ጸጋዬ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የአንዱ መሪ ነበር። ጸጋዬ መጠነኛ የሥነ መለኮት ትምህርት ስለ ተከታተለ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች መጋቢያቸው አድርገው መረጡት። ጸጋዬ ከእነርሱ የበለጠ ሥልጠና ስለ ነበረው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱን በመቆጣጠር የሽማግሌዎችን ቦርድ ተጫነ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ኣምባገነን ሆነ። ሰዎችን እንዲህ አድርጉ አታድርጉ እያለ ያዝዝ ጀመር። እርሱ ግን ትእዛዙን ለመፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ ኦይረዳቸውም ነበር። ብዙውን ጊዜ የሰዎችን ኃጢአት እያጋለጠና በፀያፍ ቃላት እየተጠቀመ ይሰብክ ነበር። ጸጋዬ ቁጡ፥ ቁጥጥሩ ጠንካራ፥ እና በትምህርቱና በሥልጣኑ ይኩራራ የነበረ ሰው ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የጸጋዩ ኣመለካከት ከክርስቶስ የሚለየው እንዴት ነው? ለ) ማቴ. 12-13 አንብብ። ስለ ክርስቶስና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት ምን እንማራለን? ሐ) ይህ ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን ይነግረናል?
ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋጨ (ማቴ. 12)
ክርስቶስ የዋህና ትሑት ቢሆንም፥ ቅን ያልሆኑ ሰዎችንና ክፋትን መቃወሙ አልቀረም። በአዲስ ኪዳን ሁሉ፥ ክርስቶስ የተራ ሰዎችን ኃጢአት አጥብቆ እንዳልተቃወመ እንመለከታለን። የሮምን መንግሥት ክፋት ያን ያህል አልተቃወመም። እርሱ አጥብቆ የተቃወመው እንደ ጸጋዬ ያሉትን የሃይማኖት መሪዎች ክፋት ነበር። ትዕቢተኞችን፥ ድሆችን የሚበድሉ፥ የእነርሱን የመንፈሳዊነት ግንዛቤ የማይከተሉትን ሰዎችና ነገሮችን ሁሉ የሚቃወሙ የሃይማኖት መሪዎችን ኃጢአት ይጠላ ነበር። ክርስቶስ የሃይማኖት መሪዎችን ኃይል የሚገድብ፥ ፍጹም የተለየ የመንፈሳዊነትና የኣመራር አቅጣጫ እያስተማረ ስለ ነበር፥ ከፈሪሳውያን ጋር መጋጨቱ አልቀረም ነበር። ማቴዎስ በ12ኛው ምዕራፉ፥ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለምን እንደ ጠሉትና እንዲሰቀልም ለምን እንደ ፈለጉ ለአይሁዶች ይገልጻል። ይህ ክፍል የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሥልጣን ለተሰጠን ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። ዛሬ ክርስቶስ በኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ እየተመላለሰ ቢሆን፥ በእኛም ላይ ጠንካራ ቃላት ይሰነዝር ይሆን?
በዚህ ክፍል፥ ማቴዎስ ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር እንዴት እንደ ተጋጨ ምሳሌዎችን ይሰጠናል። በዚህም ማቴዎስ ክርስቶስ በሰው-ሠራሽ ሕጎች ላይ ሥልጣን እንዳለው በማሳየት፥ ወደፊት የሚነሡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሕግጋት ላይ ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ጋር ግላዊ ግንኙነት በማድረጉ ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቧል።
ሀ. በሰንበት እሸትን በመቅጠፍ የተነሣ ክርስቶስ ከፈሪሳውያን ጋር ተጋጨ (ማቴ. 12፡1-8)። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ ፈሪሳውያን እግዚአብሔርን ለማስደሰት ብዙ የተለያዩ ሕግጋት የሚጠብቁ አጥባቂ ሃይማኖተኞች ነበሩ። እነርሱም የአይሁዶች የአምልኮ ቀን ስለሆነው ሰንበት ብዙ ሕግጋት አውጥተው ነበር። ብሉይ ኪዳን ኣይሁዶች ሰንበትን የዕረፍት ቀን አድርገው እንዲጠብቁ አስጠንቅቋቸው ነበር። (ዘዳግ. 31፡14–17 አንብብ)። ብሉይና አዲስ ኪዳን መካከል በነበረው ዘመን ሰንበትን መጠበቅ እግዚአብሔርን ማስደሰት ከሚቻልባቸው ዐበይት መንገዶች አንዱ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። (ነህ. 18፡5-22 አንብብ።) ስለሆነም፥ የሃይማኖት መሪዎች የተለያዩ ደንቦችን፥ (በ39 ምድቦች የሚከፈሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕግጋት አውጥተው ነበር)። እነዚህ ሰዎች ብዙ ሕግጋትን መጠበቅ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ መንገድ ሰንበትን እንደሚያከብር ያሳያል ብለው ያስቡ ነበር። ስለሆነም፥ ፈሪሳውያን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በሰንበት እሸት ሲቀጥፉ ሳሉ ክርስቶስ ሳይከለክላቸው ስለቀረ፥ ቁጣቸውን ገለጹ።
ክርስቶስ ግን ያደረገው የእነርሱን ተቃራኒ ነበር። ክርስቶስ ያከበረው እግዚአብሔር ሰንበትን ቅዱስ አድርጎ የለየበትን መንፈስ ነበር ። ሰው ሠራሽ ደንቦች ከመንፈሳዊነትና አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ከሚያደርገው ግንኙነት ጋር የሚገናኙ ባለመሆናቸው፥ እነርሱን ያለመጠበቅ ነጻነት ነበረው። እንዲያውም፥ አዲስ የተጨመሩት የሃይማኖት መሪዎች ሕግጋት፥ ሰዎች «ከእግዚአብሔር ጋር እንደ አብርሃም ሕያውና ግላዊ ግንኙነት የማደርገው እንዴት ነው?» ብለው እንዳይጠይቁ ስለ ከለከሏቸው፥ እግዚአብሔር የፈለገውን መልእክት እንዳስተጓጎሉ ያውቅ ነበር። ሕዝቡ የተጨመሩትን ሕግጋት ለመፈጸም ይታገል ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የቤተ ክርስቲያን ሕግጋት መልካሞች ሊሆኑ ቢችሉም፥ ሰዎች ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ኣቋርጠው በሕግጋቱ ላይ እንዲያተኩሩ ካደረጉ፥ አደገኞች ናቸው።
ክርስቶስ ከፈሪሳውያን ክስ ምላሽ የሰጠው በአራት የተለያዩ መንገዶች ነበር።
- እግዚአብሔር ሕጉን ከመከተሉ በላይ የሚያሳስበው የግለሰብ የልብ አመለካከት ነው። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ለበለጠ ዓላማ ሕጎች እንዲጣሱ ይፈቅዳል። ክርስቶስ አይሁዶች ጀግናቸው አድርገው ስለሚመለከቱትና የእግዚአብሔር የልብ ወዳጅ ስለነበረው ዳዊት፥ አንድ እውነት አሳሰባቸው። ይህም ምንም እንኳ ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን ኅብስት በቤተ መቅደስ ውስጥ መብላት የተከለከለ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ዳዊት ኅብስቱን ስለበላ እንዳልቀጣው ነበር። ዳዊት ይህን ሕግ እንዲጥስ የተፈቀደለት፥ ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረው ግንኙነትና እግዚአብሔርም ከዚያ የበለጠ ችግር እንደ ደረሰበት በመገንዘቡ ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት ከሕግ ፊደል በላይ አስፈላጊ የሆነ ነበር።
- በየሰንበቱ ካህናት የሰንበትን ሕግ ለመተላለፍ ይገደዱ ነበር። ሕጉ ማንም እንዳይሠራ ቢደነግግም፥ ካህናት የግድ መሥዋዕቶችን ማቅረብና ቤተ መቅደሱን መንከባከብ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም እግዚአብሔር ሰዎች በሰንበት ቀን እንዲሠሩ እንደ ፈቀደ ያሳያል። ካህናት እርሱን በማገልገል ላይ በመሆናቸው፥ ክርስቶስ ሕጉን እንዲጥሱ ፈቅዶላቸዋል። ክርስቶስ ግን ከካህናት በላይ በመሆኑ፥ ሰው ሠራሽ ደንቦችን በጣሰ ነበር። እንድ ሰውከክርስቶስ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት፥ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማምለክ ከሠሩዋቸው ደንቦች ሁሉ ከመከተል ይበልጣል።
- የሃይማኖት መሪዎች ሕግጋትን በመጠበቁ ላይ፥ ከመጠን በላይ በማተኮራቸው፥ ብሉይ ኪዳን ስለ አምልኮ ምን እንደሚያስተምር ዘንግተው ነበር። እግዚኣብሔር ከሕግጋትና ደንቦች ይልቅ በግንኙነቶች ላይ የሚያተኩር አምላክ ነው። በመሆኑም በብሉይ ኪዳን ሁሉ የአምልኮ አመለካከት (ለምሳሌ፡- መታዘዝ [1ኛ ሳሙ. 5፡22] እና አንድ ሰው ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት (ለምሳሌ፥ ምሕረት [ሆሴዕ 6፡6]) ለእግዚአብሔር ከውጫዊ የሕግ ተገዥነትና ሰው ሠራሽ የአምልኮ ሥርዐቶች ይበልጣሉ። የሃይማኖት መሪዎች በሕግጋት ላይ በማተኮራቸው እግዚአብሔር ከእርሱና ከሌሎችም ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲመሠርቱ መፈለጉን ዘንግተው ነበር። እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን የለየው ሰዎች እርሱን እንዲያመልኩና እርስ በርሳቸው እንዲተጋገዙ ለማበረታታት ነበር። ይህ ካልሆነ ሰዎች በየዕለት ሥራዎቻቸው ተጠምደው እርሱን ለማምለክና የተቸገሩትን ሰዎች ለመርዳት ጊዜ እንደማያገኙ ያውቅ ነበር።
- አምላክ የሆነው መሢሕ ራሱ በመካከላቸው ነበር። ስለሆነም፥ ስለ ሰንበት ሕግጋት የእግዚአብሔርን ልብ ስለሚያውቅ፥ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የመበየንና የመተርጎም ሥልጣን ነበረው።
ለ. በዕንበት ዕለት ሰው በመፈወሱ ምክንያት ከፈሪሳውያን ጋር መጋጨቱ (ማቴ. 12፡9-14)። ማቴዎስ በሌላ ክስተት ተጠቅሞ ኣይሁዶች ክርስቶስን ለምን አጥብቀው እንደ ጠሉት አብራርቷል። በሰንበት ቀን ሰው ስለ ፈወሰ ሊገድሉት ቆርጠው ተነሡ። ክርስቶስ በሰንበት ቀን በመፈወሱ፥ እግዚኣብሔር ከሃይማኖታዊ ተግባራት በላይ ምሕረትን እንደሚወድ አሳይቷል።
ክርስቶስ ፈሪሳውያን እየተከታተሉት እንደሆነ ቢያውቅም፥ ስለ ሕጉ ከነበራቸው የተሳሳተ ግንዛቤ ሊመልሳቸው ፈለገ። ስለሆነም፥ ፈሪሳውያኑን ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገባቸው ነገሮች ለማስተማር እጁ የሰለለችውን ሰው ፈወሰ። ክርስቶስ ሰው ሠራሽ ሕግጋት ሰዎች ሰዎችን እንዳይረዱ በሚከለክሉበት ጊዜ፥ እነዚህን ሕግጋት ማስወገድ እንደሚገባ አስተምሯል። ራሳቸው የሃይማኖት መሪዎች እንኳ የበግ ከጉድጓድ ውስጥ መውደቅ ዓይነት ድንገተኛ አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ፥ ሰዎች የሰንበትን ሕግጋት እንዲያፈርሱ ይፈቅዱላቸው ነበር። ነገር ግን ድንገተኛ አደጋ በማይኖርበት ጊዜ (ግለሰቡ እስከ ነገ በሕይወት ሊቆይ ካልቻለ በቀር)፤ እርዳታ ማድረጉ እንደ ኃጢአት ይቆጠር ነበር። ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ በላይ ጠቃሚ ስለሆነ ርዳታ ማድረጉ እንስሳትን ከመሠዋት፥ ከመዘመር፥ ከመጸለይ እኩል እግዚአብሔርን የሚያስከብር ተግባር ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች የሚከተሏቸውና ከእግዚአብሔር ይልቅ በሕግጋት ላይ እንዲያተኩሩ የሚያደርጓቸው ሰው ሠራሽ ደንቦች ምንድን ናቸው? ለ) ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ሕያው ግንኙነት ከማድረግና ለሌሎች ከፍቅርና ርኅራኄ የመነጨ እገዛ ከመስጠት ይልቅ በአምልኮ ተግባራት ላይ ሊያተኩሩ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
ሐ. የክርስቶስ ተግባራትና ባሕርያት የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ይፈጽማሉ (ማቴ. 12፡15-21)። ማቴዎስ በክርስቶስና በሃይማኖት መሪዎች መካከል ስለተከሰተው ሌላ የግጭት ምሳሌ ከመግለጹ በፊት፥ ክርስቶስ በኢሳ. 42፡1-4 ስለ መሢሑ ከተነገሩት እጅግ ጠቃሚ ትንቢቶች አንዱን እንደ ፈጸመ አመልክቷል። ፈውሱ፥ ትምህርቱና አመለካከቱ ሁሉ ኢሳይያስ የተነበየለት የእግዚአብሔር ባሪያ መሆኑን አሳይቷል። ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ባካሄደው ግብግብ ለፍትሕና ለሰዎች ሁሉ ትክክል ስለሆነው ጉዳይ ተሟግቷል። ነገር ግን ለሰዎች የነበረው አመለካከት የሃይማኖት መሪዎች ወይም የሮም ባለሥልጣናት የሚያራምዱት ዓይነት አልነበረም። ሰዎችን አልገፋም፥ አልገፈተረምም። ከቃላቱ በላይ በተግባሩ የእግዚአብሔርን ባሕርያት እያሳያቸው በዝምታ ተመላልሷል። የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ለመሳብ አልሞከረም። ለዚህ ነበር ክርስቶስ ሰዎች ስለ ታምራቱ እንዳይናገሩ ያስጠነቀቃቸው (ማቴ. 12፡16)። መሢሕ ቢሆንም ክርስቶስ እጅግ ገር በመሆኑ፥ «የተቀጠቀጠን ሸንበቆ» አይሰብርም። ይህም የሰዎችን የተጎዳና የተዳከመ አኗኗር የሚያመለከት አገላለጽ ነበር። የዓለም ፈጣሪ ቢሆንም፥ «የሚጤስ ጧፍ» አያጠፋም። ይህም ተስፋ የቆረጡትን ደካሞች ሁኔታ የሚያሳይ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ መሪዎች የተራ ሰዎችን ስሜቶችና ፍላጎቶች በመርገጥ ይበድሏቸዋል። ብዙ መሪዎች የሚጥሩት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ነው። ክርስቶስ ግን የተናቁትን ጨምሮ ለሰዎች ፍላጎት ስለሚሳሳ፥ ከራሱ ይልቅ የእነዚህን ወገኖች ፍላጎት አሟልቷል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስን የአመራር አመለካከት ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አነጻጽር። ለ) የክርስቶስን የአመራር አመለካከት ዛሬ ከምንመለከታቸው ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር አነጻጽር።
መ. ክርስቶስ ስለ ኃይሉ ምንጭ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋጨ (ማቴ 12፡22-37)። ግልጽ ተአምራት በሚከሰቱበት ጊዜ፥ «እነዚህን ተአምራት ለመፈጸም የሚያስችል ኃይል ከየት መጣ?» የሚል ጥያቄ መነሣቱ የማይቀር ነው። ለዚህ ሁለት አማራጮች አሉ። በመጀመሪያ፥ እግዚኣብሔር ተአምራትን እንደሚሠራ አያጠራጥርም። ሁለተኛ፥ ሰይጣንም ተአምራት ይሠራል። እንዲያውም፥ ሐሳዊ መሢሕ በሰይጣን ኅይል ተአምራትን እንደሚሠራ ተገልጾአል (ራእይ 13፡14 19፡20)።
ሁሉም ሰው የክርስቶስን ተአምራት አድራጊነት ያውቅ ስለነበር፥ «ኃይሉ ከየት መጣ?» የሚል ጥያቄ ተነሣ። ፈሪሳውያን ቀደም ብለው ክርስቶስ ከእግዚአብሔር እንዳልሆነ ስላሰቡ፥ ብቸኛው አማራጭ ምላሽ የክርስቶስ ኀይል ብዔል ዜቡል ብለው ከጠሩት ሰይጣን እንደ መጣ ማመልከት ነበር። ብዔል ዜቡብ፥ የሚለው ስም የመጣው ከከነዓናውያን ጣዖታት አንዱ ለነበረው በኣል ከተሰነዘረው ስድብ ነበር። ብዔል ዜቡል «ከፍ ያለው በዓል» የሚል ፍች ነበረው (2ኛ ነገ. 1፡2)። አይሁዶች ግን ይህን ስም «በዓል ዜቡብ» ማለትም «የዝንቦች ጌታ» ወደሚል ስላቅ ለውጠውት ነበር። ሰይጣን ከአምልኮተ ጣዖት በስተ ጀርባ የሚሠራ ኃይል መሆኑን በመገንዘብ፥ ለሰይጣን ብዔል ዜቡብ የሚል ቅጽል ስም አወጡለት። ምናልባትም ይህ ስም የመጣው የበኣልን የአምልኮ መቅደስ ከደመሰሱና ከኢየሩሳሌም ውጭ በሚገኝ አንድ ሸለቆ ውስጥ ከጣሉት በኋላ ሳይሆን አይቀርም። ሸለቆው በኋላ የከተማይቱ የቆሻሻና የዝንቦች ማከማቻ ሆኗል።
የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስ አጋንንትን በሰይጣን ኃይል እንደሚያስወጣ በገመቱ ጊዜ፥ ክርስቶስ ይህ የሞኝነት አስተሳሰብ መሆኑን አሳይቷቸዋል። ክርስቶስ ለሃይማኖት መሪዎች በሰጠው ምላሽ፥ በሰይጣንና መንግሥቱ ላይ መንፈሳዊ ሥልጣን እንዳለውም አመልክቷል።
- ውስጣዊ ዓመፃ ያለበት የትኛውም መንግሥት ሊጸና አይችልም። ስለሆነም፥ ሰይጣን ለክርስቶስ አጋንንትን የማስወጣት ኃይል በመስጠት በራሱ መንግሥት ላይ ጥቃት ሊሰነዝር አይችልም። ሰይጣን ለመንግሥቱ ተጨማሪ ሥልጣን የሚያገኘው በኣጋንንቱ አማካኝነት የሰዎችን ሕይወት በመቆጣጠር ነበር። አጋንንትን ማስወጣት የሰይጣንን መንግሥት ማዳከም ስለሆነ፥ ሰይጣን ለክርስቶስ እገዛ እንደማያደርግ ግልጽ ነበር።
- ክርስቶስ አጋንንትን እያስወጣ መሆኑንና ሰይጣን የራሱን መንግሥት ለመደምሰስ ክርስቶስን አለማዝዙ፥ ወደ አንድ ድምዳሜ ማድረሱ የግድ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመመሥረት የሰይጣንን መንግሥት እንዲያፈርስ እየረዳው ነበር። በንጉሡ ክርስቶስ ኣማካኝነት የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላቸው የተገኘላቸው ኣይሁዶች፥ የትኛውን መንግሥት እንደሚደግፉ መወሰን ነበረባቸው።
- ክርስቶስ ከሰይጣን የበለጠ ብርቱ ነው። ክርስቶስ አጋንንትን በማስወጣት ብርቱ የሆነውን ሰይጣንን ኣስሮ ቤቱን (መንግሥቱን) በማፍረስ የብዙ ሰዎችን ነፍስ ያድናል።
- አንድ ሰው ለክርስቶስ የሚሰጠው ምላሽ የታሰበበት ሊሆን ይገባል። ወደ አንድ አቅጣጫ ሳያደሉ እንዲህ ነኝ ማለት ያስቸግራል። ክርስቶስን ስለ ማመን ሰዎች ምርጫ ማካሄድ አለባቸው። አንድ ክርስቶስን በሚገባ የማይደግፍ፥ በእርሱ የማያምንና ወደ መንግሥቱ የማይቀላቀል ሰው፥ የጠላት መንግሥት አካል ሆኖ ክርስቶስን እየወጋ መሆኑ ግልጽ ነው።
- አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን እንዳይሰድብ መጠንቀቅ አለበት። ምክንያቱም የማይሰረይ ኃጢአት ነው። ይህ የክርስቶስ አባባል በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ውይይትን አስነሥቷል። ይህ ይቅር የማይባል ኃጢአት ምንድን ነው? አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህንን ኃጢአት እንዳይፈጽሙና ንስሐ የመግባት ዕድል እንዳይነፈጉ ይሰጋሉ። ይህን ኣሳብ ለመረዳት፥ የሚከተለውን ማጤን ይኖርብናል።
ሀ. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ በክርስቶስ ለማመን የሚፈልግ ሰው ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደ ፈጸመና በክርስቶስ የማመን ዕድል እንደማይኖረው አልተነገረውም። ሴተኛ አዳሪዎች (መግደላዊት ማርያም – ሉቃስ ፡36-50)፥ ነፍሰ ገዳዮች (ከክርስቶስ ጋር የተሰቀለው ወንጀለኛ – ሉቃስ 3፡39-48)፥ ክርስቶስን የካዱ (ለምሳሌ፥ ጴጥሮስ) ሁሉ ይቅርታን አግኝተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈልጎ የተከለከለ አንድም ሰው ስለሌለ፥ ንስሐ ገብተን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንዳናገኝ የሚከለክል ኀጢአት የለም።
ለ. ደኅንነት እንዳናገኝ የሚከለክለን ክርስቶስን ለማመንና ለመከተል ያለመፈለግ ኃጢአት ብቻ ነው። የአዲስ ኪዳን ትእዛዝ ሁልጊዜም «በክርስቶስ ኢየሱስ አምነህ ዳን» (የሐዋ. 16፡3) የሚል ነው። ማስጠንቀቂያውም ሁልጊዜ ግልጽ ነው። «በልጁ ያላመነ ግን ይፈረድበታል» ይላል (ዮሐ 3፡18)። ይህ አሳብ በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ ተብራርቶ ቀርቧል። ሌላ የደኅንነት መንገድ ስለሌለ፥ በክርስቶስ ለማመን የማይፈልጉ ሰዎች ተስፋ የላቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እግዚአብሔርን ለመታዘዝ በማይፈልጉበት ጊዜ እንደ ፈርዖን ልባቸውን ሊያደነድኑ እንደሚችሉ በመግለጽ ያስጠነቅቃል (ዘዳ 8፡5)። እግዚአብሔር ራሱን ለአንድ ግለሰብ በሚገልጥበት ጊዜ ግለሰቡ ማመንን ወይም አለማመንን ይመርጣል። ላለመታዘዝ በሚመርጥበት ጊዜ ልቡ እየደነደነ በመሄድ የማመን ዕድሉን ያጣብብበታል። ለረዥም ጊዜ እግዚአብሔርን መቃወም፥ የልብን ድንዳኔ ሂደት እንዲቀጥል ያደርገዋል። («እግዚአብሔር የሚለው፥ ልብህን ለማደንደን ወስነሃል። እኔም ፍላጎትህን በማክበር የበለጠ ላደንድንልህ» ነው)። ይህ ልብን የማደንደኑ ተግባር እየቆየ በሚሄድበት ጊዜ፥ ግለሰቡ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ ለማመን የበለጠ ይቸገራል። ግለሰቡ ሲሞት በክርስቶስ ለማመን አለመፈለጉን ከፍጻሜ ስላደረሰ፥ እንደ ተኮነነ ይሞታል። ሁለተኛ የንስሐ ዕድል ስለሌለ ግለሰቡ ይኮነናል።
ከላይ የተጠቀሱት እውነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ተብራርተዋል። እንግዲህ፥ ክርስቶስ ይቅርታ የማይደረግለት ኃጢአት ሲል ምን ማለቱ ነው? ምሑራን የተለያዩ አሳቦችን ሰጥተዋል። በመጀመሪያ፥ ክርስቶስ የማይሰረይ ኃጢአት በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብቻ ሊፈጸም እንደሚችል መግለጹ ነበር። ሰዎች መሢሕ ስለ መሆኑ ይጠራጠሩ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ እስከ ትንሣኤው ድረስ ሙሉ በሙሉ ማንነቱን አላወቁም ነበር። ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የፈጸማቸው ተአምራት፥ እግዚአብሔር በመካከላቸው ለመገኘቱ ግልጽ መረጃዎች ነበሩ። ተአምራቱ በሰይጣን እንደሚከናወኑ ተናግረው ከሆነ፥ ልባቸው መመለሻ እስከማይኖረው ድረስ ደንድኗል ማለት ነው። ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን መስደብ ስለሆነ፥ በዘላለም ሞት ይቀጣሉ፡ ክርስቶስ የፈጸማቸውን ግልጽ ተአምራት ለመቀበል ባለመፈለጋቸው፥ የልባቸውን ድንዳኔ ስላሳዩ፥ ማመኻኛ የላቸውም። ይህን አመለካከት የሚከተሉ ምሑራን እንዲህ ዓይነት ተአምራት የነበሩት ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ በመግለጽ፥ ክርስቶስ ተአምራት ሲፈጽም ይመለከቱ ከነበሩት አይሁዶች ውጭ ማንም የማይሰረይ ኃጢአት ሊሠራ እንደማይችል ያስረዳሉ።
ሁለተኛ፥ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ከእርሱ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ አልተናገረም። እርሱ ለማለት የፈለገው ስለ ክርስቶስ የሚያስረዳውን የወንጌል እውነት ቸል ማለት ሊኖር እንደሚችል ነው። አንድ ሰው ከመሞቱ በፊት ሁልጊዜም እውነቱን ለይቶ ከኃጢአቱ ንስሓ የሚገባበትና የሚያምንበት ዕድል አለው። አንድ ሰው ሊሰረይ የማይችል ኃጢአት የሚፈጽመው ክርስቶስ ለኃጢአቱ በመስቀል ላይ እንደ ሞተለት እያወቀ፥ ሆን ብሎ ሳያምን ሲቀር ነው። ይህ ሰው ሆን ብሎ መንፈስ ቅዱስ በልቡ ውስጥ ያከናወነውን ተግባር ቸል ብሏል። አንድ ምሑር እንዳሉት፥ «እግዚአብሔር ይቅር ሊል የማይችለው ይቅርታን ለመቀበል ያለመፍቀድን ብቻ ነው።» ይህ አተረጓጎም በዕብ 6፡4-6 10፡26-31 እና 1ኛ ዮሐ 5፡16 የተጠቀሱትንም አሳቦች ጭምር ለመረዳት ያዘናል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለማይሰረይ ኃጢአት ከቀረቡት ማብራሪያዎች የትኛውን ትደግፋለህ? ለምን? ለ) ከዚህ በመነሣት፥ አንድ ሰው የማይሰረይ ኃጢኣት እንደ ፈጻመና ንስሐ ሊገባ ቢፈልግም እንኳ ጉዳዩ ተስፋ ቢስ እንደሆነ በሚያጫውትህ ጊዜ፥ ምን ምላሽ ትሰጠዋለህ?
- የሰው ንግግር የልቡን ምንነት ያመለክታል። የሕክምና ባለሙያዎች የሰውነታችንን ሙቀት ለመለካት በቴርሞ ሜትር መለኪያ ይጠቀማሉ። ክርስቶስ መንፈሳዊ ሁኔታችንን የሚያሳይ መሣሪያም እንዳለ ተናግሯል። ይህም ከአፋችን የሚወጣው ቃል ነው። ፈሪሳውያን በሰይጣን ኃይል እንደሚሠራ በመግለጽ፥ ክርስቶስን ላለመቀበል ወስነዋል። እነዚህ ቃላት፥ ሰዎቹ የእግዚአብሔር ጠላቶች መሆናቸውን ያሳያሉ። ስለሆነም፥ እንደማይጠቅም ደረቅ እንጨት በመሆናቸው፥ ሊቆረጡና የእግዚአብሔርን ፍርድ ሊቀበሉ ተቃርበዋል። ይህ ለእኛም ማስጠንቀቂያ ነው። ከኣፋችን ውሸት የሚፈልቅ ከሆነ፥ የገባነውን ቃል የማንፈጽም ወይም የምንሳደብ ከሆንን፥ እሑድ እሑድ ምንም ዓይነት ጣፋጭ መዝሙሮችን ብንዘምርም እንኳ፥ ልባችን ንጹሕ አይደለም ማለት ነው። የምናጉረመርም፥ በውሸት መሪዎችን የምንከስ የምናማ፥ በትምክህት የምንናገር ከሆንን፥ እነዚህ ሁሉ ኃጢኣቶች የልባችንን ሁኔታ ያሳያሉ። ነገር ግን የፍቅርንና የርኅራኄን ቃላት ብናመነጭሰዎችን ብናበረታታ፥ የምንናገረውን ብንቆጣጠር፥ እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ መሥራቱን እንመሰክራለን። ክርስቶስ በግድየለሽነትም እንኳ ለምንናገረው ለማንኛውም ቃል፥ በእግዚአብሔር ፊት እንደምንጠየቅ በመግለጽ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል።
የውይይት ጥያቄ ሀ) ባለፈው ሳምንት የተናገርሃቸውን ቃላት አስታውስ። በአብዛኛው የተጠቀምከው አጥፊ ቃላትን ነበር ወይስ ገንቢ? ለ) እነዚያ ቃላት ስለ መንፈሳዊ ሕይወትህ ምን ያሳዩ ነበር? አስፈላጊ ከሆነ፥ የተወሰነ ጊዜ ወስደህ በመጸለይ እግዚአብሔር ልብህን እንዲለውጥና ቃሉችህ እርሱን የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ጸልይ። ሐ) ምሳሌ 10፡10-14፥ 18-21፥ 31-32፡ 12፡6፥ 18፤ 16፡24፤ 17፡27፤ 18፡8 አንብብና ስለምንናገራቸው ቃላት ምን እንደሚያስተምሩ የለጽ።
ሠ. ስለ ተአምራዊ ምልክት አስፈላጊነት ክርስቶስ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ተጋጨ (ማቴ 12፡38-46)። በዛሬው ዘመን ሰዎች ተአምራትን በሚያዩበት ጊዜ ይደሰታሉ። ዝነኛ ታምራት ሠሪዎች ከውጭ ኣገር እየመጡ ፈውስና ሰፊ ስብከተ ወንጌል ያካሄዳሉ። አብያተ ክርስቲያናትም የፈውስ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። ይሄ ጤናማ ተግባር ነው? እግዚአብሔር ተአምራት ሠሪ አምላክ ነው። ሰዎችን ይፈውሳል። ነገር ግን እግዚአብሔር ተአምር ካልሠራ መኖሩን የመጠራጠር አደጋ ተጋርጦብናል። ለብዙ ክርስቲያኖች፥ የአስደናቂ ተአምራት ናፍቆት እንደ ሱስ አስያዥ ዕፅ አደገኛ ሆኗል። አይሁዶችም ተአምራትን ይፈልጉ ነበር። ክርስቶስም ተአምራትን ሠርቷል። ነገር ግን ተአምራት ሰዎች በክርስቶስ ላይ የጠለቀ እምነትን እንዲጥሉ አላስቻሏቸውም። (ማስታወሻ፡- ታላላቅ ተአምራት በተፈጸሙባቸው ሦስት ክፍለ ጊዜያት፥ ማለትም እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በሚቅበዘበዙበት ወቅት፥ በኤልያስ ዘመን እና በክርስቶስ ዘመን፥ ሰዎች በእነዚህ ታምራት እገዛ ጥልቅ እምነት ሊያዳብሩ አልቻሉም ነበር። እንዲያውም፥ እነዚህ ክፍለ ጊዜያት ተለይተው የሚታወቁት በሕዝቡ እምነት ማጣት ነው)
የሃይማኖት መሪዎች ባለማመን ተነሣሥተው፥ ክርስቶስ ታላላቅ ተኣምራትን በማድረግ መሢሕነቱን እንዲያረጋግጥላቸው ጠየቁት። ነገር ግን ክርስቶስ ተአምራትን የሚሠራው ሰዎችን ለመርዳት እንጂ ለማስደነቅ አልነበረም፡፡ ስለሆነም፥ ኃይሉን ለማሳየት አልፈለገም፡፡ ለሃይማኖት መሪዎች ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ እንደማያሳያቸው ገለጾላቸዋል። ዮናስ በተምሳሌታዊነቱ መንገድ እንደ ሙት በዓሣ ነባሪ ሆድ ውስጥ ሦስት ቀናት ቆይቶ እንደ ወጣ ሁሉ፥ ክርስቶስም ሞቶ መነሳት ነበረበት (ክርስቶስ ዓርብ ከሰዓት ተሰቅሎ እሑድ ጠዋት ስለተነሳ፥ እንዴት ለሦስት ቀናት በመቃብር ውስጥ ቆይቷል ብለን እናስባለን የሚሉ ሰዎች አሉ። ይህ ከ 36 ሰዓታት አይበልጥም፡፡ አይሁዶች ቀን የትኛውንም የቀን ክፍል እንደ ሙሉ ቀን ይቆጥራሉ። ስለሆነም ክርስቶስ ዓርብ፣ ቅዳሜ ሙሉ ቀንና ከእሑድ የተወሰነ ሰዓት መቃብር ውስጥ መቆየቱ በአጠቃላይ ሦስት ቀናትን ያመለክታል) የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መሢሕነቱን የሚያረጋግጥ ዐቢይ ተአምር ነበር፡፡ ባለማቋረጥ ሌሎች ተአምራትን ለመመልከት መናፈቁ የእምነት ሳይሆን፥ ያለማመን ምልክት ሊሆን ይችላል። ክርስቶስ ለማንም መሢሕነቱን ሊያረጋግጥ የሚል መረጃ እንዳለ በማመልከት አይሁዶችን አስጠንቅቋቸዋል። የነነዌ ከተማ ነዋሪዎችና ንግሥት ሳባ አሕዛብ ቢሆኑም እንኳ፥ ክርስቶስን አይተውት ቢሆኑ ኖረ ባመኑበት ነበር። ስለሆነም፥ ሳባና ሌሎችም ተአምራቱን ያልተመለከቱ ሰዎች አይሁዶችን ለልባቸው ድንዳኔ ይኮንኗቸዋል።
ከዚያም ክርስቶስ አጋንንት የወጣላትን ግለሰብ ምሳሌ ነገራቸው፡ አጋንንቱ ክወጣለት በኋላ በቦታው ምንም ነገር ስላልተተካ አጋንንቱ ሌሎች ሰባዎችን ይዞ በመመለስ የከፋ ሥቃይ ያሳየዋል፡ ክርስቶስ ይህን ምሳሌ የሰጠው ለሁለት ዓላማዎች ነበር። በመጀመሪያ፣ የሃይማኖት መሪዎችና አይሁዶች አጋንንቱ እንደ ወጣለት ግለሰብ መሆናቸውን እያመላከተ ነበር፡፡ አይሁዶች ብሉይ ኪዳንና ሃይማኖታዊ ሕግጋት ነበሯቸው። በመጥምቁ ዮሐንስና በክርስቶስ ትምህርት አማካኝነትም የአይሁዶች ሕይወት ነጽቷል። ነገር ግን ገለልተኛ ወይም በራስ የመሞላት አመለካከት ይዘው በክርስቶስ ባለመሆናቸው፥ ልክ እንደ ባዶ ቤት ሆነው ነበር። ይህም ለሰይጣን ጥቃት ስላጋለጣቸው፥ ክርስቶስ በመካከላቸው ሆኖ ሕይወታቸውን እንዲሞላ እስካልመረጡ ድረስ ከበፊቱ የበለጠ እስረኞች ያደርጋቸዋል። ክርስቶስ በአካል ተገኝቶ አይሁዶች ክርስቶስን ለመቀበል ስላልፈለጉ ፍርዳቸው ከበፊት የከፋ ሆኖአል። ሁለተኛ፣ ይህ ክፉ መናፍስትን ለምናስወጣላቸው ሰዎችም የሚያገለግል ማስጠንቀቂያ ነው። ክፉ መናፍስት እንዲወጡ ማዘዙ ብቻ በቂ አይሆንም። ርኩስ መንፈስ የወጣለት ሕይወት በክርስቶስ ላይ በሚጣል ጽኑ እምነትና ደቀ መዛሙርቱ በመሆን እርሱን ብቻ በማክበሩ ተግባር እንዲተካ ከሰይጣን ጋር ከተያዙት ነገሮች ሁሉ እንዲርቅ ተግተን ልንሠራ ይገባል። ባዶውን ስፍራ በክርስቶስና በመንፈስ ፍሬ ካልሞላነው፥ ክፉ መንፈስ ማስወጣቱ፥ ግለሰቡ ለሰይጣን ጥቃት የበለጠ እንዲጋለጥ ያደርገዋል።
ረ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ከሥጋ ዘመዶቻቸው በላይ እንዲዛመዱ አስተማረ (ማቴ. 12፡46-50)፡፡ ለቤተሰብ ያለን ተፈጥሯዊ ፍቅር የእግዚአብሔር በረከት ቢሆንም፥ ለወንጌሉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ተፈጥሯዊ ቤተሰቦቻችንን ከመንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን በላይ የምንወድና የምንከባካብ ከሆንን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች ይከሰታሉ። አንድ ቀን የክርስቶስ እናትና ወንድሞቹ (የዮሴፍና ማርያም ልጆች) ሊጎበኙት መጡ። ክርስቶስም አጋጣሚውን በመጠቀም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ከሥጋዊ ዝምድና በላይ አስፈላጊ መሆኑን አስተማረ፡፡ በክርስቶስ የሚያምኑና እግዚአብሔርን የሚታዘዙ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናቸው፥ የክርስቶስ እውነተኛ ዘመዶች ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል በመሆናቸው፥ እርስ በርሳቸው መንፈሳዊ ዘመዶች ናቸው። ይህም ከሥጋ ዝምድና የበለጠ አፈላጊ ነው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)