የተራራው ስብከት [እግዚአብሔር የባረከው ሰው ባሕርይ] (ማቴ. 5፡1-12)

የውይይት ጥያቄ፡- እራት ዓምዶች ያሉት ሠንጠረዥ በወረቀት ላይ ሣል። የመጀመሪያውን ዓምድ «ባሕርይ»፥ ሁለተኛውን «ያ ባሕርይ ምን ማለት እንደሆነ»፤ ሦስተኛውን ዓምድ «ክርስቶስ ተስፋ የሰጠው በረከት»፥ እንዲሁም አራተኛውን ዓምድ «ዓለም ሰዎች እንዴት እንዲኖሩ እንደምትፈልግ» በሚሉ ርእሶች ለይ። በማቴ. 5፡3-12 የሚገኙትን የብፅዕና ዓይነቶች በሠንጠረዥ ውስጥ ሙላ።

ይህ የመጀመሪያው ክፍል በክርስቶስ ተከታዮች ባሕርይ ላይ ያተኩራል። እኛ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያን ሊያደርገው ይገባል ወይም አይገባም በምንለው ውጫዊ ተግባር ላይ ስናተኩር፥ ክርስቶስ ግን የተገቢው ተግባር መሠረቱ፥ ባሕርይ መሆኑን ያመለክታል። ክርስቶስ የባሕርያችን መለወጥ የተግባራችንን መለውጥ እንደሚያስከትል ያውቃል። ከእነዚህ ባሕርያት ውስጥ አንዱን መርጠን ሌሎችን መተው አንችልም። እነዚህ ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮችን መለያ ባሕርያት ለመመሥረት በአንድነት የሚታዩ ናቸው። አንድ ሰው እንደ ተናገረው፥ እነዚህ ባሕርያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደር የሌላቸው የክርስቶስ መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ ባሕርያት ዓለም አስፈላጊዎች ናቸው ብላ ከምታስተምረው ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ናቸው።

ሀ. በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ለአይሁዶች «ብፁዕ» የሚለው ቃል ደስተኛ ከመሆን የላቀ ፍች ነበረው። ይህ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትንና የበረከቱ ተቋዳሽ መሆንን ያሳያል። የመጀመሪያው በረከት የተሰጠው፥ በመንፈስ ድሆች ለሆኑት ሰዎች ነው። እዚህ ላይ ክርስቶስ የሚናገረው ስለ ሥጋዊ ድህነት ሳይሆን፥ ስለ መንፈሳዊ ድህነት ነው። ሥጋዊ ድህነት ያጠቃቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ በሰዎች ላይ ጥገኞች ሆነው የሚኖሩ ናቸው። የራሳቸው ሀብት ስለሌላቸው ለኑሮአቸው የሚደገፉት በሰዎችና በእግዚአብሔር ላይ ነው። በመንፈስ ድሀ መሆን ማለት፥ እግዚአብሔርን የሚያስደስትና ለእግዚአብሔር ለመኖር የሚያስችል መንፈሳዊ ሀብት እንደሌለን መገንዘብ ነው። ስለሆነም እርሱ ይረዳን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እንመለከታለን። በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ቢኖር፥ ወደ እግዚአብሔር ጸጋና ምሕረት ፊታቸውን መመለስ እንደሆነ ያውቃሉ። ወደ እርሱ ስለሚመለከቱ እግዚአብሔር ምሕረትን፥ ጸጋንና መዳን ይሰጣቸዋል። በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች በራሳቸው ችሎታ ሳይመኩ ማንኛውም መፍትሔ ከእግዚአብሔር እንደሚመጣ ያምናሉ።

ዓለም የምታስተምረው የዚህን እውነታ ተቃራኒ ነው። የኋላ ኋላ ዓለም በሌሎች ላይ በሚደገፍ ሰው ትቀልድበታለች። ዓለም በማንነታችንና በተግባራችን እንድንኮራ ታስተምረናለች። ስለዚህ በሃይማኖታዊ ውርሳችንና በመንፈሳዊነታችን እንኩራራለን። እንዲሁም ተነሣሽነት ያላቸውን፥ ብልሆችን፥ ሀብታሞችንና ኃይለኞችን እናደንቃለን። በራሳቸው ብርታት ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች የሥልጣን ስፍራ ይሰጣቸዋል። የሃይማኖት ሰዎች ሳይቀሩ መንፈሳውያን ለመሆንና ደኅንነትን ለማግኘት በመቻላቸው ይኩራራሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በመንፈሳዊ ባለጸግነታቸው በመመካታቸው ክርስቶስ ሊሰጣቸው የሚፈልገውን በረከት ያጣሉ። በመንፈስ የሚታበዩ ሰዎች የክርስቶስ መንግሥት አካል አለመሆናቸውን ያሳያሉ።

በመንፈስ ድሆች የሆኑ መንግሥተ ሰማይን ከእግዚአብሔር ዘንድ በስጦታ ይቀበላሉ። ክርስቶስ እንደ አማኑኤል ከእነርሱ ጋር ይኖራል። እርሱ በሕይወታቸው ላይ ይነግሣል። ስለሆነም በመንፈስ ድሆች የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ የእርሱ መንግሥት አካል ሲሆኑ፥ መንፈሳዊ በረከቶቹን ይቀበላሉ። ከዚህም በላይ የክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት አካል ለመሆናቸው እርግጠኞች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ድሃ ከመሆን ይልቅ፥ በመንፈስ ሀብታም ሊሆን የሚችልባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በመንፈስ ድሃ የሆነው ክርስቲያን፥ በመንፈስ ትዕቢተኛ ከሆነው ክርስቲያን በአኗኗሩ እንዴት እንደሚለይ ግለጽ።

ለ. የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መጽናናትን ያገኛሉና። ክርስቶስ በምን ምክንያት እንደሚያለቅሱ አልገለጸም። ዐውደ ምንባቡ ግን መንፈሳዊ ባሕርይ ያለው ነው። በኃጢአተኛነታቸውና በልባቸው ድንዳኔ የሚያዝኑ፥ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያንና በአገራቸው ኃጢአት ምክንያት የሚያለቅሱ ወገኖች ይጽናናሉ [መዝ. (119)፡136 አንብብ። የሚያለቅሱት የራስ ወዳድነት ፍላጎቶቻቸው ስላልተሟሉላቸው ሳይሆን፥ ዓለምና ሰዎች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ባለመጓዛቸው ምክንያት ነው።

ይህም ዓለም ከምታስተምረው አሳብ ተቃራኒ ነው። ዓለም በሕይወታችን እንድንደሰት ታስተምረናለች። ስለዚህም «ሰው እስከሆንህ ድረስ ለኃጢአት መጨነቅ የለብህም፥ የቤተ ክርስቲያንም ሆነ የአገር ኃጢኣት ሊያስጨንቅህ አይገባም ልትለውጠው አትችልምና» ትለናለች።

ክርስቶስ ስለ ኃጢአት የሚያለቅሱ ሰዎች እንደሚጽናኑ ተናግሯል። እነርሱም እግዚኣብሔር የሚሰጣቸውን ይቅርታ ስለሚያውቁ ይጽናናሉ። እግዚአብሔር በእነርሱና በጸሎታቸው አማካይነት የራሳቸውንንና የሌሎችንም ሕይወት እንደሚለውጥ ስለሚያውቁ ይጽናናሉ። በኀዘናቸው ጊዜ ራሱ ክርስቶስ አብሯቸው እንደሚሆን ስለሚያውቁ፥ ይጽናናሉ። ኣንድ ቀን ኀዘንም ሆነ ለቅሶ የሌለበት መንግሥት ቤተሰቦች ስለሚሆኑ ይጽናናሉ (ራእይ 7፡17፤ 21፡4)።

የውይይት ጥያቄ፡- ለመጨረሻ ጊዜ በሕይወትህ ውስጥ ወይም በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ስለተከሰተው ኃጢአት ያለቀስኸው መቼ ነበር? አልቅሰህ ከሆንህ ይህ ስለ ልብህ ሁኔታ ምንን ያሳያል?

የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። የዋህ የሚለውን ቃል ለመተርጎም አስቸጋሪ ነው። ብዙውን ጊዜ የዋህነት ሰዎች ያሻቸውን ነገር ሲያደርጉ መልስ አለመስጠት ወይም ሞኝነት እንደሆነ እናስባለን። ይህ ግን ክርስቶስ ያስተማረው የዋህነት አይደለም። ክርስቶስ የዋህ የነበረ ቢሆንም፥ ይፋዊ ተቃውሞ ሳያሳይ ኢ-ፍትሐዊ የሆነ ነገር እንዳይደረግ ተከላክሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የዋህነት የተለያዩ ጽንሰ አሳቦች አሉት። በሕይወታችን ውስጥ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ቁጡና መራር ሳይሆኑ፥ በትዕግሥት መገዛት የዋህነት ነው። ወይም የዋህነት ነገሮችን በራሳችን መንገድ ከማከናወንና የምንፈልገውን የማያደርጉትን ከመቃወም ይልቅ፥ በገር መንፈስ መመላለስ ሊሆን ይችላል። የዋህ ሰው እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደሚሠራና የኋላ ኋላም ለጥቅማችን እንደሚያውለው ይገነዘባል። ስለሆነም እግዚአብሔር በሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ ፍጹም ፈቃዱን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ይተማመናል። የዋህነት በራስ ጥረት ሳይመኩ ሕይወትን ከእግዚአብሔር እጅ እንደተቀበሉ አድርጎ ማስተናገድ ነው። የዋህነት ራሳችንን ወይም አሳባችንን ለመከላከል አለመሞከርና ስሕተታችንን መቀበል ነው።

ከዚህ በተቃራኒው ዓለም ዐመፅን፥ ተቃውሞንና የግል ፍላጎትን ታከብራለች። አንድን ነገር ከፈለግህ ተጠቀምበት። አንድ ሰው ካበሳጨህ እርሱን የሚያበግን አንድ እርምጃ ውሰድ። በሕይወት ቀዳሚ ሆነህ ለመገኘት፥ ከሌሎች ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ለማግኘት፥ የተሻለ ሥራ ለመያዝ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪ ለመሆን፥ ጠልፈህ መጣል፥ ካስፈለገም ሰዎችን መገፍተርና ማጭበርበር ይኖርብሃል ትላለች። የዓለም ሥርዐት በሰዎች ላይ ኃይልን እንድንቀዳጅ ያበረታታል።

በዚህ ሁኔታ ዓለም ሰዎች በማታለልና በማጭበርበር የቀዳሚነትን ስፍራ እንደሚይዙ ስታስተምር፥ ክርስቶስ ግን የዋሆች ምድርን እንደሚወርሱ አስተምሯል [መዝ. (37)፡9-11 አንብብ።] ይህ እንዴት ይሆናል? በመጀመሪያ፥ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ዓለም ከምትጠብቀው ተገላቢጦሽ የሆነውን ይሠራል። የቀዳሚነትን ስፍራ ለመያዝ የሚፍጨረጨሩ ሰዎች ምንም እንኳ ለጊዜው መጠቀም ቢችሉም፥ የኋላ ኋላ ፍሬያማ አይሆኑም። እግዚአብሔር በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ እንደሚባርካቸው የሚተማመኑ ግን፥ ባልተጠበቅ መንገድ የእግዚአብሔርን በረከት ይቀበላሉ። ይህም ሆኖ በረከቶቹ ይገቡናል፥ በበጎ ሥራችን አገኘናቸው የሚል ስሜት የላቸውም። ማቴዎስ ያተኮረው ግን በወደፊቱ ጉዳይ ላይ ነው። ክርስቲያኖች ምድራዊ በረከት ልንቀበል ወይም ላንቀበል ብንችልም፥ ከክርስቶስ ጋር እንደምንነግሥ ግን ጥርጥር የለውም። ይህ አጭር ምድራዊ ቆይታ፥ በዘላለማዊ መንግሥት የሚተካ ሲሆን፥ ምድራዊ የዋህነታችን መንፈሳዊ በረከትን ያስገኝልናል (ሉቃስ 22፡29-30፤ ራእይ 20፡4)።

የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ የየዋህነት ጉድለት ችግር ያስከተላበትን አጋጣሚ ግለጽ።

መ. ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። በዓለም ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ጠንካራ ስሜቶች ሁለቱ ረሃብና ጥማት ናቸው። ምግብና ውኃ ሳናገኝ ብንቀር፥ አሳባችን ሁሉ እነዚህን ሁለት ነገሮች በማግኘቱ ላይ ያተኩራል። ያለእነዚህ ነገሮች ለመኖር አንችልም። ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ መንፈሳዊ ፍላጎትን ከረሃብና ከጥማት ጋር ያነጻጽራል [መዝ (42)፡1-2 ኣንብብ።] ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በጊዜያዊ ነገሮች ከመወሰድ ይልቅ፥ ጽድቅን ሊራቡ እንደሚገባ አስተምሮአቸዋል። ጽድቅ ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ማድረግ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ ነው። በአሉታዊ ጎኑ፥ ከኃጢአትና እግዚአብሔርን ከማያስደስቱ ነገሮች መራቅ ነው። በአዎንታዊ ጎኑ፥ እግዚአብሔርን የሚያስደስቱትን ነገሮች ማድረግ ነው። እግዚአብሔርን በበለጠ ለማወቅና እርሱን ለማስከበር መፈለግ ነው። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በዓለም ሰዎች ትክክለኛና የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበትን ሕይወት ሲመሩ ለማየት መፈለግ ነው።

ዓለም ግን የምትራበው ሌሎች ነገሮችን ነው። ትምህርትን፥ ገንዘብን፥ ኃይልና ሥልጣንን፥ ሌሎችንም ነገሮች ትራባለች። ዓለማውያን እግዚኣብሔርን በሚያስደስት መንገድ የሚኖር ሰው ሞኝ እንደሆነ ያስባሉ።

ኢየሱስ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ እንደሚጠግቡ ተናግሯል። ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት እያደገ ሲሄድ ይመለከታሉ። ጽድቅን የሚሹ ሰዎች ባሕርያቸው ተለውጦ፥ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ሲስማማ ያያሉ። በእነርሱ አማካይነት በቤተ ክርስቲያናቸውና በማኅበረሰቡም መካከል ለውጦች ይከሰታሉ። ከሁሉም በላይ ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ሰዎች፥ ጽድቅ የሚገዛበት ዘላለማዊ መንግሥት ዜጎች በመሆናቸው ይጠግባሉ።

9ኛ ጥያቄ፡- ሕይወትህን መርምር። የምትራበውና የምትጠማው ለምንድን ነው? ጽድቅን የምትራብና የምትጠማ ከሆነ፥ ይህ በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደታየ ግለጽ።

ሠ. የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ምሕረት ለማይገባቸው ሰዎች መልካምን ነገር ማድረግ ነው። እግዚአብሔር የዘላለም ፍርድ የሚገባን ሆነን ሳለ ይቅርታን በማድረግ ይምረናል። እኛም የእግዚአብሔርን ምሳሌ ተከትለን ምሕረትን ልናሳይ ይገባል። ይቅርታ ባይገባቸውም እንኳ ለሚበድሉን ሰዎች ይቅርታን በማድረግ ምሕረትን ልናሳያቸው ይገባል። ምሕረት ከኃጢአት ጋር የሚታገሉትን ወይም አንድ አካላዊ ችግር የሚጋፈጡትን ወገኖች መርዳት ነው። ምሕረት የርኅራኄ ስሜት ብቻ ሳይሆን፥ ተግባራዊም ነው። በሕይወታችን ውስጥ የምሕረት መኖር የሚታወቀው የተጎዱትን ወይም የሚጎዱንን ሰዎች የምንረዳ ከሆንን ብቻ ነው።

የዓለም አመለካከት ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። ዓለም እንድ መጥፎ ነገር በፈጸሙብን ሰዎች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ታስተምራለች። በሽማግሌዎች፥ በቤተሰቦች፥ በጎሳዎች ወይም በአገሮች መካከል የሚደረገው ትግል በብቀላ ላይ የተመሠረተ ነው። ሰዎች ምሕረትን ገንዘባቸው ቢያደርጉ፥ ይቅርታ ሰፍኖ ጥላቻ ይርቅ ነበር። ዓለም የሚጎዱንን ሳይሆን፥ ራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን መርዳት እንዳለብን ታስተምራለች። ሌሎችን ከረዳን ደግሞ፥ ከዚህ ተግባር ለራሳችን ጥቅም እንፈልጋለን።

ኢየሱስ ምሕረትን የሚያደርጉ ሰዎች በራሳቸው ሕይወት ምሕረትን እንደሚያገኙ ተናግሯል። ክርስቶስ የሚናገረው የእግዚአብሔርን ምሕረት ከማግኘታችን በፊት ለሌሎች ምሕረትን ማሳየት እንዳለብን ሳይሆን፥ ከእውነተኛ የደቀ መዝሙርነት ምልክቶች አንዱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ማንጸባረቅ እንደሆነ ነው። ምሕረት ከሌለን፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስለ መሆናችን መጠራጠር አለብን። ምሕረትን ካላሳየን በእግዚአብሔር ላይ ማመፃችን ስለሆነ፥ የእርሱን ምሕረት አናገኝም። በችግራችንም ጊዜ የሌሎች ሰዎችን ምሕረት፥ ይቅርታና ዕርዳታ አናገኝም። ክርስቲያን ምሕረትን ለማሳየት እስኪፈቅድ ድረስ የውጊያው ዑደት ይቀጥላል። ምሕረትን በሚያሳይበት ጊዜ ግን ብዙውን ጊዜ ውጊያው ይቆማል። ምሕረት ስናደርግ፥ ሰዎች እኛንም ይምሩናል።

10ኛ ጥያቄ፡- እየተጎዱ ያሉትን ወይም ኣንተን የጎዱትንና ምሕረት የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ዘርዝር። ለእነዚህ ሰዎች በዚህ ሳምንት በምን ዐይነት ተግባራዊ መንገድ ምሕረትን ልታሳያቸው እንደምትችል እግዚአብሔር እንዲያሳይህ በጸሎት ጠይቀው።

ረ. ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። እዚህ ላይ ክርስቶስ ሁለት ባሕርያትን የሚያመለክት ይመስላል። በመጀመሪያ፥ ስለ ልበ ንጹሐን እየተናገረ ነበር። እነዚህ ሰዎች በውጫዊ ተግባራት ላይ ሳይሆን በልባቸው ሁኔታ ላይ ያተኩሩ ነበር። ሁለተኛው፥ ግብዝነት ስለሌለበት ሕይወት እየተናገረ ነበር። ልበ ንጹሐን በቤትም ሆነ በአደባባይ ተመሳሳይ ባሕርይ ይኖራቸዋል። አሳባቸውን በተግባር ይገልጹታል። ለተግባራቸው ምንም ዐይነት ስውር አጀንዳ የላቸውም። ልበ ንጹሓን ሌሎችን ወይም ራሳቸውን ሳያታልሉ እውነተኛ ተግባር ያከናውናሉ። በሙሉ ልባቸው ክርስቶስን ለማክበር ስለሚፈልጉ፥ ልባቸው በምንም ዐይነት ርካሽ ነገር አይያዝም።

ዓለም ግን ግብዝነትን ታበረታታለች። ሰዎችን ለማስደነቅ ትምህርታችንን፥ ሀብታችንን፥ ወዘተ. . . እንድናሳይ ታደርጋለች። ከሰዎች ጋር በምንሆንበት ጊዜ መንፈሳዊና ጥሩ ሰዎች እንደሆን ታስመስላለች። ማንም ሰው በሌለበት ስፍራ በምንሆንበት ጊዜ ግን ፍጹም የተለየ ተግባር እናከናውናለን። በሰዎች ፊት ጥሩ መስለን እንታይና ዘወር ሲሉ እናማቸዋለን? የምንፈልገውን ለማግኘት ስንል ሰዎችን እናታልላለን።

1ኛ ጥያቄ፡- ሀ) ምናልባትም ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ያወገዘው ኃጢኣት ግብዝነት ነው። ስለ ግብዝነት በሕይወትህና በቤተ ክርስቲያንህ፥ በተለይም በመሪዎች መካከል የምታያቸውን ምሳሌዎች ዘርዝር። ለ) ሰዎች የግብዝነትን አደገኛነትና ልበ ንጹሐን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን ምን ልታስተምር ይገባል?

ኢየሱስ ልበ ንጹሓን እግዚአብሔርን እንደሚያዩ ገልጾአል። ይህን ሲል እንደ ሙሴ እግዚኣብሔርን ፊት ለፊት ያዩታል ማለቱ ሳይሆን፥ በሕይወታቸውና በቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን እጅ በሥራ ላይ ያዩታል ማለቱ ነበር። እንዲሁም በዘላለሙ መንግሥት የእግዚአብሔርን ክብር እንጂ ፍርድ ስለማይቀበሉ፥ የወደፊቱን ዘመን አይፈሩም።

ሰ. የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ከኢየሱስ ስሞች አንዱ «የሰላም አለቃ» (ኢሳ 9፡6) የሚል ሲሆን፥ ተከታዮቹም ይህንኑ ባሕርይ እንዲያንጸባርቁ ይፈልጋል። ለክርስቶስ ተከታዮች ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ብቻ በቂ እንዳልሆነና ለሌሎችም ሰላምን ለማምጣት መትጋት እንደሚገባቸው አስረድቷል። የእግዚአብሔርን ሰላም ከሚሰጣቸው ኢየሱስ ጋር ሰዎችን ስለሚያስተዋውቁ ሰላምን ያመጣሉ። በተጨማሪም አስታራቂዎች በወጣቶችና በሽማግሌዎች መካከል፥ በተለያዩ ቤተሰቦች፥ በተለያዩ ነገዶችና ጎሳዎች፥ በአገር ውስጥም ሰላምን ለማምጣት ይሠራሉ። ይህ ግን ችግሮችን ከመደበቅ የሚመጣ አይደለም። ነገር ግን የችግሩን ሥር በማግኘት፥ ኃጢኣተኝነትን በመገንዘብ ይቅርታን በመስጠት፥ የሰዎችን ተግባርና አስተሳሰብ በመለወጥ የሚመጣ እውነተኛ ሰላም ነው።

ዓለም ግን ጠብን የሚወድ ይመስላል። ሰዎች በሚጣሉበት ጊዜ ዙሪያውን ከብበው የሚያውኩ ወገኖች ይበዛሉ። ለመብታችን እንድንታገል ይነግሩናል። ዓለም ሰላምን ለመፍጠር የምትሞክረው ዘለቄታዊ ሰላም ይኖር ዘንድ ጽድቅን ከመከተል ይልቅ የተሳሳተውን ነገር በመሸፋፈን ነው።

ኢየሱስ ለሰላም መስፈን ተግተው የሚሠሩ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች እንደሚባሉ ተናግሯል። እግዚአብሔር «ልጆቼ የሚላቸው የእርሱን የሰላም ባሕርይ ስለሚያንጸባርቁ ነው። ከእነዚህ ሰዎች የሰላም ፍላጎት የእግዚአብሔርን ባሕርይና ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን የተለየ ግንኙነት የሚመለከቱ ሌሎች ሰዎችም የእግዚአብሔር ልጆች ብለው ይጠሯቸዋል። ብሉይ ኪዳን በዘር ውርስ ላይ በመመሥረት እስራኤላውያን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ሲገልጽ (ዘዳግ 14፡1-2፤ ሆሴ. 1፡10)፥ የእግዚአብሔር ልጅነት ይበልጥ የባሕርይ ጉዳይ እንደሆነ አመልክቷል።

12ኛ ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህና በማኅበረሰብህ ውስጥ የሚጣሉትን ሰዎች ዘርዝር። ለ) ሰላምን ለመጀመር እግዚአብሔር ምን ዐይነት እርምጃ ዎችን እንድትወስድ የሚፈልግ ይመስልሃል?

ሸ. ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና፡፡ በአንድ በኩል ይህ የመጨረሻ ብፅዕና ያለቦታው የገባ ይመስላል። እስካሁን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እነማን እንደሆኑ ስለሚያሳዩት መንፈሳዊ በረከቶችና ስለሚያስገኙላቸው ውስጣዊ ባሕርያት ሲናገር ነበር። ሆኖም ይህ የመጨረሻው ብፅዕና የተጠቀሰው ግን በምክንያት ነበር። ክርስቶስ የዓለምን ተቃራኒ ሕይወት የሚመራ ሰው በዓለም እንደሚጠላ ያውቅ ነበር። እንስሳት የእነርሱ ወገን ያልሆነውን ለየት ያለውን እንስሳ እንደሚጠሉ ሁሉ፥ ዓለምም ለየት የሚሉትን ትጠላለች። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱን መከተል ስደትን እንደሚያስከትልባቸው አልሸሸገም። ነገር ግን ስደት እንደሚደርስብን መጠበቅ እንዳለብንና፥ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ለመሆን ስንመርጥ ዋጋችንን መተመን እንዳለብን አስቀድሞ ነግሮናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መሰደድ የሚገባቸው ስለ ጽድቅ መሆን እንዳለበት አስጠንቅቋቸዋል። ከባሕርያችን ወይም ከተግባራችን ጉድለት የተነሣ መሰደድ አይገባም።

ክርስቶስ የእርሱ ተከታዮች በመሆናቸው ምክንያት ስደትን የሚቀበሉና እንደ እርሱ የሚመላለሱ ሰዎች ደስ ሊሰኙ እንደሚገባቸው ተናግሯል። ስደት ሊደርስብን ማጉረምረም፥ ማዘን፥ መበቀልና ሌሎችን መጥላት የለብንም። ነገር ግን እየሆነ ያለውን ጉዳይ ባናውቅም እንኳ፥ ስደት፥ ክርስቶስ በሚፈልገው መንገድ እየኖርን መሆናችንን ከሚያሳዩ እጅግ ጥርት ካሉ ማረጋገማዎች አንዱ ስለሆነ፥ ደስ ልንሰኝ ይገባል። (ክርስቶስ እጅግ ደስ እንድንሰኝ ነግሮናል።) ዓለም የምታጠቃው ከእርሷ የሚለዩትን ብቻ ነው። ሰዎች ከሚያደርሱብን ባሻገር፥ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ዜጋ መሆናችንን የሚወስድብን ማንም ስለሌለ ክርስቲያኖች ደስ ልንሰኝ ይገባል። እግዚአብሔር ስለ እርሱ ለተቀበልነው መከራ ስለሚሸልመን ደስ መሰኘት አለብን። ስደት እንደ ኢሳይያስ በመጋዝ ለሁለት ከተሰነጠቁት ነቢያት ጎን ስለሚያሰልፈን ደስ ልንሰኝ ይገባል። ይህ ከመንፈሳዊ ጀግኖች ተርታ ያሰልፈናል።

ማቴዎስ መጭው ጊዜ ለአይሁድ ክርስቲያኖች እንደማይመች ተገንዝቦ ነበር። አስቸጋሪ ምርጫዎችን ለማድረግ ተገድደው ነበር። ከሌሎች አሕዛብ ክርስቲያኖች ጋር መተባበርና የክርስቶስን መሢሕነት በይፋ መናገር ቢጀምሩ፥ አይሁዶች ይስቁባቸው ነበር። የአይሁድ ክርስቲያኖች ከምኩራብ የመባረር፥ ከሌሎች አይሁዶች ጋር ያለመገበያየት፥ ብሎም የመገደል ኣደጋ ሊደርስባቸው ይችል ነበር። እነዚህ የአይሁድ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ለመደበቅ ወይም ለመካድ ተፈትነው ነበር። ማቴዎስ ግን ለጊዜው አሠቃቂ ቢሆንም እንኳ ስደት ታላላቅ ዘላለማዊ በረከቶችን እንደሚያስገኝላቸውና፥ ከስደት ለማምለጥ ብሎ ክርስቶስን መካዱ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንደሚያመጣ አመልክቷል።

ምሑራን እንደሚነግሩን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ብቻ በቀደሙት 1900 ዓመታት ከተገደሉት ሰዎች የሚበዙ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ተሠውተዋል። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ከስደት እንደሚጠብቀንና በሀብት እንደሚባርከን ቢያስተምሩም፥ ክርስቶስ የተነበየው ተቃራኒውን ነው። ክርስቶስን ለመከተል ከፈለግን፥ ሰዎች እንደሚጠሉን፥ እንደሚያሳድዱንና እንደሚገድሉን ጭምር መጠበቅ አለብን። እነዚህን የሥቃይ ጊዜ ለማሸነፍ የምንችልበት መንገድ ቢኖር በሰማይ ዋጋችን ታላቅ እንደሆነ በመገንዘብ ነው።

13ኛ ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን ባሕርያት ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ማስተማር የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል? በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ እነዚህ ባሕርያት ሲኖሩ፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነገሮች እንዴት የሚለወጡ ይመስልሃል? ሐ) አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በዚህ መንገድ ቢመላለሱ ማኅበረሰቡ እንዴት ሊለወጥ ይችላል? መ) ብዙ ክርስቲያኖች በዕለታዊ ሕይወታቸው እነዚህን ባሕርያት የማያንጸባርቁት ለምን ይመስልሃል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

%d bloggers like this: