የኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎት መዘጋጀት (ማር. 1፡1-13)

ብዙ ሰዎች በተቻለ ፍጥነት የአመራር ሥልጣን ለመያዝ ይሽቀዳደማሉ። ከዩኒቨርስቲ የሚመረቁ ወጣቶች ሥልጣን ላይ ለመውጣት ይፈልጋሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች የሚመረቁ ወጣቶች ወዲያውኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የኃላፊነትና የሥልጣን ስፍራዎችን እንደሚይዙ ይገምታሉ። ሽማግሌዎች የሚከበሩበት ታሪካዊ የአፍሪካ ባሕል እየሞተ፥ በስፍራው ለትምህርት የሚሰጥ ትኵረት እየተተካ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ለውጥ ሊካሄድ የተመለከትኸው እንዴት ነው? ለ) የተማሩ ወጣቶች አመራር ጠቃሚ ጎኖች ምንድን ናቸው? ሐ) ከችግሮቹ አንዳንዶቹ ምን ምንድን ናቸው?

ጥሩ ትምህርት ለሕይወትና አገልግሎት ጠቃሚ መሣሪያ ቢሆንም፥ ለአመራር ከዚያ የበለጠ ዝግጅትን ይጠይቃል። መልካም እመራር ብስለትን ይፈልጋል። ስለ ሕይወት ሁኔታዎች፥ ከሰዎች ጋር ስለሚደረጉ ግንኙነቶች፥ ችግሮችንና አለመስማማቶችን ለማስወገድ በልምድ ማደግ ያስፈልጋል። መንፈሳዊ ብስለት፥ ከክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ማድረግ፥ የመንፈስ ፍሬ መጨመርና የመንፈሳዊነት ባሕርያት መታየት ይኖርባቸዋል። ዓለም በትምህርትና አመራር ላይ ያለውን አመለካከት፥ እኛ በትሕትናና በአገልጋይነት አመለካከት መተካት አለብን።

ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን ቀደም ብሎ ለመጀመር ይችል ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ብስለትና የአመራር ኀላፊነት ወደ 30 ዓመት አካባቢ እንደሚመጣ አመልክቷል። (ዘኁል. 4፡3 አንብብ።) ስለሆነም፥ ክርስቶስ አገልግሎቱን ለመጀመር 30 ዓመት አካባቢ እስኪሆነው ድረስ ቆየ (ሉቃስ 3፡23)። እኛም ወደ አመራር ሥልጣን ለመውጣት ከመጣር ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በማሳደግ መንፈሳዊ ባሕርያትን ማጎልበት ይኖርብናል። ከዚያም ዝግጁዎች በምንሆንበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ አመራር ያመጣናል። ሰዎች የእግዚአብሔርን እጅ በሕይወታችን ውስጥ ያያሉ። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአመራር ኃላፊነቶችን ይሰጠናል። ከዚህ ውጭ የሆነው ሁሉ የዓለም መንገድ ነው። ይህም ከትዕቢት የመነጨ አመራር የምንሰጥበት በመሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይስማማም።

የውይይት ጥያቄ፡- ማር 1-4 አንብብ። ሀ) ከዚህ ክፍል ስለ ክርስቶስ የምንማራቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ስለ ደቀ መዝሙርነት ምን እንማራለን?

ማርቆስ ኢየሱስ በእግዚአብሔር ከመጠራቱ በፊት በገሊላ እውቅና አግኝቶ እንዳልቆየ አድርጎ በመተረክ፥ ረዥም የዝግጅት ጊዜ እንዳሳለፈ አልጠቀሰም። ስለ ኢየሱስ ልደትም ሆነ የልጅነት ታሪክ ምንም ዓይነት ገለጻ አላቀረበም። ማርቆስ ታሪኩን የጀመረው ኢየሱስ ይፋዊ አገልግሎቱን ሊጀምር አቅራቢያ በተከሰቱት ነገሮች ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ለማሳየት ሲል፥ በመጥምቁ ዮሐንስ ታሪክ ጀመረ (ማር. 1፡1)።

ማርቆስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ብዙ ነገር አልነገረንም። ስለ ዮሐንስ የሚያቀርበውን ገለጻ የጀመረው ከብሉይ ኪዳን ነው። ዮሐንስ ሰዎችን ለመሲሑ ለማዘጋጀት ስለሚላከው ስለ «ጌታ መልእክተኛ» በብሉይ ኪዳን የተነገረውን ትንቢት ፈጸመ። ልክ የአውራ ጎዳና ሠራተኞች መንገዱን ጠግነው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ምቹ እንደሚያደርጉት ሁሉ፥ መጥምቁ ዮሐንስም ሰዎችን «ለጌታ» ለማዘጋጀት ነበር የተላከው። ይህ ትንቢት ክርስቶስን «ጌታ» ብሎ በመጥራት ለክርስቶስ መለኮታዊ ባሕርይ ፍንጭ ይሰጣል።

እንደ ብሉይ ኪዳን ነቢይ ለብሶ በመምጣት፥ ዮሐንስ «ለኃጢአት ይቅርታ የንስሐ ጥምቀት» ሰብኳል። ማርቆስ ሰዎች በመጠመቅ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኙ አልገለጸም። የዚህ ክፍል ትክክለኛ አተረጓጎም ዮሐንስ ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ ስለገቡ ወይም ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት አጠመቃቸው የሚለው ነው። ይህ በልባችን ውስጥ ለተካሄደው ለውጥ ውጫዊ ምልክት ነበር። ምክንያቱም ለመሢሑ መምጣት በመዘጋጀት ከአሮጌው አኗኗራቸው ተመልሰው (ንስሐ ገብተው)፥ እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው በመጠየቅ ላይ ነበሩ። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ አንድ ሰው የሚጠመቀው ወዲያውኑ ንስሐ እንደገባ ነበር። እነዚህ ሁለቱ እንደ አንድ ተግባር የተያያዙ ነበሩ። ነገር ግን ጥምቀት ብቻውን ሊያድን እንደሚችል የሚገልጽ አሳብ ከአዲስ ኪዳን ውስጥ ልታገኙ አትችሉም።

የውይይት ጥያቄ፡- አንዳንድ ወንጌላውያን ጥምቀት እንደሚያድንና ያልተጠመቁ ሰዎች እውነተኛ ደኅንነትን እንዳላገኙ ያስተምራሉ። ከማርቆስ 1፡4 ምን መልስ ትሰጣቸዋለህ? ስለዚህ ለሰዎች እውነቱን ለማስተማር የምትጠቀምባቸው ሌሎች ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው?

የዮሐንስ ሌላኛው ዐቢይ መልእክት፥ «ለመሢሑ ተዘጋጁ» የሚል ነበር። ዮሐንስ ዝነኛ ነቢይ በመሆኑ፥ ሰዎች ከዓለም ሁሉ እየመጡ ይጎበኙት ነበር። ነገር ቀን ከመሢሑ ጋር ሲነጻጸር፥ ባሪያው ሊሆን እንኳ እንደማይገባው ተናግሯል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ ከባሪያ ተግባራት አንዱ ጌታው ወደ ቤቱ በሚመለስበት ጊዜ ጫማውን መፍታት ነበር። ዮሐንስ ለሌላ ሰው እንዲህ ዐይነት አገልግሎት ሊሰጥ ስለማይችል ይህም ለኢየሱስ መለኮታዊነት ሌላው ፍንጭ ነው። ዮሐንስ የመሢሑን ታላቅነት ለማጉላት በመንፈስ ቅዱስ እንደሚያጠምቅ ገልጾአል። ማርቆስ እሳትን አለመጥቀሱ አስገራሚ ነው። ምናልባትም በቤቱ ውስጥ በተካሄደው የበዓለ ኀምሳ ሥነ ሥርዓት ላይ የነበረውን ሁኔታ ላያስታውስ አይቀርም። የእግዚአብሔር ልጅነቱን በማረጋገጥ መንፈስ ቅዱስን ለክርስቲያኖች የላከው ክርስቶስ ነበር። የክርስቶስ የእሳት ፍርድ የሚመጣው ገና ወደፊት ስለሆነ አልተጠቀሰም።

ኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሉቱ ያካሄደው ሁለተኛው ዝግጅት በዮሐንስ መጥመቁ ነበር። ማርቆስ በኢየሱስ ላይ አጽንኦት በመስጠት ታሪኩን ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በኢየሱስ ላይ ከመውረዱም በላይ፥ እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ የእርሱ ልጅ መሆኑን በግልጽ አስታውቋል። እግዚአብሔር አብ ኢየሱስን እንደሚወድና በእርሱ ደስ እንደ ተሰኘ ተናግሯል።

ኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎቱ ያደረገው ሦስተኛው ዝግጅት መፈተን ነበር። ማርቆስ ይህን ታሪክ ጠቅለል አድርጎ አቅርቧል። መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ እንደ ወሰደውና በሰይጣን እንደ ተፈተነ አመልክቷል። እዚህ ላይ ማርቆስ አንድ አስገራሚ አሳብ አክሏል። ይኸውም ኢየሱስ በምድረ በዳ ከዱር አራዊት ጋር እንደነበረ የሚያመለክት ነው። ብዙ ምሑራን ይህ ማርቆስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዱር አራዊት ፊት የሚጣሉትን ክርስቲያኖች ለማበረታታት የጠቀሰው እንደሆነ ይገምታሉ። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከዱር አራዊት ጠብቆታል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ይህ ክርስቲያኖች ሊቋቋሙት የሚገባ ችግር እንደሆን ያውቅ ነበር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “የኢየሱስ ለይፋዊ አገልግሎት መዘጋጀት (ማር. 1፡1-13)”

Leave a Reply

%d bloggers like this: