በሰዎች ላይ ከፍተኛ ፍርሃትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚያስከትሉ ሁለት ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፥ ከሁሉም የከፋው የሰው ልጅ ጠላት ሞት ነው። ኢየሱስ በሞት ላይ ምን ሥልጣን አለው? የሚለው ምላሽን የሚሻ ጥያቄ ነበር። ሁለተኛ፥ የረዥም ጊዜ ሕመም አለ። ኢየሱስ ለረዥም ጊዜያት ሐኪሞችን ሁሉ አሸንፎ የቆየን በሽታ ሊፈውስ ይችላል? ማርቆስ እነዚህን ሁለት ታሪኮች በመጠቀም የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ፥ እነዚህን ሁለት ጠላቶች ሊያሸንፍ እንደሚችል አሳይቷል።
የመጀመሪያው ታሪክ ለ 12 ዓመታት ደም ስለሚፈሳት ሴት የሚናገር ነበር። ከዚህ በሽታ የተነሣ ሴትዮዋ ከማኅበረሰቡ ተገልላ ትኖር ነበር። የዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ብዙ ሴቶች ከትዳራቸው ለመፈናቀል ተገድደዋል። ይህች ሴት መፍትሔ ለማግኘት ወደ ብዙ ሐኪሞች ዘንድ ብትሄድም አልተሳካለትም ነበር። የመጨረሻ ተስፋዋ ኢየሱስ ስለነበር፥ በሕዝብ መካከል እየተጋፋች ሄዳ ልብሱን ነካችው። ወዲያውም ተፈወሰች።
ኢየሱስ በነበረበት ስፍራ እንዲቆምና ይህች ሴት እንደነካችው እንድታምን ያስገደዳት ለምን ነበር? ኢየሱስ ሁሉንም ነገር ስለሚያውቅ፥ እንደ ነካችው ቀድሞውኑ ተረድቶ ነበር። ክርስቶስ ይህንን ያደረገው የመፈወስ ችሎታውን ለማሳየት አልነበረም። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ስለ ተአምራቱ ለሌሎች እንዳይናገሩ ሰዎችን ያስጠነቅቅ ነበርና። ነገር ግን ኢየሱስ ለዚህች ሴት ስለ ራሱ አንድ ነገር ለማስተማርና ወደ መንፈሳዊ ፈውስም ለመምራት ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ምንጊዜም በሥጋዊ ፈውስ ብቻ ስለማይረካ፥ ለእያንዳንዱ ሰው የመንፈሳዊ ፈውስ ዕድል ለመስጠት ይፈልጋል። ለዚህም ነው ሕዝቡን ሁሉ ከመፈወስ ይልቅ በግለሰብ ደረጃ መፈወስን የመረጠው። ስለሆነም ኢየሱስ ሴቲቱ የተከሰተውን ሁኔታ እንድታምን በማድረግ፥ እምነቷ ሥር እንዲሰድ እያደረገ ነበር። ሴትዮዋ ሥጋዊ ፈውስ ብታገኝም፥ መንፈሳዊ ፈውስና እውነተኛ ሰላምን ማግኘት ያስፈልጋት ነበር። በማርቆስ ወንጌል ኢየሱስ ለፈውስ የተጠቀመው ቃል «መዳን» ከሚለው ጋር ተመሳሳይ ነው። ስለሆነም ሥጋዊ ፈውስ አግኝታ ከመከራዋ የዳነችው ይህች ሴት፥ አሁን ደግሞ መንፈሳዊ ፈውስን አግኝታ ሰላምን ተጎናጽፋለች።
በሁለተኛው ታሪክ፥ ኢየሱስ በቀላል የትእዛዝ ቃል የኢያኢሮስን ልጅ ከሞት አስነሥቷል። ከኢየሱስ ጋር ሲነጻጸር ሞት ኀይል ያለው ጠላት አይደለም። በቀላል የትእዛዝ ቃል ሁላችንም ከሞት እንነሣለን። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የሞት መውጊያ እንደ ተሰበረ የጻፈው (1ኛ ቆሮ. 15፡53-56)።
በዚህ ታሪክ ውስጥ ሌላም አስገራሚ ነገር ተከስቷል። ኢየሱስ ተአምሩን ለማሳየት ደቀ መዛሙርቱን ሁሉ ከመውሰድ ይልቅ፥ ዮሐንስን፥ ያዕቆብንና ጴጥሮስን ብቻ ወሰደ። ይህ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ቁልፍ መሪዎች ለሚሆኑት ለእነዚህ ሦስት ደቀ መዛሙርት፥ የሥልጠና ዓይነት ተግባር ነበር። ኢየሱስ ከ12ቱ በላይ በጥልቀት አስተምሯቸዋል።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)