ክርስቶስ ለተከታዮቹ ያቀረበው ግብረገባዊ ትምህርት ማጠቃለያ (ማቴ. 5-7)

ክርስቶስ በማቴ. 5-7 ላይ ያስተማራቸው ትምህርቶች፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ዐበይት እውነቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 5፡1-2 ኣንብብ። ሀ) ክርስቶስን ስለ መከተል የምንማራቸው ዐበይት ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚታገሏቸው የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

ተመስገን በወንጌላዊነት የሚያገለግል ወንድም ሲሆን፥ ለሌላ ጎሳ ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክር ቤተ ክርስቲያኑ ላከችው። እርሱ የተላከባቸው ሰዎች አርብቶ አደሮች ነበሩ። ምንም እንኳ ተመስገን ለእነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ቢመሰክርም፥ የወንጌል ትምህርቱን ያቀረበበት መንገድ ከእነርሱ አኗኗርና ባሕል የተለየ ነበር። በክርስቶስ በሚያምኑበት ጊዜ ሰውነታችውን እንዲታጠቡ፥ ልብስ እንዲለብሱ፥ መጠጥ እንዲያቆሙ፥ ሁለተኛ ሚስቶቻቸውን እንዲፈቱ አሳሰባቸው። ጌታሁን ለቤተ ክርስቲያን ቅድስና የሚያስብ መጋቢ ነበር። ስለሆነም በሚሰብክበት ጊዜ ሰዎች ከመጠጥ፥ ከዝሙትና ከጫት እንዲታቀቡ እስጠነቀቀ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰባኪ ወይም ወንጌላዊ፥ ሰዎች ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ወይም የማይገባቸውን ነገሮች በመዘርዘር ወንጌልን ሲሰብክ የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ከማቴ. 5፡1-12 ክርስቶስ ስለ መንግሥት ያቀረበው ስብከት፥ ብዙውን ጊዜ እኛ ወንጌሉን ከምንገልጽበትና ክርስቶስን ስለ መከተል ከምናስተምርበት መንገድ የሚለየው እንዴት ነው? ሐ) ሰዎች መንፈሳዊነትን እንዲማሩ ከመምከር ይልቅ፥ ውጫዊ ተግባራት ላይ በማተኮር ይህን አድርጉ፥ ያን አታድርጉ የሚሉ ዝርዝሮችን ሰጥቶ፥ አፈጻጸማቸውን መለካት የሚቀልለው እንዴት ነው?

ማቴዎስ 5-7 ድረስ የተጻፈው ትምህርት ከየትኞቹም ወንጌላት በላይ ሰፋ ብሎ የቀረበ ሲሆን፥ ክርስቶስ ምን ትምህርት እንዳስተማረ ያብራራል። ምሑራን ይህ ትምህርት በኣንድ ስብከት ስለ መጠናቀቁ ይከራከራሉ። ምናልባትም ክርስቶስ ይህን ትምህርት በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ ለሕዝቡ ያስተማረው ትምህርት አጠቃላይ አሳብ ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ስለሚያስተምር፥ ከእነዚህ እውነቶች ብዙዎቹ በሌሎችም ስፍራዎች ላይደገሙ አልቀሩም። አንዳንድ ምሑራን ማቴዎስ መጽሐፉን በሚጽፍበት ወቅት፥ ክርስቶስ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሊኖሩት የሚገባቸውን ሕይወት በአንድ ላይ እንዳሰባሰበ ይናገራሉ። ስለሆነም ምንም እንኳ ማቴዎስ ኢየሱስ ለረዥም ጊዜ በተራራ ላይ ሆኖ ማስተማሩን ቢገልጽም፥ ክርስቶስ በሦስት ዓመት ይፋዊ አገልግሎቱ ጊዜያት ያስተማራቸውን ሌሎች እውነቶችም ጨምሯል።

ኢየሱስ በገሊላ በአገለለባቸው ጊዜያት ለደቀ መዛሙርቱ፥ የእርሱ ተከታይ መሆን፥ ፈሪሳውያን ብቁ አይሁዳዊ ስለ መሆን ከሚያስተምሩት ትምህርት የተለየ መሆኑን ኣሳይቷል። ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች ትምህርቱን ቢከታተሉም፥ ማቴዎስ እንደሚነግረን፥ ክርስቶስ በተለይ ትምህርቱን ያተኮረው በደቀ መዛሙርቱ ላይ ነበር። ከማቴዎስ 5-7 ድረስ የተጠቀሱትን እውነቶች ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ውስጥ ሲተገበሩ ለመመልከት ፍላጎት ነበረው።

በየዘመኑ ውስጥ የኖሩ ክርስቲያኖች እነዚህን እውነቶች ተግባራዊ ለማድረግ ታግለዋል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ መፈጸም አልተቻላቸውም። አንዳንድ ክርስቲያኖች የእነዚህ ምዕራፎች ትምህርት በተራ ክርስቲያኖች የማይሞከሩ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ብቻ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ እንደሆነ አስተምረዋል። ሌሎች ደግሞ ክርስቶስ እነዚህን ትምህርቶች መፈጸም የማይቻል መሆኑን እያወቀ፥ ሰዎች ወደ ጸጋው እንዲመለሱ ለማበረታታት እንዳስተማረ አድርገው ገልጸዋል። የተቀሩት ደግሞ ክርስቶስ እነዚህን ትምህርቶች ለክርስቲያኖች እንዳልሰጠና፥ ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ ለሺህ ዓመታት በሚነግሥበት ጊዜ ለሚኖሩት አይሁዶች የታቀዱ እንደሆነ አስረድተዋል። እነዚህ ሁሉ ክርስቶስ ከአስተማረው አስቸጋሪ ትምህርቶችና ደቀ መዛሙርቱ እንዲኖሩት ይፈልግ ከነበረው ሕይወት ለመሸሽ የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል የሚፈልጉ ሁሉ ራሳቸውን ለእርሱ ሊያስገዙና በተለወጠ ሕይወት የመንግሥቱ አካል እንዲሆኑ ይሻል። ባሕርያቸው፥ ከሌሎች ጋር የሚዛመድበት መንገድና ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት አምልኮ ሁሉ መለወጥ አለበት። የክርስቶስ ተከታይ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ዐቢይ ለውጥ ማሳየት ይኖርበታል። ማቴዎስ 5-7 የተሰጠው ትምህርት ምናልባትም እንደ ክርስቶስ ተከታዮች እንዴት መኖር እንደሚገባን ከኣዲስ ኪዳን ምንባቦች ሁሉ ጥርት ባለ ሁኔታ የሚያስተምረን ክፍል ነው። ምንም እንኳ ይህ በራሳችን ኃይል የማይቻል ቢሆንምና ማናችንም ከመቅጽበት ለመለወጥ ባንችልም፥ ክርስቶስ እንድንኖር የሚፈልገው በዚህ መንገድ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

%d bloggers like this: