የዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት መላክ (ማቴዎስ 10:1-42)

ክርስቶስ ታላቁ መምህርና ፈዋሽ ብቻ ሳይሆን፥ ዋንኛ አሠልጣኝም ነበር። ብዙውን ጊዜ ስለ ትምህርት ስናስብ፥ በትምህርት ቤት የተወሰኑ እውነቶችን ተምሮ ቤት ክርስቲያንን ስለ መምራት እናስባለን። ይህን አይነቱን ስልጠና ካገኘን በኋላ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል ብቁዎች ነን ብለን እናስባለን። የዚህ ዓይነቱ የአመራር ሥልጠና ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ፍላጎቶች ለማሟላት ኣልቻለም።

በትምህርት ቤት ውስጥ መማር የክርስቶስ ሥልጠና ተቃራኒ ነው። ክርስቶስ መጽሐፍ ቅዱስ ያልነበረው ከመሆኑም በላይ ቁጭ ብሎ ንድፈ አሳቦችን (ቲዎሪ) አላስተማረም። በአንድም ጊዜም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አላስተማረም። ለክርስቶስ አገልግሎት ውጤታማነት ከሚጠቀሱት ዐበይት ነገሮች አንዱ፥ ደቀ መዛሙርቱን ያመሰገነበት ሁኔታ ነው። ደቀ መዛሙርቱን ደህና አድርጎ ባያሠለጥናቸው ኖሮ፥ ክርስቶስ ወደ ሰማይ እንዳረገ ቤተ ክርስቲያን ትሞት ነበር። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ እንደ ክርስቶስ ለመሆን በመብቃታቸው፥ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላውን የሮም ግዛት በአንድ ትውልድ እስክታጥለቀልቅ ድረስ አደገች። እንግዲህ፥ ከክርስቶስ ሥልጠና ውስጥ ልንመለከታቸውና ዓለምን የሚለውጡ መሪዎችን ለማፍራት የምንጠቀምባቸው ቁልፍ አሳቦች ምንድን ናቸው?

  1. ክርስቶስ የሕያው እምነትና ከእርሱ ጋር የተጋጋለ ግንኙነት የማድረግን ሁኔታን አሳይቷል። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር ኖረው ለሶስት ዓመታት ያህል ሲመለከቱት ቆይተዋል። በዚህም ከቃላቱ ይልቅ ከምሳሌው የበለጠ ተምረዋል።
  2. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚያስተዳድሩ፥ እንደሚሰብኩና እንዴት ታምራትን እንደሚፈጽሙ ሳይሆን፥ እንዴት የተለወጠ ባሕርይ ሊኖራቸው እንደሚችል አስተምሯቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው አንድን ተግባር እንዴት እንደሚያከናውን ማሳየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን በሕርዩን ወደ መንፈሳዊ መሪነት መለወጡ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ብዙ እውቀት ኖሮት የመንፈሳዊ አመራር ባሕሪው የሌለው ሰው፥ ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለማውደም የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው።
  3. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ትክክል ነው ብለው ያሰቡትን የዓለምን የአመራር ሁኔታ በጥብቅ ተቃውሟል። ደቀ መዛሙርቱ ኃይልን፥ ሥልጣንንና የመሪነትን ጥቅሞች ለማግኘት ሲፈልጉ፥ ክርስቶስ ግን መሪነት አገልግሎት እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ይህንንም እግራቸውን በማጠብ አርኣያነቱን ያሳያቸው ሲሆን፥ የዚህ ዓይነቱ አመራር አገልግሎት መሆኑን አስተምሯቸዋል። ክርስቶስ በመንግሥቱ ውስጥ ታላቁ የተባለ ሰው የሌሎችን ፍላጎቶች ከራሱ የሚያስቀድምና ዝቅ የሚልና የሚያገለግል እንደሆነ በመግለጽ አስተምሯቸዋል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር ብዙ መሪዎች አሁንም የዓለምን የአመራር አመለካከት የሚያንጸባርቁ መሆናቸው ነው።
  4. ክርስቶስ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ማገልገል እንደሚቻል አሳይቷል። እንዴት ማስተማር፥ መስበክ፥ መፈወስ፥ መጸለይ እንደሚቻል በራሱ ምሳሌነት አስተምሯቸዋል። ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ያደረጉት ሁሉ እርሱ ሲያደርግ የተመለከቱት ነበር።
  5. የክርስቶስ ትምህርት እውነትን ከሕይወት ጋር የማዛመድ ተግባር ነበር። ክርስቶስ ያስተማረው ስለ እግዚአብሔር እውነትን ወይም በንድፈ አሳባዊ መንገድ መመስከርን አልነበረም። ክርስቶስ የተመላለሰውና ያስተማረው ምሳሌዎችንና የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ለደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ እውነቶችን በመግለጽ ነበር።
  6. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ እየተመለከታቸው እንዲያገለግሉ በማድረግ ሲያጠፉ አርሟቸዋል። . (ይህንን በዛሬው ትምህርታችን እንመለከተዋለን።)
  7. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ኣገልግሎታቸውን በሚያካሂዱበት ጊዜ፥ መንፈስ ቅዱስ እንዲያድጉ እንደሚረዳቸው ተማምኗል (ዮሐ. 14፡26)። እርሱ ያስተማረበት ጊዜ፥ የትምህርት መጨረሻ ሳይሆን መጀመሪያ ነበር። ለራሳቸው እንዴት እንደሚማሩ በማሳየት፥ መማራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- የአመራር የሥልጠና ፕሮግራሞቻችንን የክርስቶስን ምሳሌነት ተከትለን ብናዋቅር፥ ምን ምን ነገሮችን መለወጥ ይኖርብናል?

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴዎስ 10–11 አንብብ። ሀ) ከዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ምን እንማራለን? ለ) ስለ ደቀ መዝሙርነትና አመራር የምንማራቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ደቀ መዛሙርቱ እግዚአብሔር ብዙ ትክክለኛ መሪዎችን ያስነሣ ዘንድ እንዲጸልዩ ከነገራቸው በኋላ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ የሰዎችን ፍላጎቶች እንዲያሟሉና ስለ መጪው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲያስተምሩ ላካቸው። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ሌላ ሰው ለችግሩ የእግዚአብሔር መፍትሔ እንዲሆን ከመጻለይ አልፈው ራሳቸው በትጋት በአገልግሎቱ ውስጥ ይሳተፉ ነበር።

ክርስቶስ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርትን መርጦ ለአገልግሎት አሰማራቸው (ማቴ. 10)

ክርስቶስን በደቀ መዝሙርነት የሚከተሉት ብዙ ሰዎች ነበሩ። ክርስቶስ እነዚህን ሁሉ ደቀ መዛሙርት በእኩል ደረጃ ካለመመልከቱም በላይ፥ በተለያየ ብቃት ደረጃ አሠልጥኗቸዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ደቀ መዛሙርት በብዛት የሚከተሉት ነበሩ። በክርስቶስ ዕርገት ጊዜ፥ ቢያንስ 120 ደቀ መዛሙርት እንደነበሩ ሲታወቅ፥ ቁጥራቸው ከዚህ እንደሚበልጥ የሚያጠራጥር አይሆንም (1ኛ ቆሮ. 15፡6)። ሁለተኛ፥ የሰባ ደቀ መዛሙርት ቡድን ነበር። ክርስቶስ እነዚህንም ለአገልግሎት አሰማርቷቸዋል (ሉቃስ 10፡)። ሦስተኛ፡ 12ቱ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ማቴዎስ ክርስቶስ እነዚህን ደቀ መዛሙርት እንዴት እንደ መረጣቸው በመግለጽ፥ ስማቸውን ዘርዝሯል። እነዚህ ሰዎች በጥልቀት የሠለጠኑ ሲሆኑ፥ የሐዋርያነት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። እነዚህ ሰዎች በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን፥ የክርስቶስን ሥልጣን ይዘው በእንደራሴነት አገልግለዋል። በመጨረሻም፥ ከክርስቶስ ጋር እጅግ ቀርበው የሚሠሩ ሦስት ደቀ መዛሙርት ነበሩ። በልዩ አጋጣሚዎች ክርስቶስ ጴጥሮስን፥ ዮሐንስንና የያዕቆብን በመውሰድ አንዳንድ እውነቶችን ገልጦላቸው ነበር (ለምሳሌ፥ ማቴ. 17፡1)። ክርስቶስ አንድ ከሁሉም በላይ የቀረበ ወዳጅ እንደነበረው የሚያሳዩ ፍንጮች አሉ። ዮሐንስ ራሱን የገለጸው «ክርስቶስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር» በማለት ነበር (ዮሐ. 20፡2)። ክርስቶስ ከሁሉም ደቀ መዛሙርት ጋር እኩል ዝምድና አልነበረውም። ክርስቶስ ዓለምን ለመለወጥ ጥቂት ሰዎችን በብቃት አሠልጥኗል። ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የክርስቶስን አብነት ተከትለው ብዙ ሰዎች ከማሠልጠን ሊቆጠቡና ጥቂቶችን ደህና አድርጎ በማሠልጠኑ ላይ ሊያተኩሩ አይገባም ትላለህ?

ማቴዎስ 10 ክርስቶስ 12ቱ ደቀ መዛሙርት በአንድ የአገልግሎት ጉዞ እንዲያከናውኑ የሚፈልገውን መስፈርት የቀድሞይቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የ12ቱን ደቀ መዛሙርት ምሳሌነት ተከትለው ወንጌልን በዓለም ሁሉ በሚመሰክሩበት ጊዜ ሊጠብቁ ከሚገባቸው ገጠመኝ ጋር የሚያዋህድ በመሆኑ፥ አስገራሚ የወንጌል ክፍል ነው። ማቴዎስ የ12ቱን ደቀ መዛሙርት ለአገልግሎት መላክ ተጠቅሞ፥ ከሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን እንደሚጠበቅ አስተምሯል። በምኵራብ መደብደብን የመሳሰሉት ብዙዎቹ ነገሮች ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ባይከሰቱም፥ ክርስቶስ ካረገ በኋላ በአይሁድ ክርስቲያኖች ላይ ደርሰዋል።

ከዚህ ክፍል የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፡

ሀ. መጀመሪያ ክርስቶስ 12ቱ ደቀ መዛሙርቱ አሕዛብን ወይም ሰማርያውያንን ሳይሆን አይሁዶችን እንዲያገለግሉ አዝዟቸዋል። በኋላ ግን ክርስቶስ ይህንን አመለካከት ለውጧል። በማቴዎስ 28፡19-20 እና የሐዋ. 1፡8 ክርስቶስ እነዚህ አገልጋዮች ወደ ሰዎች ሁሉ እንዲሄዱ ኣዝዟቸዋል። ምናልባትም በማቴዎስ የቀድሞይቱን ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አሠራር እያሳየ ይሆናል። እንደ ጳውሎስ ከአይሁዶች ይጀምሩና ወንጌሉን በፍጥነት ወደ አሕዛብ ይወስዱ ነበር። (የሐዋ. 8፡44-48 አንብብ)

ለ. ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የጠራ መልእክት ሰጥቷቸዋል። ይኸውም ስለ መንግሥተ ሰማይ እንዲያስተምሩ ነበር። ያስተላለፉት መጥምቁ ዮሐንስና ክርስቶስ ያስተማሩትን ተመሳሳይ መልእክት ነበር። የክርስቶስ ተከታዮች አዳዲስ እውነቶችን ከመሻት ይልቅ መልእክታቸውን ቀለል አድርገው ማቅረብ ነበረባቸው።

ሐ. ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ዓይነት አገልግሎት በማካሄድ፥ ሊፈውሱ፥ ሙታንን ሊያስነሡና አጋንንትን ሊያስወጡ ይገባቸው ነበር። በኋላም እነዚህ 12ቱ ደቀ መዛሙርት፥ «ሐዋርያት» ተብለው ተጠርተዋል። ለዚህም ምክንያቱ መልእክቱን ለማወጅና ተግባራቱን ለማከናወን በክርስቶስ ሥልጣን የተላኩ መሆናቸው ነው።

መ. ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ገንዘብና ተጨማሪ ልብስ በመውሰድ ራሳቸውን ከሚንከባከቡ ይልቅ በሰዎች እንግዳ ተቀባይነት ላይ እንዲደገፉ ነግሯቸዋል። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ወደ አዲስ አካባቢ በሚሄድበት ጊዜ፥ ለምግብና መኝታ የሚከፍለውን ገንዘብ፥ ተጨማሪ ልብስ ይይዛል። ክርስቶስ ለዚህ የደቀ መዛሙርት የጉዞ አገልግሎት የሰጠው መመሪያ ጊዜያዊ ነበር። የክርስቶስ ትእዛዝ ሌሎችን ለእግዚአብሔር መንግሥት የማዘጋጀቱ ተግባር አጣዳፊ እንደሆነ ያሳያል። እርሱም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመቆየት ብዙ ጊዜ አልቀረውም። ይህ ትእዛዝ ጊዜያዊ በመሆኑ፥ ክርስቶስ በኋላ ለውጦታል (ሉቃስ 22፡5-37)። ክርስቶስ ካረገ በኋላ፥ ሐዋርያት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሚስማማ ሌላ አሠራር ተከትለዋል።

ደቀ መዛሙርቱ ወደ አንዲት ከተማ በሚደርሱበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ቤቱ ወስዶ የሚንከባክባቸውን ሰው ያዘጋጅላቸው ነበር። ባለቤቱና የከተማይቱ ነዋሪዎች የክርስቶስ መልእክተኞች አድርገው ሲቀበሏቸው፥ በእነርሱ ላይ የእግዚአብሔርን ሰላም የማወጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ የክርስቶስን ደቀ መዛሙርት ለመቀበል ካልፈለጉ፥ ደቀ መዛሙርቱ የእግራቸውን ትቢያ ማራገፍ ነበረባቸው። ይህም አይሁዶች ከከተማይቱ ምንም ነገር እንዳልወሰዱና እግዚኣብሔር በከተማይቱ እንደሚፈርድ ለማመልከት የሚጠቀሙበት ተምሳሌት ነበር። ሕዝቡ ወንጌሉን ሰምተው ሊቀበሉ የሚችሉበት ዕድል ነበራቸው። ይህን ለማድረግ ባለመፈለጋቸው፥ እግዚአብሔር በአብርሃም ዘመን ካጠፋቸው የሰዶምና ገሞራ ከተሞች በላይ፥ ኃጢአተኞች ይሆናሉ (ዘፍጥ. 19)። ስለሆነም፥ በፍርድ ቀን በእግዚአብሔር ይኮነናሉ።

ማቴዎስ፥ ለክርስቶስ የሚሰጠው አገልግሎት ክርስቶስ የሚያስፈልገኝን ያሟላልኛል በሚል ፍጹም የጥገኛነት ስሜት መካሄድ እንዳለበት ያሳያል። እርሱ አገልጋዮቹን ሊረዷቸው ወደሚችሉ ትክክለኛ ሰዎች ይመራቸዋል፤ ከረሃብ ይጠብቃቸዋል። ስለሆነም፥ ደቀ መዛሙርቱ ስለሚበሉት ወይም ስለ ገንዘብ ጉዳዮች መጨነቅ አያስፈልጋቸውም ነበር። ክርስቶስ ፍላጎታቸውን ሁሉ ያሟላላቸዋል።

ሠ. እንደ ክርስቶስ አገልጋዮች፥ የገንዘብ ድጋፍ መቀበል ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ለሚያካሂዱ ሰዎች፥ «ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋል» ሲል አጠቃላይ መርሕ ሰጥቷል። ወንጌሉን ከመስበክ የተጠቀሙ ወገኖች ለደቀ መዛሙርቱ ማካፈል ያስፈልጋቸው ነበር። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ በወንጌል ሰበካ መበልጸግ አያስፈልጋቸውም ነበር። የሐሰት አስተማሪ ከሚታወቅባቸው መንገዶች አንዱ የቤተ ክርስቲያን አባላትን እየበዘበዘ በአገልግሎት ስም መክበሩ ነው። ነገር ግን ሠራተኞች ለኑሯቸው የሚበቃ ገቢ ሊኖራቸው ይገባል። ስለሆነም፥ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከምእመናኑ ኑሮ የበለጠ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ገንዘብ መጠየቁ ተገቢ አይደለም። ምእመናንም መሪዎቻቸው ያለ ደመወዝ ወይም ከሌሎች ምእመናን ባነሰ የኑሮ ደረጃ ሆነው እንዲያገለግሉ መጠበቁ ተገቢ አይደለም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 400 አባላት ባላት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም አሥራት የሚከፍል ቢሆን፥ በምእመናን ደረጃ የሚኖሩ ስንት ሰዎች መቅጠር ይቻላል? ላ) አብያተ ክርስቲያናት ብዙውን ጊዜ ለሠራተኞች የምንከፍለው ገንዘብ የለንም ሲሉ ያማርራሉ። ይህ ለምን ይመስልሃል? ሐ) አንዳንድ ጊዜ ከምእመናን የበለጠ ትምህርት ያላቸው አገልጋዮች የበለጠ ደመወዝ ይጠይቃሉ። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው? ለምን?

ክርስቶስ እርሱ ካረገና ቤተ ክርስቲያን ካደገች በኋላ፥ ወደፊት ስለሚሆነው ሁኔታ እያሰበ ሳይሆን አይቀርም። እርሱ በምድር ላይ ሳለ የተጠቀሱት ስደቶች መከሰታቸውን የሚያመለክት መረጃ የለም። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ወደፊት አገልግሎታቸው የሰጣቸው ዋንኛ ማስጠንቀቂያ የስደት መምጣት ነበር። ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ወንጌል ስርጭት ካስተማራቸው ትምህርቶች ከግማሽ የሚበልጠው ስደትን የሚመለከት ነው። ይህ ዛሬ ብዙ ሰዎች ከሚያስተምሩት የተለየ ነው። ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ስደት የወንጌሉ አካል እንደሆነና ክርስቶስን መከተል ማለት የስደቱ አካል የሆነውን መስቀል መከተል እንደሆነ አንናገርም። በተለይ ወጣቶችና የተማሩ ሰዎች ላደትና የገንዘብ ችግር እንዳይከሰትባቸው ይፈራሉ። ነገር ግን ሁሉም የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በሆነ መንገድ እንደምንሰደድ ይገልጻሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 1፡20-21፤ ዮሐ 16፡33፣ የሐዋ. 8፡1፣ ሮሜ 8፡35፤ ዕብ 10፡፡ 2ኛ ቆሮ. 12፡10፤ 2ኛ ተሰ 4 ኣንብብ። ስለ ስደት ምን እንደሚያስተምሩ ግለጽ።

ክርስቶስ ስለ ክርስቲያኖችና ስደት ብዙ ተናግሯል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደመሆናቸው መጠን፥ ሐዋርያት፥ ነቢያት፥ መጋቢያንና ወንጌላውያን ብዙውን ጊዜ በቀዳሚነት ይሰደዳሉ። ቀጥሎ ያለው ክርስቶስ ያስተማረው አሳብ ማጠቃለያ ነው፡

ሀ. ክርስቲያኖች ተቃውሞና ስደት እንደሚደርስባቸው መጠበቅ አለባቸው። የክርስቶስን በጎች ሊያጠቁ የሚፈልጉ ብዙ ተኩላዎች ይመጣሉ። ወደፊት የሚነሣውን የአይሁዶች ተቃውሞ በማሰብ፥ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከምኩራቦች እንደሚባረሩና ለፍርድ ወደ አይሁድ የሽማግሌዎች ካውንስል እንደሚወሰዱ አስጠንቅቋል። ክርስቶስ በጲላጦስ ፊት እንደተናገረው ሁሉ፥ እነርሱም ወደ ሮም ገዥዎች ይጎተቱ ነበር። ጳውሎስ በቄሣር ፊት እንደ ቀረበ ሁሉ፥ ወደ ነገሥታት ይወሰዱ ነበር። ይህ ግን ወንጌሉን የሚመሰከሩበትን ዕድል ያዘጋጅላቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ስደት በሚደርስባቸው ጊዜ፥ ሊደነቁም ሆነ ሊጨነቁ ኣይገባም። ምንም እንኳ ሁኔታዎች አስቸጋሪዎች ሊሆኑና ሐዋርያት እንዴት መመለስ እንዳለባቸው ላያውቁ ቢችሉም፥ መንፈስ ቅዱስ የሚናገሯቸውን ቃላት ይሰጣቸዋል።

ለ. የሚያሳድዷቸውን ከመጥላት፥ ከመሸሽ ወይም ከመበቀል ይልቅ፥ ደቀ መዛሙርቱ እንደ እባብና ርግብ መሆን እንደሚገባቸው ገልጾላቸዋል። በአገልግሎት ንጹሕ ምክንያት ሊኖረንና እንደ ርግብ ቀናዎች ልንሆን ይገባል። ነገር ግን የሰዎችን ኃጢኣተኝነት ተገንዝበን እንደ እባብ ብልሆች ልንሆንም ይገባል፡

ሐ. የክርስቶስ ተከታዮች ከስደት ሳይሸሹ፥ ስደቱ ባለበት አካባቢ መቼ ሊቆዩና መቼ ከአካባቢው ገለል ሊሉ እንደሚገባቸው ማወቅ ኣለባቸው። እንድንቆይ እግዚአብሔር በግልጽ እስካልነገረን ድረስ፥ ለነፍሳችን ከሚያሰጋው የስደት አካባቢ ገለል ማለቱ ጥበብ እንጂ ፍርሃት አይደለም።

መ. ክርስቶስ ወንጌሉ ቤተሰቦችን ሳይቀር እንደሚከፋፈል አስጠንቅቋል። አንዳንዶች ክርስቶስን ለመከተል ሲፈልጉ፥ ሌሎች በከፍተኛ ደረጃ ይቃወማሉ። ይህ ሁኔታ ከሚያስከትላቸው ነገሮች አንዱ የወዳጆቻችንን ጥላቻ ማትረፍ ይሆናል። በቤተሰብ ውጥረት ሳቢያ ክርስቶስን አለመከተል ማለት ቤተሰቦቻችንን ከክርስቶስ በላይ መውደድ ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የደቀ መዝሙርነት መንገድ አይገባቸውም።

ሠ. ደቀ መዛሙርት ለመሆን የሚመርጡ ሰዎች በመጽናት ስለሚድኑ፥ ስደትን ችለው ማለፍ አለባቸው። የሚያድነን መጽናታችን ባይሆንም፥ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በመከራ ውስጥ ጸንተው እውነተኛነታቸውን ያረጋገጣሉ።

ረ. የስደት ጊዜ የተወሰነ ነው (ማቴ. 10፡23)። ክርስቶስ «የሰው ልጅ» እስኪመጣ ድረስ ወንጌሉን ወደ እስራኤል ወስደው እንደማይፈጽሙ ሲናገር ምን ማለቱ እንደሆነ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። አንዳንድ ምሑራን ክርስቶስ ይህን ሲል በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ መንደሮች ሁሉ ስለ ራሱ ከመስማታቸው በፊት በመስቀል ላይ እንደሚሞት መናገሩ እንደሆነ ያስባሉ። ሌሎች እስራኤል በ70 ዓ.ም. በሮም ሥር ስትወድቅ የሚደርስባትን ፍርድ እየተነበየ እንደሆነ ያስረዳሉ። ሌሎች ምሑራን ደግሞ ክርስቶስ ከሞት በተነሣ ጊዜ በድል እንደ «መጣ» ይናገራሉ። አንዳንዶች ይህ ከክርስቶስ ምድራዊ አገዛዝ በፊት የሚነሣውን ታላቅ መከራ እንደሚያመላክትና፥ የመከራ ጊዜው የተወሰነ በመሆኑ የአይሁድ መስካሪዎች ስለ ክርስቶስ ለአይሁዶች ሁሉ ከመናገራቸው በፊት እንደሚያበቃ ያስባሉ። ክርስቶስ ለአይሁዶች ስለሚሰጠው የወንጌል አገልግሎት እየተናገረ እንደሆነና ሥራው ከባድ በመሆኑ ምክንያት እስከ ዳግም ምጽአቱ እንደማይጠናቀቅ የሚያስረዱም አሉ። ለዚህ አስቸጋሪ ጥቅስ ግልጽ መልስ ማግኘት አልተቻለም።

ሰ ክርስቶስ መከራ የመቀበል ምሳሌ ነው። ስደትን በመቀበል ረገድ የጌታችንና የመምህራችንን ፈለግ መከተል አለብን። ክርስቶስ «ብዔልዜቡል» (ሌላው የሰይጣን ስም) እንደተባለ ሁሉ ተከታዮቹም በዚህ ዓይነት ቃላት ሊጠሩ እንደሚችሉ መጠበቅ አለባቸው።

ሸ. በስደት ጊዜ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ የሌለ ቢመስልም፥ ደቀ መዛሙርቱ ተቆጣጣሪነቱን ማወቅ አለባቸው። እግዚአብሔር በምሥጢር እንኳ እኛን በመቃወም የሚሰነዘሩትን ቃላት ሁሉ ያውቃል። በፍርድ ቀን ሰዎች ለተናገሯቸው ነገሮች በኃላፊነት ይጠየቃሉ። እግዚአብሔር በገበያ የሚሸጡትን ድንቢጦች ሁሉ እንደሚያውቅ፥ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ የሚሆነውን በበለጠ ያውቃል። እግዚአብሔር ሳያውቅ ከልጆቹ ፀጉር አንድ እንኳ አትነቀልም።

ቀ. የክርስቶስ ተከታዮች የደቀ መዝሙርነትን ዋጋ መተመን አለባቸው። ሁለት ዓይነት ሕይወት እንዳለ መገንዘብ አለብን። በምድር ጊዜያዊ ሕይወት፥ በሰማይ ደግሞ ዘላለማዊ ሕይወት አለ። በምድር ላይ፥ ሰዎች ሊያጠፉ የሚችሉት የሰውን ሥጋ ብቻ ነው። የሰውዬውን ነፍስ ሊነኩ አይችሉም። ሞትም ቢሆን የክርቶስን ደቀ መዝሙር ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያሸጋግር በመሆኑ፥ ጎጂ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ነፍስን መግደል ይችላል። ሰዎች ሊፈሩት የሚገባቸው ይህንኑ ሞት ነው። የሥጋ ሞት ፍርሃት አንድ ሰው ክርስቶስን እንዲክድ ቢያደርግ፥ ያ ሰው የዘላለምን ሕይወት ያጣል። በእምነታችን መጽናትና በስደት ጊዜ ክርስቶስን አለመካድ በዘላለሙ መንግሥት ክርስቶስ በይፋ የእርሱ መሆናችንን እንዲያውጅ ያደርገዋል። ነገር ግን እምነታችንን ከካድን፥ ክርስቶስ በፍርድ ቀን ደቀ መዛሙርቱ መሆናችንን ይክዳል። የመስቀሉ መስመር የሆነውን ስደት ብንክድ፥ የዘላለምን ፍርድ እንቀበላለን።

ሲ. በስደት ጊዜ አማኝ ወዳጆቻችንን መደገፍ አለብን። የክርስቶስ ተከታዮችን በመደገፍ ለክርስቶስ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። እምነታችንን ደብቀን ከክርስቲያኖች ጋር ላለመተባበር ብንሞክር፥ ክርስቶስን ከድተናል ማለት ነው። ነገር ግን መከራ ከሚቀበሉት ክርስቲያኖች ጋር ብንተባበር ወይም ሌሎች የተሰደዱ ክርስቲያኖችን ወደ ቤታችን ብናስገባ፥ እግዚአብሔር አብንና ክርስቶስን ወደ ቤታችን እንደተቀበልን ያህል ይቆጠራል። ስደት ሊያስከትልብን ቢችልም እንኳ ከ«ነቢያት» (ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወይም ሠራተኞች የተሰጠ ሌላው ስም) ጋር በመተባበር ብንረዳቸው፥ ነቢያቱ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የሚቀበሉትን ሽልማት እንጋራለን። እርዳታው ለሌላው ክርስቲያን ቀዝቃዛ ውኃ የመስጠትን ያህል ያነሰ ቢሆንም እንኳ፥ እግዚኣብሔር ያከብረዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ያጋጠመህን ስደት ግለጽ። ለ) ሁሉም ክርስቲያኖች ስደት የክርስቶስ ተከታይ የመሆን አካል መሆኑን አስቀድመው መገንዘብ የሚገባቸው ለምንድን ነው? ሐ) ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያንህ ምእመናን ሊማሩት የሚገባ ምን ጠቃሚ የስደት ትምህርት አስተማረ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: