ማቴዎስ 22፡15-46

  1. የሄሮድስ ደጋፊዎች ኢየሱስን ለማጥመድ ያነሡት ሁለተኛው ጥያቄ (ማቴ 22፡15-22)

መሪዎቹ ኢየሱስን በሃይማኖታዊ ጥያቄዎች ሊያታልሉት ስላልቻሉ፣ ፊታቸውን ወደ ፖለቲካ መለሱ፡፡ የሄሮድስ ደጋፊዎች በይሁዳ ላይ ለመንገሥ የቻሉት በተለያዩ የሄሮድስ ዝርያዎች ድጋፍ ነበር። የእነዚህ ሰዎች ፍላጎት ሃይማኖት ሳይሆን ፖለቲካ ነበር፡፡ ኢየሱስ በእስራኤል ከነገሠ ኃይላቸው ስለሚከስም፥ ኢየሱስ ለእነርሱ የስጋት ምንጭ ነበር፡፡ ስለሆነም፥ ፖለቲካዊ የቀረጥ ጥያቄ አንሥተው ኢየሱስን ለማጥመድ ሞከሩ። ኢየሱስ የቀረጥን መከፈል ባይደግፍ በሮማውያን ፊት ሊከሱትና ሊያሳስሩት ይችሉ ነበር። የቀረጥን መክፈል ቢደግፍ ደግሞ የሕዝቡን ድጋፍ ያጣ ነበር። ሕዝቡ ይህ የሮማውያንን አገዛዝ እንደሚያሳይ በመገንዘብ ቀረጥ መክፈልን ይጠሉ ነበር፡፡ ቀረጥ በመክፈል የሚታየውንና ምድራዊውን መንግሥት መታዘዝ ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም የቄሣር ምስል ባለበት የሮማውያን ሣንቲም ምልክትነት ተገልጾአል። ለመንፈሳዊ መንግሥት ደግሞ ቀዳሚ ታማኝነታቸውን በመስጠት መታዘዝ ያስፈልጋቸው ነበር።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ቀረጦችን ወይም መንግሥት የሚፈልጋቸውን ክፍያዎች ላለመክፈል ይሞክራሉ፡፡ ክርስቶስ ስለዚህ ጉዳይ ምን የሚል ይመስልሃል? ለ) ክርስቲያኖች የሆንን ከምድራዊ መንግሥታችን በላይ መንፈሳዊ መንግሥታችንን እንዴት ልናከብር እንደምንችል ምሳሌ ጥቀስ።

  1. ሰዱቃውያን ኢየሱስን ለማጥመድ የሞከሩበት ሦስተኛው ጥያቄ (ማቴ 22፡23-33)

ሰዱቃውያን በአብዛኛው የሊቀ ካህንነቱንና የሃይማኖታዊ አመራሩን ሥልጣን የተቆጣጠሩ ካህናት ነበሩ፡፡ ብዙውን ጊዜ ፖለቲካውም በእነርሱ ቁጥጥር ሥር ነበር፡፡ በሥነ መለኮታዊ ክርክር ኢየሱስን ለማጥመድ ሞከሩ። ሰዱቃውያን በትንሣኤ ስለማያምኑ ይህ ጥያቄ የቀረበው እውነትን ለመሻት ሳይሆን ለክርክር ነበር፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ወንድምየው ሚስቱን እንዲያገባ ይደረግ ነበር፡፡ በዚህ ጋብቻ የተወለደው የመጀመሪያው ልጅ የሟች ልጅ እንደሆነ ተቆጥር የቤተሰቡን የዘር ሐረግ ይቀጥላል፡፡ ሰዱቃውያን ይህን ሕግ ለመፈጸምና ልጅ ለመውለድ በመሞከር ሰባት ወንድማማቾች አንዷን ሴት ስላገቡበት ሁኔታ የሚተርክ የፈጠራ ታሪክ ነገሩት፡፡ ሁሉም ከሞቱ በኋላ በዳግም ትንሣኤ ይህች ሴት የማን ሚስት ትሆናለች? ሊሉ ጠየቁት።

ኢየሱስ ትርጉም የማይሰጥ ሥነ መለኮታዊ ክርክር ለማካሄድ ስላልፈለገ፥ ወደ ጉዳዩ ሥር ዘልቆ የተሳሳተ ሥነ መለኮታዊ ግንዛቤ እንደነበራቸው አመለከተ። በመጀመሪያ የትንሣኤ አካለ ሥጋዊ ጋብቻን እንደማይቀበል አለመገንዘባቸውን አወዝ፡፡ ከሙታን የተነሡ ሰዎች ሚስት አግብተው ልጅ እንደማይወልዱና እንደ መላእክት እንደሚሆኑ ገለጸላቸው። ሁለተኛ፥ በትንሣኤ ባለማመናቸው ሙሉ በሙሉ መሳሳታቸውን በማመልከት ወቀሳቸው። ኢየሱስ ሰዱቃውያን እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚቀበሉትን የዘፍጥረት 1 መጽሐፍ በመጠቀም (ከሙሴ ሕግ ውጭ ያሉትን መጻሕፍት ሁሉ አይቀበሉም)፣ አብርሃም፥ ይስሐቅና ያዕቆብ ከሞቱ በኋላ እንደ ሕያዋን እንደተጠቀሱ አሳያቸው። እግዚአብሔር “እኔ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነበርኩ” ሳይል፥ “እኔ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ” ብሏል። እነዚህ ሰዎች በሥጋ ቢሞቱም በመንፈሳቸው ሕያዋን ሆነው የትንሣኤን እውነተኛነት ያረጋግጣሉ።

  1. ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማጥመድ ያነሡት አራተኛው ጥያቄ (ማቴ 22፡34-40)

ከብሉይ ኪዳን ሕግጋት እጅግ አስፈላጊው የትኛው ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ የሃይማኖት መሪዎች በተደጋጋሚ ይከራከሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግጋት የሚያስፈልጉና የማያስፈልጉ ብለው ለሁለት ለመክፈል በመቻላቸው አንዳንዶቹን ሊጠብቁና ሌሎቹን ሊተዉ እንደሚችሉ ያስቡ ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ አርቀው ከሚመለከቱት አምላካቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ብዙም አያሳስባቸውም ነበር። ምክንያቱም ለእነርሱ ዋናው ነገር ሕግጋትን መጠበቅ ነበር፡፡ ኢየሱስ ግን የእግዚአብሔርን ሕጋት ሁሉ የሚያካትቱ ሁለት ትእዛዛት ነበሩት። እነዚህም አድርጉ አታድርጉ በሚባሉ ዝርዝሮች ብቻ የሚፈጸሙ ሳይሆኑ፥ በግንኙነት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን በመግለጽ የሥነ መለኮት አስተምህሯቸውን አናግቷል። በፍጹም ማንነትህ እግዚአብሔርን አክብር የሚለው ትእዛዝ፥ ሁሉንም አምልኮና ከእግዚአብሔር ጋር የመዛመድን ሕግጋት ያካትታል። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለው ደግሞ ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት ያጠቃልላል። ፍቅር ልባችንን እስከገዛው ድረስ፥ ተግባራችን ትክክል ስለሚሆን፥ ሌሎች ሕግጋት በሙሉ ተግባራዊ ይሆናሉ።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚዛመዱ ትእዛዞችን ዘርዝር። በሙሉ ልብ መውደድ የሚለው ትእዛዝ እነዚህን ትእዛዞች የሚፈጽመው እንዴት ነው? ለ) ከሌሎች ሰዎች ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚዛመዱ ትእዛዞችን ዘርዝር። ራሳችንን የምንወደውን ያህል ሌሎችንም መውደድ አለብን የሚለው ትእዛዝ እነዚህን ትእዛዞች የሚፈጽመው እንዴት ነው?

  1. ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎቹን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው (ማቴ. 22፡41-46)

ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎቹን በጥያቄዎቻቸው በሙሉ ከረታ በኋላ፥ ጥያቄ የመጠየቁ ተራው የእርሱ ሆነ። መሲሑ የማን ልጅ እንደሆነ ጠየቃቸው። መሲሑ የዳዊት ልጅ ነው የሚለውን የተለመደውን መልሳቸውን ሰጡት። ነገር ግን ኢየሱስ ስለ መሲሑ በመዝ. (110)፡1 የተተነበየውን በመጥቀስ፥ እግዚኣብሔር መለኮትነቱን ለማመልከት «ጌታ» ብሎ እንደጠራው ነገራቸው። ኢየሱስ ከአይሁዶች ጋር መከራከሩን አልፈለገውም። ይልቁንም፥ እርሱ የሚፈልገው ዓይኖቻቸውን ከፍቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ሌሎች እውነቶችን እንዲመለከቱና እርሱን እንደ ዳዊት ልጅ ሳይሆን፥ እንደ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲያውቁት ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: