ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና የኦሪት ሕግ መምህራንን ነቀፈ (ማቴ. 23:1-39)

የክርስቶስን ሕይወት የመጨረሻ ሳምንት ሁኔታ ባጠናንበት ወቅት ማቴዎስ የሃይማኖት መሪዎች ከክርስቶስ ጋር ያካሄዷቸውን አያሌ ግጭቶች እንዴት እንደገለጸ ተመልክተናል። አይሁዶች፥ «ክርስቶስ መሢሕ ከሆነ፥ ለምን ተሰቀለ? እርሱ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ ከሆነ፥ የሃይማኖት መሪዎች ለምን አልተከተሉትም?» እያሉ ይጠይቁ ነበር። ማቴዎስ የሃይማኖት መሪዎቹ ክርስቶስ ምን ዓይነት መሢሕ እንደነበረ እንዳልተገነዘቡና፥ ከሁሉም በላይ በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን ቅናት በመግለጽ ለእነዚህ ጥያቄዎች የመሰላቸውን መስጠታቸውን ጽፎአል። የሃይማኖት መሪዎቹ ክርስቶስን የተቃወሙት አንዳች ስሕተት ስላገኙበት ሳይሆን፥ እግዚአብሔርን ለመከተልና ሰዎችን ለመርዳት ባልነበራቸው ፍላጎት ተመርተው ነበር።

ማቴዎስ 23-25 የክርስቶስን ትምህርት የሚያቀርብ የመጨረሻው ዐቢይ ክፍል ነው። ይህ ክፍል የፈሪሳውያንን ሃይማኖትና ስለመጨረሻው ዘመን የሚያስተምሩትን ትምህርት መከተል እንደማይገባን ያስጠነቅቃል።

ክርስቶስ በሃይማኖት መሪዎች ላይ ስምንት የ«ዋይታ» ፍርዶችን አስተላልፎአል (ማቴ. 23)

ክርስቶስ በሥልጣን ላይ የተቀመጡት ማለትም (የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ) ሰዎች በሚያጠፉበት ጊዜ ተከታዮቹ ዓመፅ እንዲያካሂዱ አላስተማረም! ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ በመታዘዝና ተቀባይነትን በማግኘት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲማሩ ነግሯቸዋል። ለሃይማኖት መሪዎች የሃይማኖት ሥልጣን የሰጣቸው እግዚአብሔር ነው። ስለሆነም፥ በዚያን የታሪክ ወቅት እግዚኣብሔር ፈሪሳውያን «በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠው»፥ በሕዝቡ ላይ ሃይማኖታዊ ሥልጣን እንዲያካሂዱ ፈቅዶላቸዋል።

ነገር ግን ለፈሪሳውያንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች መታዘዝ ማለት በሚያደርጓቸውን እኩይ ተግባራት መሳተፍን አይጨምርም፡፡ እንደ ብዙ ሰባኪዎች፥ ፈሪሳውያን የሚመላለሱት በሁለት ደረጃዎች ነበሩ። ሲያስተምሩ ወይም ሲሰብኩ፥ በሰዎች ላይ ብዙ ትእዛዛትን ያሸክሙ ነበር። እነርሱ ግን በግል ሕይወታቸው አይፈጽሙትም ነበር። እነዚህ ሰዎች ሕዝብ እንዲጾም እያዘዙ እንደማይጾሙ፥ ወይም ወንጌሉን ለጎረቤቶቻቸው እንዲመሰክሩ እየተናገሩ ራሳቸው እንደማይመሰክሩ ሰባኪዎች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች ብዙውን ጊዜ ተግባራዊ የማያደርጓቸውን ነገሮች እንዴት እንደሚሰብኩ ምሳሌዎችን ስጥ። ለ) እንደሚገባቸው በመንፈሳዊነት ለማይመላለሱ መሪዎች ክርስቶስ ምላሻችን (በተለይም ወጣቶች) ምን መሆን እንዳለበት ኣስተማረ?

ክርስቶስ ተከታዮቹ የሃይማኖት መሪዎችን በመምሰል ለሰው ምስጋናና ክብር እንዳይኖሩ ተናግሯል። በገላትያ 1፡10 ጳውሎስ፥ «ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም» ብሏል። መሪዎች ሁለት ምርጫዎች አሏቸው። እግዚአብሔርን ወይም ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ወስነው መሥራት፡፡ ፈሪሳውያን በአብዛኛው ለአገልግሎት የሚነሣሡት የሰዎችን ምስጋና ለማግኘት ነበር። ስለሆነም የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ በግንባራቸው ላይ ሰፋፊ አሸንክታቦችን ያደርጉ ነበር (ዘዳግ. 6፡4-9 አንብብ።) እንዲሁም በብዙ ጥለት ያጌጡ ማራኪ ሃይማኖታዊ ልብሶችን ይለብሳሉ። በምኩራብ ውስጥ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፥ «እዩን፥ እኛ የሃይማኖት መሪዎች ነን» በሚል አመለካከት የፊት ወንበር ይዘው ይቀመጣሉ። በዚህም ከአመራር የሚገኘውን ክብር ይፈልጉ ነበር። ሰዎች «ረቢ» (መምህር) እያሉ በአንቱታ ይጠሯቸዋል። ዛሬም ቢሆን በትምህርታቸው የገፉ ሰዎች «ዶክተር» ተብለው ለመጠራት እንደሚፈልጉት ማለት ነው።

ክርስቶስ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳይኖራቸው አስጠንቅቋቸዋል። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ በሁለት መንገዶች ይህን አመለካከት መዋጋት ነበረባቸው። በመጀመሪያ፥ በሥራዎቻቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅነት ማጉላት ያስፈልጋቸው ነበር። እግዚአብሔር ሰብአዊ መምህራንን ቢጠቀምም፥ መንፈሳዊ ስኬት ሊገኝ የሚችለው እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ያስተማረ እንደሆነ ነው (ዮሐ 14፡26)። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ሰብአዊ መሪዎችን ቢሾምም፥ የሁሉም መሪ የሆነው እርሱ ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ኃይል፥ ከብርና ሀብት ከመፈለግ ይልቅ፥ ትሕትናንና ዝቅ ብሎ ማገልገልን ሊያከብሩ ይገባል። ብዙውን ጊዜ ቢናቁና በሰዎች ዘንድ ባይከበሩም፥ ራሳቸውን የሚያዋርዱ ሰዎች በእግዚአብሔር መንግሥት ከሁሉም ይልቃሉ። የመሪነትን ክብርና ጥቅሞች የሚፈልጉ ሰዎች፥ በእግዚአብሔር ዓይን ምንም ካልተማሩት ምእመናን አንሰው ይታያሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ የሰይጣን ወጥመድ ውስጥ የወደቀን አንድ መሪ በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በትሕትና እግዚአብሔርን ቢያከብሩ የቤተ ክርስቲያን አመራር እንዴት ሊለወጥ ይችላል?

ክርስቶስ በፈሪሳውያን ላይ ሰባት የዋይታ ፍርዶችን ሰንዝሯል። (የተጠቀሱት ስምንት ዋይታዎች ሲሆኑ፥ ቀጥለን እንደምንመለከተው፥ አንደኛው ዋይታ በመጀመሪያው መጽሐፍ ውስጥ ያልተካተተ ይመስላል።) «ዋይታዎች» ከፍተኛ ቅጣት ያስከተሉ የፍርድ መግለጫ ቃላት ናቸው። በእነዚህ በሰባቱ ዋይታዎች ክርስቶስ ፈሪሳውያንን «ግብዞች» ብሏቸዋል። በግሪክ ቋንቋ “ግብዝ” የሚለው ቃል ከድራማ የመጣ ቃል ነው። በድራማ ውስጥ ሰዎች ያልሆኑትን ባሕርያት ወክለው ይጫወታሉ። መንፈሳዊ ግብዝ በርግጥ መንፈሳዊ ሳይሆን፥ ነኝ እያለ የሚኖር ሰው ነው።

ሀ. ዋይታ 1፡ ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዳይገቡ ስለ ከለከሉ፥ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ቁ. 13)። ክርስቶስን ለመከተል ባለመፈለጋቸው፥ ፈሪሳውያን ወደ ክርስቶስ መንግሥት አይገቡም። እንዲሁም በሥልጣናቸው ተጠቅመው ሌሎችም በክርስቶስ አምነው እንዳይድኑ ስለሚያደርጉ፥ እግዚአብሔር ከፍተኛ ፍርድ ያደርስባቸዋል።

ለ. ዋይታ 2፡ የደካሞችን መብት በመጣሳቸው፥ እግዚአብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ቁ. 14)። ፈሪሳውያን ረዥም ጸሎት በመጸለይ፥ ምናልባትም እግዚኣብሔር ድሆችን እንዲረዳ በመጠየቅና መንፈሳዊ ለመምሰል በመሞከራቸው ክርስቶስ አውግዞአቸዋል። መሪዎቹ ለድሆች ምሕረትን ስላላሳዩና ሀብታቸውን ለመበዝበዝ ስለጣሩ፥ እግዚአብሔር ፈርዶባቸዋል።

ዋይታ 3፡ ሰዎችን ሃይማኖታዊ ባሪያዎች ስላደረጉ፥ እግዚአብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ቁ. 15)። ፈሪሳውያን ሰዎችን ወደ አይሁድ እምነትና ወደ ራሳቸው አመለካከት ለመመለስ ከፍተኛ ተግባር ያከናውኑ ነበር። እነርሱም ሰዎች ሕጋቸውን እንዲያከብሩ፥ የፖለቲካ ቡድናቸው አባላት እንዲሆኑ በማስገደድና የሌላ ቡድን አባል ከሆኑ ደግሞ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ በባርነት ይገዟቸው ነበር። በምድር ላይ ሕይወታቸው በሸክሞች የተሞላ ነበር። በተጨማሪም፥ ፈሪሳውያን ተከታዮቻቸው እውነትን እንዳያውቁ በመከልከል ወደ ዘላለማዊ ፍርድ የሚጓዙ የሲዖል ልጆች አድርገዋቸው ነበር።

መ. ዋይታ 4፡ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ላለመጠበቅ ሊሉ ሕግጋቱን በማጣመማቸው፥ እግዚአብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ቁ. 16-22)። ጥሩና መጥፎ ስለሆኑት ነገሮች ፈሪሳውያን ሕግጋትን በሚያወጡበት ጊዜ፥ በራሳቸው ሕይወት ላይ ችግርን አስከተሉ። ስለሆነም፥ ሕጉ የተሰጠበትን ምክንያት ዘንግተው፥ ዙሪያ ጥምጥም ተግባር ለማካሄድ የሚችሉበትን ጥረት ሁሉ አደረጉ። ይህን ከሚያደርጉባቸው መንገዶች አንዱ፥ ለእግዚአብሔር ስጦታ ለመስጠት ቃል በሚገቡበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የአንድ ወር ደመወዙን ለመስጠት ቃል ገብቷል እንበል። በኋላ ግን ገንዘቡን ለራሱ ለማስቀረት ይፈልጋል። ፈሪሳውያን ይህን ለማድረግ የሚቻልበት መንገድ እንዳለ ያስተምሩ ነበር። ሁለት ዓይነት ስለቶች እንዳሉ ያስረዳሉ። አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ወይም በእግዚአብሔር ፊት ከተሳለ ስዕለቱን ማፍረስ አይችልም። ነገር ግን አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው መሠዊያ ፊት ከተሳለ፥ ለመጠበቅ አይገድድም ነበር። ስለሆነም ሕጋቸውን እንዳሻቸው እየጠመዘዙ ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች የገቧቸውን የተስፋ ቃሎች ስለሚጥሱ፥ እግዚአብሔር ፈርዶባቸዋል። ፈሪሳውያን ከራሳቸው አልፈው ሌሎችም ቃላቸውን እንዲያፈርሱ ያስተምሩ ነበር።

ሠ. ዋይታ 5፡ በማይጠቅሙ ሕግጋት ላይ እያተኮሩ፥ እግዚአብሔር የሚፈልጋቸውን ዐበይት ጉዳዮች ስለዘነጉ፥ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ይፈርዳል (ማቴ. 23፡23-24)። ብሉይ ኪዳን አይሁዶች ከምርታቸው የተወሰነውን ድርሻ ለእግዚኣብሔር ኣስራት መክፈል እንዳለባቸው አዝዛል። ፈሪሳውያኑም ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ከእህልና ከቅመም ሁሉ አንድ አሥረኛውን እጅ በጥንቃቄ ይሰጣሉ። ክርስቶስ ይህ መጥፎ ስላልሆነ ሊቀጥሉበት እንደሚገባ ነግሯቸዋል። ነገር ግን ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ተገቢውን ግንኙነት የማድረጉን ዋንኛ ተግባር ባለማከናወናቸው፥ እግዚአብሔር እንደሚፈርድባቸው ገልጾላቸዋል። ፈሪሳውያን ትናንሽ ዝርዝር ጉዳዮችን ለመፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ እንደ ምሕረት፣ ፍትሕ፥ ፍቅርና ታማኝነት የመሳሰሉ ዐበይት ተግባራትን ዘንግተው ነበር።

ረ. ዋይታ 6፡ ፈሪሳውያን ልባቸውን ሳይለውጡ በውጫዊ ነገሮች ላይ ያተኩሩ ስለነበር፥ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ማቴ. 23፡25-26)። በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ከሁሉም የሚልቀው የግለሰቡ ልብ፥ አነሣሽ ምክንያት እና ብሎም ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ያለው ግንኙነት ነው። ፈሪሳውያን ግን በውጫዊ ነገሮች ላይ ያተኩሩ ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ልባቸውን ሳይለውጡ፥ መንፈሳውያን መስለው ለመታየት አድርጉ! አታድርጉ የሚሉትን የትእዛዛት ዝርዝር ይጠብቃሉ። እግዚአብሔር ቅድሚያ የሚሰጠው ግን በልብ ለውጥ ላይ ነው። ይህ ተግባራትን እንደሚለውጥ ግልጽ ነው። በሕግጋት ላይ ማተኮሩ የወጪቱን የውስጥ እድፍ ሳያጸዱ፥ ውጭውን የማጥራት ያህል የሞኝነት ተግባር ነው።

ሰ. ዋይታ 7፡ ፈሪሳውያን የሰውን ኃጢአተኛ ልብ ሳይነካ ለሃይማኖታዊ ሥርዓት አጽንኦት ስለሚሰጡ፥ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል (ማቴ. 23፡27-28)። ይህ ከዋይታ 6 ጋር ተመሳሳይ ነው። ፈሪሳውያን ከእጅ መታጠብ አንሥቶ ለሃይማኖታዊ የመንጻት ሥርዓቶች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። ነገር ግን ለሰው የልብ መንጻት አያስቡም ነበር። አንድ ሰው ለሥርዓታዊ ርኩሰት ከሚጋለጥባቸው መንገዶች አንዱ፥ በመቃብር ላይ በመሄድ እንደሆነ ይታመን ስለነበር፥ ክርስቶስ ይህን ሕግ በመጠበቃቸው ከውጫዊ ርኩሰት ቢድኑም። እንደ ሙታን ሙሉ በሙሉ የረከሱ መሆናቸውን ገልጾኣል። (አይሁዶች የሞትን አስከፊነት ለማስወገድ መቃብሮችን በኖራ ቢለስኑም፣ በመቃብሮቹ ውስጥ ያሉትን ሙታን የመበስበስ አስከፊ ገጽታ ለመቀየር አይችሉም ነበር።)

ሸ. ዋይታ 8፡ ንስሐ እንደማይገቡ አባቶቻቸው ስለሆኑ፥ እግዚኣብሔር በፈሪሳውያን ላይ ይፈርዳል (ማቴ 23፡29-32)። ፈሪሳውያን ራሳቸውን ከታላላቅ የብሉይ ኪዳን ዘመን ነቢያት ጋር የማስተባበር ፍላጎት ነበራቸው። በመጋዝ ለሁለት የተሰነጠቀውን ኢሳይያስንና እንደ እርሱ ያሉትን ነቢያት ለማክበር ታላላቅ መቃብሮችን ይሠሩላቸው ነበር። «በእነርሱ ዘመን ብንኖር ኖሮ እናከብራቸው ነበር።» ሲሉ ይናገራሉ። ነገር ግን መጥምቁ ዮሐንስንም ሆነ ክርስቶስን ለመስማት ባለመፈለጋቸው፥ እነርሱም እንደ ዓመፀኛ ኣያት ቅድማያቶቻቸው መሆናቸውን በተግባር እስመስክረዋል።

እነዚህ አይሁዶች እንደ ቀደምት አባቶቻቸው መሆናቸውን በምሳሌ ለማስረዳት፥ ክርስቶስ የሃይማኖት መሪዎቹ ወደፊት በደቀ መዛሙርቱ ላይ የሚፈጽሙትን ተግባር ተንብዮአል። (ለምሳሌ፥ እስጢፋኖስና ያዕቆብ ይታወሳሉ – የሐዋ. 1፡54-60፤ 12፡1-2)። በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያው ሰማዕት አቤል ሲሆን፥ የመጨረሻው ዘካርያስ ነበር (2ኛ ዜና 24፡20-21)።

ክርስቶስ በአንድ ትውልድ ዘመን፥ (በ 70 ዓ.ም.)፥ የእግዚአብሔር ቅጣት በሮማውያን ሠራዊት አማካኝነት እንደሚደርስባቸው ተንብዮአል። ስለ ሮም ሠራዊትና ስለ መጭው የኢየሩሳሌም ውድመት ማሰቡ፥ በክርስቶስ ልብ ውስጥ ኀዘንን አስከተለ። በ40 ዓመታት ውስጥ ታላቁ ቤተ መቅደስና ታላቁ ከተማ እንደሚወድሙ ክርስቶስ ያውቅ ነበር። ሕዝቡ ክርስቶስን እንደ መሢሐቸው ቢቀበሉት ኖሮ እንደ እናት ዶሮ ሊንከባከባቸው ፈልጎ ነበር። ይህንን ለማድረግ ስላልፈቀዱ ግን አንድ ቀን መሢሕነቱን እስከሚቀበሉበት ጊዜ ድረስ፥ በአይሁዶች ላይ ፍርድ መድረሱ ይቀጥላል። ከ 70 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ድረስ፥ አብዛኞቹ አይሁዶች ክርስቶስን ለመቀበል ፍላጎት የላቸውም። ነገር ግን ክርስቶስን መሢሐቸው አድርገው የሚቀበሉበት ጊዜ ይመጣል። (ሮሜ 1፡25-32 ኣንብብ)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ክርስቲያኖች እንዴት የፈሪሳውያን ዓይነት አመለካከቶችን ሊያንጸባርቁ እንደሚችሉ ግለጽ። ለ) ይህ ክፍል የዚህ ዓይነት አመለካከት እንዳይኖራቸው ምን ዓይነት ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣቸዋል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

1 thought on “ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና የኦሪት ሕግ መምህራንን ነቀፈ (ማቴ. 23:1-39)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: