ክርስቶስ በምሳሌዎች አማካኝነት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማረ (ማቴዎስ 13:1-58)

ክርስቶስ ካስተማረባቸው ዘዴዎች አንዱ በምሳሌዎች መጠቀም ነበር። (አንዳንድ ምሑራን ከ60 በላይ ምሳሌዎች ወይም ምሳሌ መሰል አባባሎች እንዳሉ ይናገራሉ። ይህም ከክርስቶስ ጠቅላላ ትምህርት ሲሶው ያህል ነው።) ምሳሌዎችን በትክክል ለመተርጎም ይቻለን ዘንድ፥ የምሳሌዎችን ምንነትና እንዴት ልንረዳቸው እንደሚገባን ማወቅ አለብን። ምሳሌዎች ስውር መልእክት የሚያስተላልፉ እንቆቅልሾች (allegories) አይደሉም። እያንዳንዱ የታሪኩ ዝርዝር መንፈሳዊ ትርጉም እንዲሰጥ ሆኖ የተዘጋጀ ልብወለዳዊ ታሪክም አይደለም። ነገር ግን ምሳሌዎች አንድ ዐቢይ መንፈሳዊ እውነት ለማብራራት የሚቀርቡ ቀላል ታሪኮች ናቸው። ክርስቶስ አንዳንድ ምሳሌዎችን የተረጎመ ቢሆንም፡ አብዛኞቹ ምሳሌዎቹ አልተተረጎሙም። ስለሆነም፥ ምሳሌዎችን በምንተረጉምበት ጊዜ፥ የሚከተሉትን የትርጉም ሂደቶች መከተል አለብን፡፡

ሀ. ጠቅላላውን ታሪክ ክርስቶስ ምሳሌውን ከተናገረው የአይሁድ ባሕል አንጻር መረዳት አለብን።

ለ. ከዚያም፥ «በዚህ ታሪክ እየተብራራ ያለው ዐቢይ መንፈሳዊ እውነት ምንድን ነው?» ብለን መጠየቅ ኣለብን።

ሐ. በመጨረሻም፥ «ይህ መንፈሳዊ እውነት ዛሬ ከእኛ ሕይወት ጋር እንዴት ይዛመዳል?» ብለን እንጠይቃለን።

ክርስቶስ በተአምራት አማካኝነት በማስተማር ሁለት ነገሮችን አከናውኗል። በመጀመሪያ፥ ለምትህርቱ ልባቸውን ለከፈቱት ሰዎች፥ እነዚህ ምሳሌዎች ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማብራራት እንደ መልካም የማስተማሪያ መሣሪያዎች አገልግለዋል። ክርስቶስ ብዙ ሰዎች ንድፈ አሳባዊ እውነቶችን ለመረዳትና ከሕይወታቸው ጋር ለማዛመድ እንደሚቸገሩ ስለሚያውቅ፥ መንፈሳዊ እውነቶችን ለማብራራት በእነዚህ ምሳሌዎች ተጠቅሟል። ሁለተኛ፡ ለመንፈሳዊ እውነቶች ልባቸውን ላልከፈቱ ሰዎች፥ እነዚህ ምሳሌዎች የወንጌሉን እውነት ስለሚደብቁ የእግዚአብሔርን ፍርድ ያመለክታሉ።

ማቴዎስ ከክርስቶስ ምሳሌዎች ብዙዎችን ሰብስቦ በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ያሰፈረ ይመስላል። ክርስቶስ የጀመረውን የመንግሥተ ሰማይ ምሥጢራት የሚያብራሩ ሰባት ምሳሌዎች ቀርበዋል።

ሀ. የአራት ዓይነት መሬቶች ምሳሌ (ማቴ. 3፡1-23)። ክርስቶስ የመጣው ወንጌልን እየሰበከ ነበር። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱና እኛም መልካሙን የምሥራች ወደ ሰዎች ሁሉ እንድናደርስ አዝዞናል። ነገር ግን ሰዎች ለምስክርነታችን የምንፈልገውን ዓይነት ምላሽ በማይሰጡበት ጊዜ፥ እንዳንደነቅ ወይም ተስፋ እንዳንቆርጥ፥ ክርስቶስ አራት የተለያዩ ነገሮች ስላጋጠሙት ስለ ግብርና የሚያስረዳ ምሳሌ ተናግሯል።

 1. አንዳንድ ዘሮች በፍጹም አይጎነቁሉም። ይህ ወንጌሉን ከሰሙ በኋላ ለማመን ከመወሰናቸው በፊት፥ ሰይጣን ዘሩን በመውሰዱ ምክንያት ምላሽ ከመስጠት የሚታቀቡትን ሰዎች የሚያመላክት ነው።
 2. ሌሎች ዘሮች በድንጋያማ መሬት ላይ ይወድቃሉ። እነዚህ ሰዎች ወንጌሉን ሰምተው ማመናችውን ይናገራሉ። ነገር ግን ያልተጠበቁ ነገሮች፣ ችግሮች ወይም ስደት ስለሚደርስባቸው፥ ለወንጌሉ ጀርባቸውን ሰጥተው ወደ ዓለም ይመለሳሉ።
 3. በአረሞች መካከል የሚወድቁ ዘሮች ይታነቃሉ። እነዚህ ወንጌሉን ሰምተው በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ናቸው። ነገር ገን የዓለም ነገሮች (ገንዘብ፥ ሥራ፥ ትምህርት፥ ቤተሰብ፥ ወዘተ…) እምነታቸውን አንቆ ስለሚገድልና ወደ ዓለም እንዲመለሱ ስለሚያደርግ፥ ልባቸው የተከፋፈለ ይሆናል።
 4. አንዳንድ ዘሮች በመልካም መሬት ላይ ይወድቃሉ። እነዚህ ወንጌሉን ሰምተው በሚያምኑትና እምነታቸውም በመንፈሳዊ ፍሬዎች የሚታዩ ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ አራት ምላሾች ለወንጌሉ ሲሰጡ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ።

ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ በማቴ. 5-7 ካቀረባቸው ዓይነት ግልጽ ስብከቶች፥ ስውር ትርጉም ወዳላቸው ምሳሌዎች በመዛወር፥ የማስተማር ዘዴ መቀየሩን ተመልክተዋል። ምክንያቱን በጠየቁት ጊዜ፥ እንደ ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት የመማር ዕድል እንደነበራቸው ገልጾአል። በክርቶስ ማመናቸውን ስላሳዩ፥ የበለጠ እውነት ጨምሮላቸዋል። ነገር ግን ሌሎች፥ በተለይም የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን የመቃወም አቋም ስለወሰዱ፥ የመገንዘብ ዕድል አልነበራቸውም። ተቃውሟቸው ድንገተኛ ክስተት አልነበረም። በኢሳይያስ ዘመን ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቶስም ዘመን የሚኖሩትን ሰዎች የገለጸውን የኢሳይያስ 6፡9-10 ትንቢት ፈጽሟል። ደቀ መዛሙርቱ ዕድለኞች ነበሩ። ምንም እንኳ የብሉይ ኪዳን ነቢያት የክርስቶስን መምጣት ሲናፍቁም፥ እርሱንም ሆነ የትንቢታቸውን ፍጻሜ ለመመልከት አልታደሉም ነበር።

ለ. የአረሞች ምሳሌ ማቴ. 13፡24-30)። አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት፥ ጠላቶቻቸውን እንደሚያወድምና በክፉዎች ላይ እንደሚፈርድ አስበው ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን መንግሥቱ የዚያን ዓይነት መንገድ እንደማይከተል ገልጾላቸዋል። የመንግሥቱን ዘገምተኛ ዕድገት ከሁለት ሰዎች ጋር አነጻጸረ። ገበሬው ስንዴ ሲዘራ ጠላቱ ከስንዴው ጋር የሚመሳሰል እንክርዳድ ጨመረበት። ሠራተኞቹ እንክርዳዱን ለመንቀል ሲፈልጉ፥ ገበሬው ስንዴውና እንክርዳዱ አድገው በቀላሉ እስከሚለዩበት ጊዜ ድረስ እንዲታገሡ ነገራቸው።

ክርስቶስ የምሳሌዎቹን ትርጉም በማቴ. 3፡36-43 ኣብራርቷል። ገበሬው ክርስቶስ፣ እርሻው ዓለም፥ ስንዴው እማኛችን ይወክላሉ። ጠላት የተባለው ሰይጣን ሲሆን፥ አረሞቹ የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ የሰይጣን «ልጆች። ናቸው። ክርስቶስ መንግሥቱ ቀስ እያለች ስታድግ በክርስቶስና በሰይጣን መንግሥታት መካከል የማያቋርጥ ትግል እንደሚካሄድ አስረድቷል። ከዚህ ትግል ውስጥ የተወሰነው በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚካሄድ የተሰወረ ይሆናል። ለዚህም ምክንያቱ የሰይጣንና የክርስቶስ መንግሥት ተከታዮች መኖራቸው ነው። ማን እውነተኛ፡ ማን ደግሞ ሐሰተኛ አማኝ እንደሆነ ለመረዳት ያስቸግራል። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች፥ ክርስቲያኖች እንዳልሆኑት፥ ክርስቲያኖች ያልሆኑት ደግሞ እንደ ክርስቲያኖች ሊመላለሱ ይችላሉ። የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ያልሆኑ ሰዎች፥ ክርስቶስን «ጌታ ሆይ» ብለው ሊጠሩትና ተአምራትን ሳይቀር ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ቀደም ብለን ተመልክተናል። እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሐሰተኞቹ መለየት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ኃላፊነት አይደለም። የመጨረሻው ዘመን በመጣበት ጊዜ ክርስቲያኖች ባልሆኑት ላይ ፍርድ ይሰጣል። በዚያን ጊዜ በስንዴ ተምሳሌትነት የተገለጹት የእግዚአብሔር ልጆች በከፍተኛ ደረጃ ይባረካሉ። ንጹሕ ቤተ ክርስቲያን ብንሻም፣ ይህ በዘመናችን የሚሳካ አይሆንም። ሁልጊዜም ክርስቲያኖች ነን ብለው የሚገበዙና የሐሰት አስተማሪዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይኖራሉ። ስለዚህ ከስንዴው ወገን ነን ወይስ ከእንክርዳዱ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ይህን እሳት በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ያየኽው እንዴት ነው?

ሐ. የሰናፍጭ ንጣትና ያእርሾ ምሳሌዎች (ማቴ 13፡31-35)። ክርስቶስ መንግሥቱ ከትንሽ ብትጀምርም እንኳ እያደገች በመሄድ ታላቅ እንደምትሆን ተናግሯል። ክርስቶስ ተመሳሳይ ፍች ያላቸውን ሁለት ምሳሌዎች ተናገረ፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት በአይሁዶች ዘንድ ከታወቁ ትናንሽ የተክል ዘርች አንዱ ነው፡ ነገር ግን ይህ አነስተኛ ዘር በከፍተኛ ደረጃ በማደግ የወፎች መኖሪያ እስከ መሆን ድረስ ይደርሳል፡፡ ብዙ ሑራን ይህ የወፎች ማረፊያነት ምሳሌ፥ ከዳን. 4፡20-21 እንደ መጣ ያስባሉ። ይህ ምሳሌ የክርስቶስ መንግሥት በ12 ደቀ መዛሙርት አማካኝነት በአነስተኛ ደረጃ እንደሚጀምር ያሳያል፡ ነገር ግን በምድር ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማኞች እስኪኖሩት ድረስ ማደጉን ይቀጥላል። መንግሥቱ ከፍጻሜ በሚደርስበት ጊዜ፥ ክርስቶስ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ልብ ውስጥ ይገዛል። ይኽው መንግሥት ክርስቶስ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ እስከሚቆጣጠርበት ጊዜ ድረስ ማደጉን ይቀጥላል።

እርሾም በጣም አነስተኛ ነገር ነው። ነገር ቀን ትንሽ እርሾ ብዙ ሊጥ ሊያቦካ ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እርሾን የጥፋት ተምሳሌት አድርጎ ይጠቀማል ማቴ 16፡6፤ 1ኛ ቆሮ. 5፡6-8)። እዚህ ላይ ግን እንደ ስናፍጭ ቅንጣት ሁሉ እርሾ የክርስቶስን መንግሥት መስፋፋት ያመለክታል፡፡ ከአይሁድ ሕዝብ ወይም ከርመ ሠራዊት ሲነጻጸሩ፥ ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ከቁም ነገር የማይቆጠሩ ሊመስሉ ቢችሉም፣ ከጊዜ በኋላ በአለም ሁሉ ይስፋፋሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- የእግዚአብሔር መንግሥት (ቤተ ክርስቲያንን ከአነስተኛ ጀምሮ ወደ ታነት ሊያድ የተመለከትንው እንዴት ነው?

መ. የተሰወረች መዝገብና የዕንቁ ምሳሌዎች (ማቴ 13፡44-46)። የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ ያመጣል? አንድ ሰው ይህን መንግሥት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርበታል? የእግዚአብሔር መንግሥት ለሰው ሕይወት እጅ አስፈላጊ መሆኑንና ይህን መንግሥት ለማግኘት ሌሎች ሀብቶቻችንን መተው እንዳለብን ለማሳየት፥ ክርስቶስ እነዚህን ሁለት ምሳሌዎች ተናግሯል። አንድ ሰው ብዙ ሀብት ያለውን መሬት ለመግዛት ንብረቱን ሁሉ መሸጥ ነበረበት። እንዲሁም አንድ ነጋዴ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ዕንቁ ለመግዛት ትናንሽ ጌጣጌጦቹን ሁሉ ሸጠ። በዚህ መሠረት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት አባል ለመሆንና እጅግ የላቀ በረከት ለመቋደስ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ፥ የሚወዷቸውን ሌሎች ነገሮች ትተው መንግሥቱን መሻት ይኖርባቸዋል። የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማግኘት፥ እያንዳንዳችን ራሳችንን የሰጠን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ሰዎች የሚወዷቸውን ነገሮች መተው እንዳለባቸው ሳያስቡ ክርስቲያኖች ይሆናሉ። እነዚህ ምሳሌዎች ስለ እነዚህ ሰዎች ምን ያስተምራሉ? ለ) ዛሬ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ዘላለማዊ መንግሥት ለማግኘት ከልባቸው ከፈለጉ ሊተዉአቸው የሚገቧቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ሠ. የመረብና ዓሣ ምሳሌ (ማቴ. 13፡47-50)። የስንዴና እንክርዳድ ምሳሌ፥ የክርስቶስን መንግሥት ዕድገት ረዥም ሂደትና እስከ መጨረሻው ዘመን ድረስ ክርስቲያኖችና ዓለማውያን ጎን ለጎን እንደሚጓዙ ሲያመለክት፥ ይህ ምሳሌ መጭውን ፍርድ ያሳያል። ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹ ዓሣ አጥማጆች ስለነበሩ፥ ክርስቶስ ይህንን ሙያ በምሳሌነት ተጠቅሟል። ዓሣ አጥማጆቹ ከሚጠቀሙባቸው መረቦች አንዱ በሁለት ጀልባዎች መካከል የሚታሰር ነበር። ዓሣ አጥማጆቹ በጀልባዎች እየተጓዙ መረቦቹን በመጎተት ዓሣዎችን ይይዙ ነበር። ነገር ግን ከእነዚህ ዓሣዎች ለመብል የሚያገለግለው ጥቂቱ ብቻ ነበር። ስለሆነም፥ በመረብ ተይዞ የተሰበሰበው አሣ ተለይቶ መጥፎው ሲጣልና ጥሩው ሊቀመጥ ያሻል። ክርስቶስ በመጨረሻው ዘመን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደሚመጣ ገልጾአል፡፡ የክርስቶስ መንግሥት የሰዎችን ልብ ሁሉ ሊማርክ አይችልም፡፡ ሊያድግና ሊስፋፋ ቢችልም፣ ሁሉንም ሰው አያሸንፍም። ስለሆነም፥ የክርስቶስ መንግሥት መምጣቱ ሲቃረብ፣ መልካም ከክፉ ይለያል፡፡ ስለሆነም፣ መልካሞቹ ዓሦች (የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት) ከመጥፎዎቹ ዓሦች (የክርስቶስ ተከታዮች ካልሆኑት) ይለያሉ።

ክርስቶስ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ያምፁበት ከነበሩ ሰዎች አልሸሸገም፡፡ በብዙ አገሮች ሰዎች ካላመኑ ወደ ሲዖል እንደሚገቡ አለማስጠንቀቅ የተለመደ ነው፡፡ ይህ ትዕቢት ወይም ፈራጅነት እንደሆነ ያስባሉ። ሙስሊም፥ ሂንዱ ወይም አረማዊ ወደ ሲዖል እንደሚሄድ እንዴት ልነግረው እችላለሁ? ይህን ለማለት ምን መብት አለኝ? ይላሉ። ክርስቶስ ግን ለሰዎች የምርጫቸው ውጤት ምን እንደሚሆን ከማሳሰብ አልቦዘነም። ይህን ማላመም ፈራጅነት አይደለም፡፡ ሰዎች በክርስቶስ ካላመኑ ወደ ሲዖል እንደሚሄዱ በማስጠንቀቅ ለእነርሱ ያለንን ርኅራኄ እናሳያለን ይህ ካልሆነ፥ እንድ ሰው ወደማይታየው ጉድጓድ አቅጣዋ ሲሄድ፥ እያዩ ሳያስጠነቅቁት መተዉ ይሆናል።

ብዙውን ጊዜ ክርስቶስ ስለ ሲዖል በሚናገርበት ጊዜ እጅግ አስፈሪ በሆኑ አገላለጾች ይጠቀማል። ሲዖል የለቅሶ፥ የጥርስ ማፋጨት፥ የጥልቅ ኃዘን፥ የጸጸትና ሥቃይ ስፍራ እንደሆነ ተናግሯል። በሌሎች ጊዜያት ሲኦልን ትሎች የሰውን ሥጋ ከሚበሉበት ስፍራ ጋር አነጻጽሯል። ይህም የማያቋርጥ ስራና ውድመት የሚኖርበት ስፍራ እንደሆነ ያሳያል (ማር. 9፡45-48)። እንዲሁም፥ ሙሉ በሙሉ ሳያጠፋ ጥልቅ ሥቃይና ሕመም ከሚያስከትል የማያቋርጥ እሳት ጋር አነጻጽሮታል (ማር. 9፡43)። እነዚህ ምሳሌዎች ሲኦል የዘላለማዊና የላቀ ሥቃይ ስፍራ እንደሆነ ያሳያሉ። ብዙ ሰዎች እንደዚህ ወዳለው የፍርድ ስፍራ ሲሄዱ እየተለመለከትን በዝምታ ልናልፍ እንችላለን? ተመለሱ እያልን “መናገር የለብንም? ካልተናገርን፣ እዚአብሔር ልናስጠነቅቃቸው ስለሚገባ ሰዎች ሞት በኀላፊነት እንደሚጠይቀን ተናግሯል (ሕዝ. 3፡18-21)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ወደ ሲኦል የሚሄዱትን ሰምቶ የሚያስጠነቅቁት ለምንድን ነው? ለ) ወንጌሉ ለሚያስፈልጋቸው ሦስት ሰዎች ጸልይ። ሐ) በእግዚአብሔር ላይ ማመጻቸውና በክርስቶስ ለማመን አለመፈለጋቸው ወደ ሲኦል እንደሚወስዳቸው ለምታውቃቸው ሦስት ሰዎች ወንጌሉን በመልካም ሁኔታ መስክርላቸው፡፡ ውጤቱን ለውይይት ቡድንህ (ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አባላቱ) ለማካፈል ተዘጋጅ፡፡

ረ. ትምህርቱ የገባቸው ደቀ መዛሙርት የእውነት መምህራን ይሆናሉ ማቴ. 13፡51-52)። የአይሁድ ሃይማኖታዊ «የሕግ  መምህራን የብሉይ ኪዳን ትምህርትን ማወቅና ብቃት ካለው መምህር መማር የአስተማሪነት መብት እንደሚያሰጣቸው ያመኑ ነበር። ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ መንፈሳዊ እውነቶችን ከተገነዘቡ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ሕግ እውነተኛ አስተማሪዎች የመሆን ብቃት እንደሚኖራቸው ተናግሯል። ብሉይ ኪዳንን (አሮጌ መዝገብ) እና ክርስቶስ ያስተማራቸውን መንፈሳዊ እውነቶች (አዲስ መዝገብ) ሙሉ ለሙሉ ከተገነዘቡ በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱ የተማሩትን ለሌሎች ያካፍላሉ። ለሎች የሚመኩባቸው ውሣዊ ብቃቶች ባይኖራቸውም፥ ክርስቶስን ያውቁ ነበር። እርሱ ንጉሣቸው ስለሆነ፥ የእግዚአብሔርን መንግሥትና የደቀ መዝሙርነትን መንፈሳዊ መርሆዎች ይነዘቡ ነበር። ላለሆነ በዓለም የሚታወቁ ብቃቶች ባይኖራቸውም፡ መፍራት አይገባቸውም ነበር። እነርሱ ጠቃሚ እውነቶችን ስለሚያውቁ፥ እውነተኛ መምህራን ነበሩ፡

ክርስቶስ ባደገባት የናዝሬት ከተማ ተቀባይነትን አጥቶ ነበር (ማቴ 13፡53-58)። በአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላደገ ሰው፥ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አክብሮትን ማግኘቱ ከባድ ነው። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያንም ይህን ሰው ሁልጊዜ እንደ ልጅ ስለምትመለከተው ነው። እንደዚሁም አንዲት ዘማሪ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን ኣክብሮትን ለማግኘት ትቸገራለች፡፡ ስለዚህ ብዙውን ጊዘ መጀመሪያ ዕውቅና የምታገኘው ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ነው፡፡ እንዲሁም ስጦታ ያለው አዲስ መሪ ወይም ሰባኪ ባደገበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እምብዛም አይከበርም። ሽማግሌዎች ይህን ሰው ከራሳቸው የሥልጣን ክልል ለማስገባት ይቸገራሉ። የሚያሳዝነው ብዙ አዳዲስ ዘማሪዎችና መሪዎች አክብርትና የአገልግሎት ዕድል ስለማይሰጣቸው፥ ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ለመሰደድ ይገደዳሉ። በዚህ የሚጎዳው ማን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ ስጦታ እያላቸው ቤተ ክርስቲያናቸውን ለቅቀው የሚሰደዱ ሰዎች ብስጭት ይሰማቸዋል። በዚህ የኋላ ኋላ ግን በጣም የምትጎዳው አጥቢያዋ ቤተ ክርስቲያን ነች።

ክርስቶስም ይህንኑ የመሰለ ችግር ደርሶበታል። በናዝሬት በነበረ ጊዜ፥ ሰዎች ሊመለከቱ የቻሉት ለ30 ዓመታት አብሯቸው የኖረውን ሰው ብቻ ነበር። በአካባቢያቸው ከተወለደው ከዚህ ልጅ አልፈው፥ የእግዚአብሔርን አሠራር ሊያውቁ አልቻሉም ነበር። ስለሆነም፥ ክርስቶስ ካደገባት ከተማ ርቆ ይኖር ነበር። ከሕዝቡ አለማመን የተነሣ በናዝሬት ብዙ ተአምራትን ሊያደርግ አልቻለም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስጦታ ያላቸው የቤተ ክርስቲያንህ አባላት እውቅናና የአገልግሎት ዕድል በማጣታቸው ምክንያት ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ሲሄዱ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስጦታ ያላቸውን ሰዎች ፈልገው በማግኘት በስጦታቸው እንዲያድጉና እንዲያገለግሉ ለማገዝ ምን ሊያደርጉ ይገባል?

ማቴዎስ ሕዝቡ ባለማመናቸው ምክንያት ክርስቶስ ሊሠራ አልቻለም ሲል ምን ማለቱ ነበር? ክርስቶስ እንዳይሠራ የከለከለው አለማመናቸው አልነበረም። ክርስቶስ የሰዎችን እምነት ሳይጠይቅ በብዙ ስፍራዎች ተአምራት ሠርቷል። ስለሆነም፥ የእምነት አለመኖር የክርስቶስን ኃይል አይቀንሰውም። ነገር ግን እግዚአብሔር የመሥራት ኃይል ቢኖረውም፥ ሕዝቡ ሳያምን በሚቀርበት ጊዜ ላለመሥራት ይመርጣል። ይህ ለታመሙት ሰዎች በምንጸልይበት ጊዜ ልናስታውሰው የሚገባን ጠቃሚ እውነት ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ያልተፈወሱት እምነት ስለሌላቸው ነው ብለን እናስባለን። በመጀመሪያ፥ ችግሩ ክርስቶስ ለመፈወስ አለመቻሉ ሳይሆን፥ አለመምረጡ ነው። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ ተኣምር ሊሠራ እንደ ፈለገና በሰዎች አለማመን ምክንያት ግን ይህንኑ ሊያደርግ እንዳልቻለ በመግለጽ የተማረረበት ሁኔታ አልተጠቀሰም። ለማመን የማይፈልጉትን ሰዎች ቀድሞውኑ ላለመፈወስ ይወስናል። ነገር ግን የፈውስን ቃል ከተናገረ ግለሰቡ ይፈወሳል። ስለሆነም የፈውስ ኃይል ያለው በግለሰቡ እምነት ውስጥ ሳይሆን፥ በክርስቶስ ዘንድ ነው። ስለሆነም፥ የሰዎችን እምነት ፈውስን ከሚያስገኝ ደረጃ ለማድረስ መጣር የለብንም። ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ማንነት በመግለጽና እንዲያምኑበት በማበረታታት፥ ለፍጹም ፈቃዱ ወደሚዙበት ደረጃ ልናደርሳቸው ይገባል። በሌላ በኩል፥ እግዚአብሔር የሰዎችን እምነት ተከትሎ የሚሠራ ይመስላል። እምነታቸውን ያከብራል። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር በእርሷ አማካኝነት ወንጌሉን እንዲያስፋፋ የምትጠይቅ ቤተ ክርስቲያን፥ እግዚአብሔር ይህንኑ ጥያቄ ሲያከብርላት ትመለከታለች። እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲፈውስ የምትጠብቅ ቤተ ክርስቲያንም እግዚአብሔር እምነቷን ሲያከብር ታያለች። ነገር ግን የተለምዶን ፈቃድ የምትከተልና ከእግዚአብሔር ብዙ የማትጠብቅ ቤተ ክርስቲያን፥ ከእግዚአብሔር ብዙ ነገር አታገኝም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በእምነትና የእግዚአብሔር አሠራር መካከል ምን ዓይነትግንኙነትን ታያለህ? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ ያልሠራበት ምክንያት የእምነት አለመኖር እንደሆነ ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ሁኔታውን አብራራ። ይህ አባባል ትክክል ይመስልሃል? ለምን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

3 thoughts on “ክርስቶስ በምሳሌዎች አማካኝነት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማረ (ማቴዎስ 13:1-58)”

 1. ስለ ሁሉ የእግዝ/ር ስም የታባረከ ይሁን ምክንያቱም እንድታስተምረን ጭንቅላትህን የከፈታ እርሱ ነውና።በትምህርትህ ተባርኬዋለሁ ብዙ ማወቅ ስገባኝ እስከዛሬ ያላወኩትን ነገር አውቄያለሁኝ።እንግድህ እግዛብሔር ዘመንህን ይባርክ፣ሀሌም ልማርና የተማርኩትንም ለሌሎች ለማስተማር ዝግጁ ንኝ።

  1. ወንድሜ ተክሌ፣

   ስለአስተያየትህ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ ዌብሳይቱ እንደጠቀመህ ማወቄ ደግሞ ደስታዬን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ የተማርከውን ለሌሎች ለማድረስ የገባከው ቃል ደግሞ የመማርን አላማ ጠንቅቅህ መረዳትህን አስገነዝበኛል፡፡ ጌታ ጥረትህን አብዝቶ ይባርክ፡፡ እንዲሁ እየተጋን ጌታን የምንጠብቅ እንድንሆን የዘወትር ጸሎቴ ነው፡፡

   አዳነው ዲሮ
   የወንጌል በድረገጽ አገልግሎት አዘጋጅ

Leave a Reply

%d bloggers like this: