ያለማመንን የሚገልጹ ሦስት ምሳሌዎች (ማቴ. 21፡28-22፡14)

ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎች በጥያቄ ጥቃታቸው እንዲገፉበት ከመፍቀድ ይልቅ በምሳሌዎች ተጠቅሞ በእርሱ ያለማመን ስለሚያስከትለው ውጤት መግለጽ ጀመረ።

ሀ. የሁለት ልጆች ምሳሉ (ማቴ 21፡28-32)። ክርስቶስ በምሳሌው እንደ ገለጸው፥ እንደኛው ልጅ መጀመሪያ አባቱ የሰጠውን ትእዛዝ ላለመፈጸም ይወስናል። በኋላ ግን በልቡ ተጸጽቶ የታዘዘውን ይፈጽማል። ሁለተኛው ልጅ ግን የተሰጠውን ተግባር እንደሚያከናውን ቢናገርም፥ ቃሉን በሥራ ሳይተረጉም ይቀራል። የመጀመሪያው ልጅ ፈሪሳውያን እንደሚንቋቸው የታወቁ ኃጢአተኞች፥ ቀራጮችና ሴተኛ አዳሪዎች ነበር። እነዚህ ሰዎች በግልጽ በእግዚአብሔር ላይ ቢያምፁም፥ በዮሐንስና በኢየሱስ ትምህርት አማካኝነት ንስሐ ገብተው ሕይወታቸውን ለውጠዋል። ስለሆነም፥ እግዚአብሔር ተቀብሏቸዋል። ፈሪሳውያን እንደ ሁለተኛው ልጅ ብዙ ሕጋትን ለመጠበቅ ታዘዋል። ነገር ግን ፈሪሳውያን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እግዚአብሔርን ስላልታዘዙት፥ የእግዚአብሔርን ፍርድ ይቀበላሉ።

ለ. የገባሮች ምሳሌ (ማቴ. 21፡33-46)። ሁለተኛው ምላሌ ርስቱን ለገባሮች ስላከራየው የመሬት ባለቤት ይናገራል። ብዙውን ጊዜ የመሬቱ ባለቤት እንደ ዘር ያሉትን ነገርች ለመስጠት፥ ገባሮቹ ደግሞ ሥራውን አከናውነው የተወሰነውን እጅ ለባለቤቱ ለመስጠት ይስማማሉ። ባለቤቱ የድርሻውን የሚቀበልበት የመከር ጊዜ ሲደርስ፥ ባሮቹንና የኋላ ኋላ ልጁን ቢልክም፣ ገባሮቹ ለመተባበር አልፈቀዱም፣ ኣንዳንድ ባሮችንና በመጨረሻም የወይኑ እርሻ ወራሽ የሆነውን ልጁን ገደሉ።

እስራኤል የእግዚአብሔር ወይን መሆኗን ከብሉይ ኪዳን እንረዳለን። (ኢሳ 5ን አንብብ።) እግዚአብሔር መሪዎቹ እስራኤልን እንዲመሩ መብት ሰጥቷቸው ነበር። እነርሱ ግን ራስ ወዳዶች በመሆናቸው፥ መብታቸውን አላግባብ ተጠቀሙ። እግዚአብሔር የላካቸው ባሪያዎች የብሉይ ኪዳን ነቢያትና መጥምቁ ዮሐንስ ነበሩ። ነገር ግን አብዛኞቹ መሪዎችና ሕዝብ ሊሰሟቸው አልፈለጉም። በመጨረሻም እግዚአብሔር ልጁን ላከ። ኢየሱስ እርሱንም ብዙም ሳይቆይ እንደሚገድሉት ተነበየ፡፡

ኢየሱስ ትክክለኛው ፍርድ ምን ሊሆን እንደሚገባ ሕዝቡን ጠየቀ። የፈሪሳውያንና የሰዱቃውያን የራስ ወዳድነት አገዛዝ ያሰለቻቸው ተራ ሰዎች ኢየሱስ የሚያስተላልፈውን መልእክት ሳይረዱ አልቀሩም፡፡ ስለሆነም፥ እግዚአብሔር መሪዎቹን ሙሉ በሙሉ አጥፍቶ በሌሎች እንደሚተካቸው ተናገረ፡፡ በ70 ዓ.ም. ጠቅላሳዎቹ ሰዱቃውያን ሲገደሉና ፈሪሳውያንም በአይሁዶች ላይ የነበራቸውን ሥልጣን ሲነጠቁ የተከሰተው ይኸው ነበር። ይህ ቀን ከመሪዎች ቅጣት ያለፈ ነበር። ጠቅላላው የአይሁድ ሕዝብ ኢየሱስን እንደ መሢሓቸው ባለመቀበላቸው ተፈርዶባቸዋል። የእግዚአብሔር ወይን የመሆኑ በረከትም ለአሕዛብ ተሰጠ።

ኢየሱስ ይህ ሁሉ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደሚፈጽም ገልጾአል። እርሱ አይሁዶች ለእግዚአብሔር ሕንጻ አይጠቅምም ብለው የጣሉትና እግዚአብሔር ግን የማዕዘን ራስ ያደርገው መሢሕ ነበር። እንደማይጠቅም አድርገው የጣሉት ድንጋይ በናቡክደነፆር ሕልም ውስጥ ታላቅ ሆኖ የታየው ነበር (ዳን. 2፡44-45)። እርሱ ሙሉ በሙሉ ያጠፋቸዋል፡፡

ሐ. በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ (ማቴ. 22፡1-14)።

ብዙውን ጊዜ አይሁዶች የመሢሑ መንግሥት እንደ የሰርግ ግብዣ ታላቅ እንደሚሆን ያስቡ ነበር። ስለሆነም፥ ኢየሱስ የንጉሥ ልጅ ስለሚያገባበት ሰርግ ምሳሌ ተናገረ። ታላላቅ ሰዎች የተባሉት ሁሉ ቢጠሩም፥ ማመኻኛዎችን ሰጥተው ለሰርጉ ከመታደም ታቅበዋል። ይጠሯቸው ዘንድ ባሪያዎቹን ሲልካቸው፥ ባሪያዎቹን አጉላሏቸው፤ አንዳንዶቹንም ገደሏቸው። ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ ሠራዊቱ ሄዶ እንዲያጠፋቸው አዘዘ። ከዚያም ንጉሡ አድራሻ ያልነበራቸውን ድሆች ከመጋበዙም በላይ፥ ለሰርጉ የሚስማማ ነፃ ልብስ አደላቸው። ኣንድ ሰውዬ በነፃ የተሰጠውን ልብስ ለመልበስ ባለመፈለጉ የእድምተኝነት ዕድሉን አጣ።

ንጉሡ እግዚኣብሔርን ሲወክል፥ ሙሽራው ክርስቶስን ያሳያል። ሰርጉ እግዚአብሔር ለሰዎች የሚሰጠው ደኅንነትና በረከት ያመለክታል፡፡ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎች አይሁዶች ግን በክርስቶስ በኩል የቀረበውን የደኅንነት ስጦታ ለመቀበል ባለመፈለጋቸው፥ ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ንቀት አሳይተዋል። ከዚህም የተነሣ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ ወገኖች ላይ በመፍረድ ያጠፋቸዋል። እግዚአብሔር የተናቁትን ኃጢአተኞችንና አሕዛብን ጨምሮ ለሁሉም የደኅንነትን ስጦታ ይሰጣል። የጽድቅ ልብሱንም እንዲሁ ይሰጣቸዋል። ነገር ግን በራሳቸው የጽድቅ ልብሶች በመተማመን፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ በማመን የሚሰጠውን የጽድቅ ልብስ ላለመቀበል ከወሰኑ፥ ወደ እግዚአብሔር መንሥት የመግባቱን በረከት ተነፍገው ወደ ዘላለማዊ ሲዖል ይወርዳሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ከእነዚህ ምሳሌዎች እግዚአብሔር ስለሚሠራበት መንገድ፣ ስለ ሰዎች ማንነትና ስለ ራሳችን ኃላፊነት ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: