ማቴዎስ 26:1–46

የውይይት ጥያቄ፡- ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ በላይ ታላቅ እንደሆነ ሲነገር እንሰማለን። ኢየሱስ ያደረገውና ታሪክን ሁሉ የለወጠው አንድ ዐቢይ ነገር ምን ይመስልሃል? መልስህን አብራራ።

ስለ ክርስቶስ ሕይወት አጽንኦት ልንሰጥባቸው የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ብዙዎቻችን በፈውስ አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር እንፈልጋለን። እርግጥ በምድር ላይ ከጤና በላይ ምን አለ? ወይም በማስተማር አገልግሎቱ ላይ ለማተኮር እንፈልጋለን። ነገር ግን የወንጌላት ጸሓፊዎች ሁሉ ያተኮሩት በክርስቶስ ሞት ላይ ነው። ሁሉም የወንጌላት ጸሓፊዎች ከክርስቶስ ሕይወት እጅግ ጠቃሚውና ታሪክን ሁሉ የተገዳደረው ተኣምራት ሠሪነቱ ወይም ማስተማሩ ሳይሆን፥ (እነዚህ ነገሮች አስፈላጊዎች ቢሆኑም)፥ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። ክርስቶስ በሞቱ ኃጢአተኞች የእግዚአብሔር ቤተሰብ የሚሆኑበትን መንገድ ከፍቷል። በትንሣኤው ክርስቶስ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር የኃጢአት መሥዋዕቱን እንደ ተቀበለ አረጋግጧል።

ማቴዎስ ክርስቶስን በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት ያካሄደውን አገልግሎት፥ (ፈውስና ማስተማሩን ጨምሮ) በአጭሩ ጠቅለል አድርጎ ካቀረበ በኋላ፥ በዘመናት ከሁሉም በላቀው እውነት ላይ አጽንኦት እድርጓል። ይህም የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው። እኛ ክርስቶስ ለሰው ልጆች በተቀበለው ሰብአዊ ሥቃይ ላይ ብናተኩርም፥ የወንጌላት ጸሓፊዎች በዚህ ጕዳይ ላይ አላተኮሩም። ብዙ ስቅለቶችን ያዩ በመሆናቸው ጸሓፊዎቹ ክርስቶስ ለእኔና ለእናንተ ምን ያህል እንደ ተሠቃየ ሊያብራሩ ይችሉ ነበር። ነገር ግን በሐቆች ላይ ለማተኮር መረጡ። በተለይም ማቴዎስ አይሁዶችን በሚያስገርም መልኩ የክርስቶስ ሞት የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል እንደሆነ በሚገባ ለማብራራት ፈልጓል።

  1. የኢየሱስ ጠላቶች ሊገድሉት ተዘጋጁ (ማቴ. 26፡1-16)

ቀደም ሲል ማቴዎስ በኢየሱስ የአገልግሎት ጊዜ ሁሉ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲጋጭ መቆየቱን አስረድቷል። አሁን ያ ግጭት ወደ ባሰ ደረጃ እየደረሰ ነው። የሃይማኖት መሪዎቹ በሕዝብ ፊት ብዙ ጊዜ ስላሸነፋቸውና ስላዋረዳቸው ከክርስቶስ ጋር ከመከራከር ይልቅ ገድለውት ሊገላገሉ ወሰኑ።

ነገር ግን በዚህ ግጭትና ኢየሱስ ወደሚያዝበት ደረጃ ባደረሱት ድርጊቶች መካከል፥ ማቴዎስ ጠቃሚ የፍቅር ታሪክ አውግቷል። ይህም ኢየሱስ በለምጻሙ ስምዖን ቤት ማዕድ ሊበላ ተቀምጦ ነበር። እርሱም ኢየሱስ የፈወሰው ግለሰብ ሳይሆን አይቀርም። ምግቡ እየተበላ ሳለ፥ አንዲት ሴት መጥታ ኢየሱስን ሽቱ ትቀባው ጀመር። ዮሐንስ ይህች ሴት ኢየሱስ ከሚቀርባቸው ልዩ ወዳጆች አንዷ ማርያም እንደ ነበረች ገልጾአል (ዮሐ 12፡1-8)። ሴትዮዋ ውድ ሽቶ አምጥታ ጌታን ስትቀባ ያዩ ደቀ መዛሙርት ሀብት ማባከን መሰላቸው። ምናልባትም ለድሆች ማሰብ እንደሚያስፈልግ ከኢየሱስ መማራቸውን ለማሳየት ሲሉ፥ ደቀ መዛሙርቱ ሴቲቱ ሽቱውን ሸጣ ገንዘቡን ለድሆች ባለመስጠቷ ገሠጹኣት። ነገር ግን ለኢየሱስ ልባዊ ፍቅርን በስጦታ መግለጥ ምን ጊዜም የሞኝነት ተግባር አልነበረም። ማርያም ለእርሱ ክብር ለሞቱ መታሰቢያ ሽቶውን እንደ ቀባችው ክርስቶስ ተናግሯል። ኢየሱስ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተይዞ እንደሚገረፍ፥ ከዚያም እንደሚሰቀል፥ በተጨማሪም ከሃይማኖት መሪዎችና ከሕዝቡ የሚደርስበትን ጥላቻ እያሰበ ይህን የመታሰቢያ ሽቶ ስትቀባው አክብሮ ተቀበለ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ የተጋነነና ያልተለመደ ነገር በማድረግ ለኢየሱስ ያለህን ፍቅር ገልጸህ ታውቃለህ? ምን ነበር ያደረግኸው? ፍቅርህ ለኢየሱስ እንዲበዛ ያደረገው ምንድን ነው? ለ) አንዳንድ ጊዜ ባልተለመዱ መንገዶች፥ ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር የማናሳይ ከሆነ፣ ይህ ስለ ልባችንና ስለ ፍቅራችን ምን ያሳየናል?

ከማርያም በተቃራኒ፥ ይሁዳም የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ነበር። እርሱ ግን ኢየሱስን በ30 ብር ሸጦታል። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስ የመጀመሪያውን በደል የተቀበለው ከይሁዳ ነበር። ይህ ኢየሱስን ምን ያህል እንደ ጎዳው የሚያውቁት የቅርብ ወዳጃቸው የከዳቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። ይሁዳ ለሦስት ዓመታት ኢየሱስ ጋር አብሮ እየኖረ ትምህርቱን አድምጧል። እርሱም የቡድኑን ገንዘብ እስከ መያዝ ድረስ የተከበረ ደቀ መዝሙር ነበር። ይሁዳ ኢየሱስን ለምን አሳልፎ ሰጠ? ለገንዘብ ብሎ ነው? አይመስልም። ምናልባትም ይሁዳ ኢየሱስ ሲናገር የነበረውን ምድራዊ መንግሥት እንዲጀምር ለማስገደድ አስቦ ይሆናል። ክፉዎቹ የአይሁድ መሪዎችና እስራኤልን የሚቆጣጠሩት ሮማውያን ሲገረሰሱ ለማየት ፈልጎ ይሆናል።

  1. ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚክደው መተንበዩና የጌታን እራት ማክበሩ (ማቴ. 26፡7-35) በአይሁዶች ሃይማኖታዊ የጊዜ ሰሌዳ፥ በአንድነት የሚከበሩ ሁለት ሃይማኖታዊ በዓላት አሉ። የመጀመሪያው አይሁዶች ከግብጽ ለመውጣት መዘጋጀታቸውን የሚገልጽ የአንድ ቀን የቂጣ በዓል ነበር። ሌላው የፋሲካ በዓል ሊሆን፥ ይህም የእግዚአብሔር መልአክ በበራቸው ላይ ደም የረጨትን ሰዎች እያለፈ የግብኦችን የበኩር ልጆች የገደለበትን ሁኔታ የሚያስታውሱበት ነበር። እነዚህ ሁለቱም በዓላት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያመለክቱ ነበር። ኢየሱስ ለዓለም ኃጢኣት በመሞት የእግዚአብሔርን ልጆች፥ (አይሁዶችንም አሕዛብንም) ከመንፈሳዊ እስራት ነፃ አወጣ።

ማቴዎስ ስለዚህ የፋሲካ በዓል ምግብ ባቀረበው ገለጻ፥ በክርስቶስ አልፎ መሰጠት ላይ ያተኩራል። ኢየሱስ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጠው አስቀድሞ ተናግሯል። ክርስቶስ የሚሆነውን ሁሉ ቀደም ብሎ እያወቀ በፈቃደኛነት ወደ መስቀል ሞት አመራ። ምናልባትም ኢየሱስ በእራት ላይ ለይሁዳ ምግብ ያጎረሰው ከኃጢአቱ ንስሐ እንዲገባ ዕድል ሊሰጠው ይሆናል።

በተጨማሪም፥ ጴጥሮስና ሌሎችም ደቀ መዛሙርቱ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት በመፈጸም እንደሚክዱት ኢየሱስ ተናግሯል። ማቴዎስ ሁለቱን ክህደቶች የጠቀሰው ለምንድን ነው? ክርስቲያኖች በስደት ጊዜ እንዴት ክርስቶስን ሊክዱ እንደሚችሉ ለማስተማር ፈልጎ ይሆን? ምናልባትም ይሆናል። በማቴዎስ ዘመን፥ አይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች በስደት ምክንያት ለክርስቶስ መከራ መቀበል ወይም መሞት ይገባቸው እንደሆነ በማሰብ ይጨነቁ ነበር። አንዳንዶች ከፍርሃት የተነሣ ይክዱት ነበር። እነዚህ ሰዎች ከዚያ በኋላ ተስፋ ይኖራቸዋል? ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት ምላሽ ልትሰጣቸው ይገባል? ማቴዎስ በይሁዳና ጴጥሮስ ታሪክ አማካኝነት ሁለት ዓይነት ክህደት እንዳለ ይናገራል። በመጀመሪያ፥ አንድ ሰው ክርስቶስን ከካደ በኋላ ንስሐ ሳይገባ የሚሞትበት የይሁዳ ዓይነት ክህደት አለ። የዚህ ዓይነቱ ክህደት ተስፋ የለውም። ክርስቲያኖች በፍርሃት ሳቢያ ከክርስቶስ ሲለዩና ንስሓ ገብተው ወደ ክርስቶስ ከመመለሳቸው በፊት ቢሞቱ፥ የይሁዳን ዓይነት ፍርድ ይቀበላሉ። ነገር ግን አንድ ሰው ለሕይወቱ ፈርቶ ከክርስቶስ ወደ ኋላ ካፈገፈገ በኋላ፥ ንስሐ ቢገባ፥ እንደ ጴጥሮስ ሙሉ በሙሉ ይቅርታ ተደርጎለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ፍሬያማ አገልግሎት ይመለሳል። ክርስቶስ መሓሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል፥ በስደት ምክንያት ክርስቶስን የካዱትን ወገኖች ይቅር ሊሏቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህን ሁለት ዓይነት ክህደቶች ያየህባቸው ምሳሌዎች ካሉ ግለጽ። ለ) ኤር. 31፡31-34 እና ሕዝ. 36፡25-27 አንብብ። ስለ አዲስ ኪዳን የተሰጡት የተስፋ ቃሎች ምንድን ናቸው? እነዚህ የተስፋ ቃሎች ለክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን የተፈጸሙት እንዴት ነው? ሐ) ክርስቶስ ዘመናችንን «አዲስ ኪዳን» ሲል ምን ማለቱ ይመስልሃል?

ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የበላው የመጨረሻው ምግብ በሌላ ምክንያት ልዩ ነበር። ክርስቶስ «የጌታ እራት» የምንለውን ሥርዓት መሥርቷል። ይህ የመታሰቢያ ምግብ ነው። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት ደሙ በመፍሰሱ፥ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት እንዳበቃ ገልጾአል። በኤርምያስ የተተነበየው አዲስ ኪዳን ተጀመረ። ክርስቲያኖች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት በሞቱ ላይ የተመሠረተ መሆኑን በተደጋጋሚ እንዲያስታውሱ ለማድረግ፥ ደቀ መዛሙርቱ ወይን በመጠጣትና እንጀራ በመቁረስ ሞቱን የሚያከብሩበትን ቀን እንዲያስቡ ነገራቸው። ይህ በዓል ለክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ የተሰጠ ሲሆን፥ በአዲስ ኪዳን ዘመን ሁሉም ክርስቲያኖች የጌታ እራት ሥነ ሥርዓት ተሳታፊዎች ነበሩ።

  1. ኢየሱስ በጌቴሴማኒ ጸለየ (ማቴ. 26፡36-46)

ኢየሱስ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው ነው። አንድ ሰው እንዴት በአንድ ጊዜ ሰውና አምላክ ሊሆን እንደሚችል ምሥጢር ቢሆንም፥ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እውነት ነው። ኢየሱስ ከሞት እንደሚነሳ ቢያውቅም፥ ጭንቀት ስለ ጸናበት ከተቻለ እግዚአብሔር ሌላ አማራጭ እንዲሰጠው ሦስት ጊዜ በጸሎት ጠይቋል። ነገር ግን በእያንዳንዱ ጊዜ ክርስቶስ «ፈቃድህ ይፈጸም» በማለት ለእግዚኣብሔር መታዘዙን አሳይቷል። አንዳንድ ሰዎች ለፈውስ በምንጸልይበት ጊዜ ፈቃድህ ከሆነ» ማለቱ ያለማመን ምልክት ነው ይላሉ። ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህ የትሕትናና ራስን የማስገዛት ምልክትም ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር አንድን ነገር እንዲፈጽምልን ልናስገድደው አንችልም። እርሱ ዓለምንና ድርጊቶችን ሁሉ የሚቆጣጠር ፈጣሪና ሁሉን ቻይ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነገር ፈቃዱ እንደሆነ በግልጽ ካልነገረን፥ “ፈቃድህ ይፈጸም” ማለታችን በፈውስም እንኳ ትልቁ ፍላጎታችን የእግዚአብሔር መክበር መሆኑን ያሳያል። ይህም፥ ፈቃዱና ዓላማው ምንም ይሁን ምን እንደምንገዛለት ያመለክታል።

የውይይት ጥያቄ:- ሀ) “ፈቃድህ ይፈጸም” የሚለው ሐረግ እንደ ማመኻኛ ወይም የአለማመን ምልክት ሆኖ ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው? ለ) ለእግዚአብሔር ፈቃድ የመገዛት ምልክት ሊሆን የሚችለውስ እንዴት ነው? ሐ) ይህን ሐረግ መጠቀም የማያስፈልጋቸውንና ለእግዚአብሔር ያለንን እምነት ወይም መሰጠት ለማመልከት ይህ ሐረግ የሚያስፈልጋቸውን ሁኔታዎች ግለጽ፡፡

ኢየሱስ የፈራው ሞቱን ነበር? በከፊል ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም እንደ መስቀል ላይ ሞት በሰው ልጆች የተዘጋጀ አሠቃቂ ሞት የለም። ነገር ግን ኢየሱስን ከሁሉም በላይ ያለጨነቀው የዓለም ሁሉ የሥነ ምግባር ጉድለት ኃጢአት በእርሱ ላይ እንደሚከመር ማወቁ ላይሆን አይቀርም። ሁልጊዜም ፍጹም ሆኖ የኖረው ክርስቶስ፥ አሁን በኃጢአታችን ይሸፈን ነበር። (2ኛ ቆር. 5፡21 አንብብ) እንዲሁም በኃጢአታችን ምክንያት ሁልጊዜም ከአብ ጋር ሲያካሂድ የነበረው ግልጽና በፍቅር የተሞላ ግንኙነቱ ይበላሽ ነበር። አብ ለልጁ ጀርባውን የሚሰጥበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: