የኢየሱስ ትንሣኤ (ማቴ. 28:1-20)

ማቴዎስ ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ የሰጠው ገለጻ በጣም አጭር ነው። ብዙ ያተኮረው መቃብሩን ይጠብቁ በነበሩት ወታደሮች ላይ ነው። የመሬት መንቀጥቀጥ ሲነሣና መልአኩን ሲመለከቱ ምን ያህል እንደ ፈሩ ገልጾአል። ሊቀ ካህናቱ ለወታደሮቹ ገንዘብ በመክፈል የኢየሱስ ኣስከሬን ስለ ጠፋበት ሁኔታ ማመኻኛ ማቅረባቸውን አመልክቷል። በሮም ሕግ እስረኞች ካመለጡ ጠባቂ ወታደሮች ይገደሉ ነበር። የሃይማኖት መሪዎቹ የፈጠራ ታሪካቸውን ለማስፋፋት ሲሉ ወታደሮቹን ከጲላጦስ ቅጣት ለማዳን ቃል ገቡ።

ማቴዎስ ስለ ትንሣኤው እሑድ ሁለት አጋጣሚዎችን ብቻ አመልክቷል። በመጀመሪያ፥ ሴቶች ባዶውን መቃብር እንዳዩና መልአኩ የኢየሱስን ትንሣኤ እንዳበሰረላቸው ገልጾአል። ሁለተኛ፥ ኢየሱስ ለሴቶቹ እንደ ተገለጠ ጠቅሷል። እነርሱም አካሉን በመዳሰስ መንፈስ አለመሆኑን አረጋግጠዋል። አምላክነቱን በማወቅም ሰግደውለታል።

የውይይት ጥያቄ:- ማቴ. 29፡19-20 አንብብ። በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኙትን ትእዛዛትና የተስፋ ቃሎች ዘርዝር።

የማቴዎስ ታሪክ፥ ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በኋላ በገሊላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደተገናኘበት ሁኔታ ያመራል። ከዚያም ኢየሱስ ለዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርትና ለጠቅላላው ተከታዮቹ በሰጠው ተልዕኮ ላይ ያተኩራል። በዚህም ሦስት ጠቃሚ እውነቶችን ይጠቅሳል።

ሀ. ኢየሱስ ሙሉ መለኮታዊ ሥልጣን አለው። በዚህ ጊዜ የዳንኤል 7፡13-14 ትንቢት ተፈጽሟል። እግዚአብሔር አብ በሰማይና በምድር ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ሁሉንም የሚቆጣጠረው እርሱ እንጂ የአይሁድ ወይም የአሕዛብ መሪዎች ወይም ሰይጣን አልነበሩም። ክርስቲያኖች በሚገደሉባቸው ጊዜያት ኢየሱስ ነገሮችን በመቆጣጠር ላይ ያለ ላይመስል ቢችልም፥ አማኞች ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱና በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ድርጊቶች በሙሉ እንደሚቆጣጠር ማወቅ አለባቸው።

ለ. የኢየሱስ ተከታዮች የሚፈጽሙት ሥራ ነበራቸው። ይህም ወደ ሁሉም የጎሳ ቡድን ወንጌሉን ይዘው መሄድ ነው። በግሪኩ በዚህ ስፍራ “አሕዛብ” የሚለው የጎሳ ቡድን ማለት ነው፡፡) ሥራችን ግልጽ ነው። ኢየሱስ 12 ደቀ መዛሙርትን እንዳስተማረ ሁሉ፥ እኛም ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ አለብን። ኣዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት የእኛ ሳይሆኑ፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን አለባቸው። ይሁንና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት የምናደርገው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ በእነርሱ ምትክ ባቀረበው መሥዋዕት እንዲያምኑ እንመሰክርላቸዋለን። አለበለዚያ እንዴት የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ይችላሉ?

ሁለተኛ፥ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሆኑ አዳዲስ ክርስቲያኖች በሥላሴ ስም መጠመቅ አለባቸው። የኢየሱስ ይህ ድርጊትም ተከታዮች ብቻ ከሚያስተምሩት ማለትም አንዱ አምላክ (አብ፥ ወልድና መንፈስ ቅዱስ) ሦስት አካል መኖሩን የሚያመለክት መልካም ማረጋገጫ ነው። (ማስታወሻ፡- በቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን፥ አንድ ሰው የሚጠመቀው ባመነበት ቅጽበት ነበር። ዛሬ እንደሚታየው ሰው አምኖ ለመጠመቅ ብዙ ጊዜ አይቆይም ነበር (የሐዋ. 22፡16)፡፡

ሦስተኛ፣ ክርስቶስ ያዘዘንን ሁሉ ለአዳዲስ ክርስቲያኖች ማስተማር አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ክርስቲያኖች ነን እያሉ በታዛዥነት በማይመላለሱ ብዙ ሰዎች፥ መርካት የለባቸውም። የታዘዝነውም ሰዎችን እንድናሳምን ሳይሆን፥ ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ ነው። ደቀ መዝሙር ደግሞ በአንዳንድ እውነት ላይ የስምምነት ምልክት የሚያሳይ ሳይሆን፥ ሙሉ በሙሉ የሚከተል ነው። ይህ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በትጋት የማይወጡት ተግባር ነው። ሰዎች በክርስቶስ እንዲያምኑ ጥሩ አድርገው እየመሰከሩ፥ ነገር ግን አዳዲስ አማኞች እንደ እውነተኞች ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን የሚከተሉበትን ትምህርት፥ ጊዜ ወስደው አይሰጡም። ይህም ቤተ ክርስቲያን፥ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀደውን ያህል ባልተለወጡ ዓለማዊና ደካማ ክርስቲያኖች እንድትሞላ አድርጓታል።

ሐ. የክርስቶስ ተከታዮች፥ ክርስቶስ ሁልጊዜም አብሮን የሚኖር አማኑኤል እንደሆነ ማስታወስ አለብን።በግርግም የተወለደው ሕፃን አማኑኤል ተብሎ ተጠርቷል። አሁንም ከሞት የተነሣው ጌታ አማኑኤል ነው። በምድር ላይ ለሠላሣ ዓመታት በቆየባቸው ጊዜያት እንደ ነበረው፣ ለደቀ መዛሙርቱ በአካል ባይታይም፥ በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ አብሯቸው ይሄዳል። ከዚህ በበለጠ አደጋ፥ በአዳዲስ ጎሳዎች፥ መካከል ለክርስቶስ ተከታዮች ድፍረትን የሚሰጣቸው ምንድን ነው? አምስት ሺዎችን የመገበው፥ በውኃ ላይ የተራመደው፥ በሽተኞችን የፈወሰውና አጋንንትን ያስወጣው እርሱ ከእኛ ጋር ነው። የምንፈራበት ምክንያት የለንም። የክርስቶስ ተከታዮች እርሱ ያስተማረውን የደቀ መዝሙርነት ትምህርት ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ የሚፈለግባቸው ነገር አይኖርም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከዚህ «ታላቁ ተልዕኮ» ከተባለው ክፍል ለራስህና ለቤተ ክርስቲያንህ የተማርሃቸው ዐበይት ትምህርቶች ምንድን ናቸው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ መልካሙን የምሥራች ለሰዎች ሁሉና ለጎሳ ቡድኖች ሁሉ በተጠናከረ ሁኔታ የምታደርሰው እንዴት ነው? ሐ) ወንጌሉን ላልደረሳቸው ለማድረስና ላመኑት የደቀ መዝሙርነት ትምህርት ለመስጠት በግልህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? መ) በተማርኸው መሠረት፥ አዳዲስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን፥ እንደ ደቀ መዛሙርት በሚከተሉበት ጊዜ ሊማሯቸው ይገባል የምትላቸውን እውነቶች ዘርዝር፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: