የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት ማጠቃለያ (ማቴ. 4፡12-25)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ማቴ. 4፡12-25ን አንብብ። የክርስቶስ የመጀመሪያው አገልግሎት ዐበይት ባሕርያት ምንድን ናቸው? ለ) የክርስቶስ ትምህርት ከመጥምቁ ዮሐንስ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ከማቴ. 3፡2 ጋር አነጻጽር።

የክርስቶስ የመጀመሪያ ዓመት አገልግሎት እንደ ቀጣዩ ሁለት ዓመት ጥድፊያ የበዛበት አልነበረም። ማቴዎስ የመጀመሪያውን ቀዳሚ ዓመት አገልግሎቱን አልጠቀሰም። ክርስቶስ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ እንደ ለወጠ ወይም በኢየሩሳሌም ከኒቆዲሞስ ጋር እንደ ተገናኘ ማቴዎስ አልገለጸም። ማቴዎስ ከመጀመሪያው ዓመት ብዙ ሥራዎችን አልፎ፥ ይፋዊ አገልግሎቱን ብቻ በማጠቃለያ መልክ ይጀምራል። ይህንንም ያደርገው መጥምቁ ዮሐንስ ከታሰረበት ዓመት በመጀመር ነው። ምናልባትም ማቴዎስ ታሪኩን በዚህ መልክ የጻፈው፥ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የመጥምቁ ዮሐንስ «የመንገድ ጠራጊነት» ተግባር እንደ ተጠናቀቀ ለማሳየት ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ መሢሑ መጥቷል። ማቴዎስ ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያ አገልግሎት ሲያጠቃልል በቀረው ማጠቃለያ ላይ በአራት ነገሮች ላይ ትኩረትን አድርጓል፡

ሀ. ክርስቶስ በቀዳሚነት በገሊላ ስለ ማገልገሉ

በተከታዩ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ፥ ክርስቶስ በአብዛኛው ከናዝሬት 25 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ በምትገኝ በገሊላ ባሕር ጫፍ ላይ በነበረችው የቅፍርናሆም ከተማ አገልግሏል። ከተማይቱ ጠቃሚ በሆነ የንግድ መስመር ላይ ትገኝ ስለነበር፥ በቅፍርናሆም የሚያልፉ ብዙ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሰምተው ሊያምኑበት ችለዋል። በተጨማሪም ቅፍርናሆም ጴጥሮስንና ማቴዎስን ጨምሮ የብዙ ደቀ መዛሙርት መኖሪያ ነበረች።

ማቴዎስን ያስደነቀው ነገር ቢኖር፥ ክርስቶስ በገሊላ የሰጠው አገልግሎት የትንቢት ፍጻሜ መሆኑ ነበር (ኢሳ. 9፡1-2)። ገሊላ በብሉይ ኪዳን ዘመን በዛብሎንና በንፍታሌም ነገዶች ግዛት ውስጥ ትገኝ ነበር። እነዚህ ሁለቱም አካባቢዎች በኢየሩሳሌም በሚኖሩ አይሁዶች ዘንድ የተናቁ ነበሩ። ለዚህም ምክንያት የነበረው፥ በእነዚህ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ከአሕዛብ ጋር ተጋብተው ጣዖታቸውንም ያመልኩ ስለነበር ነው። በ722 ዓ.ዓ እስራኤል በአሦር ከተማረከችበት ጊዜ አንሥቶ፥ ይህ የጳለስታይን ክፍል በኣሕዛብ ቅኝ ግዛት ሥር ውሎ ነበር። ከዚህ በኋላ አይሁዶች በመቃባውያን ዘመን በገሊላ ሰፈሩ። እነዚህ አነስተኛ የአይሁድ ቅኝ ግዛቶች እያደጉ የሄዱ ሲሆን፥ ብዙውን ጊዜ በይሁዳ ከሚኖሩ አይሁዶች በላይ ብሔራዊ ስሜት ይሰማቸው ነበር። ይህም ሆኖ፥ በይሁዳ የሚኖሩ አይሁዶች የገሊላ አይሁዶችን ይንቋቸው ነበር። እንኳን መሢሑ አብዛኛውን ጊዜውን በምድር ላይ ማሳለፉ ቀርቶ፥ ምንም መልካም የሆነ ነገር ከገሊላ ይመጣል ብሎ የጠበቀ ሰው አልነበረም። (ዮሐ1፡45-46፤ 1፡41፥ 52 አንብብ።) ምንም እንኳን ገሊላ በብዙ ሰዎች ብትናቅም፥ እንደ ሰው የአገርና የጎሣ ኩራት በማያጠቃው አምላክ ተከበረች።

. ኢየሱስ፥ «መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ አስተማረ።

ማቴዎስ፥ የክርስቶስ መሠረታዊ ትምህርት የመጥምቁ ዮሐንስ ዓይነት መሆኑን አሳይቷል። ይህም ለሰዎች መንግሥተ ሰማይ እንደ ቀረበችና ንስሐ መግባት እንዳለባቸው የሚያሳስብ ትእዛዝ ነበር። መሢሑ በመካከላቸው ስለነበረ፥ ሕዝቡ ሕይወታቸውን መለወጥ ነበረባቸው። ከአሮጌው ሕይወታቸው ተመልሰው ለመሢሑ መንግሥት መዘጋጀት ያስፈልጋቸው ነበር።

ሐ ኢየሱስ ሰዎች ደቀ መዝሙሩ ሆነው እንዲከተሉት ጠርቷል።

በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው፥ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ስለ እግዚአብሔር ዐበይት እውነቶችን የሚያስተምሯቸው ደቀ መዛሙርት ነበሯቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት መምህሮቻቸው ወደሚሄዱበት ሁሉ እየሄዱ ይረዷቸውና ትምህርት ይቀስሙ ነበር፡ ክርስቶስ ይህንን ትውፊት በመከተል ከመጀመሪያው ራሱን እንደ ሃይማኖት መሪ አስተዋውቋል። ክርስቶስ ሰዎች እስኪከተሉት ከመጠበቅ ይልቅ፥ ደቀ መዛሙርቱን ለመምረጥ የአስተዋይነት ምርጫ አድርጓል። ማቴዎስ ክርስቶስ ከመረጣቸው ደቀ መዛሙርት የመጀመሪያ አራቱን ጠቅሷል። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ፥ ስምዖን ጴጥሮስና እንድርያስ የሚባሉ ወንድማማቾች ሲሆኑ፥ ሌሎቹ ሁለቱ ያዕቆብና ዮሐንስ የሚባሉ ወንድማማቾች ነበሩ። ክርስቶስ ከዚህ በፊት የነበራቸውን ሥራ ትተው እንዲከተሉት ጠራቸው። ዓሣ ማጥመዳቸውን እንዲተዉና የእርሱን ትምህርት ተቀብለው ሰዎችን እንዲያጠምዱ አሳሰባቸው። (ይህንን በዮሐንስ 1 ከሚገኘው ታሪክ ጋር በምናነጻጽርበት ጊዜ፥ አራቱም ደቀ መዛሙርት ለተወሰነ ጊዜ ክርስቶስን ከተከተሉ በኋላ ወደ ቀድሞ ሥራዎቻቸው በመመለሳቸው፥ ክርስቶስን ለመከተል እንደገና የተጠሩ ይመስላል።)

በወንጌላት ውስጥ ብዙውን ጊዜ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለመሆን ያገለገለው ቃል፥ «መከተል» የሚል ነው። ክርስቶስ ይህን ቃል በመጠቀም በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ላለው ሥልጣን እንዲገዙ እየጠየቃቸው ነበር። ዕቅዶቻቸውን ትተው የክርስቶስን ፈቃድ መፈጸም ያስፈልጋቸው ነበር። አኗኗሩን፥ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ቅርበት፥ ከሰዎች ጋር የነበረውን ቅርበትና ያገለገለበትን መንገድ መከተል ነበረባቸው። ተከታዮቹ እርስ በርሳቸው ኅብረት ነበራቸው። ይህም ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ይባላል። አካሉ በሆነችው ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሠራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለጴጥሮስ፥ እንድርያስ፥ ያዕቆብና ዮሐንስ ክርስቶስን የመከተሉ ምርጫ አስቸጋሪ ሊሆን የቻለው እንዴት ነበር? ለ) ከዚህ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስለ መሆን ምን እንማራለን? ሐ) የክርስቶስ «ተከታይ» መሆንህን እንዴት እያሳየህ እንደሆነ አብራራ።

በማቴ 28፡19-20 ላይ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የራሱን አርአያ በመከተል ሌሎች ደቀ መዛሙርትን እንዲያፈሩ ነግሯቸዋል። በምድር ላይ ከሚገኙ ነገዶች ሁሉ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ ይኖርባቸዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን ተጠርቷል። ይህ ምን ማለት ነው? ማቴዎስ ደቀ መዝሙር የክርስቶስን አዲስ የሕይወት ልምምድ ለመቀበል ሲል፥ አሮጌ ሕይወቱን የሚተው ሰው እንደሆነ ይነግረናል። ይህ በቀዳሚነት ስለ ኢየሱስ በመመስከር፥ ደቀ መዛሙርት ይሆኑ ዘንድ «ሰዎችን ማጥመድ»ን ጭምር የሚያካትት ነው። ክርስቶስ እርሱን ለመከተል ሥራችንን እንድንተው አይጠይቀን ይሆናል፤ ይሁንና ሕይወታችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንድናስገዛ ይፈልጋል። ማቴዎስ ክርስቶስን መከተል ማለት እርሱን ለመከተል ሁሉንም ነገር መተው እንደሆነ አመልክቷል። ይህ ከፍተኛ ዋጋን የሚያስከፍለን እንጂ ቀላል ውሳኔ አይደለም።

መ. ኢየሱስ ሲያስተምር፥ ሲሰብክና ሲፈውስ ዝናው እየገነነ መጣ።

ማቴዎስ፥ ክርስቶስ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ከመዘርዘር ይልቅ በማቴዎስ 5-7 ላይ በቀረበው የትምህርት አገልግሎቱ ላይ ያተኩራል። ነገር ግን የክርስቶስ ትምህርት የታላቁ አገልግሎት አካል እንደሆነ ለማሳየት ሲል፥ ማቴዎስ የክርስቶስን ተግባራትና የሕዝቡን ምላሽ ጠቅለል አድርጎ ገልጾአል። እንደ ተጻፈው ሁሉ ክርስቶስ በገሊላ ከተማ ውስጥ ከስፍራ ወደ ስፍራ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። በምኩራብና በሜዳ ላይ ባለማቋረጥ ያስተምር፥ ይሰብክና ይፈውስ ነበር። አንድ ምሑር እንደ ገለጸው፥ «ማስተማር» ኢየሱስ ሰዎች እንዲያውቁ የፈለጋቸውን እውነቶች ማሳወቁን ያመለክታል። ስብከት ደግሞ ክርስቶስ ሰዎች እውነትን ተግባራዊ ለማድረግ ሕይወታቸውን እንዲለውጡ መፈለጉን ያሳያል። ፈውስ ደግሞ ክርስቶስ ለሕዝቡ የነበረውን ርኅራኄ ብቻ ሳይሆን፥ መሢሕ መሆኑንም በይፋ ያሳየበት አገልግሎት ነበር። ከፈውሱ ዓይነት ኣንዱ ከኣጋንንት ነፃ መውጣት ሲሆን፥ ይህም የክርስቶስ መንግሥት የሰይጣንን መንግሥት እያሸነፈ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስ በዚህ ባሕሪው በሰዎች ዘንድ ተወዳጅነትን እያተረፈ ሊመጣ ችሏል። ከገሊላ በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከሶሪያ እስከ ደቡባዊቷ ኢየሩሳሌምና በስተምሥራቅ እስከሚገኙት ዐሥሩ ከተሞች ድረስ ስለ እርሱ ሥራ በሰፊው ይወራ ነበር።

ማቴዎስ ክርስቶስ የፈጸመውን ተግባር ጠቅለል ባለ ይዘት ካቀረበ በኋላ፥ በተቀረው የመጽሐፉ ክፍል ሁሉ በክርስቶስ ተአምራትና ዐበይት ትምህርቶች ላይ ያተኩራል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ አይ ኤም ከታተመውና የዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው)

Leave a Reply

%d bloggers like this: