የመጀመሪያው ምእተ ዓመት ሃይማኖቶችና ፍልስፍናዎች

ሰዎችን ለማወቅ በምንፈልግበት ጊዜ ፖለቲካቸውንና ታሪካቸውን ብቻ ሳይሆን፥ ሃይማኖታቸውንም ጭምር መመርመር ይኖርብናል። እግዚአብሔር ሰዎችን ለልጁ መምጣት ለማዘጋጀት የዓለምን ሃይማኖት ይመራ ነበር።

የውይይት ጥያቄ- ወንጌሉን ከማብራራታችን በፊት ስለ አንድ ሰው ሃይማኖት ማወቅ የሚጠቅመን ለምንድን ነው?

ይሁዲነት

በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን 4 ሚሊዮን የሚሆኑ አይሁዶች እንደ ነበሩ ይገመታል። (ዛሬ 6 ሚሊዮን ያህል አይሁዶች አሉ።) ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆኑት አይሁዶች በጳለስቲና ውስጥ ይኖሩ ነበር። የቀሩት በሮም ግዛቶች ውስጥ፥ በተለይም በታላላቅ ከተሞች ተበትነው ይኖሩ ነበር። ለአይሁዶች ሁሉ የዳዊት ከተማ የሆነችው ኢየሩሳሌም የይሁዲነት መዲና ነበረች። አይሁዶች የትም ይኑሩ የት፥ ሁልጊዜ ኢየሩሳሌምን እንደ እውነተኛ ቤታቸው ስለሚመለከቷት በሚያስፈልገው ሁሉ፤ በተለይም ገንዘብ በመላክ ይደግፉዋት ነበር።

ዛሬ በክርስቲያን ቤተ እምነቶች መካከል ልዩነት እንዳለ ሁሉ፥ በአይሁድ እምነት ተከታዮች መካከልም ልዩነት አለ። ይህም ሆኖ፥ አይሁዶች ሁሉ በጋራ የሚከተሏቸው አንዳንድ መሠረታዊ እምነቶች አሉ።

 1. አይሁዶች ልዩና የተመረጡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሆኑ ያምኑ ነበር። ይህም በአብርሃም፥ በይስሐቅና በያዕቆብ፥ እንዲሁም በሲና ተራራ በሙሴ አማካይነት፥ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር ልዩ ግንኙነትን እንደመሠረተ ይታወቃል። ከዚህም የተነሣ አይሁዶች ልዩ የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆኑና ከሌሎች ሕዝቦች ይልቅ እግዚአብሔር እነርሱን የመባረክ ዕቅድ እንዳለው ያምኑ ነበር።
 2. አይሁዶች ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለ በጽኑ ያምናሉ። እርሱ መንፈስ ስለሆነ፥ በጣዖት ሊመሰል አይችልም፥ ስለሆነም፥ የትኛውም ዐይነት አምልኮተ ጣዖት የተወገዘ ነው፤ ምክንያቱም ይህ እግዚአብሔርን እንደ መካድ ይቆጠራል ይላሉ።
 3. እግዚአብሔር ለአይሁዶች የራሳቸው መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። ይህችም የጳሊስትና ምድር ናት። እግዚአብሔር ይህችን ምድር ለዘላለም ሰጥቷቸዋል። እግዚአብሔር የአምልኮቱ ማዕከል የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ልዩ አድርጓታል። ይህም የእግዚአብሔር ምድራዊ ዙፋን በኢየሩሳሌም እንደተቀመጠ ያህል አስቆጥሮታል። ስለሆነም አይሁዶች የጳለስቲናን ምድርና ቤተ መቅደስ ለመጠበቅና ለመከላከል ነፍሳቸውን እንኳ አሳልፈው ከመስጠት አይመለሱም ነበር።
 4. አይሁዶች አንድ ቀን እግዚአብሔር የመረጠው የተለየ ሰው ወደ ጳለስቲና እንደሚመጣ ያምኑ ነበር። ይህ መሢሕ ሮማውያንን እንደሚያሸንፍና ሕዝቡን ከአሕዛብ አገዛዝ ነፃ እንደሚያወጣ ተስፋ ነበራቸው። በኢየሩሳሌም ከተማ ሆኖ በመግዛት በዓለም ላይ ሰላም ያሰፍናል ይሉ ነበር።
 5. በመላው ዓለም የተበተኑ አይሁዶች ለአምልኮና ለማኅበራዊ አገልግሎት፥ ምኩራቦችን በማዕከልነት ይጠቀሙ ነበር። በኢየሩሳሌም ከተማ ከ400 በላይ ምኩራቦች የነበሩ ሲሆን፥ በቤተ መቅደሱም ውስጥ ሳይቀር አንድ ምኩራብ ነበር። በአሕዛብ አገዛዝ ዘመን አይሁዶች ሃይማኖታቸውን ከአካባቢያቸው ጋር አስማምተው ለመኖር ተገድደው ነበር። ለምሳሌ፥ ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውጭ እንስሳትን ሊሠዉ አይችሉም ነበር። ለመሆኑ እንስሳትን ሳይሰዉ እግዚአብሔርን የሚያመልኩት እንዴት ነው? ይህን ችግር ለማስወገድ ነበር የአይሁድ ማኅበረሰብ የአምልኮና የትምህርት ማዕከል የሆኑት ምኩራቦች የተመሠረቱት። አይሁዶች በሰንበታት ቀን ከብሉይ ኪዳን እያነበቡና የዳዊትን መዝሙር እየዘመሩ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ከዚያም ስብከት ያዳምጣሉ። ብዙውን ጊዜ ስብከቱን የሚያቀርበው ከሌላ ስፍራ የሚመጣ አገልጋይ ነበር። ክርስቶስ በየሰንበቱ ወደ ምኩራቦች እየሄደ ያመልክ ነበር። ብዙ ጊዜም እንዲሰብክ ይጋበዝ ነበር (ሉቃስ 4፡16-21 አንብብ)። በኋላም ሐዋርያው ጳውሎስ በደረሰበት ከተማ ሁሉ መጀመሪያ በምኩራብ ውስጥ ይሰብክ ነበር። የአይሁድ መሪዎች እስከአባረሩት ጊዜ ድረስ በምኩራብ ውስጥ መስበኩን አልተወም ነበር (የሐዋ. 13፡42-50፤ 14፡1-5)።

ከአምልኮ በተጨማሪ፥ ምኩራቦች የትምህርትም ማዕከል ነበሩ። የአይሁዳውያን ልጆች ስለ ሃይማኖታቸውና ስለ ብሉይ ኪዳን በምኩራቦች ውስጥ ይማሩ ነበር።

 1. ትኩረት የሚሰጠው በአስተምህሮዎች ላይ ሳይሆን፥ በውጫዊ ተግባራት ላይ ነበር። አይሁዶች የተለያየ ሥነ መለኮታዊ አስተምህሮ ቢኖራቸውም በአንድነት ለመኖር ፈቃደኞች ነበሩ። ይህም ሆኖ አይሁድ ሁሉ አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዐት እየፈጸሙ አንድ ዓይነት የሕይወት ዘይቤ እንዲከተሉ አጥብቀው ይሻሉ።

ከጊዜ በኋላ አይሁዶች ሕያው የሆነውን አምላክ ከማምለክ ይልቅ ሥርዓቶችንና ሕጎችን መከተል ጀመሩ። ስለሆነም በብሉይ ኪዳን ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕጎችን ጨመሩ። እነዚህ ተጨማሪ ሕጎች አይሁዶች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዴት ከሕይወታቸው ጋር እንደሚያዛምዱ የሚተረጉሙ ነበሩ። ለምሳሌ፥ በብሉይ ኪዳን በሰንበት ቀን ሥራን የሚከለክል ሕግ አለ። ነገር ግን አይሁዶች «ሥራ ምንድን ነው?» የሚል ጥያቄ አንሥተው የራሳቸውን ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት በሰንበት ቀን ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ በእግራቸው አይሄዱም፤ ጉድጓድ ውስጥ የወደቀ ሰው አያወጡም፤ እንዲሁም እህል አያጭዱም። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች እነዚህን ሕጎች ከመጀመሪያዎቹ የብሉይ ኪዳን ሕጎች እኩል ያከብሯቸውና ያስከብሯቸው ነበር። ለሕዝቡ ግን እነዚህ ሕግጋት ተጨማሪ ሸክሞች ነበሩ። ከእነዚህ ሕግጋት የተነሣ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መዛመዳቸውንና እርሱንም ደስ ማሰኘታቸውን ትተው የሕግ ዝርዝሮችን መከተል ጀመሩ። ክርስቶስ አብዛኛውን ጊዜ ከአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲጋጭ የነበረው እነዚህን ሕግጋትና ሥርዓቶቻቸውን ባለመፈጸሙ ምክንያት ነበር (ማር. 1፡1–15 አንብብ።) ኢየሱስ በሰው ውስጣዊ ነገር ማለትም በልቡና በአመለካከቱ ላይ በማተኮር፥ ውጫዊ ልማዶችን መከተል ምንም ፋይዳ እንደሌለው አስተምሯል። ከዚህም የተነሣ፥ የሃይማኖት መሪዎች ጠሉት።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖች ዛሬም የአንድ ሰው ውጪአዊ ልምምድ ከአመለካከቱና ከእምነቱ እንደሚበልጥ አድርገው የሚያስቡት ለምንድን ነው?

ከጊዜ በኋላ ሁለት ዓይነት የአይሁድ እምነት ተከታዮች ተነሡ። እነርሱም በጳለስቲና አገር ያደጉ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን እውነተኛና እጅግ ንጹሕ አይሁድ አድርገው ይቆጥሩ ነበር። እነዚህ አይሁዶች ይሁዳዊ አኗኗራችንን በንጽሕና መጠበቅ አለብን ብለው ስላመኑ፥ ከአሕዛብ ባህል ጋር ተስማምቶ የመኖርን ነገር ሙሉ በሙሉ ይቃወሙት ነበር። ሌሎቹ ደግሞ በአሕዛብ አገር ያደጉ አይሁዶች ነበሩ። እነዚህ አይሁዶች የግሪክ እንጂ የአረማይስጥ ቋንቋ ስለማይናገሩና የአሕዛብን ባህል ስለሚከተሉ፥ እንደ ንጹሕ አይሁዶች አይታዩም ነበር። አንዳንድ ጊዜ በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ውጥረቶች ይቀሰቀሱ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 6፡1-7 አንብብ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ይህ ልዩነት የተንጸባረቀው እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ማቴ. 3፡7፤ 5፡20፤ 16፡1፤ 22፡23፤ የሐዋ. 23፡6-10 አንብብ። ሀ) በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የተጠቀሱት የተለያዩ የሃይማኖት ቡድኖች የትኞቹ ናቸው? ለ) እነዚህ ቡድኖች አንዱ ለሌላው የነበራቸው አመለካከት ምን ይመስላል? ሐ) ስለ እነዚህ ቡድኖች የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት የሚሰጠውን ማብራሪያ አንብብና እምነታቸው እንዴት እንደሚለያይ ግለጽ።

አብዛኛውን ጊዜ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች እርስ በርስ ይናቆራሉ፤ ሰዎችም እነርሱንና አመለካከታቸውን እንዲከተሉ ለማድረግ ይጥራሉ። በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ሌሎች ቡድኖችን የሚቃወሙ ቡድኖች አሉ። እነዚህም የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት፥ ካሪዝማቲክና ኢ-ካሪዝማቲክ፥ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱ መከፋፈል በክርስቶስና በሐዋርያት ዘመንም የተለመደ ነበር። በወንጌላት ውስጥ ክርስቶስንና ሐዋርያትን የሚቃወሙ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ድርጅቶች እንደ ነበሩ ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ቡድኖች ክርስቶስን ይጠሉትና እንዲሰቀል ይፈልጉ የነበረው ለምንድን ነው? መልሱ በፖለቲካዊ ፍላጎት ምክንያት ነው የሚል ነው። ኢየሩሳሌም ሃይማኖታዊ ማእከል በመሆኗ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ቁርኝቶች ነበሩ። ሊቀ ካህናቱ የአይሁድ ሃይማኖትና የፖለቲካ መሪ ነበር። ስለሆነም እነዚህ ቡድኖች የሚታገሉት ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እምነቶች ስም ሳይሆን፥ በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ ነበር።

 1. ፈሪሳውያን፡- በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ወቅት ፈሪሳውያን በቁጥር የበዙና ኃይልም የነበራቸው ሃይማኖታዊ ቡድኖች ነበሩ። ፈሪሳውያን ምናልባት መሠረታቸውን ያገኙት በ135 ዓ.ዓ አንዳንድ አይሁዶች በይሁዲነት ውስጥ ምግባረ ብልሹነትን ተመልክተው ራሳቸውን ከሕዝቡና ከወቅቱ ፖለቲካዊ ሥልጣን በለዩበት ጊዜ ሳይሆን አይቀርም ተብሎ ይገመታል። ፈሪሳውያን በአብዛኛው የፖለቲካ ሥልጣን ከያዙትና ይስማሙ ከነበሩት፥ እንዲሁም የግሪክን ባህል ለመከተል ይፈልጉ ከነበሩ ሰዱቃውያን ጋር ጠላቶች ነበሩ።

በሥነ መለኮታዊ አቋማቸው ፈሪሳውያን በጣም አክራሪዎች ነበሩ። ሁሉንም የብሉይ ኪዳን ሕጎችና ከዕዝራ ዘመን አንሥቶ የአይሁድ መሪዎች በየጊዜው የደነገጓቸውን ሕጎች በሙሉ ለመከተል የቆረጡ ነበሩ። ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ድረስ ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ያምናሉ። በሙታን ትንሣኤና እግዚአብሔር በሰዎች ሁሉ ላይ የሚፈርድ አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። አምልኮ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረግ ሕያው ግንኙነት ሳይሆን፥ ሕግን እንደ መጠበቅ አድርገው ይመለከቱ ነበር። ከልባቸው እግዚአብሔርን የሚፈልጉና በሕይወታቸው ደስ ሊያሰኙት የሚፈልጉ ብዙ ፈሪሳውያን ነበሩ። ችግሩ ሃይማኖታዊ ሥርዐታቸው ወደ እግዚአብሔር በትሕትና ቀርበው ምሕረቱን እንዳይሹ ይልቁንም በገዛ ጽድቃቸውና ሥራቸው እንዲታበዩ አድርጓቸዋል (ሉቃስ 18፡9-14)። ኒቆዲሞስና የአርማቲያው ዮሴፍ ክርስቶስን የተከተሉ ፈሪሳውያን ምሳሌዎች ነበሩ።

ፈሪሳውያን ክርስቶስ ሕግ አጥባቂና የአይሁድ አባቶች የደነገጉትን ልማድ የሚያጣጥል ስለመሰላቸው፥ በብርቱ ይቃወሙት ነበር። በተጨማሪም ክርስቶስ ሕግጋትንና ሥርዓቶችን ለመጠበቅ ከመጣር ይልቅ፥ በማኅበረሰቡ ዘንድ ኃጢአተኞች ተብለው ከተገለሉ ከቀራጮች ጋር ይታይ ስለነበርና ሌሎችንም ይረዳ ስለነበር ፈሪሳውያን ሊገድሉት ፈለጉ።

ፈሪሳውያን ጳውሎስንም በብርቱ ተቃውመውት ነበር። ጳውሎስ በክርስቶስ ከማመኑ በፊት ፈሪሳዊ ነበር (የሐዋ. 23፡6)። በዚያን ጊዜ ሳውል ይባል የነበረው ጳውሎስ፥ ሕግን ለመጠበቅ ከነበረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሣ፥ ለብሉይ ኪዳን እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን የክርስቶስን ተከታዮች በብርቱ ያሳድዳቸው ነበር። በአፀፋው ደግሞ ጳውሎስ በክርስቶስ ባመነ ጊዜ ፈሪሳውያን ያሳድዱት ጀመር። ጳውሎስ ደኅንነት ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚገኝ ሲያስተምር፥ የፈሪሳውያንን የእምነት መሠረት እንደሚያናጋ ሰው አድርገው በመቁጠር ተቃወሙት። ከዳኑ በኋላ የአሕዛብ ክርስቲያኖች መገረዝ አለባቸው ያሉት፥ ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ለማግኘት እንዲችሉ ወደ ይሁዲነት መለወጥ እንዳለባቸው በየቤተክርስቲያኑ እየዞሩ አስተምረዋል (የሐዋ. 15፡1-2፣ ገላ. 2፡1-15)።

ፈሪሳውያን የአይሁድ እምነት ቅድመ አያቶች ናቸው። መደበኛው የፈሪሳውያን ቡድን ኢየሩሳሌም ከተደመሰሰች በኋላ ቢጠፋም፥ ትምህርታቸው ግን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ክርስቲያኖችም እግዚአብሔርን በትሕትና ከማፍቀርና ከማምለክ ይልቅ፥ በውጫዊው ሕግ ላይ በማተኮር ራሳቸውን የሚያጸድቁት እንዴት ነው?

 1. ሰዱቃውያን፡- የፈሪሳውያንን ያህል ብዙ ቁጥር አልነበራቸውም። ነገር ግን በአይሁድ ላይ ሊቀ ካህንና ገዥ ሆነው የሠሩና ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ቡድኖች ነበሩ። ሰዱቃውያን የዘር አመጣጣቸውን የሚቆጥሩት በንጉሥ ዳዊት ዘመን ከነበረው ዛዶክ ከተባለ ካህን ነው። እስከ ምርኮ ዘመን ድረስ ዘሮቻቸው በሊቀ ካህንነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል (2ኛ ዜና 31፡10፤ ሕዝ. 40፡46፤ 44፡15)። አብዛኛዎቹ ሰዱቃውያን በአመዛኙ ካህናት ነበሩ። ለእነርሱ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥልጣን ትልቅ ስፍራ ነበረው። ሰዱቃውያን ሥልጣናቸውን ጠብቀው ለማቆየት ሲሉ በሥልጣን ላይ ካለው ከማንኛውም ቡድን ጋር ከመተባበር ወደ ኋላ አይሉም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች አይሁዶች በላይ የአሕዛብን አገዛዝና የግሪክን ባህል ለመቀበል ፈቃደኞች የነበሩ ናቸው። በክርስቶስና በሐዋርያቱ ዘመን ሰዱቃውያን የቤተ መቅደስ አምልኮና የአይሁዶች ሸንጎ መሪዎች ነበሩ።

ሰዱቃውያን አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ብቻ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ ስለሚያምኑ እነዚህን መጻሕፍት በጥንቃቄ ይከተሏቸዋል። ሌሎቹ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል እንደሆኑ አድርገው አያምኑም ነበር። ሰዱቃውያን ለሃይማኖት አባቶች ትውፊት ደንታ የማይሰጣቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ በመናፍስቱ ዓለምና በሙታን ትንሣኤ አያምኑም ነበር።

ሰዱቃውያን ክርስቶስን ለመቀበል ያልፈለጉት ይቀናቀነናል ብለው ስለ ሰጉ ነበር። መሲሕ እንደ መሆኑ፥ በሕዝቡ ላይ የነበራቸውን ሥልጣን ይወስድብናል ብለው ፈሩ። ብዙ ሰዎች እየተከተሉት ሲመጡ፥ የሰዱቃውያኑ ስጋት ይበልጥ እያየለ መጣ። እንዲሁም ክርስቶስ በሮም ላይ የዐመፅ እንቅስቃሴ ካቀጣጠለ፥ ሮማውያኑ በዐመፀኞቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀሳውስቱም ጭምር (በሰዱቃውያኑም) ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ሲያስቡ እጅግ ፈሩ። ሊቀ ካህናቱ እንደተናገረው ሕዝቡ ከሚጠፋ ክርስቶስ ቢሞት ይመርጡ ነበር (ዮሐ 11፡49-50)። ያም ሆነ ይህ ሕዝቡ ተደምስሶ ነበር። ይህ የሆነው ግን በ64 ዓ.ም. የአገርና የነጻነት ቀናኢ ቡድንና ሌሎችም በማመፃቸው እንጂ፥ በክርስቶስ ምክንያት አልነበረም። በ70 ዓ.ም ሮማውያን ኢየሩሳሌምን በከበቡ ጊዜ፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዱቃውያን ሞቱ ቡድናቸውም ህልውናውን አጣ።

 1. ጸሐፍት፡- ከዕዝራ ዘመን ጀምሮ «ጸሐፍት» ተብሎ የሚጠራ አንድ ቡድን ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እነዚህን ሰዎች፥ «የሕግ መምህራን» ብሎ ይጠራቸዋል። አይሁዶች በምርኮ ከተወሰዱ በኋላ፥ የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር እየመነመነ ሄደ። የመግባቢያ ቋንቋቸው አረማይስጥ በመሆኑ፥ ብሉይ ኪዳንን የሚተረጉምላቸው ሌላ ሰው ያስፈልጋቸው ነበር። ይህም የተወሰኑ ሰዎች የብሉይ ኪዳን ምሑራን እንዲሆኑ አደረገ። እነዚህ ሰዎች በዕብራይስጥ ቋንቋና በብሉይ ኪዳን ላይ ጥልቅ ጥናት ስላደረጉ ሊቅ ለመሆን በቁ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ለማወቅ ሲፈልጉ፥ እነዚህን ሰዎች ይጠይቁ ነበር። ጸሐፍት የተባሉ ሰዎች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን እንዲጠብቁ ይረዳል ያሉትን ማብራሪያ እየሰጡ፥ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር አብረው ይሠሩ ነበር። እነዚህ ጸሐፍት ብዙውን ጊዜ በምኩራቦችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ያስተምሩ ስለ ነበር፥ ራሳቸውን የእውነት ጠባቂዎች አድርገው ይቆጥሩ ነበር።

ጸሐፍት ራሱን የቻለ ቡድን ስላልመሠረቱ፥ በፈሪሳውያንም በሰዱቃውያንም ቡድኖች ውስጥ ነበሩ። ክርስቶስ በሕግ ትርጓሜያቸውና በእነርሱ እገዛ በረቀቁት ደንቦች ላይ ተቃውሞውን ስለ ገለጸ፥ ጸሐፍትም ጠላቶቹ ሆኑ።

 1. ኢሴናውያን፡- አዲስ ኪዳን ይህን ቡድን በስም ባይጠቅሰውም፥ ብዙ ምሑራን በመጥምቁ ዮሐንስ፥ በኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት፥ እንዲሁም በዮሐንስ ጽሑፎች ውስጥ፥ የኢሴናውያን ተጽዕኖ እንዳለ ያምናሉ። ኢሴናውያን ቅድስናን ለማግኘት ከማኅበረሰቡ መገለል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምሩ ነበር። ይህም አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከሕዝቡ ተለይተው በገዳም ውስጥ በምናኔ ከሚኖሩበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። እነዚህ ሰዎች በሙት ባሕር አካባቢ አያሌ ማኅበረሰቦችን አቋቁመው ይኖሩ ነበር። ሰዎች ከኢሴናውያን ጋር በሚቀላቀሉበት ጊዜ መጠመቅና የዚያን ማኅበረሰብ ሕግ ለማክበር መስማማት ነበረባቸው። በኢሴናውያን ዘንድ ጋብቻ የተከለከለ ሲሆን፥ ሀብታቸውን በጋራ ይጠቀሙ ነበር። እንደ ፈሪሳውያን ሁሉ የተለያዩ ሕጎችንና ደንቦችና በመጠበቁ ላይ እንጂ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት በማድረጉ ላይ አጽንኦት አይሰጡም ነበር። ክፉዎችን አጥፍቶ የጻድቃንን መንግሥት የሚመሠርተው መሢሕ፥ በፍጥነት እንዲመጣላቸው ይናፍቁ ነበር። ከሚወዷቸው አገላለጾች መካከል ኃጢአተኞችን «የጨለማ ልጆች»፥ ጻድቃንን «የብርሃን ልጆች» የሚሉ ይገኙባቸዋል። ምሑራን ከኢየሩሳሌም መውደም በኋላ ይህ ቡድን በምን ምክንያት እንደጠፋ አላወቁም።

የውይይት ጥያቄ፡- የኢሌናውያን ትምህርትና ልምምድ ከጥንቷና ከቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚመሳሰለውና የሚለያየው እንዴት ነው?

 1. የአገርና የነጻነት ቀናኢ ቡድን፡- ይህ ቡድን ሃይማኖታዊ ቡድን ባይሆንም በክርስቶስና በሐዋርያት ዘመን በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ቡድን ነበር። ይህ ቡድን ፖለቲካዊ ቡድን ሲሆን፥ በዐመፅ ተዋግተው ከሮም አገዛዝ ነፃ ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው። እነርሱም ስግደትና አምልኮ የሚገባው ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ፥ ቀረጥም መክፈል ካስፈለገ ለእርሱ ብቻ ሊሰጥ እንደሚገባ ያምኑ ነበር። ሮማውያን በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ በመሠልጠንና ቀረጥም ከእነርሱ በመሰብሰብ በአይሁድ አምልኮ ውስጥ ጣልቃ ይገቡ ነበር። በመሆኑም ቀናተኞች በአነስተኛ ቡድኖች ተደራጅተው ሮማውያንን ይወጓቸው ነበር። ማንኛውንም የተቃውሞ መንገድ ከመጠቀም አይመለሱም ነበር (የሐዋ. 21፡38)። በዚህም ተግባራቸው የመቃብያንን ምሳሌነት እንደሚከተሉ ያምኑ ነበር። ይህ ፓርቲ የገሊላው ይሁዳ በተባለ ግለሰብ በ6 ዓ.ም እንደተመሠረተ ይታመናል (የሐዋ. 5፡37)። አብዛኞቹ ቀናተኞች ገሊላውያን ነበሩ። ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ ስምዖን በአንድ ወቅት የዚህ ቡድን አባል የነበረ ይመስላል (ሉቃስ 6፡15)።

ከ66-70 ዓ.ም በሮማውያን ላይ ጦርነት የከፈቱት እነዚህ ቡድኖች ነበሩ። የሚያሳዝነው ከሮማውያን ይልቅ እርስ በርሳቸው ወይም ከሌሎች አይሁዶች ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል። አንድ ግንባር አለመፍጠራቸው ሮማውያን በቀላሉ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። ከኢየሩሳሌም መፈራረስ በኋላ ውጊያቸውን ቀጥለው በ135 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ በሮማውያን ተደምስሰዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- እነዚህ ቡድኖች ክርስቶስና የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በነበሩበት ዘመን ካሳደሩት ተጽዕኖ ምን እንማራለን?

የአሕዛብ ሃይማኖቶች

በኢየሱስ ዘመን አሕዛብ እንዴት በዓይን የማይታይ አምላክ ማምለክ እንደሚቻል ለመገንዘብ ተቸግረው ነበር። የእነርሱ አምልኮ ያተኮረው በዓይን በሚታዩና በጣዖታት በተወከሉ አማልክት ላይ ነበር። በተጨማሪም እያንዳንዱ የሕይወት ክፍል ጣዖታዊ ጥበቃ ይደረግለት ዘንድ ብዙ አማልክትን ያመልኩ ነበር። ስለዚህ የዝናብ፥ የውኃ፥ የመሬት፥ የሰላምና የጦርነት ጣዖቶች ነበሯቸው። የልምላሜና የሌሎችም ጉዳዮች ጣዖቶች ነበሩዋቸው። ሰዎች ከእነዚህ ጣዖቶች ጋር የነበራቸው ግንኙነት በእርዳታና በበረከት ፍለጋ ላይ የተመሠረተ ነበር። ትኩረታቸው ጣዖታቱ እንዴት መመለክ አለባቸው በሚለው ሁኔታ ላይ አልነበረም።

የውይይት ጥያቄ፡– ይህ ለጣዖታት የነበረው ግምት፥ ክርስቲያኖች አንዱን እውነተኛ አምላክ ከሚመለከቱበት ሁኔታ ሊለይ የሚገባው እንዴት ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ስላደረገላቸው መልካም ነገርና ስለ አምላክነቱ ከማምለክ ይልቅ ራስ ወዳድ ሆነው እንዲባርካቸውና አንድ ነገር እንዲያደርግላቸው የሚፈልጉት እንዴት ነው?

በአሕዛብ አገሮች ሁሉ ብዙ ጣዖቶችና ቤተ መቅደሶች ነበሩ። በአቴና ሰዎች የማያውቁትን አምላክ ቅር እንዳያሰኙ በማሰብ፥ «ለማይታወቅ አምላክ» የሚል መሠዊያ ይሠሩ ነበር (የሐዋ.17፡23)። ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ግን፥ ብዙ ሰዎች በእነዚህ ጣዖቶች ላይ የነበራቸውን አመለካከት ቀይረው ነበር። ከሰዎች ብዙም በማይለዩት ደካማ ጣዖታት ላይ መደገፉ ሰልችቷቸው ነበር። የእነዚህም ጣዖታት ምግባረ ብልሹነት ሰልችቷቸው ነበር። ስለሆነም እውነትን መፈለግ ጀመሩ። በመጀመሪያ በአንዱ እውነተኛ ፈጣሪ አምላክ ላይ በሚያተኩረው የአይሁድ ሃይማኖት ትምህርት ተስበው ነበር። እነዚህ አሕዛብ ወደ ምኩራቦች ሄደው የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙና ለእውነተኛው አምላክ ይሰግዱ ነበር። አንዳንድ አሕዛብም ግዝረትን ተቀብለው ወደ ይሁዲነት ተለውጠዋል። ነገር ግን ወደ እውነተኛው አምላክ የተሳቡት አሕዛብ የአይሁዶችን ትዕቢትና እግዚአብሔርን ለማምለክ የአሕዛብን ባህል ሙሉ በሙሉ መተው አለባችሁ የሚለውን የአይሁድ ቃል እምብዛም ባይወዱትም፥ «እግዚአብሔርን የሚፈሩ» አሕዛብ ሆኑ (የሐዋ. 10፡1-2፤ 16፡14፤ 17፡4፥ 17)። እነዚህ አሕዛብ ግዝረትን ሳይቀበሉ እግዚአብሔርን ያመልኩና ይጸልዩ ነበር። እነዚህ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አሕዛብ ለደኅንነቱ ወንጌል ዝግጁ ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፥ ቆርኔሌዎስ በክርስቶስ በማመን ብቻ ሊድን እንደሚችል ሲሰማ፥ በፍጥነት አምኖ ድኗል (የሐዋ. 10፡24-44)።

በክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ችግር ካስከተሉት ነገሮች አንዱ፥ ነገሥታትን ማምለክ ነበር። እንደ ግብፅ ያሉ ጥንታዊ ሕዝቦችም ንጉሣቸው አምላክ እንደሆነ ያምኑ ነበር። ሮማውያንም ይህንን እምነት መከተል ጀመሩ። ከንጉሡ ሥልጣንና ሕዝቡ ለንጉሡ ያለውን ታማኝነት ከመፈለግ የተነሣ ቄሣር አምላክ ስለ ሆነ መመለክ አለበት የሚል አመለካከት ተንጸባረቀ። ይህ አመለካከት በተለይ በዶሚቲያን ዘመን ይበልጥ አይሎ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ለንጉሡ እንዲሰግዱና፥ መሥዋዕትም እንዲያቀርቡ የሚደነግግ ሕግ ወጣ። ክርስቲያኖች ይህንን አናደርግም በማለታቸው ሮማውያን እንደ ዐመፅ ቆጠሩት። ለቄሣር መሥዋዕት አናቀርብም በማለታቸው ምክንያት የተከሰተው የመጀመሪያው ስደት የብዙ ክርስቲያኖችን ሕይወት ቀጠፈ። ለ200 ዓመታት ቄሣሮችን አናመልክም በማለታቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ተገደሉ።

ሌሎች ሃይማኖቶችም ነበሩ። ከጣዖት ጋር የተለየ ግንኙነት አለን የሚሉ ምሥጢራዊ የሆኑ ማኅበረሰቦች የሚያካሂዷቸው «ምሥጢራዊ ሃይማኖቶች» ነበሩ። በእነዚህ ምሥጢራዊ ማኅበረሰቦች የሚሰጡትን የአምልኮ ትምህርቶች የሚያውቁ ሰዎች ብቻ በረከትን እንደሚያገኙ ይታመን ነበር። ለጥንቆላም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ነበር። በምትሐት በመጠቀም፥ የእንስሳትን ሞራ በማንበብ ወይም ከዋክብትን በመቁጠር፥ እነዚህ ጠንቋዮች ከፍተኛ ኃይል አለን ብለው ይመኩ ነበር። ሰዎችን ለመርገምና ለመፈወስ እንደሚችሉ ይናገሩ ነበር። አንድ ሰው በሥራው ስኬታማ መሆን አለመሆኑን ይተነብዩ ነበር። መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ጠንቋዩ እስካልነገራቸው ድረስ ምንም ነገር አይፈጽሙም ነበር። ይህ ከዋክብትን የመቁጠርና ሰዎች የተወለዱበት ዓመት በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ ያደርሳል የሚለው እምነት፥ ዛሬም ትኩረት ተሰጥቶት ሰዎች በጋዜጦች ላይ ሲከታተሉት እንመለከታለን። (ለምሳሌ፥ በአዲስ አበባ በሚታተሙ አንዳንድ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ የሚወጣውን የኮከብ ቆጠራ ዐምድ እየተከታተሉ በሕይወታቸው ላይ ስለሚደርሰው ነገር ለማወቅ የሚጥሩ ሰዎች አሉ።)

ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትሄድ፥ ከእነዚህ ሃይማኖቶች ጋር ትጋፈጥ ጀመር። በተጨማሪም ክርስትናን ከተለያዩ ሃይማኖቶች ጋር የማቀያየጡን ፈተና ተቋቁማለች። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ክርስትናን እንደ ምሥጢራዊ የማኅበረሰብ እምነት ይመለከቱት ጀመር። የቅዱሳን ምስሎችን በማስተዋወቅ አምልኮተ ጦዖት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባ አድርገዋል። የክርስቶስም ስም በሚፈሩበት ጊዜ የሚናገሩት ወይም የሚይዙት ምትሐት ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፡ ሀ) የጥንት ዘመን ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ሃይማኖቶች ጋር የሚመሳለሉት ወይም የሚለያዩት እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስትና ላይ ሌሎች ነገሮችን በመጨመር እንዴት እንዳበላሹት ግለጽ።

በክርስቶስ ዘመን የነበሩት የዓለም ፍልስፍናዎች

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የነገሡትን ሦስት መንግሥታት ግለጽ። ለ) እያንዳንዱ መንግሥት የተመራበት መሠረታዊ ፍልስፍና ምን ነበር?

ለብዙዎቻችን «ፍልስፍና» የሚለው ቃል አስፈሪ ነው። ነገር ግን ፍልስፍና አንድ ሰው ስለሚጠቅመው ነገር ለማሰብ የሚረዳውና አቅጣጫ የሚያሲዘው ነው። ሰዎች ሁሉ ተግባራቸውን የሚመሩበት የየራሳቸው ፍልስፍና አላቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ሰዎች የተለያዩ ተግባራትን (ሥራዎችን) ያካሂዳሉ። ይህም ሥራ ለሁሉም፥ ለተማሩት ወይም እግዚአብሔር ማንኛውንም ሥራ እንደሚያከብር ባላቸው አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። በብሔራዊ ደረጃ አገሮች መንግሥታቸውን ይበጀናል በሚሉት ፍልስፍና መሠረት ያዋቅራሉ። አንዳንዶች ሥልጣንና ኃይል ይወረሳል ብለው (እንደ ፊውዳሉ ሥርዐት) መንግሥታቸውን ያዋቅራሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎች ሁሉ ሀብታቸውን እኩል መካፈል አለባቸው ብለው (እንደ ኮሙኒስቱ ሥርዐት) መንግሥታቸውን ያዋቅራሉ። አንዳንዶች ሰዎች የመምረጥ መብት ስላላቸው ለእነርሱ የሚጠቅመውን ራሳቸው መምረጥ ይኖርባቸዋል ብለው (እንደ ካፒታሊስትና ዴሞክራቲክ ሥርዓት) መንግሥታቸውን ያዋቅራሉ። ክርስቲያኖች እንዲህ የሚል ፍልስፍና ሊኖራቸው ይገባል፡- «ለሰዎች ትልቁ ነገር እግዚአብሔርን ማክበርና በእርሱም ደስ መሰኘት ነው።»

በጥንቱ ዓለም ብዙ የተለያዩ ፍልስፍናዎች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ፍልስፍናዎች የክርስቲያኖችን አስተምህሮዎች ይፈታተኑ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ትምህርት የበለጠ ተቀባይነት እንዲኖረው በማሰብ፥ ክርስትናን ከእነዚህ ፍልስፍናዎች ጋር ለማስማማት ተፈትነው ነበር።

የጥንቱ ግሪክ ፈላስፋ ፕላቶ ሕይወት በሁለት ደረጃ እንደምትታወቅ እስተምሯል። በመጀመሪያ፥ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የማይታይ የአሳቦች ዓለም አለ። ሁለተኛው፥ እንደ ጥላ ዓይነት የሚታይ ዓለም አለ። የሚታየው ነገር የማይታየውን ያህል ጠቃሚ አይደለም። ይህ አመለካከት ከሐዋርያት ዘመን በኋላ በቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይህ ፍልስፍና ክርስቲያኖች ምግብና ወሲብ የሚፈልገው አካላዊ ሰውነት ክፉ ነው ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። ስለሆነም ክርስቲያኖች በዓለም ጠቃሚ ናቸው የተባሉትን ነገሮች ትተው በገዳም ውስጥ መኖር ጀመሩ። ላለማግባት ወስነው ስለ መልካም ነገሮች ብቻ ለማሰብ ይሞክሩ ነበር።

ቁሳዊ ነገሮች መጥፎ እንደሆኑና የማይታዩ ነገሮች መልካም እንደሆኑ ከሚያስረዳው ከዚህ ፍልስፍና ኖስቲሲዝም የተባለ ልዩ ፍልስፍና ፈለቀ። ይህ ፍልስፍና በአንዳንድ የአዲስ ኪዳን እሳቤዎችና በወንጌሎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። አንዳንድ ሐዋርያት እንደ ቆላስይስና 1ኛ ዮሐንስ በመሳሰሉት መጻሕፍት ውስጥ ኖስቲሲዝምን ተቃውመው ጽፈዋል። ኖስቲኮች መንፈስና መልካም በሆነው አምላክ እና ክፉ በሆነው ሰውና ተፈጥሮ መካከል ትልቅ ገደል እንዳለ አስተምረዋል። ገደሉን ለመደልደል ብዙ ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላሉ። ገደሉን የሚሞላ መንፈሳዊ አካል መኖር አለበት። የሰው መንፈስ ከቁሳዊው እስር ቤት እንዲያመልጥ የሚያደርግ ልዩ የእውቀት ቁልፍ ያስፈልጋል ይላሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህን አሳብ በመውሰድ በቅዱሱ አምላክና በክፉዎች ሰዎች መካከል የነበረውን ክፍተት የሞላ መንፈስ የሆነው ኢየሱስ እንደሆነ አስተምረዋል። ስለ ክርስቶስ ያለን ልዩ እውቀት ደኅንነትን እንደሚያስገኝም ገልጸዋል። ኖስቲኮች እግዚአብሔር በጣም ቅዱስ ስለሆነ ቁሳዊ ነገሮችን ሊፈጥር አይችልም ይላሉ። የደኅንነት መንገድ የሆነው ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሰው ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሰው ከሆነ ቁሳዊ ነገር ተካፍሏልና ርኩስ ይሆናል በማለት አስተምረዋል። ስለሆነም ክርስቶስ ሰው አልሆነም ይላሉ። ነገር ግን መንፈስ መጥቶ በክርስቶስ ሰውነት ውስጥ እንደኖረና ከትንሣኤ በኋላ እንደተለየው ይናገራሉ። 1ኛ ዮሐንስ 1፡3፣ 4፡1-3 ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ሰው እንደሆነና እንደ ተዳሰሰ፥ እንደ ታየና እንደ ደማ፥ እንደ ሞተና ከሞት እንደ ተነሣ በመግለጽ ለኖስቲኮች ትምህርት ምላሽ ይሰጣል። ክርስቶስ መንፈስ ብቻ አልነበረም።

ይህን ትምህርት የሚከተሉ ሰዎች በሁለት የተለያዩ መንገዶች መልስ ይሰጡ ነበር። አንዳንዶች ፍጹማዊው ሕይወት በተቻለ መጠን ከቁሳዊ ነገሮች ርቆ በምድረ በዳ ውስጥ መኖር አለበት ይላሉ። ይህም ሰዎች በገዳም ውስጥ ራስን የመጨቆን ሕይወት እንዲመሩ አድርጓቸዋል። ጳውሎስ በቆላስይስ 2፡16-23 ላይ ይህንን አመለካከት ነቅፎ ጽፎአል። ሁለተኛው ምላሽ፥ መንፈሳችን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እስካደረገ ድረስ፥ በአካላችን ላይ የሚደርሰው ነገር አሳሳቢ አይደለም ይላሉ። አንዳንድ ሰዎች በሥጋ የምናደርገው ነገር መንፈሳዊ ሕይወታችንን አይጎዳውም ይላሉ። ስለሆነም ሰዎች ከፍተኛ የዝሙት ኃጢአት ሲፈጽሙም እንኳ ችግር እንደማይኖር ያስረዳሉ። ሰይጣን ይህን ውሸት በመጠቀም ብዙ ተከታዮችን አፍርቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ትምህርት ለእምነታችን አደገኛ የሚሆንባቸውን ሦስት ምክንያቶች ጥቀስ። ለ) የዚህን ትምህርት ክፍሎች በኢትዮጵያ ውስጥ የተመለከትነው እንዴት ነው?

በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በስፋት ይታወቅ የነበረው ሌላው ፍልስፍና ኤፊቆሮሳውያን የሚባለው ነው። ይህ ፍልስፍና እንደ ዘገምተኛ ለውጥ ፍልስፍና ሁሉ ሕይወት የአጋጣሚ ውጤት እንደሆነችና በአተሞች ግጭት እንደ ተከሰተች ያስተምራል። ይህም መልካም ወይም ክፉ የሚባል ነገር እንደሌለ ያመለክታል። የሕይወት ዓላማ በሕይወት እስካሉ ድረስ መደሰት ብቻ ነው። ይህን አመለካከት ጠቅሶ ጳውሎስ ሲናገር ትንሣኤ ሙታን ከሌለ ከሞት በኋላ ምንም ተስፋ የለም፤ ስለዚህ ትርፉ መብላት፥ መጠጣትና መጋባት ብቻ ነው ብሎ ገልጾአል (1ኛ ቆሮ. 15፡32)። ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሙታን ሲያስተምር ያላገጡበት ኤፌቆሮሳውያን ናቸው (የሐዋ. 17፡18፥ 32)።

በመጀመሪያው ምእተ ዓመት በዋነኛነት የሚታወቀው ሌላው ፍልስፍና ስቶይሲዝም ነው። ስቶይኮች ዓለም ሩቅ በሆነው አምላክ እንደምትተዳደርና ሰዎች ሕይወታችውን ለመለወጥ ብዙም ተስፋ እንደሌላቸው ያመኑ ነበር። ስለዚህ ስሜታችንን ገዝተን የሚሆነውን መጠበቅ ይኖርብናል ይላሉ። የሰውን ስሜት የሚቀሰቅሱ እንደ ወሲብና ምግብ የመሳሰሉ ነገሮች መወገድ አለባቸው። ሰው በሚችለው ሁሉ ንጹሕ ሕይወት መኖር አለበት ይላሉ። ይህም ፍልስፍና ወንጌሉን ይቃረን ነበር። እግዚአብሔር የሩቅ ሳይሆን የቅርብ አምላክ ነው። እግዚአብሔር ልጁን ወደ ዓለም ልኳል። ከዚህም በተጨማሪ፥ እግዚአብሔር ለሰዎች እርሱን ለመታዘዝ ወይም አለመታዘዝ፤ ማክበር ወይም አለማክበር ምርጫ ሰጥቷቸዋል። ይሁንና፥ እግዚአብሔር ሰዎችን በምርጫቸውና በተግባራቸው በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች፥ እነዚህን ሁለት ፍልስፍናዎች ቢከተሉ ኖሮ ክርስትናን እንዴት የሚጎዱ ይመስልሃል? ለ) ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙና ቤተ ክርስቲያን ልትዋጋቸው የሚገቡ ፍልስፍናዎች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: