ላይ ሕግ እየጨመሩ ሰዎች እንዲጠብቁ የሚያስገድዱ ወገኖች ነበሩ። ከማቴዎስ ልዩ ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለ ሃይማኖትና ሕግ ከፈሪሳውያን ጋር የሚያካሂደው የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።
መ. አምላክ በመሆኑ ክርስቶስ ክብሉይ ኪዳን ሕግ ጋር እኩል ነበር። እግዚአብሔር ነፍስ ግድያ፥ ዝሙት ወይም ሰንበትን ማክበር ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ የበየነው እርሱ ነበር። ቃሉቹ እንደ ብሉይ ኪዳን ሕግ ዘላለማዊ ነበሩ (ማቴ. 24፡35)።
6ኛ የውይይት ጥያቄ፦ ሀ) እኛም መንፈሳዊነትን ሕግን በመጠበቅ እንደምንናገር የሚያሳዩ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ደንቦችን እየጠቀስህ አብራራ። ለ) ይህ ጠቃሚ የሚሆነው እንዴት ነው? ጎጂስ የሚሆነው? ሐ) ሰዎች ከሚደነግጓቸው አንዳንድ ሕግጋት ይልቅ ከኃጢአት በስተ ጀርባ ያሉትን እመላካከቶችና ምክንያቶች የማናጤነው ለምንድን ነው? አንድ ምሳሌ ስጥ። ይህንን የምናደርገው እንዴት ነው?
(ማብራሪያዎቹ ሁሉ የተወሰዱት በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የብሉይ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)