ክርስቶስ ላልተጠበቀው ምጽአቱ ስለ መዘጋጀት የሚያስረዳ ምሳሌ ተናገረ (ማቴ 25:1-46)

ለክርስቲያኖች የመጨረሻው ዘመን ምን ዓይነት እንደሚሆን ማሰቡ ቀላል ነው። ብዙውን ጊዜ በተለያዩ አተረጓገሞች ክርክሮች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ይህ ብዙውን ጊዜ ጥቅም የሌለው የሞኝነት ተግባር ነው። ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ዘመን ባስተማረበት ወቅት፥ መዘጋጀት እንዳለብን ተናግሯል። ዋናው ነገር ይኸው ነው። ክርስቶስ በየትኛውም ጊዜ እንደሚመለስ ተገንዝበን ከተዘጋጀንና በየዕለቱ በታማኝነት ከተመላለስን፥ የሚያሳስበን ነገር አይኖርም። በዚህ ዓይነት ከኖርን፥ እርሱ ሲመጣ አናፍርም። ክርስቶስ እርሱ በሚመለስበት ጊዜ የማያሳፍር ሕይወት መምራት እንደምንችል ሦስት የተለያዩ እውነቶችን የሚያስተምሩ ሦስት ምሳሌዎችን ሰጥቷል:-

ሀ. ለክርስቶስ ምጽአት የተዘጋጁ ክርስቲያኖች ብቻ፥ ወደ ዘላለማዊ የበረከት መንግሥት ይገባሉ (ማቴ. 25፡1-13)። የመሢሑን መንግሥት ለማመልከት አይሁዶች ከሚጠቀሙባቸው ዐበይት ምሳሌዎች አንዱ፥ ጋብቻ ነበር (ራእይ 19፡7-9)። ክርስቶስ የአይሁድን ጋብቻ ሁኔታ ምሳሌ በማቅረብ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለምጽአቱ እንዲዘጋጁና ካልተዘጋጁ ደግሞ ምን እንደሚገጥማቸው አብራርቷል። (ማስታወሻ፡- እንደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሁሉ፥ በአይሁዶች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አፈጻጸም ሰዓት አይወሰንም ነበር። በተለይም ሙሽራው ከርቀት የሚመጣ ከሆነ፥ እስኪመጣ ድረስ የሙሽራይቱ እድምተኞች ሲጠብቁት ይቆያሉ።) በዚህ ታሪክ ውስጥ አሥሩ ቆነጃጅት የክርስቶስን ተከታዮች ይወክላሉ። ወደ ሰርጉ በዓል የሄዱት አምስቱ ቆነጃጅት የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በትጋት ለመጠበቅ የተዘጋጁትን አማኞች ያመለክታሉ። አምስቱ ሞኞች ክርስቶስ በፍጥነት ይመለሳል ብለው ያላሰቡና ብዙ ለመጠበቅ ያልተዘጋጁ አማኞችን ይመስላሉ። (እስካሁን 2000 ዓመታት አልፈዋል።) እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የመሆኑ ምልክት፥ ሁልጊዜም ለክርስቶስ ምጽአት ተዘጋጅቶ መኖር ስለሆነ፥ ያልተዘጋጁ ሰዎች የሰርጉን በዓል (የክርስቶስን መንግሥት) በረከቶች የመቋደስን ዕድል ተነፍገዋል።

ለ. የክርቶስን ምጽአት በምንጠባበቅበት ጊዜ፥ ታማኝ መጋቢዎች ልንሆን ይገባል (ማቴ. 25፡14-30)። በሁለተኛ ምሳሌው፥ ክርስቶስ ራሱን ሩቅ አገር ከሄደ ሀብታም ጌታ ጋር ያነጻጽራል። ባሪያዎቹን ጠርቶ ለእርሱ ጥቅም እንዲያውሉ የተለያዩ ሀብቶችን ሰጣቸው። ከሩቅ አገር ጉዞው ሲመለስ፥ እያንዳንዱ ባሪያ ሀብቱን እንዴት እንደ ተጠቀመበት በመገምገም የሽልማት ወይም የፍርድ ውሳኔ ሰጠ።

በተመሳሳይ መንገድ፥ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ የእርሱ ተከታይ ልዩ ስጦታዎችን ሰጥቶ ወደ ሰማይ ሄዷል። እነዚህ ስጦታዎች የተሰጡን ለራሳችን ጥቅም ሳይሆን ጌታችንን እንድናገለግልባቸው ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ፥ በሕይወታችን ውስጥ ለእርሱ ምን እንዳተረፍን ይገመግመናል። አንዳንዶች ታላላቅ ሽልማቶችን ያገኛሉ። የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ያልነበሩና ሕይወታቸውን ለእርሱ ጥቅም ያላዋሉ ግን በዘላለማዊ ሞት ይቀጣሉ።

እዚህ ላይ ልንገነዘባቸው የሚገቡን ሦስት ዐበይት እውነቶች አሉ። በመጀመሪያ፥ እያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ የሚጠቀምባቸው ሀብቶች ተሰጥተውታል። እነዚህ ሀብቶች ገንዘብ፣ ጊዜ፥ ወይም ለቤተ ክርስቲያን ኣገልግሎት የሚውሉ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁለተኛ፥ ለእያንዳንዱ አማኝ የተለያዩ ሀብቶች ተሰጥተውታል። ለእያንዳንዱ ባሪያው ምን መስጠት እንዳለበት የሚወስነው ክርስቶስ ነው። ይህም አንዱ ባሪያ ባገኘው ሀብት ሊኩራራ፥ ሌላው ደግሞ ሊቀና እንደማይገባ ያሳያል። ሦስተኛ፥ እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ማን የበለጠ ወይም ያነሰ ሀብት አለው? የሚለው ሳይሆን፥ እርሱ የሰጠንን በታማኝነት መጠቀማችን ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ለእንተ ብቻ የሰጣቸውን ሀብቶች ዘርዝር። እነዚህን ሀብቶች ለክርስቶስ ክብርና ለመንግሥቱ መስፋፋት እየተጠቀምክ ያለኸው እንዴት ነው?

ሐ. ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ አንዳንዶች ወደ ዘላለማዊ በረከት፥ ሌሎች ወደ ዘላለማዊ ፍርድ ይሄዳሉ (ማቴ. 25፡31-46)። በአይሁዶች ባሕል፥ በጎች (የበለጠ ጠቀሜታ አላቸው)፥ ስለዚህ ጌታ በፍየሎች ምሳሌ የተናገረው እርሱ በሚመለስበት ጊዜ የሚሆነውን ሁኔታ ለማሳየት ነበር። እርሱ በበጎች የተመሰሉትን እውነተኞች የእግዚአብሔርን ሕዝብ፥ ከፍየሎች ከተመሰሉት የማያምኑ ሰዎች ይለያል። ለመሆኑ ክርስቶስ ጥሩዎችን ከመጥፎዎቹ ለመለየት የሚጠቀምበት መመዘኛ ምን ነበር? መመዘኛው ተግባራቸው ይሆናል። ለተራቡት፥ ለታመሙትና ለታሰሩት ርኅራኄን ያሳዩት ሰዎች የዘላለምን ሕይወት ያገኛሉ። ርኅራኄን ያላሳዩት ግን በዘላለማዊ ሞት ይቀጣሉ።

ይህ ማለት በሰናይ ምግባራችን ወደ መንግሥተ ሰማይ ልንገባ እንችላለን ማለት ነው? አይደለም። በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደዳንን ግልጽ ነው (ኤፌ. 2፡8-9)። በዚህ ስፍራ ኢየሱስ ሦስት ዐበይት እውነቶችን አስተምሯል።

በመጀመሪያ፥ በእግዚአብሔር ቤተሰብ እርስ በርሳችን ልንዋደድና ልንረዳዳ እንደሚገባን ያሳያል። ሁልጊዜም የተቸገሩትን እንድንረዳ የተጠየቅን ብንሆንም፥ «ታናናሾች» [ማቴ. 25፡45] የሚለው ክርስቲያኖችን እንጂ ሁሉንም ሰው አያመለክትም።) ክርስቲያኖች ከሚደርስባቸው ስደት የተነሣ፥ ብዙዎች ሥራቸውን አጥተው ይራቡና መጠለያ አጥተው ይቸገሩ፥ ሌሎች ደግሞ ይታሰሩ ነበር። ኢየሱስ ስደትን በመፍራት እነዚህን ሰዎች ቸል ከማለት ይልቅ፥ ተከታዮቹ ቀርበው ሊረዷቸው እንደሚገባ አስተምሯል።

ሁለተኛ፥ ኢየሱስ የክርስቶስን አካል ኣንድነት እያሳየ ነው። ክርስቲያኖችን መርዳት ኢየሱስን መርዳት ነው። ሌላው ክርስቲያን በችግር ላይ እያለ አለመርዳት ማለት ደግሞ ኢየሱስን አለመርዳት ነው። ኢየሱስ በሌላው ክርስቲያን ውስጥም ነውና።

ሦስተኛ፥ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን ከሚያሳዩ ዐበይት ማስረጃዎች ኣንዱ፥ እርስ በርሳችን የምንቀራረብበት መንገድ ነው። ለራሳችን ፍላጎት ብቻ የምናስብ ብልጦች ከሆንን፥ ክርስቶስና የእርሱ ፍቅር በልባችን ውስጥ እንደሌለ ግልጽ ነው። ስለሆነም፥ በመልካም ሥራችን የዘላለምን ሕይወት ከማግኘት ይልቅ፥ መዳናችንን በአኗኗራችን እናሳያለን። የክርስቶስ ተከታዮች መሆናችንን የምንመሰክረው በቀዳሚነት በምንናገራቸው ቃላት ወይም በምንዘምራቸው መዝሙሮች ሳይሆን፥ ሌሎችን ክርስቲያኖችና ተጎጂዎችን በምናስተናግድበት መንገድ ነው። የክርስቶስ ዓይነት የርኅራኄ ልብ ከሌለን፥ የእርሱ ተከታዮች አለመሆናችንና እርሱን አለማወቃችን ግልጽ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ዛሬ ፍቅራችንን እንዴት ማሳየት እንደሚገባን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሆነን እንዴት ነው? ለ) ሌሎች ክርስቲያኖችንና ድሆችን ለመርዳታ እጅህን የምትዘረጋባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ሐ) ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ድሆችን ለመርዳት ባለመፈለጋቸው ይታወቃሉ። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይህንን ዝና ለውጠን እርስ በርሳችን በመዋደዳችንና ድሆችን በመውደዳችን ልንታወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: