በብሉይና በአዲስ ኪዳን መካከል የነበረው ዘመን

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ታሪካችን ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚፈጸሙት ነገሮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ለ) ታሪክን ማጥናት የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙት ነገሮች ባለፉት 100 ዓመታት ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር የሚተሳሰሩ ናቸው። የምኒልክ፥ የኃይለ ሥላሴ፥ የደርግና የኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመናት ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙትን ክስተቶች ይወስናሉ። የኢትዮጵያ ድንበሮች፥ የመሬት ይዞታ አመለካከቶች፥ የኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖት ግንኙነቶችና የመሳሰሉት ታሪካዊ መሠረት ያላቸው ነገሮች ናቸው። ስለዚህም ዛሬ ፍሬያቸውን እንመገባለን።

ይህም ሆኖ ዛሬ የሚከሰቱት ነገሮች ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ውጤቶች ብቻ አይደሉም። በሰፊው ዓለም ውስጥ የተፈጸሙት ነገሮችም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል። በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓውያን ኣፍሪካን በቅኝ ለመግዛት ያካሄዷቸው ተግባራት፥ ለምሳሌ ጣሊያኖች አንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎችን መግዛታቸው በዛሬዎቹ ክስተቶች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በኃይለ ሥላሴና በደርግ ዘመን፥ በሩሲያና በአሜሪካ መካከል የነበረው ትግል ዛሬም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጥሏል። ለምሳሌ፥ የምዕራቡ ዓለም ፈሊጥ የሆነው ፋሽን፥ ቪዲዮና የእንግሊዝኛ ቋንቋ በወጣቶቻችን ስሜት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ላይ ይገኛል።

በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ከአዲስ ኪዳን ዘመን በፊትም ሆነ በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ በእስራኤልና በሌሎች አገሮች ውስጥ ይካሄዱ የነበሩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በምንገነዘብበት ጊዜ፥ ስለ አዲስ ኪዳንና የቤተ ክርስቲያን ዕድገት ግልጽ አሳብ ይኖረናል። ክርስቶስ በእስራኤል ኣገር በተወለደ ጊዜ አገሪቱ በሮማውያን ኣስተዳደር ሥር ነበረች። ክርስቶስ ከመወለዱ ከ400 ዓመታት በፊት በእስራኤልና በአሕዛቡ ዓለም የተፈጸሙት ክስተቶችም በእስራኤልና በኣይሁድ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

ጳውሎስ በገላትያ 4፡4-5 ላይ እንደ ገለጻው፥ ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ»። ጳውሎስ ይህን ሲል ክርስቶስ ወደ ምድር መጥቶ እንዲሞትና ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሠርት፥ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ሁሉም ነገር እንደ ተዘጋጀ መግለጹ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት ልታድግና በአንድ ትውልድ ዘመን ወንጌል በጥንቱ ዓለም እንዲህ ሊስፋፋ የቻለው ለምን ነበር? መልሱን የምናገኘው እግዚአብሔር የዓለምን ታሪክ ካደራጀበት ሁኔታ ነው። ምንም እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳምና በሔዋን፥ ወይም በዳዊት ወይም በኢሳይያስ ዘመን ወይም ዛሬ ሊመጣ ቢችልም፥ እነዚህ ሁሉ ጊዜዎች/ዘመኖች ከእግዚኣብሔር እይታ አንጻር ትክክል አልነበሩም። ነገር ግን በእስራኤልና በአሕዛብ አገሮች የነበረው ጊዜ ምቹ ሲሆን፥ እግዚአብሔር ልጁን ላከው። ይህን ጊዜ ምቹ እንዲሆን ያደረጉት ነገሮች ምን ምን ነበሩ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የእስራኤል ሕዝብ በ586 ዓ.ዓ. በምርኮ ከተወሰደ በኋላ በዓለም ውስጥ የተፈጸሙትን ክስተቶች መመርመር ይኖርብናል።

የውይይት ጥያቄ፡– ዳንኤል ምዕራፍ 7ን አንብብና ዳንኤል በራእዩ የተመለከታቸውን የተለያዩ እንስሳት ዘርዝር። እነዚህ እንስሳት ያመለከቱት የትኞቹን መንግሥታት ነበር?

በባቢሎን ምርኮ ጊዜ እግዚአብሔር ለዳንኤል በቀጣይ 600 ዓመታት ውስጥ በአይሁዶች ታሪክ ውስጥ ስለሚፈጸሙት ነገሮች ገልጾለታል። በአራት እንስሳት የተመሰሉት አራት የተለያዩ የአሕዛብ መንግሥታት አይሁዶችን እንደሚገዙ እግዚአብሔር ለዳንኤል አሳይቶታል። አንበሳው ዳንኤል የነበረበትን የወቅቱን የባቢሎን መንግሥት ሲያመለክት፥ ድቡ የሜዶን/ፋርስ መንግሥት ነበር። ከባቢሎን በኋላ ሜዶን/ፋርስ ሁለተኛው የዓለም ኃያል አገር ለመሆን ችሏል። ነብር የግሪኮች መንግሥት ነበር። አራተኛውና እጅግ የሚያስፈራው እንስሳ የተመሰለው ደግሞ በሮም መንግሥት ተምሳሌት ነበር። እነዚህ አራት መንግሥታት የአይሁድን ሕዝብ ገዝተውት ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የመሲሑንና የቤተ ክርስቲያንን መንገድ ለማዘጋጀት ሲል፥ እነዚህን መንግሥታት መልሶ ይቆጣጠር ነበር። እነዚህ መንግሥታት እያንዳንዳቸው እግዚአብሔር ለአይሁዶች በነበረው ታሪካዊ ዕቅድ ውስጥ የየራሳቸው ድርሻ ነበራቸው።

የባቢሎን መንግሥት (626 ዓ.ዓ. – 539 ዓ.ዓ.)

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ነገሥት 25ን አንብብ። ሀ) በይሁዳ ላይ ምን እንደ ተፈጸመ በአጭሩ ግለጽ። ለ) የባቢሎን ምርኮ የአይሁዳውያንን ሕይወት እንዴት የለወጠው ይመስልሃል? ሐ) ከመጽሐፉ መጨረሻ ላይ ያለውን ካርታ ተመልከትና በባቢሎን ግዛት ውስጥ የተካተቱትን ዘመናዊ ኣገሮች ዘርዝር።

አልፎ አልፎ የአሕዛብ አገሮች ከሚሠነዝሩባት ጥቃት ውጭ እስራኤል ለ900 ዓመታት ያህል (ከ1400-586 ዓ.ዓ.) ነፃ አገር ነበረች። አይሁዶች «የእግዚአብሔር ፈቃድ ሁልጊዜም ከውጭ አገሮች ጥቃት ይጠብቀናል። ተግባራችንም ሆነ ማንኛውንም ጣዖት ማምለካችን አሳሳቢ ጉዳይ አይደለም። እኛ የእግዚአብሔር ልዩ ሕዝብ ስለሆንን፥ ወደ ምርኮ ሊሰድደንና ሊያጠፋን አይፈልግም» ብለው ያስቡ ነበር። እግዚአብሔር ነቢያትን እየላከ ሕዝቡን እንደሚቀጣ ቢያስጠነቅቅም፤ ሕዝቡ አልሰሟቸውም። የባቢሎን ጦር በድንገት ኢየሩሳሌምን በመያዝ ከ605 እስከ 586 ዓ.ም ድረስ ሦስት ዐበይት ወረራዎችን አካሄደባት። በዚህ ጊዜ የይሁዳ አገር ፈጽማ ወደመች። ቤተ መቅደሱ ሲፈርስና የእንስሳት መሥዋዕቱ ሊቆም፥ ለ500 ዓመት ሲካሄድ የነበረው የቤተ መቅደሱ አምልኮ ተቋረጠ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሁልጊዜ በቅድስና ባይኖሩም እንኳ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል በመሆናቸው፥ እግዚአብሔር ለስደት አሳልፎ እንደማይሰጣቸው የሚያስቡት እንዴት ነው? ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን ማስጠንቀቂያዎች ችላ እያልን፥ ክርስቲያኖች በመሆናችን ብቻ ነገሮች ቀላል እንደሚሆኑልን የምናስበው እንዴት ነው? ሐ) እግዚኣብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ሕዝቡ የነበሩትን አይሁድ ወደ ምርኮ በመውሰድ ከቀጣበት ሁኔታ ምን እንማራለን?

የሰባ ዓመቱ ምርኮ የአይሁድ ሕዝቦችን ሕይወት ሙሉ በሙሉ የለወጠ ሂደት ነበር። ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣ ጊዜ የአይሁዶች አኗኗርና የአምልኮ ሁኔታ በዳዊትና በኢሳይያስ ዘመን ከነበረው የተለየ ነበር። በምርኮ ዘመን የተለወጡ አምስት ነገሮች ነበሩ።

1.  አይሁዶች «በዳዊት ልጅ» የሚመራ የራሳቸው ነፃ መንግሥት አልነበራቸውም። ከ166-63 ዓ.ም. ከነበሩት ጥቂት ዓመታት በስተቀር እስከ 1948 ዓ.ም. ባሉት 2500 ዓመታት፥ አይሁዶች በአሕዛብ አገዛዝ ሥር ነበሩ። ዘመኑ እያለፈ በሄደ ቁጥር አይሁዶች «የዳዊት ልጅ የሆነው መሢሑ» የሚመጣበትን ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ይናፍቁ ጀመር። ይሁን እንጂ ክርስቶስ መንግሥቱን ለመመሥረት እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ አይሁዶች በዳዊት ልጅ አይገዙም። 

2. አይሁዶች በቤተ መቅደስ እንስሳት በመሠዊያ ላይ በማይሠዉበት አገር፥ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን መንገድ ማግኘት ነበረባቸው። ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ አይሁዶች ምኩራቦችን ገንብተው በዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና የዳዊት መዝሙር ዝማሬ እንዲያደርጉ አስቻላቸው።

3. ኣይሁዶች በዓለም ሁሉ ተበተኑ። ከ1000 ዓመታት በፊት በትንሽዋ የእስራኤል አገር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች፥ በተለያዩ አገሮች ተበተኑ። በመጀመሪያ የሰሜኑ የእስራኤል ሕዝብ በአሦራውያን አማካይነት ሲበተን፥ በባቢሎናውያን ደግሞ ደቡባዊውን የይሁዳ ሕዝብ በተኑት። በዚህ ሁኔታ ቀስ በቀስ አይሁዶች በዓለም ሁሉ ላይ ተሰራጩ። ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመን አይሁዶች ከስፔይን እስከ ሕንድ በሚደርስ ሰፊው የሮም ግዛት ውስጥ በነበሩ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ይገኙ ነበር። ወደ ጳለስቲና የሚመለሱበት ሁኔታ ከተመቻቸ በኋላ እንኳ አብዛኞቹ አይሁዶች በአሕዛብ አገሮች የተመቻቸ ኑሯቸውን መምራታቸንው እንደቀጠሉ ነበር። በኣሕዛብ አገሮች ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች በጳለስቲና አገር እንደነበሩት አይሁዶች እምነታቸውን አጥባቂ አልነበሩም። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አብዛኛውን ጊዜ ምስክርነቷን የምትጀምረው ክርስቶስ መሲሕ መሆኑን አምነው ለመቀበል ዝግጁ በሆኑት በእነዚህ አይሁዶች ነበር። (የሐዋ. 14፡1፤ 21 አንብብ።)

4. አይሁዶች የእግዚአብሔርን ቃል ማክበርና በጥንቃቄ መታዘዝን ተማሩ። እንደ ዕዝራ የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ የሚያጠኑ ሰዎች ነበሩባቸው። ይህም ጸሐፍት ብለው የሚጠሯቸውና የእግዚአብሔርን ቃል በሚገባ ያጠኑ የነበሩ አይሁዳውያን ምሁራን እንዲገኙ አደረገ። ሕዝቡም ቀደም ሲል ያልነበረውን የእግዚአብሔርን ቃል በትጋት የማጥናት ተግባር ያከናውን ጀመር። ከሁሉም በላይ ሕዝቡ በአሕዛብ አገሮች ሐሰተኛ በሆኑ ኣማልክትና ጣዖታት ተከብበው እያሉ እንኳ ጣዖታትን ከማምለክ ተቆጠቡ።

የአይሁድ ሃይማኖት ምሁራን ይህ ለእግዚአብሔር ቃል የነበራቸው ቅንአት፥ ሌሎች ሕግጋትንም እንዲያወጡ አደረጋቸው። እነዚህ ሕግጋት ሁለት ዓላማ ነበራቸው። አንደኛው፥ አይሁዶች በምርኮ አገር ከአሕዛብ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ረዱዋቸው። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ሕግ ለመጠበቅ አስተዋጽኦ አድርገውላቸዋል። አንድ አይሁዳዊ የተጨመሩትን ሕግጋት ቢተላለፍ እንኳ፥ ከተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ስለማይወጣ እግዚአብሔር አይቀጣውም ነበር። እነዚህ የተጨመሩ ሕግጋት በክርስቶስ ዘመን ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ወሳኝ ሆነው መገኘታቸው አሳዛኝ ነበር።። 

5. የአይሁዶች ቋንቋ መለወጥ ጀመረ። እስከዚህ ጊዜ ድረስ አይሁዶች ይናገሩት የነበረው የዕብራይስጥ ቋንቋ ነበር። በአንጻሩ የሶርያ ቋንቋ የነበረውን አረማይስጥ ይናገሩ የነበሩት የተማሩና የንግድ ሰዎች ብቻ ነበሩ። አይሁዶች በመካከለኛው ምሥራቅ ሲበተኑ ግን የአረማይስጥን ቋንቋ ለመማር ተገደዱ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ፥ አይሁዶች የአረማይስጥን ቋንቋ እየለመዱ የዕብራይስጥን ቋንቋ እየረሱ ሄዱ። በክርስቶስ ዘመን የዕብራይስጥን ቋንቋ የሚናገሩ አይሁዶች ጥቂቶች ሲሆኑ፥ አረማይስጥ ግን ዋንኛው ቋንቋቸው ሆነ።

የፋርስ መንግሥት (539-331 ዓ.ዓ.)

የውይይት ጥያቄ፡– ዳንኤል 8ን አንብብ። ሀ) ዳንኤል በራእይ ያያቸው ሁለቱ እንስሳት ምንና ምን ነበሩ? ለ) ኢሳይያስ 45፡1-13ን ኣንብብ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ ነፃ ያወጣል ያለው ማንን ነው? እግዚአብሔር እርሱን የማያመልከውን ቂሮስን የመረጠው ለምንድን ነው? ሐ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካርታ ተመልከትና ፋርስን፥ ሜዶንን፥ እንዲሁም የግዛቱን ስፋት አሳይ። ዛሬ በሜዶንና ፋርስ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን አገሮች ዘርዝር።

የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት ኃይልን ከማግኘታቸው ከ200 ዓመታት በፊት፥ እግዚአብሔር ቂሮስ የተባለ ሰው እንደሚያስነሣ ለነቢዩ ኢሳይያስ ገለጠለት። ምንም እንኳ ቂሮስ እግዚኣብሔርን ባያውቅም፥ እግዚአብሔር ግን እርሱን ወደ መሪነት በማምጣት ሕዝቡን እንዲድዳቸውና እነርሱም ወደ አገራቸው ተመልሰው ቤተ መቅደሱንና ኢየሩሳሌምን እንዲገነቡ እንደሚያደርግ ተናገረ። ሁለተኛው ዐቢይ ግዛት የተዋሃደው የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ነበር። የባቢሎን መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆየው ለ70 ዓመት ብቻ ሲሆን፥ የሜዶንና የፋርስ መንግሥታት ግን ለ200 ዓመት ይቆያሉ። ይህም የፋርስ መንግሥት በእነዚያ ረዥም ዘመኖች በአይሁዶችና በባህላቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ለማሳደር ችሎ ነበር።

የሜዶንና የፋርስ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጣው በፍጥነት ነበር። ፋርሳዊው ቂሮስ ሜዶንን ከፋርስ ጋር በማዋሃድ አነስተኛ የነበረችውን አገር በ550 ዓ.ዓ. ኃያል የዓለም አገር ሊያደርጋት ችሏል። ቂሮስ በ546 ዓ.ዓ. ታላቁን የሊዲያን መንግሥት ሲያሸንፍ፥ በ539 ዓ.ዓ. በአነስተኛ ጦርነት ባቢሎንን ወግቶ በማሸነፍ የፋርስና የሜዶን አካል አድርጓል። ስለሆነም በ11 ዓመት ውስጥ ቂሮስ ፋርስን በምሥራቅ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወደ ምዕራብ ቱርክና ወደ ደቡብ ግብጽ ለማስፋፋት ቻለ። ይህም የፋርስን መንግሥት በዘመኑ ከነበሩት ሁሉ ታላቅ አድርጎታል።

የአይሁድ ትውፊት እንደሚለው፥ ቂሮስ ወደ ባቢሎን በመጣ ጊዜ የአይሁድ መሪዎች የእርሱ መምጣትና ስሙም እንኳ ሳይቀር ከ200 ዓመት በፊት በነቢዩ ኢሳይያስ መተንበዩን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩት። ቂሮስ አይሁዶችን የደገፈውና በእግዚአብሔር ስም እንደሚያሸንፍ ከተናገረባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነበር።

የቂሮስ አገዛዝ ስልት ከባቢሎናውያኑ እና ከአሦራውያኑ በጣም የተለየ ነበር። ሰዎችን አስገድዶ ወደ ምርኮ ከመስደድ ይልቅ፥ በአገራቸው እየኖሩ ለፋርስ መንግሥት እንዲገዙ ያበረታታቸው ነበር። በመሆኑም፥ ቂሮስ በአዲሱ የፋርስ መንግሥት ውስጥ በነበሩት ሰዎች ተወዳጅነት ያተረፉለትን ሁለት ተግባራት አከናውኗል። አንደኛው፥ የየአገሮቹን ሃይማኖቶች ያከብር ነበር። ለምሳሌ፡- ወደ ባቢሎን ከተማ በገባ ጊዜ ማርዱክ የተባለው የከተማይቱ ጣዖት ሥልጣንን እንደሰጠውና የባቢሎን ንጉሥ ችላ ያለውን የማርዱክን አምልኮ ለመመለስ እንደ መጣ ተናግሯል። ለአይሁዶችም ይህንኑ ነበር የተናገረው። እግዚአብሔር የባቢሎንን ግዛት እንደሰጠው በመግለጽ፥ አይሁዶች ወደ አገራቸው ተመልሰው ለአምላካቸው ቤተ መቅደስ እንዲሠሩ ፈቀደላቸው።

ሁለተኛ፥ የባቢሎን ግዛት በተፈናቃዮች የተሞላ ሲሆን፥ ነዋሪዎቹም እዚያ በነበራቸው ሕይወት ደስተኞች አልነበሩም። ስለሆነም ቂሮስ አይሁዶችና ሌሎችም በባቢሎን የነበሩ ሕዝቦች ወደየአገሮቻቸው እንዲሄዱ ፈቀደላቸው። ይህም አይሁዶች በዘሩባቤል ወይም ሽሽባዛር (539 ዓ.ዓ.) [ዕዝራ 1:8፥ 11፥ በኋላም በዕዝራ (458 ዓ.ዓ) [ዕዝራ 7፡6-9] እና በነህምያ (445 ዓ.ዓ.) [ነህ. 2፡1) አማካይነት አይሁዶች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ አደረገ። በዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ቂሮስንና ሌሎች የፋርስ መሪዎችን እርሱ በሚፈልገው መንገድ እየመራቸው እንደሆነ ለአይሁዶች ግልጽ ነበር። በመጀመሪያው ዙር በሽሽባዛር አማካይነት 50,000 አይሁዶች ብቻ ተመለሱ። ይህም አብዛኞቹ አይሁዶች በባቢሎን የተደላደለ ሕይወት ይመሩ ስለነበር፥ ኋላቀርና በኢኮኖሚም ወደ ደቀቀችው ኢየሩሳሌም ለመመለስ አለመፈለጋቸውን ያሳያል። ይህ ዛሬ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ገጠሪቱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተመልሰው ለመኖር ከማይፈልጉበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይህ የዓለም ፍቅር አብዛኞቹ አይሁዶች እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሮቹ ተስፋ ወደ ገባላቸው አገር እንዳይመጡ ከለከላቸው።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) ይህ የዓለምና የምድር በረከቶች ፍቅር ክርስቲያኖች እግዚኣብሔር የሚፈልገውን እንዳያደርጉ የሚከለክላቸው እንዴት ነው? ለ) ከዚህ ችግር ጋር የታገልኸው እንዴት ነው?

አነስተኛ የአይሁድ ማኅበረሰብ ወደ ይሁዳ ሲመለስ፥ ቅድሚያ የተሰጠው የቤተ መቅደሱ ግንባታ ጉዳይ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን ተቃውሞ ተነሣበት። በአሦራውያን አስተዳደር ሥር በነበረችው ሰሜን ፍልስጥኤም ከፊል አይሁዳዊና ከፊል አሕዛብ የሆኑ ሰዎች ነበሩ። በኣዲስ ኪዳን ዘመን፥ እነዚህ ሰዎች ሳምራውያን ተብለው ተጠርተዋል። ሳምራውያን አይሁዶች ቤተ መቅደሱንና የኢየሩሳሌምን ከተማ መልሰው ለመገንባት ቆርጠው እንደ ተነሡ ሲያዩ፥ መልእክተኞችን ልከው በሥራው ሊተባበሯቸው እንደሚፈልጉ አስታወቋቸው። እነዚህ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዶች፥ ሳምራውያኑ እንዳይቆጣጠሯቸውና ንጹሑ የአይሁድ አምልኳቸው እንዳይረክስ በመስጋት ይመስላል የሥራ ትብብሩን ለመቀበል አልፈለጉም። ይህም በኢየሩሳሌም በነበሩት አይሁዶችና በሰማርያ በነበሩት ከፊል አይሁዶች መካከል ለዓመታት የዘለቀ ግጭትን አቀጣጠለ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐንስ 4፡9 አንብብ። በዚህ ክፍል አይሁዶች በሳምራውያን ላይ የነበራቸው ጥላቻ የተመለከተው እንዴት ነው?

አይሁዶች ትብብራቸውን ላለመቀበል ሲወስኑ፥ በአገሪቱ የመንግሥት ሥልጣን የነበራቸው ሳምራውያን የቤተ መቅደሱን ሥራ ለማስቆም ጥረት አደረጉ። ይህም የቤተ መቅደሱ ሥራ ለ5 ዓመታት እንዲስተጓጎል አደረገ።

በፋርስ መንበረ ሥልጣን ላይ አለመረጋጋት ከተከሰተ በኋላ ንጉሥ ዳርዮስ (521-486 ዓ.ዓ.) ወደ ሥልጣን መጣ። ይህ ንጉሥ ሁለት ነገሮችን አድርጓል። አንደኛው፥ ለአካባቢው ገዥዎች የበለጠ የቁጥጥር ሥልጣን ሰጣቸው። ከደቡብ ሜሶፖታሚያ እስከ ግብጽ ድረስ ያለው ግዛት ሁሉ፥ «ከወንዝ ማዶ» ተብሎ ይጠራ ነበር። መንበረ ሥልጣኑም ሰማርያ ላይ ነበር። ዳርዮስ አብዛኛውን ጊዜ በፋርስ መንግሥት ላይ የሚያምጸውን የግብጽ አካባቢ ግዛት ይበልጥ ለመቆጣጠር ሲል ለኢየሩሳሌም መገንባት ድጋፉን ይሰጥ ጀመር። በዚህም መሠረት፥ በ520 ዓ.ዓ. አይሁዶች ቤተ መቅደላቸውን መልሰው እንዲገነቡ ፈቀደላቸው። የቤተ መቅደሱ ሥራ በ55 ዓ.ዓ. ተጠናቀቀ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ታላቁ ሄሮድስ ይህንኑ ቤተ መቅደስ በማሻሻል በጥንቱ ዓለም ውስጥ ከነበሩት ሕንጻዎች እጅግ አስደናቂ ይዘት እንዲኖረው አድርጓል። ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ያመልኩ የነበሩት በዚሁ ሄሮድስ አሻሽሎ ባሠራው ቤተ መቅደስ ውስጥ ነበረ። አይሁዶችም በዚህ ቤተ መቅደስ ይኩራሩ ነበር። ክርስቶስ ግን ሙሉ በሙሉ ስለሚወድምበት ጊዜ ተነበየ (ማቴ. 24፡2)። አይሁዶች በሮም ላይ ካመፁ በኋላ በ70 ዓ.ም. የሮም ሠራዊት ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ ሙሉ በሙሉ ደምስሶታል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አይሁዶች የብሉይ ኪዳንን ሥርዓት ተከትለው የሚያመልኩበት ቤተ መቅደስ የላቸውም። ብዙ ምሁራን አይሁዶች ክርስቶስ ዳግም ሊመለስ ሲል ቤተ መቅደሳቸውን እንደገና የመገንባት ፈቃድ እንደሚያገኙ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህም ቤተ መቅደስ ይፈርስና ክርስቶስ በሺሁ ዓመት መንግሥቱ ጊዜ ሌላ ቤተ መቅደስ ይገነባል (ራእይ 20፡4-6)። እነዚህ ምሁራን ሕዝቅኤል 40 ይህንኑ የሺህ ዓመቱን ቤተ መቅደስ እንደሚያመለክት ያምናሉ።

ከቤተ መቅደሱ ዳግም ግንባታ በኋላ አይሁዶች በብዙ ችግር ተወጠሩ። በንጉሥ አርጤክስስ (Xerxes) ዘመን (486–465 ዓ.ዓ.) በፋርስ ግዛት ውስጥ የነበሩትን አይሁዶች ሁሉ ለማጥፋት ጥረቶች ይደረጉ ነበር። ነገር ግን እግዚኣብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠሩ ሐማና ሌሎችም የአይሁድ ጠላቶች ተገደሉ።

በእርጤክስስ (Artaxerxes) ዘመን (465-423 ዓ.ዓ.) ግብጽ በፋርስ መንግሥት ላይ ዐመፀች። በተመሳሳይ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች በኢየሩሳሌም ከተማ ዙሪያ ያለውን ቅጥር እንደገና ለመገንባት ፈለጉ። በጥንት ዘመን ቅጥር የሌላት ከተማ ክብር ስለማይሰጣት እንደ መንደር ትቆጠር ነበር። በተጨማሪም ለጠላት ጥቃት ትጋለጥ ነበር። ስለሆነም አይሁዶች የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ለመሥራትና የጥንት ክብሯን ለመመለስ ተነሣሡ። እነዚህ ቅጥሮች ከጠላት ጥቃትም እንዲከላከሏት ፈልገው ነበር። ነገር ግን ያለ መንግሥት ፈቃድ ከተሞችን መገንባት የተከለከለ ነበር። ሳምራውያን አይሁዶች የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ዳግም እየገነቡ መሆናቸውን ሲገነዘቡ፥ ሥራውን አስቁመው ለፋርስ መንግሥት ሪፖርት ላኩ። አርጤክስስ አይሁዶች ሳምራውያን ከግብጾች ጋር ተባብረው ያምፁብኛል በሚል ፍርሃት ሥራውን አስቆመ። ሳምራውያን ለአሁዶች የነበራቸውን ጥላቻ ለማሳየት ሲሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው የተሠራውን ቅጥር አፈረሱ።

አርጤክስስ ለስድስት ዓመት ከግብጾች ጋር ተዋግቶ በመጨረሻው አሸነፋቸው። ከዚያም በ445 ዓ.ዓ ነገሮች የተለየ ቅርጽ ያዙ። ምሑራን አርጤክስስ፥ ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች እንዲሠራ የፈቀደበትን ምክንያት አያውቁም። አንዳንዶች እንደሚሉት፥ በሰማርያ አነስተኛ ዓመፅ ስለነበረ የኢየሩሳሌምን ይዞታ ለማጠናከር ፈልጎ ይሆናል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ አርጤክስስ የኢየሩሳሌምን መጠናከር የፈለገው ግብፆች ዳግም ሊያምፁ ይችላሉ ከሚል ፍርሃት ነው ይላሉ። በተጨማሪም፥ ኢየሩሳሌም በምቹ የንግድ ስፍራ የምትገኝ ከተማ በመሆኗ አርጤክስስ ለዚሁ ዓላማ ሊጠቀምባት ፈልጎ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

እግዚአብሔር በነህምያ የተጠቀመው የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ ለመገንባት ብቻ ሳይሆን፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁዶች መንፈሳዊ መነቃቃትን እንዲያመጣ ጭምር ነበር። እግዚአብሔር በነህምያና በዕዝራ በመጠቀም ሕዝቡ በአምልኮና በመታዘዝ ላይ እንዲያተኩር አድርጓል። እንደ ብዙዎቻችን ሁሉ ጊዜው እየገፋ ሲሄድ ሕዝቡ ከእግዚኣብሔር ይልቅ በግል ጉዳዮቻቸው ተጠምደው ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር መነቃቃትን አመጣላቸው።

ዕዝራ በአይሁድ ታሪክ ውስጥ ደምቀው ከሚታዩት ታላላቅ ሰዎች አንዱ ለመሆን በቃ። ሥራውም ለብዙ መቶ ዓመታት በአይሁዶች ሃይማኖታዊ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ሲያደርግ ቆይቷል። በእርሱ ሥራ ምክንያት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል፡-

1. ዕዝራ አይሁዶች ለሙሴ ሕግ እንዲታዘዙ አስተምሯል። አይሁዶች በአሕዛብ አገሮች በመኖራቸው ምክንያት፥ የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ ተቸግረው ነበር። አሁን ግን ወደ አገራቸው ስለተመለሱና ስራሳቸው ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለሚያመልኩ– የሙሴን ሕግ ለመጠበቅ ይችሉ ነበር። በዕዝራ ዘመን የሙሴ ሕግ በፍልስጥኤም የሚኖሩ አይሁዶች የሚተዳደሩበት ሕገ መንግሥት ሆነ። በአካባቢያቸው በሚኖሩት አሕዛብ ባህል ከመዋጥ ይልቅ ዕዝራና ከእርሱ በኋላ የተነሡት መሪዎች ከአሕዛብ መለየቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል። ከአሕዛብ ጋር መጋባትንም ከልክለዋል።

2. ከጊዜ በኋላ ብሉይ ኪዳን የሚል ስም የተሰጣቸው መጻሕፍት እንዲሰበሰቡ ያደረገው ዕዝራ እንደ ሆነ የአይሁድ ትውፊት ይናገራል።

3. በዕዝራ አማካይነት የኢየሩሳሌም ይዞታ ተለውጧል። ኢየሩሳሌም ትንሽ መንደር ወይም የፖለቲካ ከተማ መሆኗ ቀርቶ፥ ሃይማኖታዊ ከተማ ሆነች። ስለሆነም፥ አይሁዶችና ኢየሩሳሌም በእንክብካቤ ይያዙ ጀመር። (ይህ በምኒልክና በኃይለ ሥላሴ ዘመን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ከነበረበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው)። ግብር እንዲከፍሉ አይጠየቁም ነበር። ኣይሁዶች በካህናት አመራር- አብዛኛውን ጉዳያቸውን ለመቆጣጠር ይችሉ ነበር። ይህ ልዩ ሃይማኖታዊ ክንዋኔ በግሪክና በሮም ግዛቶችም ቀጥሎ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ሕዝቡን በአሕዛብ ባህሎች ከመዋጥ ጠብቋል።

4. ዕዝራ በአይሁድ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱት ጸሐፍት ግንባር ቀደም ሰው ነበር። በዕዝራ ዘመን አብዛኛዎቹ አይሁዶች የዕብራይስጥ ቋንቋ ረስተው በአረማይስጥ ቋንቋ ብቻ ይግባቡ ስለነበር፥ ብሉይ ኪዳንን ማንበብ አይችሉም ነበር (ነህ. 8፡1-8 አንብብ)። ስለሆነም ጸሐፍት የሚባሉ እንደ ዕዝራ ያሉ ሃይማኖታዊ ምሁራን ለሕዝቡ የብሉይ ኪዳንን መጻሕፍት ተርጉመው ያብራሩላቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ጸሐፍት የብሉይ ኪዳንን ሕግ እየተረጎሙ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ካልተጠቀሰው የአይሁዶች ታሪክ ጋር ያዛምዱ ነበር። ከዚያም አይሁዶች የብሉይ ኪዳንን ሕግ ከልብ እንዲታዘዙ ለማድረግ እነዚህ ጸሐፍት ሌሎች ሕጎችን ጨምረው ማስተማር ጀመሩ። እነዚህ የተጨመሩት ሕጎች «ሚሽና» በተባለ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ሲሆኑ፥ በኋላ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ያህል ጥብቅ እየሆኑ ሄዱ። ይህ ይሁዲነት የተባለው የአምልኮ ዘይቤ በቀጣይ ምእተ ዓመታት እየተስፋፋ ሄደ። ዛሬ ኦርቶዶክስ አይሁዶች የአምልኮ ዘዬአቸውን የሚያያይዙት ከዕዝራና ይህንኑ አዲስ አምልኮ ከመሠረቱት ጸሐፍት ጋር ነው። ሚሽና ጊዜው እያለፈበት ሲሄድ የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች እነዚህን አዳዲስ ሕግጋት የሚያብራሩ አሳቦችን ጽፈው በታልሙድ ውስጥ እንዲካተት ኣደረጉ።

5. ምንም እንኳ አንዳንድ ምሁራን በምኩራብ የሚደረገውን አምልኮ መሪዎቹ እንደጀመሩት ቢናገሩም፥ ታላቁን ምኩራብ የመሠረተው ዕዝራ እንደሆነ ይታመናል። ይህ የአይሁዶችን ሃይማኖታዊ ሕይወት የሚቆጣጠሩ አንድ መቶ ሃያ ቁልፍ ሃይማኖታዊ መሪዎች የሚገኙበት መማክርት ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ታላቅ ምኩራብ ተለውጦ የአይሁዶች ዐቢይ ፖለቲካዊ አካል ሆኗል። በክርስቶስ ዘመን፥ ይህ የመማክርት ጉባኤ የአይሁድ ሸንጎ (Sanhedrin) ይባል ነበር። ክርስቶስ የተመረመረውና የሞት ቅጣት የተበየነበት በዚህ ሸንጎ ፊት ነበር (ማቴ. 26፡59-60)።

የውይይት ጥያቄ፡– ማቴ. 2፡4፤ 5፡20፤ 9፡3፤ 16፡21፤ 23፡25 26፡51 አንብብ። የሕግ መምህራን (ጸሐፍት) ምን ምን ደረጃዎችና ሥልጣን እንደነበራቸው ግለጽ። ከክርስቶስ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንደነበራቸው ግለጽ።

በክርስቶስ ዘመን፥ የአይሁድን ሕይወት በሙሉ የሚዳስሱ እጅግ ብዙ ሕጎች ወጥተው ነበር። ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ እነዚህን ሕጎች ባለማክበራቸው ምክንያት ጸሐፍትና ቀናተኛ ፈሪሳውያን በቁጣ ገንፍለው በክርስቶስ ላይ ተነሡ። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለመስቀል ከፈለጉባቸው ምክንያቶች አንዱ በብሉይ ኪዳን ላይ የጨመሯቸውን በርካታ ሕግጋት ስላላከበራቸው ነበር።

ዕዝራና የመጨረሻው የብሉይ ኪዳን ነቢይ የሆነው ሚልክያስ ከሞቱ በኋላ፥ የአይሁድ ሕዝብ፥ «400 የፀጥታ ዓመት» ወደሚባለው ዘመን ገቡ። በእነዚህ ዓመታት እግዚአብሔር ምንም ዓይነት አዲስ ቃል ሳይሰጣቸው በዝምታ ተቀመጠ። ብሉይ ኪዳን የሚጠናቀቀው «ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ» በፊት ኢሳይያስ እንደሚመጣ በመግለጽ ነው (ሚልክ. 4፡5)። ከዚህ የመጨረሻ ትንቢት በኋላ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ እንዲያዘጋጅ መጥምቁ ዮሐንስን እስከላከበት ጊዜ ድረስ ለ400 ዓመታት በነቢያቱ በኩል አልተናገረም (ማቴ. 1፡2-8)።

በፋርስ መንግሥት ጊዜ የታዩ ሌሎች ዕድገቶች

የፋርስ መንግሥት እየተስፋፋ ሲሄድ፥ ወደፊት በኣዲስ ኪዳን ዘመን ከፍተኛ ስፍራ የሚኖራቸው ሌሎች ነገሮች ይከሰቱ ጀመር። 

1. በአይሁዶችና በሰማርያ ሰዎች መካከል የማያቋርጥ መከፋፈል ተከሰተ። በሰማርያ ብዙ ሰንበላጦች ስለ ነገሡ፥ የታሪክ ጸሐፊዎች የነገሮችን የአፈጻጸም ቅደም ተከተል ለማወቅ ይቸገራሉ። ነገር ግን ነህምያ የኢየሩሳሌም መሪ በነበረበት ዘመን መጨረሻ ላይ ይሁን (ነህ. 13፡8) ወይም ከዚያ በኋላ፥ ምናሴ የሚባል አንድ ኣይሁዳዊ ከሰንበላጥ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ በመዛመድ በቤተ መቅደስ ኣካባቢ መኖር ጀምሮ ነበር። እርሱም ሳምራዊት ሚስቱን ለመፍታት ባለመፈለጉ ከቤተ መቅደሱ ተባሯል። በዚህ ጊዜ ምናሴ ወደ ሰንበላጥ ተመለሰ። ሁለቱ ሰዎች በትብብር ከጥንታዊቷ የሴኬም ከተማ አጠገብ በሚገኘው የገሪዛም ተራራ ላይ ከኢየሩሳሌሙ ቤተ መቅደስ ጋር የሚመሳሰል ቤተ መቅደስ ገነቡ። ምናሴ የዚህ ቤተ መቅደስ ሊቀ ካህናት ሆነ። ሳምራውያን የሚቀበሉት 39ኙን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሳይሆን፥ 5ቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ ነበር። ይህ እስከ ዛሬ ድረስ ያለው የአምልኮ ሥርዓት በኢየሩሳሌም በሚኖሩ አይሁዶች ዘንድ የተወገዘ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዮሐ 4፡19-24 አንብብ። ሀ) ይህ ተቀናቃኝ የአምልኮ ስፍራና ሥርዓት በዚህ ታሪክ ውስጥ የታየው እንዴት ነው? ለ) ክርስቶስ እውነት ማን ዘንድ እንዳለና እውነተኛ አምልኮ ምን ዐይነት እንደ ሆነ የገለጸው እንዴት ነው? 

2. በዚህ ጊዜ የሊቀ ካህናቱ ኃይል እየበረታ ሄደ። የፋርስ መንግሥት ለይሁዳ ሃይማኖታዊ መንግሥት የበለጠ ኃይል በመስጠቱ፥ ሊቀ ካህናቱ የአይሁድን ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውን ጭምር ሊቆጣጠር ቻለ። ከፋርስ መንግሥት ጀምሮ እስከ 70 ዓ.ም. ድረስ ሊቀ ካህናቱ የአይሁድ ሕዝብ የፖለቲካ መሪም ጭምር ነበር። ይህም በአዲስ ኪዳን ክርስቶስ በሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ፊት ለምርመራ በቀረበበት ጊዜ ተስተውሏል (ማቴ. 26፡57)።

3. አይሁዶች ራሳቸውን እያሳዩና ፀረ አሕዛብም እየሆኑ መጡ። እግዚአብሔር አይሁዶችን የጠራቸው ለአሕዛብ ብርሃን እንዲሆኑ ነበር (ኢሳ. 42:6-7)። እግዚአብሔር የፈለገው አይሁዶች በሥነ ምግባራቸውና በአምልኳቸው ንጹሓን እንዲሆኑና ስለ እርሱ ለአሕዛብ እንዲመሰክሩ ነበር። አይሁዶች ግን ለንጽሕናቸው በማሰብ ሌላ መንገድ መረጡ። ከአሕዛብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግና አይሁዳዊነታቸውን አጉልተው ለማሳየት ፈለጉ፡ በክርስቶስ ዘመን፥ እግዚአብሔር አሕዛብን የፈጠረው ሊፈርድባቸው ብቻ ነው የሚል አመለካከት የያዙ አይሁዶች ነበሩ። ብዙ አይሁዶች እግዚኣብሔር ለአሕዛብም ዕቅድ እንዳለው ወይም ከእርሱ ጋር ኅብረት ያደርጉ ዘንድ እንደሚፈልግ አያምኑም ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ከማያምኑ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ባለድረግ ክርስቶስ የሞተላቸውን ወገኖች ሊጠሉ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች በምሳሌዎች አብራራ።

4. ምኩራብ የአይሁድ ሕይወት ማዕከል ሆነ። ምሑራን ምኩራቦች መቼ እንደ ተጀመሩ አያውቁም። የአይሁድ ትውፊት እንደሚለው ከሆነ በባቢሎን ምርኮ ወቅት ተጀምረው በፋርስ መንግሥት ዘመን ሊስፋፉ ችለዋል። ምኩራብ ማለት «ማኅበረ ምእመናን» ማለት ነው። ይህ የአይሁዶች ስብስብ ሲሆን፥ በኋላ ምኩራብ የሚለው ቃል አይሁዶች ለአምልኮ የሚሰባሰቡበትን ስፍራ በማመልከት አገልግሏል። አይሁዶች በተበተኑባቸው አገሮች ሁሉ ምኩራቦችን ማነጽ ጀመሩ። ምንም እንኳ በእነዚህ ምኩራቦች ውስጥ የእንስሳት መሥዋዕቶች ባይቀርቡም፥ አይሁዶች እየተሰባሰቡ የብሉይ ኪዳኑን አምላክ ያመልኩ ነበር። ዛሬም እንኳ ቁጥራቸው በርከት ያለ ኣይሁዶች በሚኖሩባቸው ኣገሮች ምኩራቦችን ይሠራሉ። በዚያም የብሉይ ኪዳንን ሕጎች የሃይማኖት መሪዎችን ሕግ ለልጆቻቸው ያስተምራሉ። በዚህ ዓይነት አይሁዶች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሲቀመጡ ለ2500 ዓመታት ያህል የዘርና የሃይማኖት መለያቸውን ጠብቀው ቆይተዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን ለጥንቱ ዓለም በሰበከበት ጊዜ፥ መጀመሪያ ይሰብክ የነበረው በምኩራቦች ነበር (የሐዋ. 14:1)። እነዚህ ምኩራቦች ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የስብክት ሞዴሎች ሆነዋል። የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የኣምልኮ ስልት ከምኩራብ የተወሰደ ይመስላል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሕንፃውን ሳይሆን የክርስቶስ ተከታዮችን ነበር። እንዲያውም የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የማምለኪያ ሕንፃ ስላልነበራት ስብሰባው የሚካሄደው በግለሰብ ቤቶች ነበር። የአምልኮ ሕንፃዎች መሠራት የጀመሩት ክርስቶስ ከሞተ ከአያሌ መቶ ዓመታት በኋላ ነበር።

5. አረማይስጥ የአይሁዶች የኣፍ መፍቻ ስለመሆኑ፡- በክርስቶስ ዘመን በጳለስቲና ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ዘመን ይነገር የነበረውን የዕብራይስጥ ቋንቋ ሳይሆን የአረማይስጥን ቋንቋ ይጠቀሙ ነበር። እንደ ግእዝ ቋንቋ ሁሉ፥ ዕብራይስጥም ለንግግር የማይውል ቋንቋ ሆኖ ነበር።

6. ሁለት ዐበይት የአይሁድ እምነት ማዕከላት ተመሠረቱ። ዋንኛይቱ የዳዊት ከተማ የምትባለውና የይሁዳ ታሪካዊት መዲና የሆነችው ኢየሩሳሌም ነበረች። በፋርስ መንግሥት ዘመን ግን ጥቂት አይሁዶች የሚኖሩባት አነስተኛ ከተማ ነበረች። እንዲያውም ብዙ አይሁዶች በዚያ ለመኖር ስላልፈለጉ ነህምያ በይሁዳ የነበሩ አይሁዶች ዕጣ እንዲያወጡና ዕጣው የወጣላቸው ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው እንዲኖሩ ለማድረግ ተገድዶ ነበር (ነህ.11፡1-4)።

ሁለተኛዪቱ ዐቢይ ማዕከል ባቢሎን ነበረች። በፋርስ መንግሥት ዘመን አይሁዶች በባቢሎን በልጽገው ይኖሩ ነበር። አይሁዶች እንደ ጉራጌ ሕዝቦች የንግድ ስጦታ ስለ ነበራቸው፥ ብዙ አይሁዶች ሀብት አፍርተው ነበር። በባቢሎን ብዙ አይሁዶች ይኖሩ ስለ ነበር፥ ባቢሎን የሃይማኖቱ ማዕከል ሆነች። በባቢሎን የነበሩት አይሁዶች የራሳቸውን ባሕልና ሃይማኖታዊ ትምህርት ያሳድጉ ነበር። እንደ ዕዝራ ያሉ ሰዎች አይሁዶች በባቢሎን ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ ጥረዋል። በኢየሩሳሌም የነበሩ አይሁዶች ችግር በገጠማቸው ጊዜ፥ በባቢሎን (ዕዝራ) እና የፋርስ መዲና በሆነችው ሱሳ (ነህምያ) የነበሩት እነዚህ ሰዎች ነበሩ የረዷቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ተጽዕኖዎችና የፋርስ ግዛት ዕድገቶች በአዲስ ኪዳን ውስጥ እንዴት እንደታዩ ምሳሌዎችን በመስጠት አብራራ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: