ለመጀመሪያው ወንጌል የተሰጠው ስያሜ፥ «የማቴዎስ ወንጌል» የሚል ነው። ይህ ስያሜ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስለሚገኘው የመጀመሪያው መጽሐፍ ሁለት ዐበይት ቁም ነገሮችን ያስጨብጠናል። አንደኛው፥ መጽሐፉ «ወንጌል » እንደሆነ ተገልጾአል። በሌላ አነጋገር መጽሐፉ ለሌሎች መነገር የሚገባው መልካም የምሥራች ነው። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ በመሞት፥ ሰዎች የዘላለም ሕይወትን ስለሚያገኙበት መንገድ የሚናገር የምሥራች ነው። ሁለተኛው፥ ርእሱ ማቴዎስ የመጽሐፉ ጸሐፊ መሆኑን ያሳያል።
ምሑራን ለመጽሐፉ የተሰጠውን ስያሜ ማቴዎስ ይጻፈው ወይም አይጻፈው እርግጠኞች አይደሉም። ምናልባትም ስያሜው የመጽሐፉ አካል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን «የማቴዎስ ወንጌል» የሚለው ስያሜ የመጀመሪያው ወንጌል ከተጻፈ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ተጨመረ የሚያመለክት መረጃ አለ። በ125 ዓ.ም. የነበረው የማቴዎስ መጽሐፍ ቅጂ «የማቴዎስ ወንጌል» የሚል መጠሪያ ነበረው። ይህም የመጀመሪያው ወንጌል የክርስቶስ ሐዋርያ በሆነው ማቴዎስ እንደ ተጻፈ የሚያመለክተውን የቀድሞ ክርስቲያኖች አመለካከት ያጠናክራል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ምሑራን መጽሐፉ በማቴዎስ መጻፉን መጠራጠር ጀምረዋል። መጽሐፉ የዐይን ምስክር በነበረ ሰው የተጻፈ አይመስልም ይላሉ። በተጨማሪም፥ ከማቴዎስና ከሌሎችም ሐዋርያት ሞት በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰቱትን ሁኔታዎች እንደሚጨምር ያስረዳሉ። ነገር ግን ይህ መጽሐፍ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እንደምታምነው የክርስቶስ ሐዋርያ በነበረው በማቴዎስ እንደ ተጻፈ የሚያመለክት ጠንካራ መረጃ አለ።
ማቴዎስ በሰው አስተሳሰብ፥ ሐዋርያ መሆኑ ቀርቶ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እጅግ ጠቃሚ ከሆኑት መጻሕፍት አንዱን ለመጻፍ ብቁ አይመስልም። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር የሚሠራው እኛ በምንጠብቀው መንገድ አይደለም። ለዚህም ነው መንፈስ ቅዱስ ማቴዎስ የመጀመሪያው ወንጌል ጸሐፊ እንዲሆን ያደረገው።
ሌዊ ይባል የነበረው ማቴዎስ፥ አይሁዳዊ ነበር (ማር. 2፡14)። ነገር ግን፥ በመንፈሳዊ ሕይወቱና በብሉይ ኪዳን ዕውቀቱ የተከበረ ኣጥባቂ አልነበረም። ማቴዎስ ቅፍርናሆምን አቋርጠው በሚያልፉ ዐቢይ የንግድ ጎዳናዎች እየዞረ ቀረጥ የሚሰበስብ ሰው ነበር። ማቴዎስ ይህንን ሥራ ለማግኘት የአሕዛብ ወይም የፖለቲካ ባለሥልጣናት ወዳጅ መሆን ሳያስፈልገው አልቀረም። ብዙውን ጊዜ ይህን ሥራ የሚያገኙት ለአሕዛብ መሪዎች ጉቦ የሰጡ ወይም የአይሁድ ሊቀ ካህናት ነበሩ። ምንም እንኳ አይሁዶች ቀራጮችን ቢጠሏቸውም፥ ማቴዎስ ገንዘብን በመውደዱ ምክንያት አሕዛብ ለዚህ ሥራ ይመርጡት ዘንድ እንደ አይሁዳዊ ራሱን ለማዋረድና እንዳንድ ጥብቅ የአይሁድ ልማዶችን ለመተው ወስኗል። ምናልባትም ከአሕዛብ ጋር የነበረውን
ወዳጅነቱን የሚጠሉ አይሁዶች ሳይተፉበት፥ ሳያላግጡበትና ሳይንቁት አልቀሩም። አብዛኞቹ ቀራጮች ተጨማሪ ገንዘብ ለመሰብሰብ ይስገበቡ ነበር። ስለሆነም ሮማውያን ከአንድ ተጓዥ ነጋዴ ላይ 100 ብር እንዲቀበሉ ቢያዛቸው፥ ነጋዴው መቶውን ብር ከመክፈል ነፃ የሚሆንበትን መንገድ ለማመቻቸት ጉቦ መቀበል ወይም ተጨማሪ 20 ብር በመጠየቅ፥ በጠቅላላው 120 ብር ያስከፍሉት ነበር። ሮማውያኑ የጠየቁትን ገንዘብ ከተቀበሉ፥ ቀራጩ ከነጋዴው ምን ያህል እንደ ተቀበለ አያሳስባቸውም ነበር።
1ኛ የውይይት ጥያቄ፡– በኢትዮጵያ ብዙ ሰው የሚጠላቸው ሰዎች ምን ዐይነት ናቸው? የቤተ ክርስቲያን ምእመናን እንደዚያ ያለውን የማይመርጡበት ወይም ለቤተ ክርስቲያን መሪነት የማያጨበት ምክንያት ምንድን ነው? (ለምሳሌ፥ እንዲት ሴተኛ አዳሪ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥታ በክርስቶስ ለማመን ብትፈልግ የምእመናን ምላሽ ምን ይሆናል? በክርስቶስ ካመነች በኋላስ ከእርሷ ጋር የሚዛመዱት እንዴት ነው? ከእርሷ ጋር ጓደኛ ለመሆን ይፈቅዳሉ?
አንድ ቀን ኢየሱስ ማቴዎስ እንዲከተለው ጠየቀው። ማቴዎስ ክርስቶስን ለመከተል ስለመሞከሩ የሚያመላክት መረጃ የለም። ነገር ግን ማቴዎስ የክርስቶስን ማንነት ሳያውቅ አይቀርም። ክርስቶስ በቅፍርናሆም ከማገልገሉም በላይ፥ ትምህርቱ ብዙዎችን አስደንቋል። ማቴዎስ ከክርስቶስ ተአምራት ስለ አንዳንዶቹ ሳያውቅ አልቀረም። ምናልባትም ክርስቶስ በማቴዎስ ልብ ውስጥ የነበረውን ባዶነት፥ ሕይወቱን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስተካከልና በሰዎች ላለመናቅ መናፈቁን ተመልክቶ ይሆናል። ክርስቶስ በጠራው ጊዜ ማቴዎስ ከአስቸጋሪ ምርጫ ላይ ወደቀ። ክርስቶስ ሥራውንና ኑሮውን ትቶ ሥራ የሌለው ድሃ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ነበር የጠየቀው። በሥራው ላይ ለመቆየት፥ ገንዘብ ለመሰብሰብና በሕይወቱ ለመደላደል ይመርጥ ይሆን? ወይስ ሥራም፥ ሀብትም፥ ዋስትናም የሚሆነውን የጌታን መንገድ ይከተል ይሆን?
2ኛ የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በማቴዎስ ቦታ ብትሆን ኖሮ ምርጫህ ምን ይሆን ነበር? ለ) ክርስቲያን በሆንህ ጊዜ፥ ክርስቶስ ያስመረጠህ ነገር ምን ነበር?
ማቴዎስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ሲል፥ ሁሉንም ነገር ተወ። ማቴዎስ ክርስቶስን መከተል ስለሚያስከፍለው ዋጋ ለማስተማር የፈለገው ምናልባትም ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስን መከተል ድህነት ቢኖርበትም እንኳ የዘላለምን ሕይወት ያስገኛል።
ማቴዎስ ክርስቶስን በመከተሉ የቀራጭነቱን ተግባር ያቆመ ብቻ ሳይሆን፥ ድርጊቱ የሕይወት አመለካከቱን በሙሉ ሊለውጠው ችሎአል። ማቴዎስ በመጀመሪያ ለማድረግ ከፈለጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ፥ የቀድሞ ወዳጆቹን በሙሉ ከክርስቶስ ጋር በማስተዋወቅ፥ የክርስቶስ ተከታይ መሆኑን በይፋ ማሳወቅ ነበር። ለዚህም ያመቸው ዘንድ ወዳጆቹንና ቀራጭ የሥራ ባልደረቦቹን ግብዣ ጠራቸው።
ከዚያም ብዙ ሳይቆይ፥ ክርስቶስ ማቴዎስን ከ12ቱ ቁልፍ ደቀ መዛሙርት አንዱ እንዲሆን መረጠው (ማቴ. 10፡1-4)። እነዚህ አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በኋላ የቤተ ክርስቲያን ዋና መሪዎች ለመሆን ችለዋል። ክርስቶስ «ሐዋርያት» ብሎ በመሰየም በዓለም ውስጥ የእርሱ አምባሳደሮችና እንደራሴዎች አድርጎ በመሾም ልኳቸዋል። ማቴዎስ ከሦስት ዓመታት በላይ የክርስቶስን ትምህርት እየተማረና፥ ተአምራቱን እየተመለከተ ተከትሎታል። ከሞት የተነሣውን ጌታ ከመመልከቱም በላይ፥ ክርስቶስ ለተቀረው ዓለም ሁሉ ወንጌሉን እንዲያዳርሱ ሲያዛቸው ሰምቷል (የሐዋ. 1፡8)።
ማቴዎስ ከመጀመሪያው የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ ማቴዎስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አገልግሎታቸውን ያተኮሩት የመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አካል እንደሆነ ይታወቃል። የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ስለ ማቴዎስ የሚሰጠን መረጃ ግልጽ አይደለም። አንድ ትውፊት እንደሚለው፥ በኢየሩሳሌም አሥራ አምስት ዓመት ከተቀመጠ በኋላ፥ በውጪ አገሮች ወንጌልን ሰብኳል። ይህም በኢትዮጵያ፥ በፋርስ(ኢራን)፥ እንዲሁም በአርመን ወንጌልን እንደ ሰበከ ይናገራል። የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚለው፥ ማቴዎስ በእምነቱ ምክንያት ሰማዕት ሆኖ ተሠውቷል።
ለሮም መንግሥት ዝርዝር ታሪኮችን የሚመዘግብ ቀራጭ የነበረው ማቴዎስ፥ ከክርስቶስ ጋር በነበረ ጊዜም ታሪክ መመዝገቡን ቀጥሎ ይሆናል። ከክርስቶስ ስብከቶችና ተአምራት አንዳንዶቹን ሳይጽፍ አልቀረም። ምናልባትም የክርስቶስን ታሪክ የጻፈው በእነዚህ ታሪኮች ላይ ተመሥርቶ ይሆናል። ክርስቶስ ቀረጥ የከፈለበትን ሁኔታ ቀራጩ ማቴዎስ ብቻ መጥቀሱ ሌላው አስገራሚ ነገር ነው (ማቴ. 17፡24-27)።
3ኛ የውይይት ጥያቄ፡- የማቴዎስ ታሪክ፥ በሰዎች ላይ አስቀድመን በመፍረድ፥ ሰዎች ክርስቲያኖች ሊሆኑና እግዚአብሔርን ሊያገለግሉ እንደማይችሉ አድርገን ከማሰብ እንድንቆጠብ የሚያስተምረን እንዴት ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)