የማርቆስ አንዳንድ ልዩ ገጽታዎች

1. ማርቆስ ሰዎች ለኢየሱስ በሚሰጧቸው ምላሾች ላይ ያተኩራል።

ሀ. መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስን የጫማ ክር መፍታት እንደማይገባው ባሪያ አድርጎ ራሱን ተመለከተ (ማር. 1፡7)።

ለ. የኢየሱስን ቃል የሰሙ ሰዎች በሥልጣን በማስተማሩ ተደንቀዋል (ማር. 1፡27፤ 6፡2፤ 10፡24)።

ሐ. ሰዎች ኢየሱስ በፈጸማቸው ተአምራት ተደንቀዋል (ማር. 2፡12፤ 6፡5)

መ. ምንም እንኳ መጥምቁ ዮሐንስ፥ አጋንንት፥ አሕዛብና አንዳንድ አይሁዶች የኢየሱስን ልዩ መሆን ቢገንዘቡም፥ የሃይማኖት መሪዎች ሊያምኑበት አልፈለጉም።

2. የማርቆስ ታሪክ በኢየሱስ ሞት ላይ ያተኩራል። ማርቆስ የኢየሱስን ጠቅላላ አገልግሎት የሚሸፍን 10 ምዕራፎች የጻፈ ሲሆን፥ 6 ምዕራፎች ስለ መጨረሻው ሳምንትና የኢየሱስ ሞት ይነግሩናል።

3. ማርቆስ ተግባራዊ ወንጌል በመባል ይታወቃል። በብዛት ከሚጠቀምባቸው ቃላት አንዱ «ወዲያው» የሚለው ሲሆን፥ ከ40 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል (ለምሳሌ፥ 1፡12፥ 18፥ 20፥ 23፤ 6፡45፥ 50፤ 9፡20)። ይህም ታሪኩ ወደፊት እንደሚንቀሳቀስና የክርስቶስ ሕይወት እንዴት በፍጥነት ወደ ሞቱ እንዳመራ ያመለክታል። የክርስቶስ ሞት በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን፥ በእግዚአብሔር የታቀደ ነበር።

ሌሎች ወንጌላት የክርስቶስ አገልግሎት ከሦስት ዓመታት በላይ እንደተካሄደ ሲያመለክቱ፥ ማርቆስ ግን ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ አልጠቀሰም። በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮች ሁሉ በአንድ ዓመት ውስጥ ሊከናወኑ ይችላሉ። ይህም የሆነው ለማርቆስ ታሪኩን ፈጠን ፈጠን አድርጎ ማቅረቡ ከሕይወት ታሪካዊና ቅደም ተከተላዊ አተራረክ የበለጠ ተመራጭ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ማርቆስ፥ ታሪኮቹ አጫጭርና ፈጣን እንዲሆኑለት በማሰብ እንደ ሉቃስና ማቴዎስ ዝርዝር ገለጻዎችን አስወግዶ፥ ጠቅለል ባለ መልኩ ያቀርባቸዋል። ማርቆስ የክርስቶስን መምህርነት ቢጠቅስም ከክርስቶስ ምሳሌዎች ብዙዎቹን አላሰፈረም። ከአንድ የበለጠ ዐቢይ የማስተማሪያ ክፍልም በመጽሐፉ ውስጥ አልተጠቀሰም።

4. ማርቆስ፥ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ባሪያ” በመሆኑ ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥቷል (ማር. 10፡45)። (ማቴዎስ ግን የክርስቶስን ንጉሥነት አመልክቷል፡፡) የእግዚአብሔር ባሪያ እንደ መሆኑ መጠን፥ ለሰዎች የእግዚአብሔርን መንገድ አስተምሯል (ማር 1፡4-5፡ 21-27፥ 38)። ኢየሱስ፥ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ፥ ለሕዝቡ ራርቶ ተአምራትን አድርጓል (ማር. 1፡32-34)።

5. ማርቆስ፥ ክርስቶስ በተደጋጋሚ ሕዝቡ ያደረገላቸውን ወይም የነገራቸውን ነገር ለሌሎች እንዳያወሩ ማዘዙን ገልጾአል (ማር. 1፡34፥ 44፤ 3፡12፣ 5፡43፤ 7፡36-37)። ይህንን ያደረገው በሦስት መንገዶች ነው። መጀመሪያ፣ አጋንንት ማንነቱን እንዳይናገሩ አዝዟቸዋል። የተናገሩት እውነት ቢሆንም እንኳ የጠላቱን ምስክርነት አልፈለገም ነበር። ሁለተኛ፥ ብዙውን ጊዜ የፈወሳቸው ሰዎች ያደረገላቸውን ነገር ለሌሎች እንዳይናገሩ አዞል። ሰዎች ለተሳሳተ ዐላማ እንዲከተሉት አልፈለገም ነበር። በተጨማሪም፥ የፈውስ አገልግሎቱ ሰዎችን ወደ ንስሐ ከመጥራቱና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ከማስተማሩ ቀዳሚ አገልግሎት እንዲያስተጓጉለው አልፈለገም ነበር። ሦስተኛ፣ አንዳንድ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መሢሕነቱን ለሰዎች እንዳይናገሩ ያዝዛል። ምናልባትም ሞቶ ከመነሣቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ምን ዓይነት መሢሕ እንደሆነ በትክክል አያውቁም ነበር (ማር. 8፡20-30፣ 9፡9-10)።

6. ከማርቆስ ታሪኮች ከ90 በመቶ የሚበልጡት በማቴዎስ ወይም በሉቃስ ውስጥ ይገኛሉ። ስለዚህ በሌሎቹ ወንጌላት የማይገኙት ምንባቦች እጅግ ጥቂቶች ናቸው።

7. ምሑራን የማርቆስ ወንጌል የት ላይ ያበቃል በሚለው ጥያቄ ላይ ይከራከራሉ። የተለያዩ ጥንታዊ ቅጂዎች መጽሐፉ በማርቆስ 16፡8 ላይ እንደሚያበቃ ይስማማሉ። ነገር ግን ከ16፡8 በኋላ መጽሐፉ የሚያበቃባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። አንዳንድ መዛግብት 9 ቁጥርን ሲጨምሩ፥ ሌሎች ደግሞ ከ9-20 ያሉትን ቁጥሮች ይጨምራሉ። አብዛኛቹ ምሑራን ማርቆስ 16፡9-20 በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ያለ አይመስላቸውም። የመጀመሪያው መጽሓፍ ቁጥር 8 ላይ እንዳበቃ ያስባሉ። አንዳንድ ምሑራን የማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያው ማጠቃለያ ስለ ጠፋ፥ የኋለኞቹ ጸሐፊዎች ጥሩ አጨራረስ እንዲኖረው ለማድረግ፥ ከ9-20 ያሉትን ቁጥሮች እንደ ጨመሩ ያስባሉ። የዚህ ክፍል እስትንፋሰ እግዚአብሔር መሆኑ አጠራጣሪ ስለሆነ፥ ሥነ መለኮታችንን ከዚህ ላይ ከመመሥረት መቆጠብ ይኖርብናል። በማርቆስ 16፡18 መሠረት፥ አንዳንድ የተሳሳቱ ምዕራባውያን ክርስቲያኖች ቢነድፉኝም አልሞትም በማለት እባቦችን ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: