የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው ፈልግና ልጅ በነበሩበት ጊዜ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ መኪና፥ ኤሌክትሪክ ወይም መንገዶች ባልነበሩበት ወቅት ሁኔታዎች ምን ይመስሉ እንደነበር ጠይቃቸው። ሰዎች ምን ያህል ርቀት ይጓዙ ነበር? እንዴት ይጓዙ ነበር? ምን ይለብሱ ነበር? . . . ወዘተ. ለ) ጥንታዊውን የጳለስቲናን ካርታ ተመልከትና ዐበይት ክፍሎችን ዘርዝር። ሐ) የመካከለኛውን ምሥራቅ ዘመናዊ ካርታ ተመልከት። ዛሬ ከጥንታዊ የእስራኤል ግዛቶች የትኞቹን ማን እንደሚያስተዳድር ግለጽ። መ) ጥንታዊ የሮም ግዛትን ካርታ ተመልከት። ጳውሎስ የሄደባቸውንና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን ዐበይት ክፍሎች ዘርዝር። እነዚህን ነገሮች ካላወቅሃቸው፥ የጳውሎስን የሚሲዮናዊነት ጉዞ ካርታዎች ተመልከት። ሠ) በጥንታዊ የሮም ግዛት ውስጥ የነበሩትን ዘመናዊ አገሮች ዘርዝር። ከእነዚህ ዘመናዊ አገሮች ሐዋርያው ጳውሎስ የሄደው ወደየትኞቹ ነበር።
የጳለስቲና መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ
መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበት ጊዜ በኢየሱስ ዘመን የነበረው ሕይወት በዚህ ዘመን ካለው ሕይወት ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ እናስባለን። ነገር ግን በጳለስቲና የነበረው ሕይወት ከጣሊያን ወራሪ በፊት ከነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት ጋር ተመሳሳይ ነው። ያኔ መኪና፥ መንገድ፥ መብራት፥ ኤሌክትሪክ፥ ትምህርት ቤት፥ ጤና ጣቢያ አልነበሩም። ይህን በአእምሮአችን ከያዝን፤ የክርስቶስና የደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበረ ልንገነዘብ እንችላለን። አኗኗራቸው ከትላልቅ ከተሞች ይልቅ በኋላ ቀር የገጠር መንደሮች ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ይመሳሰል ነበር።
ሌላው ብዙውን ጊዜ ለመረዳት የሚከብደን የጳለስቲና ምድር ምን ትመስል እንደነበር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጳለስቲናን «ማርና ወተት የምታፈልቅ አገር» (ዘዳግ 31፡20) ሲል ይጠራታል። ነገር ግን ከደቡብ ኢትዮጵያ ለም መሬት ጋር ሲነጻጸር፥ ጳለስቲና ምድረ በዳ ናት። በስፋትም ቢሆን እስራኤል ከኢትዮጵያ ታንሳለች። ግዛቱ እጅግ ሰፊ በነበረበት በታላቁ ሄሮድስ ዘመን፥ የግዛቱ ጠቅላላ ርዝመት 400 ኪሎ ሜትር ያህል ነበር። ይህም ከአዲስ አበባ እስከ ወላይታ ሶዶ ያህል ነው። በአብዛኛው ግን ፍልስጥኤም 70 ኪሎ ሜትር ያህል ነች። ይህም ከአዲስ አበባ እስከ ናዝሬት ካለው ርቀት ትንሽ አነስ የሚል ነው። ከሌሎች የዓለም አገሮች ጋር ስትነጻጸር፥ የተስፋይቱ ምድር ትንሽ አገር ናት። በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ግን ይህች አነስተኛ ምድር ልዩ ስፍራ አላት። እግዚአብሔር አነስተኛ ቁጥር የነበራቸውን አይሁዳውያን በዚህች አነስተኛ አገር ምስክሮቹ እንዲሆኑ መረጣቸው። እግዚአብሔር ራሱ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ በተለየ መንገድ አደረ። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው መሢሕ ለዓለም ኃጢአት ለመሞትና ለመኖር የመጣው ወደ አነስተኛ አገር ነበር።
እንደ ኢትዮጵያ በጳለስቲናም የተለያዩ የመሬት ዐይነቶች አሉ። በጥንቷ ጳለስቲና ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ብንጓዝ፥ በሜድትራኒያን ባሕር አጠገብ ያለው መሬት እንደ ስንዴ የመሳሰሉ ዐበይት እህሎች የሚበቅሉበት ለምለም ሜዳ መሆኑን እንረዳለን። ወደ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ስንጓዝ ደግሞ እንደ ሰንሰለት የተያያዙ ተራሮችና ኮረብታዎችን እናገኛለን። ብዙዎቹ እነዚህ ተራሮች እምብዛም ዛፍ ከሌለበትና ድንጋያማ ከሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው። ኢየሩሳሌም የተመሠረተችው ከጠላት ጥቃት ከለላ ታገኝ ዘንድ በተራራው ጫፍ ላይ ነው። (የኢትዮጵያ ነገሥታትም ለደኅንነታቸው ሲሉ በተራሮች ላይ ቤተ መንግሥቶቻቸውን ሠርተው ይቀመጡ ነበር።) ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ወደ ኢያሪኮ በምንጓዝበት ጊዜ፥ መሬቱ ድንጋያማና ረባዳ ሆኖ እናገኘዋለን። ከ25 ኪሎሜትር ርቀት በኋላ መሬቱ በሙት ባሕር አካባቢ ወደ 1600 ሜትር ዝቅ ይላል። ይህም ከዓለም እጅግ ዝቅተኛና ሞቃታማ ስፍራዎች አንዱ ነው። ይህ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ የደንክል ሸለቆ ጋር ይመሳሰላል።
ከደቡብ ወደ ሰሜን በምንጓዝበት ጊዜ ምድሪቱ የተለያዩ ገጽታዎች እንዳሏት እንረዳለን። በደቡብ ከኬብሮን አጠገብ መሬቱ ደረቅና አለታማ፥ ተራሮች የሚበዙበት፥ ለበጎችና ለፍየሎች መሰማርያ የሚውል ነው። ከኢየሩሳሌም ወደ ሰሜን ስንጓዝ ደግሞ ድንጋያማው ተራራ በሰንሰለታማ ኮረብታዎች ይተካል። ይህም ከደቡብ ኢትዮጵያ ተራሮች ጋር የሚመሳሰል ነው። እነዚህ ተራሮች ለምለምና አረንጓዴ ናቸው። ከሰማርያ በስተሰሜን እስከ ገሊላ ድረስ ጥሩ የእርሻ መሬት ይገኛል። በገሊላ ባሕር ዳርቻ ዓሣ በማጥመድ የሚተዳደሩ ሰዎች የሚገኙበት ብዙ ከተሞች ነበሩ። የክርስቶስ አገልግሎት ያተኮረው በእነዚህ ዓሣ በማጥመድና በግብርና በሚተዳደሩ ማኅበረሰቦች ላይ ነበር። ከሰሜን ገሊላ እስከ ሊባኖስ ድረስ ምድሪቱ አሁንም ተራራማ ገጽታ አላት። እነዚህ ተራሮች በሚዛን ተፈሪ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዱሮች ጋር የሚመሳሰሉ ነበሩ።
ሐዋርያው ጳውሎስ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ጠቢባንንና ታላላቆችን ሳይሆን ድሆችንና ዓለም እንደ ሞኝነት የሚቆጥረውን ነገር እንደ መረጠ ገልጾአል። እግዚአብሔር መንግሥቱን የሚመሠርተው ዓለም እንደ ምናምንቴ በሚቆጥረው ነገር ላይ ነው (1ኛ ቆሮ. 1፡18-25)። ይህ ሁኔታ አይሁዶችንና አገራቸውን በተመለከተ እውነት ነው። አይሁዶች በጣም የሠለጠኑና በአካባቢያቸው ከሚገኙ አገሮች ሁሉ የተሻሉ ናቸው ብለን እናስብ ይሆናል። እውነቱ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ጳለስቲናን እንደ ምናምንቴና ኋላቀር አገር ነበር የሚመለከቱት። አሕዛብ ጳለስቲናን ዝቅ አድርገው ይመለከቷት ስለነበረ ያለምንም ስጋት አይሁዶች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ይፈቅዱላቸው ነበር። ጳለስቲና ለአሕዛብ አገር የምትጠቅም ያደረጋት አንድ ነገር ቢኖር ከተለያዩ አገሮች ለሚመጡ ነጋዴዎች ዋነኛ መተላለፊያ መሆኗ ነበር። በግብፅና በሜሶጶጣሚያ፥ እንዲሁም በሳውዲ ዓረቢያና በሜሶጶጣሚያ መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ይደረግ የነበረው በጳለስቲና በኩል ነበር።
ይህች አነስተኛ የነበረች የዓለም ክፍል፥ እግዚአብሔር ለዓለም ሕዝቦች ለወጠነው ዕቅዱ መዲና ነበረች። እግዚአብሔር ያይ የነበረው ሥልጣኔዋን ወይም ፖለቲካዊ ኃይሏን አልነበረም። እርሱ ይፈልግ የነበረው ከሌሎች ሕዝቦች የተለየ ሕይወት እየኖረ እርሱን የሚያከብርና የሚታዘዝ ሕዝብን ነበር፡ እግዚአብሔር ቁጥራቸው ጥቂት በሆነ ሕዝብ ምሳሌነት ዓለምን ለመለውጥ ይችላል። እግዚአብሔር ልጁን የላከው ወደዚህች ዝቅተኛና ኋላ ቀር አገር ነበር። አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ከጳለስቲና ምድር አይወጣም ነበር። የጳለስቲና የሥልጣን ማዕከል በነበረችው በሮም መወለድ ይችል ነበር። የሥልጣኔ ማዕከል በሆነችው በግሪክ መወለድ ይችል ነበር። ነገር ግን የፖለቲካ ሥልጣንና ሥልጣኔ ክርስቶስን ወደ ጳለስቲና ለላከው እግዚአብሔር ዐቢይ ጉዳዮች አልነበሩም።
የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ጳለስቲናን የዕቅዱ ማዕከል ካደረገበት ሁኔታ ስለ አሠራሩ ምን እንማራለን? ለ) ይህን እውነት በሕይወትህ እንዴት እንደተመለከትህ ግለጽ።
የሮም ግዛት መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ
እግዚአብሔር በዕቅዱ የሮም ግዛት በምዕራቡ ዓለም ታሪክ፥ ከሁሉም የበለጠ ጠንካራና ለረዥም ጊዜ የቆየ መንግሥት እንዲሆን አድርጓል። የሮም ግዛት ከሕንድ እስከ ታላቋ ብሪታኒያና ከዚያም እስከ ሰሜን አፍሪካ ድረስ የተንሰራፋ ነበር። ለ1600 ዓመታት ቤተ ክርስቲያን በብዛት ያደገችው በዚሁ የዓለም ክፍል ነበር።
በመጀመሪያዎቹ 15 ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷ ያተኮረው በጳለስቲና አካባቢ ነበር። በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስ ወንጌልን ወደ ኢየሩሳሌም፥ ይሁዳና ሰማርያ እንዲወስዱ የሰጣቸውን ትእዛዝ በመፈጸም ላይ ነበሩ። ነገር ግን እግዚአብሔር በራሱ መንገድ ሥራውን በመሥራቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ወንጌል ወደ አንጾኪያ ከተማ ደረሰ። አንጾኪያ በመካከለኛው ምሥራቅ የግሪክ መንግሥት ነበረች። እግዚአብሔር ዓለምን በወንጌል ለመድረስ ያዘጋጀው ዕቅድ የጀመረው፥ ወንጌል በአንጾኪያ በአሕዛብ መካከል ሥር ከሰደደ በኋላ ነበር። እንደ ጳውሎስና በርናባስ ባሉት ታላላቅ የወንጌል መልእክተኞች አማካይነት ወንጌል በሮም ግዛት ውስጥ መስፋፋት ጀመረ።
ጥንታዊው ሥልጣኔ ተስፋፍቶ የሚገኘው በሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ 100 ኪሎ ሜትር አካባቢ ነበር። ጳውሎስና በርናባስ ወንጌልን ያደረሱት ወደ ባሕር ዳርቻ አካባቢዎች ነበር። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ወንጌል ሥር የሰደደባቸው እንደ አንጾኪያ፥ ቆላስይስ፥ ኤፌሶን፥ ፊልጵስዩስ፥ ተሰሎንቄ፥ ቆሮንቶስ፥ ሮምና እስክንድርያ የመሳሰሉ አገሮች፥ ለባሕር ዳርቻ ቅርብ ነበሩ። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ ላይ፥ ክርስቲያኖች በዛሬዎቹ ግብፅ፥ እስራኤል፥ ሶሪያ፥ ቱርክ፥ ግሪክና ጣሊያን አገሮች ውስጥ ይኖሩ ነበር።
የጥንቱ ሥልጣኔ የተመሠረተው በሜሶጶጣሚያ ባሕር አካባቢ በመሆኑ፥ ሐዋርያት ሁለት የጉዞ አማራጮች ነበሯቸው። እነዚህን ከተሞች በሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች በእግራቸው ይጓዙ ነበር። ጳውሎስ በወንጌል አገልግሎት ጉዞው ወቅት በሁለቱም አማራጮች ተጠቅሟል። ብዙውን ጊዜ በሮም ዋና ዋና መንገዶች የሚጓዘው ከከተማ ወደ ከተማ በሚሄድበት ጊዜ ነበር። ነገር ግን ከአንዱ አውራጃ ወደ ሌላው ርቆ በሚሄድበት ጊዜ በመርከቦች ይጓዝ ነበር።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)