ማቴዎስ 18፡15-35

  1. የእግዚአብሔር ደቀ መዝሙር መሆን ማለት ስለ ኃጢአትና ስለ ተበላሸ ግንኙነት መጨነቅን ይጠይቃል (ማቴ 18፡15-20)

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአትና የተበላሸ ግንኙነት በሚከሰትበት ጊዜ፥ ሰዎችን በሦስት መንገዶች እናስተናግዳለን። በመጀመሪያ፣ ጉዳዩን ችላ ብለን እንተወዋለን። ይህም፥ ሁሉም ኃጢአት ይፈጽማል፣ ሰዎች ሁልጊዜም በትግል ላይ ናቸው፡፡ እኔ ምን ላደርግ እችላለሁ? ይህ የእኔ ሥራ አይደለም” የሚል ምክንያት እናቀርባለን፡፡ ይህም መከፋፈል እንዲበዛ፥ ኀጢአት እየጨመረ እንዲሄድ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን ኅብረትና ምስክርነት፣ ደግሞም የክርስቶስ ስም እንዲሰደብ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ ስለ ጉዳዩ ማውራት እንጀምራለን፡፡ «ለእገሌ ትጸልይለታለህ? እባክህ በዝሙት ወድቋል፡፡ እገሌና እገሌ እየተጣሉ መሆናቸውን ታውቃለህ? ለእነዚህ ሰዎች መጸለይ አለብን፡፡ ስለ እኔ ምን እንዳለች ታውቃለህ?» እያልን ለሌሎች እናወራለን፡፡ ብዙውን ጊዜ በኀጢአት ስለወደቁት ወይም በጠብ ውስጥ ስላሉት ሰዎች መንፈሳዊ ሽሙጥን የተላበሰ ቃል እንናገራለን። ጉዳዩን በጸሎት ርእስነት ብናቀርበውም፥ የሚያስደስተን ስለተከሰተው ችግር ለሰዎች ማውራቱ ነው። ይህም ቤንዚን እንደ ተጨመረበት እሳት መከፋፈሉንና ኃጢአቱን ያባብሰዋል።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኃጢአትና መከፋፈል ሲደርስ እንድንጠቀምበት የተፈቀደልንን ብቸኛና ሦስተኛ አማራጭ ኢየሱስ ሰጥቶናል። እዚህ ላይ ችግሩን ቸል እንድንል ወይም ለሌሎች እንድናወራ አልተፈቀደልንም። እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት ኢየሱስ ያቀረባቸው ዘዴዎች ምንድን ናቸው?

ሀ. የኃጢአትንና የተበላሸ ግንኙነት ምክንያት መመርመር የእያንዳንዱ ክርስቲያን ኃላፊነት ነው፡፡ ክርስቶስ አንድ ሰው ከበደለን፥ ስለ ጉዳዩ ለመነጋገርና አለመግባባትን ለማስወገድ የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ እንዳለብን ተናግሯል። ነገር ግን የማቴዎስ 7፡1-5ን መርሆዎች ማወቁ ጠቃሚ ነው፡፡ ልባችንን በመመርመር የትኛውንም የኃጢአት “ምሰሶ”፥ ማለትም ጥላቻ ወይም ቁጣ ከሕይወታችን ማስወገድ አለብን፡፡ ከዚያ በኋላ በክርስተቶስ (ወንድማችን ወይም እኅታችን) ከሆነው ሰው ጋር ልንወያይ እንችላለን።

ለ. ችግሩ በወሬ መዛመት የለበትም፡፡ ስለ ጉዳዩ ደብዳቤ መጻፍም ሆነ ለጓደኛ ማውራት አያስፈልግም፡፡ በቀጥታ ወደ በደለን ግለሰብ ሄደን በደሉን በመግለጽ፣ ለኑዛዜ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርብናል። ዓላማችን ፍርድ ሳይሆን፥ ይቅርታና ዕርቅ መሆን አለበት፡፡

ሐ. የኃጢአቱ ምንነት ከታወቀ በኋላ፣ “ግለሰቡ ንስሐ ገብቶ ወደ እውነት ለመመለስ ካልፈለገ፣ ሁለት መንፈሳውያን ሰዎች ምስክር እንዲሆኑ አድርግ። እነዚህ አንተን የሚደግፉ ጓደኞችህ ላይሆኑ፥ ትክክለኛ ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ትክክል የሆነውን እና ስሕተት የሆነውን የሚለዩ እንዲሁም ግልጽ ብያኔ ሊሰጡ የሚችሉ መንፈሳውያን ሰዎች ሊሆኑ ይገባል። (ዋናው ነገር አንደኛው ጥፋተኛ መሆኑና ሌላኛው ትክክል መሆኑ ሳይሆን፥ ኃጢአትን ለማስወገድና የተበላሸውን ግንኙነት ለማደስ የማይፈልግ ሰው በሚያጋጥምበት ጊዜ እንዴት ምላሽ መሰጠት እንዳለብን ማወቁ ነው፡፡) አሁንም በሐቆቹ ላይ ውይይት ተካሂዶ አድልዎ የሌለበት ፍርድ መሰጠት አለበት። ሦስት ሰዎች ብቻ ጉዳዩን ማወቃቸው የግለሰቡን አእምሮ ለመለወጥና ወደ ንስሐ ለመምራት ሊቀልል ይችላል።

መ. ግለሰቡ ንስሐ ለመግባት ባይፈልግና ግንኙነቱ ባይጠገንስ? ለለ ጉዳዩ ልንዘናጋና እግዚአብሔር እንዲያስተካክለው ልንተወው ይገባልን? ኢየሱስ «አይሆንም!» ብሏል። ኃጢአትና መከፋፈል የኋላ ኋላ ጠቅላላይቱን ቤተ ክርስቲያን ስለሚያጠፉአት፣ እንደ እባጭ የሚወገድበትን መንገድ መፈለግ ያሻል። ስለሆነም፥ ሽማግሌዎቹ ጉዳዩን በግልጽ ወደ ቤተ ክርስቲያን ማምጣት አለባቸው። ችግሩን ገልጸው ለመፍታት የሞከሩባቸውን መንገዶች ማብራራት አለባቸው። ከዚያም ግለሰቡን (ካልታዘዝ) ከቤተ ክርስቲያን አባልነት መሰረዝ ይኖርባቸዋል። ግለሰቡን እንደ አረማዊ ወይም ቀራጭ መቁጠር ማለት መጥላትን ኣያመለክትም፡፡ ነገር ግን የቤተሰቡ አባል እንዳልሆነ መቍጠር ማለት ነው። የዚህ እርምጃ ዓላማ ኃጢአትን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፥ ዕርቅም ጭምር ነው። ጳውሎስ ይህንን ሂደት «ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት» ሲል ይጠራዋል (1ኛ ቆሮ. 5፡5)። ግለሰቡን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንክብካቤ በማስወጣታችን፥ እግዚአብሔር ንስሐ ይገባ ዘንድ እንዲፈርድበት መጠየቃችን ነው፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መከፋፈልን ስላስከተለ ወይም በማስከተል ላይ ስላለ ኃጢአት ግለጽ። የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ችግሩን ለማስተካከል ምን እርምጃ ወሰዱ? ለ) በማቴ. 18፡15-20 ላይ በመመሥረት እንዴት ሊያስተካክሉት ይገባ ነበር?

ኢየሱስ ክርስቲያኖችና ሽማግሌዎች ይህን ሂደት በሚከተሉበት ጊዜ፥ በሥልጣኑ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ገልጾላቸዋል። ኢየሱስ የዘረዘራቸውን ደረጃዎች ከተከተሉ በኋላ ግለሰቡን ለፍርድ አሳልፈው ሊሰጡ ይችላሉ። ይቅርታ ከተደረገም ግለሰቡ ሙሉ በሙሉ ይቅር መባሉን ሊያሳውቅ ይችላል። የክርስቶስ ደም ኃጢአትን ሁሉ ይሸፍናልና። ኢየሱስ አንድነት፥ ለመንፈሳዊ ጤንነትና ለቤተ ክርስቲያን ኃይል በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልጾአል፡፡ ክፍፍል ካለ፣ እግዚአብሔር ተግባሩን በሚገባ አያከናውንም፡፡ አንድነት ካለ ግን የሰዎቹ ቁጥር ሁለት ወይም ሦስት ቢሆንም፣ አማኑኤል የሆነው ኢየሱስ ጸሎታቸውን ለመስማት በመካከላቸው ይኖራል።

  1. ክርስቶስ ስለ ይቅርታና ምሕረት ኣስተማረ (ማቴ. 18፡21-35)

አንድ ሰው ሌላውን በመበደሉ ምክንያት ክፍፍል በሚከሰትበት ወቅት፥ ሁለት ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። በመጀመሪያ፣ ይቅርታንና ዕርቅን ያለመፈለግ ችግር ሊኖር ይችላል። ኢየሱስ የተበደለው ግለሰብ እንኳ ለዕርቅ የመጀመሪያውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ በመግለጽ፥ በመጨረሻው ክፍል ለዚህ ጉዳይ እልባት ሰጥቷል። አይሁዶች አንድ ሰው ሦስት ጊዜ ይቅር ማለት እንዳለበት ያምኑ ስለነበር፥ ጴጥርስ ሰባት ጊዜ ሲል ጉዳዩን ያጋነነው መስሉት ነበር፡፡ ክርስቶስ ቀን 490 ጊዚያት ማለትም ሁልጊዜ ይቅር ማለት እንዳለብን ተናግሯል በደልን መቁጠር የለብንም (1ኛ ቆሮ. 13፡5)።

ሌሎችን ይቅር ለማለት አለመፈለጉ ምን ያህል የሞኝነት ተግባር እንደሆነ ለማሳየት፣ ኢየሱስ የሁለት ባሪያዎችን ምሳሌ ተናገረ። አንደኛው ባሪያ ከጌታው እንድ ሚሊዮን ብር ተበድሮ ነበር። እንዲከፍል በተናገረው ጊዜ ምሕረት በመጠየቁ፣ ይቅር ተባለ። ሌላ ባሪያ አንድ ሚሊዮን ብር ከተበደረው ባሪያ ጥቂት ገንዘብ ተበድሮ ነበር፡፡ እንዲከፍለው በጠየቀው ጊዜ ምሕረትን እንዲያደርግለት ለመነው፡፡ ሰውዬው ግን ምሕረትን ለማድረግ ስላልፈለገ፥ አሳሰረው። የባሮቹ ጌታ ስለ ጉዳዩ በሰማ ጊዜ፣ የመጀመሪያውን ባሪያ በጭካኔው በከፋ ሁኔታ ቀጣው፡፡ በዚህ ምሳሌ ውስጥ በባሮቹ ጌታ የተመሰለው እግዚአብሔር ሲሆን የመጀመሪያው ባሪያ ሁላችንንም ይወክላል፡፡ ሁላችንም በእግዚአብሔር ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኃጢአቶች የፈጸምን ቢሆንም፥ ምሕረትን በጠየቅን ጊዜ ግን ይቅር ይለናል። ከዚህ እንጻር አንድ ሰው በእኛ ላይ የሚፈጽመው ኃጢአት የጥቂት ገንዘብ ዕዳ ያህል ነው። እንዲህ ዓይነቱን አነስተኛ ኃጢአት ይቅር ለማለት ባንፈልግ፣ የእግዚአብሔርን ጸጋና ምሕረት በትክክል አልተረዳንም ማለት ነው። ይህም ከእግዚአብሐር አሰቃቂ ቅጣት እንድንቀበል ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ሰዎች በቃል ብቻ ሳይሆን ከልባቸው ይቅር ለማለት ባለመፈለጋቸው አለመስማቶችና ክፍፍሎች እየጨመሩ ይሄዳሉ። ለዚህ አንድ ምሳሌ ስጥ፡፡  ለ) የሌሎችን ኃጢአት ይቅር ለማለት በማንፈልግበት ጊዜ፥ ኢየሱስ አግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ስለ ማለቱ ምን አስተማረ? ሐ) በቤተ ክርስቲያንህ ክፍፍል ካለ፣ ይህንን ምንባብ እንዴት አድርገህ ታስተምራለህ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: