ተስፋዬ ክርስቲያን ነጋዴ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ንግዱን በሚያካሄድበት መንገድ ሊከብር እንደሚፈልግ ያውቃል። ነገር ግን ጉቦ ካልከፈለ ባለሥልጣናቱ የንግድ ፈቃዱን እንደማያድሱለት ይገነዘባል። «ጉቦ ብሰጣቸው ምን አለበት?» ሲል አሰበ። ስለሆነም ተስፋዬ ጉቦ በመስጠት የንግድ ፈቃዱን ኣሳደሰ። ሰዎች ጉቦ መስጠቱን ሲገነዘቡ፥ ወዲያው እውነተኛ ሰው አለመሆኑን አወቁ። ጌታሁን ወደ አሜሪካ ሄዶ ለመማርና እዚያው ለመኖር የሚፈልግ ብሩኅ አእምሮ ያለው ተማሪ ነበር። በታማኝነት እዚያው ለመኖር እንደሚፈልግ ለኤምባሲው ኃላፊዎች ሲናገር ቪዛ እንደማይሰጠው ያውቃል። ስለሆነም ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ተመልሶ እንደሚመጣ ቃል ገባላቸው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች የሚፈልጓቸውን ነገሮች ለመፈጸም ሲሉ የተሳሳቱ ነገሮችን ለማከናወን እንደሚፈተኑ የሚያሳዩ ሌሎች ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) ፈተናቸው ምን ነበር? ሐ) እግዚኣብሔር ተግባሮቻቸውን እንዲያከናውኑ የሚፈልገው እንዴት ይመስልሃል? መ) የምንፈልገውን ነገር ለማግኘት ስንል የተሳሳቱ ዘዴዎችን የምንጠቀም ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ላይ ስላለን እምነት ምን እያሳየን ነው? ሀ) በቅርቡ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ስትል ምን ለማድረግ ተፈትነህ ነበር?
ሁላችንም ሰይጣን ፈታኝ መሆኑን እናውቃለን። እርሱና ረዳቶቹ የሆኑት ኣጋንንት የእግዚአብሔር ሕዝብ ኃጢኣትን እንዲፈጽም ባለማቋረጥ ይፈትናሉ። ከፈተኑን በኋላ ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ይከሱናል። (ሰዕብራይስጡ «ሰይጣን» እና በግሪኩ «ዲያብሎስ› ማለት ከሳሽ ማለት ነው። ይህም ሰይጣን አማኞች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ እንደሚከሳቸው ያሳያል።) አንድ የተሳሳተ ተግባር ለመፈጸም በምንነሣበት ጊዜ እንፈተናለን። ነገሩ መልካም ወይም አስደሳች ይመስላል። የምንፈልገውን ነገር የምናገኝበት አቋራጭ መንገድ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ይህ ሁልጊዜም እግዚአብሔር ለእኛ ከሚፈልገው መንገድ ውጭ ነው። ሔዋን እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ስለ ፈለገች፥ መልካሙንና ክፉውን የምታስታውቀውን ፍሬ በላች። ወሲባዊ እርካታን ስለምንፈልግ፥ የጋብቻችን ጊዜ ሳይደርስ አሁኑኑ በአቋራጭ መንገድ ለመፈጸም እንሻለን። ወይም ቁሳዊ ሀብቶችን እንፈልግና እግዚአብሔር በጊዜው እንዲባርከን ከመጠበቅ ይልቅ አንድን ነገር ለማግኘት እንዋሻለን፤ ስለዚህ ጉቦ እንሰጣለን።
ስለ ክርስቶስ ከሚያስደንቁን ነገሮች አንዱ፥ እግዚአብሔር ልጁም እንደኛ እንዲፈተን መፍቀዱ ነው። በዕብ 2፡17-18፤ 4፡15 ላይ ከኃጢአት በስተቀር በሁሉም ነገር እንደኛ የተፈተነ ሊቀ ካህናት እንዳለን ተገልጾአል። ፈተና ሲያጋጥመን እንድናሸንፍ የሚረዳን ስለዚህ ነው።
ልጁ ለአገልግሎት በሚዘጋጅበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆን ብሎ ልጁ እንዲፈተን አድርጓል። እንዲያውም በምድረ በዳ በዲያብሎስ እንዲፈተን ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነበር። ክርስቶስ ለ40 ቀናት ያለምግብ በቆየባቸው ጊዜያት በተለያዩ መንገዶች ተፈትኗል። ዋንኛው ፈተና የተከሰተው ግን፥ ያለ ምግብ በቆየባቸው 40 ቀናት መጨረሻ ላይ ነበር። መሢሑ አካላዊ ድካም በተጫጫነው ሰዓት፥ ሰይጣን እርሱን ለማጥመድ የሚችልበት አጋጣሚ እንደደረሰ አሰበ። ሰይጣን ሁልጊዜ የሚፈትነን ደካማ በምንሆንበት ነገር ነው። በክርስቶስም ላይ ያደረገው ይህንኑ ነበር ። ፈተናዎቹ ክርስቶስ እንደ መሢሕ ከሚያጋጥሙት ነገሮች ጋር የሚዛመዱ ነበሩ።
ማቴዎስ ይህንን ታሪክ የሚገልጸው ሰይጣን እያንዳንዳችንን እንዴት እንደሚፈትነንና ፈተናውን እንዴት እንደምንቋቋም ለማሳየት ነው። ክርስቶስ የተፈተነው በሦስት የሕይወት ፈርጆች ሲሆን፥ እነዚህም የሥጋ ምኞት፥ የሕይወት ትምክሕትና የዐይን አምሮት ናቸው (1ኛ ዮሐ. 2፡16)። አንዳንድ ምሑራን የዚህ ፈተና ውጤት የኣዳምና ሔዋን ፈተና ውጤት ተቃራኒ መሆኑን ይናገራሉ። የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ ወላጆች በፈተናው ወድቀው ሞትን ሲያመጡ፥ «ሁለተኛው አዳም» ፈተናውን ተቋቁሞ የሰውን ልጅ ሊታደግ ችሏል (ሮሜ 5፡12-19)። ሌሎች ምሑራን የክርስቶስን ፈተና ከአይሁዶች በምድረ በዳ መቅበዝበዝ ጋር ያመሳስላሉ። ኣይሁዶች ለ40 ዓመት በምድረ በዳ እንደ ተቅበዘበዙ ሁሉ፥ ክርስቶስም ለ40 ቀናት በምድረ በዳ ውስጥ ቆይቷል። በምድረ እስራኤል ውስጥ በመቅበዝበዟ እንደ አገር የምትደራጅበትን ሁኔታ እንዳዘጋጀ ሁሉ (ዘዳግ. 8፡2-3)፥ የክርስቶስም ፈተና የእስራኤል መሢሕ እንዲሆን አዘጋጅቶታል። ኢየሱስ፥ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ከእስራኤል የፈለገውን ታዛዥነትና በመከራ ውስጥ በእርሱ የመታመን ምሳሌ ሆነ።
የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ 2፡15-18፤ 5፡ 7-8 ኣንብብ። ሀ) የክርስቶስ መፈተንና መሠቃየት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ለ) ክርስቶስ እንደ እኛ መፈተኑ በምን መንገዶች ሊያበረታታን ይችላል?
የመጀመሪያው ፈተና ድንጋይን ወደ ዳቦ መለወጥ ነበር። ክርስቶስ ለ40 ቀናት ከጾመ በኋላ በረሃብ ደክሞ ነበር። ድንጋይን ወደ ዳቦ መለወጡ ምን ችግር አለው? ክርስቶስ እንጀራ አብዝቶ ሰዎችን መግቦ የለ! በተራበበት በዚያ ሰዓት ለምን ኃይሉን ተጠቅሞ ድንጋዩን ዳቦ አላደረገውም? ፈተናው ሥልጣኑን ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለእግዚአብሔር ክብር ማዋሉ ነበር። እግዚአብሔር የፈቀደው ክርስቶስ ኃይሉን ለሌሎች ጥቅምና ለእግዚአብሔር ክብር እንዲያውል ነበር። ተኣምራትን የማድረግ ኃይሉ ለግል ጥቅሙ አልነበረም። በተጨማሪም ኢየሱስ ኃይሉን ይጠቀም የነበረው በእግዚአብሔር ሲፈቀድለት ብቻ ነበር። በኋላም ክርስቶስ አብ የነገረውን ብቻ እንደሚያደርግ ገልጾአል (ዮሐ 5፡19-20)። ሰይጣን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲጠራጠር ለማድረግ አልሞከረም። ሰይጣንም ሆነ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነቱን ያውቁ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ፥ ሥልጣኑን እግዚኣብሔር ባልፈቀደው መንገድ እንዲጠቀም እየፈተነው ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን መሪዎች ሥልጣናቸውን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ጥቅም የሚያውሉት እንዴት ነው? ለ) ይህ ስሕተት የሚሆነው እንዴት ነው?
በፊልጵ. 2፡5-8 ላይ ክርስቶስ ወደ ምድር በመምጣቱ መለኮታዊ ባሕርያቱን «ባዶ» እንዳደረገ ተገልጾአል። ምንም እንኳ ክርስቶስ አምላክነቱን ባያጣም፥ በምድር ላይ ሳለ እውነተኛ ሰው መሆኑ ይታወቅ ዘንድ እግዚአብሔር እስካልፈቀደለት ድረስ መለኮታዊ ኃይሉን ሳይጠቀም ቀርቷል። ክርስቶስ ድንጋዩን ወደ ዳቦ ለመለወጥ ወይም የግል ጥቅሞችን ለማሟላት በኃይሉ ቢጠቀም ኖሮ፥ እውነተኛ ሰው አይሆንም ነበር። በእግዚአብሔር ዕቅድ ክርስቶስ በመከራ አማካይነት መታዘዝን መማር ነበረበት (ዕብ. 5፡7-8)። ለሥጋዊ ፍላጎቶች ቅድሚያ ከሰጡት እስራኤላውያን ባሻገር፥ ፍጹም ሰው የሆነው ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለመታዘዝ ራሱን አስገዝቷል።
እዚህ ላይ ክርስቶስ ሰይጣንን እንዴት እንዳሸነፈ ማጤኑ ጠቃሚ ነው። ሔዋን እንዳደረገችው ከሰይጣን ጋር አልተሟገተም። ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቅሞ እግዚአብሔርን መታዘዝ ከምግብና ከግል ጥቅም እንደሚልቅ ገለጸለት። ያንን ሁሉ ሥልጣን የያዘው ክርስቶስ፥ ሰይጣንን ለማሸነፍ ይጠቀምበት ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ካስፈለገው፥ እኛስ ሰይጣን በሚፈትነን ጊዜ እናሸንፈው ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት ምን ያህል እጅግ ያስፈልገን ይሆን?
ለሁለተኛው ፈተና ሰይጣን ክርስቶስን በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የቤተ መቅደስ ጫፍ ወስደው። ይህ ፈተና የተሰጠው በአይሁድ ሕዝብ ፊትና በሃይማኖት ማዕከል ውስጥ ነበር። ይህ የሆነው ክርስቶስ በአካል በተገኘበት ስፍራ ይሁን በመንፈስ አልተገለጸም። (ለምሳሌ፥ ጳውሎስ ወደ ሦስተኛው ሰማይ የተወሰደው በአካል ይሁን በመንፈስ እንዳላወቀ ተናግሯል። 2ኛ ቆሮ.12፡24።) የሄሮድስ ቤተ መቅደስ ከጥንቱ ዓለም አስደናቂ ሥራዎች አንዱ ነበር። በዚህ ጊዜ ለ50 ዓመት ያህል በመገንባት ላይ ነበር። ከአንደኛው የቤተ መቅደሱ ጣሪያ ጫፍ፥ ኢየሱስ አሽቆልቁሎ የኢየሩሳሌምን ከተማ ለመመልከት ይችል ነበር።
ሰይጣን ኢየሱስ ያደረገውን በማስመሰል ለሁለተኛው ፈተና መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሷል። ክርስቶስ ከቤተ መቅደሱ ወደ ታች ራሱን እንዲወረውር ነገረው። ለዚህም አሳቡ፥ እግዚኣብሔር ክርስቶስን ለማዳን መላእክቱን እንደሚልክ የእግዚአብሔርን ቃል ጠቀሰለት [መዝ. (91)፡11-12]። ሰይጣን ይህን ሲል መጽሐፍ ቅዱስን ለራሱ ጥቅም በተሳሳተ መንገድ እየጠቀሰ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰዎች ውሸትን እንዲያምኑ ለማድረግ ሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ የሚጠቀመው እንዴት ነው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። ለ) የእግዚአብሔር ቃል በተሳሳተ መንገድ መተርጎሙን ወይም አለመተርጎሙን ለማረጋገጥ ምን ልናደርግ እንችላለን?
ይህ ሁለተኛው ፈተና ምን ነበር? አንዳንድ ሰዎች ይህ ክርስቶስ አስደናቂ ተአምራትን በመሥራት ሰዎች በራሱ እንዲያምኑ የሚረዳ እንደ ነበር ይናገራሉ። እነዚህ ወገኖች ክርስቶስ ራሱን ከቤተ መቅደሱ ቢወረውርና መላእክት ቢይዙት፥ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ሊያምኑ እንደሚችሉ ይናገራሉ። ነገር ግን ክርስቶስ በአስደናቂ ተአምራት ምክንያት ሰዎች እንዲያምኑበት አይሞከርም።
የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ሰዎች ፈተናን በትክክለኛ ምክንያት ሳይሆን፥ መንፈሳዊነታቸውን ወይም ኃይላቸውን ለማሳየት የሚጠቀሙበት እንዴት ነው?
ሰይጣን ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዲፈትን እየጠየቀው ሳይሆን አይቀርም። «አንተ የእርሱ ልጅ ነህ። እግዚአብሔርን ፈትነውና ካንተ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት እንዲያሳይ አድርግ። ራስህን ወደ ታች ወርውርና እንዲያድንህ አስገድደው» ማለቱ ነው።
ይህ ፈተና ሁለት በጣም ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስተምረናል። በመጀመሪያ፥ ሰይጣን ኃጢአት እንድንሠራ ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ እንደሚጠቀም ያሳየናል። መዝ 90፡11-12 እግዚአብሔር ልጆቹ በታዛዥነት በሚመላለሱበት ጊዜ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል። ይህ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን የምናስገድድበት አይደለም። ለዚህ ነው እግዚአብሔር በቃሉ የሚናገረውን በትክክል መተርጎም የሚያስፈልገን። ቃሉን ከጠመዘዝነው እኛ የፈለግነውን ሁሉ እንዲልልን ማድረግ እንችላለን። የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል መጠቀማችንን ለማረጋገጥ የምንችልበት አንድ ጠቃሚ መንገድ፥ ጠቅላላውን የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ማወቅና አንዱን እውነት ከሌላው ጋር ማነጻጸር ነው። እግዚአብሔር ከራሱ ጋር ስለማይቃረን፥ የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወይም አሳብ ከሌላው ክፍል ጋር እንደማይቃረን እርግጠኛች ልንሆን እንችላለን፡፡ ክርስቶስ ይህንን ስለሚያውቅ፥ እግዚአብሔር እንዲጠብቀን ለማስገደድ መፈተን እንደማይገባን ቃሉ በትክክል እንደሚያሳይ አመልክቷል።
ሁለተኛው፥ በእግዚአብሔር ላይ እምነት መጣል ምን ማለት እንደሆነ ያስተምረናል። ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር ማመናችን ከእግዚአብሔር አንድን ነገር የመጠየቅና እርሱን የመፈተን መብት ይሰጠናል ብለን እናስባለን። «እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ መፈወስ ትችላለህ። ስለሆነም፥ ይህን ግለሰብ እንድትፈውሰው እፈልጋለሁ» እንላለን። ከዚያም በቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ፊት ግለሰቡን ጠርተን ፈውስን እናውጃለን። «እግዚአብሔር እንዲፈውሰን ከነገርነውና በተለይም ኃይሉን በተአምራዊ መንገድ ለማሳየት በምንፈልግበት ጊዜ አይፈውስ ይሆን?» ብለን እናስባለን። ወይም ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት እንፈልጋለን። ምንም እንኳ የቤተ ክርስቲያኒቱ የገንዘብ አቅም ከዕቅዳችን ጋር ባይጣጣምም፥ በእግዚአብሔር «በማመን» ሥራውን እንጀምራለን። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዐይነቱ ተግባር እኛን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርንም ስም በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሳንሳል። እግዚአብሔር አንድን ሰው እንደሚፈውስ ወይም አንድን ሕንጻ እንደሚገነባ በግልጽ እስካልተናገረን ድረስ፥ እግዚአብሔር ለአስገዳጅ እምነታችን ምላሽ እንዲሰጥ መሞከሩ እርሱን መፈተን ነው። ይህም ሰይጣን ክርስቶስን የፈተነውን ዓይነት ኃጢኣት ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የሚፈልጉትን ነገር እንዲፈጽምላቸው በማስገደድ እንዴት ሊፈታተኑት እንደሚችሉ ሌሎች ምሳሌዎችን ዘርዝር። ለ) እግዚኣብሔርን የሚፈትን አስገዳጅ እምነት ከእውነተኛው እምነት እንዴት ይለያል?
አሁንም ክርስቶስ ከሰይጣን ጋር አልተከራከረም። ሰይጣን ለምን እንደሚፈትነው ተረድቶ ነበር። ጉዳዩ የራስ ወዳድነት ምክንያት መሆኑን ስለተገነዘበ፥ ወደ ዘዳግም 6፡16 በመሄድ ማንም ሁኔታዎችን በመጠቀም እግዚአብሔርን ለአንዳች ተግባር ሊያስገድደው እንደማይችል ነገረው። ማንም እግዚአብሔርን መፈተን አይገባውም።
ክርስቶስ ድርሻው በየዕለቱ እግዚአብሔር አብ ያዘዘውን መፈጸም እንደሆነ ያውቅ ነበር። ተአምራት የማድረግ ኃይሉም ሆነ የእግዚአብሔር ጥበቃ የሚመጣለት የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሚያደርግበት ጊዜ እንደሆነ አልጠፋውም። በኋላ እግዚኣብሔር ክርስቶስን በድንጋይ ከመወገር፥ ከመታሰርና ያለጊዜው ከመገደል ጠብቆታል። እርሱን እየታዘዝን በምንመላለስበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚጠብቀን እሙን ነው። ካስፈለገም መላእክቱን በመላክ ይታደገናል። ይህ ግን እግዚአብሔር መቼ ተኣምር መፈጸም እንዳለበት ወይም እንዴት እኛን መጠበቅ እንዳለበት ለማዘዝ መብት አይሰጠንም። ከራሳችን ግዴለሽነት የተነሣ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቀን እግዚአብሔር እንዲረዳን ለማድረግ መብት አይሰጠንም።
ሦስተኛው ፈተና የተከሰተው ሰይጣን ክርስቶስን ወደ ረጅም ተራራ በወሰደው ጊዜ ነበር። አሁንም ሰይጣን ክርስቶስን የወሰደው በሥጋ ይሁን በመንፈስ አናውቅም። ተራራው የት እንደሚገኝም አናውቅም። ተራራው የሚገኘው በሊባኖስ ወይም ከሲና ተራራ በታች ሊሆን ይችላል። ስፍራው የትም ይሁን የት ሰይጣን ለክርስቶስ የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በራእይ አሳየው። ከዚያም እነዚህን መንግሥታት እሰጥሃለሁ አለው።
ክርስቶስ የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው። በብሉይ ኪዳን በዓለም ሁሉ ላይ እንደሚነግሥ የሚገልጹ ብዙ የተስፋ ቃሎች ተሰጥተውታል። ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ የኃጢአትን ቅጣት ለመክፈልና ለራሱ ቅዱስ ሕዝብ ለመሰብሰብ በመስቀል ላይ መሞት ነበረበት። ይህም ክርስቶስ በዓለም ላይ የሚነግሥበትን ጊዜ በብዙ መቶ ምእተ ዓመታት ያርቅበታል (ፊልጵ. 2፡91)። አሁን ሰይጣን ለክርስቶስ አቋራጭ መንገድ በማቅረብ በመስቀል ላይ ሳይሞት የምድርን መንግሥት ሊጨብጥ እንደሚችል ገለጸለት። ሰይጣን የዚህች ዓለም ጊዜያዊ ገዥ መሆኑን ክርስቶስ ያውቅ ነበር (ዮሐ 12፡3)። ስለሆነም ሰይጣን በጊዜያዊው የዓለም መንግሥት ላይ ለክርስቶስ ሥልጣን መስጠት ይችል ነበር። ነገር ግን ለሰይጣን ቢሰግድ ኖሮ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ላይ የሚካሄድ የሰይጣን ዐመፅ ተሳታፊ ይሆን ነበር። ሰይጣን የወደቀው እንደ እግዚአብሔር ለመሆንና ለመመለክ በመፈለጉ ምክንያት ነበር (ኢሳ. 14፡12-15)። ክርስቶስ ሰይጣንን ማምለክ ለእግዚኣብሔር ብቻ የሚገባውን አምልኮ መንሳት እንደሆነ ያውቅ ነበር። አይሁዶች፥ ክርስቲያኖችም ሆኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ውጭ ምንም ነገር ወይም ማንንም ሰው እንዲያመልኩ ኣልተፈቀደላቸውም። ስለሆነም ክርስቶስ ዘዳግም 6፡13ን በመጥቀስ ከእግዚአብሔር ውጭ ማንንም ለማምለክ እንደማይፈልግ ለሰይጣን ነገረው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር የሚሰጠንን አንድ ነገር በአቋራጭ ለመቀበል ክርስቲያኖች ልንፈጽማቸው የምንችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ስንል በለይጣን ወጥመድ ተይዘን እርሱን ልናመልክ የምንችልባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ሐ) ብዙውን ጊዜ ሥቃይ ያለበትንና ረዥም ጊዜ የሚወስደውን የእግዚአብሔርን መንግድ ትተን በፍጥነት የሚመጣውን የሰይጣንን በረከት በሁከት በምንከተልበት ጊዜ፥ ለእግዚአብሔር ስለ መገዛታችን የምናስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው?
ክርስቶስ የኋላ ኋላ የእርሱ የሚሆነውን በረከት ለማግኘት ሲል አቋራጭ መንገድ ለመከተልና እምነቱን ለማመቻመች አልፈለገም። እግዚአብሔር የዓለምን መንግሥት ሁሉ እንደሚሰጠውና ሁሉም እንደሚንበረከክለት ያውቅ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔርን መንገድ በመስቀሉ በኩል ማለፍ እንዳለበት ያውቃል። ጊዜያዊ በረከት እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ ማመኻኛ ሊሆነን አይችልም።
ሰይጣን ክርስቶስ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ከጠቀሰለት በኋላ፥ በእግዚአብሔር ልጅነት ሥልጣኑ ከእርሱ እንዲርቅ አዘዘ። ሰይጣንም ታዘዘ። ነገር ግን በቀረው የክርስቶስ የአገልግሎት ዘመንና በተለይም በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ፥ ሰይጣን ክርስቶስን በኃጢአት ለመጣል ፈትኖታል። ማቴዎስ ከዚያ በኋላ መላእክት ቀርበው እንዳገለገሉት ገልጾአል። ሰይጣን ክርስቶስ፥ እግዚአብሔርን መላእክትን እንዲልክለት እንዲያስገድደው ቢፈልግም፥ ክርስቶስ ለፈቃዱ ራሱን ካስገዛ በኋላ እግዚአብሔር መላእክት ልኮለታል።
የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ክርስቶስን ለይፋዊ አገልግሎቱ ካዘጋጀበት መንገድ ምን እንማራለን? እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ መሪዎችን ለኣገልግሎት የሚያዘጋጅበትን አንዳንድ ምሳሌዎች ዘርዝር።
አብዛኛውን ጊዜ ወደ መሪነት ሥልጣን ለመውጣት እንቸኩላለን። የተወሰነ ትምህርት ካገኘን በኋላ የመሪነት ሥልጣን መያዝ እንደሚገባን እናስባለን። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሥልጣን ማግኘታችን ለአመራር ኃላፊነት ብቁ አያደርገንም። ብዙ መሪዎች ለመሪነት ዝግጁ ባለመሆናቸው ሥልጣኑን በሚረከቡበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ጉዳት ያስከትላሉ ። እግዚኣብሔር እንደኛ አይቸኩልም። ኢየሱስ በመሪነት ስፍራ ላይ የተቀመጠው 30 ዓመት ሲሞላው ነበር። እግዚአብሔር የበለጠ ትኩረት ያደረገው ልጁን ወደፊት ለሚጠብቁት ኃላፊነቶች ማዘጋጀቱ ላይ ነበር። ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነትና በባሕርዩ መዘጋጀት ያስፈልገው ነበር። ከዝግጅቱ መካከል ኣንዱ የእግዚአብሔርን ዕቅዶች የጊዜ ሰሌዳ ማወቅ ነበር። በገጠሪቱ ገሊላ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ካገለገለ በኋላ፥ የእግዚኣብሔር ጊዜ በመድረሱ ክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎቱን ጀመረ። ክርስቶስ ለይፋዊ አገልግሎቱ የተዘጋጀው መከራን በመቀበልና በመፈተን ነበር። እግዚአብሔር ሰዎችን ለመሪነት ለማዘጋጀት ከሚጠቀምባቸው ዐበይት መሣሪያዎች መካከል ሦስቱ ዝምታ፥ ኣለመታወቅና መከራ ናቸው። የእግዚአብሔርን ጊዜ ለመጠበቅ ዝግጁ ነን? ከእግዚአብሔር በቀር ማንም በማያውቀን ጊዜ እንኳ በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነን? መከራን ለመቀበል ዝግጁ ነን? እግዚአብሔር መሪዎችን ለማዘጋጀት የሚጠቀምበትን መንገድ በትክክል ብንረዳ፥ ብዙ የመሪነት ችግሮች ይቀረፋሉ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)