ማቴዎስ 11፡1-30

  1. መጥምቁ ዮሐንስ ክርስቶስ መሢሕ ስለመሆኑ ጠየቀ (ማቴ. 11፡1-19)

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ እምነትህ የተጠራጠርህበትን ጊዜ ግለጽ። የተጠራጠርኸው ምን ነበር? በክርስቶስ ላይ ያለህን እምነት መልሰህ እንድትቀዳጅ የረዳህ ምን ነበር?

በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ሁሉም ክርስቲያኖች ጥርጣሬዎች ይኖሯቸዋል። ለጸሎትህ መልስ ስትጠብቅ አይመጣም። ደግሞም እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ይሠራል ብለህ የማታስበው አንድ ነገር ይከሰታል። የመኪና አደጋ ደርሶ ለኣገልግሎት የወጣ ጠንካራ ክርስቲያን ወንድም ሽባ ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ጊዜያት እግዚአብሔርን ልንጠራጠር እንችላለን።

መጥምቁ ዮሐንስ ለተወሰነ ጊዜ ታስሮ ቆይቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ቢገልጹለትም፥ ለዮሐንስ ስሜት አልሰጠውም። የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና የእሳት ፍርድ የታሉ? ክርስቶስ ክፉዎችን አጥፍቶ የጽድቅ መንግሥቱን የሚጀምረው መቼ ነው? ክርስቶስ የመጣው እርሱ ከጠበቀው መንገድ ሙሉ በሙሉ በተለየ ሁኔታ በመሆኑ፥ ዮሐንስ ግራ ተጋባ። እግዚአብሔር የክርስቶስን መሢሕነት ለእርሱ መግለጹ ስሕተት ይሆን?

ስለሆነም፥ ዮሐንስ የክርስቶስን መሢሕነት ወይም ሌላ መጠበቅ እንዳለባቸው ለማረጋጥ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ክርስቶስ ላከ። ክርስቶስ ወደ ተአምራቱ በማመልከት፥ «እግዚአብሔር በእኔ በኩል ያደረገውን ሄዳችሁ ንገሩት። እነዚህ ለመሢሕነቴ በቂ ማረጋገጫዎች ናቸው። አትጠራጠር በሉት» አላቸው። ማቴዎስ ተመሳሳይ ጥርጣሬ ለነበራቸው አይሁዶችም ይህንኑ ምላሽ ሰጥቷቸዋል። አይሁዶች መሢሕ ድልነሺ ንጉሥ እንደሚሆን ጠብቀው ነበር። ማቴዎስ በመጽሐፉ «ክርስቶስ ያደረጋቸውን ተአምራት ተመልከቱ። እነዚህን ተአምራት እንዳደረገ ታውቃላችሁ። እነርሱም የመሢሕነቱ ማረጋገጫዎች ናቸው። ሌላ ሰው አትፈልጉ።» ሲል አስረድቷል። ለጥርጣሬዎች ምላሽ ለመስጠት የእግዚአብሔርን ቃል እውነት እንጠቀማለን። ክርስቶስም የመጥምቁ ዮሐንስን ዓይኖች ለእግዚአብሔር እውነቶች አብርቷል።

ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስና ከመጭው እግዚአብሔር መንግሥት ጋር ስላለው ግንኙነት አስተምሯል። ባማረ ልብስ ባያጌጥና ተአምራት ባይሠራም፥ ዮሐንስ ለመሢሑ መንገድ እንዲጠርግ የተላከ ክቡር ነቢይ ነበር። ስለሆነም፥ ዮሐንስ ታላቅ አገልጋይ ነበር። ከዚያ በኋላ ክርስቶስ ለመረዳት የሚያስቸግር አሳብ ሰንዝሯል። ዮሐንስ ታላቅ ቢሆንም፥ በመንግሥተ ሰማይ እጅግ አነስተኛ ሰው ይበልጠዋል። ክርስቶስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? በክርስቶስ መምጣት አዲስ የዘመን ምዕራፍ ተከፍቷል። የብሉይ ኪዳን ዘመን አብቅቶ የአዲስ ኪዳን ዘመን እየተጀመረ ነበር። ዮሐንስ ታላቅ ነቢይ ቢሆንም፥ የብሉይ ኪዳን ዘመን አካል ነበር። መሢሑን ለዓለም የማስተዋወቅን ልዩ ዕድል ስላገኘ፥ የአሮጌው ዘመን ታላቅ ነቢይ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ለማየት አልታደለም ነበር። የቤተ ክርስቲያን አባል አልሆነም ነበር። አዲሱ ዘመን ከብሉይ ኪዳን ዘመን ስለሚልቅ፥ የአዲሱ ዘመን ተራ አባል ከአሮጌው ዘመን ታላቅ ሰው ይበልጣል።

ክርስቶስ በተጨማሪም፥ «ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል» ብሏል። ይህም ለመረዳት የሚያስቸግር አሳብ ነው። አንዳንድ ምሑራን ከማቴዎስ 10 ዐውድ በመረዳት፥ ስደትን እንደሚያመለክት ይገልጻሉ። በአንድ በኩል፥ የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋፋት ጠላትን እያሸነፈ ነበር። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን እንደሚመሠርትና የገሃነም ደጆች እንደማይቋቋሟት ገልጾአል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ፥ ይህ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ቆይቷል። በተመሳሳይ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት መስፋፋት የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ። ስደት የቤተ ክርስቲያን ያማያቋርጥ ሂደት ነው። መጥምቁ ዮሐንስ የታሰረ ሲሆን፥ ክርስቶስ ደግሞ ተሰቅሏል። በታሪክ ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያን ስደትን ስትጋፈጥ ቆይታለች። መጥምቁ ዮሐንስንና አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት ከመቅጽበት መጥቶ አሕዛብን ወይም የክፋት ኃይሎችን ሁሉ እንደማያስወግድ መገንዘብ ነበረባቸው። የእግዚአብሔር መንግሥት ቀስ በቀስ እያደገ ሲሄድ፥ የክፉ ሰዎች ተቃውሞ አይለየውም።

ምሑራን የክርስቶስን አሳብ የሚረዱበት ሌላው መንገድ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል ለመሆን ጥረትን እንደሚጠይቅ ነው። አንድ ሰው የክርስቶስ ተከታይ ሆኖ ካለመወለዱም በላይ፥ ምርጫውም ቀላል አይደለም። የመንግሥቱ አካል መሆንን፥ አንድ ሰው ከምንም ነገር በላይ ሊሻው ይገባል። ሁልጊዜም ስደት ስለሚኖር፥ ብርታት፥ ኃይልና ቁርጥ ውሳኔ ኣስፈላጊዎች ይሆናሉ።

ከዚያም ክርስቶስ አይሁዶች የእግዚአብሔርን አሠራር ለመገንዘብ ባለመቻላቸውና በሌሎች ላይ በመፍረዳቸው ገሥጾአቸዋል። መጥምቁ ዮሐንስ ቆዳ ለብሶ ጠንካራ የፍርድ መልእክት እየሰበከ ሲመጣ፥ ወግ አጥባቂ ነው አሉት። ይህም በጋኔን ቁጥጥር እንደሚሠራ የመግለጽ ያህል ነበር። ክርስቶስ ደግሞ ከሰዎች ጋር በመብላትና በመጠጣት የቅርብ ወዳጃቸው ሆነ። ከኃጢአተኞች ጋር ወዳጅነትን በመመሥረቱ፥ ብዙውን ጊዜ ይጋብዙት ነበር። ኣይሁዶች ግን ይህን ባሕርዩን በመጥላት ቀለል ያለ በላተኛና ጠጪ እንደሆነ ተናገሩ። በቂ መንፈሳዊነት እንደሌለውና የቀራጮችና ኃጢአተኞች ወዳጅ በመሆን የተሳሳተ ዝምድና እንዳፈራ ገለጹ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ከሴተኛ አዳሪዎች፥ ከጎዳና ተዳዳሪዎችና ዱርዬዎች ጋር ወዳጅነትን እየጠበቀ በቤተ ክርስቲያንህ ቢያገለግል፥ ምን ዓይነት ስም የሚሰጠው ይመስልሃል? በሽማግሌዎች የሚወደድ ይመስልሃል? ለምን? ለ) ክርስቶስ በዚህ ተግባሩ የማይወደድ ከሆነ፥ ይህ ክርስቶስን መምሰልን አስመልክቶ የተሳሳተ አመለካከት መያዛችንን የሚያሳየው እንዴት ነው?

  1. ክርስቶስ ሰዎች ንስሐ ባልገቡባቸው ከተሞች ላይ ፍርድን ማወጁ እና ለሚያምኑበት ዕረፍትን እንደሚሰጣቸው መግለጡ (ማቴ. 11፡20-30)  

ብዙ ከተሰጠው ብዙ እንደሚጠበቅ የሚያመለክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሕ አለ (ሉቃስ 12፡48)። ይህም ገንዘብ፥ ምህርት፥ የክርስቶስ እውቀትና መንፈሳዊ ስጦታ ላላቸው የሚሠራ ነው። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ይህን ስጦታ የሰጠን ለክብሩ እንደምንጠቀምበት በመገንዘብ ሲሆን፥ እንዴት እንደተጠቀምንበት ይጠይቀናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እንደ በረከት የሰጠህን አንዳንድ ነገሮች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ነገሮች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምትጠቀምባቸው እንዴት ነው?

የኮራዚንና የቤተሳይዳ ከተሞች፥ ክርስቶስ አብዛኞቹን ታምራት ባደረገበት በገሊላ ውስጥ የሚገኙ ስፍራዎች ነበሩ። በዚያ ዘመን እነዚህ ከተሞች ከሌሎች ከተሞች ሁሉ በላይ ተባርከው እንደነበር ታሪካቸው ይመሰክራል። ክርስቶስን በሥጋ ማየታቸውና ታምራቱን መመልከታቸው ኀላፊነትን የሚያስከትል በረከት ነው። ክርስቶስ ተአምራቱን እየተመለከቱ ያላመኑበት ሰዎች በመሢሕነቱ ሊያምኑ እንደሚገባቸው አስጠንቅቋቸዋል። ክርስቶስ ሊዶናና ጢሮስ የተባሉት የአሕዛብ ከተሞች እነዚህን ተአምራት ቢመለከቱ ኖሮ፥ በእርሱ ያምኑ እንደነበር ተናግሯልና። ነገር ግን አይሁዶች እርሱን ባለመቀበላቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ካላዩት ሰዎች ይልቅ ጥፋተኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። ሰዶምና ገሞራ የኣይሁዶችን ያህል ግልጽ ምስክርነት አላገኙም ነበር። ስለሆነም በአይሁዶች ላይ ፍርድ ይሰጣል። በ70 ዓ.ም. ብዙ ከተሞቿ በመደምሰሳቸው ገሊላ ፍርዱን የተቀበለች ስትሆን፥ ሌሎች ኣይሁዶች በመጨረሻው ዘመን ፍርድን ያገኛሉ።

ማቴዎስ ስዚህ መልእክቱ በዘመኑ የነበሩትን አይሁዶችና በየትኛውም ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች እያስጠነቀቀ ነበር። ወንጌሉ ተጨማሪ ተጠያቂነትን ያስከትላል። ወንጌሉን ከሰሙና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከተመለከቱ በኋላ፥ በክርስቶስ ለማመን የማይፈልጉ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ሰምቶ ከማያውቅ ሰው የከፋ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

  1. ክርስቶስ ለሚያምኑበት ዕረፍትን እንደሚሰጣቸው ቃል ገባ (ማቴ. 11፡25-30)

ወንጌሉ ሁልጊዜም የሚያምኑትን ሰዎች ከማያምኑት ይለያል። ክርስቶስ ኣብዛኛው ሰው በእርሱ ባለማመኑ ተስፋ ሳይቆርጥ፥ በዘመናት ሁሉ እውነት የሆነውን ምሥጢር ለመመልከት ችሏል። በአጠቃላይ፥ እንደ ፈሪሳውያንና የዩኒቨርስቲ መምህራን ምድራዊ ዕውቀት የነበራቸው ሰዎች ወንጌሉን ከሞኝነት ስለ ቆጠሩት ወንጌሉን አልተቀበሉም ነበር። እንደ ሊቀ ካህናትና የሮም ገዥዎች ያሉት ሀብታሞችና ባለሥልጣናትም ልባቸውን በሌሎች ነገሮች ስላጣበቡ፥ ወንጌሉን ለመቀበል አልፈለጉም። ዓለም የናቃቸው ድሆች ግን በክርስቶስ አመኑ። አብዛኞቹ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ኣባላት፥ ባሮችና ድሆች የነበሩ ሲሆን፥ ይኸው ሁኔታ በታሪክ ሂደት ውስጥ ሁሉ ቀጥሏል።

የውይይ ጥያቄ፡- ሀ) 1ኛ ቆሮ. 1፡18–31 አንብብ። ጳውሎስ ይህን የወንጌል ምሥጢር ያብራራው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ጠቢባንን፥ ሀብታሞችንና ኃይለኞችን ለመማረክ እየሞከርንና ድሆችንና የተናቁትን እየተውን ይህንን ምሥጢር ችላ የምንለው እንዴት ነው?

ክርስቶስ ሊከተሉት የሚፈልጉት ተራ ሰዎች መሆናቸውን በመገንዘቡ፥ እግዚኣብሔርን ለሚሠራበት መንገድ አመሰገነው። ክርስቶስ፣ ደኅንነት የሰው ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ገልጾአል። እግዚአብሔር የመንግሥቱን ምሥጢራት ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቷል። ክርስቶስም የወንጌሉን ምሥጢራት ገልጾ ለመረጣቸው ሰዎች ሰጥቷል። ይህ በሲኖፕቲክ ወንጌላት ውስጥ ከቀረቡት የክርስቶስን አምላክነት ከሚያስረዱትና ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለውን ልዩ ግንኙነት ከሚያሳዩት ግልጽ መግለጫዎች አንዱ ነው።

ክርስቶስ አንድ ሰው እርሱን ለመከተልና ለመዳን የሚያጋጥመውን ስደት ከገለጸ በኋላ፥ አሁን ደግሞ ሌላኛውን የወንጌሉን ምሥጢር ገጽታ ያሳያል። ክርስቶስ፥ የሕይወት ውጥረትና ሸክም ያደከማቸው ሰዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ ጋብዟል። ፈሪሳውያንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ብዙ ሕጎቻቸውን በሰዎች ላይ ሲጭኑ፥ ክርስቶስ ከባድ ነገር እንደማይጠይቃቸው ተናግሯል። የምንፈልገውን አግኝተን ውስጣዊ ሰላም የምናገኘው በክርስቶስ ብቻ ነው።

ነገር ግን ሌሎች ሰዎች የደቀ መዝሙርነትን መንገድ ይከተሉ ዘንድ፥ ሕይወታችን ከክርስቶስ ጋር እንዲጣመር (ልክ ሁለት በሬዎች በአንድ ቀንበር እንደሚጣመሩ) ልናደርግ ይገባል። ልባችንንና ሕይወታችንን ከክርስቶስ ፈቃድ ጋር ማስማማት አለብን። ከክርስቶስ ጋር ለመሥራት መትጋት አለብን። ከክርስቶስ ጋር በምንሠራበት ጊዜ ውጫዊ ውጥረቶች ቢኖሩብንም፥ ቀንበሩና ሸክሙ ቀላል ይሆንልናል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ የሆነው በርግጥ ሸክሙና ቀንበሩ ቀላል ስለሆነ አይደለም። ብዙውን ጊዜ የክርስቲያን ሕይወት ከዓለማዊው በላይ ከባድ ነው። ነገር ግን ትልቅ በሬ ከትንሽ ለማጅ ወይፈን ጋር እንደሚጠመድ ሁሉ፥ አብዛኛውን ተግባር የሚያከናውነው ክርስቶስ ነው።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ክርስቶስ በኣንድ ስፍራ ብቻ ራሱንና ማንነቱን መግለጹ አስገራሚ ነው። ክርስቶስ ጨካኝ ሳይሆን፥ ለሰዎች ነፍስና ፍላጎቶች የሚራራ የዋህ መሪ መሆኑን ተናግሯል። እንዲሁም፥ ለራሱ ክብር ሳይሆን ለእግዚአብሔርና ከእርሱ ጋር ለመጣመር ለሚፈልጉ ወገኖች ጥቅም ለመሥራት የሚፈልግ ትሑት መሆኑን አስረድቷል።

ስለሆነም፥ የክርስትና ሕይወት ከባድ ብቻ ሳይሆን የማይቻልም ነው። ነገር ግን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ፍላጎቶቻችንን መግታት እንዳለብን ክርስቶስ ያስተምረናል። ሁልጊዜም በሚዝለው የራሳችን ጉልበት ከመሥራት ይልቅ፥ ፈቃዳችንን ለእርሱ በማስገዛት ከእርሱ ጋር መጣመር አለብን። በዚህ ጊዜ ከመቅጽበት አስቸጋሪ ያልሆነ መንገድ እናገኛለን። የዋህና አፍቃሪያችን የሆነው ክርስቶስ በጭካኔና በትዕቢት አይገዛንም ይልቁንም፥ እርሱ ከእኛ ጋር አማኑኤል ነው!

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች እንዲታገሉና ከባድ ጭነት እንዲሸከሙ የሚያደርጉ ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) ብዙውን ጊዜ በልባቸው ውስጥ ተቀምጦ እንዲታገሉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ሐ) ሸክማቸውን አራግፈው የልብ ሰላም እንዲያገኙ የሚረዳቸው ምንድን ነው? መ) ልብህን ለመመርመር ጊዜ ውሰድ። በእንድ ነገር ላይ እየታገልህ ከሆነ፥ ራስህን ለክርስቶስ ስጥና ቀንበሩን ተሸከም።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

1 thought on “ማቴዎስ 11፡1-30”

Leave a Reply

%d bloggers like this: