የንጉሡ የኢየሱስ ልደት (ማቴ. 1፡18-2፡23)

የክርስቶስን ልደት የሚገልጹ ወንጌላት ሁለት ብቻ ናቸው። ከእነዚህ ሁለቱ መካከል፥ ሉቃስ ስለ ክርስቶስ ልደት ሰፊ ምርምር ኣካሂዷል። ሉቃስ የክርስቶስን ልደት ከማርያም እይታ አንጻር ሲመለከት፥ ማቴዎስ ግን ከዮሴፍ እይታ አንጻር ይመለከታል።

የክርስቶስ ልደት የሆነው ዮሴፍና ማርያም ተጫጭተው ባሉበት ወቅት ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ፥ የአይሁድ መተጫጨት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ስለ ነበሩ፥ መቋረጥ የሚችሉት በፍች ነበር። በሚተጫጩበት ወቅት ማርያም «በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች» (ማቴ. 1፡18)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እጮኛህ ያረገዝሁት ከሌላ ወንድ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ ነው ብትልህ ምን ትላታለህ? ለ) ለዮሴፍ ማርያምን ማመኑ ምን ያህል ከባድ ነበር?

ማርያም ስለሆነው ነገር ለዮሴፍ ገልጻለት ይሆናል። ስለዚህ የተጠቀሰ ነገር የለም። ነገር ግን ዮሴፍ በሆነ መንገድ ደርሶበታል። ነገር ግን ዮሴፍ የዋህ ሰው ስለ ነበር፥ ከሌላ ወንድ ለማርገዟ በይፋ ሊወቅሳት አልፈለገም። ስለሆነም ለእርሷ ሳይነግራት በስውር ሊተዋት አሰበ። እግዚአብሔር ግን ማርያም በትክክል ከመንፈስ ቅዱስ እንደፀነሰች ለዮሴፍ ለመንገር መልአኩን ላከ። ማርያም ከሌላ ሰው ጋር አላመነዘረችም ነበር። ምንም እንኳ ማርያም በማርግዟ ቢቀልዱባትም፥ ዮሴፍ እግዚአብሔርን ታዝዞ ማርያምን ወሰዳት።

እግዚአብሔር በዚህ መሢሑን ወደ ዓለም በመላኩ ሂደት ማርያምን ብቻ ሳይሆን ዮሴፍንም አክብሯል። እንደ ባልና የቤት ራስ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ዮሴፍ ለልጁ ስም እንዲያወጣ መብት ሰጠው። ለክርስቶስ ስም በማውጣቱ፥ ዮሴፍ ሕጋዊ ኣባትነቱን እያረጋገጠ ነበር። እግዚአብሔር ዮሴፍ ልጁን «ኢያሱ» (ዕብራዊ ስም) ወይም «ኢየሱስ» (ግሪካዊ ስም) ብሎ እንዲጠራ ነገረው። የሁለቱም ስሞች ፍች «እግዚእብሔር ደኅንነት ነው» የሚል ነው። ይህም የመሢሑ ቀዳሚ ተግባር ድል ነሺ ንጉሥ መሆን ሳይሆን፥ አዳኝ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። ክርስቶስ «ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድን» መንፈሳዊ አዳኝ እንጂ ፖለቲካዊ ነፃ አውጪ እንዳልሆነ ማቴዎስ ገልጾአል።

ማቴዎስ፥ የድንግሊቱ መውለድና የክርስቶስ ልደት ዝርዝር ጉዳዮች ሁሉ፥ በእግዚአብሔር በጥንቃቄ እንደታቀዱና በብሉይ ኪዳን እንደተተነበዩ አስረድቷል። ማርያም በሚያስደንቅ መንገድ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ስለ ወለደች፥ ኢየሱስ ሰውም አምላክም ሆኗል። ይህም እርሱ ብቻ «አማኑኤል» ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆኖኣል (ኢሳ. 7፡14)። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር የክብር ደመናውን በሰዎች መካከል ያኖረ ሲሆን፥ አሁን ግን እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በሰዎች መካከል አድሯል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከመመለሱ በፊት፥ ለደቀ መዛሙርቱ አሁንም አማኑኤል እንደሚሆን፥ ማለትም እስከ መጨረሻው አብሯቸው እንደሚሆን ገልጾአል (ማቴ. 28፡1820 አንብብ።) ማቴዎስ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት በመፈጸም በቤተልሔም እንደ ተወለደ ተናግሯል።

ለአይሁዶች እግዚአብሔር ለአሕዛብም ዕቅድ እንዳለው ማቴዎስ አመልክቷል። እንዲሁም መጀመሪያ ክርስቶስን ያከበሩትና ያመለኩት ሰብዓ ሰገል መሆናቸውን ገልጾአል። ማቴዎስ እነዚህ ሰብዓ ሰገል ከየት እንደ መጡ ወይም ስንት እንደሆኑ አልጠቀሰም። በክርስትና ትውፊት ሦስት ሰዎች እንደሆኑ የሚታመነው ካበረከቱት ስጦታ በመነሣት ነው። ለእነዚህ ሰዎች የተሰጠው የግሪክ ስያሜ «ማጂ» (magi) የሚል ነው። ማጂ የልዩ ሃይማኖታዊ ሰዎች ቡድን ሲሆን፥ ብዙ ምሑራን ከፋርስ ወይም ከሳውዲ ዓረቢያ እንደ መጡ ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች በከዋክብት ጥናት ይካኑ እንጂ፥ ስለ እግዚአብሔርም በቂ ግንዛቤ የነበራቸው ይመስላል። ያዩት አዲስ ኮከብ ለአይሁዶች ልዩ ንጉሥ እንደ ተወለደ የሚያመለክት መሆኑን የተረዱ ይመስላል። ለመስገድ መፈለጋቸው ደግሞ ይህ ንጉሥ ከተራ ንጉሥ በላይ መሆኑን እንደ ተገነዘቡ ያሳያል። የአይሁዶች መዲና ወደሆነችው ኢየሩሳሌም እስኪደርሱ ድረስ ለብዙ ወራት ኮከቡን ተከትለው ተጓዙ። ንጉሡ በቤተ መንግሥት ይወለዳል ብለው ስለ ገመቱ፥ ወደ ንጉሥ ሄሮድስ ሄደው ኣዲስ ስለ ተወለደው ንጉሥ ጠየቁ።

ቀደም ሲል ዙፋኔን ይነጥቁብኛል በሚል ስጋት ከቤተሰቡ አባላት መካከል ብዙ ሰዎችን የፈጀው ንጉሥ ሄሮድስ፥ ይህን ሲሰማ ደነገጠ። በመጀመሪያ፥ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎችን ሰብስቦ ጠየቃቸው። እነዚህ ሰዎች በብሉይ ኪዳን እንደተነገረው መሢሑ ከኢየሩሳሌም ሰባት ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በምትገኘው በቤተልሔም እንደሚወለድ ያውቁ ነበር። ሄሮድስ ያለበትን ስፍራ አይተው እንዲነግሩት በማዘዝ ሰብዓ ሰገልን ወደ ቤተልሔም ላካቸው። ምንም እንኳ ሄሮድስ ሕጻኑን ንጉሥ ለማክበር እንደፈለገ ቢነግራቸውም፥ እውነተኛ ፍላጎቱ ግን ሕጻኑን መግደል ነበር። ኮከቡ እንደገና ለሰብዓ ሰገል ተገልጦ፥ ኢየሱስ ወደነበረበት ወደ ቤተልሔም መራቸው።

ማቴዎስን ከሉቃስ ትረካ ጋር በማነጻጸር እንደምንገነዘበው፥ ኢየሱስ ከተወለደ የተወሰነ ጊዜ አልፎ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ከተወለደበት ግርግም ወደ ቤት ተዛውሮ ነበር። ይህም የዘመድ ቤት ወይም እነዮሴፍ የተከራዩት ቤት ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ከተወለደ ምን ያህል ጊዜ እንዳለፈ አናውቅም። ሄሮድስ ከሰብዓ ሰገል ኮከቡ መጀመሪያ የታየበትን ጊዜ ተረድቶ እስከ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ሕጻናት ሁሉ ስለ ገደለ፥ ኢየሱስ ከተወለደ ሁለት ዓመታት ሳይሞላው ኣይቀርም ተብሎ ይገመታል። ሰብዓ ሰገል ስጦታዎችን በመስጠትና እንደ አምላክ በማምለክ ክርስቶስን አክብረውታል።

እግዚአብሔርም ለሰብዓ ሰገል ያዩትን ለሄሮድስ ሳይናገሩ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል። በዚህ ታሪክ ማቴዎስ እግዚአብሔር የአይሁዶች ብቻ አምላክ እንዳልሆነና አሕዛብም የዕቅዱ አካል መሆናቸውን አመልክቷል። ክርስቶስ መሢሕ እንደሆነ በመጀመሪያ ከተገነዘቡት ሰዎች አንዳንዶቹ አሕዛብ ነበሩ። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን አንቀበለውም ቢሉም፥ የአሕዛብ ሃይማኖት መሪዎች ግን ሰግደውለታል። ዓለም ስለ እነርሱ ምንም ዐይነት አመለካከት ቢኖረውም ወንጌሉን ብዙውን ጊዜ እናውቃለን ከሚሉት የተሰወረው እውነት ልባቸውን ለከፈቱት ተገልጧል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ዓለም የሚንቃቸውን እየመረጠ፥ ታላላቆች ነን ብለው በማሰብ በዕውቀታቸው ወይም በሥልጣናቸው የሚኩራሩትን ሰዎች እንዴት እንደሚንቅ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ከመሢሑ ታሪክ በስተጀርባ መንፈሳዊ ውጊያ አለ፡፡ ሰይጣን መሢሑን ለማጥፋት ፈልጎ ነበር። ይህንንም ያደረገው በዓለም ላይ ያለውን ኃይሉን እንደሚሽርበት ስለ ተገነዘበ ነበር። እግዚአብሔር ግን ልጁ ዕቅዶቹን ፈጽሞ፥ በመስቀል ላይ እንዲሞት ወስኖ ነበር። ስለዚህ ሰይጣን ኢየሱስን ለመግደል በሄሮድስ ልብ ውስጥ ያሴር እንደነበረ እግዚአብሔር በመገንዘብ፥ ዮሴፍ በመጀመሪያ ወደ ግብፅ ይዞት እንዲወርድ ከዚያም ወደ ናዝሬት ይዞት እንዲመለስ አዘዘው። ከዚያም ሄሮድስ ወደ ቤተልሔም ተጉዞ እስከ ሁለት ዓመት ዕድሜ የሆናቸውን ሕጻናት ሁሉ አስገደለ። ይህም ሰብዓ ሰገል ኢየሱስን ለማየት የመጡት ቢያንስ ከኣንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት በሆነው ጊዜ ሳይሆን አይቀርም ወደሚል ድምዳሚ ይመራናል።

በክርስቶስ ልደት ዙሪያ በተከናወኑት በእነዚህ ክስተቶች ሁሉ፥ የእግዚአብሔር እጅ እንደ ነበረበት ማቴዎስ ያውቅ ነበር። የሕጻናቱ መገደል፥ የክርስቶስ ከግብፅና በኋላም ከናዝሬት መምጣት፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ተተንብዮአል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ ታሪኮች፥ የታሪክ ጌታ ስለሆነው ልዑል አምላክ ምን መማር እንችላለን? ለ) እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ነገሮችን ሁሉ መቆጣጠሩ እንዴት ሊያበረታታን ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

%d bloggers like this: