የኢየሱስ ተከታዮች ሊከተሏቸው የሚገቡ መሠረታዊ መርሖዎች (ማቴ. 6፡19-7፡29)

አንዳንድ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እናወሳስበዋለን። የተለያዩ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ክርስቲያን ፍሬያማ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ብዙ አሳቦችንና ደንቦችን ያስተምራሉ። ይህ ደግሞ ክርስቲያኖች ተስፋ እንዲቆርጡና የበደለኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ከማድረጉም በላይ በኋላ ሰዎችን ለማስደሰት ከመጣር በቀር ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን አያደርግም።

ኢየሱስ በቀጣዩ የተራራው ላይ ስብከቱ የመንፈሳዊ ሕይወትን መሠረታዊ መርሖዎች ቀለል አድርጎ አቅርቧል። እነዚህን መርሖዎች ከግል ሕይወታችን ጋር ብናዛምድ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን አድገን የክርስቶስ በሳል ደቀ መዛሙርት ለመሆን እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 6፡19-7፡29 አንብብ። ሀ) ክርስቶስ የሰጣቸውን መሠረታዊ ትምህርቶች ዘርዝር። ለ) የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት እነዚህን መርሖዎች መገንዘብ የሚያስፈልገን እንዴት ነው?

መርሕ አንድ፡- በግል ሕይወትህ ላይ ሳይሆን፥ በዘላለሙ መንግሥት ላይ ትኩረት አድርግ።

ክርስቲያኖችን ከሚያጋጥሙ ዐበይት ፈተናዎች ኣንዱ፥ የገንዘብ ጉዳይ ነው። ሁላችንም ለመተዳደሪያ የምንፈልገው ነገር በመሆኑ ገንዘብ በራሱ መጥፎ አይደለም። በዛሬው ዓለም ውስጥ ገንዘብ ከሌለን፥ ምግብ ለመመገብ ልብስ ለመግዛት፥ የመኖሪያ ቤት ለመከራየት አንችልም። ነገር ግን ከዚህ አልፈን ገንዘብን በልባችን ውስጥ ከዐበይት ፍላጎቶቻችን ኣንዱ እንዲሆን በቀላሉ እናደርጋለን። ብዙ ገንዘብ ካገኘን ደስታችን የሚጨምር ይመስለናል። ኣዳዲስ ልብሶችን ልንገዛ፥ የተሻለ ምግብ ልንመገብ፥ በምርጥ ቤት ውስጥ ልንኖር እንችላለን። ይህም ብዙዎቻችን ተጨማሪ ገንዘብን እንድናገኝና ገንዘቡ የሚያስገኘውን ተጽዕኖና ደኅንነት እንድናሳድድ ያደርገናል።

ገንዘብ ሕይወታችንን እንዲቆጣጠር የምንፈቅድበት ዋንኛው ምክንያት፥ የተሳሳቱ ነገሮችን መመልከታችን እንደሆነ ኢየሱስ ራሱ ገልጾአል። ሥጋዊና መንፈሳዊ ዓይኖቻችን ለራሳችን የተመቻቸ ሕይወትን በማዘጋጀት ላይ ካተኮሩ፥ ልባችን በመንፈሳዊ ጽልመት ይሞላል። ነገር ግን መንፈሳዊ ዓይኖቻችን በመንፈሳዊ ነገሮችና በዘላለማዊ ጉዳዮች ላይ ካተኮሩ፥ ከሁሉም የሚልቀው ምን እንደሆነ በመገንዘብ ለዘላለም ሕይወታችን የሚጠቅም አኗኗርን እንከተላለን። ሥጋዊ ዓይኖቻችን መንገድ አይተን እንድንሄድ እንደሚረዱን ሁሉ፥ መንፈሳዊ ዓይኖቻችንም መንፈሳዊ እውነቶችን ተረድተን በመንፈሳዊ አኳኋን እንድንመላለስ ይረዱናል። የዓለም ነገሮች መንፈሳዊ ዓይኖቻችንን እንዲያሳውሩ ከፈቀድንላቸው መንገዳችን በጨለማ ተደናቅፎ ከእግዚአብሔር እውነት እንርቃለን። ከዚያ በኋላ ክርስቶስን ልንከተል አንችልም። (ይህ የምንመለከታቸውን ቪዲዮዎችና የምናነባቸውን መጻሕፍት በጥንቃቄ መምረጥ እንዳለብን ያስጠነቅቀናል። የምንመለከታቸው ቪዲዮዎች፥ የምናነባቸው መጻሕፍትና መጽሔቶች በአስተሳሰባችንና በተግባራችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖን ያስከትላሉ።)

ኢየሱስ አንድ ልብ ከአንድ ጌታ የበለጠ ሊያስተናግድ እንደማይችል ገልጾአል። ይህም ክርስቶስ ወይም እንደ ገንዘብ ያለ ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ገንዘብን ወይም ሌላ ማንኛውንም ሥጋዊ ነገር የሕይወቱ ቀዳሚ ትኩረት እያደረገ የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ሊል አይችልም። ብዙም ሳይቆይ የገንዘብ ፍቅሩ ከምድርና ከሰማይ መርሖዎች አንዱን እንዲመርጥ ስለሚያስገድደው፥ ምድርንና ጊዜያዊ በረከቶቿን መምረጡ አይቀርም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰዎች እጅግ የሚፈልጓቸውና እነርሱን ለማግኘት ሲሉ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያመቻምቹላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) እነዚህ ሰዎች ዓይኖቻቸውን ከዘላለማዊ ነገሮች ላይ ያነሡት እንዴት ነው?

መርሕ ሁለት፡- ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቅ፥ ለሁሉም በእግዚአብሔር ተማመን (ማቴ. 6፡25-34)

በዕብ. 11፡6 ላይ፥ ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደማይቻል ይናገራል። በአንድ ደቀ መዝሙር ሕይወት ውስጥ እጅግ መሠረታዊ የሆነው መርሕ በነገር ሁሉ በእግዚአብሔር የመታመን መርሕ ነው። በምንጨነቅበት ጊዜ ሁሉ፥ እግዚአብሔር ፍላጎታችንን ስለ ማሟላቱ መጠራጠራችን ነው። ሰዎች የሚጨነቁባቸው መሠረታዊ ነገሮች ምንድን ናቸው? ምግብና ልብስ ናቸው። ክርስቶስ ግን ለእነዚህም መጨነቅ እንደማያስፈልግ አስተምሯል። ገንዘብ የሚያስቀምጡባቸው ባንኮች ወይም ምግብ የሚገዙባቸው የገበያ አዳራሾች ባይኖሯቸውም፥ እግዚአብሔር የምድር ፍጥረታትን ሁሉ ይመግባል። እነዚህ ፍጥረታት ምግብ አጥተው አይራቡም። እግዚኣብሔር ሰዎች ከአዕዋፋትና ከእንስሳት እንደሚበልጡ ገልጾአል። ስለሆነም እግዚአብሔር አነስተኛ አስፈላጊነት ያላቸውን እንስሳት ከመገበ፥ የሰዎችን ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ ልጆቹን ፍላጎቶች እንደሚያሟላ እንገነዘባለን።

ክርስቶስ የንጉሥ ሰሎሞንን ውብ (ማለፊያ) ልብሶች ከአትክልቶች ጋር አነጻጽሯል። እግዚአብሔር ትናንሽ ተክሎችን እንደ ሰሎሞን ካሉት እጅግ ሀብታሞች የበለጠ አድምቆ ያላብሳቸዋል። እነዚህ አበቦች ከጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት የበለጠ ዕድሜ የላቸውም። ወዲያው ጠውልገው በእሳት ይቃጠላሉ። ሰዎች፥ በተለይም የእግዚአብሔር መንፈሳዊ ልጆች፥ ለእግዚአብሔር ከአበቦችና ከተክሎች በላይ አስፈላጊዎች ናቸው። ስለሆነም ያለጥርጥር የምንፈልገውን ልብስ ያለብሰናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የምትጨነቀው ምን ለማግኘት ነው? ለ) ጭንቀት በእግዚአብሔር አለመታመንህን የሚያሳየው እንዴት ነው?

የጭንቀት ተቃራኒ ምንድን ነው? ከጭንቀት ለመገላገል የሚረዳን ምንድን ነው? በሕይወት የተሳሳቱ እሴቶችን ከመያዝ የሚጠብቀን ምንድን ነው? ክርስቶስ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል። ዓይኖቻችንን በእግዚኣብሔር ዘላለማዊ ነገሮች ላይ ልንጥል ይገባል። ክርስቶስ ሀ) በእርሱ አገዛዝና ለእርሱ አስፈላጊ በሆኑት ነገሮችና ለ) ከእርሱ ጋር ካለን ግንኙነት በሚመጣው ጽድቅ ላይ ብናተኩር፥ ጭንቀታችን እንደሚወገድ ገልጾአል። ይህም ጽድቅ በታዛዥነትና በትክክለኛ መንገድ በመመላለስ ራሱን ይገልጻል። ጠቃሚዎቻችን ናቸው የምንላቸው ነገሮች ከእግዚአብሔር መንገዶች ጋር የሚስማሙ ሲሆኑ፥ እንደ ገንዘብና ትምህርት ያሉ ሌሎች ጌቶች እንዲቆጣጠሩን አንፈቅድም። ይህም ሲሆን እግዚኣብሔር ብዙውን ጊዜ የሚያስጨንቁንን መሠረታዊ ፍላጎቶቻችንን ያሟላል።

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 6፡33ን በቃልህ አጥና። ሀ) የክርስቶስን መንግሥትና ጽድቅ በትጋት የምትሻባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) ጭንቀት በዘላለማዊ ነገሮች ላይ አለማተኮራችንን የሚያመለክተው እንዴት ነው?

በመጨረሻም ክርስቶስ ስለ ወደፊቱ ዘመን መጨነቁ ሞኝነት እንደሆነ አብራርቷል። ምንም ያህል ብንጨነቅ የነገን ክስተቶች መለወጥ አንችልም። ጭንቀት የሚያስከትለው ነገር ቢኖር ኀዘን፥ ሽበትና የጨጓራ ሕመም ብቻ ነው። አባታችን የወደፊቱን ዘመን እንደሚቆጣጠርና እርሱ ያልወሰነው ነገር እንደማይደርስብን እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። በእርሱ ላይ ዓይኖቻችንን ተክለን በታዛዥነት የምንመላለስ ከሆን፥ እግዚአብሔር ወደፊት የሚመጣውን የትኛውንም ችግር ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል። ችግሩ የሚመጣው መፍትሔውን ከራሳችን ለማመንጨት በምንታገልበት ጊዜ ነው።

መርሕ ሦስት፡- ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት የፈራጅነትን አመለካከት አታንጸባርቅ (ማቴ. 7፡1-6)።

«የሆነ ምሥጢራዊ ነገር ስላለ ተጠንቀቅ። ልታታልልህ እየሞከረች ነው። አፉዋ የሚናገረው ቃል ከልቧ የፈለቀ አይደለም። «ይህንን ለምን እንዳደረገች አውቃለሁ። ስለማትወደኝ ልትጎዳኝ ትፈልጋለች።» «ከእኔ ለመቅደም ስለሚፈልግ፥ ከእኔ ጋር አይስማማም። ይህን ያደረገው እርሱ የሌላ ጎሳ አባል ስለሆነና የእኛን ጎሳ ስለማይወድ ነው።» «ሊፕስቲክ መቀባቷ መንፈሳዊት ሴት አለመሆኗን ያሳየናል።»

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ክርስቶስ በማቴ. 7፡1-6 ላይ ካስተማረው ኣሳብ ጋር የማይስማሙት እንዴት ነው? ለ) የሌሎች ሰዎችን አነሣሽ ምክንያቶች ለመፍረድ የምንሞክርባቸው ሌሎች መንገዶች ምንድን ናቸው?

የክርስቶስ ተከታዮችን ከሚያጋጥማቸው ታላላቅ ችግሮች አንዱ፥ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር መልካም ግንኙነት አለማድረግ ነው። የችግሩም መንሥዔ በጎሳዎች፣ በመሪዎችና በግለሰቦች መካከል ጥርጣሬ የሚከሰትባቸውን ዐበይት ምክንያቶች አለመገንዘባችን ነው። ከግለሰቡ ተግባር ባሻገር ዘልቀን፥ ልቡን የምንመረምርበት የተለየ ዓይን ያለን ይመስለናል። ይህ ግን ስሕተት ነው። የሰውን ልብ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከዚህ የሰዎች ዝንባሌ እንዲታቀቡ «አትፍረዱ» ሲል አጥብቆ አስጠንቅቋቸዋል። «መፍረድ» የሚለው ቃል ሁለት ፍካሬያዊ ትርጉሞች ኣሉት። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች ሊያደርጉ የሚገቧቸውን ነገሮች መገምገምን ሊያመለክት ይችላል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰዎችን፥ በተለይም የሐሰተኛ አስተማሪዎችን ሕይወት በመገምገም እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆን አለመሆናቸውን እንዲለዩ ነግሯቸዋል (ማቴ. 7፡15-20)። ግምገማው የሚካሄደው ግን በግልጽ መረጃዎች እንጂ በስውር አነሣሽ ምክንያቶች አይደለም። ሁለተኛው፥ መፍረድ የሌሎችን ኣነሣሽ ምክንያቶች በንቀት መመልከትን ሊያመለክት ይችላል። ይህንን በምናደርግበት ጊዜ ኣመለካከታችን፥ «እኛ ከእነርሱ እንሻላለን» የሚል ነው። ከተግባራቸው አልፈን ልባቸውን ለማየት የምንችል ይመስለናል። ክርስቶስ በዚህ መንገድ መፍረድ እንደሌለብን ተናግሯል።

ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ስንተች የራሳችንን ልብ በኃጢአት መቆሸሽ ከምንም አንቆጥርም። ኢየሱስ በዓይኑ የእንጨት ግንድ (ምሰሶ) ስላለበት ሰው በሚናገር ኣስገራሚ ምሳሌ ተጠቅሟል። ይህ ሰው በዓይኑ ጉድፍ ያለበት ሰው ሲያጋጥመው ለመርዳት ይሽቀዳደማል። በራሱ ዓይን ውስጥ ያለው ግንድ ግን ይህን ከማድረግ ይከለክለዋል። በተመሳሳይ መንገድ፥ የሌላውን ሰው የባሕርይ ችግር ወይም ድብቅ ኃጢኣት ማየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን ብዙዎቻችን ራሳችንን አጥርተን አንመለከትም። ለዚህ መፍትሔው የሌላውን ሰው ችግር ለማቃለል አለመሞከር አይደለም። ችግር ያለበትን ሰው መርዳቱ ተገቢ ነው። በመጀመሪያ ግን የራሳችንን ሕይወት አይተን ሌሎች ሕይወታችንን ለመመርመር እንዲረዱን ልንጠይቃቸው ይገባል። መጀመሪያ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲስተካከል ካደረግን በኋላ፥ ሌላው ሰው በእግዚአብሔር ቃል ብርሃን ሕይወቱን እንዲመረምር በትሕትና ልንረዳው እንችላለን (ያዕ. 5፡19-20፤ ገላ. 6፡0።

የሌሎች ሰዎችን ችግሮች እየተመለከትን አነሣሽ ምክንያቶቻቸውን መፍረድ በምንጀምርበት ጊዜ፥ ምን ይከሰታል? በመጀመሪያ፥ ሰዎች በእኛ ላይ ይፈርዳሉ። በሁለተኛ ደረጃ ፥ ለአመለካከታችን በእግዚአብሔር ፊት እንጠየቃለን።

ይህን ኣሳብ ወደ ተቃራኒ ኣቅጣጫ እንዳንወስድ መጠንቀቅ አለብን። አንዳንድ ሰዎች ግምገማ መፍረድ እንደሆነ በመግለጽ የዚህ ዓይነት ተግባር እንዳንፈጽም ያስጠነቅቁናል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን በእግዚአብሔር ቃልና በግልጽ ተግባራቸው ላይ ተመሥርተን ሰዎችን መገምገም እንዳለብን ያስተምራል። ለዚህ ነው ክርስቶስ የተቀደሰን ነገር ለውሸትና ለእሪያዎች መስጠት እንደሌለብን የሚያስረዳውን ምሳሌ የተናገረው። በዚህ ክፍል ውሾችና እሪያዎች ወንጌሉን ለመቀበል የማይፈልጉትን ሰዎች ያመለክታል። ስለሆነም ክርስቶስ፥ ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔርን የሚቃወም አመለካከት ይዘው መስማት ለማይፈልጉ ሰዎች በመመስከር ጊዜያቸውን ማጥፋት እንደሌለባቸው ገልጾአል።

መርሕ አራት፡- እግዚአብሔር የትጋት ጸሎትን ያከብራል (ማቴ. 7፡7-10)

ኢየሱስ ቀደም ሲል ስለ ጸሎት አስተምሯል (ማቴ. 6፡9-15)። ክርስቶስ የጸሎት ኣመለካከታችን ከእግዚአብሔር በምንቀበላቸው ነገሮች ላይ ሳይሆን፥ «እግዚኣብሔር ከሁሉም በላቀ ሁኔታ እንዴት ሊከብር ይችላል?» በሚለው ጉዳይ ላይ ማተኮር እንዳለበት አሳይቷል። በተጨማሪም ክርስቶስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ዐበይት የለውጥ አሳቦችን እያስተማረ ነበር። ብዙዎቻችን ፈጥነን የምንሰጠው ምላሽ፥ «ይሄ የማይቻል ነው።» «እኔ ጠላቶቼን ልወድ፥ ባሕሪዩን ልቀይር አልችልም» የሚል ነው። ክርስቶስም ይህ በተፈጥሯዊ ብርታታችን ሊሳካ እንደማይችል ተናግሯል።

ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን መጠን፥ ሁሉንም ነገር የሚያስችል የኃይል ምንጭ አለን። ያ የኃይል ምንጭ የሚገኘው በጸሎት ነው። ኢየሱስ ወደ ጸሎት ርእሰ ጉዳይ ተመልሶ ደቀ መዛሙርቱ እንዲጠይቁ፥ በር እንዲያንኳኩና እንዲሹ አበረታቷቸዋል። (በግሪክ፥ ይህ የአንድን ጊዜ ሳይሆን የሁልጊዜ ጥያቄዎችን ያሳያል።) በተለይ ክርስቶስ እንደሚሆኑና እንደሚቻሉ ስለገለጸላቸው ጉዳዮች ባለማቋረጥ ከጸለይን፥ እግዚአብሔር ጸሎታችንን በመመለስ ኃይልን ይሰጠናል። በዚህ ጊዜ ባሕርያችን ይለወጥና ለዓለም በማይቻል መንገድ እንመላለሳለን። (ማስታወሻ፡- ምንም እንኳ ይህ የጸሎት መርሕ ከእግዚአብሔር ለምንፈልጋቸው ነገሮች ሊሠራ ቢችልም፤ ዓውደ ምንባቡ የሚያሳየው እግዚኣብሔር የክርስቶስን ትእዛዛት የምንፈጽምበትን መንፈሳዊ እይታና ባሕርይ እንዲሰጠን መጠየቅን ነው።)

እግዚአብሔር ጸሎትን የዕድገታችን ሂደት አካል አድርጎ ይጠቀማል። በጸሎት ሳይተጋ መንፈሳዊ ብስለትን ሊያገኝ የሚችል ሰው የለም። በጸለይን ጊዜ እግዚአብሔር ፈጥኖ የሚመልስ ቢሆን ኖሮ፥ ማናችንም ለጸሎት ልንተጋ አንችልም ነበር። እርግጥ እግዚአብሔር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥባቸው ጊዜያት አሉ። እንደዚሁም ደግሞ ትዕግሥትንና ለፈቃዱ መገዛትን እንማር ዘንድ ምላሹን የሚያዘገይባቸው ጊዜያትም አሉ።

በጸሎት ላይ ልበ ሙሉነትንና ባለማቋረጥ መትጋትን የሚሰጠን ስለ እግዚአብሔር ማንነት ያለን ግንዛቤ ነው። እርሱ ከምድራዊ አባቶቻችን በላይ ለእኛ ከሁሉም የሚሻለውን ነገር ለመስጠት ይቸኩላል። ነገር ግን ለእኛ የሚሻለንን የሚያውቀው እርሱ ነው። የትኛው ዳቦ፥ የትኛው እባብ እንደሆነ ያውቃል። ለዚህ ነው እግዚአብሔርን በመተማመን፥ ለእርሱ በመገዛትና ለፈቃዱ መፈጸም ሳናቋርጥ መጸለይ የሚገባን።

የውይይት ጥያቄ፡- ብዙውን ጊዜ የምትጸልየው ምን ለማግኘት ነው? ለሚቀጥለው ሳምንት የጸሎት ጥያቄዎችህን ሰብስብ። ለእግዚአብሔር ክብር ምን ያህል ጊዜ ትጸልያለህ? እግዚአብሔርን ስለ ማንነቱ ምን ያህል ጊዜ ታመሰግነዋለህ? እግዚአብሔር በማቴዎስ 5-7 ላይ የተጠቀሱትን አመለካከቶችና ባሕርይ እንዲሰጥህ ምን ያህል ጊዜ ትጠይቀዋለህ? ለግል ጥያቄዎችህ ምን ያህል ጊዜ ትጸልያለህ?

መርሕ አምስት፡- ለሌሎች ያለን አመለካከት ትክክለኛ መሆኑን ለእኛ እንዲደረግልን በምንፈልገው እናውቃለን (ማቴ. 7፡12)።

ይህ መርሕ ተግባራችን መንፈሳዊ መሆን አለመሆኑን የምናውቅበት በመሆኑ፥ «ወርቃማው ሕግ» እየተባለ ሲጠራ ቆይቷል። ሰዎች ችግር በሚገጥመን ጊዜ እንዲረዱን፥ በሥራችን ላይ እንዲያበረታቱን፥ ላከናወንናቸው ተግባራት እንዲያመሰግኑን እንፈልጋለን። ክርስቶስ ይህ እውነት ከሆነ፥ ለሌሎች ልናደርገው እንደሚገባን ገልጾአል። ለእኛ እንዲሆን የምንፈልገውን ለሌሎች ማድረግ አለብን። ለእኛ የማንፈልገውን ደግሞ ለሌሎች ማድረግ የለብንም። ሌሎች ሰዎችን በአግባቡ ስለ ማስተናገድ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሚገኘው ሕግ ሁሉ (ሕግና ነቢያት) በዚህ ትእዛዝ ተጠቃሏል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች እንዲያደርጉልህ የምትፈልጋቸውን ነገሮችና እንዴት እንዲያስተናግዱህ እንደምትፈልግ ዘርዝር። ለ) የቅርብህ የሆኑትን እሥር ሰዎች ስም ዘርዝር። ለእነዚህ ሰዎች እነዚህን ነገሮች የምታደርግባቸውን መንገዶች ግለጽ።

የኢየሱስ ክርስቶስ ስብከ ፍጻሜ (ማቴ. 7፡13-28)

እግዚአብሔር ምንም ነገር በግድ እንዲሠራ አይፈልግም። እርሱ እንድንሄድበት የሚገባንን መንገድ በፊታችን ያኖራል፤ የተሳሳተ ምርጫ የሚያስከትሏቸውን አንዳንድ ሁኔታዎችንም ይነግረናል። ከዚያ በኋላ መታዘዝ ወይም አለመታዘዝ የእኛ ድርሻ ይሆናል። ክርስቶስም ስብከቱን የቋጨው ከፊታችን ያለውን ምርጫና ውጤቱን በማሳየት ነው። ክርስቶስ እራት ንጽጽሮችን አቅርቧል።

ሀ. ሁለት መንገዶች፥ ሁለት ደጆች (ማቴ. 7፡13-14)። ሕይወት የሁለት መንገዶች ወይም ደጆች ድምር ውጤት ነው። ብዙ ሰዎች የሚሄዱበት ሰፊና ቀላል መንገድ አለ። እያንዳንዱ ሰው ሲወለድ በሰፊው ደጅ ይገባና በሰፊው ጎዳና መመላለስ ይጀምራል። ይህ ተወዳጅ መንገድ ነው። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ የማመፅ ጎዳና ስለሆነ፥ የዘላለምን ፍርድ ያስከትላል። ሌላው መንገድ ጠባብና አስቸጋሪ ነው። በዚያ መንገድ የሚሄዱ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። ይህ ሰዎች በልደት ሳይሆን፥ በምርጫ የሚያገኙት መንገድ ነው። ይህ የስደት የመስቀል፥ ወይም ለእግዚአብሔር የመታዘዝ መንገድ ነው። ይህ መንገድ አስቸጋሪ ቢሆንም፥ በመጨረሻ የዘላለምን ሕይወት የሚያስገኝ በመሆኑ አስደሳች ነው። ስለሆነም ለሕይወት የምንመርጠው መንገድ ፍጻሜውን ይወስነዋል። ከእነዚህ መንገዶች አንዱን የመምረጥ ዕድል ቢሰጠንም፥ መንገዱ እኛን የሚወስድበትን አቅጣጫ ልንቆጣጠር አንችልም።

ለ. ሁለት ዓይነት ዛፎችና ፍሬዎች (ማቴ. 7፡15-20)። እንደዚሁም ሕይወት ተመሳሳይ የሚመስሉ ሁለት ዛፎች ናት። እነዚህ ሁለት ዛፎች የሃይማኖት መሪዎች ቢሆኑም፥ ክርስቲያኖችንም ሊያካትቱ ይችላሉ። አንዱ እውነተኛ መንፈሳዊ መሪ ሲሆን፥ ሌላኛው የሐሰት ነቢይ ነው። ሁለቱም ተመሳሳይ ቃላትን በመናገር፥ መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ፥ በተመሳሳይ ጊዜ በመሥራት፥ አንድ ዓይነት ይመስላሉ። ማን ከእግዚአብሔር እንደሆነና ማንስ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን? ክርስቶስ ልዩነቱ ከፍሬያችው እንደሚታይ ተናግሯል። እንደ ክርስቶስ ሕይወቱን ሌሎችን ለማገልገል የመስጠት ባሕርይ ያለው ሰው፥ መንፈሳዊ መሪ ነው። ነገር ግን የክርስቶስ ባሕርይ የሌለውና የራሱን የግል ክብር የሚፈልግ፥ ለቤተ ክርስቲያን ምእመናን ራሱን እንደ መስጠት ፈንታ ከእነርሱ ትርፍ የሚሻ ሰው እርሱ የሐሰት መሪ ነው። (ይህ ሰዎች እውነተኛ መሢሕ የሆንውን ክርቶስን ሐሰተኛ የሃይማኖት መሪዎች ከሆኑት ፈሪሳውያን እንዲለዩ ፍንጭ ሳይሰጥ አልቀረም። እነርሱ የሚያገለግሉት ለራሳቸው ጥቅም ሲሆን፥ ክርስቶስ የመጣው ሕይወቱን ለሌሎች ለመስጠት ነበር። ማር 10፡45 አንብብ።)

ይህ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። ሕይወታቸው በማቴዎስ 5-7 ላይ በተገለጹት ባሕርያት ካልተሞላ፥ ወይም ከአመራሩ ስፍራ የግል ጥቅም የሚፈልጉ ከሆነ፥ በእግዚአብሔር ሳይሆን በክፉው ተጠርተዋል ማለት ነው። እነዚህ ለጥፋት የተላኩ ተኩላዎች ናቸው። ስለሆነም፥ ፍሬ የማይሰጥ ዛፍ የኋላ ኋላ ተቆርጦ እንደሚጣል ሁሉ፥ እነዚህም መሪዎች ይጠፋሉ።

ሐ. በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ሁለት ዓይነት የክርስቶስ ተከታዮች (ማቴ 721-23)። ይህ ክርስቶስ ከሐሰተኛ መሪዎች ይልቅ በሐሰተኛ ደቀ መዛሙርት ላይ ትኩረት አድርጎ ሲያስተምር የቆየው አሳብ ተከታይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና እንዳልሆነ መለየቱ ቀላል አይሆንልንም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት በምንቆምበት ጊዜ ልዩነቱ በግልጽ ይታያል። አንዳንድ ሰዎች ትንቢትን የመናገር፥ አጋንንትን የማስወጣት፥ ተአምራትን የማድረግ፥ በቃላቸው የክርስቶስን ጌትነት የመቀበል ባሕርይ ይታይባቸዋል። (ማስታወሻ፡- ክርስቶስ በዚህ ስፍራ አምላክነቱን በግልጽ በማመልከት፥ በሰዎች ላይ መፍረድን ወደ ሲኦል ወይም መንግሥተ ሰማይ መግባት እንዳለባቸው የመወሰን ሥልጣን እንዳለው ገልጾአል።) ነገር ግን ለራሳቸው ኖረው ለራሳቸው ስለ ሠሩና ከክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ስላልመሠረቱ፥ እነዚህ ሰዎች ወደ ሲኦል እንደሚላኩ ክርስቶስ ተናግሯል። ሌሎች በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የተገለጹትን የደቀ መዝሙርነት ባሕርያት ተላብሰው ለእግዚአብሔር እየተገዙ የሚኖሩ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ይገባሉ።

ይህ ክርስቶስ ለእያንዳንዳችን የሚሰጠን ማስጠንቀቂያ ነው። የሰዎች እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት የሚታወቀው ከንግግራቸው፥ ወይም ከሚሠሯቸው አስደንቂ ተአምራት አይደለም። የእውነተኛ ደቀ መዝሙር ዋንኛ ማረጋገጫ ከክርስቶስ ጋር ያለው ግንኙነትና ውስጣዊ የግል ሕይወቱ ብቃቶች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ተኣምራትን የሚሠራ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደሆነ እንዳናስብ የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው? ለ) ኢየሱስ ባሕርይና ታዛዥነት፥ ከተእምራትና ንግግርን ከማሳመር እንደሚበልጥ የተናገረው ለምንድን ነው?

መ. ሁለት ቤት ሠሪዎችና ሁለት ቤቶች (ማቴ. 7፡24-27)። ኢየሱስ ሰዎች ምርጫ እንዲያደርጉ ለማገዝ አንድ ተጨማሪ አጠቃላይ ጥሪ በማቅረብ ስብከቱን አጠቃሏል። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ቀላል ተግባር አይደለም። ሕይወት በችግሮች የተሞላች ናት። ሰዎች በዓለም ውስጥ የሚጋፈጧቸው የተለመዱ ችግሮች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ደግሞ ከጥላቻና ስደት ጋር በተያያዘ ጊዜያት ተጨማሪ ችግሮች አሉባቸው። እነዚህ ችግሮች በሚመጡበት ጊዜ የግለሰቡ የእምነት ሕንጻ ጸንቶ ይቆማል ወይስ ይፈራርሳል። የእምነቱ መጽናት ወይም መፈራረስ የሚወሰነው በእምነቱና በመሰጠቱ መሠረት ላይ ነው። የክርስቶስን ትምህርት በጥንቃቄ አጥንቶ ከሕይወቱ ጋር ካዛመደ፥ እምነቱ ይጸናል። ነገር ግን ጠንካራውን የደቀ መዝሙርነት ጥሪ ሰምተው ጠባቧን መንገድ ካልመረጡ፥ እምነታቸው ወዲያውኑ ይጠፋል።

በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች ከእምነታቸው እየወደቁ ናቸው። ይህ ለምን ሆነ? ለሰዎች የተሳሳተ ምርጫ ስለምናቀርብላቸው ይሆን? ሊያጋጥማቸው ስለሚችለው አስከፊ ስደት ሳንጠቁም፥ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመኑ እያልን እንጠራለን። የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን በሕይወታቸው፥ በተግባራቸውና ከዓለም ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ የሚያስከትላቸውን ዐበይት ለውጦች አንናገርም። ስለሆነም ሰዎች ቀላል ውሳኔ ይሰጡና ችግር ሲመጣ ይሸሻሉ። ነገር ግን ቀደም ብለው ለውጦቹን ካወቁና ጠባቧን መንገድ ከመረጡ፥ ዋጋቸውን ተምነዋልና ችግር ሊመጣ እምነታቸውን አይተዉም።

የውይይት ጥያቄ፡- የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ ለማብራራት፥ የወንጌል ምስክርነታችንና አዳዲስ ክርስቲያኖችን የምናስተምርበት መንገድ እንዴት ሊለወጥ ይገባል?

ማቴዎስ፥ ክርስቶስ ባስተማረ ጊዜ፥ የሰሙትን ሰዎች ምላሽ በማቅረብ፥ ይህን ክፍል ደምድሟል። ሰዎችን ያስደነቀው የክርስቶስ ትምህርት ብቻ ሳይሆን፥ ያስተማረበት መንገድ ጭምር ነበር። እንደ አይሁድ ሃይማኖት መምህራን ሌላ ታላቅ ሰው የተናገረውን እየደገመላቸው አልነበረም። ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ሥልጣን እንዳለው ነበር ያስተማራቸው። እንደ መሢሕ፥ እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን ሲሰጥ ምን አሳብ እንደ ነበረው ያውቅ ነበር። ለሰዎቹም የሕይወት ምርጫቸው የዘላለም ሕይወት ወይም ሞት እንደሚያስከትል በግልጽ ለመናገር ይችል ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading