የክርስቶስ ተከታዮች ለዓለም ብርሃንና ጨው መሆን አለባቸው (ማቴ. 5፡13-16)

ብዙ ክርስቲያኖች፥ «ዓለም ለእኛ በጣም መጥፎ ስለሆነች የመንግሥት ሥራ ትተን ወደ ክርስቲያናዊ ድርጅቶች ብንሄድ ይሻላል። ወይም ከማኅበረሰባችን ወጥተን ከሚመስሉን ሰዎች ጋር የምንሠራበትንና የምንኖርበትን ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ እንመሥርት» ይላሉ። ነገር ግን ይህ ክርስቶስ ያስተማረው የደቀ መዝሙርነት ዐይነት ነው ወይ? ከማኅበረሰቡ ወጥተው የራሳቸውን የቅዱሳን ማኅበረሰብ ከመሠረቱት ኢሴናውያን በተቃራኒ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ በዓለም ውስጥ እንደ ጨውና ብርሃን እንዲያገለግሉ የሚፈልግ መሆኑን ገልጾአል።

ኢየሱስ በዓለም ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ከሦስት ነገሮች ጋር በማነጻጸር አብራርቷል። በመጀመሪያ፥ ከጨው ጋር አነጻጽሯቸዋል። በጥንት ዘመን ጨው በጣም ጠቃሚ ነገር ነበር። እንደ ጥንታዊት ኢትዮጵያ በመሳሰሉት አገሮች፥ የመገበያያ ገንዘብ ሆኖ አገልግሏል። ጨው ለሁለት ነገሮች ያገለግል ነበር። ሀ ለጣዕም፥ ወጥ እንዲጣፍጥ፥ በገጠር በቡና ጭምር ጨው እንደሚጨመር ሁሉ፥ በክርስቶስ ዘመን ጨው ለጣዕም መስጫ ያገለግል ነበር። 2) ለማቆያ። ሥጋ እንዳይበላሽ በጨው ቀምመው ቋንጣ ያደረጉት ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ በቁጥር ቢያንሱም እንኳ እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ቢኖሩ ክርስቲያኖች በማኅበረሰቡ ውስጥ እነዚህን ሁለት ተግባራት መፈጸም ይችላሉ። መንፈሳዊ ምሳሌነት ያለው ሕይወት በመምራት በክፋት ለተሞላው ማኅበረሰብ መልካም መዓዛ ይጨምራሉ። በተጨማሪም እግዚኣብሔር ክፋት እንዳይጨምርና ማኅበረሰቡ የበለጠ ክፉ እንዳይሆን ለመከላከል፥ በውስጡ ያሉትን ክርስቲያኖች ይጠቀማል።

እስራኤላውያን ጨው የሚያገኙት ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ ምሥራቅ ከሚገኘው ሙት ባሕር ነበር። ከመሬትም ቆፍረው ያወጡታል። ነገር ግን ይህ ንጹሕ ጨው ስላልሆነ፥ በፍጥነት ካልተጠቀሙበት ጨውነቱን እያጣ ይሄድ ነበር። ከዚያ በኋላ ሊያገለግል የሚችለው ወደ መሬት በመጣል፥ ወይም ጣሪያቸው እንዳያፈስ ከዚያው ላይ በማስቀመጥ ብቻ ይሆናል። ዛሬም እንኳ ብዙ የአይሁድ ቤቶች ውኃ የሚያስገቡ ጣሪያዎች አሏቸው። ዛሬም ድረስ ያረጀና የማይጠቅም ጨው በጣሪያቸው ላይ በማድረግ ዝናብ ይከላከላሉ።) በተመሳሳይ ሁኔታ የአንድ ክርስቲያን ባሕርይ የዓለምን ሲመስል፥ ለማኅበረሰቡ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ሊኖር አይችልም። ሁለተኛው ማብራሪያ ብርሃን ነበር። በጥንት ዘመን ኤሌክትሪክ ስላልነበረ፥ ሰዎች በወይራ ዘይት የተሞሉ ኩራዞችን ይጠቀሙ ነበር። ብርሃን አስደናቂ ነገር ነው። ትንሽ ብርሃን ብዙ ጨለማ ትገፋለች። የክርስቶስ ተከታዮች በቁጥር ቢያንሱም እንኳ፥ የክርስቶስን ባሕርያት በዓለም ውስጥ ማብራት አለባቸው። የሰዎችን ክፋት አብርተን በማሳየት፥ ሕይወታቸውንና ማኅበረሰባቸውን በሚለውጥ መንገድ እንዴት ሊኖሩ እንደሚችሉ እናሳያቸዋለን፡ ነገር ግን ሕይወታችን ዓለምን በመምሰል በኃጢአት ከጨለመ፥ ይህ በማሰሮ ውስጥ እንዳለ መብራት ይሆናል። ወይም ደግሞ ስደትን ፈርተን ብርሃናችንን ብንደብቅ፥ እግዚአብሔር ጽድቁን ለማብራት እኛን የተጠቀመበት ዓላማ ከግቡ ሳይደርስ ይቀራል፡፡

ሦስተኛው ምሳሌ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ናት። እንደተለኮሰ መብራት፥ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አትችልም። በተመሳሳይ ሁኔታ እነዚህን ክርስቶስ የጠቀሳቸውን ባሕርያት የያዙ ክርስቲያኖች ለሁሉም በግልጽ የሚለዩ ይሆናሉ። ምስክርነታችን የሚመጣው ከአፋችን ሳይሆን ከተግባራችን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለእግዚአብሔር የሚኖሩ ጥቂት ክርስቲያኖች እንደ ብርሃንና ጨው ኅብረተሰቡን ሲለውጡ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) እንደ ዓለማውያን በመኖራቸው ምክንያት የብርሃንነትና የጨውነት አገልግሎታቸው የጠፋበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ሕይወትህ እንደ ብርሃንና ጨው የሆነው እንዴት ነው? ብርሃንህና ጨውህ የበለጠ እያደገ በማኅበረሰቡ ላይ የበለጠ ለውጥ ለማስከተል ትችል ዘንድ ምን ታደርጋለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: