ማርቆስ 3፡7-35

1. የሕዝቡ ክርስቶስን መከተልና የክርስቶስ 12 ተከታዮችን መምረጥ (ማር. 3፡7-19)። ማርቆስ የሕዝቡን አመለካከት ከሃይማኖታዊና የአይሁድ የፖለቲካ መሪዎች አመለካከት ጋር ያነጻጽራል። ይህንንም ያደረገው መሪዎች ክርስቶስን ጠልተው ሊገድሉት ሲፈልጉ፥ ሕዝቡ ግን ከፍልስጥኤም ምድር ሁሉ ሊጎበኘው እንደሚመጣ በማሳየት ነው። ክርስቶስም ወደ እርሱ የሚመጡትን ሰዎች ይረዳ ነበር። ማርቆስ አጋንንት ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ማወቃቸውን በድጋሚ ገልጾአል።

የክርስቶስ ዓላማ ግን ብዙ ሕዝብ እንዲያጅበው ማድረግ አልነበረም። ስለሆነም፥ ከዚያ ሁሉ ሕዝብ 12ቱን መረጠ። «ሐዋርያት» ብሎ ሰየማቸው። ማርቆስ እነዚህ 12ቱ ሐዋርያት በቤተ ክርስቲያን ላይ ሥልጣን እንዳላቸው እያመለከተ ሳይሆን አይቀርም። ሁሉም ክርስቲያኖች የክርስቶስ ተከታዮች ወይም ደቀ መዛሙርት ናቸው። ነገር ግን «ሐዋርያት» ተብለው የተጠሩ ወይም ክርስቶስን ለመወከልና በእርሱ ፋንታ ለማገልገል ሙሉ ሥልጣን የተሰጣቸው ጥቂቶች ብቻ ነበሩ። እንደ ሐዋርያት፥ ክርስቶስ ሲያካሂድ የነበረውን ተግባር የማከናወን፥ ወንጌልን የመስበክና አጋንንትን የማስወጣት ኀይል ተሰጥቷቸው ነበር። ማርቆስ፥ ክርስቶስ ሐዋርያትን የመረጠባቸውን ሁለት ምክንያቶች ጠቅሷል። ከእርሱ ይማሩና ይሠለጥኑ ዘንድ አብረውት ሊሆኑ ይገባ ነበር። በክርስቶስ ፋንታ ለመጠራት ይላኩ ነበር።

2. ኢየሱስ በአጋንንት ላይ የነበረው ኀይል፥ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መሆኑ መጠን፥ በበለጠ ኃያል መንግሥት እየመሠረተ መሆኑን ያሳያል (ማር. 3፡20-30)። ለሮማውያን ኀይልና ሥልጣን በጣም አስፈላጊ ነገሮች ነበሩ። ሮማውያን ኀይልና ሥልጣን ሁሉ፥ ከንጉሡ እንደሚመነጩና ከእርሱ ጋር በመዛመድ እነዚህን ነገሮች ማግኘት እንደሚቻል ያምኑ ነበር። የክርስቶስ ኃይል የመጣው ከየት ነበር? ማርቆስ የክርስቶስ ኀይል ከሰይጣን እንዳልመጣ ገልጾአል። ምክንያቱም አጋንንትን በሰይጣን ኃይል ማስወጣት እንደ እርስ በርስ ጦርነት የሰይጣንን መንግሥት የሚያፈራርስ ነበር። ነገር ግን የክርስቶስ ኀይል የመነጨው ከመለኮታዊ ንግሥናው ሲሆን፥ የሰይጣንን (የብርቱውን ሰው) መንግሥት በማጥቃትና በማሸነፍ ላይ ይገኛል።

3. ኢየሱስ መንፈሳዊ ቤተሰባችን፥ ከሥጋዊ ቤተሰባችን በላይ አስፈላጊ መሆኑን አስተማረ (ማር. 3፡31-35)። ደቀ መዛሙርቱ ከሚወስኗቸው ነገሮች አንዱ፣ ታማኝነታቸው ለማን እንደሚሆን መወሰን ነው። ማርቆስ፥ ከደቀ መዛሙርቱ በተቃራኒ፥ የክርስቶስ የሥጋ ዘመዶች የአእምሮ በሽተኛ እንደሆነ ማሰባቸውን አሳይቷል (ማር. 3፡20-21)። በክርስቶስና በአገልግሎቱ አልተደሰቱም ነበር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ከቤተሰቡ በላይ የቅርብ መንፈሳዊ ዘመዶቹ አድርጎ ተመለከተ። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሥጋዊ ቤተሰባቸውን ዐቢይ የዋስትናቸው ምንጭ አድርገው በመመልከት፥ የተፈለገውን ዋጋ ከፍለው ቤተሰባዊ ግንኙነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥሉ ያደርጋሉ። ክርስቶስ ግን ደቀ መዛሙርቱ በእርሱ በማመንና ትእዛዛቱን በመጠበቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየፈጸሙ ላሉት ተከታዮቹ፥ ስለ መንፈሳዊ ቤተሰቦቻቸውን የበለጠ ግድ እንዲላቸው አስተምሯቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሥጋዊ ቤተሰቦቻችንን ከመንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን በምናስበልጥበት ጊዜ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰቱትን ችግሮች ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: