ማቴዎስ 26፡47- 27፡66

  1. ወደ ኢየሱስ ስቅለት የሚመሩ ክስተቶች (ማቴ. 26፡47-27፡8)

ከኢየሱስ ጸሎት በኋላ ነገሮች በፍጥነት ተከናወኑ። ይሁዳ ወታደሮችን አስከትሉ በመምጣት ኢየሱስን በመሳም አሳልፎ ሰጠ። ክርስቶስ በሚያስደንቅ ሁኔታ መንግሥቱ በውጊያና በዐመጽ እንደማትሸነፍ አሳይቷል፡፡ አልፎ በመሰጠቱ፥ በመያዙና በሞቱ ሳይቀር፥ ኢየሱስ ይህ ሁሉ በብሉይ ኪዳን የተተነበየ የእግዚአብሔር ዕቅድ አካል መሆኑን ያውቅ ነበር (ማቴ 28፡54፣ 56)። ክርስቶስ ከተያዘ በኋላ፥ ደቀ መዛሙርቱ ፈርተው ሸሹ፡፡

ማቴዎስ ለአይሁዶች በጻፈው ወንጌሉ፥ እያንዳንዱ በኢየሱስ ላይ የተካሄደው ምርመራ ሕገወጥ እንደ ነበረ አመልክቷል። ኢየሱስ የተሰቀለው ሰዎች በደለኛና ሞት የሚገባው እንደሆነ በማመናቸው አልነበረም። ንጹሕ እንደሆነ ያውቁ ነበር። ግን ኣይሁዶች በፍትሕ አልባነት ነበር የመረመሩት።

ማቴዎስ የጠቀሰው የመጀመሪያው ምርመራ የተካሄደው 70 አባላት በሚገኙበት የአይሁድ ሸንጎ ፊት ነበር። የዚህ ሸንጎ ሕገ መንግሥት የሞት ፍርድ ለመበየን በምሽት ሊሰባሰቡ እንደማይችሉ ያስረዳል። እንዲሁም፥ መረጃውን ከቀረበላቸው በኋላ የፍርድ ውሳኔ ከመስጠታቸው በፊት፥ አዳዲስ መረጃዎችን በመጠባበቅ ብዙ ጊዜ መቆየት እንደሚገባቸው ይደነግጋል። ማቴዎስ እንዳመለከተው ግን እነዚህ ሰዎች ስለ ፍትሕ ሳይጨነቁ ኢየሱስን ለመግደል አሰፍስፈው ተነሡ። ምርመራው የተካሄደው በሌሊት ሲሆን፥ ምስክሮቹ ስምምነት አልነበራቸውም። ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ፥ «ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ» መሆን አለመሆኑን እንዲነግረው አዘዘው። ኢየሱስ ዳንኤል 7፡13-14ን በማመልከት የሰው ልጅ መሆኑን ከገለጸ በኋላ ነበር፥ እርሱን ለመግደል የሚያስችል መረጃ እንዳላቸው ያመኑት። የአይሁድ መሪዎች ይህ ስድብ ነው ብለው ያምኑ ነበርና። ተፈላጊውን የሕግ ሂደት ጊዜ ሳይጠብቁ መሪዎቹ ወዲያውኑ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ወሰኑ። ምንም እንኳ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ሥልጣን ባይኖራቸውም፥ እነዚህ የአይሁድ መሪዎች በኢየሱስ ላይ በመሳለቃቸውና ድብደባ በመፈጸማቸው ሌሎች ሕግጋትን ጥለዋል።

ማቴዎስ በዚህን ጊዜ የተከናወኑ ሁለት ክስተቶችን ይገልጻል። መጀመሪያ፥ ጴጥሮስ የኢየሱስን መገረፍ አይቷል። የተለያዩ ሰዎች ጴጥሮስን የኢየሱስ ተከታይ እንደሆነ አውቀውታል። ጴጥሮስ ግን ኢየሱስን አላውቀውም ሲል ሦስት ጊዜ ማለ። የዶሮ ጩኸት የኢየሱስን ትንቢት አስታወሰው፥ እርሱም በኃጢአተኝነቱ ተጸጽቶ አለቀለ።

ሁለተኛ፥ በዚህን ጊዜ ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ዘንድ በመሄድ ኢየሱስ ንጹሕ መሆኑን ገልጾ እንዲለቅቁት ለመናቸው። ፈቃደኞች ሳይሆኑ ሲቀሩ፥ ራሱን በስቅላት ገደለ። ጸጸቱ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ አላደረገውም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳይቀር ማቴዎስ የእግዚአብሔርን እጅ አይቷል። አሳልፎ የሰጠው የይሁዳ ሞትና ለወንጀለኞች የመቃብር መሬት መገዛቱ፥ የብሉይ ኪዳንን ትንቢት ፈጽሟል። (ኤር. 32፡6-9፣ ዘካ. 11፡12-13 አንብብ።)

ማቴዎስ የገለጸው ሁለተኛው ምርመራ የተካሄደው የሮም ገዥ በነበረው በጲላጦስ ፊት ነበር። ጲላጦስ ለአይሁድ ሃይማኖት ግድ ስላልነበረውና ኢየሱስ አምላክ ነኝ በማለቱ ምክንያት በሞት ስለማይቀጣው፥ አይሁዶች ነገሩን ፖለቲካዊ አድርገው በማቅረብ፥ ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሥ ነኝ ብሏል አሉ። ይህ ደግሞ በሮም ላይ የሚካሄድ የዓመፅ ተግባር ነበር። ጲላጦስ ክርስቶስ ሮምን ያሚያሰጋ ኣማፂ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። የጲላጦስም ሚስት ስለ ክርስቶስ ንጽሕና የሚያስረዳ ሕልም አይታ ነበር። ነገር ግን ጲላጦስ አይሁዶን ፈራ። (ማቴዎስ ለክርስቶስ ሞት አብዛኛው ጥፋት የጲላጦስ ሳይሆን፥ የአይሁዶች እንደሆነ አመልክቷል።) ጲላጦስ አንድ እስረኛ በመፍታት ኢየሱስን ነፃ ለማውጣት ሲሞክር፥ አይሁዶች ከኢየሱስ ይልቅ ነፍሰ ገዳዩን በርባንን መረጡ። ጲላጦስ ሌላ ቅጣት በመረጠ ጊዜም ኢየሱስን እንዲሰቅል አስገደዱት። አይሁዶች እነርሱንና ልጆቻቸው ለኢየሱስ ደም ኃላፊነት እንደሚወስዱ በመግለጽ ለተግባራቸው ተጠያቂነታቸውን አመልክተዋል።

ጲላጦስም ከኀላፊነት አያመልጥም። በሥነ ምግባራዊ ድክመቱና በፍርሃቱ ምክንያት ንጹሕ ሰው እንዲደበደብ፥ በወታደሮቹ መሳለቂያ እንዲሆንና በመጨረሻም እንዲገደል ፈቅዷል። ስለሆነም አይሁዶችም ሆኑ አሕዛብ ኢየሱስን በመስቀላቸው በድለዋል።

  1. የኢየሱስ ስቅለት፥ ሞትና ቀብር (ማቴ. 27፡2-66)

ሮማውያን ወንጀለኛው ክሱ የተጻፈበትን ምልክት ተሸክሞ እንዲሄድና በመስቀል ላይ እንዲሰቀል የማድረግ ልማድ ነበራቸው። በክርስቶስም ላይ «የአይሁድ ንጉሥ» የሚል የክስ ቃል ተጻፈ። የክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት ጉዳይ ሦስት ጊዜ ተነሥቷል። መጀመሪያ ሕዝቡ (ቁ 40)፥ ከዚያም ካህናቱ ቁ 43) ለስቅላት ተጠቅመውበታል። ነገር ግን ከስቅለቱ ባሻገር ተመልክቶ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልዩ ልጅ እንደሆነ የተገነዘበው አንድ የአሕዛብ ወታደር ነበር ቁ 54)። አይሁዶች ሊያዩ ያልቻሉትን ኢየሱስን ለመስቀል የቆመው የአሕዛብ ወታደር እየ። ሕዝቡ «እስኪ ከመስቀል ውረድ» እያሉ ሲፈታተኑት ኢየሱስ ይህንኑ ሊያደርግ ይችል ነበር። መላእክት እንዲረዱት በመጥራት የመሢሕነት ኃይሉንና ሥልጣኑን ሊያሳይ ይችል ነበር። እንዲሁም ኢየሱስን በመስቀል ላይ ያቆየው በእጆቹና እግሮቹ ላይ የተቸነከሩት ምስማሮች፣ ወይም የአይሁድ እና የሮም ባለሥልጣናት አልነበሩም። ክርስቶስን በመስቀል ላይ ያኖረው ታላቅ ፍቅሩና እኔና አንተ የዘላለምን ሕይወት እንድናገኝ መቁረጡ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ክርስቶስ ፍቅርና ለአንተ ለመሞት ስለ መፍቀዱ እያሰብህ ጸልይ። ለፍቅሩ እመስግነው። በአኗኗርህ ለእርሱ ያለህን ፍቅር ለመግለጽ ቃል ኪዳንህን እድስ።

ኢየሱስ ለስድስት ሰዓታት በመስቀል ላይ ቆየ። በዚህ ጊዜ የሰው ልጆች ኃጢአት በላዩ ላይ ስለነበር አብ ፊቱን አዞረበት። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው ነገሮች ማቴዎስ የጠቀሰው በአባቱ የመተውን ሥቃይ ብቻ ነበር። ከዚያም ኢየሱስ ነፍሱን እንደ ተወ ገልጾአል። ክርስቶስ የእግዚአብሐርን ዕቅድ ከፈጸመ በኋላ፥ መንፈሱን ተወ እንጂ በአይሁዶች ወይም በሮማውያን አልተገደለም።

ኢየሱስ በሞተባት ቅጽበት፥ አንድ አስደናቂ ነገር ተከሰተ። ከሙሴ ዘመን ጀምሮ በቤተ መቅደስ ውስጥ እግዚአብሔር ከሚኖርበት ቅድስተ ቅዱሳን የሚለይ መጋረጃ ነበር፡ ያ የመለያ መጋረጃ በቅዱሱ አምላክና በኃጢአተኞች ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት በዘላቂነት የሚያስታውስ ነበር። ይህ መጋረጃ «ወደዚህ ብትጠጋ ትሞታለህ» አንተ ኃጢአተኛ ስትሆን፥ እኔ ቅዱስ ነኝ» ለሚለው መለኮታዊ ቃል ዘላቂ ማስታወሻ ነበር። ከኢየሱስ ሞት በኋላ ግን ያ ክፍፍል ተፈጸመ። ለዓለም ኃጢአት ተገቢው ዋጋ ስለ ተከፈለ፥ በኢየሱስ የሚያምኑ ሰዎች ወደ ቅዱስ አምላክ ያለ ፍርሃት ሊቀርቡ ቻሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዕብ 4፡5-16፤ 8፡1-2፤ 9፡11-15፥ 24-28፤ 10፡19–22 ኣንብብ። የክርስቶስ ሞት ያለ ፍርሃት ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ ያስቻለን እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች (ለምሳሌ፥ ኦርቶዶክሶች) የብሉይ ኪዳንን ዓይነት መጋረጃ የሚጋርዱት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ ያለመረዳት የሚሆነው እንዴት ነው?

በዘጠኝ ሰዓት ኢየሱስን ከመስቀል ላይ አውርደው ቀበሩት። ቅዳሜ ዕለት የአይሁድ መሪዎች ጲላጦስ በልዩ የሮም ወታደሮች መቃብሩን እንዲያስጠብቅላቸው ጠየቁት። የዚህ ምክንያት ኢየሱስ ከሦስት ቀናት በኋላ ከሞት መነሣቱን እንደተናገረ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት ይነሣል ብለው ባያምኑም፥ ደቀ መዛሙርቱ አስከሬኑን ከሰረቁ በኋላ ሕያው ነው ብለው እንዳያስወሩ ፈርተው ነበር። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ የእግዚአብሔር ልጅነቱ እንደሚረጋገጥ ያውቁ ነበር። ማቴዎስ ይህንን የመቃብር ጥበቃ ታሪክ ጨምሮ የጻፈው ያለ ምክንያት አይደለም። ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ፥ የአይሁድ መሪዎች ደቀ መዛሙርቱ አስክሬኑን እንደ ሰረቁ የሚገልጽ ልብ ወለድ ታሪክ ለማስወራት ተገደው ነበር። ይህ የአይሁድ መሪዎች ከትንሣኤው በኋላ ያሰራጩት ውሸት ነበር።

የአንዳንድ ጻድቃን መቃብሮች ተከፍተው ሙታኑ ለተወሰነ ጊዜ ሕያዋን ሆነው መቆየታቸውን የገለጸው ማቴዎስ ብቻ ነው። ማቴዎስ የትንሣኤው ጊዜ እስካለፈበት ቀን ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ አለመታየታቸውን ስለገለጸ፥ ምሑራን ይህ ክስተት ኢየሱስ ከሞት በተነሣበት እሑድ ጠዋት እንደ ተፈጸመ አምነዋል። ይህም በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ምክንያት ሞት በሰዎች ላይ የነበረውን ኀይል እንዳጣ ያሳያል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: