ማቴዎስ 20፡1-34

  1. የወይን ሠራተኞች ምሳሌ (ማቴ. 20፡1-16)

ሁላችንም ፍትሐዊ ስለሆነውና ስላልሆነው ጉዳይ ጠንካራ ግንዛቤ አለን። አንድ ሰው እኛ የምንሠራውን ሥራ እየሠራ የበለጠ ደመዎዝ ቢያገኝ እናማርራለን። በዚህም ሁሉም ሰው እኩል ሊስተናገድ እንደሚገባ እናስባለን። ይሁንና፥ እግዚአብሔር ፍትሐዊ ነው? ሁሉንም ሰው በእኩል ደረጃ ያስተናግዳል? ወይስ እግዚአብሔር የሚሠራው በፍትሐዊነት ሳይሆን በጸጋ ይሆን? ኢየሱስ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ላለማነጻጸር ወይም እግዚአብሔር በእኩል ደረጃ እያስተናገደን መሆኑን ለመፍረድ የሚያስችል ምሳሌ ተናግሯል።

ርስት የነበረው አንድ ሀብታም ሰውዩ ነበር፡፡ ይህ ሰው ሠራተኞችን ለመቅጠር ፈለገና ጠዋት በሁለት ሰዓት ላይ ወደ ከተማ ሄዶ፥ የተወሰኑ ሰዎችን አንድ ዲናር ለመክፈል ተስማምቶ ቀጠረ። አንድ ዲናር በዘመኑ የአንድ ቀን ደመወዝ ነበር፡፡ አሁንም በሦስት ሰዓት፣ በቀትርና በዘጠኝ ሰዓት ወደ ከተማ ተመልሶ ሄዶ ሌሎች ሠራተኞችን ቀጠረ። ለእነዚህ ሰዎች አከፋፈሉ ፍትሐዊ እንደሚሆን እንጂ ስንት እንደሚከፍላቸው አልነገራቸውም ነበር። ደመወዛቸውን የሚከፍልበት ጊዜ ሲደርስ አርፍዶ ለቀጠራቸው ሰዎች ቅድሚያ ሰጠ። ለእነዚህ ሰዎች የሙሉ ቀን ደመወዝ ነበር የከፈላቸው። ቀኑን ሙሉ ሠርተው የዋሉት ሰዎች ይህንን ሲመለኮቱ ደስ አላቸው። ለእነርሱ የበለጠ የሚከፍላቸው መስሏቸው ነበር። ባለ ሀብቱ ግን ለሁሉም እኩል አንድ ዲናር ሰጣቸው። “ይሄ ፍትሐዊ አይደለም” ብለው ቅር አላቸው። ቀኑን ሙሉ ሲሠራ የዋለው ሰውዬ ያማርር ጀመር። ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራው በፍትሐዊነት ሳይሆን በጸጋ ነው። ሞግሱን የምናገኘው በጥረታችን ሳይሆን በነጻ ነው። ስለሆነም፥ ባለ ሀብቱ ለሁሉም ቃል የገባውን ስለ ሰጠ ፍትሐዊ ነበር።

እነዚሁ መርሆዎች ለእግዚአብሔርም መንግሥት ይጠቅማሉ። እኛ ፍትሐዊነትን በምንረዳበት መልኩ እግዚአብሔር ቢሠራ ማናችንም ከዘላለም ፍርድ በስተቀር፥ ከእግዚአብሔር ምንም ነገር ልንቀበል አንችልም ነበር። ስለሆነም ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ነገር ሁሉ ነፃ የጸጋ ስጦታ ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር አንድ ከእኛ በላይ የስብከት ችሎታ ያለው ሰው መርጦ ከእኛ በላይ ቢከፍለው፥ ራሳችንን ከዚያ ሰው ጋር የማወዳደርም ሆነ የማማረር መብት የለንም። ምክንያቱም የተቀበልነው የሥራችንን ውጤት ሳይሆን ነጻ ስጦታ ስለሆነ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ራሳችንን ከሌሎች ሰዎች ጋር ስናነጻጽርና ከእግዚአብሔር ዘንድ እኩል ወይም ፍትሐዊ መስተንግዶ እየተደረገልን እንዳልሆነ ስናስብ፥ እንዴት እንደምናዝን ወይም እንደምንቀና የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ። ለ) በዚህ ምሳሌ መሠረት፥ ሌሎች ከእኛ የበለጡ በሚመስልበት ጊዜ ኢየሱስ ምን ዓይነት ምላሽ እንድንሰጥ የሚፈልግ ይመስልሃል?

  1. ኢየሱስ አሁንም በመንግሥቱ ስለሚኖረው አመራር አስተማረ (ማቴ 20፡17-28)

ኢየሱስ በገሊላና ከሊላ ውጭ ያካሄደውን አገልግሎት ፈጽሞ ወደ ኢየሩሳለም በመጓዝ ላይ ነበር፡ ሊሰቀል ጥቂት ወራት ብቻ ቀርተውታል። በመንገድ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ፥ ስለ መጭው ሞቱና ትንሣኤው ቢናገራቸውም፥ አእምሯቸው በግል ጉዳዮች ተይዞ ነበር። በጉዞ ላይ ሳሉ የያዕቆብና የዮሐንስ እናት ወደ ኢየሱስ መጥታ፥ ሁለቱ ልጆቿ ከእርሱ ቀጥሎ ከፍተኛ ሥልጣን እንዲኖራቸው ጠየቀች፡፡ ይህ ከፍተኛ ሥልጣን የመፈለጉ አዝማሚያ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክፍፍልን እንዳያስከትል ያሰጋ ነበር፡፡ ስለሆነም ኢየሱስ እንደገና ለዚህ ችግር በመመለስ ለደቀ መዛሙርቱ ሦስት ጠቃሚ ትምህርቶችን ሰጥቷል።

ሀ. በእግዚአብሔር መንግሥት፤ መሪነት የሚገኘው የስደትን «ጽዋ» በመጠጣት ነው፡፡ ይህም የኢየሱስ መንገድ ወደ መስቀልና ሞት እንደመራው መሆኑ ነው።

ለ. ለእያንዳንዱ ግለሰብ የሚሰጠውን የመሪነት ደረጃ የሚወስነው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በምድራዊ መንግሥት፥ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሰማያዊ መንግሥት ነገሮች የሚወሰኑት በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ነው። ስለሆነም ማንም ሰው ለመሪነት ሊታገልም ይህን ዕድል በሚያገኙት ላይ ሊቀና አይገባውም፡፡

ሐ. የእግዚአብሔር መንግሥት አመራር፥ ከሰው መንግሥት አመራር የተለየ ነው። አመራር ዝናን፥ ሀብትንና ሥልጣንን በማምጣትና በኃይል የሚፈጸም ላይሆን፥ መሥዋዕትነትንና ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቅ ነው። በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ከሁሉም የሚበልጠው መሪ፣ በከፍተኛ ትሕትናና መሥዋዕትነት ሌሎችን የሚያግለል ነው። ነገር ግን አምላክ የሆነው ክርስቶስ የተናገረው ስለዚህ ጉዳይ ብቻ አልነበረም። እርሱ አምላክ በመሆኑ ሰዎች እንዲያከብሩት፥ ገንዘብ እንዲሰጡት፥ እንዲያመልኩት፣ ጥሩ ቤት እንዲያዘጋጁለት ሊጠይቅ ሲችል፥ እርሱ ይህን ሁሉ አልፈለገም፡፡ ድሀ ሆኖ እየተመላለሰ ሕይወቱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሰጠ። “ቤዛ” አንድን ባሪያ፣ ነጻ ለማውጣት የሚከፈለውን ዋጋ ያመለክታል። ክርስቶስ በሞቱ እንድንወጣ የሚያስፈልገውን የኃጢአት ዋጋ ከፍሎልናል። መንፈሳዊ መሪዎችም ሕይወታቸውን ለሌሎች አሳልፈው መስጠት ስላለባቸው ሰማያዊ ዋጋ መክፈል ይኖርባቸዋል።

የውይይት የያቄ:- በቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ መሪ መሆን የሚያስከፍላቸውን የተለያዩ መንፈሳዊ ዋጋዎች ዝርዝር

  1. ኢየሱስ ሁለት ዓይነ ስውራንን ፈወሰ (ማቴ 20፡29-34)

ኢየሱስ ለሁለት ዓይነ ስውራን በሰጠው ምላሽ፣ የመሢሕነት ኃይሉን ከማሳየቱም በላይ አመራር እንዴት ሊካሄድ እንደሚገባ ምሳሌ ሰጥቷል። አይነ ስውራኑ ኢየሱስ የዳዊት ልጅ እንደሆነ በመግለጽ እንዲፈውሳቸው ተማጥነውታል። ምንም እንኳ ሥራ ቢበዛበትና ወደሚሞትባት ኢየሩሳሌም በመሄድ ላይ የነበረ ቢሆንም፥ ኢየሱስ የዓይነ ስውራኑን ልመና በማድመጥ ዓይኖቻቸውን ፈውሷል። ይህ ራሱን ለሰዎች አሳልፎ እንደ ሰጠ ያመለክታል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading