ማርቆስ 1፡40-3:6

ማርቆስ የክርስቶስን የመጀመሪያ ክፍል አገልግሎት ጠቅለል ባለ ይዘት ያቀረበ ሲሆን፥ አሁን ግን በዝርዝር ማብራራት ይጀምራል። እነዚህ ታሪኮች እያንዳንዳቸው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነና እንደ ደቀ መዝሙር ከእርሱ ጋር መዛመድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማስተማር የተመረጡ ናቸው።

ሀ. ኢየሱስ ለምጻሙን ሰውዩ ፈወሰ (ማር. 1፡40-45)። በጥንት ዘመን ለምጽ በጣም የተፈራ በሽታ ስለነበረ፥ ማርቆስ ክርስቶስ ይህንኑ አደገኛ በሽታ እንዴት በቀላል የትእዛዝ ቃል ሊፈወስ እንደ ቻለ ያሳያል። ክርስቶስ ለምጻሙን በፈወሰ ጊዜ፥ ለማንም እንዳይናገር እንዳዘዘው ማርቆስ አመልክቷል። አሁንም ክርስቶስ በመፈወስ ኃይሉ ዝነኛ ሆኖ ለመታወቅ እየፈለገ አልነበረም፡፡ የተፈወሰው ግለሰብ የተሰጠውን ትእዛዝ ባለመጠበቅ ለሰዎች ሁሉ ስለ ክርስቶስ ኃይል በመናገሩ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ይህም በከተሞች ውስጥ መኖሩን ትቶ ከከተሞች ውጥ እንዲያገለግል አደረገው።

ኢየሱስ ሽባውን ፈወሰው (ማር. 2፡1-12)። ማርቆስ፥ ክርስቶስ አስቸጋሪ በሆነ ሰብአዊ ሁኔታ ላይ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ብቻ ሳይሆን፥ ለሌላ ዓላማ ጭምር ሽባውን እንደ ፈወሰ ገልጾአል። (አንድ ሰው ለረዥም ጊዜ ሽባ ሆኖ የቆየ፥ በሕክምና ነርቮቹን ለማዳንና ግለሰቡ እንደገና እንዲራመድ ለማድረግ አይቻልም።) በዚህ ጊዜ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ልጅ (ክርስቶስ ራሱን መለኮታዊ «የእግዚአብሔር ልጅ» እያለ መጥራቱን ይመርጥ ነበር [ዳን. 7፡13-14]፥ ኃጢአትን የማስተሰረይ ኀይል እንዳለው ለማሳየት ፈለገ። የበሽታው ምንጩ የግል ኃጢአት ነበር። ስለዚህ ክርስቶስ ኃጢአቱን ይቅር አለው። ኃጢአትን ሊያስተሰርይ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ግን ከሰዎች ዓይን የተሰወረ ክስተት በመሆኑ፥ ኀጢአትን ይቅር ለማለት መቻሉን እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ይህን ሊያውቁ የሚችሉት ክርስቶስ በሽተኛውን ሲፈውስ በማየት ነበር። እግዚአብሔር ኃጢአትን ይቅር የማለት መለኮታዊ ኃይል አለኝ ብሎ በድፍረት የተናገረን ሰው፥ ተአምር እንዲሠራ በማገዝ ሊያከብረው አይችልም።

ኢየሱስ ማቴዎስን (ሌዊን) ደቀ መዝሙሩ እንዲሆን ጠራው (ማር. 2፡13-17)። ወንጌላት ሁሉ የማቴዎስን ለደቀ መዝሙርነት መጠራት ይዘግባሉ። ለዚህ ምክንያቱ ይህ ታሪክ ስለ ክርስቶስና አገልግሎቱ ሁለት ዓበይት ትምህርቶችን የሚያስተምር መሆኑ ነው። በመጀመሪያ፥ ይህ ታሪክ ክርስቶስ እንደ እግዚአብሔር ልጅ ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት እንዲመሠርቱ ሊጠራ መምጣቱን ያሳያል። አንድ ሰው ሀብታም ወይም ድሀ፥ የተማረ ወይም መሐይም፥ ምርጥ የማኅበረሰቡ አባል ወይም ተራ ማኅበረሰቡ የማያከብረው ወይም ያራቀው ቢሆን ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል። እውነቱ ይህ ሲሆን፥ ጻድቃን ነን ብለው ያሰቡት ሰዎች ግን የክርስቶስን ጥሪ ተቀብለው ወደ ክርስቶስ አልተመለሱም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያ «ኃጢአተኞች» ወይም ማኅበረሰቡ የማይቀበላቸው ተብለው የተመደቡትን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ ለእነዚህ ለዎች ምን ዓይነት አመለካከት የሚኖረው ይመስልሃል? ሐ ቤተ ክርስቲያንህ ለእነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አላት? አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ንስሐ ለመጥራት የምትተጉት እንዴት ነው?

ሁለተኛ፡ ይህ ታሪክ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከፍለውንም ዋጋ ያሳያል። ማቴዎስ ክርስቶስን ለመከተል ሁሉንም ነገር መተው እንደ ነበረበት ሁሉ፥ በዘመን ሁሉ የሚኖሩ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን ለመከተል የቀድሞ ክፉ ልማዳቸውን፥ ለገንዘብና ለቤተሰብ የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት፥ ክርስቶስን የማያስከብር ባሕላቸውን ሁሉ መተውና መለወጥ ነበረባቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስ ተከታይ ከሆንህበት ጊዜ አንሥቶ በሕይወትህ ውስጥ የተለወጡት ነገሮች ምንድን ናቸው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች አሁንም ያልተላቀቋቸውና ክርስቶስን ከመከተል የሚያደናቅፉአቸው አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

መ. ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት መፍጠር የሚቻልበትን ፍጹም አዲስ መንገድ ለመጀመር እንደ መጣ ገለጸ (ማር. 2፡18-22)። ክርስቶስ ለምን እንደማይጾም የቀረበለትን ጥያቄ ካደመጠ በኋላ ነገሮች አሁን የተለወጡበትን ሁኔታ አብራራ። ጾም እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብሮ በሚኖርበት ጊዜ ሊያከናውነው የሚገባው ተቀዳሚ መንፈሳዊ ተግባር እንዳልሆነ አስተምሯል። ምክንያቱም እርሱ ፍላጎታቸውን እያሟላላቸው በመሆኑ፥ መጾም አያስፈልጋቸውም ነበር። ይህ ለእነርሱ ሙሽራውና ሙሽራይቱ እንደሚደሰቱበት የሰርግ ጊዜ ነበር። ክርስቶስ ዋንኛው አስፈላጊ ነገር መጾም እንዳልሆነና እርሱ ከመጣ በኋላ ነገሮች እንደ ተለወጡ አመልክቷል። ክርስቶስ ከመጣ በኋላ፥ አንድ ሰው ስለ ብሉይ ኪዳን ሕግጋትና ሰው ሠራሽ የፈሪሳውያን ሕግጋት የሚኖረው ግንዛቤ መለወጥ ነበረበት። የክርስቶስ ተከታዮች የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓት ማለትም (አርጌ የወይን አቁማዳዎች) እንዲከተሉ ማስገደድ፥ የአዲስ ቃል ኪዳን መንገድ ማለትም (አዳዲስ አቁማዳዎች) የሆነውን የክርስቶስን አምልኮ ከማጥፋት አልፎ፥ የክርስቶስን ትምህርት (አዲስ ወይን) ያበላሽ ነበር። ማርቆስ ይህንን አሳብ ያካተተው በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖች አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓት ለማስፈጸም የሚያቀርቡትን ውትወታ እንዳይሰሙ ለማስጠንቀቅ ይሆናል።

ሠ. የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በሰንበት ላይ ሥልጣን አለው (ማር. 2፡23-3፡6)። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ክርስቶስን ለማስገደል መፈለጋቸው ሮማውያንን ሳያስገርም አልቀረም። ጥላቻቸው ከምን የመነጨ ነበር? ማርቆስ የችግሩ ምንጩ በቁልፍ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ የነበረው የግንዛቤ ልዩነት መሆኑን ያሳያል። ከእነዚህ ልዩነቶች አንዱ የሰንበት ጉዳይ ነበር።

ማርቆስ ይህንኑ የሰንበት ግጭት ለመግለጽ ሁለት ታሪኮችን ተናግሯል። በመጀመሪያው አጋጣሚ፥ ክርክሩ የተነሣው ደቀ መዛሙርቱ እሸት በመቅጠፋቸው ነበር። ይህም አይሁዶች በሰንበት ቀን ምንም ዓይነት ሥራ እንዳይሠራ የሚከለክለውን የብሉይ ኪዳን ሕግ እንደ መተላለፍ አድርገው የሚቆጥሩት ተግባር ነበር። ክርስቶስ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው በሁለት መንገዶች ነበር፡፡ በመጀመሪያ፥ በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ለካህናት ብቻ የተፈቀደውን የመገናኛ ድንኳን የመሥዋዕት እንጀራ ዳዊት ሲበላ እንዳልቀጣው ገለጸላቸው። እግዚአብሔር ይህ መንፈሳዊ ሰው በሰንበት ቀን የበለጠ መልካም ተግባር ለመፈጸም ሲል የሕጉን ዝርዝር ጉዳዮች እንዲጥስ ፈቅዶለታል። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም መንፈሳዊ ስለነበሩ፥ እግዚአብሔር ሕጉን በትንሹ በመተላለፋቸው ሊቀጣቸው አልፈለገም። ለዚህም ምክንያቱ ከእርሱ ጋር የነበራቸው ግንኙነትና ሰንበትን የጣሱት ለመጥፎ ዓላማ አለመሆኑ ነው። ሁለተኛ፣ ክርስቶስ እንደ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ፥ መጥፎውንና ጥሩውን፥ እንዲሁም በሰንበት ቀን ሊሠራ የሚገባውንና የማይገባውን የመወሰን ሥልጣን እንዳለው አስረዳ። የሰንበት ሕግጋት የተሰጡት በሰዎች ላይ ሸክም ለመሆን ሳይሆን፥ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ፥ እርስ በርሳቸው መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸውና ከአጣዳፊ የሳምንቱ ሥራ እንዲያርፉ ለማገዝ ነበር።

ሁለተኛው ታሪክ ክርስቶስ እጁ የሰለለችውን ሰው በሰንበት ቀን እንደ ፈወሰ ያስረዳል። ሰንበትን ተላልፈሃል ብለው በከሰሱት ጊዜ፥ ክርስቶስ መልካምን ማድረግ መቼም ቢሆን በእግዚአብሔር ፊት ስሕተት ሊሆን እንደማይችል አብራርቷል። ይህ ከልብ ሁኔታና ሰዎችን ከመረዳት ይልቅ በሕግጋት ላይ የማተኮሩ ተግባር ክርስቶስን በጣም አስከፋው።

የውይይት ጥያቄ፡ እኛም ከሰዎች ልብ ይልቅ በሕግጋትና ደንቦች ላይ ልናተኩር የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

6 thoughts on “ማርቆስ 1፡40-3:6”

  1. ወንድሜ ኤርሚያስ፣

   በድረ ገጻችን አገልግሎት ደስተኛ መሆንህን የሚገልጽ መልእክት ስላስነበብከን ደስታችን ወደር የለውም፡፡ እናመሰግናለን፡፡

   የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች (https://goo.gl/fDtBXd)፣ የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ ማኑዋሎች (https://goo.gl/26UzGK)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሳሪያዎች (https://goo.gl/Eou24Y)፣ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች (https://goo.gl/UWbZjw)፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርጫህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

   እግዚአብሔር አንተን እና ቤተሰብህን ይባርክ!

  1. ወንድሜ ደርቤ፣

   በመጀመሪያ ለዝግጅት ክፍላችን ስለጻፍክልን አመሰግናለሁ፡፡ የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች (https://goo.gl/fDtBXd)፣ የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ ማኑዋሎች (https://goo.gl/26UzGK)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሳሪያዎች (https://goo.gl/Eou24Y)፣ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች (https://goo.gl/UWbZjw)፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርጫህ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትህን ማካሄድ ትችላለህ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖርህ በሚከተለው ኢሜይል ልትልክልኝ ትችላለህ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

   አዳነው ዲሮ ዳባ
   የወንጌል በድረገጽ አገልግሎት አዘጋጅ

Leave a Reply

%d bloggers like this: