1 እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሰዎች ከእርሱ ጋር ኅብረት የሚያደርጉበትን መንገድ ያዘጋጃል። ብዙውን ጊዜ ኃጢኣትን ከሚንቁ ሰዎች በተቃራኒ፥ እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ ነው። ስለሆነም በሰዎች ኃጢአትና ዓመፃ ላይ ይፈርዳል። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ እንደሚሞቱ ነግሯቸው ነበር (ዘፍጥ. 2፡16-17)። ይህ ሞት ሁለት ገጽታዎች ነበሩት። አንደኛው፥ የሰዎችን መንፈስ ከእግዚአብሔር የሚለይ ቅጽበታዊ የመንፈስ ሞት ነው። አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር በተደበቁ ጊዜ መንፈሳቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዳልሆነ አሳይተዋል። ሁለተኛው፥ ይኸው ሞት የኋላ ኋላ ሥጋዊ ሞትን አስከትሏል። ይህም የሰው መንፈስ ከሥጋው የሚለይበት ሁኔታ ነው።
ደኅንነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው አይደለም። እኛ እግዚአብሔርን እንደመረጥነው ወይም የደኅንነትን መብት የሚያስጨብጥ አንድ ትክክለኛ ነገር እንዳደረግን በምናስብበት ጊዜ፥ የኩራት ምልክት እናሳያለን። ለምሳሌ ለድሆች መመጽወት፥ ጥሩ ክርስቲያን መሆንና የመሳሰሉት ናቸው። ስለሆነም ብዙውን ጊዜ የዳንሁት በክርስቶስ ስላመንሁ ነው እንላለን። ይህ እውነት የሆነ አባባል ነው። ከማመናችን በፊት የደኅንነትን መንገድ ያዘጋጀልን እግዚአብሔር ነው። የደኅንነት ምንጩ እግዚአብሔር እንጂ ሰው አይደለም። ኣዳምና ሔዋን ኃጢአትን ከፈጸሙ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ለማደስ ሌላ መላ አልነበራቸውም። ስለዚህም ነው እግዚአብሔር የግድ ለእነርሱ አንድን ነገር ማድረግ የነበረበት።
በሰው ልጆች ታሪክ ሁሉ ውስጥ ሰዎች የራሳቸውን የደኅንነት መንገድ ለማግኘት ሲሞክሩ ኖረዋል። ነገር ግን ሰዎች ከእርሱ ጋር የሚታረቁበትን መንገድ ሊያሳይ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቡድሂስቶች፥ ሂንዱዎች፥ ሙስሊሞች፥ ሌሎችም ሕግን በመጠበቅና ጥሩ ሰዎች በመሆን የእግዚአብሔርን ይቅርታ ለማግኘት ይጥራሉ። ብዙ ክርስቲያኖችም ይህንኑ የተሳሳተ የይቅርታ መንገድ ይከተላሉ። አንዳንድ ሰዎች ብዙ ከጸለዩ፥ ሳያቋርጡ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሄዱ፥ አሥራታቸውን ከሰጡ፥ እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር የሚል ይመስላቸዋል። ይህ ግን የተሳሳተ ድርጊት ነው። እኛ ሰዎች በፈጣሪያችን ላይ ስላመፅን በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን የሚገባው ፈጣሪያችን ራሱ ነው። እግዚአብሔር እኛን እንዴት ይቅር ብሎ እንደሚያድነን የመወሰን ሥልጣን የለንም። ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን፥ እግዚአብሔር የይቅርታንና የዕርቅን በር ስለሚከፍትበት መንገድ ይናገራሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ለእግዚአብሔር አንድ ነገር በማድረግ ይቅርታን ሊያገኙ እንደሚችሉ የሚያስቡበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ አመለካከት የተሳሳተ የሚሆነው ለምንድን ነው?
እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ኅብረትን ለመመሥረት የተጠቀመው በመሥዋዕት ነው። በዕብራውያን 9፡22 ላይ፥ «ደም ሳይፈስ ስርየት የለም» የሚል ቃል እናነባለን። እግዚአብሔር ቅዱስና ጻድቅ አምላክ በመሆኑ፥ በኃጢአተኞች ላይ በጽድቅ ሳይፈርድ እንዲሁ በደፈናው ይቅር አይላቸውም። ነገር ግን እግዚአብሔር የፍቅርና የምሕረት አምላክ በመሆኑ፥ ለይቅርታ የሚሆን መንገድ ያዘጋጅላቸዋል። እግዚአብሔር እንስሳት ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ በመደንገግ፥ «ሕይወት ለሕይወት» የሚል መንፈሳዊ መርሕ መሥርቷል።
በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን በኃጢአተኞች ምትክ የሚሰዉ ጊዜያዊ እንስሳትን አዘጋጅቷል (ዕብ. 10፡1-14)፡፡ እግዚአብሔር ለአዳምና ለሔዋን ቆዳን በማልበስ የእንስሳት መሥዋዕት ማቅረብ እንዳለባቸው አስተምሯል። የኣዳምና ሔዋን ልጆች የሆኑት ቃየንና አቤል ይህንን የአምልኮ ሥርዓት ያውቁ ነበር። በተቀረው የብሉይ ኪዳን ሰዎችም እግዚአብሔርን የሚያመልኩት የእንስሳትን መሥዋዕት በማቅረብ ነበር። ሰዎች ይኖሩ ዘንድ የእንስሳቱ መሞት የግድ ነበር። ምንም እንኳ እንስሳት ኃጢአት ባይሠሩም በሌሎች ምትክ በመሞት የኃጢአትን ዋጋ ለመክፈል ተገድደው ነበር። ይህንን የምትክ ሞት ለማሳየት፥ አብዛኛውን ጊዜ መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ሰው እጆቹን በሚሠዋው እንስሳ ላይ በመጫን ኃጢአቱን ይናዘዝ ነበር (ዘዳግ. 29፡10፤ ዘሌዋ. 16፡21)። እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳንና በቤተ መቅደስ የአምልኮን ሥርዓት ሲመሠረት፥ ሥርዓቱ መሥዋዕቶችን እንዲያካትት አድርጓል (ዘሌዋ. 1-5)።
ነገር ግን እንስሳት ለኃጢኣት ችግርና ለይቅርታ ጊዜያዊ መፍትሔዎች ብቻ ነበሩ። እግዚኣብሔር ክርስቶስን ፍጹምና የመጨረሻው መሥዋዕት አድርጎ ለመላክ ሲያቅድ ቆይቷል። ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ «ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ እንደ ተመረጠ» የሚናገረው (1ኛ ጴጥ. 3፡19-20)። የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ወደ ክርስቶስ መሥዋዕት የሚያመለክቱ ነበሩ። ምንም ኃጢአት ባይገኝበትም፥ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ልጅ የሆነው ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞተ። በመስቀሉ ላይ ክርስቶስ የሰዎችን ሁሉ ኃጢኣት ተሸከመ። ከአዳምና ሔዋን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት በሚጀመርበት ጊዜ እስከሚኖሩት የመጨረሻዎቹ ሰዎች ድረስ ይህን አደረገ (ዕብ. 9፡26-28)። ለዚህም ነው «የእግዚአብሔር በግ» የሆነው ክርስቶስ ( ዮሐ. 1፡29)፤ «እኔ መንገድ፥ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በቀር ማንም ወደ አብ ሊመጣ አይችልም።» ያለው (ዮሐ. 14፡6)። ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ለሰዎች ሁሉ የሚሆን መሥዋዕት ለኣንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቀረበ (ዕብ. 9፡26-27)። ለሰው ልጆች የራሱን ሕይወት ሰጠ። ጳውሎስ እንዳለው፥ «እኛ ከእርሱ ጋር ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢኣት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው» (2ኛ ቆሮ. 5፡21)፡፡
2 እግዚአብሔር ሰዎች እንደገና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዲመሠርቱ ዕድል ይሰጣቸዋል። እግዚአብሔር ሰዎች ከእርሱ ጋር የሚታረቁበትን መንገድ ቢያዘጋጅም፥ ማንንም አያስገድድም። ምርጫው የሰዎቹ ነው። በዓመፃችንና በኃጢአታችን ልንቀጥል ወይም ሰው ሠራሽ መንገዶቻችንን ልንከተል እንችላለን። ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ያዘጋጀውን መሥዋዕት ተቀብለን ከአምላካችን ጋር ልንታረቅ ዕድል አለን። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሁለቱ አንዱን መንገድ የመምረጥ ዕድል ቢሰጥም (ማቴ. 7፡13-14)፥ እነዚህ ሁለት መንገዶች ወዴት እንደሚወስዱን መጨረሻውን ልንቀይር አንችልም። ስለሆነም የዐመፀኛነትንና ሰውን ያማከለ አምልኮ ከመረጥን፥ የዘላለምን ፍርድ እንደምንቀበል እግዚኣብሔር ያስጠነቅቀናል (ዮሐ. 8፡24፤ 12፡46-48)። ነገር ግን የእርሱን የደኅንነት መንገድ ከተቀበልን ልጆቹ እንደምንሆን (ዮሐ 1፡12)፥ የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝና (ዮሐ 3፡16)፥ ለዘላለም በበረከቶቹ ደስ እየተሰኘን ከእርሱ ጋር እንደምንኖር ይነግረናል (ራእይ 20)፡፡
ወንጌሉን በምንመሰክርበት ጊዜ በአብዛኛው ይህንን እንደ ቀላል ውሳኔ እንመለከተዋለን። «በክርስቶስ እመንና ዳን» እንላለን። ምንም እንኳ ይህ ቀላል አሳብ እውነት ቢሆንም፥ እግዚአብሔርን ለመከተል በምንመረጥበት ጊዜ ልንገነዘባቸው የሚገቡንን ሌሎች ጉዳዮች ይሰውርብናል። በመልካም ወጥ ውስጥ የተለያዩ ቅመሞች እንደሚጨመሩ ሁሉ፥ እምነታችንም እውነተኛ እንዲሆን ከተፈለገ አያሌ የተለያዩ ነገሮችን ማካተት አለበት። የሚከተሉት ለእውነተኛ ደኅንነት የሚያስፈልጉ አንዳንድ “ቅመሞች” ናቸው፡፡
ሀ. ትሕትና፡- የኃጢአት ሁሉ ማዕከል ትዕቢትና ዓመፅ ነው። ሔዋን ኃጢኣትን በፈጸመች ጊዜ፥ ድርጊትዋ «የራሴን መንገድ በመምረጥ የምፈልገውን ኣደርጋለሁ፤ ለእግዚአብሔርም አልገዛም» የሚል ነበር። ኃጢአትን በምንሠራበት ጊዜ ሁሉ ለእግዚአብሔርና ለመንገዶቹ ከመገዛት ይልቅ በራስ ወዳድነት እየተመላለስን የራሳችንን ክብርና ምቾት ለመጠበቅ እንሻለን።
የውይይት ጥያቄ፡- ባለፈው ሳምንት የፈጸምሃቸውን ኃጢአቶች ዘርዝር። ትዕቢት፥ ዓመፅና ራስ ወዳድነት የእነዚህ ኃጢአቶች ምንጭ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ የሚያደርገን ራሳችንን ስናዋርድ ብቻ እንደ ሆነ በተደጋጋሚ ይናገራል (ያዕ. 4፡6፤ 10፤ 1ኛ ጴጥ. 5፡5-6)። እግዚኣብሔር ትዕቢተኞችን ይጠላል፤ ትሑታንን ግን ያከብራል (ኢሳ. 2፡12፤ 13፡1)። ስለሆነም ደኅንነትን ለማግኘት ወደ እግዚአብሔር በምንመጣበት ጊዜ ሊኖረን የሚገባው የመጀመሪያው “ቅመም”፥ ለራሳችን ጥቅም ሳይሆን ለእግዚአብሔር ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ነው። ፍጥረት ለፈጣሪው የመገዛትን አመለካከት ሊያሳይ ይገባል። በልባችን ውስጥ የትዕቢትና የዓመፅ አመለካከት ካለ እውነተኛ ደኅንነት ሊኖረን አይችልም።
ለ. ንስሐ፡- መጥምቁ ዮሐንስ «ንስሐ ግቡ» በማለት እየሰበከ ነበር የመጣው (ማቴ. 3፡2)። ክርስቶስም ንስሐን ሰብኳል (ማቴ. 4፡17)። ጴጥሮስ በመጀመሪያው ስብከቶቹ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ አሳስቧቸዋል (የሐዋ. 2፡38)። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር ዕርቅ ለማድረግ ከተፈለገ፥ የንስሐ ቅመም መኖር አለበት። ነገር ግን ብዙ ክርስቲያኖች የዚህን ቃል ትርጉም በትክክል አይገነዘቡም። ንስሐ ስንገባ ወይም እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር እንዲልልን ስንጸልይ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔር ለኃጢአታችን ቀለል ያለ አመለካከት እንዲኖረው የምንጠይቅ ይመስላል። «እግዚአብሔር ሆይ ኃጢአትን ፈጽሜአለሁ። ነገር ግን እርሳው እንላለን»። ነገር ግን እግዚኣብሔር ጻድቅ አምላክ በመሆኑ፥ ኃጢአትን ሊረሳ አይችልም። ኃጢአት ቅጣትን ያስከትላል። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለመሞት የተገደደው ለዚህ ነው። ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት እንዲችል ዋጋውን ከፍሏል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ ሁለት ዐበይት እውነቶችን ያካትታል። አንደኛው፥ ስለ ማንነታችንና ስለፈጸምነው ተግባር እውነተኛውን ነገር ተቀብለን በእግዚአብሔር ፊት ስለ ዓመፀኛነታችን እንናዘዛለን። ለተግባራችን ማመኻኛ ሳናቀርብና ሌላውን ሰው ወይም ነገር ሳንወቅስ ጥፋታችንን በሙሉ አምነን እንቀበላለን። የፈጸምናቸውን ኃጢኣቶች አንድ በአንድ እንዘረዝራለን። ይህ በተለይ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን በኋላ ለምንፈጽመው ኃጢአት የሚሠራ መርሕ ነው። «እግዚአብሔር ሆይ፥ ኃጢአተኛ ነኝና ይቅር በለኝ» ማለቱ ብቻ አይበቃም። «እግዚአብሔር ሆይ፤ ለእገሌ ውሸት ተናግሬአለሁና ይቅር በለኝ» ወይም «ክፉ አሳብ በልቤ አስተናግጃለሁና ይቅር በለኝ» ማለት አለብን። ዛሬ ስለ ሰረቁት ገንዘብ፥ ስለ ጥላቻቸው፥ ስለ መከፋፈላቸውና ስለ ትዕቢታቸው ላይገልጹ፥ በደፈናው «ይቅር በለኝ» እያሉ የሚጸልዩ ብዙ ክርስቲያኖች አሉ። ለእግዚአብሔር ኃጢአቶቻችንን ዘርዝረን በመናዘዝ ይቅር እንዲለንና እነዚህን ኃጢአቶች የምናሸንፍበትን ኃይል እንዲሰጠን እስካልጠየቅን ድረስ፥ ከኃጢአት የፀዳ ሕይወት መኖር አንችልም። ቤተ ክርስቲያናችንም የተቀደሰች ልትሆን አትችልም። ብዙዎቻችን ዝርዝር ኃጢአቶቻችንን በጥቅል የይቅርታ ጸሎት ሥር እንደብቃለን። ለዚህም ነው ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እግዚአብሔርን መፍራትና የቅድስና ሕይወት ጠፍቶ ስናይ የምንደነቀው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በዚህ ሳምንት ውስጥ የፈጸምሃቸውን ኃጢአቶች ዘርዝርና እግዚኣብሔር እነዚህን ዝርዝር ኃጢኣቶች ይቅር እንዲልህ ጠይቅ። ለ) ከእነዚህ ኃጢአቶች መካከል በሌሎች ሰዎች ላይ የተፈጸሙት የትኞቹ ናቸው? ወደ ሰዎቹ ሂድና እነርሱንም ይቅርታ ጠይቃቸው።
ሁለተኛው፡- መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ የአሳብንና የድርጊትን ለውጥ ያካትታል። እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን ከጸለይን በኋላ በእርሱ ፊት መጥፎ ተግባር መፈጸማችንን ከቀጠልን ንስሐ አልገባንም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንስሐ የሚሰጠው ማብራሪያ አንድ ሰው ወደታች እየሄደ ሳለ አሳቡን ቀይሮ ወደ ላይ የሚመለስበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ስለሆነም፥ ለደኅንነት ንስሐ መግባት ማለት፥ በራስ ወዳድነት፥ በኃጢኣትና በዓመፅ ጎዳና ቁልቁል አልሄድም ብሎ መወሰን ነው። ይልቁንም አቅጣጫችንን ለውጠን ለእግዚአብሔር በመገዛት የታዛዥነትን መንገድ መከተል ነው። ደኅንነትን ካገኘን በኋላ ይኸው ተመሳሳይ አመለካከት በንስሐችን ውስጥ መኖር አለበት። ያደረግነው ነገር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ እንደሆነ አምነን ሳንቀበል እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን መጠየቁ ፋይዳ የለውም። ወይም ደግሞ ከኃጢአት ተመልሰን እግዚአብሔርን በሚያስከብር አቅጣጫ ካልተጓዝን ይቅርታን እናገኝም።
ሐ. እምነት፡- በዕብ.11፡6 ላይ፥ «ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም» የሚል ቃል እናነባለን። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ተጽፎ የምናገኘው ሌላው ጭብጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት በልባችን ውስጥ ያለ ስሜት አይደለም። ወይም ደግሞ በእግዚአብሔር ማመን አለብን እያልን ለራሳችን የምንናገረው ተጨባጭነት የሌለው አሳብ ኣይደለም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት፥ እግዚአብሔር በሚገልጠው እውነት ውስጥ ለመኖር መወሰን ነው። አብርሃም፣ የእምነት አባት ነበር። የእርሱ እምነት ግን ስሜት ብቻ አልነበረም። ነገር ግን እግዚአብሔር ወደ አብርሃም መጥቶ ራሱን በገለጠለት ጊዜ፥ የተስፋ ቃልና የሚታዘዘውን ነገር ሰጠው (ዘፍጥ. 12፡1-3)። በዚህ ጊዜ አብርሃም በእግዚአብሔር ቃል ላይ በመመሥረት ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ መምረጥ ነበረበት። የማይቻል ቢመስልም እንኳ ሕይወቱን እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ ላይ ለመመሥረት ወሰነ።
በብሉይም ሆነ አዲስ ኪዳን ሰዎች ከእግዚኣብሔር ጋር ኅብረት ለማድረግ ከፈለጉ፥ ይህንኑ የእምነት መርሕ መከተል ይኖርባቸዋል። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለደኅንነት የተሰጠው ትእዛዝ ግልጽ ነው፤ «በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እመንና ዳን» (ዮሐ 16፡3)። በክርስቶስ ካመንን የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝ የተስፋ ቃል ተሰጥቶናል (ዮሐ. 3፡16)።
የሚያድን እምነት ሦስት ነገሮችን ማካተት አለበት። አንደኛው፥ እውነት መኖር አለበት። የሚያድነን እምነት አይደለም። የማንኛውም ሃይማኖት ተከታዮች እምነት አላቸው። ነገር ግን የብዙዎቹ እምነት እውነት ባልሆነ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። እምነታችን የሚያድን እምነት እንዲሆን ከተፈለገ፥ ትክክለኛ ዕውቀትና ትክክለኛ እምነት ሊኖረው ይገባል። ለዚህ ነው ጳውሎስ እምነት ከመስማት እንደሚመጣና የምንሰማው ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደሆነ የሚነግረን (ሮሜ 10፡17)። እንግዲህ ለመዳን ልናውቀው የሚገባን እውነት ምንድን ነው? ይህ እውነት ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ እንደ ሞተ፥ የኃጢአታችንን ቅጣት እንደ ከፈለና በእርሱ በማመን ብቻ ልንድን እንደምንችል የሚያመለክት ነው።
ሁለተኛው፥ ምርጫ እንድናደርግ የሚረዱን የተስፋ ቃሎች አሉ። እግዚአብሔር አብርሃምን ለመባረክ የተስፋ ቃል ሰጥቶታል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ቤተሰቡን ትቶ እግዚአብሔር ወደሚያሳየው ስፍራ እንዲሄድ የሚያደርግ ትእዛዝም ሰጥቶታል። አብርሃምም በእግዚአብሔር ኣመነ፤ የእምነቱንም እውነተኛነት በመታዘዝ ገለጠ። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የተስፋ ቃል ሰጥቶናል። በኢየሱስ ክርስቶስ ካመንን ኃጢአታችን ሁሉ ይቅር እንደሚባልልን፥ ከእርሱ ጋር እንደምንታረቅ፥ ልጆቹ እንደምንሆንና የዘላለምን ሕይወት እንደምናገኝ ገልጾአል። ይህንን ሁሉ ለማግኘት ግን በክርስቶስ እንድናምን የተሰጠንን ትእዛዝ ማክበር አለብን።
ሦስተኛው፥ እውነተኛ በሆነውና ተስፋ በተሰጠው ነገር መሠረት ለመመላለስ ቃል መግባት ያስፈልጋል። ብዙ ሰዎች ክርስቲያኖች ነን ቢሉም እናምናለን በሚሉት እውነት መሠረት አይመላለሱም። አብርሃም ቤተሰቡን ትቶ ወደ ከነዓን ባይሄድ ኖሮ የሚያድን እምነት አይኖረውም ነበር። እኛም ብንሆን በቤተሰባችን የሃይማኖት ውርስ፥ በመልካም ተግባራችንና በመሳሰለው መተማመናችንን ትተን በክርስቶስ ብቻ ካላመንን የሚያድን እምነት ሊኖረን አይችልም። የሚያድን እምነት ማለት ለእግዚአብሔር እየተገዙ መታዘዝ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በክርስቶስ ባመንህ ጊዜ እነዚህ ሦስት የእምነት ክፍሎች ተግባራዊ ስለሆኑበት ሁኔታ አብራራ። ለ) ለማመን የሚፈልጉ ሰዎች ስለሚያድን እምነት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማድረግ፥ ከወንጌል ምስክርነታችን ውስጥ ልንለውጠው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
መ. ይቅርታ፤ እግዚአብሔር የሚያድን እምነት በሚኖረን ጊዜ ሊሰጠን ተስፋ ከገባቸው ነገሮች መካከል፥ ይቅርታን እንደምናገኝና ከእርሱ ጋር ኅብረት እንደምናደርግ ነው። ከእግዚአብሔር ዘንድ ሁለት ዓይነት ይቅርታን እናገኛለን። አንደኛው፥ እግዚአብሔር ከዐመፀኛነት ወደ ልጅነት ይመልሰናል። ይህም ‹ጽድቅ› ይባላል። እግዚአብሔር በደለኞች አይደላችሁም ሲል ያውጃል። ጳውሎስ የሚያድን እምነት ያላቸው ሰዎች እንደማይኮነኑ ገልጾአል (ሮሜ 8፡1)። ምንም እንኳ ኃጢኣት ልንሠራ ብንችልም፤ ኃጢአታችን በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ያለንን ተቀባይነት (የዘላለምን ሕይወት ተስፋ) አይነጥቀንም። ይህ ለኃጢአታችን ሁሉ ስርየት የሚደረግበትና የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚደረግ ይቅርታ ነው።
ሁለተኛው፥ የፈረሰውን ኅብረት ከእግዚአብሔር ጋር ለመቀጠል የምንቀበለው ይቅርታ አለ። ሁላችንም ወደ ሰማይ እስክንደርስና እግዚአብሔር የኃጢአት ተፈጥሯችንን እስኪያስወግድ ድረስ በየጊዜው ኃጢኣት መሥራታችን የማይቀር ነው። ይህ ኃጢኣት ግን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነታችንን ወይም የዘላለም ሕይወታችንን አይቀማንም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት ያቋርጣል። በዮሐንስ 1፡9 ላይ እንደተገለጸው፥ ኃጢአታችንን ብንናዘዝ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለንና ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ክርስቶስ የእነዚህን ኃጢአቶች ቅጣት ቀደም ሲል በመስቀል ላይ ስለ ከፈለ፥ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ብሎ የተበላሸውን ኅብረት ያድሰዋል።
ይቅርታ በደል እንዳልተፈጸመ ቆጥሮ ‹መርሳት› ማለት አይደለም። ሁልጊዜ ኃጢአትን የፈጸመው ሰው ምንም ዓይነት የኃጢአት ፍሬ አይቀበልም ማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ከኣንድ ሰው ገንዘብ ከሰረቅን በኋላ ግለሰቡን ይቅርታ ከጠየቅን ገንዘቡን ከመክፈል ነፃ እንደምንሆን እናስባለን። ነገር ግን ኅብረቱን ብቻ ሳይሆን ገንዘቡንም እስካልመለስን ድረስ በኃጢአታችን ተጸጽተን እውነተኛ ይቅርታ አልጠየቅንም ማለት ነው (ዘሌዋ. 6፡1-7)። የወሲብ ኃጢኣት ፈጽመን እግዚአብሔርን ይቅርታ ብንጠይቅም፥ ከእርግዝና፥ በኤድስ ከመያዝ ወይም ከትዳር ጓደኛችን ጥርጣሬ ልንድን አንችልም።
ሠ. መታዘዝ፡- ኃጢኣት ፍጡር በፈጣሪው ላይ የሚፈጽመው ዓመፅ ነው። ስለሆነም ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ኅብረት በሚስተካከልበት ጊዜ እግዚአብሔር በፈጣሪና በፍጡሩ መካከል እንዲኖር ወደሚፈልገው ግንኙነት እንመላለሳለን ማለት ነው። ይህም እግዚአብሔርን የምንታዘዝበት ግንኙነት ነው። ክርስቶስ አንድ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ፥ «ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ ትሉኛላችሁ፥ የምለውንም አታደርጉም» ብሏል (ሉቃስ 6፡46)። ከእግዚአብሔር ጋር ለምናደርገው ኅብረት ትልቁ ነገር እርሱን በመታዘዝ መመላለሳችን ነው።
ሁለት ዓይነት መታዘዝ እንዳለ ማወቅ ይኖርብናል። ኣንደኛው፥ አንድ አገልጋይ ቅጣት ፈርቶ የሚያደርገው መታዘዝ ነው። ወይም ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍቅርና በረከት ለመቀበል ሲባል የሚደረግ መታዘዝ ነው። ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን የሚታዘዙት እነዚህን ሁለት አመለካከቶች ይዘው ነው። ካልታዘዝን ይቀጣናል በሚል ፍርሃት ይታዘዙታል። ወይም ደግሞ በራስ ወዳድነት የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት ሲሉ ይታዘዙታል። ይህ አንድ ልጅ አባቱ ለትምህርት ቤት ክፍያ ገንዘብ ይሰጠው ዘንድ ወደ እንጨት ለቀማ ከሄደበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ አይደሉም።
ሁለተኛው፥ ከምስጋናና ከፍቅር የሚመነጭ ታዛዥነት ነው። ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ አንድ ነገር ለማግኘት ሳይሆን፥ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት የሚደረግ ነው። በመጀመሪያ የወደደንን እግዚአብሔርን ስለምንወደው፥ እርሱን ደስ ልናሰኘው እንፈልጋለን። ስለሆነም የማያስደስቱትን ነገሮች በማድረግ ልናሳዝነው አንፈልግም። የሚያስደስቱትን ነገሮች ደግሞ ከልባችን እናደርጋለን። ስለሆነም፥ ከፍርሃት ወይም አንድ ነገር ከመፈለግ የተነሣ ሳይሆን፥ ልናስደስተው ስለምንፈልግ እግዚአብሔርን እንታዘዘዋለን። እግዚአብሔር ከመንፈሳውያን ልጆቹ የሚፈልገው የዚህ ዓይነቱን ታዛዥነት ነው። ጳውሎስ እንዳለው፥ እኛ ልጆቹና ወራሾቹ እንጂ ባሮቹ አይደለንም (ገላ. 4፡1-7)።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እንድ ክርስቲያን ከፍርሃትና አንድን ነገር ለማግኘት ከመፈለግ ወይም ከፍቅር የተነሣ እንዴት እግዚአብሔርን ሊታዘዝ እንደሚችል በምሳሌ እብራራ። ለ) በእነዚህ እግዚአብሔርን መታዘዝ በሚቻልባቸው ሦስት አመለካከቶች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ሐ) ብዙውን ጊዜ የምትለማመደው ታዛዥነት የትኛውን ነው?
3 እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የሚያደርገው ግንኙነት በቃል ኪዳኑ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ መሠረት ከሰዎች ጋር ግንኙነት የመመሥረቱ አሳብም፥ ሌላው በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ትኩረት የተሰጠው እውነታ ነው። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱሳችን «ብሉይ ኪዳን» እና «አዲስ ኪዳን» ተብሎ በሁለት የተከፈለው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ሁለት የተለያዩ ቃል ኪዳኖችን ሲገባ እንመለከታለን። አንደኛው፥ በሕዝቡ መታዘዝና አለመታዘዝ ላይ የተመሠረተ ቃል ኪዳን ነው። ይህ ባለ ሁለት ወገን ቃል ኪዳን ነው። ለዚህ ዋንኛ ምሳሌ የሚሆነን እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር በሲና ተራራ ላይ ያደረገው ነው። በዚያ ስፍራ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን፥ «እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዛት ብትቀበሉ እኔ መሪያችሁና ጠባቂያችሁ እሆናለሁ፤ እባርካችኋለሁ» ብሏቸው ነበር (ዘዳግ. 6፡25፣ 7፡12)። ስለሆነም፥ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረው ግንኙነት ሁለቱም ባለ ቃል ኪዳኖች ማድረግ የሚጠበቅባቸው ነገር እንዳለ የሚያመለክት ነበር። እስራኤል እግዚአብሔርን ለመታዘዝና በፊቱም በታማኝነት ለመመላለስ ቃል ገባ፡፡ እግዚአብሔርም አይሁዶችን ለመባረክ ቃል ገባ። በቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ቃል ኪዳን፥ እንደ አይሁዶች፥ የሚቀበሉ ወገኖች ድርሻቸውን በማይወጡበት ጊዜ ሊፈርስ ይችላል። ስለሆነም የብሉይ ኪዳን አብዛኛው ክፍል የሚያሳየው እስራኤል የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ባለመታዘዙ ፍርዱን እንደ ተቀበለ ነው።
ሁለተኛው፥ በቅድመ ሁኔታ ላይ ያልተመሠረተ ቃል ኪዳን አለ። ይህም በኤርምያስ 31፡31-34 ላይ እግዚአብሔር ስለሚሰጠው ስለዚሁ ኣዲስ ኪዳን እናነባለን። ይህ ባለ ሁለት ወገን ኪዳን ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ብቻ ተግባራዊ የሚያደርገው ቃል ኪዳን ነው። የ27ቱ መጻሕፍት መጠሪያ የሆነው፥ «አዲስ ኪዳን» የሚለው ስያሜ፥ እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ከሰው ልጆች ጋር ያደረገውን ይህንኑ ቃል ኪዳን ያመለክታል። እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሕዝቡ በረከቱን ከመቀበላቸው በፊት እንዲታዘዙት አይጠይቅም። ነገር ግን እግዚአብሔር ሰዎች በክርስቶስ ይቅርታ አምነው ልጆቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል። ሰዎች ሊያደርጉ የሚገባቸው ነገር ቢኖር በእምነት እጆቻቸውን ዘርግተው የእግዚአብሔርን ስጦታ መቀበል ብቻ ነው። ከእንግዲህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት እርሱን ለመታዘዝና ቅዱሳን ለመሆን በሚያደርጉት ጥረት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ለቅድስናና ለይቅርታ ባዘጋጀው መንገድ ላይ የሚመሠረት ይሆናል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል ያሉትን ልዩነቶች በራስህ አገላለጽ ጻፍ። ለ) በአዲስ ኪዳን ውስጥ የመኖር በረከት የተሰጠን ለምንድን ነው? ከበረከቶቹ አንዳንዶቹን ዘርዝር።
4 ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዓላማና የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ከሚታዩ ጭብጦች መካከል እንዱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ለዓለም የወሰነው ዕቅዱ ማዕከል መሆኑ ነው። በብሉይ ኪዳን ውስጥ የክርስቶስ መኖር የተረጋገጠ ቢሆንም በግልጽ ኣልተጠቀሰም ነበር። ለምሳሌ፥ በብሉይ ኪዳን ስለ ልዩ የእግዚአብሔር መልአክ የተጻፈውን እናነባለን። እርሱም የእግዚአብሔር መልእክተኛ እግዚአብሔር ነው (ለምሳሌ፥ ዘፍጥ. 16፡7፥ 13፥ 22፡ 11-18፤ ዘዳ 3፡2፥ 4)። ብዙ ምሁራን ይህ ልዩ መልአክ ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ዘመን ራሱን የገለጠበት መንገድ እንደሆነ ያምናሉ።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ለዓለም ችግር የእግዚኣብሔር መፍትሔ ይሆን ዘንድ የሚላክ ልዩ መልእክተኛ ነበር። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ትንቢት የተናገረው በዘፍጥረት 3፡15 ላይ ሲሆን፥ የሲቲቱ ዘር የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጥ ተገልጾአል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን በመስቀል ላይ እንዳሸነፈው አንድ ቀን ደግሞ እባብ የሆነውን ሰይጣንን ወደ እሳት ባህር ውስጥ እንደሚወረውረው ከአዲስ ኪዳን እንረዳለን (ቆላ. 2፡13-15፤ ራእይ 20፡7-10)። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ዕቅድ ቀስ በቀስ ሲገለጥ፥ እግዚአብሔር ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሌሎች በርካታ መረጃ ዎችን ይሰጥ ጀመር። ያዕቆብ «ዘንግ» ሲል ጠርቶታል። ይህም ክርስቶስ የእስራኤል ሕዝብ ንጉሥ እንደሚሆን ያሳያል (ዘፍጥ. 49፡10)። ሙሴ ክርስቶስ ከእርሱ የሚበልጥ ነቢይ እንደሆነ በመግለጽ፣ የእስራኤል ሕዝብ እንዲሰሙት አዝዟል (ዘዳግ. 18፡5-18)። እግዚአብሔር ለዳዊት ዘሩ ለዘላለም እንደሚነግሥ ገልጾአል (2ኛ ሳሙ. 7፡12-16)። በብሉይ ኪዳን መጨረሻ አካባቢ እግዚአብሔር ስለ ክርስቶስ የሚሰጠው መገለጥ ይበልጥ እያበራ መጣ። በሥጋ የሚገለጥ አምላክ (አማኑኤል) እንደሚሆን ተገለጸ (ኢሳ. 7፡14)። መሢሕ እንደ መሆኑ መጠን፥ የእስራኤል ብቻ ሳይሆን የዓለምም ገዥ ይሆናል (ኢሳ. 42፡1፤ 55፡3-5)። ለመላው ዓለም ኃጢአት መሥዋዕት ይሆናል (ኢሳ. 53፡4-5፤ 10-12)።
የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ ብቻ ሳይሆኑ፥ አገልግሎቱንም በልዩ ልዩ ተምሳሌቶች ገልጸዋል። ስለሆነም ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች ሁለተኛው መሥመር የሆነው ሁለተኛው አዳም ነው (ሮሜ 5፡12-14፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡45-49)። ክርስቶስ ከአሮን የሚበልጥና እንደ መልከ ጼዴቅ ካህንና ንጉሥ የሆነ ሊቀ ካህናት ነው (ዕብ 6፡20፤ 7፡516)። የብሉይ ኪዳን ጊዜያዊ መሥዋዕቶች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ በመስቀል ላይ እንደ «እግዚአብሔር በግ» ይሞት ዘንድ ወደሚላክበት የመጨረሻው መሥዋዕት ያመለክታሉ። ምንም እንኳ ክርስቶስ እንደ ሁለተኛው የሥላሴ አካል በብሉይ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ባይነገርም፥ በብሉይ ኪዳን ውስጥ መኖሩ ግን ግልጽ ነው።
ይህ «ተሰውሮ የነበረው» ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ታወቀ። የዕብራውያን ጸሐፊ እንደገለጸው፥ «ከጥንት ጀምሮ [በብሉይ ኪዳን ዘመን] እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፤ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢኣታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ» ይላል (ዕብ 1፡1-3)። በቤተልሔም በግርግም ውስጥ የተወለደው ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠው አምላክ ነበር። የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን በመፈጸም ለሰዎች የእግዚአብሔር ፍጹምና የመጨረሻ መሥዋዕት ሆኖ ተሠውቷል። አዲሱን የእግዚአብሔር ሕዝብ (ቤተ ክርስቲያን) የመሠረተው እርሱ ነው። ይህ አዲስ አካል ከኣንድ ጎሳ ሳይሆን፥ በምድር ላይ ከሚገኙ የተለያዩ ወገኖች የተመሠረተ አካል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አሳቡን የሚቋጨው፥ ክርስቶስ በምድር ሁሉ ላይ ለመግዛት አንድ ቀን እንደሚመለስ በመግለጽ ነው። በዚህም ኃጢኣትና ሞት የማይኖርበትን ዘላለማዊ መንግሥት ይመሠርታል። (ራእይ 19-21)
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ እንዴት በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንደ ተሰወረና በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንደ ተገለጠ ምሳሌዎችን በመስጠት አብራራ። ለ) ክርስቶስ የእግዚአብሔር ዕቅዶች ማዕከል የመሆኑ እውነት፥ ብሉይና አዲስ ኪዳንን ስለምንረዳበት መንገድ ምን ያስተምረናል?
የውይይት ጥያቄ፡- ሁለት ዓምዶች ባሉት ሠንጠረዦች ሥር በግርጌ በኩል፥ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ያሉትን ዐበይት ጭብጦች ጻፍ። በግራ በኩል ባለው ዓምድ፥ እነዚህ ጭብጦች የሚገኙባቸውን የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ጻፍ። ለእያንዳንዱ ጭብጥ፥ የብሉይ ኪዳን ርእሰ ጉዳዮች በአዲስ ኪዳን የተገለጹባቸውን ቢያንስ 5 ምሳሌዎች ስጥ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)
ስለ ሁሉ አስቀድሜ ሁሉን የሰራና ያዘገጀ እግዚአብሔር ይክብር፤ እንግድህ ይህንን ጥበብና መስተዋልንም በዉስጥህ ያኖረዉ ጌተችንና መድሃንተችን ኢያሱስ ይበርክ፤በጠም ተበርኬዋለሁ ጌታ ዘመንህን በሙሉ ይበርክ።